×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Tuesday, 06 June 2017

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2009 "ባክ ቱ ስኩል ኢትዮጵያ ኤክስፖ 2017" የተሰኘ የመጀመሪያው የትምህርት ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው።

ኤክስፖው ከነሀሴ 4 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ቀናት በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ይካሄዳል።

የኤክስፖው አዘጋጅ አቶ ሮቤል ከበደ እንደገለጹት በመላ አገሪቱ የሚገኙ ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች በኤክስፖው እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

የኪነ ጥበብና ሙዚቃ ትምህርት ቤቶች፣ የምርምርና ማሠልጠኛ ተቋማት፣ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የትምህርት ግብዓት አቅራቢዎችም ይሳተፋሉ።

ኤክስፖው ትምህርት ቤቶች ልምድ የሚለዋወጡበትና የጋራ የሥራ ትብብር መድረክ የሚያመቻቹበት ይሆናልም ነው ያሉት።

የትምህርት ዘርፉን እድገት የሚያንፀባርቅና የትምህርት አማራጮችን በጥራት በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ የሚያበረክት እንደሚሆንም ገልፀዋል አቶ ሮቤል።

ኢትዮጵያዊ መልክና ይዘት ያላቸውን ትምህርቶች ከዘመናዊዎቹ ጋር ማጣመርና ማቆራኘት የሚያስችሉ የመፍትሄ ሃሳቦች የሚነሱበትና የተለያዩ ኮንፍረንሶች የሚካሄዱበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

ኤክስፖው ኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ለትምህርት ያላቸውን አስተዋፅኦ በማሳየት ዘርፉን ለማጎልበት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የገለፀው ደግሞ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት አርቲስት ዳዊት ይፍሩ ነው።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ተወካይ አቶ የማነህ መኮንንም ኤክስፖው ሁሉም ትምህርት ቤቶች አካል ጉዳተኞችን ያካተተ ሁሉን አቀፍ ትምህርት እንዲሰጡና የመማር ማስተማሩ ሂደት ለእነሱ ምቹ እንዲሆን ግንዛቤ እንደሚያስጨብጥ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ባክ ቱ ስኩል ኤክስፖ "ደብተራ ግዕዛን 2009" ወይም የነፃነት ድንኳን በሚል ስያሜ የሚዘጋጅ ነው።

በቀጣይም ኤክስፖው በየዓመቱ እንደሚዘጋጅ ተገልጿል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2009 የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት መርኃ ግብር በኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ተቋማት አቅም ግንባታ ላይ የሚሰራ የ40 ሚሊዮን ዶላር መርኃ ግብር ይፋ አደረገ።

መርኃ ግብሩ ከተያዘው ወር ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት እንደሚቆይ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት መርኃ ግብር ተወካይ አሁና ኢዚአኮንዋ እንደተናገሩት መርኃ ግብሩ የዴሞክራሲ ተቋማት የተሻለ የአፈጻጸም አቅም እንዲኖራቸው ያስችላል።

ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ከተጠያቂነታቸው ጋር አገናዝበው የሚጠበቅባቸውን እንዲከውኑ የማስፈጸም አቅም እንደሚፈጥርላቸውም ጠቁመዋል።

የዴሞክራሲ ተቋማቱ ለመሥራት ያቀዷቸውን ወደ ሥራ በመለወጥ ኅብረተሰቡ በእነሱ ላይ ያለውን አመኔታ ከፍ ለማድረግ ይረዳቸዋልም ብለዋል።

መርኃ ግብሩ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ የሕዝብ ተሳትፎ እንዲጎለብትና ግልጸኝነትን በማስፈን ሁለንተናዊ እድገትን ለማስመዝገብ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። 

ተወካይዋ፤ መንግሥት በዘርፉ ያቀዳቸው እቅዶች ግባቸውን እንዲመቱ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት በኩል የመርኃ ግብሩ አስተዋጽዖ የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

ለመርኃ ግብሩ የመጀመሪያ ዙር ማስፈጸሚያ የሚውል የ5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በዛሬው ዕለት የተደረገ ሲሆን መርኃ ግብሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። 

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ በበኩላቸው መርኃ ግብሩ ከዓለም አቀፉና ከአገሪቱ የዘርፉ እቅድ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ተናግረዋል።

መርኃ ግብሩ በአግባቡ በታቀደለት የጊዜ ገደብ እንዲፈጸምና በዘርፉ ለውጥ ለማምጣት የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባባር እንደሚሰሩም ቃላቸውን ሰጥተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲሰ አበባ ግንቦት 29/2009 ወጣቶች በአደንዛዥ ዕፆች ሱስ እንዳይያዙና ማህበራዊ እሴቶችን ጠብቀው እንዲሄዱ የሃይማኖት አባቶች ሚናቸውን እንዲወጡ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽህፈት ቤት ሃላፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ ጠየቁ።

ጉባኤው "ከደባል ሱሶችና ከአደንዛዥ ዕፆች የጸዳ ጤናው የተጠበቀ ባለራዕይ ትውልድ ለከተማችን አዲስ አበባ ብሎም ለዓለማችን ሰላም ዘላቂ ልማትና እድገት ያለው ፋይዳ" በሚል መሪ ሃሳብ የምክከር መድረክ አካሄዷል።

በምክክር መድረኩ "አደንዛዥ ዕፆች ተጠቃሚነትና ሱሰኝነት በትውልድ ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት" የሚል ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የከተማዋ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ወጣቶች በስነ ምግባር ታንጸው አገር የመረከብ ሚናቸውን በብቃት እንዲወጡ የሃይማኖት አባቶች ምክርና ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከየካ ክፍለ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የመጡት ሃጂ ሲራጅ ደባ እንደተናገሩትም የሃይማኖት አባቶች ወጣቶችን በእምነት አስተምህሮ በማነጽ በአደገኛ ሱሶች እንዳይያዙ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል።

ከሃይማኖት አባቶች በተጨማሪም ወላጆች የልጆቻቸውን አዋዋል በቅርበት መከታተል እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

በልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ሃላፊ ኮማንደር ርስቱ ታመነ በበኩላቸው "ከሱስ ጋር ተያይዞ አሁን ያለው የከተማዋ ወጣቶች ሁኔታ አደገኛ ሲሆን ችግሩን ለመቅረፍ የጸጥታ ሃይሎች ከጉባኤው ጋር በጋራ ይሰራሉ" ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ከችግሩ ስፋት አንጻር መሰል መድረኮች በቀጣይነት ሊካሄዱ እንደሚገባና የሃይማኖት አባቶችም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ከሁሉም ቤተ እምነቶች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችና ከክፍለ ከተሞች የመጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2009 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የታክስ ማጭበርበርን ለመከላከልና ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት ከተለያዩ አገራት ጋር ስምምነት የተደረሰባቸውን ረቂቅ አዋጆች ለዝርዝር እይታ ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መራ።

ምክር ቤቱ የስምንት አገራትን ረቂቅ አዋጆች በጥልቀት ከመረምረ በኋላ ነው ለቋሚ ኮሚቴው የመራው።

የአገሪቱ ህግ ሆነው እንዲወጡ የተዘጋጁት ረቂቅ አዋጆቹ ከፖላንድ፣ ስሎቫክ፣ ፍልስጤም፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር፣ ሞሮኮ፣ ቆጽሮስና ሞዛምቢክ ጋር ስምምነት ተደርሶባቸው የተፈረሙ ናቸው።

በስምምነቶቹ በአንድ አገር ነዋሪ የሆነ ሰው ወይም ኩባንያ በሚኖርበትም ሆነ በሚሰራበት አገር ባገኘው ገቢ ታክሱን ለዚያው አገር እንዲከፍል የሚስችሉ ናቸው።

በተጨማሪም ነዋሪው ወይም ኩባንያው ከማይንቀሳቀስ ንብረት የሚከፈለውን የገቢ ግብር ንብረቱ በሚገኝበት አገር ብቻ እንዲሰበስብ  የሚያደርግ ነው።

በተወሰኑ የገቢ አይነቶች የገቢው ምንጭ የሆነው ኩባንያ ባለቤት አገር ታክሱን እንዲሰበስብ የሚያስችል መሆኑን ረቂቅ አዋጆቹ ደንግገዋል።

በተጨማሪም የገቢው ምንጭ ለሆነው አገርም በስምምነቱ በተወሰነው የታክስ ምጣኔ መሰረት ታክስ እንዲከፍል የሚደነግጉ አንቀጾች በአዋጆቹ ተካተዋል።

ስምምነቶቹ የስምንቱም አገር ነዋሪዎች አንዱ በሌላው የሚፈጽሙት ኢንቨስትመንት የሰመረ እንዲሆን ለማድረግ እንዲሁም ተደራራቢ ግብርን በማስቀረት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ መሆናቸው ታምኖበታል።

በተለይም ከበለጸጉ አገሮች በመልማት ላይ ወደሚገኙ የሚደረግ የኢንቨስትመንትና የካፒታል ፍሰት እንዲሁም የቴክኖሎጂ፣ የእውቀትና ክህሎት ሽግግር እንዲፈጠር የሚያግዙም ናቸው።

በተጨማሪም የማምረት አቅም ከፍ እንዲል፣ ለዜጎች የስራ እድል እንዲፈጠርና በውጭ ገበያ የሚኖረው ተሳትፎ እንዲጨምር ለማድረግም ያስችላሉ ነው የተባለው።

 

Published in ኢኮኖሚ

አሶሳ ግንቦት 29/2009 በክረምት ወራት አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ እንዳይከሰት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ  ክልል  ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ባለፈው ዓመት በአራት ወረዳዎች ውስጥ የአተት በሽታ መከሰቱን ያስታወሱት በቢሮው የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ጌታቸው አበበ ዘንድሮ ግን እስካሁን በሽታው እንዳልታየ ገልጸዋል፡፡ 

በሽታው ከተከሰተም በአፋጣኝ ለመቆጣጠር የሚስችሉ የህክምና ግብአቶች እየተሟሉ መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

"የተለያዩ ተቋማትን በአባልነት ያካተት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በሽታው እንዳይከሰት ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተከናወነ ይገኛልም "ብለዋል፡፡

እስካሁን ድረስ በክልሉ በሽታው ባይከሰትም በአጎራባች ክልሎችና አጎራባቹ  ደቡብ ሱዳን መታየቱን መረጃዎች እንዳሉ ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

"ባለው የሰዎች ዝውውር በሽታው ወደ ክልሉ እንዳይዛመት በትኩረት እየተሰራ ነው"  ብለዋል፡፡

በሽታው በአይን በማይታዩ ተዋሲያን የሚከሰት በመሆኑ የግልና የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ፣  ምግብ ከማዘጋጀት፣ ከማቅረብና ከመመገብ በፊት እጅን መታጠብ ሊደረጉ ከሚገባቸው ጥንቃቄዎች መካከል እንደሆኑ ባለሙያው ጠቅሰዋል፡፡

የህመሙ ምልክቶች ሲያጋጥም የህክምና እርዳታ እስኪገኝ ድረስ ስምንት ማንኪያ ስኳር እና ግማሽ ማንኪያ ጨው በውሃ አፍልቶና አቀዝቅዞ መውሰድ አማራጭ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2009 ለሃጅ ተጉዘው በሳዑዲ በስደተኝነት የሚቀሩ ዜጎችን ቁጥር ለመቀነስ መንፈሳዊ መሃላና የገንዘብ መያዣ መስፈርቶች ሆነው ሥራ ላይ መዋላቸውን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።

ከስምንት ሺህ ወደ 15 ሺህ ባደገው የመንፈሳዊ ጉዞ ድርሻ ለመጓዝ እስካሁን በተለያዩ ክልሎች አራት ሺህ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከመካከላቸው 700 የሚሆኑት ትክክለኛ ተጓዦች መሆናቸው ተረጋግጧል።

የዘንድሮው የአንድ ሺ 438ኛ ዓመት ሂጅራ የሃጅ ተጓዞች ምዝገባ እየተካሄደ ነው።

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ ሙሃመድ-አሚን ጀማል-ዑመር ዛሬ እንዳስታወቁት ለመንፈሳዊው የሃጅ የፀሎት ጉዞ ከአገር ወጥተው ለስደት የሚዳረጉ ዜጎችን ቁጥር ለመቀነስ ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች የሆኑ ተጓዦች 100 ሺህ ብር ያሲዛሉ።

ከ2008 ዓ.ም በፊት በነበሩ መንፈሳዊ ጉዞዎች ከ800 እስከ አንድ ሺህ፣ በ2008 ዓ.ም ደግሞ 200 ተጓዦች በዚያው መቅረታቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ የአሁኖቹ ተጓዦች መንፈሳዊ መሃላ እንደሚጠብቃቸው አስታውቀዋል።

ሼህ ሙሃመድ፤ የሳዑዲ መንግስት የመኖሪያና የስራ ፍቃድ የሌላቸው የውጭ አገር ዜጎች ከሚላቸው መካከል በመንፈሳዊ ጉዞው የሄዱ እንደሚገኙበት ነው የተናገሩት።

የዘንድሮው መንፈሳዊ ተጓዦች ቁጥር ወደ 15 ሺህ ያደገ ቢሆንም ቁጥሩን የሚመጥን ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የተጓዦች ማረፊያ፣ የሚያገኙት አገልግሎት፣ የደህንነት ጥንቃቄዎችና ቆይታቸውን የመሳሰሉ የጋራ ኃላፊነት ጉዳዮች ላይ ከሳዑዲ መንግስት ጋር ስምምነት ተፈፅሟል።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመምከርም ከዚህ በፊት ሲከሰቱ የነበሩ የጉዞ መዘግየትና ሌሎች ችግሮች እንዳያጋጥሙ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ከሌላው ጊዜ በተለየና በፍጥነት የሚጠናቀቅ በቴክኖሎጂ የታገዘ የምዝገባ ሂደት መዘርጋቱንም ሼህ ሙሃመድ ገልፀዋል። 

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ ግንቦት 29/2009 በጋምቤላ ክልል እየተሰጠ ባለው ሀገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ለማጭበርበርና ለመኮረጅ  ሲሞክሩ የተደረሰባቸው 24 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ የፈተና ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።

የፈተና ኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማህበር ኮር ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል 20 ግለሰቦች በተለያዩ የፈተና ጣቢያዎች ለጓደኛና ለዘመድ ለመፈተን ተመሳስለው ለመግባት የሞከሩ ናቸው፡፡

ቀሪዎቹ አራት ተማሪዎች ደግሞ  ሞባይል ይዘው በመግባት ፈተና ለመኮረጅ ሲሞክሩ የተደረሳባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከእነዚህ መጠነኛ ችግሮች በስተቀር በክልሉ በሚገኙ 13 ጣቢያዎች ፈተናው በተረጋጋ ሁኔታ ያለ ምንም ችግር እየተሰጠ መሆኑን ነው የተናገሩት ሰብሳቢው ።

በቀጣይም ከክልል እስከ ወረዳ የተቋቋመው የፈተና ኮማንድ ፖስት ቀሪ የ12ኛና የ8ኛ ክፍል ፈተናዎች ያለምንም ችግር ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል አቶ ማህበር።

የጋምቤላ ከፍተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት ፈተና ጣቢያ አስተባበሪ አቶ ደረጃ ኃይለማሪያም በሰጡት አስተያየት  ለተማሪዎች አስፈላጊውን ማብራሪያ በመስጠት ፈተናውን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን  ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በትናንትናው ዕለት የተሰጣቸውን ማብራሪያና ገለፃ  በመጣስ  ወደ ፈተና ክፍል ሞባይል ደብቀው በማስገባት ለመኮረጅ ሲሞክሩ የተገኙ አራት ተማሪዎች ከፈተና ተሰርዘው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል በሚገኙ 13 የፈተና ጣቢያዎች ከሶስት ሺህ 200 በላይ ተማሪዎች ሀገር አቀፉን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና በመውሰድ ላይ ናቸው።

Published in ማህበራዊ

ጎንደር ግንቦት 29/2009 በአጎራባች ዞኖች የተከሰተው ተምች ወደ ሰሜን ጎንደር እንዳይዛመት ለመከላከል  ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ግዛት ጀመረ ለኢዜአ እንደገለጹት  ተምች  እስካሁን በዞኑ ባይከሰተም አጎራባች በሆነው የደቡብ ጎንደር ዞን በዚህ ሳምንት መከሰቱን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ተምቹ ተዛምቶ ጉዳት ሳያደርስ አስቀድሞ መከላከል እንዲቻልም በየደረጃው የተዋቀረ ኮሚቴ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የማሳ ላይ የተባይ አሰሳንና ለአርሶአደሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በመከናወን ላይ ነው፡፡

እስካሁንም ከ200 ለሚበልጡ ባለሙያዎች ስለ ተባዩ መዛመቻና መከላከያ መንገዶች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ከአቅም በላይ ከሆነም የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ለተባይ መከላከያ ርጭት የሚውል ኬሚካል በህብረት ስራ ማህበራት በቂ ክምችት መኖሩን ጠቁመው፤ "የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት መድኃኒት ጥቅም ላይ እንዳይውል ተገቢው ክትትል ይደረጋል "ብለዋል።

የአለፋ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ተላይነህ እንዳሉት ተባዩ ቢከሰት አስቀድሞ መቆጣጠር እንዲቻል በበራሪ ወረቀቶችና በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች የታገዘ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለአርሶአደሩና ለሙያተኛው ተሰጥቷል፡፡

የመከላከሉ ስራ በኬሚካል ጭምር መቆጣጠር እንዲቻልም በቂ የጸረ ተባይ መድኃኒትና የመርጫ መሳሪያዎች ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

"ተምቹ ወደ ወረዳችን ገብቶ ጉዳት እንዳያደርስ የበቆሎ ማሳዬን እለት በእለት አሰሳ እያደረኩ እገኛለሁ "ያሉት ደግሞ በአለፋ ወረዳ በቆሎ አምራች የሆኑት አርሶአደር መርሻ መኩሪያው ናቸው፡፡

የደንቢያ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር ገላዬ ጫኔ በበኩላቸው "ተምች ስለ ሚያደርሰው ጉዳትና የመከላከያ ዘዴው በግብርና ጣቢያ ባለሙያዎች በቂ የግንዛቤ ትምህርት ወስጃለሁ "ብለዋል፡፡

በዞኑ አለፋ ፣ደንቢያ ፣ጣቁሳ ፣ጭልጋና ላይአርማጭሆ ወረዳዎች ለበቆሎ ልማት ተስማሚ አካባቢዎች ናቸው፡፡

በወረዳዎቹ በተያዘው  ክረምት 40ሺ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በበቆሎ ተሸፍኗል፤ ከዚህም  ከ2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2009 የዓለም ኅብረት ስራ ማኅበራት ቀን በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት መዲና ሐዋሳ በመጪው ዓርብ ይከበራል።

በዓሉ "የኅብረት ስራ ማኅበራት ሁሉ አቀፍ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣሉ" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ለሁለት ቀናት እንደሚከበር የገለፀው የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ነው።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር በዓሉን አስመልከተው በሰጡት መግለጫ በዓሉ የኅብረት ስራ ማኅበራት የአባላትን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ የሚያደርጉት ጥረት የሚጠናከርበት ነው።

ማኅበራት እርስ በእርሳቸው ልምድና ተሞክሮ በመለዋወጥ አቅማቸውን የሚያሳድጉበት መድረክ እንደሚሆንም ገልፀዋል።

ኅብረት ስራ ማኅበራት በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ውስጥ ያበረከቱት አስተዋጽኦ በበዓሉ እንደሚንጸባረቅ ጠቁመው ህብረተሰቡ ስለ ማኅበራቱ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ረገድም የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ዕለቱ በዓመቱ በስራ አፈጻጸማቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ማኅበራት፣ አመራሮችና ፈጻሚዎች የማበረታቻ ሽልማት የሚሰጥበትም ነው።

የዓለም ኅብረት ስራ ማኀበራት ቀን በዓለም ለ95ኛ፤ በኢትዮጵያ ደረጃ ደግሞ ለ9ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው።

በኢትዮጵያ ከ15 ሚሊዮን በላይ አባላትን ያፈሩ ከ79 በላይ መሰረታዊ የኅብረት ስራ ማኅበራት ያሉ ሲሆን፤ 370 የኅብረት ስራ ዩኒየኖችና አራት የኀብረት ስራ ፌዴሬሽኖችም ተቋቁመዋል።

የኅብረት ስራ ማኅበራቱ በአጠቃላይ 19 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማፍራት መቻላቸውን ከኤጄንሲው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ሶዶ ግንቦት 29/2009 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በዳውሮ ዞን በሚቆይባቸው  አስር ቀናት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡፡

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግድቡ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ አበበ አታሮ ለኢዜአ እንደገለጹት ዋንጫው ትናንት ከካፋ ዞን  ዳውሮ  ሲገባ ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

"ዋንጫው በዞኑ በሚኖረው የአስር ቀናት ቆይታ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ይሰበሰባል" ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከልማት ቡድን ጀምሮ የተለያዩ ማህበራትና ተቋማት ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተው ይሰበሰባል ካሉት በላይ ለመፈጸም ጠንክረው እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

ዋንጫው በዞኑ ገና ወረዳ በነበረው የአንድ ቀን ቆይታም ስጦታን  ሳይጨምር ከ9 ሚሊየን ብር በላይ በመሰብሰብ ዛሬ ወደ ቀጣዩ ሎማ ወረዳ ማቅናቱንም ጠቁመዋል፡፡

በዳውሮ በሚገኙ አምስት ወረዳዎችና አንድ ከተማ አስተዳደር የሚያደርገውን ቆይታ ሲያጠናቅቅ ሰኔ 6/2009 ዓ.ም በዞኑ ዋና ከተማ ተርጫ የማጠቃለያ ፕሮግራም እንደሚኖር ተገልጿል፡፡

በተርጫ ከተማ የመናኸሪያ ሠራተኛ የሆኑት አቶ አበበ አባቴ እስካሁን በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም ከሁለት ሺ ብር በላይ ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡

"ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተሳትፎ ማድረግ ለትውልድ ታሪክ የሚሰራበትን አጋጣሚ መጠቀም ነው" ያሉት ደግሞ በከተማው በሆቴል ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ ጌታቸው ሽፈራው ናቸው፡፡

እስካሁን የአምስት ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውንና ዋንጫው ተርጫ ሲመጣም የ50 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዳውሮ ዞን እስካሁን ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ የሚውል ከ23 ሚሊየን ብር በላይ ተሰብስቧል፤  የመንግስት ሰራተኞችም  ለሶስተኛ ጊዜ በወር ደመውዛቸው ቦንድ ለመግዛት ወስነው ወደ ተግባር መሸጋገራቸውን ከዞኑ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን