×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Wednesday, 07 June 2017

መቱ ግንቦት 30/2009 ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከል  የእንስሳትን ሞት መቀነስ መቻሉን  የኢሉአባቦር ዞን ዓሳ ሀብት ልማትና ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ የእንስሳት ጤና ስራ ሂደት መሪ ዶክተር ገበየሁ ጫሊ እንደገለጹት በዞኑ  አባጎርባ፣አባሰንጋ፣ ገንዲና በሌሎችም ተላላፊ የእንስሳት በሽታዎች ምክንያት በየዓመቱ  ከ500 በላይ እንስሳት ይሞቱ ነበር።

ችግሩን ለመከላከል ባለፉት አምስት ዓመታት በተደረገው ጥረት ይህ አሃዝ ዘንድሮ ወደ 85 ዝቅ ማድረግ ተችሏል።

የመከላከያ ክትባትን በመደበኛና በዘመቻ መልክ ከመስጠት ባሸገር   ለአርሶ አደሩ በእንስሳት አያያዝና አጠባበቅ ዙሪያ ተከታታይ ያለው ትምህርት መሰጠቱ ለጉዳቱ መቀነስ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በዞኑ 13ቱም ወረዳዎች ከአምስት ዓመታት በፊት 57 ብቻ የነበረውን የእንስሳት ህክምና ኪሊኒኮች ቁጥር አሁን ላይ   ከ100 በላይ በማድረስ  አርሶአደሩ በቅርበት አገልግሎቱን እንዲያገኝ ተደርጓል።

በዚህም በየዓመቱ ለ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ያህል የቤት እንስሳት የተለያዩ በሽታዎች መከላከያ ክትባት መስጠት ተችሏል።

ዶክተር ገበየሁ እንዳሉት  በቆላማ የዞኑ አካባቢ የቆላ ዝንቦችን ለመቆጣጠርም በየዓመቱ ከ90 ሺ በላይ  የቀንድ ከብቶች  የበሽታው መከላከያ መድኃኒት እያገኙ ነው፡፡

ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል  በተሰጠው ትኩረትም የእንስሳትን ሞት መቀነስ መቻሉን  ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደር ሸረፉ ሀጂ አብደላ የበሰሌ ኖኖ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ  ቀደም ባሉት ዓመታት የጋማ እና የቀንድ ከብቶቻቸው በተለያዩ በሽታዎች በመጠቃት ይሞቱባቸው እንደነበር ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመደበኛ በዘመቻ መልክ ክትባት በቅርበት እያገኙ ችግሩ እየቀነሰ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡

በዳሪሙ ወረዳ የቤና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አብዱልቃድር አወል በበኩላቸው ባለሙያዎች የሚያደርጉላቸውን እገዛ ተጠቅመው ለሚያረቧቸውን የቤት እንስሳት ጤንነት ትኩረት ሰጥተው በመንከባከብ የሚያጋጥማቸው የበሽታ ችግር መቃለሉን ገልጸዋል፡፡

"ከእርሻ ስራዬ ጎን ለጎን  የማረባቸው አስር የቀንድ ከብቶች አሉኝ  " ያሉት  አርሶ አደሩ  ውሏቸውን  በመከታተል የበሽታ ምልክት ሲያዩ በፍጥነት ወደ ጤና ክሊንክ በመውሰድ ደህንነታቸውን እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 30/2009 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ሴቶችን ለማብቃትና ወደ አመራር ለማምጣት ያከናወኗቸው ተግባራት አጥጋቢ አለመሆናቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።

የምክር ቤቱ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ዘርፍ የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

ተቋማቱ የሴቶችን የአመራር ሰጪነት ሚና ለማሳደግ የተለያዩ ስልጠናዎች፣ ትምህርቶችና ሌሎች የአቅም ማጎልበቻዎችን በመስጠት ያከናወኗቸው ተግባራት አጥጋቢ አይደሉም ብሏል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ እምዬ ቢተው እንደተናገሩት የሴት ሰራተኞችን አቅም ለማጎልበት የአጫጭርና የረጅም ጊዜ የትምህርት እድሎችን በማመቻቸት የበቁ ሴቶችን ወደ አመራር በማምጣት በኩል ትኩረት ሊደረግ ይገባል።

"ከአቅም ግንባታ በዘለለ የአመራር ቦታ ላይ ሴቶችን በማምጣት የተሰራ ስራ ባለመኖሩ በቀጣይ ተጨባጭ ለውጥ ያስፈልጋል" ብለዋል።

መስሪያ ቤቶች ሴቶች ወደ አመራርነት እንዳይመጡ የሚያደናቅፉ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን መለየት ሊሰሩበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ሴቶችን የማብቃትና የበቁትም ወደ ውሳኔ ሰጪነት እንዲመጡ የሚሰጣቸውን ግብረ መልሶች ወስዶ ተግባራዊ በማድረግ በኩልም መስሪያ ቤቶች ክፍተት ይታይባቸዋል ብሏል።

በሌላ በኩል በወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ወጣት ሴቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በትኩረት ሊከታተሉ እንደሚገባም አሳስቧል።

ሴቶች ተረጋግተው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ለማድረግ የትራንስፖርት ሚኒስቴር በስራ ቦታ የህጻናት ማቆያ ማዕከል ማቋቋሙን ለአብነት በመጥቀስ ሌሎችም ይህን ፈጥነው እንዲተገብሩ አሳስቧል።

በተጨማሪም በሴቶችና ህጻናት ስም በእርዳታ የሚገኝ ሃብት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል መከታተል፣ የህጻናትን መብትና ደህንነት ማረጋገጥና በተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ሴቶችን ተጠቃሚ የማድረግ ጉዳዮች ትኩረት ያሻቸዋል ብሏል ቋሚ ኮሚቴው።

የተቋማቱ ኃላፊዎች ቋሚ ኮሚቴው ያነሳቸውን ክፍተቶች በግብዓትነት በመውሰድ ለሴት ሰራተኞች የአቅም ግንባታ ከመስጠት ባለፈ በተጨባጭ ወደ አመራር ሰጪነት እንዲመጡ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

Published in ማህበራዊ

ሀረር ግንቦት 30/2009 ሪፈራል ሆስፒታሎችን መገንባት ለህብረተሰቡ ዘመናዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ በማስቻል  የህክምና ቱሪዝምን እንደሚያጎለብት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በሐረር ከተማ በ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ እያስገነባ ያለውን ሪፈራል ሆስፒታል እንቅስቃሴና የተጠናቀቀውን የካንሰር ማዕከል  ዛሬ ተመልክተዋል፡፡

በዚህ ወቅት ሚኒስትሩ እንዳሉት በሀገሪቱ ከአስር ዓመታት በፊት ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ 87 የነበሩት የመንግስት ሆስፒታሎች  ቁጥር አሁን ላይ 411 ደርሰዋል። 

የሪፈራል ሆስፒታሎች ግንባታም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው ይህም  ዘመናዊ የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ከማዳረስ በሻገር የህክምና ቱሪዝም አገልግሎትን ለማጎልበት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

"የሐረማያ ዩኒቨርሲቲም እያስገነባ የሚገኘው የሪፈራል ሆስፒታልና የካንሰር ማዕከል ለምስራቅ ኢትዮጵያ ፣ ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የህክምና አገልግሎትና የጤና ሳይንስ ትምህርት መስጠት የሚያስችል ነው "ብለዋል።

ለእነዚህ የጤና ተቋማት የሚያስፈልጉ  የህክምና ባለሙያዎችን የማሰልጠኑንና የማብቃቱን  ስራ ደግሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በዩኒቨርስቲው የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ያደታ ደሴ እንደገለጹት የካንሰር ማዕከሉ ግንባታ ተጠናቋል።

አንድ ሺህ የሚጠጉ አልጋዎችንና ለተቋሙ የጤናና ህክምና ሳይንስ ተማሪዎች ጥራት ያለው ተግባር ተኮር  ትምህርት መስጪያ ክፍሎችን አካቶ የያዘው ሪፈራል  ሆስፒታሉ ደግሞ ግንባታው 77 በመቶ መከናወኑን አመልክተዋል፡፡

በ2006 ግንባታቸው የተጀመሩት እነዚህ ተቋማት አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ የምስራቁ የሀገሪቱ አካባቢ ነዋሪዎች በአቅራቢያቸው አገልግሎቱን እንደሚያገኙና ሐረር ከተማም  የህክምና ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ያስችላታል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የህይወት ፋና ሆስፒታልን ከሐምሌ 2002 ዓ.ም ጀምሮ ከክልሉ መንግስት  ተረክቦ ለህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት፣ ለተቋሙ የጤናና ህክምና ሳይንስ ተማሪዎች ደግሞ የተግባር ትምህርት እየሰጠበት ይገኛል።

Published in ማህበራዊ

 አዲስ አበባ ግንቦት 30/2009  በአዲስ አበባ እያደገ ካለው የኮንስትራክሽን ልማት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ ጋር በመሆን "የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ህዳሴን ለማፋጠን የባለድርሻ አካላት ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ የምክክር መድረክ አካሄዷል።

በመዲናዋ የኮንስትራክሽን ልማት የተለዩ ችግሮችና ቢሮው ለመፍታት የሄደበትን ርቀት የሚያሳይ ሰነድ ቀርቦም ውይይት ተደርጎበታል።

የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት፣ ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር፣ የዘርፉ ባለሙያዎች የክህሎት ማነስ፣ የሙያ ስነ ምግባር አለማክበርና የአሰራር ግልጸኝነት አለመኖር በዋናነት በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች እንደሆኑ ሰነዱ አሳይቷል።

የቢሮ ሃላፊው ኢንጂነር ዮናስ እንደገለጹት፤ የከተማዋ ኮንስትራክሽን ልማት ሰፊና ብዙ የሰው ኃይል የተሰማራበት በመሆኑ እነዚህን ችግሮች የመቅረፍ ሃላፊነት ለቢሮው ብቻ የሚተው አይደለም።

"ችግሮችን ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል" ብለዋል።

የኤም.ጂ.ኤም አማካሪ ድርጅት የኮንትራት አስተዳደር ባለሞያው አቶ ወንድሙ ጉዲሳ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ አዲስ አበባ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሻለ እድገት ብታስመዘግብም የሚስተዋሉት ችግሮች በዚያው ልክ እየጨመሩ ይገኛሉ።

በመሆኑም የኮንስትራክሽን ግብዓት አቅራቢዎችን ጨምሮ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የያዘ ፎረም ተቋቁሞ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል። 

በኢትዮጵያ ባለፉት አስር ዓመታት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በየዓመቱ በአማካይ የ20 በመቶ እድገት የተመዘገበ ሲሆን ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት እድገት ያለው ድርሻም 8 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል።

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ ግንቦት 30/2009 ሴት ታራሚዎች በህግ ጥላ ሥር ሆነው ገቢ በማመንጨት ራሳቸውን መደጎም እንዲችሉ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ገለጸ።

የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ረጋሳ እንደገለፁት ሴት የህግ ታራሚዎች  በማረሚያ ቤቶች ቆይታቸው ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ለዚህም ሴቶች ብቻ የሚስተናገዱበት ማረሚያ ቦታ  ከማመቻቸትና በስነ ምግባር ከማነፅ ባለፈ የቀለምና የሙያ ስልጠና አግኝተው በአማራጭ የገቢ ምንጮች እንዲሰማሩ ጥረት እየተደረገ ነው።

ለዚህም የልብስ ስፌት፣ ጥልፍ፣ ባልትናና አገልግሎት የተመረጡ ዘርፎች ናቸው፡፡

ከእናቶቻቸው ጋር ለሚገቡ ጨቅላ ህፃናት  ልዩ ትኩረት በመስጠት ለመደገፍ ኢንሼቲቭ ፎር ኢንፕሩቪንግ ስታንዳርድ ፎር ፕሪዝን የተባለ ድርጅት  ታራሚ እናቶች የተለያዩ የቀለምና የሙያ ስልጠና አግኝተው የራሳቸውን ገቢ በማመንጨት እንዲደጎሙ ማገዙን ተናግረዋል

የድርጅቱ  ሥ/ራ አስኪያጅ አቶ ኩምሳ ጉተታ  በበኩላቸው "ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ  ሴት የህግ ታራሚዎች የሙያና የቀለም ትምህርት እንዲያገኙ ድጋፍ አድርገናል" ብለዋል።

እንዲሁም ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ በአርሲና ምስራቅ ሐራርጌ ዞኖች ማረሚያ ቤቶች እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሰርቶ ለአገልግሎት ማብቃቱንም ጠቅሰዋል፡፡                 

ሴት የህግ ታራሚዎች በማረሚያ  ቤት ቆይታቸው በሙያ ሰልጥነው የገቢ አቅማቸውን ማሳደግ በሚቻልበት  ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 30/2009 የኢትዮጵያ ባህርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የመርከቦቹን የገቢና ወጪ ጭነት መጠን እንዲያሳድግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የድርጅቱን የ10 ወራት አቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።

ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ 10 ወራት በራሱና በኪራይ መርከቦች 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቶን ጭነቶችን ወደ አገር ውስጥ ለማጓጓዝ አቅዶ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቶን ወይም የእቅዱን 85 በመቶ አሳክቷል።

ይሁንና ወደ አገር ውስጥ ከገቡ ጭነቶች ውስጥ የኢትዮጵያ 11 መርከቦች ድርሻ 12 ነጥብ 8 በመቶ ብቻ መሆኑ በቋሚ ኮሚቴው አባላት ጥያቄ አስነስቷል።

ከኢትዮጵያ ወደ ሌሎች ዓለም አቀፍ የገበያ መዳረሻዎች ወጪ የተደረጉ ጭነቶች በተመሳሳይ ወቅት 2 ሺህ 77 ኮንቴይነር ጭነት ለማጓጓዝ አቅዶ አፈጻጸሙ 8 በመቶ ብቻ መሆኑም ሌላው ጥያቄ ያስከተለ ጉዳይ ነው።

የድርጅቱ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ተፈራ ወደ አገር ውስጥና ውጭ አገራት ለማጓጓዝ በተቀመጠው እቅድ መሰረት ማሳካት ያልተቻለው በዓለም አቀፍ ንግድ መቀዛቀዝና በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት መሆኑን ገልፀዋል።

ድርጅቱ ለዘጠኝ መርከቦች ግዥ፣ ለደረቅ ወደቦች መሰረተ ልማት ግንባታና ለተሽከርካሪዎች ግዢ ከቻይናው የገቢ ወጪ ንግድ፣ ከልማትና ንግድ ባንኮች የተበደረውን ገንዘብ በውሉ መሰረት እየከፈለ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይ "የመርከቦችን ቁጥርና የመጫን አቅም ለማሳደግ እንሰራለን" ያሉት አቶ መስፍን በጅቡቲ የመልቲ ሞዳል ጭነት አማካይ ቆይታ በ2005 ዓ.ም የ32 ቀናት ቆይታን በ2009 ዓ.ም 10 ወራት ወደ 6 ነጥብ 8 ዝቅ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የአገር ውስጥ ወደቦች የማስተናገድ አቅምም በ2005 ዓ.ም ከነበረበት 60 ሺህ ኮንቴይነር በተያዘው ዓመት ወደ 138 ሺህ 673 ማሳደግ እንደተቻለም አብራርተዋል አቶ መስፍን።

በወጪ ንግድ ለተሰማሩ 15 ድርጅቶች 695 ኮንቴይነሮች የየብስ ትራንስፖርት ዋጋ ቅናሽ ተደርጎ በ10 ወራት ውስጥ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ የተገኘ ሲሆን ጠቅላላ የድርጅቱን ገቢ ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማድረስ ተችሏል።

የበጀት አስተዳደርን በተመለከተ የ2006 በጀት ዓመት ሂሳብ በውጭ ኦዲተሮች ተመርምሮ ሲጠናቀቅ የ2007 በጀት ዓመት ሂሳብ የመዝጋት ስራ 95 በመቶ ሲደርስ ለውጭ ኦዲተሮች ምርመራ መሰጠቱን ተናግረዋል።

የ2008 በጀት ዓመት የድርጅቱን ሂሳብ መዝጋት ስራ በተመለከተ አጠቃላይ ሂሳብ የመዝጋቱ ስራ በአማካይ 58 ነጥብ 67 በመቶ ደርሷል።

በአገሪቱ የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ የባቡር መሰረተ ልማቶችን ከወደብ አገልግሎት ጋር ለማስተሳሰር ከተያዙ እቅዶች የሞጆ ወደብና ተርሚናል የባቡር እቃ መጫኛና ማራገፊያ ግንባታ 65 በመቶ ሲጠናቀቅ የድሬዳዋ ወደብና ተርሚናል የግንባታ ውል ተፈርሟል።

የቃሊቲ ወደብና ተርሚናል የወጪ እቃዎች ማደራጃ ሼድ ግንባታ የጠናቀቀ ሲሆን የመቀሌና ኮምቦልቻ ወደብና ተርሚናል መሰረተ ልማት ስራዎች በጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት የግንባታ ውል ስምምነት ይደረጋል ተብሏል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አለሚቱ ፉፋ ድርጅቱ በእቅዱ መሰረት ያላሳካቸውን ስራዎች በተለይም የመርከቦች አፈጻጸም ማሻሻል እንዳለበት አሳስበዋል።

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ቅነሳ፣ በወጪ ንግድ ድጋፍና የባቡር መስመሮችን ከደረቅ ወደቦች ጋር ማገናኘትና ስራ ማስጀመር ስራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 30/2009 የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ በብሔራዊ መግባባትና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያከናወናቸው ዘገባዎች የሚበረታቱና ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ናቸው ሲል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለፀ።

ይሁን እንጂ ተደራሽነቱን ለማስፋት 'የኦን ላይን ቴሌቪዥን ስርጭትን' በፍጥነት መጀመር እንዳለበት አሳስቧል።

ምክር ቤቱ ይህን የገለጸው ዛሬ የባህል፣ ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኤጀንሲውን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም በገመገመበት ወቅት ነው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲያ የሱፍ ኤጀንሲው በብሄራዊ መግባባትና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ የማድረስ ስራውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በሌሎች መገናኛ ብዙሃን ያልተዳሰሱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ለተጠቃሚዎች ማድረሱን የኮሚቴው ሰብሳቢ በመልካም ጎኑ  አንስተዋል።

በሌላ በኩል ኤጀንሲው 'የኦን ላይን ቴሌቪዥን ስርጭት' ለመጀመር እቅድ ቢይዝም እስካሁን አለማሳካቱን ጠቁመው ወደፊት በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በክልሎች የሚገኙ ህንፃዎች በአግባቡ ያልተያዙበትንና ለተገቢው አገልግሎት ያልዋሉበትን፣ እንዲሁም ከክልል የሚመጡ ዜናዎች በምስል ያልተደገፉበትን ምክንያት ጠይቀዋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ሙለታ በሰጡት ምላሽ የሕንጻዎቹ አያያዝ ችግር የቆየ መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅትም እድሳት እየተደረገላቸው መሆኑንና በቀጣይ በሚደረገው የማስፋፊያ ስራ የፊልም ስቱዲዮ እንደሚኖራቸው ገልፀዋል።

ከክልል የሚመጡ ዜናዎችን በተመለከተም ከ34 በላይ ላሉ ቅርንጫፎች ካሜራ ለመግዛትና የቀረጻ ባለሙያ ለመቅጠር አሁን ያለው በጀት እንደማይበቃና በቅርብ በሚደረገው የአደረጃጀት ለውጥ እንደሚሻሻል ጠቁመዋል።

''መረጃዎችን በፍጥነት ለመገናኛ ብዙሃን ተደራሽ ለማድረግ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዕድገት ስለሚያስፈለግ ጋዜጠኞች ዜናዎችን ባሉበት ቦታ ሆነው የሚፅፉበትና የአርትኦት ስራ የሚያከናውኑበት ቴክኖሎጂ ግዥ ላይ ነን'' ብለዋል።

የኦንላይን ቴሌቪዥን ስርጭቱ የተጓተተው ከግዥና ጨረታ እንዲሁም ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ መሆኑን ገልጸው እቃዎቹ እየተገዙ በመሆኑ በሚቀጥለው መስከረም ለመጀመር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የኤጀንሲው የቴሌቪዥን ፕሮግራምና ፕሮዳክሽን ዳይሬክተር አቶ ነጋሲ አምባዬ  ዕቃዎቹ ቢገቡም በሰው ኃይል በኩል ክፍተት አለብን ነው ያሉት።

የህዝብ ክንፍን ወክለው የተገኙት አቶ ወንድወሰን መኮንን በበኩላቸው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደ ዓለም አቀፍ የዜና ምንጮች ተወዳዳሪ ለመሆን መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ በአዲስ መልኩ ከተደራጀበት ከ2007 ዓም መጨረሻ ጀምሮ ተወዳዳሪ የሚያደርጉትን ስራዎች እያከናወነ ይገኛል።

Published in ማህበራዊ
Wednesday, 07 June 2017 21:42

የእቅድ ጉዞ ግስጋሴ

ከሰለሞን ተሰራ /ኢዜአ/

የመጀመሪያው አምስት ዓመት (2003-2007) የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረታዊ ዓላማዎች ኢኮኖሚውን በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ 11 በመቶ በማሳደግ፣ የሚሊኒየሙን የልማት ግቦችን ማሳካት፣ የትምህርትና ጤና አገልግሎት ሽፋንን በመጨመርና ጥራቱን በማረጋገጥ ላይ የተመሠረተ ማህበራዊ ልማት በማካሄድ ማህበራዊ ግቦችን ማሳካት ፣ የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግስትን በመፍጠርና በማጠናከር ለቀጣይ የሀገር ግንባታ ሥራ ምቹ መደላድል መፍጠር እና የተረጋጋ ማክሮ-ኢኮኖሚ በማስፈን የልማቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ መሆናቸውን ብሔራዊ የፕላን ኮሚሽን ታህሳስ 2008 ያወጣው አጠቃላይ እቅድ ያሳያል፡፡

በመጀመሪያው የእቅድ ዘመን የዓለም ኢኮኖሚ ከፍተኛ ውጣ ውረዶች ስላጋጠሙት በተለይም የዓለም የምግብና የነዳጅ ዋጋ በመጀመሪያዎቹ ሁለት የዕቅዱ የትግበራ ዓመታት ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየቱ  እና አጠቃላይ የዓለም የኢኮኖሚ ዕድገትም ዕቅዱ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ከነበሩት ሁለት ዓመታት ብዙ መሻሻል ሳያሳይ በመቆየቱ በሀገር ውስጥ ዋጋ ንረትና በወጪ ምርት ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር፡፡ ነገር ግን መንግስት በወሰዳቸው የፖሊሲና አስተዳደራዊ እርምጃዎች የገበያ ጉድለቶችን በማስተካከል ከዓለም ገበያ የመጣውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቋቋምና በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል ተችሏል፡፡

የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከ2003 በፊት በነበሩት ሰባት ዓመታት የተመዘገበውን ፈጣን ዕድገት ቀጣይነት የማረጋገጥ ግብ ያስቀመጠ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት ቢያንስ የ11 በመቶ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት የታቀደ ቢሆንም ዕቅዱ ሥራ ላይ በዋለባቸው አምስት ዓመታት (2003-2007) ኢኮኖሚው በየዓመቱ በአማካይ በ10.1 በመቶ ማደጉን የተለያዩ አካላት መስክረዋል፡፡ ይህ አፈፃፀም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ከተቀመጠው ዓመታዊ አማካይ ግብ ጋር ተቀራራቢ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ የተመዘገበው ፈጣን ዕድገት በተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ከሚገኙ ከሰሃራ-በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ  ከፍ ያለ ሲሆን ከ 1996-2007 ዓ.ም ባሉት 12 ዓመታት ኢኮኖሚው በየዓመቱ በአማካይ በ10.8 በመቶ እንዲያድግ ያስቻለ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጉዞ አካል የሆነው የቀጣዩ አምስት ዓመት (2008-2012) የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዋናው ማጠንጠኛ የግብርና ልማትን ማዘመን ፣የኢንዱስትሪያላዜሽን ትራንስፎርሜሽንንና የወጪ ንግድ ልማትን ማረጋገጥ ነው፡፡ የሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በዋናነት በ2017 ዓ.ም ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ያላት አገርን እውን የማድረግ ራዕይን መነሻ ያደረገ ነው፡፡

የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንም እ.ኤ.አ ከ2016 እስከ 2030 ያለውን ጊዜ የሚሸፍኑ አዲስ አለም አቀፍ “ዘላቂ የልማት ግቦች” የሚባሉት ተዘጋጅተው በመስከረም 2015 በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ፀድቀዋል፡፡ አፍሪካም የ“Common African Position (CAP) on Post-2015 Development Agenda” በሚል የጋራ አቋሟን ቀድማ አዘጋጅታ በአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ አፀድቃለች ፡፡ የዘላቂ ልማት ግቦችንና የአፍሪካን የጋራ አቋም ከሃገሪቱ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ልማት ቅደም ተከተል ጋር በተጣጣመ መንገድ ተግባራዊ እንዲሆኑና ኢትዮጵያም ኋላፊነቷን እንድትወጣ ያስችላል፡፡ በተጨማሪ በ50 ዓመታት ውስጥ በኢንደስትሪ የዳበረችና የበለፀገች አፍሪካን እውን ለማድረግ በአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ጉባኤ ያፀደቀውን “አጀንዳ 2063” ራዕይንና ዝርዝር ኘሮግራሙን ግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት አስራ ሶስት አመታት ባለሁለት አሐዝ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ የዜጎቿን ገቢ በማሳደግና የአኗኗር ደረጃቸውን በመለወጥ ድህነትን በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ በቅታለች፡፡አገሪቱ እያስመዘገበች ያለው ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ባልተነካው የአገሪቱ እምቅ የተፈጥሮና የሰው ሐብት በመታገዝ የውጭ ባለሐብቶችን እየሳበ ነው፡፡

የመንግስትን ተቋማት ወደ ግል ባለሐብቶች የማዛወር ሒደቱም በተሳካ መንገድ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ሁለተኛው የእቅድ ዘመን ለግል ባለሐብቶች እና ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን የገንዘብ ሚኒስቴር ሰነድ ያሳያል፡፡

አቅም ያላቸውን የውጭ ባለሐብቶች ለመሳብ አጋዥ ስለሆነው የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት የዘርፉ ባለሙያዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡የአለም ኢኮኖሚ ፎረም የ 2015-2016 አለም አቀፍ የተወዳዳሪነት ሪፖርት ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚው ባላት የምቹነት ምጣኔ -ከብጥብጥና የተደራጀ ወንጀል አንጻር ከ 140 አገራት 61 ኛ 75 ደረጃን ማግኘቷን ያሳያል፡፡ደረጃዋ ከጎረቤት አገራት በእጅጉ የቀደመ መሆኑ መረጋጋቷን ቁልጭ አድርጎ ያመለክታል፡፡

ሪፖርቱ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የተቋማቷን ጥንካሬ በማሳደግ በኩል ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቷን ጠቅሶ  በአገሪቱ ያለው የሰራተኛና የሸቀጥ ገበያ ፣የንግድ ስብጥር እና ፈጠራ ማደጉን ጠቅሷል፡፡ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ተወዳዳሪነት በ2014-2015 ከ144 አገራት 118 የነበረች ሲሆን በ2015-16 ሪፖርት ደረጃዋን ወደ 109 ኛ ማሳደጓ ተጽፏል፡፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት አመታዊ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ቀዳሚ መሆኗን መረጃው አሳይቷል፡፡የአለም ኢንቨስትመንት የ 2013 ሪፖርት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሶስተኛዋ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ በመሆን በ2012 ካስመዘገበችው ምጣኔ በ240 በመቶ ያደገ ሐብት መሳቧን አሳይቷል፡፡የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው በ2016-17 የመጀመሪያው ስድስት ወራት ወደ አገሪቱ የገባው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በአማካይ 35 በመቶ በመጨመር 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ፡፡

  • ለውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ከባቢ ሁኔታ

የተረጋጋና በፍጥነት የሚያድግ ኢኮኖሚ፣ አስተማማኝ የፖለቲካ ምህዳር፣ሰላምና ደህንነት መረጋገጡ፣ያልተነካና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገኝ የሰለጠነ ሰራተኛ፣ለአለም አቀፍ ገበያ ያለው ቅርበት፣የተሻሻለ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና የተለያዩ ማበረታቻዎች የውጭ ቀጥተኛ ሐብትን ለመሳብ ምቹ መደላድል ተደርገው ተቀምጠዋል፡፡ተወዳዳሪ የጉልበት ዋጋ፣የሰለጠነ የሰው ሐይል፣ርካሽ የሐይል እና የመሬት አቅርቦት ግዙፍ ኩባንያዎችን ለመሳብ ተጨማሪ ግብአት  ናቸው፡፡

  • የመሰረተ ልማት ግንባታ

መንግስት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብና ምቹ ከባቢ ሁኔታ ለመፍጠር በወሰደው ቁርጠኛ አቋም የመንገድ፣የባቡር መስመር፣የደረቅ ወደብ፣የአየር ትራንስፖርት፣የሐይል እና የቴሌኮም ማስፋፊያዎችን በስፋት እያከናወነ ይገኛል፡፡

  • የመንገድ መሰረተ ልማት፡ መንግስት የትራንስፖርት ክፍያን ለመቀነስ በያዘው እቅድ የተቀናጀ የመንገድ ልማትና የትራንስፖርት አገልግሎት ለመፍጠር እየሰራ ነው፡፡መንገድ የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት የጀርባ አጥንት በመሆኑ የመንገድ አውታሮችን ማሻሻልና የቀለበት መንገዶችን መገንባቱን ቀጥሎበታል፡፡በ 2010-15 የነበረው የአገሪቱ የመንገድ ሽፋን ከ50 ሺ ኪሎሜትር ወደ 110 ሺ ኪሎሜትር አድጓል፡፡በሁለተኛው እቅድ ዘመን በመገንባት ላይ የሚገኙት መንገዶች ሲጠናቀቁ በ 2019-20 ሽፋኑ ወደ 220 ሺ ኪሎሜትር እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡
  • የባቡር መሰረተ ልማት፡ ሸቀጦችን በዝቅተኛ ዋጋና በአጭር ጊዜ በብዛት ለማመላለስ ተመራጩ የባቡር መስመር ነው፡፡ብሔራዊ የባቡር መሰረተ ልማት ትስስር ግንባታ አገሪቱ ቅድሚያ ከሰጠቻቸው ፕሮግራሞች አንዱ ሲሆን በመጪዎቹ አመታት በቅድሚያ የሚተገበር መሆኑ ተጠቅሷል፡፡የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር ግንባታ ተጠናቆ በሙከራ ላይ ይገኛል፡፡ መስመሩ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር በአመት 750 ሺ መንገደኞችንና 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ሸቀጥ እንደሚያመላልስ ይጠበቃል፡፡ከዚህ በተጨማሪ መስመሩ የትራንስፖርት ዋጋንና ጊዜን በመቆጠብ ቀጥተኛ የውጭ ባለሐብቶችን በመሳብ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ያሳድጋል፡፡

የአዲስ አበባ ሞጆ የባቡር መስመር ትስስር ግንባታ እቅድ አገሪቱ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳለጥ የያዘችው የመጀመሪያ ምዕራፍ ስራ ነው፡፡ በሁለት ምዕራፍ የሚከናወነው ግንባታ አገሪቱን ከጅቡቲ፣ ታጁራና ከሞምባሳ ወደብ ጋር ያገናኛታል፡፡

የትስስሩ ሁለተኛ ምዕራፍና ከአዋሽ ተነስቶ መቀሌ የሚዘልቀው የባቡር መስመር  በቱርኩ ያፒ ሜርኬዚ ኩባንያ እና በቻይናው የኮሚኒኬሽንና ኮንስትራክሽን ኩባንያ በግንባታ ላይ ሲሆን በ2018 እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡ ሶስተኛው ምዕራፍ ደግሞ ወልድያን ከታጁራ ወደብ የሚያገናኝ ሲሆን ግንባታው ለቻይና የግንባታ ተቋምና ለህንድ ኩባንያ በጋራ ተሰጥቷል፡፡

የግንባታው አራተኛ ደረጃ አዲስ አበባን በሐዋሳ እና አርባ ምንጭ በኩል ከኮንሶ ጋር የሚያገናኝ ሲሆን በሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታው በሞያሌና ናይሮቢ አድርጎ ከኬንያና ሞምባሳ ጋር ያገናኛታል፡፡

የባቡር መሰረተ ልማት ትስስር ግንባታው የመጀመሪያ ምዕራፍ ማጠቃለያ ከአዲስ አበባ በአምቦ -ኢጃጂ እና ጂማ - በደሌ ድረስ ይዘልቃል፡፡የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ እስከ ደቡብ ሱዳን እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡

የባቡር መስመር ትስስሩ ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ እስከ አክሱም፣ ሽሬ ፣ባህር ዳር እና አሶሳ ሲዘልቅ በተጨማሪ ከላይ እንደተጠቀሰው ኬንያና ደቡብ ሱዳንን በመተማና በኩምሩክ በኩል ከሰሜን ሱዳን ጋር ያገናኛል፡፡የግንባታው ቅድሚያ የተሰጠው ሸቀጦችን በማጓጓዝ ላይ መሰረት አድርጎ ሲሆን ቡናና ፖታሽን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የግንባታ እቃዎችንና መሰረታዊ አቅርቦቶችን ወደ አገር ውስጥ ያስገባል፡፡

  • የሐይል አቅርቦት ዘርፍ ፡የአገሪቱን ተከታታይ እድገት ለማስቀጠልና ፈጣን የኢንዱስትሪ ግንባታን ለማረጋገጥ መንግስት በታዳሽ ሐይል አቅርቦት ልማት ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ መድቦ በመንቀሳቀስ ላይ ነው፡፡አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ የተለያዩ የሐይል ምንጮች ላይ እየተሰራ ሲሆን የእንፋሎት፣የንፋስ፣የጸሐይና የውሓ ሐይል ልማቶች በስፋት እየተሰራባቸው ነው፡፡በሁለተኛው የእቅድ ዘመን ማብቂያ 2020- አገሪቱ 17 ሺ 208 ሜጋዋት ሐይል እንደምታመነጭ ይጠበቃል፡፡ከዚህ ውስጥ 1 ሺ 224ሜጋ ዋት ከንፋስ ፣13 ሺ 817 ሜጋ ዋት ከውሓ፣577 ሜጋ ዋት ከእንፋሎት ፣300 ሜጋ ዋት ከጸሐይ እና ከስኳር እና ከባዮ ማስ 731 ሜጋ ዋት ሐይል ለማመንጨት እቅድ ተቀምጧል፡፡ኢትዮጵያ አሁን ላይ 5 ሺ ሜጋዋት የሚጠጋ ሐይል እያመነጨች ሲሆን ለሐይል አቅርቦት የምትጠይቀው ክፍያ ከአህጉሪቱ ዝቅተኛው ነው፡፡

3 - የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት፡

ኢትዮጵያ በማምረቻው ዘርፍ የተሰማሩ የግል ባለሐብቶችን ለመሳብ አስፈላጊው መሰረተ ልማት የተሟላለቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፡የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ የማምረቻ ዋጋን በመቀነስ፣ ምርታማነትንና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የማይተካ ሚና እንዳለው ይታወቃል፡፡በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ልማት የሚያስፈልግ መሬት በማመቻቸት ፣የመሰረተ ልማት አቅርቦትን በማዘጋጀት አስተማማኝ የመንግስት አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል፡፡

መንግስት የአገሪቱን የኢኮኖሚ ኮሪደር በመከተል የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ላይ ነው፡፡አዲስ አበባ ላይ ሁለት ፓርኮች ተገንብተዋል፡፡ ቀዳሚው የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምዕራፍ አንድ ግንባታ 342 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ትኩረቱን በጨርቃ ጨርቅ ፣አልባሳትና ቆዳ ዘርፎች ላይ አድርጓል፡፡የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ 308 ሔክታር ቦታ ላይ እየተገነባ ሲሆን የምግብ ማቀነባበሪያ፣ የምግብ፣የመጠጥ እና የመድሐኒት አምራቾችን እየተጠባበቀ ነው፡፡

በሐምሌ 2016 ወደ ስራ የገባው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ስኩዌር ሜትር ቦታ ላይ በማረፍ 35 ፋብሪካዎችን ይዟል ፡፡ የሐይል አቅርቦት መቆራረጥ ችግሩን ለመፍታት የራሱ የሆነ የታዳሽ ሐይል ምንጭ አለው ፡፡ ከፋብሪካው ከሚወጣው ፍሳሽ 85 በመቶው አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡ፓርኩ በተለይ ለጨርቃ ጨርቅ ፣ለአልባሳት ማምረቻዎችና ለግብርና ማቀነባበሪያዎች ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡

በፓርኩ ውስጥ 15 አለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው የውጭ ኩባንያዎች የገቡ ሲሆን ስድስት የአገር ውስጥ ባለሐብቶች ፋብሪካ ተረክበው ስራ መጀመራቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር የዳሰሳ ጽሑፍ ያሳያል፡፡መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ የአራት የተቀናጁ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ግንባታ ይፋ አድርጓል፡፡የተጠቀሱት አራት ፓርኮች አገሪቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለመገንባት ያቀደቻቸው 17 የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮች አካል ናቸው፡፡ ፓርኮቹ አለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው የሚሰሩ በመሆናቸው ባለሐብቶችን በቀላሉ ለመሳብ እንደሚያግዙ ታምኖባቸዋል፡፡

 

Published in ዜና-ትንታኔ

አሶሳ ግንቦት 30/2009 ፌዴራል ስርዓቱ ህዝቦች ከክልላቸው ውጪ የመስራትና የመኖር መብታቸውን ያረጋገጠና ለዘመናት አብሮ የመኖር ባህላቸውን ያስቀጠለ መሆኑን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንት ለማ መገርሳ ገለፁ፡፡

ፕሬዝዳንቱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚኖሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችና ክልሉን ከሚጎራበቱ የኦሮሚያ ወረዳዎች ከተውጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ትናንት  በአሶሳ ከተማ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት  አቶ ለማ እንዳመለከቱት ፌዴራል ስርዓቱ ከክልላቸው ውጪ የሚኖሩ ህዝቦችን መብትና ጥቅም ያስጠበቀ ነው፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ  የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች እየሰሩ እንደሚኖሩ ሁሉ ኦሮሚያን ጨምሮ በሌሎች ክልሎች የተለያዩ ብሔር ተወላጆች ይገኛሉ፡፡

"ይህም ፌዴራላዊ ስርዓቱ ተባብሮ የማደግ መርህን የተከተለ በመሆኑ ነው "ብለዋል፡፡

የወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራን በተመለከተ በሁሉም የኦሮሚያ አካባቢዎች ወጣቶችን ማዕከል በማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በውይይቱ ከተሳተፉት መካከል አቶ አዳሙ ጅባታ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ  የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከክልሉ ነባር ብሔረሰቦች ጋር ተቀራራቢ ባህል እንዳላቸው በመጥቀስ በጋብቻም ተሳስረው እየኖሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ የኦሮሞ ተማሪዎች በኦሮሚያ ልማት ማህበር ስር በሚገኘው አዳሪ ትምህርት ቤት የመማር እድል እንዲያገኙ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በክልሉ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በቋንቋቸው እንዲማሩ ሁኔታዎች ሊመቻቹ እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ አቶ አሰፋ ተሬሳ ናቸው፡፡

ከአጎራባች የኦሮሚያ አካባቢዎች ወደ ክልሉ ለስራ የሚመጡ ስራ አጥ ወጣቶችን በአካባቢያቸው የሥራ እድል እንዲያገኙ የክልሉ መንግስት መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

ፕሬዝደንቱ በበኩላቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር ህገ መንግስታዊ መብት መሆኑን ጠቁመው በጉዳዩ ዙሪያ ከክልሉ መንግስት ጋር እንደሚነጋገሩበት ተናግረዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ባህር ዳር ግንቦት 30/2009 በአማራ ክልል ለዘንድሮው የመኸር እርሻ ልማት የሚውል ከ42 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአርሶ አደሮች ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡

የተፈጥሮ ማዳበሪያው የአፈር ለምነትን ጠብቆ በማቆየት ለምርት ዕድገት የጎላ ድርሻ እንዳለው የክልሉ ግብርና ቢሮ የአፈር ለምነት ባለሙያ አቶ አቢዮት መኮንን ለኢዜአ ገልፀዋል፡፡

ይህንኑ የተገነዘቡ የክልሉ አርሶ አደሮችም የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ በማዋል ላይ ናቸው፡፡

ለዘንድሮው የመኸር ልማት አገልግሎት እንዲውል ካዘጋጁት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው  ከ760 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ ማሳ ላይ ተበትኗል፡፡

ቀሪው በቀጣይ ለሚለሙ ሰብሎች ጥቅም ላይ ይውላል፡፡

የተፈጥሮ ማዳበሪያው ከአረንጓዴ ቅጠላቅጠል፣ ከሰብል ተረፈ ምርት፣ ከከብቶች እዳሪና ሌሎች በቀላሉ መዋሃድ ከሚችሉ ንጥረ ነገሮች መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ የጎምባት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አዲሱ መንግስቴ በሰጡት አስተያየት በየዓመቱ 20 ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማደበሪያ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ ያውላሉ፡፡

የተፈጥሮ ማደበሪያውን ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ጋር  አቀላቅለው በመጠቀም ቀደም ሲል በአንድ ሄክታር 10 ኩንታል ያገኙ የነበረውን የበቆሎ ምርት በእጥፍ ማሳደጋቸውን ገልፀዋል፡፡

የእርሻ መሬታቸውን ለማልማትም በየዓመቱ ለፋብሪካ ማዳበሪያ መግዣ ያወጡት የነበረን 14 ሺህ ብር በግማሽ እንዲቀንስ አስችሏቸዋል።

በዚሁ ወረዳ የተንታ ላጉና ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ወርቁ አስማረም  የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው በማሳቸው ላይ በመበተናቸው የአፈሩ ለምነት እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

በክልሉ ሁለት ሚሊዮን በሚጠጉ አርሶ አደሮች በየዓመቱ የሚዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንደሚያለማ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን