Items filtered by date: Friday, 02 June 2017

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2009 በስነ-ምግባር የታነጸ፣ አገር ተረካቢ ትውልድን ለመፍጠር ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ፤ ስብዕናቸው የተሟላ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ለአገሪቷ እድገትና ብልጽግና የላቀ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ዜጎችን ማፍራት የሚቻለው በትምህረት በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባ ገልጿል።

ለዚህም ተማሪዎች፣ ወላጆችና መምህራን የጎላ ሚና ሊጫወቱ ይገባል።

የትምህርትን ጥራት መጠበቅና ማሳደግ እንዲሁም ተደራሽነቱን የማስፋት ስራንም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቋል።

የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አኳያ ፈተናዎች የነገ አገር ተረካቢ ምሁራን የሚለዩባቸው መሳሪያዎች መሆናቸውን ተገንዝበው ራሳቸውን በስነ-ምግባር በማነጽ ለእውቀት ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አመልክቷል።

በተጨማሪም ወላጆችና መምህራንም ተማሪዎች በእውቀት የበለጸጉና አስተማማኝ ክህሎት ኖሯቸው፣ የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ እንዲሆኑ መትጋትና የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ጠቅሷል። 

በመሆኑም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የትምህርት አመራር አባላት፣ ተቆጣጣሪዎች፣ ባለሙያዎች፣ ፈታኞች፣ አስተባባሪዎች፣ መገናኛ ብዙሃንና መላው ህብረተሰብ በጋራ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርቧል።

Published in ማህበራዊ

አዳማ ግንቦት 25/2009 በኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የሞጆ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለዘንድሮው የመኸር አዝመራ የሚውል ከ184 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ማሰራጨቱን አስታወቀ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የጽህፈት ቤቱን የስራ እንቅስቃሴ በሞጆ ከተማ በመገኘት የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

በመስክ ምልከታው ወቅት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዋሴ ጫኔ እንደገለፁት ጽህፈት ቤቱ ከውጭ የገባውን ማዳበሪያ በመረከብ ያሰራጨው ለኤረር፣ አዋሽ መልካና ለከሰም የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየኖች ነው ።

ጽህፈት ቤቱ ካሰራጨው ማዳበሪያ በተጨማሪ ፀረ አረም፣ ፀረ ፈንገስና ፣ፀረ ተባይ መድሀኒቶች ማቅረቡንም ገልጸዋል ።

በሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ ለአርሶ አደሩና ለሰፋፊ እርሻ ልማት ድርጅቶች የማሳ ዝግጅትና ምርት ማሰባሰብ አገልግሎት በመስጠት እስከ ሶስተኛው ሩብ አመት ድረስ ከ732 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ለደቡብ ኦሞ ስኳር ፋብሪካ ፣ ለኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪና ትግራይ ክልል አላማጣ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የማሳ ዝግጅት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።

ጽህፈት ቤቱ ለሚያካሄደው የግብርና ሜካናይዜሽን ዘርፍ የእርሻ ትራክተርና የመውቂያ ኮምባይነር እጥረት እንዳለበትም አብራርተዋል።

የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ የጽህፈት ቤቱ የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው በመጎብኘት ከሠራተኞች ጋር የተወያዩ ሲሆን በተለይ ጽህፈት ቤቱ እንደ ችግር ያነሳውን የመሳሪያ እጥረት እንዲቃልል ከሚመለከተው አካላት ጋር በመነጋገር ለመፍታት ጥረት እንደሚያድረጉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን፤ የግብርና ግብአት አቅርቦትና ዘመናዊ እርሻ ልማትን ማስፋፋት አላማ አድርጎ የተቋቋመው በነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም ነው፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2009 የመገናኛ ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆያ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

በ50 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የተሽከርካሪ ማቆያው ስራ መጀመር ያለውን የትራፊክ መጨናነቅና የማቆያ ቦታ ችግር ለመቀነስ እንደሚያስችል ነው የተገለጸው።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ የመኪና ማቆያውን ሲመርቁ እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ ስራ መጀመሩ ከዕድገቱ ጋር ችግር እየሆነ የመጣውን የትራፊክ ችግር ከማቃለል ባሻገር ለ40 ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሯል።

ከንቲባው አክለውም በትራንስፖርቱ ዘርፍ የሚታየውን ችግር ለማቃለል በሌሎች አካባቢዎች የማቆያ ቦታዎችን ይሰራል። የመንገድ እንቅስቃሴ ችግሮችንም ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ።

ዛሬ ተመርቆ ለስራ ዝግጁ የሆነው ባለማማ የተሽከርካሪ ማቆያ በአሳንሰር ተደግፎ የሚሰራ ሲሆን፤ 90 ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ የመያዝ አቅም አለው።

ፕሮጀክቱ በቻይናው ዲያንግ ፓርኪንግ ኩባንያና ሲስፕሮዪንግ ሲስተምስና ፕሮጀክት ኢጅነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በጋራ የተገነባ ነው።

በዚሁ ግቢ 50 ተሽከርካሪዎችን የሚይዝ የመሬት ላይ የተሽከርካሪ ማቆያና የመገናኛ አደባባይ የአውቶቡስ መቆሚያ የፕሮጀክቱ አካል ሆነው ስራ የጀመሩ ናቸው።

የመገናኛ የተሽከርካሪ ማቆሚያ በ170 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፤ ባለአሳንሰሩ ማቆያ 40 ሜትር ከፍታና 15 ደረጃዎች ያሉት ነው።

በማቆያ ስፍራው በሰውና በተሽከርካሪ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የመቆጣጠሪያ መሳሪያ እንደተገጠመለት በትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የመሰረተ ልማት ስራ ክፍል ኃላፊ ኢንጂነር ትንሳኤ ወልደገብርኤል ተግረዋል።

የግንባታውን ስራ በኃላፊነት ሲሰራ የቆየው የትራንፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ሲሆን፤ በተመሳሳይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወሎ ሰፈር 40 ተሽከርካሪዎችን የሚይዝ የተሽከርካሪ ማቆያ ገንብቶ በዛሬው ዕለት ተመርቋል።

የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ብርሃኑ ግርማ እንደገለጹት፤ ማቆያውን የሚጠቀም ተሽከርካሪ ለመጀመሪያ 1 ሰዓት 6 ብር ከዚያ በኋላ ላሉት እያንዳንዱ ሰዓታት ደግሞ 9 ብር እየከፈለ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት አገልግሎት ይሰጣል።

ከተወሰነው ሰዓታት ማቆያነት ስራው በተጨማሪ የተሽከርካሪ ማሳደር አገልግሎትም በ20 ብር ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋቱ 2 ሰዓት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ከዚሁ አገልግሎት ጎን ለጎን የተሽከርካሪ እጥበት አገልግሎትም ይሰጣል ተብሏል።

የፕሮጀክቱ ስራ በዋናነት የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት ለማስተካከል የተሰራ ቢሆንም ከስራው ተመጣጣኝ ገቢ ለማግኘት ሁለት ትላልቅ የማስታወቂያ ስክሪኖች በማማው ላይ ተገጥመዋል። በዚህም ለማስተዋወቅ ለሚፈልጉ በክፍያ አገልግሎት ይሰጣሉ።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት25/2009 የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በአንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ወጪ የስድስት ውሃና ፍሳሽ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሊያካሂድ ነው።

የባለስልጣኑ የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋለም ባዩ ከሲ ጂ ሲ፣ አሰር፣ ሲና እንዲሁም ዮት ከተባሉ የአገር በቀልና የውጭ የስራ ተቋራጮች ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ባለስልጣኑ እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ በለገዳዲ ጥልቅ የጉድጓድ ውሃ ማጣሪያ፣ በጨፌ ክፍል ሁለት ፍሳሽ ማጣሪያና በሌሎች አዳዲስ የፍሳሽ ቅብብሎሽ ጣቢያ ስድስት ፕሮጀክቶችን እንደሚያከናውን አቶ ተስፋለም ተናግረዋል፡፡

የውሃ ማምረቻ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ በቀን እስከ 86 ሺ ሜትር ኪዩብ በማምረት  ከ860 ሺ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ በቀን ከ12 ሺ ሜትር ኪዩብ በላይ የማጣራት አቅም ይኖራቸዋል፡፡

እንደ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋለም ገለጻ፤ ባለስልጣኑ የነባር ፕሮጀክቶችን የማሻሻያ ስራ በማከናወን ላይ ነው። በቅርብ ጊዜያትም ተጠናቀው አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር ግንቦት 25/2009 የህብረት ሥራ ማህበራት በክልሉ እየተመዘገበ ላለው ኢኮኖሚያዊ እድገት ሚናቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለፁ።

''የህብረት ስራ ማህበራት ግብይት ለህዳሴያችን'' በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሲፖዚየም ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በሲፖዚየሙ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት የህብረት ስራ ማህበራት በክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ እየተመዘገበ ላለው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት የላቀ እገዛ እያደረጉ ነው ።

የህብረት ስራ ማህበራት ምን ሰሩ?

ለአርሶ አደሩ የምርት ማሳደጊያ ግብአት በጥራትና በወቅቱ በማድረስ ለግብርና ምርታማነት የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ናቸው፡፡

በከተሞችም ለሸማቹ ህብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ የግብርና ምርቶችን በማቅረብ ገበያው ተረጋግቶ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።                    

በተጨማሪም በአርሶ አደሩ ዘንድ ቁጠባ እንዲለመድና እንዲስፋፋ በማድረግ ለክልሉ ልማት መፋጠን ሚናቸው እየተወጡ እንደሆነም ተናግረዋል።

በቀጣይም የህበረት ስራ ማህበራት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚያደርጉት መዋቅራዊ ሽግግር የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና  እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

 በክልሉ ያመነጩት ኢኮኖሚ

የክልሉ ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ  ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ትልቅ ሰው ይታያል በበኩላቸው በክልሉ ጠንካራ የህብረት ስራ ማህበራት እንዲፈጠሩ እየተሰራ ነው።

ባለፉት አመታት በተከናወኑ ተግባራት  ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ አባላት ያፈሩ ከ13 ሺህ የሚበልጡ የህብረት ስራ ማህበራት ተቋቁመዋል፡፡

ከእነዚሁ አባላትም  ከ1 ነጥበ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በቁጠባ ማሰባሰብ እንደተቻለ ገልፀዋል፡፡

ማህበራቱ ባደረጉት ጠንካራ የገበያ እንቅስቃሴም በዚህ ዓመት ከ76 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ምርት ወደ ውጪ ሀገራት በመላክ ከ22 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ  ገቢ አስገኝተዋል፡፡

“በህብረት ስራ ማህበራት ዘንድ የሚስተዋሉ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባርን በመከላከል የአባላቱን ተጠቃሚነት የበለጠ ለማረጋገጥ  ኤጀንሲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው'' ብለዋል።

በህብረት ስራ ማህበራት የአሰራር ግልፅነትን ለማስፈን

የፌዴራል ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው በተለይ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት የአርሶ አደሩን የፋይናንስ ችግር እያቃለሉ ይገኛሉ።

''በህብረት ስራ ማህበራት የሚስተዋለውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ለመቅረፍም የአሰራር ግልፀኝነት እንዲሰፍን በኤጀንሲው የህግ ማዕቀፍ እየተዘረጋ ነው'' ብለዋል ።

ዛሬ በተካሄደው ሲፖዚየም ላይ በአማራ ክልል ከሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት፣ ከፌዴራልና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ከ700 በላይ እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል ።

ከነገ ጀምሮ ደግሞ ለስድስት ቀናት የሚቆይ ክልል አቀፍ የህብረት ስራ ማህበራት ግብይት ኤግዚቪሽንና ባዛር እንደሚከፈት ታውቋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2009 በአፍሪካ ሕብረት በገንዘብ ራስን የመቻል ለውጥ ስራ ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን አጠናክራ እንድትቀጥል ሕብረቱ ጥሪ አቀረበ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአፍሪካ ሕብረት የከፍተኛ ፓናሊስት ሊቀ-መንበር ዶክተር ዶናልድ ካቢሩካን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በቀጣዩ ሰኔ ወር በሕብረቱ አባል አገራት ስብሰባ ላይ ለሚቀርበው የለውጥ አጀንዳ ሂደት ግብአት ለማግኘት የተደረገ ውይይት መሆኑ ተገልጿል።

የኅብረቱ አባላት ወደ አገራቸው ከሚያስገቡት ምርት የሚሰበሰብ የቀረጥ ገቢ 0 ነጥብ 2 በመቶ ያህሉን ለኅብረቱ እንዲሰጡ በ27ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ባሳለፍነው 2016 የፈረንጆች ዓመት በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ በተካሄደበት ወቅት መወሰኑ ይታወቃል።

በውሳኔው መሰረት ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ቻድ፣ ኢትዮጵያና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቀድመው ውሳኔውን መተግበር የጀመሩ አገራት ናቸው።

ዶክተር ዶናልድ በሕብረቱ በፋይናንስ ራስን የመቻል የለውጥ አጀንዳ መሰረት እስካሁን በተሰሩ ሂደቶች በሚቀሩት ስራዎች ላይ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሪፎርሙን በመደገፍ እስካሁን ላደረገችው ጥረት ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በሕብረቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ሪፎርሙ አፍሪካ በፋይናንስ ራሷን እንድትችልና ከበለጸጉ አገራት ተፅእኖ የተላቀቀችና ጠንካራ አህጉር የሚያደርት በመሆኑ ሁሉም አባል አገራት እንደ ኢትዮጵያ ለውሳኔው ተግባራዊነት እንዲተጋ ጥሪያቸውን አስተልፈዋል።

በዚሁ ሪፎርም ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ጀምሮ እያደረገች ያለችውን ጠንካራ ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጥሪ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

እስካሁን ድረስም ሁሉም የአፍሪካ አገሮች በሪፎርሙ ሂደት ጥሩ ሊባል በሚችል ደረጃ የተሳትፎ ቁርጠኝነታቸውን እያሳዩ ነው ብለዋል።

ከውጭ ተፅእኖ የተላቀቀችና በዓለም ዓቀፍ መድረክ ተሰሚነቷን ከፍ ለማድረግ በሚደረገው በዚሁ ሪፎርም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ከመወጣት አኳያ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2009 ለ17ኛ ጊዜ የሚካሄደው የቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ምዝገባ በመጪው ሰኞ እንደሚጀመር አዘጋጆቹ ገለፁ።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ በመጪው ዓመት ህዳር 17 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለሚካሄደው ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 44 ሺህ ሯጮችን ለማሳተፍ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

42 ሺህ ሯጮች በተሳተፉበት በ16ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 477 ቲሸርቶችን አስመስለው በማሳተም የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደነበር መገለጹ የሚታወስ ነው።

በመጪው ዓመት ለ17ኛ ጊዜ በሚካሄደው ውድድር ላይ ይህ አይነት ችግር እንዳይፈጠር የተለየ ዝግጅት መደረጉን አቶ ኤርሚያስ ገልጸዋል።

"በህገወጥ መንገድ ቲሸርቶች ተሰርተው በሩጫው እንዳይሳተፉ ለማድረግ ''ባር ኮድ'' የተሰኘ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ብቻ የተሰሩ ቲሸርቶችን የሚያነብ ቴክኖሎጂን እንጠቀማለን" ብለዋል።

ሩጫው በሚደረግበት ዕለት በዚህ ቴክኖሎጂ ቲሸርታቸው እየተነበበ ወደ ሩጫ ቦታው የሚገቡ በመሆኑ ተመሳሰለው የሚሰሩ ቲሸርቶችን በቀላሉ የምንለይ ይሆናል ነው ያሉት።

ቴክኖሎጂው ቲሸርቶችን በህገ-ወጥ መንገድ የሚሰሩ ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ አመቺ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2009 አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ የግንቦት 20ን 26ኛ ዓመት የድል በዓል ምክንያት በማድረግ ለፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲጎለብቱ፣ የአገሪቱ ልማትና እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ለማገዝ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት እንደምትፈልግም በመልዕክታቸው ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በዓሉን አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሁለቱ አገራት የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ በቀጣይም በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በክልላዊና በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል።

በተጨማሪም የእስራኤል ፕሬዝዳንት ሪቪን ሪቭሊን፣ እንዲሁም የፖርቹጋሉ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ማርሴሌ ሬቤሎ ደሱሳ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ አስታውቋል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2009 በአገር አቀፍ ደረጃ ሲሰጥ የቆየው የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም መጠናቀቁን የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ረዲ ሽፋ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፤  ብሔራዊ ፈተናው በተቀመጠው መርሃ-ግብር መሠረት ካለምንም መስተጓጎል በሰላም ተጠናቋል፡፡

"ከፌዴራል እሰከ ትምህርት ቤቶች የተቋቋመው ግብረ ኃይል በቅንጅት በመስራት ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል" ብለዋል።

በፈተና ወቅት የሚታዩ የህግ መጣስ ተግባራት እየተቃለሉ መምጣታቸውን ያወሱት አቶ ረዲ፤ የዚህን ዓመት የፈተና ሥርዓት ሁኔታም አጠቃላይ ሪፖርቱ ተጠናቆ ሲደርሰ ይፋ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ከግንቦት 28 እስከ ሰኔ 01 ቀን 2009 ዓ.ም የሚሰጠውን ብሔራዊ  ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አቶ ረዲ አስታውቀዋል።

ከግብረ ኃይሉ በተጨማሪ የትምህርት ባለሙያዎች፣ የፖሊስ አባላት፣ ወላጆችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ብሔራዊ ፈተናው  በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ላደረጉት አስተዋጽኦ ምሥጋና አቅርበዋል።

ከግንቦት 23 እስከ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በተሰጠው የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና 1 ሚሊዮን 206 ሺ 869 ተማሪዎች ፈተናውን የወሰዱ ሲሆን፤ 46 ነጥብ 74 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸው።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2009 የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2010 ዓመታዊ በጀት ከ320 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሆን ውሳኔ አሳለፈ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 31ኛ መደበኛ ስብሰባው በ2010 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀትን 320 ቢሊዮን 803 ሚሊዮን 602 ሺህ 160 ብር መሆኑን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ከሃምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በሚፈጸመው በአንድ የበጀት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለመደበኛ ወጪዎች 81 ቢሊዮን 839 ሚሊዮን 528 ሺህ 570 ብር እንዲሁም 114 ቢሊዮን 703 ሚሊዮን 641 ሺህ 453 ብር ደግሞ ለካፒታል ወጪዎች ይውላል።

117 ቢሊዮን 260 ሚሊዮን 432 ሺህ 137 ብር ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ ሲሆን ሰባት ቢሊዮን ብሩ ደግሞ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ እንዲውል ተመድቧል።

በጀቱ እንዲጸድቅም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርቷል።

ምክር ቤቱ ውሳኔ ያሳለፈበት የ2010 በጀት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በዘጠኝ ነጥብ ስድስት በመቶ ብልጫ አለው።

ከዚህ በተጨማሪም ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው በጤናው ዘርፍ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ለሚከናወን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ከአለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር የተፈረመው የብድር ስምምነት አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ አዋጆቹ እንዲጸድቁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተላልፏል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን