×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Friday, 09 June 2017

  አዲስ አበባ ሰኔ2/2009 በሳዑዲ ዓረቢያ ሕጋዊ የሥራና የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ዜጎች የምህረት ጊዜው ሳይገባደድ ወደ አገራቸው አንዲመለሱ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት አንዳለበት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጽህፈትቤቱ ለኢዜአ በላከው ሳምንታዊ አቋም መግለጫ እንዳስታወቀው ዜጎቹ እንግልትና ስቃይ ሳይደርስባቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከሳዑዲ መሪዎች ጋር በተደጋጋሚ በጉዳዩ ዙሪያ መምከራቸውን ለአብነት ጠቅሷል።

በርካታ ዲፕሎማቶች ከኤምባሲና ቆንሱላ ውጭ ለኑሮ በማያመቹ ሥፍራዎች ላይ ሆነው ወገኖቻችንን በተሰጠው የጊዜ ገደብ ለማስውጣት እያገለገሉ እንደሚገኙም እንዲሁ።

ይህ ጥረት አሁንም በተጠናከረ መልኩ አንደቀጠለ የገለጸው መግለጫው አሁንም ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መንግሥት ጥሪውን እያቀረበ እንደሚገኝ ነው የጠቆመው።

ዜጎችን የማሰመለሱ ብሔራዊ ጥረት ግቡን አንዲመታም ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች የበኩላቸውን  በኃላፊነት በመወጣት ከመንግሥት ጎን እንዲቆሙ ነው መግለጫው ያሳሰበው። 

በዚህም በተለይም ወላጆች ልጆቻቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ባላቸው ግንኙነት ሁሉ ግፊት ማድረግ ለነገ የማይባል ሥራቸው ሊሆን አንደሚገባም ጠቁሟል።

በሌላ በኩል የኃይማኖት አባቶች፣ እንዲሁም በሳዑዲ ዓረቢያ በግልና በቡድን እየተንቀሳቀሱ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እያደረጉ ያሉትን ጥረት አጠናክረው አንዲቀጥሉ ጠይቋል።

 የመግለጫው ሙሉ ቃል ይህ ነው፡-

 በዜጎቻችን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ አበክረን እንሠራለን!

አገራችን ኢትየጵያ በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ጥቂት አገራት መካከል በግንባር ቀደምነት የምትጠቀስ አገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ በተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት የበርካታ ዜጎቻችን ሕይወት ተቀይሯል፡፡ ይሁን እንጅ ከስሩ ገርስሰን ያልጣልነው ቀንደኛው ጠላታችን ድህነት አሁንም ከችጋር ያልተላቀቀ ብዙ ህዝብ እንዲኖረን አድርጓል፡፡

አገር ሊያድግና ሊበለጽግ፣ ሕዝብም ከልማቱ ሊጠቀም የሚችለው ጠንክረን በመስራት፣ ዘለቄታዊና አስተማማኝ ዕድገት እና ብልጽግና ማስመዝገብ ስንችል ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ስደትን ከድህነት መውጫ መንገዳችን አድርገን ልንወስደው አንችልም፡፡

ዜጎች ሕገ-መንግስታዊ መብታችን ነው በሚል በውጭ አገራት ሄደው ለመስራት እስከፈለጉ ድረስ መብታቸው መሆኑን የኢፌዴሪ መንግስት ይቀበላል፤ ሆኖም በሚሄዱባቸው አገራት ሕጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ እንዲኖራቸው ይፈልጋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ዜጎቻችን በሕገ - ወጥ መንገድ በባዕዳን አገራት ሄደው ለስቃይ እንዳይዳረጉ መከላከል ሌላኛው የመንግስት ዋነኛ ትኩረት፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሌላው የሚታየው ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎቻችን በማንኛውም ጊዜ ከሚኖሩበት አገር ውጡ በሚባሉበት ወቅት ስብዕናቸውና መብቶቻቸው ተከብረውላቸው ወደአገራቸው እንዲመለሱ ማድረግም መንግስት በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት የሚያከናውነው ተግባር ነው፡፡

 በዚሁ መሰረት መንግሥት ሕገ - ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ሰፊ ጥረት እያደረገ ባለበት በአሁኑ  ወቅት ሕጋዊ የውጭ አገር የሥራ ስምሪትን ተግባራዊ ለማድረግ ከአራት አገራት ጋር ስምምነት መፈፀሙ ይታወቃል፡፡ ሌላው በሳዑዲ አረቢያ እየታየ እንዳለው አንድም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ቢሆን እንግልት እና ስቃይ ሳይደርስበት ወይም ሳይደርስባት አገሪቱን በጊዜ ለቀው እንዲወጡ ለማስቻል የኢፌዴሪ መንግስት በፍፁም የሃላፊነት ስሜት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን እና ክቡር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ከሳዑዲ መሪዎች ጋር በተደጋጋሚ በመገናኘት ለዜጎቻችን አመች ሁኔታን ለመፍጠር ሌት ተቀን ደክመዋል። አሁንም ከመድከም አላረፉም። በርካታ ዲፕሎማቶቻችን ትላልቅ አገራዊ ጉዳዮችን ለጊዜው አቁመው ከኤምባሲና ቆንሱላ ውጭ ለኑሮ በማያመቹ በረሃማ ሥፍራዎች ላይ ሆነው ወገኖቻችንን በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማስውጣት እያገለገሉ ይገኛሉ። የኢፌዴሪ መንግሥት አንድም ዜጋ ቢሆን ጉዳት እንዲደርስበት አይፈልግምና!

በመሆኑም በሳዑዲ ዓረቢያ ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራችሁ አገሪቱን ለቃችሁ እንድትወጡ የጊዜ ገደብ የተሰጣችሁ ውድ ወገኖቻችን ሁሉ፦ እጇን ዘርግታ የምትቀበል ውብ አገር፣ ለህዝብ የወገነ መንግሥት እና ደግ ህዝብ ስላላችሁ በተሰጣችሁ ጊዜና መብት ተጠቅማችሁ ወደአገራችሁ እንድትመለሱ የኢፌዴሪ መንግሥት አሁንም አበክሮ ያስገነዝባል፡፡ አገራችን ለሥራ ፈጣሪዎች እና ለታታሪ ሠራተኞች ምቹ አገር መሆኗን እንደምታስመሰክሩም በፅኑ ያምናል።

ውድ ወላጆች፦ ልጆቻችሁ ወደ አገራቸው እንዲመለሱላችሁ ባላችሁ ግንኙነት ሁሉ ግፊት ማድረግ ለነገ የማይባል ሥራችሁ ሊሆን ይገባል፡፡

የኃይማኖት አባቶች፣ እንዲሁም በሳዑዲ ዓረቢያ በግል እና በቡድን እየተንቀሳቀሳችሁ ያላችሁ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እያከናወናችሁት ያለውን አኩሪ ተግባር አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ፣ መላው ሕብረተሰባችንም ከመንግስት ጎን በመቆም በቀሩት ጥቂት ቀናት ውስጥ ወገኖቻችንን ለማስመለስ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ የኢፌዴሪ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በዚህ አጋጣሚ የኢፌዴሪ መንግሥት ላቀረበው ጥሪ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ወደ አገራችን ለተመለሱ ወገኖቻችን እንዲሁም እነሱን በመቀስቀስ እና በማስተባበር በተለያየ መልኩ ድጋፍ እያደረጉ ላሉ ግለሰቦች እና ድርጅቶች መንግሥት ምስጋናውን ያቀርባል።  የጊዜ ገደቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ባለው ጊዜ ሁሉ አንድም ዜጋችን ቢሆን ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስበት ወይም እንዳይደርስባት መንግሥት እያካሄደው ያለውን ብርቱ ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በዚህ አጋጣሚ ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል፡፡ 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 2/2009 በሳዑዲ ዓረቢያ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች የምህረት አዋጁ የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ በፍጥነት እንዲወጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አሳሰበ።

የጋራ ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ መንግስት በሳዑዲ ዓረቢያ ህጋዊ መኖሪያ የሌላቸው ዜጎችን ለመመለስ እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታውቋል።

በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አደጋና እንግልት ሳይደርስባቸው የምህረት አዋጁ የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ ወደ አገራቸው እንዲመለሱም ጠይቋል።

የምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎችም መንግስት ዜጎቹን ወደ አገር ቤት ለመመለስ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ እንደሆነ ገልፀዋል።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሰሎሞን ታፈሰ ፓርቲያቸው ኢትዮጵያውያኑ የሳዑዲ መንግስት የሰጠውን የጊዜ ገደብ ተጠቅመው እንዲወጡ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ የሳዑዲ መንግስት ውሳኔውን ሊቀይር ይችላል በሚል የተዘናጉ ዜጎች በፍጥነት እንዲወጡ መንግስት ይበልጥ መስራት እንዳለበት ነው የተናገሩት።

የመኢብን ፕሬዚዳንት አቶ መሳፍንት ሽፈራው በበኩላቸው ዜጎቹ በደላሎች የተሳሳተ መረጃ ሳይታለሉ የምህረት ጊዜ ገደቡ ሳያበቃ እንዲወጡ አሳስበዋል።

ፓርቲያቸው መንግስት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመደገፍ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የኢዴፓ ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ አዳነ ታደሰም መንግስት ዜጎችን ለመመለስ እያደረገ ካለው ጥረት በተጨማሪ ተመላሽ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚያገኙበትን ሁኔታ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት መፍጠር አለበት ነው ያሉት።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሳዑዲ ዓረቢያ በህገወጥ መንገድ የሚኖሩ ዜጎችን በአገራቸው ከነችግሩ ሰርተው መለወጥ የሚችሉበት ዕድል መኖሩን እንዲያውቁ መስራት አለበትም ነው ያሉት።

የኢፍዴኃግ ሊቀመንበር አቶ ገረሱ ገሣ በበኩላቸው በሳዑዲ የሚገኙ ዜጎች በቀሩት ጥቂት ቀናት እንዲመለሱ ከመንግስት ጋር አብረን እንሰራለን ብለዋል።

"የክልል መንግስታት ለተመላሾቹ ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለባቸው" ያሉት አቶ ገረሱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሳዑዲ የሚገኙ ዜጎች አደጋ ሳይደርስባቸው እንዲወጡ ጥረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኢህአዴግ ተወካይ አቶ ረዳኢ ሐለፎም መንግስት በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ዜጎች ምንም ችግር ሳይደርስባቸው እንዲወጡ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።

ተመላሾች ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱን ገልፀው የተሰጠው የምህረት ጊዜ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ቢቀሩም የተመለሱት ቁጥር አነስተኛ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

በሳዑዲ ዓረቢያ በሚገኙ ደላሎችና የራሳቸውን የፖለቲካ ትርፍ በሚፈልጉ አካላት ሳይደናገሩ ወደ አገራቸው እንዲመለሱም አሳስበዋል።

መንግስት ህገወጥ ደላሎችን እንዲቀጣና ህገወጥ መተላለፊያዎች ላይም ቁጥጥር እንዲያደርግ የጋራ ምክር ቤቱ አሳስቧል።

ምክር ቤቱ ባካሄደው ስብሰባ በሶማሌ ክልል በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ያደረገውን የመስክ ጉብኝት ሪፖርት ተወያይቶ አፅድቋል።

በቀረበው ሪፖርት ክልሉ ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር ባደረገው ጥረት ድርቁ የከፋ አደጋ ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉ ተገልጿል።

ድርቁን ለመከላከል የተደረገው ጥረት በአካባቢው ድርቅን በዘላቂነት መቋቋም የሚያስችል ሁኔታ በሚፈጥር መንገድ እየተከናወነ መሆኑንም ምክር ቤቱ አረጋግጧል።

በክልሉ የከርሰ ምድር ውሃ በማውጣት ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ያተተው ሪፖርቱ የተፈጠረው ዘላቂ ሠላምም የድርቅ አደጋውን ለመከላከል አስተዋፅኦ ማበርከቱን አብራርቷል።

በክልሉ ድርቅን በዘላቂነት መቋቋም የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የፌደራል መንግስትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲቀጥልም ጠይቋል።

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ ሰኔ2/2009 የእፅዋዕት ጥበቃ ስራን ማጠናከር ምርታማነት ለማሳደግ  ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚነስቴር ገለጸ፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአለም የምግብና እርሻ ድርጅት(ፋኦ ) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው አገር አቀፍ የእፅዋት ጥበቃ ንቅናቄ መድረክ በሃዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የእፅዋዕት ጥበቃ  የነፍሳት፣ የበሽታ አምጭ ተዋሲያን፣ የአደገኛ ወራሪ አረሞችና ፀረ ሰብል ወፎች ጉዳት መከላከልን መሰረት ያደረገ መሆኑን  የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር ዴኤታው  አቶ ተስፋዬ መንግስቴ  ገልጸዋል፡፡

ችግሩ አለም አቀፍ ይዘት ያለው በመሆኑም ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሌሎችም አገራት አለም አቀፍ የእፅዋእት ጥበቃ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

" በስምምነቱም ማንኛውም በየብስ  ወይም በውሃ አካላት የሚኖሩ ፅዋዕትን እንዲያካትት በመደረጉ የስምምነቱ አካል ሆነው የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው "ብለዋል፡፡ 

ተባዮቹ ድንበር ዘለል ጥቃት ስለሚያደርሱ ከምስራቅ አፍሪካ ንዑስ ክፍለ ሃገራት ጋር የተቀናጀ ቀጠናዊ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የእፅዋዕት ጥበቃ ስራ ማጠናከር ምርታማነት ለማሳደግና የምርት ጥራት ለማረጋገጥ  ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው  ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

መድረኩም የእስካሁኑን የእፅዋእት ጥበቃ ስራዎች   በምን ደረጃ እንደሚገኝ ፣ ስኬቶችና ተግዳሮቶችን በዝርዝር በመለየት ለቀጣይ ስራ ዝግጁ ለማድረግ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የደቡብ ህዝቦች ከልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው የእፅዋዕት ጥበቃን ለማጠናከር የንቅናቄው መድረኩ   ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ አገር አቀፍ የእጽዋት ጥበቃ ንቅናቄ ሰነድ፣የተባይ ቁጥጥር መከላከል ስትራቴጂን ጨምሮ ዘጠኝ የሚሆኑ  የተለያዩ ጹሁፎች  ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ተመልክቷል፡፡

ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚቆየው የንቅናቄው መድረክ ከሃገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የግብርና ምርምር ማዕከላት ተመራማሪዎችና  ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡  

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ  ሰኔ2/2009 ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ላብራቶሪ አክሪዲቴሽን ትብብር ሙሉ አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ።

 ሰባተኛው ዓለም አቀፉ የአክሪዲቴሽን ቀን ''የአክሪዲቴሽን ለኮንስትራክሽንና ለተገነባ አካባቢ እምነት ይሰጣል'' በሚል መሪ ቃል ዛሬ ተከብሯል።

 በብሄራዊ አክሪዲቴሽን ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት የተከበረው ቀኑ አክሪዲቴሽን ለኮንስትራክሽን ባለው አስተዋጽኦ ዙሪያ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

 ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2011 የትብብሩ ዕጩ አባል፣ በ2013 ተባባሪ አባል ስትሆን በ2014 ደግሞ የትብብሩ ሙሉ አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርባለች።

 የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ፍሰሐ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ጽህፈት ቤቱ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት፣ የሰው ኃይልና ዕውቅና የሰጣቸው ተቋማት በትብብሩ የተቋቋመ ቡድን ሲገመግም ቆይቷል።

 በዚህም ኢትዮጵያ የትብብሩ አባል ለመሆን ያቀረብችው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ተናግረዋል። 

 አገሪቱ ሙሉ አባል መሆኗ የአገር ውስጥ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማስቻል ከወጪ ንግድ የተሻለ ገቢ እንዲገኝ በማድረግ ረገድ የላቀ ሚና ይጫወታል ብለዋል። 

 እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንፎርሜሽን እቅድ ዓመታት 46 የላብራቶሪ ወሰኖች የእውቅና አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን በቀጣይም ለ150 ወሰኖች ዕውቅና ለመስጠት ታቅዷል።

 የተቋማት የአክሪዲቴሽን ፍላጎት ማነስ፣ በአገሪቱ ብቃት ያለው የጥራት ደረጃ መለኪያ አገልግሎት አለመኖር፣ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ማነስና የግንዛቤ ክፍተት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች መሆናቸውን አብራርተዋል። 

 ''ትልልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ጥራቱን ማስጠበቅ ወሳኝ'' ነው ያሉት ደግሞ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ናቸው። 

 የአገሪቱን ህዳሴ ለማረጋገጥ መንግስት በመንገድ፣ ባቡር፣ ድልድይና ህንጻዎችን የመሳሰሉ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አንስተዋል።

 ''እነዚህ ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን የጠበቁና ዘመናትን የሚሻገሩ ለማድረግ ትልቅ የቤት ስራ አለብን'' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ጽህፈት ቤቱም ለግንባታ ጥራት መረጋገጥ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ አመልክተዋል። 

 መንግስትም የጥራት ጉዳይ ትልቅ አገራዊ አጀንዳ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸው የብሄራዊ ጥራት ፎረምና አክሪዲቴሽን ካውንስል መቋቋማቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

 በዕለቱ ለኢትዮጵያ ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በላብራቶሪ ኬሚስትሪ ፍተሻ ዘርፍ እንዲሁም ለአዲስ አበባ ህብረተሰብ ጤና ምርምር ድንገተኛ ቁጥጥር ዋና የሥራ ሂደት ላብራቶሪ ወሰን ማስፋት የአክሪዲቴሽን ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

 

 

 

ደሴ ሰኔ 2/2009 ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ በእንስሳት ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን ለመከላከል ክትባት እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ህክምና ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር ያለለት ወርቁ ለኢዜአ እንደገለፁት ክትባቱ በመሰጠት ላይ ያለው 55 ሺህ ለሚሆኑ በጎች ፣ ፍየሎችና የቀንድ ከብቶች ነው።

ከግንቦት 15 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በመሰጠት ላይ ሲሆን እስካሁንም 10 ሺህ እንስሳት ተከትበዋል።

ክትባቱ ደሴ ከተማ አስተዳደርና ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ 12 ቀበሌዎች ከፍለው ማሳከም የማይችሉ አርሶ አደሮችን ለማገዝ በነፃ የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ ዶክተር ያለለት ገለፃ ክትባቱ 40 በሚሆኑ የዩኒቨርስቲው መምህራን፣ የ5ኛ ዓመት የእንስሳት ጤና ተመራቂ ተማሪዎችና በወረዳ የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች አማካኝነት እስከ ሰኔ 20 ቀን 2009 እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡

ለክትባቱ 100 ሺህ ብር ወጭ ተደርጓል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ እንስሳት ኃብት ልማትና ጤና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጀማል መሐመድ በበኩላቸው የጎሮርስና አባጎርባ በሽታዎች በአካባቢው እንስሳት ላይ ጉዳት በማሰከተል የሚታወቁ ናቸው ።

በዩኒቨርሲቲው እየተሰጠ ያለው ክትባት ከዚህ ቀደም የበሽታውን መከላከያ መድሀኒት ከደብረዘይት ለማስመጣት ይወጣ የነበረውን ወጭ ማስቀረቱን ተናግረዋል  ።

በደሴ ከተማ አስተዳደር 012 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጀማል አበጋዝ በአካባቢያቸው እንሰሳት በምች በሽታ ሲያዙ ከፍለው የማስከተብ አቅም ስለሌላቸው ለሞት ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል።

እሳቸውም የችግሩ ሰለባ እንደነበሩ ያስታወሱት አርሶ አደሩ ክትባቱን በነፃ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል ።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 2/2009 ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ተመጣጣኝ ልማት ከማረጋገጥ አንፃር የፌደራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የ2009 በጀት ዓመት የአሥር ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ተመልክቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባዬ ገዛኸኝ ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ተመጣጣኝ ልማት ከማረጋገጥ አንፃር አርብቶ አደሩን በመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም የተሰሩ ሥራዎች ዝቅተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ነባር የመንደር ማሰባሰብ ማዕከላትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥና ተገቢውን የመሠረተ ልማት አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግ አንፃር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ግጭት መከላከልና አፈታትን በሚመለከት የሠላም ኮሚቴዎች፣ ፎረሞችና ክበባትን በማጠናከር ረገድ ጥሩ ጅምሮች ቢኖሩም ተዳፍነው የቆዩ ግጭቶችን በዘላቂነት ከመፍታት አኳያ ትኩረት ሊሠጥ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

በሴቶችና ወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ በጀት ከመለየት፣ ከመመደብና ሥልጠናዎችን ከመስጠት ባለፈ ወጣቶቹን ወደ ሥራ የማስገባት ስራውም ትኩረት ያሻዋል ነው የተባለው።

ቋሚ ኮሚቴው ሚኒስቴሩ በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ክልሎች በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን አቅም ለመገንባት የሠጠው ሥልጠና ካለው አገራዊ ፋይዳ አንፃር ሊበረታታ እንደሚገባ አመልክቷል።

የክልል መንግስታትን ግንኙነት ከማጠናከር፤ አዳዲስ የብድርና ቁጠባ ማህበራትን ከሟቋቋምና ከማጠናከር አኳያ ያለውን አፈፃፀም ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ አይቶታል።

በተቋሙ የለውጥ ሠራዊት በመገንባት ረገድ የተሠራው ሥራና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገው ጥረትም በጠንካራ ጎን ተነስቷል።

የፌደራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ካሳ ተክለብርሃን በየደረጃው በሚገኘው አመራር መንደር ማሰባሰብን የሞት ሽረት ጉዳይ አድርጎ የመያዝ ጉድለት መኖሩን ተናግረዋል።

የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ሥርዓቱ እንደ አገር ባለመጠናከሩ ግጭትን አስቀድሞ የመከላከል ተልዕኮው ውጤታማ አለመሆን ተግዳሮት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

እንደ ድክመት ለተነሱ ችግሮች ሚኒስቴሩ የተሠጠውን ተልዕኮ ለማስፈፀም አብዛኞቹ ሥራዎች ተጀምረው በሌሎች መሥሪያ ቤቶች የሚጠናቀቁ በመሆናቸው ሥራዎችን በታቀደው ልክ ለማከናወን ችግር እንደሆነ ነው ያስረዱት።

ሚኒስትሩ ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ የጠቀሳቸው ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና በድክመት በተነሱ ጉዳዮች ላይ መስሪያ ቤታቸው ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ እንደሚሰራም በአፅንኦት ገልፀዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ደሴ ሰኔ2/2009 በአማራ ክልል አንዳንድ ዞኖች በሰብል ላይ የተከሰተውን ተምች ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ባለሙያው  አርሶ አደሩ በማስተባበር  በቅንጅት  መስራት እንዳለበት ተመለከተ፡፡

በምስራቅ አማራ ለሚገኙ የሰብል፣የፍራፍሬና የእፀዋት ልማት ጥበቃ ባለሙያዎች በተምች ምንነትና  መከላከል ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ በኮምቦልቻ  ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መልኬ ታደሰ  እንዳሉት ተባዩ በምዕራብ አማራ  አዊ፣ምዕራብ ጎጃም፣ምስራቅ ጎጃምና ደቡብ ጎንደር  ተከስቷል፡፡

በዞኖቹ ተምቹ   ከ14 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ የሰብል ማሳ ላይ መከሰቱን ጠቁመው  ከዚህ ውስጥ አራት ሺህ የሚሆነውን በኬሚካል  ርጭትና በባህላዊ መንገድ መከላከል መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

አቶ መልኬ  እንዳሉት ተምቹ  እንደ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላና ሌሎችንም ሰብሎች የሚያጠቃ ነው፡፡

ከኬሚካል ርጭቱ በተጓዳኝ  በባህላዊ መንገድ  ለማጥፋት  በሚደረገው ጥረት በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ከአርሶ አደሮች ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡

አርሶ አደሩም በየዕለቱ  ሰብሉን እያሰሰ ለባለሙያው መጠቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ጥበቃ ባለሙያ አቶ አበበ አናጋው በበኩላቸው ተባዩ በሁሉም አከባቢዎች የመከሰት ዕድል እንዳለው ጠቅሰው " በተለይ እርጥበት አዘል የሆኑት ቆላማ ቦታዎች ይበልጥ ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉ"ብለዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በዋግ ኽምራ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ደሳለኝ አበበ  በመድረኩ ስለተባዩ ምንነት ፣ ስለሚያከተለው ጉዳትና መከላከል ቀድሞ ከነበራቸው  የተሻለ ግንዛቤ መጨበጣቸውን ተናግረዋል፡፡

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ሰኔ 2/2009 የአርሶ አደሩ በአነስተኛ ማሳ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ገበያ ተኮር ምርቶችን የማምረት አቅም እያደገ መምጣቱን የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ገለጸ።

የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር በበኩሉ እስከአሁን በነበረው ሁኔታ ሰፊው ትኩረት በምግብ እህል ራስን መቻል በመሆኑ ገበያ ተኮር ምርቶች ላይ በበቂ ሁኔታ ተሰርቷል ብሎ መገምገም አይቻልም ብሏል።

ከዓለም አቀፍ ገበያ ተኮር ምርቶች መካከል ሰሊጥ፣ ቦሎቄና ከቅባት እህሎች እንደ ኑግ፣ ተልባ፣ ጥጥ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እና ሌሎችም ይገኙበታል።

በኮርፖሬሽኑ የዘር ምርት ማዘጋጀት፣ ማሰራጨትና ማከፋፈል መምሪያ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘነበ ወልደሥላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት አርሶ አደሩ አሁን ባለው ሁኔታ ዓለም አቀፍ ገበያ ተኮር የሆኑ ምርቶችን የማምረት አቅሙና ፍላጎቱ እየጨመረ ነው።

እሳቸው እንደሚሉት ከ10 ዓመት በፊት በዓመት ከ150 ሺህ ኩንታል ያልበለጠ ገበያ ተኮር ምርቶች ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ይሰራጩ የነበረ ሲሆን አሁን ግን፤ ከ380 ሺህ ኩንታል በላይ መድረሱን ነው የሚገለጹት።

"ይህም የአርሶ አደሩ ገበያ ተኮር ምርቶች የሚያስገኙትን ጥቅም በመረዳቱ በስፋት መዝራት የቻለበት ሁኔታ መኖሩን ያመለክታል" ነው ያሉት።

አቶ ዘነበ እንደገለጹት፤ አርሶ አደሩ ገበያ ተኮር ምርቶችን አምርቶ መጠቀም እንደሚችል መካሪ የማያስፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

ይሁን እንጂ ዓለም አቀፍ ገበያ ጭማሪ ሲያሳይ ለብዛት ሲባል በንጹሁ ምርት ላይ ሌሎች ጥራቱን የሚቀንሱ ነገሮችን ስለሚጨምር የጥራት ችግር በተወሰነ ደረጃ ይስተዋላል በማለት ጠቁመዋል።

ችግሩን ለመቀነስም  አርሶ አደሩ ከብዛት ሳይሆን ከጥራት መጠቀም እንደሚችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ማከናወን ይገባል ነው ያሉት።

"የአጠቃቀም ችግር እንጂ ምርቱን እያመረቱት ነው፤ እኛ እንደ ምርጥ ዘር አከፋፋይነታችን በየዓመቱ ያለውን የአርሶ አደሩን ፍላጎት  እናውቃለን" ነው ያሉት።

የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር በበኩሉ እስካሁን ያለው የአመራረት ዘዴ በምግብ ራስን መቻል ላይ ያተኮር ስለነበር ገበያ ተኮር ምርቶች ላይ መሰራት ያለበትን ያህል አልተሰራም ነው ያለው።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለምአየሁ ብርሃኑ እንደሚሉት፤ እስካሁን ሲሰራ የነበረው አርሶ አደሮች ከእጅ ወደአፍ ከሆነ አስተራረስ እንዲላቀቁና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲችሉ የኤክስቴንሽን አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ ስራ ነበር።

አሁን በምግብ እህል ራሳችንን ስለቻልን የኤክስቴንሽን ስትራቴጂውን በመገምገም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ምርቶችን በስፋት ለማምረት ውይይቶች መካሄዳቸውን ነው ያስረዱት።

"ይህ ሲባል ግን አልተሰራም ማለት አይደለም ነገር ግን በጥራትም፣ በመጠንም በዚህ መልኩ ተሰርቷል ብሎ ለመገምገም አያስደፍርም" ሲሉ ነው የተናገሩት።

ምርትና ምርታማነት አድጓል ማለት ገበያ ተኮር የሆኑ ምርቶችም በዛው ልክ አድገዋል ማለት አይደለም ያሉት አቶ ዓለምአየሁ ወደፊት በትኩረት ለመስራት እንደታሰበ በተለያዩ ክልሎች የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።

አርሶ አደሩ ምርቶችን እያመረተ ነው፤ ነገርግን ከመንግስት በኩልም እስካሁን ትኩረቱ በምግብ ራስን መቻል ላይ ስለነበር ለምርቶቹ ጥራት እና መጠን ትኩረት ተሰጥቷል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም ነው ያሉት።

በቀጣይ ለምርቶቹ ትኩረት በመስጠት አርሶ አደሩም ተጠቅሞ ከዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ  ሰኔ2/2009 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሁለት አገራት ተወካዮች ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያዩ።

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጀመሪያው ውይይታቸው ከደቡብ ሱዳን የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ማዪካ ዴንግ ጋር ነው የተወያዩት።

 ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት የተላከላቸውን መልዕክትም ተቀብለዋል።

 በመቀጠልም ከሳዑዲ ዓረቢያ የንጉሳዊ ፍርድ ቤት አማካሪ አህመድ ኣል ክሃተብ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል። 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሰኔ 2/2009 ልመናን መቀነስ ይቻል ዘንድ ኅብረተሰቡ ምጽዋት ሊሰጣቸው የሚገባቸውን በአግባቡ መለየት እንዳለበት ተጠቆመ።

ከአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ለልመና መስፋፋት ትልቁ ምክንያት ኅብረተሰቡ የሚረዳቸውን ሳይለይ መመፅወቱ ነው።

ልመና በአዲስ አበባ በየቀኑ የተለየ ትዕይንት፣ ስልትና ዘዴዎችን እየተከተለ፤ ማሳፈሩ ቀርቶ እንደ ሕጋዊ ሥራ እየተቆጠረ ነው።

በርካታ ቁጥር ያላቸው አረጋውያን፣ ጎልማሶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ህፃናት ህይወታቸውን በልመና ይመራሉ፤ መጠጊያ ያደረጉት ደግሞ የቤተ እምነቶችን ደጃፍ ነው።

በአዲስ አበባ ቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ዙሪያ እየተበራከቱ የሚገኙት ተመፅዋቾች ለዚህ ማሳያ ይሆናሉ።

የደብሩ አስተዳዳሪ መምህር መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ፍቅረ ማርያም ምህረቱ፤ ጉዳዩ ለቤተክርስቲያኒቱም ያስቸገረና ስለ ሥራ ካለው የቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ ጋር የሚጋጭ ነው ይላሉ።

መምህር መልአከ ሰላም እንዳሉት ምጽዋት ለሁሉም ሰው ይሰጥ ዘንድ የሚፈቅድ የቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ የለም፤ ሰው ሁሉ ሠርቶ እንዲበላ ትምህርት ቢሰጥም በቤተክርስቲያኗ ዙሪያ በልመና ተግባር የተሰማሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

አሳማኝ በሆነ ምክንያት ወደ ልመና ከገቡት በቀር ኃብትና ንብረት እያላቸው ጥሪት ለማፍራት ለልመና የሚወጡና ለእርሻ ወደ ቀድሞ ቦታቸው የሚመለሱ፤ ቤታቸውን ዘግተው የመጡ ሙሉ የቤተሰብ አባላት እንዳሉም ይነገራል።

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዲቪዢን ኃላፊ ኮማንደር በየነ ዱሬሳ እንዳሉት ቀጨኔ አካባቢ በልመና የተሰማሩት አብዛኛዎቹ ለምኖ አዳሪዎች የሚያገኙት ገንዘብ ብዙ ድካም የማይጠይቅ በመሆኑ ወደ ቀዬአቸው መመለስ አይፈልጉም።

በየቀኑ ለልመና ወደ መዲናዋ ከሚገቡት በተጨማሪ ሕጻናት ልጆቻቸውን መንገድ ላይ አስተኝተው የሚለምኑ እናቶችን መመልከት አንዱ የከተማዋን ገጽታ እየቀየረ የሚገኝ ጉዳይ ነው።

"ኅብረተሰቡ መንገድ ላይ ለሚለምኑት ሁሉ ገንዘብ መስጠቱ ልመና እንዲስፋፋና ሌሎችም ወደዚያው እንዲገቡ እያደረገ ነው" የሚሉት የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማኅበራዊ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ዓለሙ አዳነ ናቸው።

ለምኖ አዳሪዎች ከመጡበት የገጠር አካባቢ የእርሻ መሬት ያላቸውና ሃይማኖታዊ የንግስ በዓላትን ጠብቀው የሚዘዋወሩ በመሆናቸው ለይቶ ለማወቅና ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ለመመለስ አስቸጋሪ እንደሆነም ተናግረዋል።

ኃላፊው ኅብረተሰቡ ምጽዋት ለሚጠይቁ ሁሉ ከመስጠት ባለፈ ሰርተው እንዲለወጡና በወዛቸው እንዲያድሩ በመንገርና ምክር በመለገስ ዘላቂ የሆነ እርዳታ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን