አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Friday, 11 August 2017

ይሁኔ ይስማው-ኢዜአ

በእንግሊዝ ለንደን በመካሔድ ላይ በሚገኘው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  ባለፉት ሰባት ቀናት ከተደረጉ ውድድሮች 24ቱ አሸናፊዎቻቸው ታውቀዋል።

ኢትዮጵያም  ከተጠናቀቁት 24  የስፖርት አይነቶች ውስጥ በሰባቱ ተካፍላ ሶስት ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች። የቀሩት አምስት ውድድሮች በቀጣዮቹ  ሶስት ቀናት ፍጻሜአቸውን እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ከተካፈለችባቸው 13 የስፖርት አይነቶች መካከል 3 ሺህ መሰናክል ወንዶች፣ 800 ሜትር ወንዶችና 1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች ውድድር አሸናፊዎች ተለይተዋል።በሁለቱም ጾታ የተካሔዱት የ10 ሺህ ሜትርና የማራቶን ፍልሚያ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል።

አገራችን ከተሳተፈችባቸው ርቀቶች መካከል  በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች አንድ ወርቅና አንድ የብር ሜዳሊያ እንዲሁም በወንዶች ማራቶን  አንድ የብር ሜዳሊያ ማግኘት ተችሏል።

በሴቶች 10 ሺህ ሜትር አትሌት አልማዝ አያና ወርቅ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ የብር ሜዳሊያ እንዲሁም በወንዶች የማራቶን ውድድር አትሌት ታምራት ቶላ የብር ሜዳሊያ ለሀገራቸው አስገኝተዋል።

ፍጻሜአቸውን ካገኙት ውድድሮች መካከል በወንዶች 10 ሺህ ሜትር እንግሊዝን የወከለው ሙሀመድ ፋራህ ፉክክሩን በበላይነት ሲያጠናቅቅ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በርቀቱ ሜዳሊያ ማጥለቅ አልቻሉም።

በተመሳሳይ በወንዶች 3 ሺህ መሰናክልና  800 ሜትር እንዲሁም በሴቶች ማራቶን የተሳተፉት አትሌቶች አጥጋቢ ውጤት አላስመዘገቡም።

አገራችን ሜዳሊያ ታገኝበታለች ተብሎ ቅድሚያ ግምት የተሰጠውና ብዙዎችን ያስቆጨ ውጤት የተመዘገበበት የሴቶች የ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር ነው።

በርቀቱ ኢትዮጵያን ወክለው ከተወዳደሩት መካከል አትሌት ጉዳፍ ፀጋይና በሱ ሳዶ ማጣሪውን ማለፍ ሲያቅታቸው ትልቅ ተስፋ የተጣለባት አትሌት ገንዘቤ ዲባባም በፍጻሜው ድል ሳይቀናት ቀርቷል።

በዚህ ርቀት ኢትዮጵያ ሜዳሊያ በማጣቷ በብዙ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ የተለያዩ አሉታዊ አስተያየቶች ተደምጠዋል።በተለይ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የሚነሱት ሐሳቦች ሚዛን የማያነሱ መሆናቸውን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

አትሌት ገንዘቤ ባለፉት ዓመታት ሀገሯን ወክላ በተሳተፈችባቸው ርቀቶች  ስምንት ወርቅ ፣ ሁለት ብርና አንድ ነሀስ በድምሩ 11 ሜዳሊያዎችን ለሀገሯ አስገኝታለች።

አትሌቷ ካለችበት እድሜ አኳያ  በቀጣይ በኦሎምፒክና በአለም ሻምፒዮና ውድድሮች በመካፈል  ለሀገሯ ብዙ ታሪኮችን እንደምትሰራም ይጠበቃል።

ለአትሌቶች ድክመታቸውን የሚያስተካክሉበትና  ጠንካራ ጎናቸውን የሚያጎለብቱበት  አስተያየት መስጠት የሚያበረታታ ሲሆን በስሜት የተሞሉ ስዎች የሚያቀርቡት ስድብ አዘል ትችት ግን ከባድ የስነልቦና ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል በቅድሚያ ሊታሰብበት ይገባል።

አንድ ሳምንት ያስቆጠረው 16ኛው የዓለም ሻምፒዮና  ከሶስት ቀናት  በኋላ የሚጠናቀቅ ሲሆን ኢትዮጵያም በቀጣይ ከምትወዳደርባቸው ስድስት የስፖርት አይነቶች በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች ተወዳዳሪዎቹ ማጣሪያውን ማለፍ አልቻሉም።በመሆኑም ኢትዮጵያ በቀሩት የውድድር አይነቶች ሜዳሊያ ለማግኘት ተሳትፎዋን ትቀጥላለች።

በ1 ሺ 500 ሜትር ወንዶች ተካፋይ ከነበሩት  ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል አማን ወጤ በጉዳት፣ተሬሳ ቶሎሳ ውድድሩን በጡንቻ ህመም ምክንያት በማቋረጡና ሳሙኤል ተፈራ ደግሞ ስምንተኛ በመውጣት ከፍጻሜው ውድድር ውጭ ሆነዋል።

 በዚህ የዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት ከ 25 በሚካሄደው የ3 ሺህ መሰናከል የሴቶች የፍጻሜ ውድድር ኢትዮጵያ በአትሌት እቴነሽ ዲሮና ብርቱካን ፈንቴ ትወከላለች።

ኢትዮጵያ ሜዳሊያ ታገኝበታለች ተብሎ ተስፋ ከተደረገባቸው ርቀቶች የወንዶች 5 ሺህ ሜትር  አንዱ ሲሆን በርቀቱ አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ ፣ሰለሞን ባረጋና ሙክታር እንድሪስ ከእንግሊዛዊ አትሌት ሙሀመድ  ፋራህ እና ከኬንያውያን ጠንካራ ፉክክር እንደሚገጥማቸው ይጠበቃል።

እሁድ በሚከናወነው 16ኛው የዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና ማጠናቀቂያ ላይ ኢትዮጵያን በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች ውድድር የሚወክሉት አልማዝ አያና፣ሰንበሬ ተፈሪና ለተሰንበት ግደይ  ከኬኒያዊቷ ሄለን ኦብሬ ጋር የሚያደረጉት ትንቅንቅ መላው የአትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪ በጉጉት የሚጠብቀው ነው።

 በውድድሩ መዝጊያ ቀን ኢትዮጵያ በሴቶች የ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር ፍጻሜ ትካፈላለች።

አትሌት ሀብታም ዓለሙ ዛሬ የሚደረገውን የ800 የሴቶች ግማሽ ፍጻሜ ማጣሪያ ማለፍ ከቻለች በሻምፒዮናው ማጠናቀቂያ እለት ለፍጻሜ የምትወዳደር ይሆናል።

በአለም አትሌቲክሰ ውድድር አንደኛ ሆነው ለሚያጠናቅቁ  አትሌቶች 1 ሚሊዮን 2 መቶ ሺህ ብር የሚጠጋ የገንዘብ ሽልማት የሚሰጥ ሲሆን ሁለተኛ ለሚወጣ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም እስከ ስምንተኛ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች የተለያየ የገንዘብ ሽልማት ይሰጣቸዋል።

ከዚያ ውጭ አትሌቶች በአለም አቀፍ ውድድሮች ሲያሸንፉ በግላቸው ስፖንሰር ካደረጓቸው የስፖርት ትጥቅ አምራቾችና ኩባንያዎች  ሽልማት የሚያገኙ በመሆኑ ጊዚያዊ የውጤት ቀውሱን ከገንዘብ ጋር ማያያዝ ተገቢ አለመሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ መንግስትም የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ላውለበለቡ አትሌቶች የሚሰጠው የራሱ የማበረታቻ ሽልማትም አለው።

መንግስት ከሚሰጠው የገንዘብ ሽልማት ባለፈ ለአሸናፊ አትሌቶች እውቅናና ምስጋና ያቀርባል፡፡ ባለድሎቹ ከሀገራቸው ህዝብም ከፍተኛ ክብርና ፍቅር የሚያገኙ መሆኑን ካለፉት ዘመን አይሽሬ አትሌቶች ስለሚገነዘቡ ምክንያቱን ከሰሙ በኋላ አሰተያየት መስጠት ብልህነት ስለሆነ ቀድመን ለወቀሳ አንቸኩል፤አበቃሁ፡፡

 

Published in ዜና-ትንታኔ

አዲስ አበባ ነሃሴ 5/2009 የአፍሪካ ወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አገራት የአቅም ማጎልበት ሥራ ላይ በሥፋት መሥራት አንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።

የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት ያልተማከለ ቀን "የእናንተ ተሳትፎ" በሚል መሪ ኃሳብ በትላንትናው ዕለት በሞሮኮ መዲና ራባት ተከብሯል።

በአፍሪካ ከ63 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች እድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች ሲሆን አማካይ እድሜው ደግሞ አስራ ዘጠኝ ነው።

ይህም ከአጠቃላይ የአህጉሪቱ ህዝብ ቁጥር 200 ሚሊዮን የሚሆነውን በመያዝ፣ በቀጣይ 20 ዓመታት ውስጥ 500 ሚለዮን ይደርሳል ተብሏል።

ከእነዚህ መካከል 72 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች በቀን ከሁለት ዶላር በታች ገቢ የሚያገኙ ሲሆን በዓመቱ ደግሞ በአህጉሪቱ ከ10 አስከ 12 ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ እድሜን ይቀላቀላሉ።

በአፍሪካ በአሁኑ ወቀት እድሜያቸው ከ6 እስከ 14 የሆኑ ሕጻናትም በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሲሆኑ በዚህም በአፍሪካ ከተሞች በርካታ ህጻናት ከመጠለያ ውጭ በመሆን ህይወታቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታ ጎዳና ላይ አንዲኖሩ አስገድዷል።

ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራትም ከአምስት ወጣቶች ሦስቱ ሥራ አጥ መሆናቸውን የዓለም የሥራ ድርጅትና የአሜሪካ የህዝብ ቆጠራ ቢሮ ሪፖርት ያሳያል።

ይህንንም ከግምት በማስገባት የአፍሪካ ኅብረት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2009 እስከ 2018 ያሉትን ዓመታት የአፍሪካ ወጣቶች ዓመታት ብሎ ሰይሞታል።

ይሁንና ይህ የፖለቲካ ድንጋጌ በአህጉሪቱ ባሉ የተለያዩ ችግሮች በወጣቶች ላይ ለማምጣት የወጠነውን ውጤት ሳያስመዘግብ ድንጋጌው ሊጠናቀቅ መሆኑ ነው የተገለጸው።

በዚህም የተነሳ ወጣቶች ለከፍተኛ የሥነ-ልቦና ቀውስና ተሰፋ ማጣት ሁኔታ ውስጥ አንዲዘፈቁ ግድ ብሏል።

በመሆኑም የአፍሪካ ሴት የከተሞች ከንቲባና ተመራጭ ሴቶች ትስስር የሚባል ቡድን 'የአፍሪካ ከተሞች ከጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት ውጪ' የሚል መርኃ ግብር ይፋ አድርጓል።

በዚህም ወጣቶችን ማብቃት የሚያስችል የወጣቶች አቅም ማጎልበቻ መርኃ ግብር በመንደፍ በወጣቶች ላይ የሚስተዋሉትን ማለትም ሥራ አጥነትን መቅረፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በተጓዳኝም የሥራ ፈጠራ ክህሎት እንዲያዳብሩ፣ በትምህርት፣ በባህል፣ በጥበብ፣ በቅርስ፣ በስፖርትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ወጣቶች  ተሳታፊና ተጠቃሚ አንዲሆኑ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም አገራት ለወጣቶች አዳዲስ እድሎችን በማቅረብ የመሪነት ሚናውን መጫወት አንዳለባቸው አሳስበዋል።

አገራት ግልጽ የሆነ አሰራር በመንደፍ ወጣቶች በሚኖሩበት ከተማ ያሉትን የምክር ቤት አባላትና አስተዳዳሪዎችን አንዲያገኙ ማመቻቸት አንደሚጠበቅባቸውም አንዲሁ።

በከተሞች አከባቢ ወጣቶችን ያቀፈ ምክር ቤት በማቋቋም፤ ወጣቶች የከተሞችን ኃላፊነት እስከ ምን ድረስ ነው የሚለውን መረዳት አንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት።

ወጣቶች የሚሳተፉባቸው መድረኮችን በማዘጋጀት የሥራ ኃላዎች ከወጣቶች ኃሳብ በመሰብሰብ የህዝቡን ኑሮ ወደ ኋላ የሚጎትቱ እንቅፋቶችን በመለየት እልባት መስጠት እንደሚገባም ጠይቀዋል።

ቡድኑ በተለይም የሚወጡ መርኃ ግብሮችና ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ መረባረብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

 

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ነሀሴ 5/2009 በተጠናቀቀው በጀት አመት ወደ ውጭ ከተላኩ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ዝቅተኛ እንደሆነ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢንስቲትዩቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀዱሾም ጡዑም ለኢዜአ እንደገለፁት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከዘርፉ 42 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ማግኘት የተቻለው ግን 19 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ ቢኖረውም አፈፃፀሙ ግን ከግማሽ በታች ሆኗል።

ከተገኘው 19 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 17 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ከሲሚንቶ ምርት የተገኘ እንደሆነም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

ቀሪው ገቢ የተገኘው ከቀለምና የቀለም ውጤቶች፣ ከሳሙናና የሳሙና ውጤቶችና ከፕላስቲክ ተረፈ ምርቶች እንደሆነም አቶ ሀዱሾም ተናግረዋል፡፡

ወደ ውጭ ከተላከው የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች የተገኘው የውጭ ምንዛሬ አነስተኛ የሆነው በዘርፉ የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች በመጠን በአይነትና በጥራት ምርቶችን የመላክ  አቅማቸው ውስንነት ስለሚታይበት ነው ብለዋል ፡፡

ከውጭ ለሚገቡ ግብዓትና ማሽን ግዥዎች የሚውል የውጭ ምንዛሬ እጥረት ፣ የማጓጓዣ ውድነት ፣ የማኔጅመንት አሰራር ያለመናበብ እና የመሰረተ ልማት አቅርቦቱ በሚፈለገው መጠን ባለማደጉ ምክንያት በታቀደው ልክ ገቢ ለማግኝት እንዳልተቻለም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የውሃና መብራት አገልግሎቶች መቆራረጥ ችግር ሌላው እቅዱን ለማሳካት የገጠመ ተግዳሮት መሆኑን  አቶ ሀዱሾም ጠቅሰዋል።

በአዲሱ በጀት አመት ከኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች 62 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኝት መታቀዱን የገለፁት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እስካሁን የነበሩትን ችግሮች በማቃለል ስኬታማ ስራዎች እንደሚከናወኑም አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለይም የባቡርና የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለማስተሳሰር የተጀመሩት ተግባራት ቀደም ሲል ከማጓጓዣ ጋር ተያይዘው ይገጥሙ የነበሩትን ችግሮች ማቃለል እንደሚያስችሉም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ለሶማሊያ ፣ ለጂቡቲ ፣ለሱዳንና ለኬንያ ትልካለች፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ ነሀሴ 5/2009 ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የፋይናንስ አሰራር በክልሉ በሚገኙ የመንግስት ተቋማት እውን እንዲሆን የጨፌ አባላት ክትትልና ቁጥጥር ሊጠናከር እንደሚገባ የኦሮሚያ ጠቅላይ ኦዲት መስሪያ ቤት ገለጸ።

በመንግስት የልማት ድርጅቶችና ሴክተር ተቋማት ላይ ለሚደረገው የፋይናንስና የአይነት ኦዲት ግኝት ውጤታማነት በየደረጃው የሚገኙ የምክር ቤት አባላት  ቁርጠኝነት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ነው ተብሏል።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ኦዲት መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አቶ ኤሌማ ቃምጴ በቅርቡ በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ ላይ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት መስሪያ ቤቱ በተጠናቀቀው  የበጀት ዓመት በ320 የክልሉ መንግስት ተቋማት ላይ የፋይናንስ ኦዲት አድርጓል፡፡

በዚሁ የፋይናንስ ኦዲትም ከ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ መባከኑን አረጋግጧል፡፡

በእስካሁኑ ሂደት በተደረገው የኦዲት ግኝት ክትትል ከባከነው ገንዘብ ውስጥ 25 በመቶ ብቻ መመለሱን ጠቅሰዋል፡፡

ለምዝበራ የተጋለጠ የፋይናንስ አስተዳደርና የንብረት አያያዝ አሰራር እንዲወገድ የጨፌው አባላት በመንግስት ወጪ አስተዳደር ላይ የሚያደርጉትን ክትትልና ቁጥጥር ይበልጥ ማጠናክር እንደሚገባቸው ዋና ኦዲተሩ ጠይቀዋል።

መስሪያ ቤቱ በ2010 ዓ.ም የክልሉን መንግስት የልማት ድርጅቶችን ጨምሮ በ600 ተቋማት ላይ የፋይናንስና የአይነት ኦዲት ለማድረግ ማቀዱንም አስታውቀዋል፡፡

የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ አቶ እሼቱ ዳሴ በበኩላቸው የህዝብና የመንግስት ሀብት ለታለመለት ዓላማ ብቻ መዋል እንዳለበት ተናግረዋል።

''ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የፋይናንስ ወጪ አስተዳደር አሰራርን እውን ለማድረግ የጨፌው አባላት ጠንክረው ሊንቀሳቀሱ ይገባል'' ብለዋል።

አቶ እሸቴ እንዳሉት፣ ለሀብቱ ብክነት ምክንያት የሆኑ አሰራሮች እንዲወገዱ ከማድረግ በተጨማሪ ከምዝበራው ጋር ግንኝነት ያላቸው ግለሰቦችን ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ ነው።

''ለመልካም አስተዳደር እጦት መንስኤ የሚሆነው ለልማት የተመደበውን በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ መዋል ሳይቻል ሲቀር ነው'' ያሉት ደግሞ የጨፌው አባል አቶ ጀማ ካዮ ናቸው።

በሀብቱ ላይ የሚካሄደው ምዝበራና ብክነት በመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የጥራት ጉድለት እንዲታይ ከማድረጉ በተጨማሪ ግንባታዎቹ በተቀመጠላቸው ጊዜ ውስጥ እንዳይጠናቀቁ አድርጓል።

በተጨማሪም መንግስትን ለተጨማሪ  ወጪ በመዳረግ የህዝብ ቅሬታ ሲያስከትሉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በመንግስት የልማት ድርጅቶችና ሴክተር ተቋማት ግልጽነት የሰፈነበት የፋይናንስ ወጪ አስተዳደር እንዲሰፍን የሚያደርጉትን ክትትልና ቁጥጥር በማጠናከር የህዝብ ውክልናቸውን በአግባቡ ለመወጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በጨፌው የፋይናንስ ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ይልማ ወዬሳ በበኩላቸው በሒሳብ ወጪ አስተዳደር ላይ የሚታየውን የአሰራር ችግር ለማስወገድ የውስጥ ኦዲተሮችን አቅም ማጎልበት አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

በክልሉ ጠቅላይ ኦዲት መስሪያ ቤት በየጊዜው የሚወጡ የሒሳብ ጉድለቶች ግኝት ተከትሎ የምክር ቤቱ አባላት ተገቢ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት አለባቸው ተብሏል ።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ነሃሴ 5/2009 በቁጠባ ቤቶች ግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ማህበራት ከመንግስት ተገቢውን ድጋፍና ክትትል አለማግኘታቸው በስራቸው ላይ ተፅዕኖ እያሳደረባቸው መሆኑን አስታወቁ።

በዘርፉ የተሰማሩት አባላት መንግስት በማህበር አደራጅቶ ወደ ስራ ማስገባቱ የሚያበረታታ መሆኑን ጠቅሰው በስራ ላይ የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ ግን በቂ አይደለም ብለዋል።

ትናንት በአዲስ አበባ ከስራ ፈጠራ ጋር በተያያዘ በተካሄደው ውይይት ላይ ያነጋገርናቸው የተለያዩ ማህበራት አባላት ቅሬታቸውን  ገልጸዋል፡፡

ከአንቀሳቃሾቹ አንዱ አቶ  ግርማ አደሜ እንዳሉት ማህበራቱ  ለግንባታ እቃዎች ማምረቻ የሚሆን የብሎኬት፣ፕሪካስትና ሌሎች ግብአቶች  እያቀረቡ ቢሆንም ለምርታቸው ተገቢውን ክፍያ በወቅቱ እያገኙ አይደለም።

ብድር ወስደው ወደስራ መግባታቸውን የገለፁት አቶ ግርማ ክፍያው ቶሎ ባለመከፈሉ ከአበዳሪ ተቋማትና እና ከማህበሩ ሰራተኞች ጋር ለመግባባት ከመቸገራቸውም በላይ ስራችውን ባግባቡ ለማከናወን እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

በማህበር ተደራጀተው ወደ ስራ የገቡት አቶ ሽታ በለጠ  በበኩላቸው ከክፍያ መዘግየት በተጨማሪ ለሚያቀርቧቸው ምርቶች  የሚያስፈልጓቸው ሲሚንቶና ሌሎች ግብዓቶች በወቅቱ እየቀረቡላቸው አለመሆኑን ጠቁመዋል።

ወደ ስራ ለመግባት ውል ከመፈራረም ጀምሮ እስከ ክፍያ ማስፈፀም ሂደት ድረስ ለሚፈጠሩ ቅሬታዎች ቶሎ ምላሽ አለመስጠትና የማጉላላት ሁኔታም እንደሚታይ ጠቅሰዋል።

በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ በቂ እውቀት ያለውና ማህበራትን የሚያግዝ ባለሙያ አለመሟላት፣የሼድ ጥበት፣የመብራትና የውሃ መቆራረጥ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን የተናገሩት  በተመሳሳይ በማህበር ተደራጅተው እየሰሩ የሚገኙት አቶ ጌታቸው ብረየስ ናቸው።

የማህበራቱ ምርቶች በወቅቱ አለመነሳታቸው ካለው የቦታ ጥበት ጋር ተዳምሮ ምርትን በበቂ መጠንና ጥራት ለማምረት እንቅፋት እንደሆነባቸውም ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ የጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ  የስራ ሂደት ባለቤት አቶ በለጠ ክንፈ  የችግሮቹ መንስኤዎች ተለይተው እየታዩ ነው ብለዋል።

በተለይም ከክፍያ መዘግየት ጋር ያለው ችግር  የተፈጠረው  ማህበራቱ ለክፍያ የሚያስፈልጋቸውን ሰነድ በማሟላት ሒደት እክል ስለሚገጥማቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ማህበራቱ ይዘው መምጣት ያለባቸውን ሰነድ አለማወቅ፣የምርታቸውን ጥራት የሚያረጋግጡላቸውን የግንባታ አማካሪዎችና ተቋራጮችን በተፈለገው ጊዜ አለማግኘታቸው ለችግሩ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው ይህንኑ ለመፍታት ቋሚ ቢሮ እንዲኖራቸው እያደረግን ነው ብለዋል።

"ምርታችን በወቅቱ እየተነሳልን አይደለም"የሚለው ጥያቄ  ከመንገድ አለመሰራት ጋር በተያያዘ  በጥቂት ማህበራት የሚቀርብ  ስለሆነ ችግሩ በአጭር ጊዜ እንደሚፈታም አቶ በለጠ ገልጸዋል።

 ከመስሪያ ቦታ ጥበት፣ከመብራትና ከውሃ መቆራረጥ ጋር የሚታዩ ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርን በመፍታት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ማህበራቱ ለሚቀርብላቸው ግብዓት ትኩረት ያለመስጠትና የማባከን ችግሮች ስላሉባቸው እንዲያስተካክሉም አሳስበዋል።

ካሁን በፊት በአንዳንድ ማህበራት ላይ የጥራት፣የብክነትና በአቋራጭ ለመክበር የሚደረጉ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ታይተው እንደነበር አስታውሰው ከማስጠንቀቂያ እስከ ውል ማቋረጥና ለህግ እስከ ማቅረብ የደረሱ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ነሀሴ 5/2009 በሀገር አቀፍ ደረጃ በወባ በሽታ የሚያዙ ህሙማን ቁጥር ከ50 በመቶ በላይ መቀነሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የሀገር አቀፍ የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሮ ህይወት ሰለሞን ለኢዜአ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ በወባ በሽታ የሚያዙ የህሙማን ቁጥር ከባለፉት ስምንት አመታት ጋር ሲነጻጸር ከ50 በመቶ በላይ ቀንሷል።

የበሽታውን ስርጭት በመከታተል በሀገር አቀፍ ደረጃ መረጃዎችን የማሰባሰብና ግብረ መልስ የመስጠት ስራዎች በመሰራታቸው በበሽታው የሚጠቁ ህሙማንን ቁጥር በመቀነሱ ረገድ ውጤታማ መሆን እንደተቻለ ገልጸዋል።

የወባ በሽታ ምርመራና ህክምና የሚሰጡ የህክምና ተቋማትም ተደራሽ ለማድረግ ተችሏልም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ20 ሺህ በላይ የጤና ተቋማት የወባ በሽታ ምርመራና ህክምና እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።

በወባ በሽታ የሚያዙ የህመምተኞች ቁጥርና በበሽታው ሳቢያ የሚከሰት የሞት መጠን ከ60 በመቶ በላይ መቀነስ በመቻሉ አገሪቱ አለም አቀፍ እውቅና አግኝታለች ብለዋል።

''ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር  የተዘጋጁ ስልቶች በአግባቡ በመተግበራቸው የአየር ንብረት ለውጥ ቢከሰትም በበሽታው ስርጭት ላይ ተጽእኖ አላሳደረም'' ነው ያሉት ወይዘሮ ሕይወት።

ወቅታዊ የአየር ንብረት መረጃዎችን በመጠቀም የዝግጁነት ስራዎች እንደሚሰሩ ገልጸው በተለይም ባለፉት 2 አመታት ውስጥ የአየር መዛባትና የሙቀት መጨመር ቢኖርም የወባ ስርጭት እንዳይጨምር መቻሉን ነው የተናገሩት።

እንደ ወይዘሮ ህይወት ገለጻ እ.አ.አ በ2030 ወባን ከአገሪቱ ለማጥፋት በተያዘው ግብ መሰረት በአሁኑ ወቅት በተመረጡ 239 ወረዳዎች ላይ የአጎበር ስርጭትና የቤት ለቤት ፀረ-ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ስራዎች እየተሰሩ ነው ።

ነፃ የወባ በሽታ ምርመራና ህክምና አገልግሎት ማስፋፋት፣የግንዛቤ ማስጨበጫና የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም አክለዋል።

በኢትዮጵያ 60 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ለወባ በሽታ ተጋላጭ ሲሆን ከበልግና ክረምት ዝናብ ወቅት በኋላ የወባ ስርጭት ሊጨምር ስለሚችል ወቅቶቹን መሰረት ያደረጉ የመከላከል ስራዎች እየተሰራ ይገኛል።

በአፍሪካ አልጀሪያና ደቡብ አፍሪካ ወባን በመከላከል ረገድ ቀዳሚዎቹ አገራት ሲሆኑ ኢትዮጵያ፣ናሚቢያና ቦትስዋና በአንጻራዊነት ተከላክለዋል፤ስዋዚላንድ ዲሞክራቲክ ኮንጎና ናይጀሪያ በበሽታው በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቁ አገራት ናቸው። 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሀሴ 5/2009 ከኬሚካል አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚለቀቁ ተረፈ ምርቶች/በካይ ኬሚካሎች/ በሰውና በአካባቢ  የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ የሚከናወነው ሥራ በቂ አይደለም ሲሉ ባለሙያዎች ገለጹ።

ባለሙያዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንዳስታወቁት ከተለያዩ የኬሚካል ውጤት አምራች ፋብሪካዎች ወደ አካባቢ የሚለቀቀው ተረፈ ምርት በቂ ጥንቃቄ ተደርጎበት አይደለም።

አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች በተረፈ ምርት አወጋገድ ላይ በወጣው መመሪያ መሰረት እየሰሩ አለመሆኑንም ተናግረዋል።

የጽዳት መገልገያዎች፣የፕላስቲክ ውጤቶች፣የውሃ ማከሚያ፣የወረቀት ማቅለሚያና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ማምረቻ ፋብሪካዎች ከኬሚካል ኢንዱስትሪዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬሚካል ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ብርሃኑ አሰፋ የኬሚካል ኢንዱስትሪው አጠቃላይ ለአገሪቷ ኢንዱስትሪ ልማትና ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይገልጻሉ።

ይሁን እንጂ አገሪቷ ካለችበት የዕድገት ደረጃ አኳያ የተረፈ ምርት አወጋገድ ስርዓቱም በዚያው መጠን እንዲያድግ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት አይደለም ብለዋል።

ከኬሚካል ኢንዱስትሪው የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን አወጋገድ ችግር የሚያቃልሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚገባም ነው ምሁሩ የገለፁት።

የኬሚካል ተረፈ ምርቶች በአግባቡ ካልተወገዱ በተለይም በወንዞች ላይ የሚያደርሱት ብክለት አደገኛ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ብርሃኑ የተበከሉ ወንዞችን ለማከም የሚወጣው ወጪም በአገር ሀብት ላይ የሚያስከትለው ኪሳራ  ቀላል አለመሆኑን አስረድተዋል።

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች አንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃዱሾም ጥሁም እንደሚሉት አብዛኞቹ የኬሚካል አምራች ኢንዱስትሪዎች የተረፈ ምርት አወጋገድ መመሪያውን መሰረት አድርገው እየሰሩ አይደለም።

ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ በማያስወግዱና አካባቢ ላይ ጉዳት በሚያደርሱ ኢንዱስትሪዎች ላይም የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

የተረፈ ምርት አወጋገድ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራ፣ኦሮሚያ፣ትግራይና ደቡብ ክልሎች የፕላስቲክ አወጋገድ ላይ ጥናት መደረጉንም አቶ ሃዱሾም ገልጸዋል።

ጥናቱ የአገሪቷ የኬሚካል ውጤቶች ተረፈ ምርት አወጋገድ ስርዓቱ ዝቅተኛ መሆኑንና  ብዙ መሰራት እንዳለበት ማመላከቱን ነው የተናገሩት።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አለሙ ስሜ በበኩላቸው በ2010 በጀት ዓመት ከማንኛውም ኢንዱስትሪ የሚወጡ ተረፈ ምርቶች በሰውና አካባቢ ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራበታል ብለዋል።

የተረፈ ምርት አወጋገድ ችግርን በተደራጀ ሁኔታ ለመፍታት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ቀደም ሲል እንዲህ አይነት ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስርዓት እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

 

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ  ነሐሴ 5/2009 በአገር አቀፍ ደረጃ  የሲሚንቶ ፍላጎትን ለማሟላት የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

 በኬሚካል ኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ኢንስቲትዩትና በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው "የሲሚንቶ ፍኖተ ካርታ" በማምረት ሒደት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ነው ።

 እ.ኤ.አ እስከ 2025 የሚያገለግለው ፍኖተ ካርታ ሲሚንቶ ከአገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ የሚያግዙ ተሞክሮዎችን መያዙንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

 የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ዓለሙ ስሜ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፍኖተ ካርታው አገሪቷ በየወቅቱ የሚያስፈልጋትን የምርት መጠን የሚያሳይ ነው።

 አገሪቱ ሲሚንቶ ለማምረት ከሚያስፈልጋት የሃይል ፍጆታ ውስጥ ከ40 እስክ 60 በመቶ የሚሸፈነው በድንጋይ ከሰል  በመሆኑ ለዚህም  የውጭ ምንዛሪ እንደምታወጣ  ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

 ''ይህም ከሌሎች አገሮች አኳያ ሲታይ የኢትዮጵያ የሲሚንቶ ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጓታል'' ብለዋል።

 የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለሙያዎች በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢራንን የሲሚንቶ አመራረት ተሞክሮ ቀስመው መመለሳቸውን  ዶክተር ዓለሙ ገልጸዋል።

 ኢራን ላይ የአንድ ቶን/10 ኩንታል/ የሲሚንቶ ዋጋ ከ 25 እስከ 30 ዶላር እንደሚደርስ የተናገሩት ዶክተር ዓለሙ በኢትዮጵያ የአንድ ኩንታል የሲሚንቶ ዋጋ 90 ዶላር መሆኑን አስታውቀዋል።

 በኢትዮጵያና በኢራን የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በዋናነት ያለው ልዩነት የኃይል አጠቃቀም  መሆኑን ጠቁመው ''የኢራንን የሃይል አጠቃቀም ልምድ ብንወስድ የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንችላለን'' ብለዋል።

 ኢራን ለሃይል አጠቃቀም እና ለአካባቢ ጥበቃ የምትጠቀምባቸው ቴክኖለጂዎች ከኢትዮጵያ የተሻሉ መሆናቸውን የግብረ ሃይሉ ሪፖርት እንደሚያመለክት ጠቅሰዋል።

 ኢትዮጵያ የኢራንን ተሞክሮ በመውሰድ የሲሚንቶ ምርቶቿን በተመጣጣኝ ዋጋ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንድትችል የሚያግዝ ጥናት እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

 ''ፍኖተ ካርታውን መሰረት ያደረገ ጥናት በማካሄድ እየጨመረ የመጣውን የአገር ውስጥ የሲሚንቶ ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ምርቱን ለአጎራባች አገራት ማቅረብ እንችላለን'' ብለዋል።

 በአሁኑ ወቅት ለሲሚንቶ ምርት የሚያገለግለው የድንጋይ ከሰል ከውጭ አገር እየገባ መሆኑን የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሀዱሾም ጥዑም አስታውቀዋል።

 ፍኖተ ካርታው በአገር ውስጥ የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ማዕድን ሲሚንቶ ለማምረት ብቁ እንዲሆን በማድረግ ከውጭ የሚገባውን ግብአት ለማስቀረት የሚያስችል አቅጣጫን አስቀምጧል።

 በሲሚንቶ ማምረት ስራ በብዛት እየተሳተፉ የሚገኙት የውጭ ባለሙያዎች የዕውቀትና  የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ ማስቻልና የሲሚንቶ  ኢንዱስትሪው በአገር ውስጥ ባለሙያ እንዲመራ ማድረግ የፍኖተ ካርታው አካል መሆኑንም አስረድተዋል።

 ፍኖተ ካርታው ከሲሚንቶ የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን ለሌላ ጥቅም ለማዋል የሚያስችሉ ሀሳቦችን እንደያዘና በ2010 ዓ.ም ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።

 ኢትዮጵያ በ2009 ዓ.ም  የኮንስትራክሽን ግብዓት ምርቶችን ወደ ጎረቤት አገራት በመላክ ከዘርፉ  42 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዳ 19 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች።

ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ብልጫ ሲኖረው ከዚህ ውስጥ 17 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ከሲሚንቶ ምርት የተገኘ ነው፡፡

      

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን