Items filtered by date: Saturday, 03 June 2017

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2009 አገሪቱ ከእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ዘርፍ የበለጠ ተጠቃሚ እንድትሆን ለግብአት አቅርቦት ትኩረት መሰጠቱን የእንስሳትና አሳ ኃብት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የክልል የዘርፍ የስራ ኃላፊዎችና የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት በተገኙበት የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸሙን በቢሾፍቱ እየገመገመ ነው።

ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

የእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለኢንዱስትሪዎች አስፈላጊውን ጥሬ እቃ ለማቅረብና ለወጪ ንግድ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል።

በተጨማሪም ለወጣቶችና ሴቶች በተሻለ መልኩ የስራ እድል ለመፍጠር እንዳስቻለና የገቢ ምንጫቸውንም የሚያሳድጉበት ዋነኛ መንገድ እንደሆነ ነው የተገለፀው።

ይሁን እንጂ እስካሁን ባለው ሁኔታ አገሪቱ በዘርፉ ያላትን እምቅ ሃብት ወደ ውጤት መቀየር አልተቻለም።

ይህንን ለመቅረፍ በቀጣይ ሚኒስቴሩ የእንስሳትንና የአሳ ሃብት ምርትንና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የግብአት አቅርቦት ላይ ትኩረት ያደርጋል ነው ያሉት።

የግብአት አቅርቦት ማለት የእንስሳት ጤናን መጠበቅ፣ በሽታዎችን መከላከልና የመኖ አቅርቦት ላይ በሰፊው እንደሚሰራ ነው ያመለከቱት።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ሌላው ዘርፉ የተፈለገውን ያህል እንዳያድግ ማነቆ የሆነው የአመለካከት ችግር በመሆኑ የህገ-ወጥ እንስሳት ግብይትን የማስተካከል ስራም ይሰራል ብለዋል።

ከሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም መረዳት እንደሚቻለው በዝርያ ማሻሻልና በመኖ አቅርቦት ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል።

በአንጻሩ ደግሞ የግብይት ሰንሰለት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ሚና አናሳ ሆኖ መገኘት እንደ ችግር ተነስቷል።

ውይይቱ ዛሬና ነገ የሚካሄድ ሲሆን ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት በዘርፉ ያከናወኗቸውን ተግባራት በተመለከተ ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2009 የጃፓን ዓለም አቀፍ ልማት ትብብር /ጃይካ/ በኢትዮጵያ አነስተኛ የአትክልትና ፍራፍሬ ማሳ ላላቸው አርሶአደሮች ገበያ ተኮር ምርት ለማምረት የሚያችላቸውን የቴክኒክ ድጋፍ ሊያደርግ ነው።

ኤጀንሲው ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚቆይና አትክልትና ፍራፍሬ አምራች አርሶአደሮችን የሚደግፍ ፕሮጀክት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ፕሮጀክቱ ከእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአማራ አዊና ምእራብ ጎጃም ዞን እንዲሁም በኦሮሚያ ጅማና አርሲ ዞን ተግባራዊ ይደረጋል።

በተመረጡ ወረዳዎች አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶአደሮች ምርታቸውን ገበያ ተኮር አድርገው በማምረት ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል ተብሏል።

ለዚህም ገበያው የሚፈልገው ምርት ምን እንደሆነ መረጃ በመሰብሰብና በማጥናት አምርተው ለገበያ የሚያቀርቡበትን አሰራር ይዘረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የፕሮጀክቱ አማካሪ ሚስተር ፉሚአኪ ሳሶ እንዳሉት ፕሮጀክቱ አርሶአደሩ አትክልትና ፍራፍሬን ለገበያ በሚሆን መልኩ እንዴት ማምረት እንዳለበት የገበያ ትስስርና የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

አርሶ አደሩ "የተመረተን መሸጥ ከሚለው ለመሸጥ ማምረት" የሚለውን አስተሳሰብ እንዲይዝ ማስቻልም ነው ብለዋል።

በእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር የአነስተኛ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዳሬክተር አቶ ደረጀ ይገዙ ፕሮጀክቱ ግብርናው በገበያው እንዲመራ ለተዘረጋው የኤክስቴንሽን ስትራቴጂ እውን መሆን ያግዘናል ብለዋል።

"አርሶ አደሩ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምርት እንዲያመርት በማድረግ የገቢ ምንጭ እንዲያገኝም የጎላ ሚና አለው" ነው ያሉት።

ኢትዮ-ሽፕ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ፕሮጀክት በተመረጡ ክልሎች ስድስት ሺህ አርሶአደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።

ፕሮጀክቱ በአፍሪካ በ2006 ኬንያ ላይ ተሞክሮ ውጤት ማምጣቱም ተነግሯል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2009 ባለድርሻ አካላት የኦሞ ጊቤ ተፋሰስን ስነ-ምህዳር በመጠበቅ/በኢኮ-ሀይድሮሎጂ/ ዘዴ ዘላቂነት ባለው መንገድ በጋራ ለማልማት ስምምነት ተፈራረሙ።   

 ባለድርሻ አካላቱ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ ውይይት ካደረጉ በኋላ ስምምነቱን የተፈራረሙ ሲሆን ተግባራዊነቱን የሚከታተል ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴም አቋቁመዋል።

 የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር በበላይነት የሚያስተባብረው ስብስብ የጅማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት፣ ጅማ ዩኒቨርስቲ፣ የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ቢሮ፣ የጅማ ከተማ አስተዳደር፣ የስነ ህዝብ ጤናና አካባቢ ጥበቃ ጥምረት በኢትዮጵያ፣ ግልገል ጊቤ 1 እና 2 የሃይል ማንጫ ጣቢያዎችና ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ከባለድርሻ አካላቱ መካከል ይገኙበታል።    

 በአዌቱ ወንዝ ላይኛው ንዑስ ተፋሰስ ላይ ከጅረቶች በመጀመር ውሃንና ንጥረ ነገሮችን ኡደትና የተፈጥሮ ኃይል ፍሰትን ማስተካከል፣ የቡና መፈልፈያ ፍሳሽ ቆሻሻ በማከም መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል፣ የተፋሰሱን አካባቢዎች ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ መጠበቅና የከተማ ጎርፍ ውሃን በማከም ጥቅም ላይ ማዋል ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ናቸው።     

 በኢትዮጵያ ካሉት 12 ተፋሰሶች ውስጥ የኦሞ ጊቤ ተፋሰስ አንዱ ሲሆን በርካታ የኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ ከተሞችና ነዋሪዎችን የያዘ ነው።

 እየጨመረ የመጣው የህዝብ ቁጥር፣ የኢንዱስትሪና እርሻ መስፋፋት፣ በውኃ ኃብት ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑ ለስምምነቱ መነሻ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው። 

 ሚኒስትር ደኤታው አቶ ከበደ ገርባ ለኢዜአ እንደገለጹት ስምምነቱ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩ በማድረግ በተፋሰስ ልማቱ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያግዝ ነው።

  ''በስምምነቱ መሰረት የትኛው የተፋሰሱ አካባቢ የጎላ ችግር አለበት፣ ምን አይነት ሥራ ይጠይቃል ለሚለው በጋራ ፕሮፖዛል ከተቀረጸ በኋላ ወደ ሥራ ይገባል'' ነው ያሉት።   

 ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ባከናወነችው ተግባር የአፍሪካ የኢኮ-ሃይድሮሎጂ ማዕከል ሆና መመረጧን ያስታወሱት አቶ ከበደ ይህን የሚመጥን የተፋሰስ ልማት ሥራዎችንን ማከናወን ይገባል ብለዋል።  

 የተፋሰስ ልማቱን ለማሳለጥ ባለፉት ዓመታት በአባይ፣ አዋሽና ስምጥ ሸለቆ ቦታዎች ላይ የተፋሰስ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች መቋቋማቸው ገልጸው በሌሎች ተፋሰሶችም ይሄው ተግባር እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

 ስምምነቱ በተፋሰስ ልማትና እንክብካቤ ላይ በተለምዶ ከሚሰራበት በመውጣት በኢኮ-ሀይድሮሎጂ ችግር ፈቺና ሞዴል ስራዎችን ለማከናወን ያስችላል ያሉት ደግሞ በሚኒስቴሩ የተፋሰስ አስተዳደር የኢኮ ሃይድሮሎጂ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስተባባሪ ዮሐንስ ዘሪሁን ናቸው። 

 ''የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ስራው ለጊዜው ከጅማ የላይኛው ጊቤ ይጀምራል'' ያሉት አስተባባሪው የሚገኘው ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንደሚሰፋ አብራርተዋል።

 ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ስምምነቱን ተፈጻሚ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።

 የጅማ ዩኒቨርስቲ ተወካይ ዶክተር ኢንጂነር ታማነ አዱኛ ዩኒቨርስቲው ስምምነቱን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚደረገውን ጥረት በጥናትና ምርመር የታገዘ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

 የጅማ ዞን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ኃላፊ አቶ ነዚፍ አባጨብሳ በበኩላቸው ስምምነቱ ላይ የተቀመጠውን ኃላፊነት ለመወጣት በመደበኛ እቅድ ውስጥ ተካቶ በየወረዳው እንዲሰራ ይደረጋል ነው ያሉት።

 ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 120 ቢሊዮን ኪዩቢክ የገጸ-ምድርና 30 ቢሊዮን ኪዩቢክ የከርሰ ምድር ውሃ ሃብት እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ።

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2009 እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ዘላቂ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገርና አረንጓዴ እንዲሆን ከአካባቢ ጋር የማጣጣም ስራው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የአካባቢ፣ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ቃሬ ጫውቻ የአካባቢና አየር ንብረት ምላሽ አፈጻጸም፣ ተግዳሮቶቻቸው እና መፍትሄዎቻቸውን በሚመለከት የተዘጋጀ ሰነድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።

የግልም ሆነ የመንግስት ድርጅቶች ከመቋቋማቸው በፊት በገቡት አካባቢንና ማህበረሰብን ከተጽዕኖ ነጻ የማድረግ ውል መሰረት በመንቀሳቀስ ረገድ በርካታ ክፍተቶች እየተስተዋሉባቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ክፍተቱን ለመቀነስ ጠንካራ የተጠያቂነት ስርዓት መዘርጋት አለበት ብለዋል። 

በህዝብ ተወካች ምክርቤት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና አካባቢ ጥበቃ ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ አሸናፊ ጋዓሚ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በገቡት አካባቢንና ማህበረሰብን ከተጽዕኖ ነጻ የማድረግ ውል መሰረት የማይሰሩ የግልም ሆነ የመንግስት ተቋማት በቀጣይ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2009 የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ውጤት ላስመዘገቡ የልዑካን ቡድን አባላትና አስተዋጽኦ ላደረጉ ክለቦች የእውቅና ሽልማት ሰጠ።

ሽልማቱ የተበረከተላቸው በ46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮናና በ18ኛው የሜጀር ጀነራል ሐየሎም አርዓያ መታሰቢያ ውድድሮች ላይ ወጤታማ ለሆኑት ነው።

በዚህም ለአትሌቶች ከወርቅ ሜዳሊያ ጀምሮ እንደየደረጃቸው ከ3ሺህ 500 እስከ 500 ብር ተሸልመዋል።

የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ቡድን አሠልጣኞችና የቡድን አባላት አስተባባሪዎች ደግሞ የሁለት ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ውጤታማ አትሌቶችን በማስመረጥ የኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌቲክስ ክለብ ቀዳሚ ሲሆን ሌሎች የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ክለቦች የምስጋናና የዕውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2009 የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ኤች. አይ. ቪ /ኤድስን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው የፌዴራል ኤች. አይ. ቪ /ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት አሳሰበ።

 ይሕ የተባለው በፌዴራል መስሪያ ቤቶች መካከል ለስድስተኛ ጊዜ በተካሔደው ኤች. አይ. ቪ /ኤድስን በመከላከልና መቆጣጠር ላይ በሚወያይ መድረክ ነው።

 የጽህፈት ቤቱ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ማስተባበር ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ምትኩ እንደተናገሩት መስሪያ ቤቶች የሚያስተዳድሩት የልማት ኃይል ለኤች. አይ. ቪ /ኤድስ ተጋላጭ እንዳይሆን ሊሰሩ ይገባል፡፡

 በአሁኑ ወቅት በስርጭቱ ቀንሷል በማለት ሳይዘናጉ ሰራተኛው ከበሽታው ራሱን እንዲጠብቅ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡

 አንዳንድ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ቫይረሱን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ አበረታች ውጤት ያመጡ ሲሆን በርካቶቹ ግን ትኩረት ሲቸሩት እንደማይታዩ ተናግረዋል፡፡

 የመንግስት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ባለሙያ ወይዘሮ ሁሉአገርሽ ታዘዝ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኤጀንሲው ባለፉት ዘጠኝ ወራት  የምክክር መድረኮች በማዘጋጀት፣ በራሪ ፅሁፎችን በማደል፣ የቡድን ውይይቶችን በማካሄድ የሰራተኞችን ግንዛቤ  እንዲጎለብት አድርጓል።

 በዚሁ ወቅትም ከሰራተኛው የተሰበሰበ 35 ሺህ 100 ብር ለ27 ሰራተኞችና ቤተሰቦቻቸውን በህመሙ ላጡ ህፃናት በየወሩ በባንክ ቁጥራቸው ገቢ መደረጉን አስታውቀዋል።

 ከዚህ በተጨማሪም 197 የሚሆኑ የተቋሙ ሰራተኞች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኤች. አይ. ቪ /ኤድስ ምርመራ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸታቸውን ነው የገለጹት፡፡

 በእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር የጸረ-ኤች አይ ቪ ሜንስትሪሚንግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ንግስት ከበደ ኤች. አይ. ቪ /ኤድስን የመከላከልና የመቆጣጠር ሰራ በመስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጡት ተግባራት መካከል ነው፡፡

 ተቋሙ ዘጠኝ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰራተኞች እና ስምንት ወላጆቻቸውን በቫይረሱ ምክንያት ላጡ ህፃናት በተቋሙ ሰራተኞች በሚደረግ መዋጮ እንደሚደግፍም ገልፀዋል።

 በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ተወካይ ሲስተር ፅጌ ህይወት ወንድምአገኘሁ እንደገለፁት በበጀት አመቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን የመስጠት፣ ብሮሸሮችን የመበተን ስራ ተሰርቷል።

 ከዚህ ባሻገር በዋናው እና በቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩ ሰራተኞችና ቤተሰቦች የምክርና የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

 የራሳቸውን ስራ ፈጥረው መስራት ለሚፈልጉም እስከ 50 ሺህ ብር ከወለድ ነጻ ብድር እንደሚሰጣቸው ተወካዩዋ ገልጸዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2009 የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች  አሰግድ ተስፋዬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

የቀድሞው ተጨዋች ዛሬ በድንገት መታጠቢያ ቤት ወድቆ በሞት እስከተለየበት ጊዜ ድረስ ''አሰግድ ተስፋዬ'' በሚል ስያሜ ታዳጊ የእግር ኳስ ፕሮጀክቶችን በማሰልጠን ላይ ነበር።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ተጨዋች አሠግድ ተስፋዬ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

''አሰግድ ተስፋዬ በመልካም ሥነ-ምግባሩና በልዩ ችሎታው የእግር ኳስ አፍቃሪዎችን የማረከ፣ አገሪቷን በክብር ያስጠራ፣ ለወጣት ተጨዋቾች ምሳሌ በመሆን በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱት ጥቂትና ምርጥ የእግር ኳስ ስፖርት ተጨዋቾች መካከል አንዱ'' ነው ብሏል፡፡

ወጣት ታዳጊዎችን በማሰልጠን አገሪቱ በእግር ኳስ ስመ-ጥር አትሌት እንድታፈራ ሳይታክት በመስራት ላይ እንደነበርም መግለጫው ጠቁሟል፡፡

ፌደሬሽኑ በተጨዋቹ  ህልፈተ-ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ ለእግር ኳስ ስፖርት አፍቃሪዎችና ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና ለአድናቂዎቹ  መፅናናትን ተመኝቷል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 26/2009 የአዲስ አበባን የትራንስፖርት እጥረት ለማቃለል የ850 የከተማ አውቶቡሶች ግዥ ሊፈጽም መሆኑን የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የበጀት አመቱን የ10 ወር እቅድ አፈጻጸም ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የከተማ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።

በሪፖርቱም በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት እጥረትና ሌሎች ከመንገድ ጋር ተያያዥ ችግሮች መኖራቸው ተገልጿል።

የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኪዳኔ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት በአዲስ አበባ ሰፊ የትራንስፖርት እጥረት ይታያል፤ ችግሩን መቅረፍ የሚቻለው አቅርቦቱን ማሻሻል ሲቻል ነው የሚል እቅድ ይዘን እየሰራን ነው ብለዋል።

በመሆኑም ቢሮው ይህን ችግር ለማቃለል 850 አዳዲስና ዘመናዊ የከተማ አውቶቡሶች ግዥ ለመፈጸም በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከሚገዙት ዘመናዊ አውቶቡሶች መካከል 100 የሚሆኑት ለተማሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ ሲሆኑ ቀሪዎች 750ዎቹ ለከተማዋ ነዋሪዎች የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከነዚህ መካከል 50ዎቹ ከላይና ከታች ሰው መጫን የሚችሉ ዘመናዊ አውቶብሶች ናቸው ተብሏል።

አጠቃላይ የሚገቡት አውቶቡሶች ከ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግባቸው የጠቀሱት የቢሮው ኃላፊ ከ2010 ጥቅምት ወር ጀምሮ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ብለዋል።

ይህም በከተማው የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ሙሉ ለሙሉ የሚቀርፍ ባይሆንም፤ ችግሩን በተወሰነ መልኩ እንዲቃለል ያደርገዋል ነው ያሉት።

ግዥው በመንግስት ደረጃ የሚፈጸም ሲሆን  ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ የመገጣጠሙን ስራ ያከናውነዋል።

ቢሮው በቀጣይም የህብረተሰቡን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል እንደሚሰራ አቶ ሰለሞን አክለዋል።

Published in ማህበራዊ

ጅግጅጋ ግንቦት 26/2009 በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጂግጂጋ አገልግሎት የማይሰጡትን  የእንስሳት ኳራንቴንና የኤክስፖርት ቄራ  ፈጥኖ ስራ ማስጀመር እንደሚገባ  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ለአንድ ሳምንት በክልሉ ፋፈን እና ሲቲ ዞኖች የተለያዩ የመሰረተ ልማትና የመንደር ማሰባሰብ ስራዎችን ተመልክተዋል፡፡

ከመስክ ምልከታው በኋላ ከክልሉ አመራሮች ጋር ውይይት ባካሄዱበት ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አጥናፉ ጌጡ  እንዳሉት በፋፈን ዞን ጅግጅጋ ከተማ አቅራቢያ የተሰራው  የእንስሳት ኳራንቲን  ግንባታ ቢጠናቀቅም ለተቋራጩ ክፍያ ባለመፈፀሙ ምክንያት ርክክብ አልተደረገም፡፡

ኳራንቲኑን አገልግሎት ለማስጀመር ከከፍያ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በመፍታት ቁሳቁስና የሰው ሃይል ተመድቦለት በፍጥነት አግልግሎት እንዲሰጥ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

"የጅግጅጋ ኤክስፖርት ቄራ በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በቅርቡ ያጋጠመውን የእንስሳት አቅርቦት እጥረት ተከትሎ ስራ እስከ ማቆም ደርሷል " ብለዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት የአርብቶ አደር ወጣቶችን በእንስሳት ንግድ ስራ ተሳታፊ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የቡድኑ አባል ወይዘሮ ሀዋ አሊ በበኩላቸው "በተለይ የኤክስፖርት ቄራው ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ አማራጭ የእንስሳት ገበያ የሚፈጥር ነው" ብለዋል፡፡

ህገ ወጥ ደላላዎችን ሰርዓት በማስያዝ  ለአርብቶ አደሩ የገበያ ትስስር በመፍጠር በቀጥታ ተጠቃሚ የሚሆንበት እድል ሊመቻችለት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ 

በጅግጅጋ ወረዳ አመድሊ ቀበሌ በአርብቶ አደሩ  የትምህርትና የጤና አገልግሎት አሰጣጥ  ላይ ያለውን ክፍተት ማስተካከል እንደሚገባም አሳስበዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በሲቲ ዞን ሀረዋ ቀበሌ የአርብቶ አደር ነዋሪዎችን በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የመንደር ማሰባሰብ ስራ ለማካሄድ የተጀመረው የቅድመ ዝግጅት ስራ መልካም አፈፃፀም እንዳለው ገልጿል፡፡

የክልሉ የእንስሳትና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አሊ ኡመር የእንስሳት ኳራንቴን አገልግሎት እንዲጀመር ከፌደራል እንሳስትና ዓሳ ሀብት ልማት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም " የጅግጅጋ ኤክስፖርት ቄራውን  በአቅራቢው በእንስሳት ንግድ ስራ ከተሰማሩ ማህበራት ጋር ለማስተሳሰር ጥረት እየተደረገ ነው" ብለዋል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም መሀድ በበኩላቸው በክልሉ እየተካሄደ ባለው የትምህርት ልማት ስራዎች የመምህራን እጥረት ዋነኛ ችግር እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ስድስት መቶ እጩ መምህራንን  በመጪው ክረምት   ለማሰልጠን ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

ከመምህራን የደመወዝ መዘግየት፣ ከመኖሪያ ቤት እጥረት፣ የትምህርት ቤቶች የመብራት እና የውሃ አገልግሎት አለመኖርን አስመልክተው በቋሚ ኮሜቴው የተነሱት ችግሮችን ለማቃለልም በ2010 በጀት ዓመት በእቅድ ውስጥ ለማካተት እንደሚሰሩ አመልክተዋል፡፡ 

የክልሉን መንግስት የሚመራው የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( ኢሶህዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኡመር መሐመድ በትምህርት፣ በጤናና በመንደር ማሰባሰብ ላይ ከቋሚ ኮሚቴው ያገኛቸውን ክፍተቶች ለማስተካከል ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አብራርተዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ
Saturday, 03 June 2017 22:46

የእድገት መሰረት

Published in ቪዲዮ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን