×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Thursday, 08 June 2017

ሃዋሳ ሰኔ 1/2009 ህብረ ብሄራዊነትና ብዝሃ ኃይማኖት ባላት ኢትዮጵያ የመቻቻልና የመከባበር እሴቶችን ማዳበር እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር ከደቡብ ህዝቦች ክልል ለተውጣጡ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መሪዎች፣ ለሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀት አመራሮች በሃዋሳ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡

የስልጠናው ተካፋዮች ለኢዜአ እንደገለጹት በቆይታቸው ያገኙትን ክህሎት ተጠቅመው በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ በመፍጠር የበኩላቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል፡፡

የጉራጌ ዞን የኃይማኖት ጉባኤ ሰብሳቢ መላከ ሰላም ካሱ መኮንን እንዳሉት የኃይማኖት አክራሪነትና ፅንፈኝነት የወቅቱ አደጋዎች ናቸው፡፡

ይህንን ለመከላከል ህብረ ብሄራዊነትና ብዝሃ ኃይማኖት ያላት ኢትዮጵያ ውስጥ የመቻቻልና የመከባበር እሴት ይበልጥ ሊዳብር ይገባል፡፡

"የኃይማኖት አባቶች አገራዊና ሃይማኖታዊ ግዴታዎች አለባቸው "  ያሉት ሰብሳቢው ሀገሪቱን የሚረከቡ ወጣቶች የጥፋት ሃይል ሰለባ እንዳይሆኑ በመልካም ስነምግባርና  ግብረገብ ትምህርት ለማነፅ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ነው ያመለከቱት፡፡

ያገኙትን ግንዛቤ ተጠቅመው የኃይማኖት አክራሪነትና ፅንፈኝነት ስለሚያስከትለው ጉዳትና መከላከያው ዘዴ እንደሚያስተምሩም ገልፀዋል፡፡

የኃይማኖት አክራሪነት እንዴት እንደሚፈጠርና ስለሚያስከትለው ቀውስ ከስልጠናው ግንዛቤ መጨበጣቸውን የተናገሩት ደግሞ ከሃዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ የሴቶችን አደረጃጀት ወክለው የመጡት ወይዘሮ ዘነበች ስልዶ ናቸው፡፡ 

የቀሰሙትን እውቀት  በከተማቸው ለሚገኘው ሴቶች አደረጃጀት እንደሚያስተምሩና በጋራ ችግሩን የመታገል ሃላፊነት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት፡፡

የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር የኃይማኖትና እምነት ጉዳዮች የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ወንድማገኝ በለጠ  በበኩላቸው አንድነትን፣ መቻቻልንና  የመከባበር ባህልን  በማጠናከር  አክራሪነትና ፅንፈኝነትን መከላከል የሚያስችል ግንዛቤ ከስልጠናው ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከኃይማኖት ጋር ተያይዞ በየአካባቢው በማወቅና ባለማወቅ የሚፈጠሩ ስህተቶች ለአክራሪነትና ፅንፈኝነት በር የሚከፍቱ በመሆናቸው ለመከላከል የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ፀሐፊ ህሉፍ ወልደ ስላሴ የኃይማኖት አክራሪነትና ፅንፈኝነት አደጋው የከፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስልጠናውን የወሰዱ መሪዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች ሃላፊነት ወስደው ይህን ችግር ለማስወገድ  መስራት እንደሚገባቸውም ጠቁመው ስልጠናውን  እስከታችኛው መዋቅር በማውረድ ለሌሎችም ማካፈል እንደሚጠበቅባቸውም ጠቅሰዋል፡፡

ስልጠናው በህብረ ብሄራዊነትና ብዝሃነት አያያዝ፣ በሴኩላሪዝም ፅንሰ ሃሳብና ኃይማኖትን ሽፋን ያደረገ አክራሪነትና ፅንፈኝነት መታገያ ስልቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ሰኔ 1/2009 ፌዴራሊዝም የሀገሪቱ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር በቋንቋቸው እንዲጠቀሙ ማስቻሉን በመቀሌ ዩኒቨርስቲ  የህግና ስነ-መንግስት ኮሌጅ ምሁራን ገለጹ፡፡

በኮሌጁ የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር ትምህርት ክፍል ምሁራን ለኢዜአ  እንዳሉት ፌዴራሊዝም የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብታቸውን ያስከበረ ስርዓት ነው፡፡

ከምሁራኑ መካከል አቶ በላይ አብርሃ በሰጡት አስተያየት  " ለብዙ ዘመናት የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የነበረው ራስን በራስ የማስተዳደር፣ በቋንቋ የመናገርና የመዳኘት መብት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችለው የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ነው "ብለዋል።

የነበረው አሃዳዊ ስርዓት ያልመለሳቸው በቋንቋ የመጠቀምና የማንነት መገለጫ የሆኑት ባህልና ወግ የማጎልበት መብቶች የተመለሰው በዚሁ ስርዓት ነው እንደ ምሁሩ ገለጻ፡፡

"ክልሎች ሲካለሉ ማንነት፣ የአሰፋፈር ሁኔታ፣ የህዝቡ ፍላጎትና ቋንቋን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ለዘመናት የቆዩትን የህዝቦች ጥያቄዎችን በፌዴራሊዝም ስርዓቱ  ምላሽ እንዲያገኙ ተችሏል" ያሉት ደግሞ ሌላው የኮሌጁ ምሁር ገብሩ ገብረህይወት ናቸው ።

የፌዴራሊዝም ስርዓት በማዕከላዊ መንግስት ብቻ የነበረውን የተማከለ ስልጣን በማስቀረት የፌዴራልና የክልል መንግስታት ተቀናጅተው ለአንድ ህዝብ በጋራ እንዲያስተዳድሩ የሚደረግበት ስርዓት እንደሆነ ተናግረዋል።

"ብዝሃነት በሚገለፅበት ሀገር የፌዴራሊዝም ስርዓት እጅግ ተመራጭ ነው" ያሉት ምሁሩ  በሀገሪቱ የነበረው አሃዳዊ ስርዓት ለዘመናት የቆዩትን የህዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ ባለመመለሱ ጦርነት  ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ምሁሩ እንዳሉት በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩት ግጭቶች ከፌዴራሊዝምና ከአከላለል ጋር በተያያዘ መልኩ የሚከሰቱ ሳይሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መገለጫ ናቸው፡፡

በቀድሞ ስርዓቶች በየደረጃው ይመደቡ የነበሩ አስተዳዳሪዎች ከማዕከል ይላኩ እንደነበር ጠቁመው ይህም የህዝቡን ባህልና ቋንቋ  ስለማያውቁ በአግባቡ ማስተዳደር እንዳልቻሉ ጠቁመዋል፡፡

በሀገሪቱ ለዘመናት በነበረው አሃዳዊ ስርዓት ምክንያት የህዝቡ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መመለስ ሳይችል መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ አቶ ብርሃነ ግደይ ናቸው።

እንደ ምሁሩ ገላጻ ፌዴራሊዝም ያስገኘው ትልቁ ሃብት ዜጎች በማንነታቸው ኮርተው ሃሳባቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲናገሩና እንዲዳኙ አስችሏል።

በሀገሪቱ  አስተማማኝ ሰላም  እንዲሰፍንና ዲሞክራሲ እንዲጎለብት ፣ህዝቦች አካባቢያቸውን የማልማትና የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አግዟል ።

መንግስት የፌዴራሊዝም ስርዓት አስፈላጊነትና ያስገኘው ጠቀሜታ እንዲሁም አንድነት ለዘላቂ ልማት ያለውን ፋይዳ ትምህርት ቤቶችና ሌሎችንም መድረኮች በመጠቀም  ግንዛቤ የመፍጠሩ ተግባር ላይ በስፋት መስራት እንዳለበት ምሁራኑ ጠቁመዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ባህር ዳር ሰኔ 1/2009 በአማራ ክልል 12 ወረዳዎች የተከሰተውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ የመከላከል ስራ እየተካሂደ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተክለሃይማኖት ገብረ ህይዎት እንዳሉት በሽታው  በበጀት ዓመቱ የአሁኑን ጨምሮ ለሶስተኛ ጊዜ ተከስቷል፡፡

ካለፈው ወር አጋማሽ ጀምሮ በደቡብ ጎንደር፣በሰሜን ጎንደርና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች 12 ወረዳዎች ተከስቶ 252 ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል፡፡

ለመከላከል በተከናወነው ስራም 205 ሰዎች የህክምና እርዳታ ተደርጎላቸው ጤንነታቸው መመለሱን ያመለከቱት አስተባባሪው 47 ህሙማን ደግሞ በህክምና ተቋም ተኝተው እየታከሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ በበሽታው የሚያዙ  ሰዎች ጊዜያዊና ቋሚ የህክምና ጣቢያዎችን በመቋቋምና ባለሙያዎችን በመመደብ ተገቢውን የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው።

በሽታው በንጽህና ጉድለት የሚመጣ መሆኑን ጠቁመው  ለመከላከልም በክልል ደረጃ የበሽታ ቅኝት፣የህክምናና ክብካቤ፣ የትምህርታዊ የቅስቀሳና የውሃ ንፅህና ኮሚቴዎች ተዋቅረው እየሰሩ ናቸው፡፡

ህበረተሰቡ የግልና የአካባቢ ንፅህናን በመጠበቅ ፣ ጎመንና መሰል አትክልቶችን አብስሎ በመመገብ በሽታውን መከላከል እንዳለበት፣ በበሽታው የተያዘ ሰው ሲያጋጥምም በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋም በማድረስ መከላከል እንደሚገባም አስተባባሪው  አሳስበዋል።

የአተት በሽታ በክልሉ ባለፈው የክረምት ወቅትና የካቲት ወር በተለያዩ ቦታዎች ተከስቶ በተደረገው የመከላከል ስራ  መግታት እንደተቻለም  ተመልክቷል፡፡ 

 

Published in ማህበራዊ

አዳማ ሰኔ1/2009 በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘርፉን በጥናትና ምርምር ሊደግፉ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስቴር አስገነዘበ።

“በሳይንስና ቴክኖሎጂ ችግር ፈች የምርምር ሥራዎች  ዘላቂ ልማትን እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ዛሬ በአዳማ በአባገዳ አዳራሽ ተጀምሯል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተሾመ ለማ ኮንፍረንሱን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማሩ ስራ ጎን ለጎን ለጥናትና ለምርምር ስራ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል።

በተለይ በሀገሪቱ  እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን ልማትና ዕድገት በጥናትና ምርምር በመደገፍ ዘላቂነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በግብርና ዘርፍ ድርቅን የሚቋቋምና ምርታማነቱ ከፍተኛ የሆነ የሰብል ዝሪያ በምርምር በማፍለቅ ረገድ በተቋማቱ መሻሻሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል ።

ይሁንና በኢንዱስትሪና በማኑፋክቸሪንግ መስክ አሁን ያሉትን ጅምር ሥራዎች አጠናክሮ ሊያስቀጥሉ የሚችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠቅሰዋል ።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ በበኩላቸው "ኮንፈረንሱ አገሪቱ ለጀመረችው ልማትና ፈጣን ዕድገት ቀጣይነት ግብዓት የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ለመለየትና ወደ ህብረተሰቡ ለማውረድ ያለመ ነው "ብለዋል።

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ በኮንፈረንሱ የአሜሪካ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ኮሪያና ሌሎችም የዓለም ሀገራት ምሁራን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ርዕስ ጉዳዮች ላይ ያካሄዷቸው 35 የጥናትና ምርምር ስራዎች ለውይይት ይቀርባሉ ።

ዩኒቨርስቲው የአገሪቱ የቀጣይ 15 ዓመት የኢንዱስትሪ ልማት ፍኖተ ካርታ፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የብረታ ብረት፣ የኬሚካል፣ የስሚንቶ፣ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስትራቴጂካዊ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ለአስፈፃሚ አካላት ማቅረቡን ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው በዙሪያው ካሉት ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር መፍጠሩን የገለፁት ኘሬዝዳንቱ ይህም ለኢንጅነሪንግና ተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የተግባር ዕውቀት እንዲቀስሙ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልፀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ሥር ካሉ አስር ካምፓኒዎች ጋር ስምምነት በመፍጠር የማማከርና የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ሥራዎች እያካሄደ ነው።

በዚህም በአገሪቷ እየተገነቡ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚፈለገውን የሰለጠነ የሰው ሀይል የማፍራትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሚያፋጥን እወቀት ለማፍለቅ  ራእይ ይዞ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂና የምርምር ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሽፈራው ፈይሳ በበኩላቸው " የአከባቢውን ህብረተሰብ ችግር በዕውቀትና በሳይንስ ላይ በመመስረት ለመፍታት እየሰራን ነው" ብለዋል።

አዳማ ከተማ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ማስተር ፕላን እንዲኖራት፣ በጎርፍ መከላከል፣ በፅዳትና አረንጓዴ ፓርክ ግንባታ፣ በአካባቢ ጥበቃና ልማት፣ እንዲሁም በድህነት ቅነሳ ላይ ያተኮሩ ጥናትና ምርም መካሄዱን ጠቅሰዋል ።

እንደ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገለፃ የጥናትና ምርምር ወጤቶቹን ወደ ህብረተሰቡ ለማውረድ ከከተማው አስተዳደር ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ነው ።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው ኮንፈረንስ ላይ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም ከአሜሪካ፣ ጀርመን፣ ኮሪያ፣ ጃፓንና ከሌሎች ሀገራት የተወጣጡት ከ400 በላይ ምሁራን በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 1/2009 በባህርዳር ለሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና የቻይናው ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮሙኒኬሽን ኩባንያ ናቸው።

በስምምነቱ ስምንት የፋብሪካ ሼዶች የሚገነቡ ሲሆን ተያያዥ መሠረተ ልማቶችን ጨምሮ ግንባታው በዘጠኝ ወራት ይጠናቀቃል ተብሏል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ 75 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍና ደረጃውን የጠበቀ የፍሳሽ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ የሚካተትበት እንደሆነም ተነግሯል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ ገመቹ የሚገነባው የኢንዱስትሪ  ፓርክ እንደ አገር የተቀመጡ ግቦችና ስትራቴጂዎችን መሰረት ያደረገ ነው።

በባህርዳር የሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክም በዋናነት የሰው ጉልበትን በስፋት በመጠቀምና በግብርና ውጤቶች ላይ እሴት በመጨመር ኤክስፖርት ለማድረግ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የቻይናው ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮሙኒኬሽን ኩባንያ የኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ሚስተር አለን ሊ በበኩላቸው ግንባታውን በተገባው ውል መሠረት አጠናቀው ለማስረከብ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የባህርዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከሃያ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል።

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ1/2009 ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ባለመስራታቸው በሚከሰቱ አደጋዎች የሚደርሰውን ጉዳት በሚፈለገው ደረጃ መቀነስ እንዳልተቻለ የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ባለስልጣን ገለጸ።

"የአደጋ ስጋት ቅነሳና ምላሽ አሰጣጥ ሂደት ላይ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ያለው ሚና" በሚል ርዕስ ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ከተላለፈላቸው ባለድርሻ አካላት ዋነኞቹ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፣ ኢትዮ ቴሌኮምና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አልተገኙም።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር አማኑኤል ረዳ እንደተናገሩት የሚመለከታቸው አካላት ቅንጅት ደካማ በመሆኑ አደጋዎች ሲከሰቱ የሚደርሰውን ጉዳት በሚጠበቀው መልኩ መቀነስ አልተቻለም።

በመሆኑም የሰው ህይወት እየጠፋ ንብረትም በከፍተኛ ደረጃ እየወደመ ነው ብለዋል።

የእሳት አደጋ ተቆጣጣሪዎች እሳት ለማጥፋት ጥረት ሲያደርጉ በወቅቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመጥፋቱ እሳቱ እንዲባባስ ማድረጉ፣ አደጋ ሲከሰት ለባለስልጣኑ ለማሳወቅ የስልክ ኔትወርክ መቆራረጥና የውሃ አቅርቦት ችግር እንደሚያጋጥም አስረድተዋል።

አደጋን በመከላከሉ ሂደት ባለስልጣኑ አያሌ ሥራዎችን እንደሰራ ያስታወሱት ኮማንደሩ ባለድርሻ አካላት በሚፈለገው ደረጃ እያገዙ ባለመሆኑ ውጤታማ ለመሆን መቸገራቸውን ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ፤ የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ በሚያደርገው ጥረት የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ለመስራት ፈቃደኛ እንዲሆኑና የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የውስጥ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ባዩ ለገሰ በበኩላቸው ከባለስልጣኑ የቀረበውን ሀሳብ በግብዓትነት በመውሰድ በቅንጅታዊ አሰራር ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ይሰራል ብለዋል።

በተለይም አደጋ በሚደርስበት ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል በፍጥነት ማጥፋት ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት አገልግሎቱ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአደጋ ስጋት ቅነሳ በቅንጅት መስራት የሚያስችለውን የጋራ መግባቢያ ሰነድ እንዲፈርሙ ከሚጠበቁት ውስጥ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ብቻ ተፈራርሟል።

የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎችን ለመቀነስ የሚሰራ ከህብረተሰቡ የተውጣጣ 400 አባላት ያሉት የህዝብ ክንፍ ፎረም ግንቦት 2009 ዓ.ም መቋቋሙ ይታወቃል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 1/2009 በጎርፍና ሌሎች አደጋዎች ለሚደርሱ ጉዳቶች መጠባበቂያ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ክምችት መኖሩን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ በብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የሚሰጠውን የዝናብ ትንበያ መረጃ መሰረት በማድረግ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ እየሰራሁ ነው ብሏል።

ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት የጎርፍ መከላከል ግብረ-ኃይል መከላከልን መሰረት በማድረግ በመልክዓ-ምድር አቀማመጣቸው ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን ለይቷል።

ከነዚህም መካከል ለመሬት መንሸራተትና ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋርና ሌሎች ክልሎች የሚገኙ ረባዳ ቦታዎች ይጠቀሳሉ።

በነዚህ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት የመከላከልና ቢከሰት የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ የሚቻልበት ተግባር ቀደም ብሎ ከክልሎች ጋር ተከናውኗል።

የመከላከል ተግባሩ በተሰራበት የጎርፍ አደጋ ቢከሰት ሊደረጉ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች ለህብረተሰቡ ማሳወቅ ሌላው ተግባር ነው ብለዋል።

የቅድመ መከላከል ስራዎችን ከመስራት ባለፈ ከተከሰተ መቋቋም የሚያስችል ምግብ፣ አልባሳት፣ የቤት መገልገያ፣ መጠለያ ድንኳኖችና ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
እነዚህ ድጋፎች ከተደረጉ በኋላም ተጎጂዎችን በዘላቂነት የመልሶ ማቋቋም ስራ ለመስራት ተዘጋጅተናል፤ ለዚህም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ክምችት አለ ብለዋል።

ኮሚሽኑ በ2008 ዓ.ም በአፋር፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ፣ በድሬዳዋ፣ በሐረሪ፣ በጋምቤላ፣ በአማራና በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች የሚኖሩ ከ125 ሺህ በላይ ዜጎች ለጎርፍ እንዳይጋለጡ ወደ ከፍተኛ ቦታዎች እንዲሰፍሩ ማድረጉ ይታወሳል።

በተያዘው የሰኔ ወር በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች በመጠንና በስርጭት የተሻለና በሌሎቹ ደግሞ አልፎ አልፎ ነጎድጓዳማና ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ትንበያ ያመለክታል።

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ሰኔ 1/2009 የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር ብቁ አንስቴዥያንን በማፍራት ለተሳካ ቀዶ ህክምና አገልግሎት እገዛ እያደረገ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ።

አንስቴዥያ በቀዶ ህክምና አገልግሎት ከዝግጅት እስከ ትግበራ ባለው ሂደት ህክምናው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የሰመመን፤ ከህክምና በኋላም ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ የመመለስና ሌሎች ተግባራትን ማከናወን ነው።

13ኛው አገር አቀፍ የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ዳንኤል ገብረሚካኤል እንደተናገሩት፤ ማህበሩ በአገሪቱ ባሉ የጤና ተቋማት ብቁ የአንስቴዥያ ባለሙያዎችን በማፍራት የተሳካ ቀዶ ህክምና እንዲሰጥ እገዛ እያደረገ ነው።

በሆስፒታሎችና በጤና ተቋማት ደህንነቱና ጥራቱ የተጠበቀ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ለመስጠት በሚደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተም ነው።

በጤና ተቋማት በሚደረገው የቀዶ ህክምና አገልግሎት ማህበሩና አባላቱ ከዝግጅት እስከ ትግበራ እገዛ እያደረጉ ነው ብለዋል።

የቀዶ ህክምና አገልግሎት የቡድን ስራ እንደሚጠይቅ የገለጹት ዶክተር ዳንኤል፤ የተሳካ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ለመስጠት የብቁ አንስቴዥያን መኖር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ማህበሩ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር ስርዓተ ትምህርትና የአንስቴዥያ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ብቁ ባለሙያ ለማፍራት በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበርና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ትብብር በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የአንስቴዥያ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ልዑልአየሁ አካሉ በቀዶ ህክምና በተለይም ለእናቶች በሚሰጥ ህክምና የሚደርሰው አደጋ እንዲቀንስ እገዛ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በአገሪቱ አዲስ አበባ፣ መቀሌ፣ ጎንደርና ጅማን ጨምሮ በ19 ዩኒቨርሲቲዎችና በሶስት ኮሌጆች የአንስቴዥያ ትምህርት እየተሰጠ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ብቻ ከ11 ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ከ400 በላይ ባለሙያዎች ይመረቃሉ ብለዋል።

ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ አክሱም፣ መቀሌ፣ ሃዋሳና ዲላ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የመከላከያና የዳግማዊ ሚኒልክ ጤና ሳይንስ ኮሌጅም በዚህ ዓመት ያስመርቃሉ።

በኢትዮጵያ የአንስቴዥያ አገልግሎት መስጠት ከተጀመረ 40 ዓመት ሲሆነው በአሁን ወቅት ከ1 ሺህ 500 በላይ ባለሙያዎች እንዳሉ የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር መረጃ ያሳያል።    

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 1/2009 የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የመንግስት በጀት ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ሁሉም አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል አለ። 

ሚኒስቴሩ የ2010 ዓ.ም. የበጀት ረቂቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ሁሉም አካላት የቀረበውን በጀት በአግባቡ ለመንግስት ልማት በማዋል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ነው ያሳሰበው።

ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ ''የመንግስት በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ ያልቻሉ መስሪያ ቤቶች እንዳሉ የዋና ኦዲተር፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የውስጥ ኦዲተሮች ሪፖርትና ሌሎች ጥናቶች አረጋግጠዋል'' ብለዋል።

ይህም የዴሞክራሲ ሥርዓትን፣ በመንግስትና ህዝቡ መካከል ያለውን መተማመን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ኃላፊነታቸውን በማይወጡ መስሪያ ቤቶች ላይ የመፍትሄ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

በመስሪያ ቤቶች ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሂሳብን መርምሮ በሚሰጠው አስተያየት ፈጥኖ ማስተካከያ ማድረግ፣ የፋይናንስ ግዥና ንብረት አስተዳደር መዋቅር ላይ አቅም መገንባት እና የህዝብን ተሳትፎ ማጠናከር የተወሰዱ እርምጃዎች ናቸው።

የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደርን በማይከተሉ መሥሪያ ቤቶች ላይ የተወሰደው እርምጃ ውጤት እያመጣ ነውም ተብሏል።

መመሪያው ከመጋቢት 15 ቀን 2009 ዓ.ም ተግባራዊ ከሆነ ጀምሮ በፋይናንስ አስተዳደር ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ 16 መስሪያ ቤቶች የበላይ ኃላፊዎች የመጀመሪያ ደረጃ ጥብቅ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በ34 መስሪያ ቤቶች በድንገት በተደረገ ክትትልና ግምገማ አራት መስሪያ ቤቶች አሳሳቢ የፋይናንስ አስተዳደር ጥሰት ተገኝቶ በአፋጣኝ እንዲያስተካክሉ ተጠይቀዋል ብለዋል።

መመሪያዎቹ ተግባራዊ ከተደረጉ በኋላ የፋይናንስና የኦዲት ሪፖርቶችን በወቅቱ በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ መሻሻል ታይቷል።

ለአብነትም ቀደም ሲል የተሟላ ወርሀዊ የሂሳብ ሪፖርት ያቀረቡ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ከ20 በመቶ የማይበልጡ ሲሆን መመሪያው ከተተገበረ በኋላ ግን ከ80 በመቶ በላይ ደርሷል።

በኦዲት በኩልም ከ18 በመቶ ወደ 65 በመቶ ከፍ እንዳለ ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት።

ድንገተኛ ክትትሉ አሁንም ከፍተኛ ስጋት በሚታይባቸው መሥሪያ ቤቶች ላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

ሚኒስቴሩ ከሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር በላይ  ሁሉም ማህበረሰብ በባለቤትን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 1/2009 የህንዱ የሳይንስና የኢንዱስትሪ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ የብረትና የኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር ለመሥራት ተስማማ።

ሥምምነቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ዓለሙ ስሜ በህንድ በኩል ደግሞ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጊሪሺ ሻሃኒ ፈርመውታል።

በሁለቱ ተቋማት የተደረሰው ሥምምነት አገራቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር መሰረት ይጥላል ተብሏል።

ሥምምነቱ በመሰረታዊነት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥልጠናና የአቅም ግንባታ መርሃ-ግብሮችን በማቅረብ ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚረዳም ነው የተጠቆመው።

የዘርፉ ባለሙያዎች በህንድ ሥመ-ጥር በሆኑ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የትምህርት ተቋማት ነጻ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተገልጿል።

በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስክ የጋራ ጥናትና ምርምር ለማድረግና በተለይም በቴሌ ሜዲሰን ያለውን ልምድና ዕውቀት ለመለዋወጥ እንደሚረዳም ተጠቁሟል።
ይህ የህንድ የዘርፉ ቀዳሚ ኢንስቲትዩት 38 ቤተ-ሙከራና 10 ሺህ የሰው ኃይል በመያዝ በዘርፉ ከአፍሪካ አገራት ጋር በትብብር ለመሥራት እየሰራ ይገኛል።

ሥምምነቱ በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

 

Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን