አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Tuesday, 01 August 2017

አዲስ አበባ ሀምሌ 25/2009 ልጆች፣ ወላጆች ፣ ጎልማሶች፣ አዛውንቶች በጥቅሉ በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ወደ እውቀት ገበያ ይጎርፋሉ።

የመጽሐፍት መደብሮች ብቻ ሳይሆኑ ደራሲያኑም ስራዎቻቸውን ይዘው ተደራሲያኑን ይጠባበቃሉ። የኤግዚቢሽን ማዕከል አዳራሾች የሕይወት ምግብ በሆኑ የስነ ጽሁፍ ሃብቶች ተጨናንቀዋል።

ከሐምሌ 21 ቀን ጀምሮ ለ5 ተከታታይ ቀናት እየተካሄደ በሚገኘው 3ኛው 'ንባብ ለሕይወት' የመጽሐፍት ዓውደ ርዕይ ደራሲያንና አንባቢያን ፊት ለፊት ተገናኝተው በአካል ከመተያየት ባለፈ የሆድ የሆዳቸውን ተጨዋውተዋል።

የዘንድሮው ዓውደ ርዕይ በርካታ አንባቢያን የጎበኙት እንደሆነና ስራቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ ከአንባቢያን ጋር ለመተዋወቅም አጋጣሚውን ፈጥሮልናል ባይ ናቸው፤ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዓውደ ርዕዩ ተሳታፊ ደራሲያንና መጽሐፍት መደብሮች።

አዲስ የግጥም መጽሐፏን ይዛ የቀረበችውና በጎብኝዎች ብዛት የተደነቀችው ገጣሚ አቢሲኒያ ፈንታው አውደ ርዕዩ ከአንባቢያን ጋር እንዳስተዋወቃት አንዷ ምስክር ናት።

በዘጠኝ ዓመታት የማስተማር ልምድ የቀመረውን የፊዚክስ እውቀት ’ፊዚክስ እና ሕይወት’ የሚል ርዕስ የፊዚክስን ትምህርት ከተግባር ጋር ለመረዳት የሚያስችል አዲስ መጽሐፍ ይዞ የቀረበው መምህር ፈቃዱ ተስፋዬ ”መጽሀፉን ከመሸጥ ባሻገር ራስህን ለሰዎች ታቀርባለህ፣  የተለያዬ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ሃሳብ ትወስዳለህ።አንተም በመጽሐፉ ራስክን ታስተዋውቃለህ። ባዛሩ ላይ 100% ማለት ይቻላል ለኔ ጥሩ እድል ነበር”ብሏል፡፡

ትኩረቱን በኢህአፓ ታሪክ ያደረገው ‘ማማ በሰማይ’ ተብሎ የተተረጎመው የ’Tower in the Sky’ መጽሐፍ እንዲሁም በቅርቡ ‘ኀሠሣ’ በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ የተመለሰው የ’Mine to wine’ መፅሃፍ ደራሲት ሕይወት ተፈራም ለ5 ቀናት በዘለቀው ዓውደ ርዕይ ታድማለች።

“በጣም ብዙ ሰዎች መፅሓፉን እንጂ (Tower in the sky) እኔን አያውቁኝም።እና ይህን አጋጣሚ ከሰዎች ጋር ለመተዋወቅ፣ለመፈረምና ለመቀራረብ  እንዲሁም ጥያቄዎች ያላቸው ሰዎች ለረጂም ጊዜ የነበሯቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ችያለሁ።” ብላለች፡፡

ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ የተሳተፈው የ’ቡክ ላይት መጽሐፍት መደብር’ ረዳት ማናጀር አቶ ተፈሪ መልካሙ በዓውደ ርዕዩ ታላቅ ቅናሽ በማድረጉ በርካታ ጎብኝዎችን ማግኘት መቻላቸውን አመልክተዋል።

በተመሳሳይ ከአውቶቢስ ተራ የመጡት የ’ሙሉጌታ በስር መጽሃፍት መደብር’ ባለቤት አቶ ሙሉጌታ በስር በዘንድሮው አውደ ርዕይ በርካታ ማስታወቂያ በመሰራቱ ድባቡ ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ነው ይላሉ።

ከሀምሌ 21 እስከ 25 ቀን 2009 ዓ.ም የተካሄደው የመፅሃፍት ዓውደ ርዕይ ከ2 መቶ በላይ መጽሐፍት መደብሮች፣ አሳታሚዎች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የብዙሃን መገናኛ ድርጅቶች ተሳትፈውበታል።

የዘንድሮውን ዓውደ ርዕይ 200 ሺህ የሚገመቱ ሰዎች እንደጎበኙት ከፕሮግራሙ ፕሮጀክት አስተባባሪዎች ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

በፕሮግራሙ ከመጽሐፍት ሽያጭ በተጨማሪ የወጣቶች ጥያቄና መልስ ውድድር፣የአዳዲስ መጽሐፍት ምርቃ አንዲሁም ምሁራንን ያሳተፈ የመጽሐፍት ሐሰሳ ሲካሄድ ቆይቷል።

Published in ማህበራዊ

ጅግጅጋ ሀምሌ 25/2009 የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ከ2 ቢልዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሁለት ነጥብ ስምንት ቢልዮን ብር የሚበልጥ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በክልሉ የሚካሄደው ኢኮኖሚያዊ እንቅሰቃሴ የሚያመነጨውን ገቢ አሰባሰብ ሂደት ላይ የነበረው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ የተሻለ እድገት መመዝገቡን የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ አቶ አብዲረህማን  መሀመድ  ተናግረዋል።

የክልሉ ህብረተሰብ በተነሳሽነት ታክስና ግብር እንዲከፍል ኮንትሮባንድን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መምጣቱንም ለገቢው ማደግ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።

በዓመቱ 2 ቢልዮን 250 ሚልዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረ ሲሆን በተደረገው ጥረት ከቀጥተኛ ታክስ፣ ቀጥተኛ ካልሆነ ታክስና ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት መሰረት በማድረግ በክልል ደረጃ፣በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደር የተሰበሰበው 2 ቢልዮን 088 ሚልዮን  578 ሺህ 34 ብር ነጥብ 46 ሣንቲም መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የእቅዱን ዘጠና ሁለት ነጥብ ስምንት በመቶ ይሸፍናል ብለዋል፡፡

እቅዱ ሙሉ ለሙሉ ያልተሳካው በክልሉ በአብዛኛው ወረዳዎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት አርብቶ አደሮች ከቤት እንስሳዎቻቸው የሚከፍሉት የነበረውን ዓመታዊ ግብር የክልሉ መንግስት በእፎይታ መልክ እንዲታለፍ በማድረጉ ነው፡፡

በክልል፣ በወረዳና በከተማ አስተዳደር በተካሄደው የተቀናጀ እንቅሰቃሴ ከአጠቃላይ የክልሉ ዓመታዊ በጀት ወደ 20 ነጥብ 8 በመቶ በራሱ ገቢ መሸፈን መቻሉን ኋላፊው ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የተመዘገበውን የገቢ እድገት በዘላቂነት ለማስቀጠል በያዝነው 2010 ዓ.ም ከሦስት ቢልየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን ገልጸው መንግስት ለህብረተሰቡ የሚሰጣቸዉን የተለያዩ አገልግሎቶች አጠናክሮ ለመቀጠል እንዲያስችለዉ ህብረተሰቡ ግብርን በወቅቱ የመክፈል ግዴታዉን እንዲወጣ አቶ አብዲ አሳሰበዋል ፡፡

ባለስልጣኑ የህግ አፈፃፀምና ታክስ ኦዲት ስራ ሂደት ተወካይ አቶ አብዲ ኢስማኤል በንግድ ተቋማት የሚታዩ በደንበኞችና ሻጮች መካከል የሚፈጠሩ አንዳንድ ቀረጥና ግብር የመደበቅ ስራዎች ለመቀነስና ቁጥጥሩን ለማጥበቅ ለ98 ሺህ 168 ግብር ከፋዮች ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።እንዲሁም በዓመቱ 9ሺህ 747 ግብር ከፋዮች መለያ ቁጥር እንዲያገኙ ተደርገዋል፡፡

በግንባታ ተቆራጭነት ስራ የተሰራማው ግብር ከፋይ አቶ ሽሬ ጉሌድ በሰጡት አስተያየት የግብር ግዴታቸውን በመወጣታቸው ከግብር ዕዳ ነፃ ለመሆናቸው ማረጋገጫ ለመውሰድ ቀደም ሲል 2 ቀናት ይፈጅባቸው እንደነበረ አስታውሰው በአሁኑ ወቅት በአንድ ቦታና በሰላሳ ደቂቃ ውስጥ አገልግሎቱን ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል።

አቶ ሽሬ “እኔ  የግንባታ ተቋራጭ ድርጅት ባለቤት እንደመሆኔ ያለብኝ ግብር በፍጥነት ከፊዬ መሄድ አለብኝ፤ ለዚህ ደግሞ ባለስልጣኑ ግልጽ  የዜጎች ቻርተር ተግባራዊ በማድረጉ ስራችንን በጊዜው ለማከናወን ረድቶናል” ብለዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሀምሌ 25/2009 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ላይ በዝግ ድርድር ማድረግ ጀመሩ።

ፓርቲዎቹ ከሁለት ሳምንት በፊት ባካሄዱት ውይይት ለደርድር የፀደቁ 12 አጀንዳዎችን ቅድም ተከተል የወሰኑ ሲሆን አጠቃላይ ድርድሩን በ90 ቀናት ውስጥ ለማጠቃለል ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በዚህ መሰረት ፓርቲዎቹ ሐምሌ ሰባት ቀን 2009 ዓ.ም በነበራቸው ውይይት ባስቀመጡት የድርድር ቅደም ተከተል መሰረት በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ላይ ዛሬ ድርድር አድርገዋል።

ለመገናኛ ብዙሃን ዝግ በነበረው ድርድር ፓርቲዎቹ ለድርድር አመቺ ነው ባሉት ከአንድ እስከ 31 በተዘረዘሩ የአዋጁ አንቀፆች ላይ የመጀመሪያ ምዕራፍ ድርድራቸውን አካሂደዋል።

ይሁንና የድርድር አጀንዳው ሙሉ በሙሉ ባለመቋጨቱ ፓርቲዎቹ በቀጣይ ሐሙስ ሐምሌ 27 ቀን 2009 ዓ.ም በቀሩ ሃሳቦች ላይ ለመደራደር በቀጠሮ ተለያይተዋል።

ፓርቲዎቹ በዚህ አጀንዳ ላይ የሚያደርጉትን ድርድር እንዳጠናቀቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች የስነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 662/2002 ላይ ድርድራቸውን ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የፀረ ሽብር ህግ፣ የብዙሃን መገናኛ አዋጅ፣ የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጅ፣ የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት ተቋማት አደረጃጀትና አፈፃፀም  እንዲሁም  የፍትህ አካላት አደረጃጀት አዋጅ እንደቅደም ተከተላቸው ፓርቲዎቹ የሚደራደሩባቸው አጀንዳዎች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች የመዘዋወር፣ የመኖርና ንብረት የማፍራት መብትና የህግ ማዕቀፍ፣ የሊዝ አዋጅና የልማት ተፈናቃዮች፣ የታክስ ስርዓት እንዲሁም ብሔራዊ መግባባት ላይ የተያዙ አጀንዳዎችም ጊዜያቸውን ጠብቀው ለድርድር ይቀርባሉ።

ፓርቲዎቹ አንድ የድርድር አጀንዳ ከአምስት ቀናት በላይ መውሰድ እንደማይኖርበት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

እስካሁን ባደረጉት 14 የግንኙነት መርሐ-ግብር አብላጫውን ጊዜ የወሰደው እንዴትና ስለ ምን እንወያይ የሚለው ሃሳብ ነበር።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ  ሀምሌ 25/2009 በአዲስ አበባ ከተማ የአተት በሽታ እንዳይከሰት ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የመዲናዋ ጤና ቢሮ ገለጸ።

የጤና ተቋማት በበኩላቸው በሽታው እንዳይከሰት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ከመስጠት በተጨማሪ በሽታው ከተከሰተ ፈጣን እርዳታ ለመስጠትና ሥርጭቱን ለመግታት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የቢሮው የሕብረተሰብ ጤና ምርምርና አደጋዎች ቁጥጥር ዋና የሥራ ሂደት መሪ ዶክተር አብርሃም ተስፋዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት ከባለፈው ዓመት ተሞክሮ በመውሰድ በሽታውን ለመከላከል በሕብረተሰብ አደረጃጀቶችና በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

የከተማዋን ንጽህና ለመጠበቅም ከጽዳት አስተዳደር፣ ከውሃና ፍሳሽና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በወረዳ ደረጃ የበሽታ ቅኝትና አሰሳ ባለሙያ እንዲኖር የሚያስችል አዲስ መዋቅር በማደራጀት ከ100 በላይ ባለሙያዎች ሰልጥነው እንዲሰማሩ ተደርጓል ብለዋል።

ሕብረተሰቡ የግልና የአካባቢውን ንጽህና በአግባቡ እንዲጠብቅና የበሽታውን ምልክት ካየም በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም እንዲሄድ አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት በሽታው ወደ ታየባቸው ክልሎች የሚጓዙ ሰዎችም ጥንቃቄ እንዲያደርጉም መክረዋል ።

በመዲናዋ የአተት በሽታ ከተከሰተ ህክምና ለመስጠትና ስርጭቱን ለመግታት የሚያስችሉ ማዕከሎች ዘውዲቱና ምኒልክ ሆስፒታሎችን ጨምሮ በአዲሱ ገበያና ሚኪሊላንድ ጤና ጣቢያዎች ተቋቁመዋል።

በተጨማሪም በዘውዲቱ ሆስፒታል በሽታው ቢከሰት ህሙማን ተኝተው የሚታከሙባቸው አልጋዎች፣መድሃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች ተዘጋጅተዋል።

በሆስፒታሉ የድንገተኛ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ሲስተር ስንዱ ኃይሉ በማዕከሉ ህክምና ለመስጠት መድኃኒት፣ የጤና ባለሙያዎችና የህክምና ቁሳቁሶች መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት

 

በአዲሱ ገበያ ጤና ጣቢያ የበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ እንደገና ቢያዝን በበኩላቸው ባለፈው ዓመት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ፣ የቁሳቁስና የባለሙያ ዝግጅት ስራ የተሰራው የአተት በሽታ ከተከሰተ በኋላ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች በመሰራታቸው በሽታውን በቀላሉ መቆጣጣር ይቻላል ብለዋል።

የመዲናዋ የቤቶች አቀማማጥ፣ የመጸደጃ ቤቶች አጠቃቀም የአካባቢ ንጽህናና ሌሎች ችግሮች ግን ፈታኝ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በጤና ጣቢያው ማዕከሉን ለማቋቋም የህክምና መሳሪያዎች፣መድሃኒቶችና የባለሙያ ቡድኖች የማደራጀትና ስልጠና የመስጠት ስራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል።

ለግልና ለአካባቢ ንዕህና መጠበቂያ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ከአጋር ድርጅቶች ጋር የማሰራጨት ስራ መሰራቱንም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የአተት በሽታ በሱማሌ፣በአፋር እና በአማራ ክልሎች መከሰቱ ይታወቃል።

ባለፈው ዓመት የአተት በሽታ በተከሰተበት ወቅት ለመከላከሉ ሥራ እንዲውል ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሀምሌ 25/2009 በአዲስ አበባ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እየተሰጠ ያለው የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ከፍለው መማር ለማይችሉ ተማሪዎች ጥሩ ዕድል እንደሆነላቸው ተማሪዎች ተናገሩ።   

በየዓመቱ  በክረምት ወራት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አገልግሎት ከሚሰጡባቸው መስኮች መካከል የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት አንዱ ነው።

በዚሁ ተግባር ላይ ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ 2 ሺ 200 ተማሪዎች በመዲናዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች  በሚገኙ 100 ትምህርት ቤቶች የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ላይ ናቸው።  

የኢዜአ ሪፖርተር በዳግማዊ ሚኒሊክ፣ በሚሊኒየምና ካራ አሎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመገኘት የአገልግሎት አሰጣጡን የቃኘ ሲሆን አገልግሎቱ በተለይም ከፍለው መማር ለማይችሉ ተማሪዎች ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣዩ አመት የስምንተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ላይ የሚቀመጠው ተማሪ ወርቁ ኃይሉ እያገኘ ያለው እውቀት ለፈተናው ቀድሞ ለመዘጋጀት እንደሚያግዘው ተናግሯል።

ተማሪ  ወይንሸት ጀንበሩ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን አካባቢዋ ላይ በተመቻቸላት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት እድል ተጠቃሚ በመሆኗ የኮምፒዩተር አጠቃቀም እውቀት እያገኘች እንደሆነ ገልጻለች።

የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርቱን በመስጠት ላይ ያሉ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች በበኩላቸው አገልግሎቱን በፈቃደኝነት ለተማሪዎቹ መስጠቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

የኮተቤ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የሁለተኛ ዓመት የሂሳብ ተማሪ ወጣት አየለ ማሞ  እንዳለው በበጎ ፈቃድ የሚሰጠው ትምህርት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን ለቀጣይ አመት ትምህርት ዝግጁ ያደርጋቸዋል ይላል።

ወጣት ዘሪሁን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት የተመረቀ ሲሆን በእረፍት ግዜው ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠቱና እውቀቱን በማካፈሉ የህሊና እርካታ እንዳገኘ ገልጾ በተሰማራበት ዘርፍም ልምድ እያገኘ መሆኑን ነው የተናገረው። 

በዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአዲስ አበባ ለሚገኙ የገንዘብ ችግር ያለባቸው 10 ሺህ ተማሪዎች የመማሪያ ግብዓትና አልባሳት መሟላቱን ከአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

Published in ማህበራዊ

መቱ ሀምሌ25/2009 በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን በዘንድሮው ክረምት ከ68 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የተሻሻለ የቡና ችግኝ መተከሉን የዞኑ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ምክትል ኃላፊ አቶ ተሾመ ዴሬሳ ለኢዜአ እንደገለፁት የቡና ችግኙ የተተከለው በዞኑ ዘጠኝ ወረዳዎች ለልማቱ ተስማሚ በሆነ ከ19 ሺህ 100 ሄክታር መሬት ላይ ነው፡፡

ከሰኔ ወር መጀመሪያ አንስቶ እስከ ሃምሌ አጋማሽ በተካሄደው የቡና ችግኝ ተከላ አንድ ሺህ  500 ሴቶችን ጨምሮ ከ51ሺ በላይ አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የቡና ችግኙ ከዚህ ቀደም በሄክታር ሲገኝ የነበረውን ስድስት ኩንታል ምርት በእጥፍ የሚያሳድግና በምርምር የተገኘ ምርጥ ዝርያ  መሆኑን አመልክተዋል።

አርሶ አደሮቹ የቡና ችግኙን ከመትከል ባለፈ ከ2 ሺ 200 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሚገኝ ያረጀ ቡና የመጎንደል ስራ ማከናወናቸውን ገልፀዋል።

በክረምት ወቅት የቡና ችግኞቹ በአግባቡ እንዲተከሉና ያረጁትን በመጎንደል እንዲንከባከቡ ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ቀደም ሲል ተሰጥቷል።

በዞኑ በ2010 የክረምት ወቅት የሚተከል ከ40 ሺ 200 ኪሎ ግራም በላይ የተሻሻለ የቡና ዝርያ ከ6ሺ በላይ በሚሆኑ የአርሶ አደርና የመንግስት የችግኝ ጣቢያዎች ላይ ተዘርቶ እንክብካቤ እየተደረገለት ነው፡፡

የበደሌ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ሃጎስ ጌታቸው በሰጠው አስተያየት በክረምት ወቅት የቡናና ሌሎች የዛፍ ችግኞች በመትከል ጥበቃና እንክብካቤ እያደረገ እንደሆነ ተናግሯል።

በጮራ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ዲንቃ ገዛኸኝ በበኩላቸው በክረምት ወቅቱ ሁለት ጥማድ የሚሆን መሬት በቡና ሸፍነው እንክብካቤ እያደረጉ ነው።

በግብርና ባለሙያዎች ምክርና የሙያ ድጋፍ በመታገዝ የቡና ማሳቸውን ከአረም በመጠበቅና ያረጁትን በመጎንደል የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

በቡኖ በደሌ ዞን በአሁኑ ወቅት ከ100ሺ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ከ65 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በቡና ልማት ተሰማርተው እንደሚገኙ የዞኑ በቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማት ባለስልጣን መረጃ ያመለክታል።

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ ሀምሌ 25/2009 በተያዘው በጀት ዓመት 33 በመቶ የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎች በራስ ገቢ ለመሸፈን እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ገለጸ።

የኦሮሚያ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ቱሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የክልሉ መንግስት ከሕብረተሰቡ የተነሱትን ዘርፈ ብዙ የልማት ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ የሚያመነጨውንና የሚሰበስበውን ገቢ ይወስናል።

በእዚህም በተያዘው የ2010 በጀት ዓመት በክልሉ ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።

በበጀት ዓመቱ የሚሰበሰበው ገቢ 33 በመቶ የሚሆነውን የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎች በራስ ገቢ ለመሸፈን እንደሚያስችልም ገልፀዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም ከመደበኛ፣ ማዘጋጃ ቤት አንዲሁም ታክስና ታክስ ካልሆኑ የገቢ ምንጮች ለመሰብሰብ ያታቀደውን 18 ቢሊዮን ብር ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ከወዲሁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ ዓመት በተደረገው የዕለት ሽያጭ ገቢ ተመን ላይ ከንግዱ ማሕበረሰብ ለተነሳው ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ምላሽ እየተሰጠና ቅሬታውም በአግባቡ እየተፈታ መሆኑን ገልጸዋል።

"እስከዛሬ ድረስ ከ45 በመቶ በላይ የሚሆነው የክልሉ ገቢ የሚሰበሰበው ከመንግስት ሠራተኞች ነው" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከንግዱ ማህበረሰብ የሚሰበሰበው ገንዘብ 30 በመቶ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።

መንግስት በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የሕብረተሰቡን የልማት ፍላጎትና ጥያቄ ለመመለስ የወቅቱን የገቢና የወጪ ዕቃዎችን ዋጋ መሰረት ያደረገ የዕለት ገቢ ሽያጭ ተመን በዘንድሮ ዓመት ተግባራዊ ማድረጉን አመልክተዋል።

በዚህም በተጠናቀቀው ዓመት በክልሉ ህገ ወጥነትን ለመከላከል በተደረገው ጥረት በህገ ወጥ ንግድ የተሰማሩ ከ60 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ወደ ግብር ከፋይ መረብ እንዲገቡ መደረጉን አስረድተዋል።

የአዳማ ከተማ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርት ቤት የሥራ አስጻሚ አባል የሆኑት አቶ ዘውዴ ዲባባ በበኩላቸው፣ መንግስት ከሕብረተሰቡ የሚነሱትን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በጀት እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።

"ከንግዱ ማህበረሰብ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎች የሚውል ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ ይገባል" ያሉት አቶ ዘውዴ የዕለት ገቢ ሽያጭ ተመኑ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ካሉት አንዳንድ ነጋዴዎች በስተቀር የጎላ ተፅዕኖ አለመፍጠሩን አመልክተዋል።

ባለስልጣኑ በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ቢያቅድም 10 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 78 በመቶ ብቻ ለማሳካት መቻሉን ተመልክቷል።

በክልሉ ከ383 ሺህ በላይ ነጋዴዎች በዕት ሽያጭ ገቢ ተመን ውስጥ የተካተቱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 344 ሺህ 238 የሚሆኑት በደረጃ "ሐ" ግብር ከፋይ ውስጥ የተቀመጡ መሆናቸውን ከኦሮሚያ ገቢዎች ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ኢኮኖሚ

ጎንደር ሀምሌ 25/2009 ከአምስት በላይ የሰብል ዘሮችን በመስመር ለመዝራት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ፈጠራ መሳሪያ ለሙከራ እየተገበረ መሆኑን አይባር አነስተኛ የእርሻ መሳሪያ ኢንጂነሪንግ ድርጅት አስታወቀ። 

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና ተመራማሪ ዶክተር መለሰ ተመስገን ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራ የተገኘው መሳሪያ ጤፍ፣ ሰሊጥ፣ ጥጥ፣ ማሽላና ስንዴን በሰው ጉልበት በመስመር መዝራት የሚያስችል ነው፡፡

ቴክኖሎጂው አንድ ሄክታር መሬትን በሦስት ሰዓት ውስጥ በመስመር ለመዝራት እንደሚያስችል ገልጸው፣ ይህም ከእዚህ ቀደም በእጅ ዘር ለመዝራት ይባክን የነበረውን ጊዜ፣ አድካሚ የዘር ሥራ እንዲሁም የሰው ጉልበትና ጊዜን ለመቆጠብ እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

"መሳሪያው በተጨማሪም የዘር ብክነትን በማስቀረት ዘርን በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችል ነው" ያሉት ዶክተር መለሰ፣ ለአንድ ሄክታር መሬት እስከ ሦስት ኪሎ ግራም ሰሊጥና ጤፍ  ብቻ በመጠቀም የዘር ወጪን በግማሽ እንደሚቀንስ አመልክተዋል።

እንደ ዶክተር መለሰ ገለጻ፣ የፈጠራ ቴክኖሎጂው ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የባለቤትነት መብት ተሰጥቶታል።

በተያዘው ክረምት በሰሜን ጎንደር መተማና በትግራይ ክልል ሁመራ አካባቢ በአነስተኛ እርሻ ሰሊጥ ፣ጥጥና ማሽላ የሚያለሙ አርሶአደሮችን የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ በማድረግ የመሳሪያውን ብቃት የመፈተሽ ሥራ እየተከናወነ ነው።

መሳሪያው በማንኛውም የአፈር ሁኔታ ላይ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ተደርጎ መሰራቱም ለየት እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።

የመሳሪያው ብቃት ከተረጋገጠ በኋላም በ2010 ዓ.ም በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች በማስተዋወቅ ወደ ሥራ ለማስገባት መታቀዱን ዶክተር መለሰ ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ ቴክኖሎጂውን በገጠሩ አካባቢ ለሚደራጁ ስራአጥ ወጣቶች በስፋት በማቅረብ ለአርሶአደሩ በኪራይ አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መታሰቡንም ጠቁመዋል፡፡

አይባር ኢንጂነሪንግ ከዚህ ቀደም በመላ ሀገሪቱ ሥራ ላይ የዋለውንና የጥቁር አፈር የዝናብ ውሃን ለማጠንፈፍ እያገለገለ ያለውን ቢቢኤም የተባለ የእርሻ መሳሪያ በመፍጠር ሥራ ላይ አውሏል፡፡ 

በኔዘርላንድስ መንግስት የበጀት ድጋፍ የተቋቋመው የሰሊጥ ግብይት መረብ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ገረመው ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ በሰሜን ጎንደርና በሁመራ አካባቢ የሚገኙ ሰሊጥ አምራቾች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ የተደረገው ቴክኖሎጂ በአነስተኛ የእርሻ መሬት ላይ ሰሊጥን በመስመር ለመዝራት የሚጠይቀውን ከፍተኛ የሰው ጉልበት ያስቀራል።

በአንድ ሰው ብቻ ተይዞ በመስመር መዝራት የሚያስችል በመሆኑም ፕሮጀክቱ መሳሪያውን በስፋት ለማስተዋወቅ እንደተዘጋጀ ገልጸዋል፡፡       

 

አዲስ አበባ  ሀምሌ 25/2009 በኢትዮጵያ 43 ሚሊዮን የሚሆነው ነዋሪ ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዳልሆነ ዋተር ዶት ኦርግ አስታወቀ።

 በተጨማሪም 71 ሚሊዮን የሚሆነው ነዋሪ ህዝብ የመጸዳጃ ቤት እንደሌለው ተቋሙ ገልጿል።

 ችግሩን በዘላቂነት መፍታት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትና ዋተር ዶት ኦርግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂደዋል።

 በኢትዮጵያ የዋተር ዶት ኦርግ ተጠሪ  አቶ ሳልፊሶ ኪታቦ  በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የንጹህ መጠጥ ውሃና የመጸዳጃ ቤት አቅርቦት ችግር በሀገሪቱ በስፋት እንደሚታይ ገልጸዋል።

 በዚህም በሀገሪቱ ካለው የህዝበ ቁጥር 43 ሚሊዮን የሚሆነው የንጹህ መጠጥ ውሃ እንደማያገኝ  ተናግረዋል።

 በሌላ በኩል 71 ሚሊዮን የሚሆነው ነዋሪ ህዝብ የግል መጸዳጃ ቤት እንደሌለውና 28 ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ የሚጸዳዳው  በየቦታው   መሆኑንም ጠቁመዋል።

 ይህም በሰው ጤና ላይ የሚያደርሰው አደጋ ከፍተኛ በመሆኑ ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት በጋራ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

 የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በበኩላቸው  በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍና ለዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃን ለማዳረስ ከመንግስትና ከግል የልማት ድርጅቶች ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን  ተናግረዋል።

 በዚህም መሰረት በሀገሪቱ የሚገኙ የተወሰኑ አነስተኛ የግል የፋይናንስ ተቋማት በረጅም ጊዜ ብድር አቅም ለሌላቸው ነዋሪዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ በቤታቸው እንዲያስገቡ ለማድረግ እንዲሁም ለመጸዳጃ ቤት አገልግሎት ግንባታና እድሳት የሚውል የብድር አገልግሎት እየሰጡ እንደሆኑም ገልጸዋል።

 በዚህም የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋምና የቪዥን ፈንድ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋም የመሳሰሉ አክሲዮን ማህበራት በዚህ ዘርፍ እየተሳተፉ ይገኛሉ ተብሏል።

 አነስተኛ የፋይናንሰ ተቋማትን በዚህ ዘርፍ ማሳተፉ አዲስ አማራጭ የሚፈጥር በመሆኑ ችግሩን ለማቃለል ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ነው የጠቆሙት።

 ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንዲቻል ሌሎች የፋይናንሰ ተቋማትና የልማት ድርጀቶች   በጋራ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

 የንፁህ መጠጥ ውሃና የመጸዳጃ ቤት አቅርቦት ችግር በጤና ላይ ቀውስ እንዳያስከትል ከጤና ተቋማት ጋርም በችግሩ ዙሪያ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

 በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ  አቅርቦት 83 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ በትግበራ ሂደት ላይ እንደሚገኝም ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ ገልጸዋል።

 ዋተር ዶት ኦርግ በኢትዮጵያ ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃና የመጸዳጃ ቤት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ድጋፍ  እየሰጠና ጥናትም እያደረገ የሚገኝ ተቋም ነው።

 በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት 57 በመቶ መድረሱን ከውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ይጠቁማል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  ሀምሌ 25/2009 በምስራቅ አፍሪካ አገራት የሚስተዋለውን ህገ ወጥ የመድኃኒት ዝውውር በጋራ ለመከላከል የሚያስችል ፕሮግራም  ሊተገበር እንደሆነ ተገለጸ።

 ይህ የተገለጸው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን /ኢጋድ/ ብሔራዊ የመድኃኒት ቁጥጥር ተቋማት ኃላፊዎች አውደ ጥናት ዛሬ በአዲስ አበባ ሲጀመር ነው።

 የኢጋድ አባል አገራት የመድኃኒት ቁጥጥር ትብብር ፕሮግራም ለአምስት ዓመታት የሚቆይ እንደሆነም ተገልጿል።

 ፕሮግራሙ  ህገ ወጥ የመድኃኒት ዝውውርን በጋራ በመከላከል ደህንነቱና ጥራቱ የተረጋገጠ መድኃኒት ለቀጣናው አገራት ዜጎች ለማድረስ  ያለመ ነው።

 ፕሮግራሙን ለማስፈጸም የተዘጋጀው አደረጃጀትና መዋቅርም የአባል አገራቱ የመድኃኒት ቁጥጥር ተቋማት ኃላፊዎች ለሶስት ቀናት በሚያካሂዱት አውደ ጥናት ላይ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

 በድንበሮች አከባቢ  የጋራ ተቆጣጣሪ ግብረሃይል ማቋቋም፣ ስለሚሰራጩ አዳዲስ ህግ ወጥ መድሃኒቶች መረጃ መለዋወጥ፣ አባል አገራቱ የተደራጀ የመረጃ ቋት እንዲኖራቸው ማድረግ የትብብር ፕሮግራሙ ከሚይዛቸው ስልቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

 የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ተወካይ ሚስ ፋቱማ አደም በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ለምስራቅ አፍሪካ አገራት ህገ ወጥ የመድኃኒት ዝውውር ትልቅ ፈተና ነው።

 አገራቱ ባላቸው የመድኃኒት ቁጥጥር የህግ ማዕቀፍ ህገ ወጥ የመድኃኒት ዝውውርን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ቢሆንም በሚፈለገው መልኩ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም ብለዋል።

 በዚህም ምክንያት ደህንታቸውና ጥራታቸው ያልተጠበቀ መድኃኒቶች እየተሰራጩ በአገራቱ የብዙ ዜጎችን ህይወት እየቀጠፉ በመሆኑ አባል አገራቱ ችግሩን ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ  በተቀናጀ መልኩ መስራት እንዳለባቸው መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

  አዲሱ ፕሮግራም ይህን ታሳቢ በማድረግ የተቀረጸና የነበሩትን ችገሮች በመቅረፍ ዜጎች ደረጃውን የጠበቀ መድሃኒት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም ሚስ ፋቱማ አመልክተዋል።

 ኢትዮጵያ የዚህ ፕሮግራም ሃሳብ አመንጪ ናት ያሉት ደግሞ  የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና እክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢቂላ ባይሳ ናቸው።

  በአባል አገራቱ እየተስፋፋ የመጣውን ህገ ወጥ የመድኃኒት ዝውውር ለመግታት በተናጠል የሚደረገው ጥረት በቂ ባለመሆኑ ችግሩን ለመከላከል የሚያስችል የተቀናጀ የትብብር ማዕቀፍ እንዲኖር ኢትዮጵያ ሀሳብ ማቅረቧን አስታውሰዋል።

 የፕሮግራሙ ተፈጻሚ መሆን ኢትዮጵያ በህገ ወጥ መድኃኒት ዝውውር ቁጥጥር ሂደት ያላትን ተሞክሮ ለማካፈልና ልምድ ለመቅሰም ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርላትም ተናግረዋል።

 "የኢጋድ አባል አገራት ለፕሮግራሙ ተፈጻሚነት ለሚያደርጉት ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ ይሰጣል" ያሉት ደግሞ የአለም የጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ኃላፊ ተወካይ ዶክተር ፖል ማዩካ ናቸው።

 ድርጅታቸው ለአገራቱ ተቋማት የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት ተወካዩ ከአገራቱ ጋር በትብብር ለመስራት ያላቸውንም ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

 በውይይቱ ላይ አለም ባንክና አጋር አካላት ፕሮግራሙን በመገምገም ለተግባራዊነቱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።

 የኢጋድ የመድኃኒት ቁጥጥርና ትብብር ፕሮግራም በአፍሪካ የተቀናጀ የመድኃኒት ቁጥጥርና ትብብር ፕሮግራም አካል ሲሆን የደቡባዊ አፍሪካ አገራት የልማት ማህበረሰብ (ሳዴቅ) እና የምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) አባል አገራትም መሰል ፕሮግራም እየተገበሩ ይገኛሉ።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን