አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Thursday, 10 August 2017

አዲስ አበባ ነሀሴ 4/2009 የአሜሪካ ኤምባሲ "ከአዲስ አበባ ጅግጅጋ መስመር በባቢሌ እና ሐረር አካባቢዎች ግጭት ተከስቶ መንገድ ተዘግቷል ፤ መንቀሳቀስ አይቻልም" ብሎ ያወጣው መረጃ ሐሰት መሆኑን የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ለኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት እንደገለጹት፤ በተጠቀሱት አካባቢዎች የተቀሰቀሰ ግጭት የለም።

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በአንድ ወቅት በአካባቢው ተከስቶ የነበረውን ችግር ለመፍታት የሁለቱ ክልሎች አስተዳደሮች መፈራረማቸውን አውስተው፤ በተወሰነ ወራት ውስጥም የወሰን ማካለሉን ሥራ ለማከናወን መስማማታቸውን አስታውሰዋል።

"ይህንን መሠረት በማድረግ የወሰን ማካለሉ ሥራ እየተከናወነ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም  ከፌዴራል እና ከሁለቱ ክልሎች የተወጣጡ ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"ይሄንኑ ሥራ የሚሠሩ ባለሙያዎች  ሥራ ላይ እያሉ በአካባቢው የሚኖሩ ነዋሪዎች የተሳሳተ ግንዛቤ በመያዝ አትሰሩም በሚል ከለከሏቸዋል፤ እነርሱም ትተው ሄዱ እንጂ ምንም ዓይነት ተኩስ እና ግጭት አልተቀሰቀሰም" ብለዋል።

አሁን ባለው መረጃም አካባቢው ሠለማዊ እንደሆነና ምንም ዓይነት የተቀሰቀሰ ግጭትም ተኩስም እንደሌለ፤ መንገድም እንዳልተዘጋ ዶክተር ነገሪ አብራርተዋል።

በመሆኑም የአሜሪካ ኤምባሲ በድረገጹ የለቀቀው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ተናግረዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ነሀሴ 4/2009 የኬኒያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሠላማዊ፣ ግልጽ እና አሳታፊ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የወቅቱ ሊቀ-መንበር ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትርና የወቅቱ ሊቀ-መንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ የኬኒያን ሕዝብ መሪውን በሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መምረጡን ማድነቃቸውን ኢጋድ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። 

የኢጋድ ሊቀመንበር ኃይለማርያም ፤ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና እጩዎች የሕዝቡን ድምጽ እንዲያከብሩ ፣ የአካባቢውን ሠላምና መረጋጋት ከማወክ እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።

አጠቃላይ የምርጫ ውጤቱ ይፋ እስኪደረግ ድረስ የሚመለከታቸው የፓለቲካ ፓርቲዎች በትዕግስት መጠበቅ እንደሚኖርባቸው ያመለከቱት አቶ ኃይለማርያም ፤ በሠላምና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተጀመረው ምርጫ ፍጻሜው እንዲያምር ሁሉም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ኢጋድ በአምባሳደር ተወልደ ገብረመስቀል የተመራ 18 አባላት ያሉት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ወደ ስፍራው መላኩ ይታወሳል።

የምርጫ ታዛቢ ቡድኑ በምርጫው ወቅት የምርጫ ኮሮጆዎች ሲከፈቱ፣ የምርጫ ሂደቱና  የድምፅ ቆጠራውን  በንቃት መታዘቡን  አመላክቷል።

በምልከታውም ምርጫው የአገሪቷን  ሕገ-መንግሥት መሠረት ባደረገ መልኩ ወጣቶችን ፣ ሴቶችንና አዛውንቶችን ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ያሳተፈ እንደነበር በመግለጫው አብራርቷል።

የኬንያ የምርጫ ኃላፊዎች  ምርጫውን  ግልጽና ተጠያቂነት በሰፈነበት መልኩ ማዘጋጀታቸውን እንደታዘበ ድርጅቱ መግለጹ ይታወሳል።

በምርጫው የተሳተፉ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የኬኒያን ህዝብ ድምጽ እንዲያከብሩም መልክቱንም አስተላልፏል።

Published in ፖለቲካ

መቀሌ ነሐሴ 4/2009 የሕዝቦችን እኩልነት በማረጋገጥ የሃገሪቱን ሰላምና ልማት ካረጋገጠው የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት አወቃቀር መልካም ተሞክሮ እንዳገኙ የሶማሊያ ሪፐብሊክ መንግስት ልዑክ  አባላት ገለጹ።

የልዑኩ  አባላት ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተገኝተው በፌደራሊዝም ስርዓት አወቃቀርና አተገባበር ላይ ከትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር የተሞክሮ ልውውጥ አድርገዋል።

የልዑኩ መሪና የሶማሊያ ሪፐብሊክ የአገር ውስጥና የፌድራል የእርቀ ሰላም ሚኒስትርና ቋሚ ፀሃፊ ዓብዱላሂ መሐሙድ ሐሰን በተሞክሮ ልውውጡ ላይ እንደገለጹት ከኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ስርዓት አወቃቀር በርካታ ጠቃሚ ልምዶችን አግኝተዋል።

እንደ ኢትዮጵያ የተሳካ የፌደራል ስርዓት በሶማሊያ ሪፐብሊክ ለመገንባት ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚወስድ ጠቅሰው ከኢትዮጵያ የተገኘውን መልካም ተሞክሮ በመውሰድ ለተግባራዊነቱ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በሶማሊያ ሪፐብሊክ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ገልጸው አሁን በሃገሪቱ ውስጥ ያሉትን የክልል መንግስታት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 በሚደረግ ምርጫ በህዝብ እንዲመረጡ እንደሚደረግም አስረድተዋል።

"ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝቡ የፌደራሊዝም ስርዓት ምንነትና ጥቅሙን በማወቁ የሀብት ክፍፍሉ በማእከላዊ መንግስት የተወሰነ ሳይሆን እስከ ክልሎች ድረስ ስለወረደ የሰላምና የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጎታል"ብለዋል።

የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር አምባሳደር አዲስ አለም ባሌማ በበኩላቸው "የሶማሊያ ሪፐብሊክ መንግስትና ህዝብ ችግሮችን እኛም የምንጋራቸው በመሆናቸው አብረን ለመፍታት በትጋት እንሰራለን" ብለዋል።

የተሞክሮ ልውውጡ ለሁለቱም ወንደማማች ህዝቦች መሰረታዊና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸው "ሁለታችን አንድ ላይ ሆነን አሸባሪነትን፣የባህር ላይ ውንብድናን ፤ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመታገል ሰላማችንን እናረጋግጣለን" ብለዋል።

በሶማሊያ የጋልሙዲ ክልላዊ መንግስት የሴቶችና ሰብአዊ መብት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ዛህራ ኦላት በበኩላቸው እንዳሉት፣የትግራይ ሴቶች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፎች ተጠቃሚ ለመሆን እያያደረጉት ካለው የነቃ ተሳትፎ ብዙ እንደተማሩ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ሴቶች መብታቸውን ለማስከበር ባካሄዱት መራራ ትግልም ዛሬ ላይ በክልሉ ምክር ቤቶችና በየደረጃው በሚገኙ መንግስታዊ የስራ ኃላፊነቶች ላይ 50 በመቶ ተሳታፊ መሆናቸውን ከተደረገላቸው ገለጻ መገንዘባቸውን አስረድተዋል።

ለሶማሊያውያን ሴቶች ይህን ተሞክሮ በመውሰድ አሁን ያለውን የ24 በመቶ የፖለቲካ ተሳትፎ በ2020   50 በመቶ ለማድረስ ጠንክረው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የልዑኩ አባላት ዛሬ የአልነጃሺን ታሪካዊና ጥንታዊ መስጊድንና መቀሌ ከተማ የሚገኘውን የሰማእታት ሃውልት ከጎበኙ በኋላ ተመሳሳይ ተሞክሮ ለመውሰድ ወደ አማራ ክልል  ተጉዘዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ነሐሴ 4/2009  ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ የ15 ኩባንያዎችና የ210 ተጠርጣሪ ግለሰቦች ንብረት እንዲታገድ  መደረጉን  የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አስታወቀ።

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ቁጥር 54 ደርሷል።

ከ15ቱ ኩባንያዎች መካከል አሰር ኮንስትራክሽን፣ ዲ.ኤም.ሲ ኮንስትራክሽን፣  ገምሹ  ኮንስትራክሽን ፣ ቲና  ኮንስትራክሽን ፣የማነ ግርማይ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ፣ ትራንስ ናሽናል ኮምፒውተር ቴክኖሎጂ (ቲሲቲ)፣ ሃይሰም ኢንጂነሪንግ አክስዮን ማህበር፣ ተማኒክ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ጂንግ ሊንግ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ይገኙበታል።

ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፀው፤ በፍርድ ቤት የታገደው ንብረት የተጠርጣሪዎችና ከተጠርጣሪዎች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ የሚታመን ነው።

ሰሞኑን በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል ለ43ቱ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፖሊስ በጠየቀው መሰረት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደፈቀደለት ተዘግቧል።

 ችሎቱ የተጠርጠሪዎቹን ጉዳይ ለማየት ለነሐሴ 15 እና 17 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መያዙ ይታወሳል።

 ፍርድ ቤቱ በቅርቡ በተለያዩ ጊዜያት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለሃብቶችና ደላሎች መካከል ጉዳያቸውን ለማየት ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል።

 መንግስት በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩና በቂ መረጃ የተሰበሰበባቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ባለሃብቶች በቁጥጥር ስር  እያዋለ መሆኑም ይታወቃል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ነሀሴ 4/2009 የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ተቀራርበው ሊሰሩ እንደሚገባ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

"ደብተራ ግዕዛን" ወይንም "ባክ ቱ ስኩል" የተሰኘ የመጀመሪያው አለም አቀፍ የትምህርት ዓውደ ርዕይ ዛሬ ተከፍቷል።

በመክፈቻው ስነስርአት ላይ የተገኙት በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ብርሃኑ ሞረዳ  እንዳሉት መንግስት  በአገሪቱ የትምህርትን ጥራትን ለማስጠበቅ  የትምህርት ግብአት አቅርቦትን ፣ የመምህራን ልማትና ሌሎች አጋዠ መሳሪያዎችን እያሟላ ይገኛል።

 "ትምህርት የመንግስት ጉዳይ ብቻ ባለመሆኑ የአጋር ድርጅቶችንና የህብረተሰቡን ተሳትፎ ይጠይቃል" በማለት አማካሪው ተናግረዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ከግሉ ዘርፍ፣ ከህብረተሰቡና ከሚመለከታቸው አካላትጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን በመጥቀስ  ቅርርቡ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

የአውደ ርዕዩ አዘጋጅ አቶ ሮቤል በቀለ በበኩላቸው ዓውደ ርዕዩ በትምህርት ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት እርስ በእርስ የሚተዋወቁበትና ስራቸውን የሚያቀርቡበት እንደሆነም ተናግረዋል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል በኢትዮጵያ አቪየሽን አካዳሚ ከፍተኛ ማርኬቲንግ ባለሙያ አቶ ዮሃንስ በለጠ በሰጡት አስተያየት ዓውደ ርዕዩ አካዳሚው የሚሰጠውን የትምህርት አገልግሎት ለማስተዋወቅና ከአዳዲስ ተቋማት ጋር ትስስር ለመፍጠር ይረዳናል ብለዋል።

አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ስራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ቆንጅት ሞገስ በበኩላቸው ከተለያዩ ተቋማት ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ዓውደ ርዕዩ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች፣ የትምህርት ግብአትና መገልገያ አቅራቢዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ ዩኒቨርስቲዎችና ከትምህርት ጋር ተያያዥ በሆኑ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ከ60 በላይ ተቋማት በዓውደ ርዕዩ በመሳተፍ ላይ ናቸው።

ዓውደ ርዕዩ በትምህርት ተቋማት መካከል ትስስር ለመፍጠር፣ ወላጆችን በትምህርት ጉዳይ ላይ ከሚሰሩ  ተቋማት ጋር ለማገናኘት፣ ፣ ልምድ ለመለዋወጥ፣ የትምህርት መድረኮችን ለማጠናከር ያለመ ነው።

ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት በተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በሚካሄደው ዓውደ ርዕይ የተለያዩ ጥናታዊ ጹሁፎች ይቀርባሉ።

 ኑስፌር አፌርስ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ አውደ ርዕይ በየአመቱ ነሃሴ ወር እንደሚዘጋጅም ተነግሯል።

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ነሀሴ 4/2009 በትግራይ ክልል በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው የአሸንዳ በዓል ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደሆናቸው በጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎችና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ገለጹ።

የአሸንዳ በዓል  በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ ፣ የባህልና የትምህርት ኮሚሽን (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ባህላዊ  ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።

በመቀሌ ከተማ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ንግድ ሥራ የተሰመሩ የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በዓሉ ለሥራቸው ማንቀሳቀሻ የሚሆን ገቢ እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሯል።

በከተማው የ"ሕዳሴ ልብስ ስፌት" ባለቤት ወጣት ገብረሕይወት ግርማይ እንዳለው ልጃገረዶች የአሸንዳ በዓልን ለማክበር በየዓመቱ ለባህላዊ ልብሶች ፣ በአንገት ለሚንጠለጠሉ የማስጌጫ ቁሶችና ለፀጉር ሥራ ከፍተኛ ገንዘብ ያወጣሉ፡፡

በዓሉ ሲደርስ በልብስ ስፌት የሚተዳደሩ ባለሙያዎች ያለእረፍት ለ24 ሰዓት በሥራ የሚጠመዱበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቅሷል።

እርሱም በበዓሉ ሰሞን ገበያው ስለሚደራ ከ30 እስከ 40 ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኝ ተናግሯል።

"የአሸንዳ በዓል ሲቃረብ የልብስ ስፌት ሥራ አቋርጠው የነበሩ ባለሙያዎች ሳይቀር ተመልሰው ወደ ሥራው ይገባሉ" ያለው ደግሞ ወጣት ተስፋይ ኃይሉ ነው፡፡

ዘንድሮ ለበዓሉ የሚሆን ባህላዊ ልብሶችን በመስፋት እስከ 15 ሺህ ብር የሚደርስ ገቢ ለማግኘት አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ወጣት ተስፋይ ተናግሯል፡፡

ለአሸንዳ በዓል ባህላዊ ልብስ መግዣን ጨምሮ ለጌጣጌጥና ለፀጉር ሥራ እስከ 2 ሺህ ብር ወጪ እንደምታደርግ የገለፀችው ደግሞ ለበዓሉ የሚሆናትን ባህላዊ ልብስ በመግዛት ላይ የነበረችው ወጣት መአዛ አሸብር ናት፡፡

ሌላው የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ወጣት ወልዳይ ዘርአይበኩሉ" የዘንድሮ የአሸንዳ በዓል ለየት የሚያደርገው በበዓሉ የሚሳተፉ ሴቶች ባህላዊ የሃገር ውስጥ ልብስ ብቻ እንዲለብሱ መወሰኑ  ነው"  ብሏል።

"ሴቶች በባህላዊ የሀገር ልብስ ደምቀው በዓሉን እንዲያከብሩ መደረጉ እንደ አገር ተጠቃሚ ያደርገናል" ሲል ወጣት ወልዳይ ተናግሯል።

የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ወይዘሮ ኢትዮጵያ ሕሉፍ እንደገለፁት የአሸንዳ በዓልን በዓለም ቅርስነት  ለማስመዝገብ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል ።

ዘንድሮም ይህንኑ ጥረት የሚያጠናክሩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የዘንድሮ የአሸንዳ በዓል በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች ከነሐሴ 15 እስከ 24 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ በድምቀት ይከበራል ።

በዓሉ "አገር በቀል ባህላዊ እሴቶቻችንና ቅርሶቻችንን በመጠበቅ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ከፍ እናድርግ" በሚል መሪ ቃል ይከበራል።

በበዓሉ ላይ የተለያዩ የብዙሀን መገናኛ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ  ነሐሴ 4/2009 በአምስተኛው አገር አቀፍ የታዳጊዎች የምዘና ውድድር 70 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ቀዳሚ ለመሆን ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

 ከ17 ዓመት በታች ታዳጊዎችን የሚያሳትፈው ይኸው የምዘና ውድድር ከነሐሴ ሰባት ጀምሮ ለሁለት ሳምንት ያህል በ13 የስፖርት ዓይነቶች በሐዋሳ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

 ነገ ጠዋት ወደ ስፍራው ለሚያቀናውና 162 ወንድና 139 ሴት በድምሩ 301  ስፖርተኞችን ለያዘው የመዲናዋ የስፖርት ልዑካን ቡድን ዛሬ አሸኛኘት  ተደርጎለታል። 

 በውድድሩ ውጤታማ ለመሆን ለሦስት ሳምንት ያህል በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ዝግጅት ማድረጋቸውን በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ገልጸዋል።

 ለቅድመ ሥራ ዝግጅቱ በተለያዩ ኮሚቴዎች  ክትትልና ድጋፍ  ሲደረግ መቆየቱን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በሥልናም የታዩ ክፍተቶችን ማረም እንደተቻለ ነው የገለጹት።

 የተሰጠው ሥልጠና ስኬታማ መሆኑን ተከትሎ በምዘና ውድድሩ 30 ወርቅ፣ 18 ብርና 12 ነሐስ በድምሩ 70 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በአንደኝነት ለማጠናቀቅ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸዋል። 

 በፓራ ኦሎምፒክም 17 ወርቅ፣ 17 ብርና 13 ነሐስ በድመሩ 47 ሜዳሊያዎችን ለመሰብሰብ ዝግጅት መደረጉን አቶ ዳኛቸው ጠቁመዋል።

 ለዕቅዱ ስኬታማነት ቢሮው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው፣ በቀጣይ ለአገሪቱ ተስፋ የሚጣልባቸው ስፖርተኞች የሚታዩበት የስፖርት መድረክ እንደሚሆንም ነው ያመለከቱት።  

 አሰልጣኞችና ስፖርተኞች በበኩላቸው የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የመዲናዋን ስም ለማስጠራት መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።

 ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉበት አምስተኛው የታዳጊዎች የምዘና ውድድር ከመጪው ዕሁድ ጀምሮ እስከ ነሐሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።

Published in ስፖርት

ነገሌ ነሀሴ 4/2009 በጉጂ ዞን በተያዘው ክረምት ከ162 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በ28 የልማት ስራ ዘርፎች ተሰማርተው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ምከትል ኃላፊ ወይዘሮ ሸዋዬ ሀይሌ እንዳሉት በዞኑ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል 3 ሺ 285 የዩኒቨርስቲና የኮሌጅ ተማሪዎች ናቸው፡፡

የነገሌ፣ አዶላና ሻኪሶ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በዞኑ 14 ወረዳዎች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩት ወጣቶች ቁጥር ካለፈው አመት በ11 ሺህ ብልጫ አለው፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የተሰማሩት ወጣቶች በዋናነት በመንገድ፣ ትምህርት፣ ችግኝ ተከላ፣ በእርሻ ስራና የአቅመ ደካሞችን ቤት መስራት ጨምሮ በ28 የልማት ስራ ዘርፎች ተሰማርተው በማገልገል ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እስካሁንም 57 ሺህ ችግኝ የተከሉ ሲሆን 21 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድ ከፈታና የ18 ኪሎ ሜትር መንገድ ጥገና አከናውነዋል፡፡

እንዲሁም የ5 አረጋዊያንን ቤት የሰሩ ሲሆን በ17 የወረዳ ከተሞችና መንደሮች የጽዳት ስራ ማከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡

ኤች አይ ቪ እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ለ143 ሺህ 800 ነዋሪዎች የግንዛቤ ማስጫ ትምህርት በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የተሰጠ ሲሆን ለ51 ሺህ 731 መደበኛ ተማሪዎችም የማጠናከሪያ ትምህርት በመሰጠት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን በተከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ358 ሺህ 300 በላይ ህዝብ ተጠቃሚ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ሐረር ነሐሴ 4/2009 መንግስት በመደበው ተዘዋዋሪ ብድር ተጠቅመው ወደ ስራ ለመሰማራት ቢዘጋጁም  የብድር አቅርቦቱ አነስተኛ መሆን እንቅፋት እንደፈጠረባቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሐረሪ ክልል ወጣቶች ገለፁ፡፡

የስራው አዋጭነት እየታየ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ብድር እየተሰጠ እንደሚገኝ የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ገልጿል።

በሀረር ከተማ በሲሚንቶና ቀለም አቅርቦት ስራ በማህበር የተደራጀው ወጣት ፍጹም ጣሰው “የማህበሩ አባላት ለምንሰማራበት የስራ ዘርፍ የሚያስፈገንን 400 ሺህ ብር የንግድ እቅድ ሰርተን ብናቀርብም  የሚያስፈልጋችሁ 100ሺህ ብር ስለሆነ በድጋሚ አስተካክላችሁ አቅርቡ ተብለናል" ብሏል፡፡

የተፈቀደው ገንዘብ አነስተኛ መሆኑን ብናሳውቅም  "ለክልሉ የተመደበው የተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ አነስተኛ ነው" የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል " ሲል ገልጿል።

''ይሁንና በተሰጠን አስተያየት መሰረት በድጋሚ  የንግድ እቅዱን  አስተካክለን ብናቀርብም እስካሁን ብድሩን ባለማግኘታችን ወደ ስራ መግባት አልቻልንም'' ሲል አባላቱ የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጿል፡፡

በሱፐር ማርኬት በሽርክና ማህበር የተደራጀው ወጣት ሐያላ አባተ በበኩሉ "50ሺህ ብር ቆጥበን 500ሺህ ብር ብድር እንዲሰጠን ብንጠይቅም በክልሉ በርካታ ማህበራት ስለተደራጁ ከተፈቀደው 100 ሺህ ብር በላይ አይሰጣችሁም ተብለናል " ብሏል።

''የሱፐር ማርኬት ስራ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚፈልግ በተደጋጋሚ ብናሳውቅም ምላሽ በማጣታችን ወደ ስራው መግባት አልቻልንም፤ ሌሎች ክልሎች እያከናወኑ ያለውን ተሞክሮ ብናቀርብም ተግባራዊ ሊደረግን አልቻለም '' ሲል  ተናግሯል፡፡

በክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ የወጣቶችና ሴቶች የንቅናቄና ግንዛቤ ባለሙያ አቶ ዮናስ ሺበሺ "መንግስት የክልሉ ስራ አጥ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ከፈቀደው  27 ሚሊዮን ብር ተንቀሳቃሽ ፈንድ ውስጥ 13 ሚሊዮን ብሩ ተለቋል" ብለዋል።

በተፈጠረው የብድር አገልግሎት 243 ኢንተርፕራይዞች በተለያዩ የስራ ዘርፍ በማህበር ቢደራጁም  መስፈርቱን ያሟሉና መቆጠብ የቻሉ 10 ማህበራት ብቻ ከ60 ሺህ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ብድር ተሰጥቷቸው ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል ፡።

እንደ ባለሙያው ገለፃ የሌሎች 20 ማህበራት የብድር አሰጣጥ በሂደት ላይ ነው።

በተጨማሪም ማህበራቱ ቁጠባን በሚያዳብሩበት የስራ እድል ፈጠራና የሚያቀርቡት የስራ አዋጭነት በባለሙያ ተመዝኖ ለማሽነሪ መግዣና ለሌሎች አገልግሎት የሚውል እስከ 1 ሚሊየን ብር ብድር እንደሚሰጥም ባለሙያው ገልፀዋል።

በማህበራቱ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች እርስ በርስ አለመስማማት፣ መቆጠብ አለመቻልና ያለቁጠባ ገንዘቡን በነጻና እጅ በእጅ እንዲሰጣቸው መፈለግ የብድር አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር ማስከተሉን ጠቁመዋል ።

ባለሙያው እንዳሉት መስፈርቱን አሟልቶ የተገኘ ማህበር ብድር የተከለከለበት ሁኔታ የለም።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ነሐሴ 4/2009 በኢትዮጵያ በተለያዩ ደረጃዎች የሚፈጸም የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል፣ ለማጋለጥና ክስ የመመስረት ተግባርን ተባብረው ለመስራትና መረጃዎችን ለመለዋወጥ እንዲቻል የሕግ አስከባሪ ተቋማት የጋራ እቅድ ይፋ ተደረገ።

ተቋማቱ የፌዴራል ስነ- ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሸን፣ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፌደራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን፣ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ናቸው። 

ተቋማቱ በእቅዱ መሰረት በአዲሱ በጀት ዓመት ሙስናን በጋራ ለመከላከል በሚያስችላቸው እቅድ ላይ እየተወያዩ ነው።

የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሸን የሙስና መከላከል ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ሙሉጌታ እንደተናገሩት፤ የጋራ እቅዱ ተቋማቱ በተሰጣቸው ተግባርና ኃላፊነት መሰረት በተበታተነ መልኩ ሙስናን ለመከላከል ሲያካሔዱት የቆዩትን እንቅስቃሴ በተቀናጀ መልኩ ለማከናወን ያግዛቸዋል።

ተቋማቱ ከዚህ በጀት ዓመት ጀምሮ የሙስና ወንጀልን የመመርመርና ክስ የመመስረት ተግባር በጋራ መስራትና መረጃዎችን መለዋወጥ እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል።

አሁን የሕግ ማስፈፀም ሥራው በአንድ ማዕከል በጠቅላይ አቃቢ ሕግና በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲመራ መደረጉን ያስታወሱት አቶ አክሊሉ፤ ተቋማቱ በተናጥል የሚያገኙትን መረጃ በማደራጀትና ለሚመለከተው አካል በማቅረብ በቅንጅት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የፊደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሀብት ጥናትና ምርምር ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተረፈ ወርዶፋ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የጋራ እቅዱ ውጤታማና ቀልጣፋ የሆነ የሕግ ማስከበር ስራዎችን በጋራ ለማከናወን ይረዳል። 

ለተቋማቱ በርካታ ተግባርና ኃላፊነትን በሰጠው በዚህ እቅድ መሰረት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ቅንጅታዊ እቅዱን ለመተግበር የሚያስችል አደረጃጀት መዘርጋት፣ በቂ የሰው ኃይልና ግብአት መመደብና ስምሪት የመስጠት ስራም እንደሚሰራ ነው ያብራሩት።

የታክስና ጉምሩክ፣ የሙስናና ሕገወጥ ንግድ ውድድር ወንጀሎች ላይ በፍርድ ቤት የሚደረግ ክርክር ደግሞ ለጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ የተተወ ተግባር እንደሆነም ተናግረዋል።

ጠቅላይ አቃቢ ህግ የፍርድ ውሳኔዎች መፈፀማቸውን የመከታተልና የማስፈጸም፣ በምርመራ መዝገብ ላይ የተጠቀሱ ኤግዚቢቶች ላይ ውሳኔ መስጠት የሚያስችል ተግባርና ኃላፊነትም እንደተሰጠው ነው የገለጹት።

የታክስና ጉምሩክ ማጭበርበር ወንጀልን በሚፈጽሙ ግብር ከፋዮችን ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት በሳምንት ቢያንስ አምስት ጊዜ የኦፕሬሽን ስራዎችን መስራት ደግሞ ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መካከል እንደሚገኙበትም ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ በመዲናዋ በገቢና ግብር አሰባሰብ ስርአቱ ላይ የሚፈፀሙ የሕግ ጥሰቶችን፣ በንግድ ውድድርና ሸማቾች መብት ጥሰት ላይ የሚፈፀሙ ሕገ ወጥ ተግባራትና የሙስና ወንጀልን በሕግ አግባብ አጣርቶ ለፍትሕ የማቅረብ ኃላፊነት ተጥሎበታል። 

የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን አስተዳደራዊ ምርመራ በሚያከናውንበት ወቅት ከፀረ-ንግድ ውድድር ተግባር ውጪ ሊመረመሩ የሚገባቸው የሕግ ጥሰቶችን ለሚመለከተው አካል እንደሚያስተላልፍም ነው አቶ ተረፈ የተናገሩት።

የተጠናቀቁ የሙስና ወንጀል ምርመራ መዛግብት በሌላው አካል ከተፈለጉ ወይም የሚጠቅሙ ሆነው ሲገኙ ሰነዶቹን የማስተላለፍና የሙስና መከላከል ጥናቶችን ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግባቸው የመረጃ ልውውጥ ማድረግም በጋራ እቅዱ ውስጥ ተካቷል።

ድርጅቶቹ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው አዋጅ 943/ 2008 መደንጉ የሚታወቅ ነው፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን