×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Monday, 05 June 2017

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2009 በሳዑዲ ዓረቢያ ህጋዊ የመኖሪያና የስራ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች መብታቸው እንደተከበረ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ጥሪ አቀረቡ።

ሳዑዲ ዓረቢያ ህጋዊ የመኖሪያና የስራ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ አገር ዜጎች እንዲወጡ የሰጠችው ጊዜ ሊያበቃ የቀረው ከሶስት ሳምንት ያልበለጠ  በመሆኑ እድሉን እንዲጠቀሙ አሳስበዋል። 

አገሪቷ የውጭ አገር ዜጎች በሶስት ወር ጊዜ እንዲወጡ ማወጇን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት በዚያ የሚገኙ ዜጎቹን በሠላማዊ መንገድ ወደ አገራቸው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነው።

ሚኒስትሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ከ50 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የጉዞ ሰነድ የወሰዱ ሲሆን ከመካከላቸው ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደአገር ቤት ተመልሰዋል።

ይሁን እንጂ ከሚጠበቀው አንፃር ቁጥሩ ዝቅተኛ በመሆኑ ዜጎች አሁንም ባለው ጊዜ የጉዞ ሰነድ በመውሰድ በሠላም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።

ሳዑዲ ዓረቢያ ያስቀመጠችው የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ ዜጎችን ለመመለስ ኢትዮጵያውያኑ ከሄዱባቸው አካባቢዎች ግብረ ኃይል በማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያኑን በተሰጠው ጊዜና ፍጥነት ለመመለስ ወደ ሳዑዲ ተጨማሪ በረራዎችን ለማድረግ "ለአገሪቱ መንግስት ጥያቄ አቅርበን ምላሽ እየጠበቅን ነው" ብለዋል።

ዜጎች መብቶቻቸው ተጠብቆ እንዲመለሱ ለማድረግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ከሳዑዲ መንግስት ጋር ምክክር ተደርጓል።

ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ በሚፈልጉት የስራ መስክ እንዲሰማሩ መንግስት ዝግጅት ማድረጉንም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

በሌላ በኩል በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ድርቅ የመከላከሉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

እየጣለ ባለው ዝናብ በአንዳንድ አካባቢዎች የውሃ እጥረቱ የተቃለለ ቢሆንም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና በአፋር ክልል አምስት ወረዳዎች ውሃ በቦቴ የማቅረቡ ስራ መቀጠሉን ገልፀዋል።

ድርቁን በዘላቂነት ለመፍታትም ከተለያዩ ሴክተሮች የተውጣጡ ባለሙያዎች ወደ ስፍራው በመሄድ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አክለዋል።

ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑት ምገባ እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል።

Published in ማህበራዊ

አክሱም ግንቦት 28/2009 ኢትዮጵያ ያላትን የእንስሳት ሃብት በዘመናዊ መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችላት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የፌደራል  ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።

ስለፍኖተ ካርታው ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀው ውይይት  በአክሱም ከተማ በተካሄደበት ወቅት እንደተገለጸው ማዕከሉ ባደረገው ጥናት የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ተቋማዊ ብቃትና ቅንጅታዊ አሰራርን ለመፍጠር ያስችላል፡፡

በውይይቱ ወቅት በማዕከሉ የእንስሳት ተመራማሪ ዶክተር ገብረ ዮሐንስ ብርሃነ "ሀገሪቱ ስላላት የእንስሳት ሃብትና ክምችት ሙሉ የዳሰሳና ጥናት ተደርጓል "ብለዋል።

ፍኖተ ካርታው ያለውን ሰፊ የእንስሳት ሃብት ወደ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለመቀየር አሰራርን፣ፕሮግራምና አጠቃቀምን የተመለከተ አቅጣጫ የሚያሳይ ነው።

በትግራይ ፣ በአማራ ፣ በኦሮሚያ ፣ በደቡብ ህዝቦች ፣ በኢትዮጵያ ሶማሌና  በአፋር ክልሎች በሚገኙ 18 ዞኖች እምቅ የእንስሳት፣ የመኖ፣የውሃ ፣የግጦሽ መሬትና የስኳር ፋብሪካ ተረፈ ምርት ክምችት በፍኖተ ካርታው ተለይቶ ተቀምጧል።

"በገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ከሌሎች ሀገራት መልካም ተሞክሮ ተወስዷዋል " ያሉት ዶክተር  ገብረ ዮሐንስ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት  የዝርያ ማሻሻል፣የመኖ ልማት ማስፋፋትና የእንስሳት ጤና ፕሮግራም የመቅረጽ ስራ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡

እንደ ዶክተር  ገብረዮሐንስ  ገለጻ፣ ፍኖተ ካርታው በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጨረሻ ላይ ወደ አውሮፓ ህብረት ጥራቱን የጠበቀ የስጋ ምርት ለመላክ ያስችላል።

ፍኖተ ካርታው ሀብቱን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል፣  ህገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድን ለመከላከልና የኳራንቲን  ስርዓት ለማጠናከር እንደሚረዳ የንግድ ሚኒስቴር ገልጿል።

በሚኒስቴሩ የወጪ ንግድ መረጃና ምክር አገልግሎት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ዶክተር ይበልጣል አሰፋ እንዳሉት  የእንስሳት ሃብት ትልቅ የኢኮኖሚ እድገት ምሰሶና የውጭ ምንዛሪን የሚያሳድግ ዘርፍ ነው።

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጨረሻ ከወጪ ንግድ የሚጠበቀውን  13 ነጥብ 9 ቢሊዮን  ዶላር ለማሳካት ፍኖተ ካርታው አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት ዶክተር ይበልጣል።

ዶክተር ይበልጣል እንዳመለከቱት የቁም እንስሳትን ጨምሮ ለወጪ ንግድ ማነቆ የሆነው ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ ከማንድ ፖስት ተቋቁሞ እየተሰራ ነው፡፡

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀውና ትናንት በተጠናቀቀው  ውይይት  ከክልሉና ከፌደራል የተውጣጡ የግብርናና ገጠር ልማት ባለሙያዎች፣የህብረት ስራ ማህበራት፣ የንግዱ ማህበረሰብና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2009 ኢትዮጵያና ኡጋንዳ ባላቸው ግንኙነት ለቀጣናው ሠላምና መረጋጋት ከፍተኛ አበርክቶ እንደነበራቸው አምባሳደር ሙል ካቴንዴ ገለፁ።

ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ቆይታቸውን ላጠናቀቁት በኢትዮጵያ የኡጋንዳ አምባሳደር ሙል ካቴንዴ አሸኛኘት አድርገውላቸዋል።

አምባሳደር ካቴንዴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ሁለቱ አገራት የቀጣናውን ሠላምና መረጋጋት ለማስጠበቅ በጋራ ውጤታማ ስራ ሰርተዋል።

በሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ሠላምና መረጋጋትን ለማስፈን በግል ከሰሯቸው ይልቅ በጋራ ያከናወኗቸው ተግባራት የሠላም አስከባሪ ወደ ሶማሊያ እስከመላክ የደረሰ እንደነበር አውስተዋል።

ከሠላም ማስከበር ባለፈም አገራቱ በውትድርናው ዘርፍ በጋራ መንቀሳቀሳቸውንና ኢትዮጵያ ለኡጋንዳ የሠላም ኃይሎች የውትድርና ሳይንስ ስልጠና መስጠቷን አክለዋል።

ከዚህ ባሻገር በንግድ ዘርፍ በትብብር ለመስራት ሊያስተሳስራቸው የሚችል መሰረተ ልማት አለመኖር በዘርፉ የተሻለ እንዳይሰሩ አድርጓቸዋል።

እ.ኤ.አ በ2014 እና 2016 ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በነበራቸው ምክክር ጉዳዩን በስፋት የተወያዩበት መሆኑን አስታውሰዋል አምባሳደር ካቴንዴ።

ይሁንና ችግሩን ለመቅረፍ አገራቱን በመንገድና በባቡር ለማስተሳሰር የተስማሙ መሆኑ ግንኙነታቸው በተለያዩ ዘርፎች እንዲሆን ያደርገዋል ነው ያሉት። 

የኢትዮጵያና ኡጋንዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በአውሮፓዊያኑ ዘመን አቆጣጠር 1970 መጀመሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

Published in ፖለቲካ

ነቀምት ግንቦት 28/2009 በሆሮ ጉዱሩ ወለጋና በምስራቅ ወለጋ ዞኖች የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ ሲካሄድ ውሏል፡፡

በአንድ ጣቢያ የፈተና ወረቀት እጥረት አጋጥሞ ነበር።

የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተናው እየተካሄደ ያለው  በሁለቱ ዞኖች በሚገኙ 32 የፈተና ጣቢያዎች  መሆኑን የየዞኑ የፈተናዎች ክላስተር አስተባባሪዎች ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

እንደአስተባባሪዎቹ ገለጻ ዛሬ የተጀመረው የፈተናው አሰጣጥ ሂደት  በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ ተካሂዷል፡፡

በሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን  በአሙሩ ወረዳ የአገምሣ መሰናዶ ትምህርት ቤት በዛሬው ጠዋት የእንግሊዝኛ ፈተና 51 የጥያቄ ወረቀቶች ጉድለት አጋጥሞ ነበር ።

የዞኑ የፈተናዎች ክላስተር አስተባባሪ አቶ ዳኜ አሰፋ እንዳሉት ጉዳዩን ወዲያውኑ ለኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ፣ለአገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲና ለትምህርት ሚኒስቴር  አሳውቀው ከሌላ መሰናዶ ትምህርት ቤት ትርፍ ወረቀት ተፈልጎ ችግሩ እንዲፈታ ተደርጓል ።

የአገምሣ መሰናዶ ትምህርት ቤት የፈተና ጣቢያ ሃላፊ መምህር ተስፋዬ ታደሰ  በሰጡት አስተያየት የፈተና ወረቀቱን የያዘው  ኮሮጆ  28 ፖስታዎች የያዘ  የሚል ፅሁፍ ቢለጠፍበትም በውስጡ የተገኘው ግን ከዚያ ያነሰ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ያጋጠመው እጥረት በመስተካከሉ ተማሪዎች ፈተናውን  እንዲወስዱ  መደረጉን ተናግረዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዳማ ግንቦት 28/2009 በመዘናጋት በሀገሪቱ እያንሰራራ የመጣውን የኤች አይቪ/ኤድስ ስርጭት ለመግታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ተጠየቀ።

የኤች አይቪ ኤድስ ዘርፈ ብዙ ምላሽ የ2009 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ግምገማና የቀጣዩ ዘመን እቅድ ላይ የሚመክር አውደ ጥናት ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ አውደ ጥናቱ ሲጀመር እንደገለጹት  በአሁኑ ወቅት ኤች አይ ቪ/ኤድስ እያንሰራራ መምጣቱን ጥናቶች ያመለክታሉ።

ለበሽታው ማንሰራራት በዋናነት የሚጠቀሱት በሁሉም አካላት ዘንድ ከኤች አይቪ መከላከልና መቆጣጠር ጋር ተያይዞ መዘናጋት በመፈጠሩ ነው።

"ያለፉትን ልምዶች በመጠቀም ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ የሆኑ ስልቶችን በመንደፍ ልንሰራ ይገባል"ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት የህብረተሰቡን ተሳትፎ በላቀ ደረጃ በማሳደግ እንደአውሮፓ አቆጣጠር  እስከ 2030 ድረስ ከበሽታው ነፃ የሆነ ትውልድ ለማፍራት ግብ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።

ለዚህ ስኬት የህዝብ አደረጃጀቶችን መጠቀም፣በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኤች አይቪ ምርመራ አገልግሎትንና የኮንዶም ስርጭትን ማስፋፋት ላይ ይሰራል፡፡

ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ሁሉም እናቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የክትትልና ድጋፍ ስራን በማጠናከር ለሀገራዊ ራዕይ መሳካት ርብርብ እንደሚረዳም አመልክተዋል።

ከ15 ዓመት በፊት በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቶ የነበረውን የበሽታው ስርጭት በመቀነስ ረገድ የጤና ዘርፍ፣ የኤች አይቪ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት፣ሲቪል ማህበራት፣የግልና የመንግስት ድርጅቶች፣መገናኛ ብዙሃን፣አጋር ድርጅቶችና አመራሩ የማይተካ ሚና እንደነበራቸውም አውስተዋል።

አሁን ላይ  በመዘናጋት እያንሰራራ የመጣውን የኤች አይቪ/ኤድስ ስርጭት በመግታት  በጋራ የተመዘገቡትን ውጤቶች ቀጣይነት ለማረጋገጥ ሁሉም ባለደርሻ አካላት በላቀ ቁርጠኝነት እንዲረባረቡም ጠይቀዋል።

የፌደራል  ኤች አይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ  ሻሎ ዳባ በበኩላቸው ከቅርብ ጊዜ  ወዲህ  ኤችአይቪን  መከላከሉ ስራ  ላይ ከአመራሩ ጀምሮ  እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ የበሽታው ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት በነፃ ከተዳረሰ ወዲህ በሁሉም ወገን  በሽታው እንደ ችግር  አይታይም።

" በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት ሀገሪቱ አሁንም በበሽታው ችግር ውስጥ  ስለምትገኝ   ሃብት  በማሰባሰብ  ሁላችንም  ልክ እንደከዚህ በፊቱ  እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንሰራ  ግድ  ይላል" ብለዋል።

በአውደ ጥናቱ  የቀረበው ሪፖርት እንደሚያስረዳው  የበሽታውን  ስርጭት ለመከላከል  ባለፉት 9 ወራት 122 ሚሊዮን ኮንዶም  በሀገሪቱ  የተሰራጨ ሲሆን ከአራት  ሚሊዮን  ለሚበልጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል።

ለአምስት ቀናት በሚቆየው አውደ ጥናት  ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳይ 

ቋሚ  ኮሚቴ አባላት፣ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ  ባለድርሻ አካላትና አጋር  ድርጅቶች  እየተሳተፉ ነው፡፡

Published in ማህበራዊ

ሚዛን ግንቦት 28/2009 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በካፋ ዞን ባደረገው የ15 ቀናት ቆይታ የዞኑ ህብረተሰብ ከ72 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ፡፡

ዋንጫው ከግንቦት 12 ቀን 2009 ጀምሮ በዞኑ በሚገኙ 10 ወረዳዎችና አንድ የከተማ አስተዳደር ሲዘዋወር ቆይቶ ትናንት ወደ ዳውሮ ዞን ተሸኝቷል፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ እንደተናገሩት ዋንጫው በየአካባቢው መዘዋወሩ ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ አሻራውን እንዲያኖር  እድል ፈጥሯል፡፡

የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስራት መኩሪያ በበኩላቸው ዋንጫው ወደ ዞኑ ሲገባ 58 ሚሊዮን 986 ሺህ ለመሰብሰብ ታቀዶ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

ዋንጫው በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በተዘዋወረባቸው 15 ቀናት ውስጥ የህብረተሰቡ ተነሳሽነት በመጨመሩ በቦንድ ግዢ ከ72 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ ከእቅድ በላይ ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በዞኑ የጠሎ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሳህለ ገብረሥላሴ እስካሁን ለግድቡ ግንባታ የ20 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውንና እስከፍጻሜው ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

በማህበርና በግል እስከ 11ሺ ብር ቦንድ መግዛታቸውን የተናገሩት አካል ጉዳተኛ አቶ ጌታቸው ፍቅሬ በበኩላቸው የህዳሴ ዋንጫው ወደ ዞናቸው መምጣቱ ሁሉም የሚችለውን እንዲያበረክት ዕድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡

ዋንጫው የካፋ ዞን ቆይታውን አጠናቆ ወደ ዳውሮ ዞን የተሸኘ ሲሆን በክልሉ እስካሁን ባደረገው ቆይታ ከ895 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዢ ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

 አዲስ አበባ ግንቦት 28/2009 በኢትዮጵያ ያለው አምራች ኃይል ምርታማነቱ  አነስተኛ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ፤ የማምረቻ ኢንዱስትሪው አዲስነትና የስልጠና ጥራት ማነስ በምክንያትነት ተጠቅሷል።

 በአፍሪካ መዋቅራዊ ለውጥ ለማፋጠን የሚሰራው የአፍሪካ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ማዕከል በዘጠኝ አገራት ላይ ያስጠናውን ጥናት ይፋ አድርጓል።

በጥናቱ እንደተመለከተው በኢትዮጵያ ያለው ኢንዱስትሪ በአነስተኛ ክፍያ የሰውና የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት ቢችልም ምርታማነቱን የሚፈታተነው የአምራቾቹ የአቅም ማነስና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ አለበት።

ጥናቱ ከተመለከታቸው ዘጠኝ አገራት የኢትዮጵያ አምራቾች ምርታማነት በተሻለ ሁኔታ 12 በመቶ እያደገ መሆኑን ጥናቱን ያቀረቡት የኦቨርሲስ ዴቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ኔይል ባልቺን ይናገራሉ። 

ጥናቱ በአገሪቱ ያለው ትምህርት፣ ስልጠናና የአገልግሎት አሰጣጥ ምርታማነትን ሊያሳድግ በሚችል ሁኔታ ሊቃኝ እንደሚገባም መክሯል።

መሰረተ ልማትና ንግድን ለማሳለጥ የሚያግዙ አቅርቦቶችን ጥራት በማሻሻል ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የወጪ ንግድን መሰረት ያደረገ የአምራች ዘርፍ የውጭ ኢንቨስመንትን መሳብ እንደሚገባም ጠቁሟል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ሚኒስትር ዶክተር አርከበ እቁባይ በኢትዮጵያ ያለው የሰው ኃይል የአቅም ማነስ ችግር እንዳለበት አምነው በሂደት በትምህርትና ስልጠና ይቀረፋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ብዙ ህዝብ ካላት ናይጄሪያ ቀጥላ ከፍተኛ የአገር ውስጥ ሸማች ያለባት አገር መሆኗን ያስታወሰው ጥናቱ ኬንያ በአንጻራዊነት የመሰረተ ልማትና የምርት ልህቀት ጥራት ላይ የተሻለች መሆኗን መስክሯል።

አጠቃላይ የጥናቱ ትንተና እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጄሪያና ዛምቢያ የወጪ ንግድ ላይ የሚሰሩ ቀጥተኛ የውጪ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ የተሻሉ ናቸው።

­ጥናቱ የተደረገው በዛምቢያ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሞዛምቢክ፣ ጋና፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳና ሩዋንዳ ነው።

Published in ኢኮኖሚ

ጎባ ግንቦት 28/2009 በባሌ ዞን የተረከቡትን ቦታ ሳያለሙ ከአስር ዓመታት በላይ አጥረው ባስቀመጡ ስድስት ባለሀብቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ፡፡

በባለሀብቶቹ ላይ እርምጃ የተወሰደው የተረከቡትን 950 ሄክታር መሬት በገቡት ውል መሰረት ባለማልማታቸው እንደሆነ የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደምሴ ለኢዜአ ገልፀዋል፡፡

በዞኑ ሲናና፣ ዳዌ ቃቸን፣ ደሎ መናና በርበሬ ወረዳዎች ባለሀብቶቹ ለግብርናና ሆቴል ኢንቨስትመንት እንዲውል የተረከቡትን ይህንኑ መሬት ተነጥቀው ወደ መሬት ባንክ ገቢ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ጽህፈት ቤቱ ይሄንን እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ባለሀብቶቹ በውሉ መሰረት ወደ ሰራ እንዲገቡ ተደጋጋሚ የምክር፣ ድጋፍና  የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ቢፃፍላቸውም ወደ ስራ መግባት ባለመቻለቸው እርምጃው መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

ከባለሃብቶች  የተነጠቀው ይሄው መሬት በግብርናና በሆቴል አገልግሎት ለሚሰማሩ ልማታዊ ባለሀብቶችና በዘርፉ ለሚደራጁ ስራ አጥ ወጣቶች እንደሚከፋፈልም አረጋግጠዋል፡፡

በዞኑ ደሎ መና ወረዳ በግብርና ኢንቨስትመንት ከተሰማሩት ባለሀብቶች መካከል አቶ ዩሱፍ ኡመር በበኩላቸው '' መንግስት የተረከብነውን መሬት በሙሉ አቅማችን ለማልማት ማነቆ የሆኑብንን የመንገድና የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር እንዲፈታልን እንጠይቃለን'' ብለዋል ፡፡

በጊኒር ወረዳ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት ወስደው በውሉ መሰረት በማልማት ላይ ከሚገኙት ባለሀብቶች መካከል አቶ ሁሴን መሐመድ እንደተናገሩት በዘርፉ በመሳተፍ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ላይ ናቸው፡፡

በተጨማሪም ለአካባቢው አርሶ አደሮች የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ሽግግር እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ዙቤር ከሊል እንደተናገሩት ባለሀብቶቹ በአካባቢያቸው ላይ በግብርና ዘርፍ ማልማት ከጀመሩ ወዲህ የተሻሻለ የግብርና አሰራር ከመቅሰማቸው ባሻገር የምርጥ ዘር ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በባሌ ዞን ባለፉት ዓመታት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 147 ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰመራታቸውን ከዞኑ የኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2009 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የህብረተሰቡን የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ በማሳደግ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስስሳት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ተናገሩ።

 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒቲሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎችና መምህራን የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ቀንን በኦሮሚያ ፊንፊኔ የደን ስፍራ ከአንድ ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል አክብረዋል።

 ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ባቱ መስቀሌ መንግሥት ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ትልቅ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።

 ሆኖም ሕገ ወጥ የደን ውጤቶች ዝውውር፣ የእርሻና የመሬት መስፋፋት እንዲሁም የደን ውስጥ ሕገወጥ ሠፈራ የአካባቢ ጥበቃ ስራው ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

 አገሪቷ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሠለፍና ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት ካልተሰጠ ያደጉ አገራት የገቡበት የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና ስጋቷ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

 በመዲናዋ ከፋብሪካዎች በሚወጡ ፍሳሾች እየደረሰ ያለው የአካባቢ ብክለትም ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ እንደሆነ አመልክተዋል።

 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ሽብሩ ተመስገን በመስኩ እየተሰራ ያለውን ስራ አብራርተዋል።

የመጀመሪያ ዓመት የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተማሪዋ ብሩክታዊት ብርሃኑ እና የሦስተኛ ዓመት ኢንቫይሮመንታል ፖሊሽን ኤንድ ሳኒቴሽን የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪው መኮንን ብርሃኔ ህብረተሰቡ ዛፎችን በመትከል የተስተካከለ የአየር ንብረት መፍጠር እንዳለበት ተናግረዋል።

 የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ቀን “ኅብረተሰብን ከተፈጥሮ ጋር ማስተሳሰር” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ለ24ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው።

 

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ግንቦት 28/2009 የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች አሰግድ ተስፋዬ ስርዓተ ቀብር ዛሬ በአዲስ አበባ ሰዓሊተ ምህረት  ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።

አሰግድ ተስፋዬ ከብሔራዊ ቡድኑ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ቡና፣ ለኢትዮጵያ መድን ድርጅትና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫውቷል።

ከ1988 ዓ ም ጀምሮ በወጣቶችና በዋናው ብሔራዊ ቡድን 50 አህጉራዊና ዓለምዓቀፋዊ ጨዋታዎችንመም አድርጓል፡፡

በተለይ በብሄራዊ ቡድኑ 16 ስኬታማ ዓመታትን አሳልፏል፡፡

የቀድሞዎቹ የብሔራዊ ቡድንና የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች  ካሊድ መሃመድና ብርሃኑ ፈይራ አሰገድ በእግር ኳስ ክህሎቱና በስነ-ምግባሩ ለወጣት ተጫዋቾች አርዓያ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲን ባሻም  “ለሀገሪቱ እግር ኳስ የራሱን አሻራ ያስቀመጠ ተጫዋች” ሲሉ ገልጸውታል።

ለአገሪቱ እግር ኳሰ እድገት ብዙ መስራት በሚችልበት ዘመኑ ከዚህ ዓለም መለየቱም የሀገሪቱን እግር ኳ አፍቃሪ ልብ የሚሰብር መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

''አሰግድ ተስፋዬ'' በሚል ስያሜ ያቋቋመው የታዳጊ እግር ኳስ ፕሮጀክቱ  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የሚቀጥልበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል።

በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ ቤተሰቦቹ፣ አድናቂዎቹና ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡

የ47 ዓመቱ አሰግድ ድሬዳዋ ከተማ የተወለደ ሲሆን ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበር።

 

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን