Items filtered by date: Sunday, 04 June 2017

ዲላ ግንቦት 27/2009 በጌዴአ ዞን  አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን የተምች ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን የዞኑ እርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት መምሪያ ገለፀ ፡፡

የመምሪያው ምክትልና የሰብል ልማት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ሠላማዊት ያሬድ ለኢዜአ እንደገለፁት ተምቹ በዞኑ በዲላ ከተማ ኦዳያአ ቀበሌ ዋለሜ አካባቢ ከግንቦት 16 ጀምሮ ነው የታየው፡፡

የተምች ወረርሽኙ አሁን ላይ ዲላ ዙሪያ እና ወናጎ ወረዳዎችን ጨምሮ በዞኑ 16 ቀበሌዎች ላይ የተከሰተ ሲሆን በስፋት በታየበት በወናጎ ወረዳ 13 ቀበሌዎችን መውረር ችሏል ፡፡

በዚህም በዞኑ 343 ሄክታር የሚጠጋ የበቆሎ ማሳ ጉዳት ደርሶበታል ፡፡

ተምቹ አስከፊ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ለመቆጣጠር በርብርብ እየተሰራ መሆኑን ያመለከቱት ወይዘሮ ሠላማዊት ፤ አብዛኛው የበቆሎ ማሳ ከሌሎች ሰብሎች ጋር በመጠጋጋቱና ደባል ሰብሎችም አብረው የተዘሩ በመሆናቸው ለኬሚካል ርጭት አመቺ አለመሆኑን አስረድተዋል ፡፡

ለዚህም በቅድሚያ ትሉን በእጅ ለቅሞ በመግደል ፤ ጉዳቱ የባሰባቸውና ሰፋፊ የሆኑ ማሳዎች ላይ ደግሞ ጥንቃቄ የተሞላበት የኬሚካል ርጭት በማድረግ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡

እስካሁን ባለው ሂደትም 207 ሄክታር የሚጠጋ የበቆሎ ማሳ ላይ ተምቹን መቆጣጠር የተቻለ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 132 ሄክታር ላይ በእጅ ለቀማ መካሄዱን ጠቁመዋል ፡፡

የወናጎ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽሕፈት ቤት ምክትልና የሰብል ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢዮብ ሰሊ ፤ በወረዳው ከ271 ሄክታር በላይ የበቆሎ ማሳ በተምቹ መወረሩን ጠቅሰዋል፡፡

መከላከሉ በስፋት በእጅ ለቀማ አማካኝነት እየተካሄደ ነው ያሉት ሃላፊው አርሶ አደሩ በልማት ቡድን እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል ፡፡

በወረዳው በቱማታ ጨረቻ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ተስፋዬ ኃይሉ የተምች ወረርሽኙ እየተባባሰ በመምጣቱ ከልማት ቡድን አጋሮቻቸዉ ጋር በህብረት በመስራት መከላከል መጀመራቸውንና ከቀናት በፊት ከተምች ነጻ ያደረጉት ማሳ ማገገም መቻሉን ተናግረዋል ፡፡

ሌላው የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር አብረሀም አታራ በበኩላቸው ከማሳቸው ስፋት የተነሳ በእጅ ለቀማ ማዳረስ ባለመቻላቸው ኩታ-ገጠም ማሳ ካሏቸው ጎረቤቶቻቸው ጋር ከባለሙያ ባገኙት ስልጠና መሰረት የኬሚካል ርጭት እያካሄዱ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ ግንቦት 27/2009 በትግራይ ክልል በስራቸው የተሻለ አስተዋጽኦ ላደረጉ 755 የማረሚያ ቤቶች ፖሊስ አመራሮችና አባላት ዛሬ ከሪቫን እስከ ወርቅ ሜዳሊያ የሚደርስ የማበረታቻ ሽልማት ተበረከተላቸው፡፡

ሽልማቱን ያበረከቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አባይ ወልዱ እንዳሉት፣ዜጎችን ወደ ስህተት እንዳይገቡ አስቀድመው በማስተማርና የተሳሳቱንም በማረም የተጀመረው ያልተቆጠበ ትግል ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

"ሌሎች አባላትም የተሸላሚዎቹ መልካም አርአያና ጀግንነት ሊከተሉ ይገባል "ብለዋል።

የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ተወካይ ኮማንደር ወልዳይ አብራሃ በበኩላቸው የፖሊስ አመራሮችና አባላቱ ለሽልማት የበቁት ከሰባት እስከ 25 ዓመት ባገለገሉበት ወቅት በዕለተ ተዕለት ስራቸውና በመልካም ስነ ምግባራቸው የተሻለ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ነው፡፡

ከተሸለሙት መካከል 161 ያህሉ ሴት አመራሮች ናቸው

ኮማንደር ህይወት ነጋሽ የመቀሌ ማረሚያ ቤት የታራሚዎች አስተባባሪና ከተሸላሚዎቹም መካከል አንዱ ሲሆኑ የደርግ ስርዓትን ለመደምሰስና ለህዝብ እኩልነት ሲሉ ከህወሓት ጎን ተሰልፎው በጽናት መታገላቸውን በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

አሁንም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እያገለገሉ መሆናቸውንና ሽልማቱም ለበለጠ ስራ እንደሚያተጋቸው ተናግረዋል፡፡

ከዓዲግራት ማረሚያ ቤት ተሸላሚ የሆኑት ኮማንደር ኪዳነ ሀፍተ በበኩላቸው በተበረከተላቸው ሽልማት ሳልኩራሩ ለበለጠ ውጤት ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

በግለኝነትና በሙስና ለሚታዩ ችግሮች በጽናት በመታገል አርአያ ለመሆን እንደሚጥሩም አመልክተዋል፡፡

በሽልማት አሰጣጡ ስነስርዓት ላይ ከፌዴራል፣ ከክልልና ከዞን የተወከሉ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዳማ ግንቦት 27/2009 አዳሚ ቱሉ የፀረ-ተባይ ማዘጋጃ አክሲዮን ማህበር በበጀት ዓመቱ ባካሄደው እንቅስቃሴ ከ42 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የአክሲዮን ማህበሩ የሥራ እንቅስቃሴን ትናንት ተመልክተዋል፡፡

የአክሲዮን ማህበሩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ፈጠነ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ትርፉን ያገኙት እስከ ሶስተኛው ሩብ የበጀት ዓመት ካመረቱት ፈሳሽና የተለያዩ ፀረ-ተባይ ዱቄት መድኃኒት ሽያጭ ነው።

የተሸጠውም ከ800 ሺህ ሊትር በላይ ፈሳሽና ከ570 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ፀረ-ተባይ ዱቄት መድኃኒት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ለሀገር ወስጥ ገበያ ከቀረበው የፀረ-ተባይ መድኃኒት የነቀዝ፣የእንስሳት ቆዳ በሽታ፣ የወባ ትንኝ መቆጣጠሪያና የሰብል በሽታ መከላከያ ይገኙበታል።

በተለይ ከፀረ-ተባይ መድኃኒት ውስጥ 55 ሺህ ሊትር የሚሆነው በሀገሪቱ በቅርቡ የተከሰተውን ተምች ለመከላከል የሚያገለግል መሆኑን ነው አቶ ተሾመ የጠቀሱት።

ከሽያጭ የተገኘውም ትርፍ በእቅድ ከተያዘው በ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል።

የማምረቻና የነዳጅ ወጪን በመቀነስ፣የስራ ሰዓትን በሙሉ አቅም በመጠቀምና የምርት ማሸጊያ እቃዎችን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉ ለትርፉ መገኘት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

እንደ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገለፃ እስከ ሦስተኛው ሩብ ዓመት ካቀረበው ፀረ-ተባይ ምርት ሽያጭ 325 ሚሊዮን 568 ሺህ 120 ብር ገቢ ተገኝቷል።

ይህ አፈጻጸምም ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር ከእጥፍ በላይ ብልጫ እንዳለው ያመለከቱት አቶ ተሾመ መንግስታዊ ተቋም የሆነው አክሲዮን ማህበሩ በግብአትነት ከሚጠቀመውን ጥሬ እቃ ውስጥ 95 በመቶ ከውጭ በማስገባት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሰው ሃይል እጥረት እንዳጋጠመው ገልጸው ችግሩን ለማቃለል ያሉትን ባለሙያዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ለማሰልጠን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በተለይ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በ2004 ዓ.ም ክፍያ የፈጸመበትን 260 ሺህ ኪሎ ግራም ዲዲቲ በተደጋጋሚ እንዲያነሳ ቢጠየቅም ባለማድረጉ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት ከመሆኑም በላይ የአክሲዮን ማህበሩን መጋዘን ማጣበቡን ምክትል ሥራ አስኪያጁ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልጸዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት  የአክሲዮን ማህበሩን የስራ እንቅሰቃሴ ከተመለከቱ በኋላም ከማህበሩ የስራ ኃላፊዎችና ከሰራተኞች ጋር ተወያይተዋል።

የአክሲዮን ማህበሩ የስራ ኃላፊዎች ያቀረቡትን ችግር  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንዲያገኝ በቅርቡ ግብረ መልስ እንደሚሰጡ የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ ሮበሌ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

 

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 27/2009 ቅዱስ ጊዮርጊስ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ኤ ኤስ ቪታ ክለብን አሸነፈ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2017 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ኤኤስ ቪታ ጋር በአዲስ አበባ ባደረገው ጨዋታ አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ሳላዲን ሰይድ በ60ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ቅዱስ ጊዮርጊስ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ማሸነፉን ተከትሎም ነጥቡን ወደ አምስት ከፍ በማድረግ በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

የዴሞክራቲክ ኮንጎው ኤኤስ ቪታ በበኩሉ ሶስት ጨዋታዎችን አድርጎ በሶስቱም በመሸነፍ ያለምንም ነጥብ በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በተደለደለበት ምድብ ሶስት የቱኒዚያው ኤ ኤስ ቴራንስ ምድቡን በሰባት ነጥብ ሲመራ ጊዮርጊስ በአምስት ነጥብ 2ኛና የደቡብ አፍሪካው ማማሎ ሰንዳውን በአራት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

Published in ስፖርት

ባህርዳር ግንቦት 27/2009 የአማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/ ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች ማከናወኑን አስታወቀ።

የማህበሩ 12ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በባህርዳር ተካሂዷል፡፡

የአልማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ብስራት ጋሻውጠና ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት ማህበሩ የተለያዩ የልማት ተግባራት ማከናወኑን ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡

ከተከናወኑት መካከልም 595 የመጀመሪያ፤ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ፣ የቴክኒክ ሙያ ተቋማትና ኮሌጆች ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁ ይገኙበታል፡፡

እንዲሁም የጤና አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች 27 ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎችን በመስራት ህብረተሰቡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆኗል።

ማህበሩ" ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች የቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ ከአራት ሺህ 830 በላይ ኮምፒዩተሮችን ደግሞ ለትምህርት ቤቶች አሰራጭቷል "ብለዋል።

ከሁለት ሚሊዮን 900 ሺህ በላይ አዲስ አባላት በማፍራትም ጠቅላላ የአባላቱን ቁጥር ከአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ በማድረስ ለማህበሩ ትልቅ የልማት አቅም መሆኑን ወይዘሮ ብስራት አመልክተዋል፡፡

ልማት ላይ ከዋለው ገንዘብ ውስጥ  ከ778 ሚሊዮን ብር በላይ ከአባላት መዋጮ የተሰበሰበ ሲሆን ቀሪው ገንዘብ ደግሞ  ከልማት አጋሮች የተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳይ ሚኒስትርና የአልማ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ካሳ ተክለብርሃን በበኩላቸው ማህበሩ ህዝቡን ትልቁ የልማት አቅም አድርጎ በማንቀሳቀስ  አሁን ለደረሰበት ስኬት መብቃቱን ገልጸዋል፡፡

"የአባላቱን ቁጥር ለማሳደግና ህዝባዊ መሰረቱን የማስፋት ስራ በማከናወኑ የክልሉን የልማት ክፍተቶች እየለየ ወደ ስራ በመግባቱም የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል "ብለዋል።

ማህበሩ ያልተማከለ አደረጃጀት በመከተል ከአባላቱ ከሚሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ለዛው አካባቢ ልማት እንዲውል መደረጉ አርሶ አደሩ እምነት እንዲይዝ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡

አልማ በቅድመ መደበኛ ትምህርት፤ ጤናና የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ እየሰራ ያለውን ስራም በቀጣይ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡   

" የክልሉን ህዝብ፣ ዕውቀት፣ ገንዘብና ቁሳቁስ በማሰባሰብ ውጤታማ ስራ አየሰራ ነው" ያሉት ደግሞ በጉባኤው ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ናቸው።

ክልሉ ያሉበትን  ክፍተቶች ለይቶ በመግባት በሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች የክልሉን ህዝብ  ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

ጉባኤው ዘጠኝ አዳዲስ የቦርድ አመራር አባላትን የመረጠ ሲሆን የማህበሩን 25ኛ ዓመት የብር ዕዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ የአልማን ያለፉት አምስት ዓመታት የልማት ተግባራትን የሚያሳይ የፎቶ ግራፍ አውደርዕይ ቀርቧል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ ግንቦት 27/2009 በመኸር ወቅት ሊኖር የሚችለውን የዝናብ እጥረት ለመቋቋም የሚያስችል አማራጮችን በመጠቀም መስራት እንደሚገባ የደቡብ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ  አሳሰቡ፡፡

በክልሉ በመኸር ወቅት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንደሚለማም ተገልጿል፡፡

የ2009/2010 የመኸር ወቅት እርሻ ልማትን ለማጠናከር በሚቻልበት ላይ ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በሀዋሳ ከተማ ሲካሄድ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በመኸር የዝናብ እጥረት ሊኖር እንደሚችል ተተንብየዋል፡፡

የዝናብ እጥረት ለመቋቋም በማሳ ውስጥ እርጥበት በማቆየት፣ የተገኘውን ውሃ በማሰባሰብና መስኖን በመጠቀም ለማልማት በሁሉም የክልሉ አከባቢዎች በተቀናጀ አግባብ መሰራት ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡

"በዚህም በበልግ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች ያመለጠውን ምርት የማካካስ ስራ ይሰራል" ብለዋል፡፡

የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ  የክህሎት ክፍተቶችን  በስልጠና በመሙላት  አመራሩ ፣ የልማት ሰራተኛውና አርሶ አደሩ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አቶ ደሴ አሳስበዋል፡፡

የክረምቱን ዝናብ  ተከትሎ የሚከሰተውን የሰብል ተምችና የተባይ ወረርሽኝ ለመከላከል የኬሚካል አቅርቦትና ሌሎችም ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን የገለጹት  ደግሞ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥለሁን ከበደ ናቸው፡፡

የዝናብ እጥረት በመቋቋም በመኸር የእርሻ ወቅት በክልሉ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት በማልማት 72 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ግብ መቀመጡን ተመለክቷል፡፡

ከዚህ ውስጥም በ300ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴና የቢራ ገብስ በኩታ ገጠም ለማልማት እቅድ መያዙ ተጠቅሷል፡፡

ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በክልሉ የለማው መሬት 900 ሺህ ሄክታር መሬት እንደነበር  ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

Published in ኢኮኖሚ
Sunday, 04 June 2017 20:41

የግንቦት 20 ትሩፋቶች

ተካ ጉግሳ (ኢዜአ)

ወላጆቿ ሕልፊ ብለዋታል። እላፊ ወይም የበለጠ እንደማለት ነው። ስሙ ከምን ጋር ተያይዞ እንደወጣ ብዙ የምታውቀው ነገር የለም። ወላጆችዋን ጠይቃም አልተረዳችም።

እንደማንኛውም ህፃን  በሰፈርዋ ጨዋታ ብቻ የምትወድ አልነበረችም። የቤት ውስጥ ስራን በጠዋት በማከናወን ከብቶችን አሰማርታ ወደ ሌላው ቀሪ ስራ መሮጥ የዘወትር ተግባሯ ነበር።

በትግራይ ማእከላዊ ዞን በዓድዋ ልዩ ስሙ ማርያም ሸዊቶ በተባለው አካባቢ ተወልዳ ያደገችው ሕልፊ ዝበሎ አንድ ቀን ግን ከራስዋ አልፎ ቤተሰቦቿንና የአካባቢውን ማህረሰብ ያስደነገጠ ክስተት ተፈፀመ።

ወቅቱ በጋ እንደነበር ትዝ ይላታል ። የዛሬ 11 ዓመት የተከሰተውን ተመልሳ ስታስታውሰው በጥልቅ ሃሳብ ተውጣ ነበር።

የልጅነት ጊዜዋን እያስታወሰች የአካባቢው ተፈጥሯዊና መልክአምድራዊ አቀማመጥ እንዲሁም በጣልያን ጦርነት ወቅት ባሻይ አውዓሎምና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን  ጀግኖች የፈፀሙት ተጋድሎ  በህሊናዋ እያሰላሰለች ቆየች። አሁን ግን በትዝታ እንጂ ልታያቸው አትችልም ። በድንገተኛ ክስተት የሁለት ዓይኖቿን ብርሃን ተነጥቃለችና ።

 እኔም በራሴ ዓለም በትዝታ ከልጅነት ጊዜዬ ጋር ተገናኝቼ ነበርና ድንገት እሺ ምን አልከኝ ስትለኝ ያነሳሁላትን ጥያቄ ፈጥኜ አስታወስኩት ።  የደረሰብሽ ጉዳት እንዴትና መቼ ነበር ? አልኳት ። የደረሰባት ጉዳት አሁን ካለችበት ስራ የሚያስተጓጉላት ባይሆንም ሁኔታውን ማወቅ ስላለብኝ ነው የጠየቅኳት። እንዲህ ስትል መለሰች።

“ሰዓቱን በትክክል ባላውቀውም ረፋድ ላይ ነበር። ወቅቱ በ1998ዓም የ22 ዓመት ወጣት እያለሁ ነው አደጋው የተከሰተው። በግቢያችን ውስጥ እያለሁ ሃይለኛ አቧራ ይነሳል። አቧራው እየተሽከረከረና ወደ ላይ ቡልል ብሎ እየወጣ ያለሁበት ቦታ ደርሶ ወረረኝ ። እናም በቅፅበት ሁለት ዓይኖቼን አጥፍቶት አለፈ” ትላለች ። ዘግናኝና አሳዛኝ ክስተት ነበር ።

የአይኖቿን ብርሃን በድንገት መነጠቅ ግን ከልማት አርበኝነቷ አላገዳትም ። በመስኖና በክረምት ዝናብ እየታገዘች በምታካሄደው ግብርና በዓመት በአማካይ 20 ሺህ ብር ገቢ ታገኛለች ።

ሕልፊ ዓመታዊ ገቢዋን በእጥፍ ለማሳደግ ጠንክራ እየሰራች መሆንዋን የምትናገረው በልበ ሙሉነት ነው  ። ብዙ ጥያቄዎች ተመላለሱብኝና ጥቂቶችን ሰነዘርኩላት ። ዓይነስውርነቱ ወደ እርሻ ቦታ ለመሄድና ወደ ቤት ለመመለስ አያስቸግርሽም ? ቀዳሚ ጥያቄዬ ነበር ።

“ ከአደጋው በፊት የእርሻ ማሳዎቻችን በደንብ አውቃቸው ነበር ። ድንጋይና ቁጥቋጦ የሚበዛበት አካባቢ የት እንደሆነም በግልጽ ትዝ ይለኛል ። ስለዚህ ያለ አደጋ¡ ሔዶ መመለስን በደንብ ተለማምጀዋለሁ “ ትላለች ።

ሕልፊ ከኩትኳቶ ጀምሮ እስከ አረም ድረስ ሁሉንም የእርሻ ስራዎች ታከናውናለች ። አስቸጋሪ የሚባለው የአረም ስራ የምታከናውነውም እራሷ ነች ። እንዴት ?

 “ አብዛኛው ጊዜ የማለማው አትክልትና ስራስር ነው ። በእጄ ስዳብሳቸው ቀጠን ያለ  ፣ ከመደበኛው ምርት የረዘመና ያጠረ ፣ በመጠኑ ያነሰና የበለጠ እጽዋት ካለ አረም መሆኑ ነው ። እናም በጥንቃቄ እነቅለዋለሁ ። ሰዎች ሲያዩትና ሲመሰክሩም ቅንጣት ታክል አልሳሳትም ።

የአደጋውን ጉዳት ተላምዳዋለች ። እንደ አመጣጡም ተቀብላዋለች ። የሚቆጫት ነገር ቢኖር

በግንቦት 20 ድል የተገኙ አንጸባራቂ ድሎችን በምትፈልገው መጠን ማጣጣም አለመቻሏ ነው ።

ሴቶች ከፆታዊ መድልዎ ነፃ ሆነው በሁሉም መስክ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን በጀመሩባት አገር ከዚህ በላይ በመስራት ጥንካሬዋን ማሳየት ነበር ። ብቸኛው ቁጭቷም ይሄው እንደሆነ ትናገራለች ።

ሴቶችና ግንቦት 20 በእጅጉ የተቆራኙ ይመስላሉ ። ሌላዋ የልማት አርበኛ ወ/ሮ አስካለ አእምሮ ይባላሉ። የወንድና የሴት የሚባል ስራ አለመኖሩን በተግባር ካስመሰከሩ አመታት አሳልፈዋል። የወንዶችን የበላይነት የሚያራምዱና የሴቶችን የበታችነት የሚቀበሉ አስተሳሰቦችን ሰባብረውታል።

ሞፈር ተሸክመው ወደ እርሻ ሲሄዱና በሬዎችን ጠምደው ማረስ ሲጀምሩ የሚያያቸው ሁሉ ራሱን ማመን እስኪያቅተው ድረስ ከውስጡ ጋር ይሟገታል። ሌላ ተአምር ተፈጥሮ ሳይሆን በውስጡ የቆየውን ትምክህትና የበላይነት ስለሚፈታተነው ነው።

በትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን በእንደርታ ወረዳ መሰቦ በተባለው የገጠር ቀበሌ ነዋሪ ናቸው ። ሴቶች ወደ አመራርነት ከመውጣት ጀምሮ በኢኮኖሚ ራሳቸውን እየቻሉ መሆናቸው የራሳቸውን አብነት በመጥቀስ ይናገራሉ ።

ከስርአቱ መውደቅ በፊት ከአምስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን አቋርጠው ያለእድሜአቸው ጋብቻ እንዲመሰርቱ መደረጉን የሚናገሩት ወ/ሮ አስኳለ አእምሮ በአሁኑ ወቅት እማወራ ሆነው ስድስት ልጆቻቸውን አሳድገው ለስራ አብቅተዋል ።

በዓመት እስከ 40 ኩንታል ምርት እንደሚያገኙና በአሁኑ ወቅት ማይመክደን በተባለ የገጠር ከተማ ሁለት ክፍል ቤት መስራታቸውን አስረድተዋል።

ያላቸውን ሁለት ጥማድ መሬት ላለፉት 20 ዓመታት ራሳቸውን በማረስ ሴቶች በማንኛውም ስራ ሊሰማሩ እንደሚችሉ በተግባር አስመስክረዋል።

ይህ በቀላሉ የተገኘ ሳይሆን የህዝብ ልጆች በከፈሉት መስዋእትነት የግንቦት 20 ድል ውጤት ነው ይሉታል - ወ/ሮ አስኳለ ።

በ2002 ዓ.ም 20ሺህ ብር ተበድረው በጀመሩት የባልትና ስራ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል በመያዝ ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩት ደግሞ ወ/ሮ ፀባቒት ፍስሃ ይባላሉ ።

በትግራይ ማእከላዊ ዞን በአክሱም ከተማ በባልትና ስራ የተሰማሩት ወ/ሮ ፀባቒት  ግንቦት 20 የሰላም ብቻ ሳይሆን የልማትና የእድገት መሰረት ጭምር ነው የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ ። የእድገታቸው ሁሉ መነሻው የግንቦት 20 ድል ነው ብለውም ያምናሉ ።

በትግራይ ምስራቃዊ ዞን በዓዲግራት ከተማ በብሎኬት ስራ የተሰማሩት ወ/ሮ ቅዱሳን ክንደያ ሌላዋ የግንቦት 20 ትሩፋት ናቸው ። ከዘጠኝ ዓመት በፊት ከደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ባገኙት የሁለት ሺህ ብር ብድር የጓሮ አትክልትና የንግድ ስራ መጀመራቸውን ገልጸው በአሁኑ ወቅት የራሳቸው መኖሪያ ቤት ሰርተዋል።

 ብሎኬት እያመረቱ በመሸጥ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር ካፒታል ማፍራት መቻላቸውን በኩራት ሲናገሩ ዘላለማዊ ክብር ለሰማእታት ማለትን አይዘነጉትም ። ስኬቱ የግንቦት 20 ድል ውጤት መሆኑን የሚናገሩትም በአፅንኦት ነው ።

በቅርቡም የብረታብረት ዎርክሸፕ ለመክፈት ከልማት ባንክ የሁለት ነጥብ ስድስት ሚልዮን ብድር ለማግኘት ፕሮጀክት አቅርበው ገንዘቡን  ለማግኘት ተራ እየጠበቁ ነው ።

“ እኛ  የትግሉ ፍሬዎች ነን “ የሚሉት ወ/ሮ ቅዱሳን የህዝብ ልጆች በከፈሉት መስዋእትነት የተረጋገጡላቸው መብቶች የማጎልበትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው የማረጋገጥ አጀንዳ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ ።

ፈተና የሌለው ምቾት እንደማይኖር ያለፈውን ስርዓት ለመገርሰስ የተካሄደው ተጋድሎ ሊያስተምረን ይገባል የሚሉት ደግሞ በመቐለ ከተማ ዓዲሓውሲ በተባለው አካባቢ ከስድስት አመት በፊት በሽርክና ማህበር ተደራጅተው የባልትና ስራ የጀመሩት ወ/ሮ አብርኸት ተክለሃይማኖት ናቸው።

በግንቦት 20 የተገኙትን መብቶች እንዲጎለብቱና በተፈጠሩ ምቹ የልማት ስራዎች ሴቶች ይበልጥ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ መስራትና የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን መቋቋም እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ ።

13 የሽርክና ማህበሩ አባላት ባዋጡት 26 ሺህ ብር ስራ መጀመራቸው የሚናገሩት ወ/ሮ አብርኸት በአሁኑ ወቅት አራት ወፍጮዎችና ሶስት የእህል ማበጠሪያዎች ያሉዋቸው ሲሆን ከ800ሺህ በላይ ካፒታል በማስመዝገብ በቅርቡ በፌዴራል ደረጃ በተካሄደው ሽልማት የመጀመሪያ ደረጃ ተሸላሚዎች ለመሆን በቅተዋል ።

የትግራይ ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር የትምወርቅ ገብረመስቀል በክልሉ ከ290 ሺህ በላይ ከሚሆኑ እማወራዎች መካከል 227 ሺህ የሚሆኑት የራሳቸው የእርሻ መሬት አላቸው፡፡

የእርሻ መሬት ካላቸው መካከል 216 ሺህ የሚሆኑት ሴቶች ራሳቸው እንዲያርሱት በማድረግ በኪራይ ሰጥተው ያገኙት ከነበረው ገቢ ከእጥፍ በላይ እንዲያገኙ እያስቻላቸው መምጣቱን የቢሮ ኃላፊዋ አስረድተዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች የእርሻ መሬታቸው የሚያከራዩት ከተመረተው ሩብ ሲወስዱ 2/3ኛው ያረሰው ግለሰብ ይወስደዋል።

 ይህም በመሬታቸው ላይ ያላቸው ተጠቃሚነት አነስተኛ እንዲሆን ያደርገዋል። ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ በመስራት ላይ መሆኑን ነው የተናገሩት ።

 የግንቦት 20 ትሩፋቶች የሆኑት ሴቶች እህቶቻችን በቀጣዮቹ አመታት ወደ ተሻለ ኢንቨስትመንት ተሸጋግረው ታሪክ መስራት እንደሚችሉ ሊያሳዩ ቆርጠው ተነስተዋል ።

አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ ማግኘት ከቻሉ ስኬታማ መሆን እንደማያቅታቸው ጥሩ ምልክት አሳይተውናል ።  ሴቶች ተአምር መስራት እንደሚችሉ በትጥቅ ትግሉ ወቅት በተግባር ማሳየታቸው የማይታበል ነው ።

Published in ግንቦት20

ወጣት የእኔዓለም ማሩ የባህርዳር ከተማ ነዋሪ ነው። ለግንቦት 20 ምስጋና ይድረሰውና ለትምህርት መስፋፋት የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ትምህርት ዘርፍ ከባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በዲፕሎማ በ2003 ዓ.ም ነው የተመረቀው።

አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው በከፈሉት መስዋዕትነት የተረጋገጠው ሰላም ለወጣቱ የመማር ዕድል በር እንዲከፈትና ሰርቶ ራሱንና ሀገሩን እንዲቀይር ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል።

እኔም የዚህ ታሪክ ተጋሪ መሆኔ የተፈጠረውን ምቹ የመማር ሁኔታ ተጠቅሜ የተማርኩትን ትምህርት በተግባር ስራ ላይ ለማዋል በ2004 ዓ.ም በጥቃቅንና አነስተኛ ስራ ዘርፍ ከ10 ጓደኞቼ ጋር ሆኜ በመደራጀት “የእኔዓለም ብርቱካንና ጓደኞቻቸው” የሚል ዘመናዊ የሽመናና የሹራብ ስራ ሽርክና ማህበር መስርተን ወደስራ እንድንገባ ዕድል አግኝተናል።

በወቅቱ ባገኘነው በ121ሺህ ብር ብድር መነሻ ካፒታል በአንድ የሽመና ማሽን የጀመርነውን ስራ ጠንክረን በመስራት አሁን ላይ ካፒታላችንን አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር በማድረስ ተጠቃሚ እንድንሆን አስችሎናል ባይ ነው።

በተሰማራንበት የስራ ዘርፍ አሁን ለደረስንበት የዕድገት ደረጃ እንድንበቃ ደግሞ ግንቦት 20 ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።

“ከራሳችን አልፈንም ለሌሎች 21 ስራ አጥ ወጣቶች ተጨማሪ የስራ ዕድል መፍጠር ችለናል” ያለው ወጣት የእኔዓለም ማሩ በተፈናጠጥንበት ሜዳ የስራ እርካባቸውንን አጥብቀን በመጋለብ በ2011 ዓ.ም መካከላኛ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ለመገንባት ከወዲሁ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን ብሏል ።

አዲሱ ትውልድ በግንቦት 20 የተፈጠረለትን ሰርቶ የመለወጥ ምቹ መደላድል ተጠቅሞ ሳይዘናጋ በጥቃቅንና አነስተኛ ስራ ዘርፍ ተደራጅቶ ወደስራ በመግባትና የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ በመሆን ሰርቶ ራሱንና ሀገሩን ለመለወጥ አዕምሮውን ሁሌም ለፈጠራ ስራዎች ራሱን ማዘጋጀት አለበት።

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በድህረ ገፆች ለሚናፈሱ አሉቧልታዎች ወጣቱ ሳይንበረከክ እንደቀደምት አባቶቹ ጠላትን በመመከት ድህነትን ድል ለመንሳት በግንቦት ሃያ የተረጋገጠለትን ሰላም፤ ልማትና ዴሞክራሲ ማስቀጠል አለበት ይላል።

“ግንቦት ሃያ የአሁኑ ትውልድ ከጦርነት ስጋት ተላቆ በተመቻቸለት የትምህርት ዕድል በመጠቀም ወደልማት ስራ በመሰማራት ራሱን ለመቻል መሰረት የጣለበት ቀን ነው” ያለው ደግሞ በባህርዳር ግንቦት ሃያ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ብሩክ ልዑል ሰገድ ነው።

የባህል አልባሳት፤ ዲዛይንና ስፌት የሽርክና ማህበርን ከአራት ጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ በማቋቋም ባለፈው ጥቅምት 2009 ዓ.ም ስራ እንደጀመረ ነው የሚናገረው።

በ47 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የጀመሩትን የባህል አልባሳት፤ ዲዛይንና ስፌት ስራም ጠንክረው መስራት በመቻላቸው ከስምንት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ሃብታቸውን ከ120 ሺህ ብር በላይ በማድረስ አባላቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑም አስችሏቸዋል።

የጀመሩትን የባህል አልባሳት፤ ዲዛይንና ስፌት ስራ በቀጣይ አሻሽለው በመስራት የተሻለ ደረጃ ላይ በመድረስ ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለመጥቀም ጠንክረው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነም ነው የሚናገረው።

“በ1983 ዓ.ም በወርሃ ግንቦት የተረጋገጠው ሰላምና ዴሞክራሲ በወቅቱ የነበሩ ወጣቶች በጋራ ታግለው ለአሁኑ ትውልድ ስኬት እንድንበቃ መሰረት የተጣለበት ቀን በመሆኑ ልንጠብቀውና ልንከባከበው ይገባል” ሲል የተናገረው ደግሞ የአማራ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት አባይነህ መላኩ ነው።

 ባለፉት ስርዓቶች በክልሉ ለትቂት የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ይደርስ የነበረው የትምህርት ዕድል አሁን በሀገራችን ከጫፍ እስከጫፍ በመስፋፋቱ እኛም ተምረን የተሻለ ደረጃ እንድንደርስ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል።

ማህበሩ ካፈራቸው ከ880 ሺህ በላይ አባላት ውስጥም ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑት በገጠር በግብርና፤ በከተማ ደግሞ በጥቃቅንና አነስተኛ በተለያዩ ስራ ዘርፎች ተደራጅተው ራሳቸውን ችለው ለሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ እድገት መፋጠን የድርሻቸውን በመወጣት አሻራቸውን ለማስቀመጥ እየተጉ ይገኛሉ።

በተለይ በየዓመቱ በክልሉ በሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ስራ በንቃት በመሳተፍ በመተግባር ላይ ለሚገኘው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ግቡን እንዲመታ አባላቱ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን እየሰሩ ነው።

ወጣቱ የተፈጠረለትን የመደራጀት፤ የመናገርና ሃሳብን በነፃ የማራመድ መብቱን በመጠቀምም በፖለቲካው ዘርፍ ሃሳቡን በነፃነት እንዲያራምድ፤ ተሳታፊና ተጠቃሚነቱንም እያረጋገጠ እንዲመጣ ምቹ መደላድል እየተፈጠረለት መምጣቱንም ለአብነት አንስቷል።

የአሁኑ ወጣት እንዳለፈው ስርዓት ሳይፈልግ ተገዶ ወደጦር ሜዳ የሚሄድበት ሳይሆን ሰርቶ ራሱንና ሀገሩን የሚያሳድግበት ዕድል የተረጋገጠው በግንቦት ሃያ በመሆኑም በአባቶቹ የተረጋገጠውን ሰላም ነቅቶ በመጠበቅ ልማቱን ማስቀጠል እንዳለበትም በፅኑ ያምናል።

በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ በይጎማ ሁለቱ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ፋንታሁን ትዕዛዙም የወጣት አቢይ መላኩን ሀሳብ ይጋራሉ። ባለፈው ስርዓት ወጣቱ ተምሮ ራሱንም ሆነ ሀገሩን ከድህነት ከማላቀቅ ይልቅ ባላመነበት ጦርነት ተገዶ የሚማገድበት ጊዜ እንደነበር ያስታውሳሉ።

የነበረው አስከፊ ስርዓት በግንቦት 20 ተወግዶ ተማሪው ወደትምህርቱ፤ ወጣቱና ጎልማሳው ወደልማት፤ አርሶ አደሩ ደግሞ የተሻሻሉ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ በመኽርና በመስኖ ሌት ተቀን በማልማት ለግብርና ምርት ዕድገት በማፋጠን የተጠቃሚነት ዕድሉን እያሰፋ ይገኛል።

ባለፈው ስርዓት የግብርና ምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎች እንደ አሁኑ ለአርሶ አደሩ በስፋት ተደራሽ ባልሆነበት ወቅት “ዝናብን ጠብቀው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ አምርተው የሚያገኙት ምርት የቤተሰባቸውን ዓመታዊ ቀለብ እንዳይሸፍን ማድረጉ ለከፋ ችግር ዳርጓቸው መኖሩን ያወሳሉ።

ያ አስከፊ ጨቋኝ ስርዓት በግንቦት 20 መወገዱ እሳቸውን ጨምሮ ሌላው አርሶ አደር የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ግብዓት በቀላሉ አግኝቶ እንዲጠቀም መልካም ዕድልን በመፍጠሩ በፊት በቆሎ በሄክታር 14 ኩንታል፤ ጤፍ ከአራት ኩንታል ያልበለጠ ምርት ያገኙ የነበረው አሁን ምርታቸውን ከሁለት ዕጥፍ በላይ በማሳደግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

ከዝናብ ጥገኝነት ተላቀው የዘመናዊ መስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸው ደግሞ ቲማቲም፤ ቃሪያ፤ ሽንኩርትና ሌሎች ቋሚ የአትክልትና ፍራፍሬ ተክሎችን በስፋት አልምተው ለገበያ በማቅረብ ከድህነት ጋር ተላቀው ተጨማሪ ሃብት እንዲያፈሩ አስችሏቸዋል።

ይህም ቀደም ሲል የነበረባቸውን የምግብ ክፍተት ሙሉ በሙሉ ከመሙላት አልፈው በዓመት እስከ 200 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ሃብትና ጥሪት እያፈሩ እንዲመጡና ልጆቻቸውንም ሳይቸገሩ አሳድገው በማስተማር ለትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ መልካም ዕድልን ፈጥሮላቸዋል።

የተፈጠረውን የተመቸ የልማት ዕድልን በመጠቀም ሳይታክቱ ሌት ተቀን መስራት በመቻላቸውም በከተማ የሁለት ቤትና የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ተሽከርካሪ ባለቤት እስከ መሆን ደርሰዋል።

ወጣቱም ሆነ አርሶ አደሩ የተገኘውን ሰላም አስጠብቆ ለመቀጠልና የሚፈልቁ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ፈጥኖ በመቀበል በጥቃቅንና አነስተኛ፤ እንዲሁም በመኽርና በመስኖ በማልማት ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ለማሳደግ በትጋት ሊሰራ ይገባል።

 

Published in ግንቦት20

መንበረ ገበየሁ (ኢዜአ) 

በቀን አምስቴና ከዚያ በላይ ለሬዲዮ ጣቢያ ደውሎ ሄሎ የማለት ልምዱን ያዳበረው ገና በልጅነት እድሜው በትውልድ መንደሩ አለታ ወንዶ ነው፡፡

በተለያዩ ጉዳዮች ደውሎ ሃሳቡን የሚያጋራው ወጣት አብዝቶ ግን ስለ ትራፊክ ጉዳይ ያወራል፡፡

ከዛሬ ሰባትና ስምንት ዓመታት በፊት በደቡብ ድምጽ ሬዲዮ ኤፍ ኤም 100.9 ስለማውቀው ወጣት ነው የማወራችሁ፡፡

ትናንት ቢሆን የሚለውን ሃሳቡን የሚያጋራን ይሄው ወጣት ዛሬ ህይወቱን የሚመራበት ስራው ሆኗል የትራፊክ ጉዳይ፡፡

ኑሮዬ ብሎ ከከተመባት ሃዋሳ በትራፊክ ማስታወቂያ ስራዎች ላይ ተሰማርቶ መደወሉን አላቆመም ። የአለታ ወንዶው ነኝ ከሃዋሳ ብሎ የሚጀምረው ሃሳቡ ማጠቃለያ "ሲጓዙ በግራ ሲሻገሩ በዜብራ" የሚለው መልእክቱ ነው፡፡

አደራጅ ዘርይሁን ይባላል ። ተወልዶ ባደገባት አለታ ወንዶ ከ2001 ዓም ጀምሮ በትራፊክ ላይ የሚሰሩ ክበባትን በመመስረት ወደ ሃዋሳ አስፋፍቶታል ።

49 የሚሆኑ ጓደኞቹ ዓላማውን ተጋርተው በትምህርት ቤቶች፣ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው አደባባዮችና በተለያዩ ስፍራዎች በትራፊክ ጉዳይ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡

በባለ ሁለት እግር ተሸከርካሪው እየተንቀሳቀሰም መፈክሮቹን ያሰማል "ሲጓዙ በግራ ሲሻገሩ በዜብራ ! ፍጥነት እድሜን እንጂ ኪሎ ሜትርን አይቀንስም ! " በቅስቀሳ ወቅት የሚጠቀምበት መለያው ነው፡፡

በቅርቡ ይደውልበት የነበረው ሬዲዮ ጣቢያ የምስረታ በዓሉን ሲያከብር እሱና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በሬዲዮ ጣቢያው ላይ የሚሳተፉ የዘወትር አድማጮች እንዲታደሙ አድርጓል ።

እኔና ጓደኖቼም ከመስራች ጋዘጤኞች ስም ዝርዝር ውስጥ ነበርንና ተሰባስበናል ፡፡ የሬዲዮ ጣቢያውን የ12 ዓመታት ጉዞ የሚያሳይ ጽሁፍ ቀርቦ ለውይይት መድረኩ ክፍት ሲሆን መድረኩን ይመሩ የነበሩት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የድርጅቱ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መለሰ አለሙ እድል ሰጡ፡፡

እድሉ እጁን ላነሳ ሁሉ የተሰጠ አልነበረም በዘወትር አድማጮች፣በተባባሪ አዘጋጆች፣ በመስራች ጋዜጠኞችና በሌሎችም የተከፋፈለና አጭር ነው፡፡

ይሄው ሁሌም ደውሎ ስለትራፊክ ጉዳይ የሚያወራው ወጣት ከጥቂቶቹ ተናጋሪዎች አንዱ ሆኖ ተከታዮቹ የሚጋሩትን የትራፊክ ጉዳይ አንስቷል፡፡

ቤተሰቦቻቸውን፣ጓደኞቻቸውና የሚያውቋቸውን በትራፊክ አደጋ ያጡ ሁሉ በማስታወስ ሬዲዮ ጣቢያውና ጋዜጠኞቹ   በትራፊክ ጉዳይ ላይ የበለጠ መሰራት እንዳለባቸው  ለክልሉ መንግስት ጭምር አደራ ብሏል፡፡

መገናኛ ብዙሃን ትልቅ ድርሻ ስላለቸው  የህብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያዳብሩ ፕሮግራሞችን ሊቀርጹ እንደሚገባም ጭምር፡፡

ወጣት አደራጅ የተሰጠውን እድል ተጠቅሞ የትራፊክ አደጋው አሳሳቢነት እስከ ቤት እየገባ ነው ሲል የቅርብ ጊዜ ትዝታውንና በበጀት ዓመቱ በሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ቱላ ክፍለ ከተማ መኖሪያ ቤት የገባው ተሸከርካሪ የአንዲት  ሴት ህይወት መቅጠፉን አንስቷል፡፡

በሃላባ ልዩ  ወረዳም መኖሪያ ቤት ድረስ ገብቶ ከስድስት በላይ ቤተሰቦችን ህይወት በአንድ ጊዜ ያጠፋበትን የዚሁ ዓመት ተመሳሳይ አደጋ አንስቶ ሲያበቃ "ሲጓዙ በግራ ሲሻገሩ በዜብራ" የሚለውን መልዕክቱን አስተላልፎ ንግግሩን ቋጭቷል፡፡

በዚህ መልዕክቱ በመገናኛ ብዙሃን የሚያውቁት የመድረኩ መሪና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በአካል ስላዩት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ስንጓዝ በግራ ስንሻገር ደግሞ በዜብራ የምትለው መልእክት ተገቢና በሃገር ደረጃ አስከፊ የሆነውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ቁልፍ ናት ብለዋል፡፡

ከክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው  በአሁኑ ወቅት አለማችንን ክፉኛ እያሳሰቧት ከሚገኙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች  ውስጥ የመንገድ ትራፊክ  አንዱ ሆኗል፡፡

ጥንቃቄ በማድረግ ልንከላከለው በምንችለው የትራፊክ አደጋ ሳቢያ ቤተሰብ እየተበተነ፣ብዙዎች ለአካል ጉዳት እየተዳረጉ፣ንብረት እየወደመና ሃገራትም ከድህነት ለመላቀቅ የሚያደርጉት ጥረት እየተጎተተ ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በ2015 ባወጣው ሪፖርት እንደሚጠቁመው ከ1ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሰዎች በትራንፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ ህይወታቸውን ሲያጡ ከ20 እስከ 50 ሚሊየን የሚደርሱት ደግሞ ለከባድና ቀላል የአደጋ ጉዳት ይዳረጋሉ፡፡

አደጋው ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት በጣም የከፋ መሆኑን የገለጸው መረጃው 90 ከመቶ መሆኑን ያሳያል፡፡

የትራፊክ አደጋ ከ15 እስከ 29 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶችን በመግደልም ቀዳሚ ከሆኑ 10 ችግሮች  አንዱ መሆኑን አመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያም በተመሳሳይ ለሃገሪቱ ወሳኝ የሆኑ ወጣቶችን፣ የተማሩና አምራች የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመቅጠፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያደረሰ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ የመንገድ ትራፊክ አደጋ መመዘኛና መለኪያ ሆኖ እየተሰራበት ባለው በ10ሺህ ተሸከርካሪዎች በሚደርሰው አደጋ ሞቱ ሲሰላ በ2008 በጀት ዓመት 61 ነጥብ 4 ከመቶ መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ይሄው ቁጥር ግን የመከላከሉን ስራ በከፍተኛ ሁኔታ በሰሩ ሃገራት ከ10 በታች ሲሆን በአፍሪካ እስከ 30 በመቶ ተመዝግቧል፡፡

ይህንን አሳሳቢ የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የ10 ዓመት የተግባር እቅድ የተዘጋጀ ሲሆን ሃገራችንም ከ2004 እስከ 2013 የሚዘልቅ የ10 ዓመት ስትራቴጅካዊ እቅድ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ናት፡፡

በመጀመሪያው አምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመኗም በ10ሺህ ተሸከርካሪ የሚደርሰውን አደጋ ወደ 27 ዝቅ ለማድረግ ብትንቀሳቀስም ቁጥሩ 61 ነጥብ 4 ከመቶ ላይ ነው ፡፡ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ  ዘመን  ወደ 27 በመቶ ዝቅ ማድረግ መታሰቡን መረጃው ያመላክታል ።

ሆኖም የ2ኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመኑ ሁለት ዓመታት ሪፖርት አዝማሚያ አስደንጋጭ በመሆኑ በተያዠው ዓመት ስራውን በንቅናቄ መምራት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

በመሆኑም መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን የመዘርጋት፣የህግ ማዕቀፎችን የማሻሻል፣ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የማገዝና ሌሎችን ተግባራትን እከናወነ ነው፡፡

በደቡብ ክልልም የመንገድ ትራፊክ አደጋ በክልሉ ህብረተሰብ ላይ እያደረሰ ያለውን ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለመከላከል በርካታ ተግባራት ቢከናወኑም አደጋው ከመቀነስ ይልቅ ከፍ ማለቱን መረጃች ያሳያሉ፡፡

በክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ስራ ሂደት ባለቤት አቶ መርከቡ ታደሰ እንደተናገሩ ከ2006 እስከ 2009 አጋማሽ በክልሉ የደረሰው የትራፊክ አደጋ የ1ሺ643 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡

አደጋውን በማድረስ  የጭነት ተሸከርካሪ 35 ነጥብ 1 በመቶውን ሲይዝ የህዝብ 22 ነጥብ 8፣ሞተር ብስክሌት ደግሞ 19 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ አለው፡፡

በእነዚህ ዓመታት በተመዘገበው ሞት ደግሞ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት በአደጋው ጊዜ ተሸከርካሪ ያልተጠቀሙ እግረኞች ናቸው፡፡

በ2009 ግማሽ ዓመት ጉራጌ፣ሲዳማ፣ጋሞጎፋ፣ወላይታ ስልጤ፣ጌዲኦ፣ሃዲያ ዞኖችና ሃዋሳ ከተማ ደግሞ ከፍተኛ ሞት የተመዘገበባቸው የክልሉ አካባቢዎች ናቸው፡:

የአሽከርካሪው ስነ ባህሪይና ክህሎት ማነስ፣ የተሸከርካሪው ብቃት ማነስና የእግረኛው የመንገድ አጠቃቀም፣ ከመንገድ ጋር የተያያዙ የዲዛይንና ተገቢ ምልክት አለማድረግም በክልሉ ለተከሰቱ አደጋዎች ቀዳሚ መንስኤዎች መሆናቸውን አቶ መርከቡ ተናግረዋል፡፡

እንደ ክልል ችግሩን ለመቅረፍ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ሲለዩም በመንገድ አጠቃቀም ላይ የሚታየውን የግንዛቤ እጥረት መቅረፍ ቀዳሚው ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም በገጠርና በከተማ አድረጃጀቶችን በመጠቀም፣ የአመራሩን ግንዛቤ በማሳደግ፣ በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች መታገዝና የሃይማኖት ተቋማት መደበኛ የስራቸው አካል እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራበት ነው፡፡

በተጨማሪም ለእግረኛ ተብለው የተገነቡ መንገዶችን ከተለያዩ ሸቀጦች መሸጫነት መከላከል ትኩረት ተሰጥቶበታል ብለዋል፡፡

የተሸከርካሪ ባለንብረቶችም የተሸከርካሪውን አካላዊና ቴክኒካዊ ደህንነት በመጠበቅ ተገቢውን መንጃ ፈቃድ ለያዙ አሽከርካሪዎች ብቻ ተሸከርካሪዎቻቸውን በመስጠት አደጋውን የመቀነስ ሃላፊነታቸው እንዲወጡ በቅንጅት እየሰሩ ነው፡፡

በክልሉ ማዕከላዊ ዞኖች አካባቢ የሚዘወተረው የሞተር ብስክሌት እያደረሰ ያለው አደጋ ከፍተኛ በመሆኑ ትርፍ በሚጭኑ፣ ያለሰሌዳና መንጃ ፈቃድ በሚያሽከርክሩና እድሜያቸው ለማሽከርከር ያልደረሱ ህጻናት ላይ ቁጥጥር በማድረግ አደጋውን የመቀነስ ስራው ተጀምራል፡፡

በዚህም ከ14ሺ በላይ ሞተር ሳይክሎችን ህጋዊ የማድረግና ትርፍ ጭኖ በሚንቀሳቀሱ ባለሁለት እግር ተሸከርካሪዎች ላይ ህብረተሰቡ ህግ አውጥቶ የመቅጣት እርምጃ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በመንገድ ጠርዝ ግራና ቀኝ ሶስት ሜትር ክፍት በማድረግ በመንገድ ዳር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማራቅና በየትምህርት ቤቱ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ክበባትን ማጠናከር ትኩረት ከተሰጠባቸው ስራዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በመንገድ ላይ የሚደረገውን የትራንስፖርት ቁጥጥር በአደጋ ቦታ፣ጊዜ፣መንስኤና ምክንያት ላይ ያተኮረ በማድረግ መስቀለኛ መንገዶች አደባባዮችና ለፍጥነት ምቹ የሆኑ መንገዶች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ትኩረት ይደረግበታል፡፡

በንቅናቄውም ከመንገዶች ባለስልጣን ጋር በመነጋገር በክልሉ ወላይታ፣ ጉራጌና ስልጤ ዞኖች ለአደጋ አስጊ የሆኑ ቦታዎች ተለይለው የማስተካከያ ስራ እየተሰራባቸው ነው፡፡

በቅርቡም የትራንስፖርት ስርዓቱን ሰላማዊና ከአደጋ የጸዳ እንዲሆን ለማድረግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 395/2009 ጸድቋል፡፡

በዚህ ደንብ ላይ ለሚመለከታቸው አካላት የግንዛቤ ስራ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት  በቢሮው የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አብርሃም ዳካ ናቸው፡፡

ባለሙያው እንዳሉት ደንቡ የትራንስፖርት ስርዓቱን ሰላማዊና ከአደጋ የጸዳ እንዲሆን የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ቢሆንም በህዝብ ንቅናቄ ችግሩን መፍታት እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

ደንቡ በማንኛውም ትራፊክ በኢትዮጵያ መንገዶች ላይ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ተፈጻሚነት ያለው በመሆኑ ክልሎች የተለያዩ ደንቦችን ከመተግበራቸው ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚፈታ ነው፡፡

94 የጥፋት ዝርዝሮችንና የሚወሰደውን እርምጃ አካቶ የያዘው ደንቡ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ የእግረኞችና የትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን የጥፋት ዝርዝሮችና የሚወሰዱ እርምጃዎችን ያካተተ ነው፡፡

አሽከርካሪዎች ተደጋጋሚ የደንብ ጥሰት እንዳይፈጽሙ ለመከላከል፣ህገ ወጥነትን ለመቀነስና እግረኞች ለአደጋ መከሰት አስተዋጽኦ እንዳያበረክቱ የሚረዳ ደንብ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በበኩላቸው አደጋውን ለመቀነስ መጋቢት 19 በተጀመረው ክልል አቀፍ የትራፊክ ንቅናቄ መድረክ አምስት ሚሊየን የሚደርሱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመድረስ የግንዛቤ ስራ ተሰርቷል፡፡

በዚህም ግንዛቤው ያደገ ህብረተሰብና አመራር መፍጠር፣ የሕግ ማስከበር  ክፍተቱንም ማረም የሚያስችል ግብ ተጥሎ በተሰሩ ስራዎች አመላካች ለውጦች ቢታዩም ውጤቱ በሃገር ደረጃ የሚገመገም ነው ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት ስርዓቱን መሰረታዊ ጉዳዮች ለማሳወቅ ከትምህርት ቤት ጀምሮ እንደሚሰራና በጤና ኤክስቴንቴሽን ፕሮግራሙም ገዳይ ከሚባሉት በሽታዎች ተርታ በመሆኑ ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታትና እስከ ያዝነው ዓመት አጋማሽ በደረሰ የትራፊክ አደጋ ከደረሰው 1ሺ643 የሞት አደጋ 1ሺ ስምንቱ ተሸከርካሪ ያልተጠቀሙ እግረኞች መሆናቸውን ያሳያል፡፡

እናም "ሲጓዙ በግራ ሲሻገሩ በዜብራ" የሚለው የወጣቱ መፈክር የሚያስፈልጋቸውን አካባቢዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች በመለየት መስራት እንደሚያፈልግ አመላካች ነው፡፡

 

Published in ዜና ሓተታ

አዲስ አበባ ግንቦት 27/2009 የአገሪቷን የእንስሳትና ዓሣ ኃብት ልማት ዘርፍ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ለግብዓት አቅርቦት ትኩረት መስጠቱን የእንስሳትና ዓሣ ኃብት ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸሙን የክልል የዘርፍ የሥራ ኃላፊዎችና የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት በቢሾፍቱ ገምግሟል።

በሚኒስቴሩ የአፈጻጸም ግምገማ ላይ የተሳተፉት በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ዮሴፍ ታደሰ  ዩኒቨርሲቲው ዝርያን በማሻሻል ረገድ ብዙ መስራቱን ተናግረዋል።

የተሻሻሉ የዶሮና የበግ ዝርያዎችን ለአካባቢው አርሶ አደሮች በማሰራጨት ላይ መሆኑንም አብራርተዋል። 

በተለይም በኦጋዴን ላሞች ላይ ባደረገው ዝርያ ማሻሻል አንዲት ላም በቀን እስከ ስምንት ሊትር ወተት እንድትሰጥ ማድረግ እንደተቻለ ገልፀዋል።  

ያም ሆኖ ስራው የታሰበውን ያህል ለውጥ ማምጣት እንዳልቻለ፤ ምክንያቱ ደግሞ ወደ አርሶ አደሩ ዘልቆ መግባት ባለመቻሉ እንደሆነ ነው የተናገሩት። 

ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ከግንዛቤ ጀምሮ በእንስሳት ጤናና እንክብካቤ በሁሉም ጉዳይ አርሶ አደሩ ድረስ ዘልቀው ካልገቡ ለውጥ አይመጣም ብለዋል።

ከሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም መረዳት እንደሚቻለው በዝርያ ማሻሻልና መኖ አቅርቦት ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።

የሚኒስቴሩ የፖሊሲ፣ የዕቅድና ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ብርቅነህ እንዳሉት በዘጠኙ ወራት መኖን በመስኖ በማምረት ድርቅ ተሻጋሪ የሆነ ማህበረሰብ ለመፍጠር ተሞክሯል።

በተጨማሪም ሚኒስቴሩ የአገሪቷን የማር ምርት ለአውሮፓ ገበያ ማቅረብ የቻለበት ወቅት እንደሆነም ጠቁመዋል።

በአንጻሩ በግብይት ሰንሰለቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ሚና አናሳ ሆኖ መገኘት እንደ ችግር ተነስቷል።

ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ በበኩላቸው በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ዘርፉን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የእንስሳትና ዓሣ ኃብት ልማት ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃ ለማቅረብና ለወጪ ንግድ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል።

ለወጣቶችና ሴቶች የተሻለ የስራ እድል መፍጠር እንዳስቻለና የገቢ ምንጫቸውን የሚያሳድጉበት ዋነኛ መንገድ እንደሆነም ተገልጿል።

ይሁን እንጂ እስካሁን ባለው ሁኔታ አገሪቷ በዘርፉ ያላትን እምቅ ኃብት ወደ ውጤት መቀየር አልተቻለም።

"ይህንን ችግር ለመቅረፍ በቀጣይ ሚኒስቴሩ የእንስሳትና ዓሣ ኃብት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ግብዓቶች አቅርቦት ላይ ትኩረት ያደርጋል" ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

የእንስሳት ጤናን መጠበቅ፣ በሽታዎችን መከላከል፣ የተሻሻሉ ዝርያዎችና የመኖ አቅርቦት ላይ በስፋት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ዘርፉ የተፈለገውን ያህል እንዳያድግ ማነቆ የሆነውን የአመለካከት ችግር መፍታትና ህገ-ወጥ የእንስሳት ግብይትን የማስቀረት ስራንም ያከናውናል።   

የክልል የዘርፍ የሥራ ኃላፊዎችና የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ተወካዮቹ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ወረዳ ወንጂ ከተማ አቅራቢያ ሁለት ሺህ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በ35 ማህበራት ተደራጅተው የጀመሩትን የእንስሳት ማድለብ ስራም ጎብኝተዋል። 

 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን