Items filtered by date: Sunday, 18 June 2017

አዲስ አበባ ሰኔ 11/2009 ለካንሰር ሕክምና ተገቢው ትኩረት ባለመሰጠቱ ‘ሕይወታችን አደጋ ላይ ነው’ ሲሉ የካንሰር ሕሙማን ገለጹ።

የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በበኩሉ ከታማሚው ቁጥር አንጻር ማዕከሉ የሕክምና መሣሪያና ቦታ እጥረት በማጋጠሙና ሕሙማኑ በወቅቱ ተገቢውን ሕክምና ባለማግኘታቸው ከተመዘገቡት መካከል ከ23 እስከ 25 በመቶ የሚሆኑት ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ ብሏል። 

የማሕፀን በር ካንሰር ታማሚ የሆኑ አክስታቸው ወይዘሮ ፀሐይ አሊን በማስታመም ላይ የነበሩት አቶ አሊ ይማም ለካንሰር ሕክምና አገልግሎት የተመዘገቡት ከሁለት ዓመት በፊት ቢሆንም አገልግሎት ያገኙት ግን ከ6 ሳምንት በፊት እንሆነ ተናግረዋል። 

የአፍንጫ ስር ካንሰር ታካሚዋ ወይዘሪት እታገኝ ጌትነት በበኩሏ ሕክምናውን ለማግኘት የተመዘገበችው በ2007 ዓ.ም ቢሆንም ወረፋው የደረሳት ግን ከሦስት ሳምንታት በፊት እንደሆነ ገልጻለች።

አቶ አሊ ይማምና ወይዘሪት እታገኝ ጌትነት ታማሚዎች ሕክምናውን በወቅቱ ባለማግኘታቸው በርካቶች ለሕልፈተ ሕይወት እየተዳረጉ መሆናቸውን በሆስፒታሉ ቆይታቸው የታዘቡትን ገልጸዋል።

በዚህም መንግሥት ለካንሰር ሕክምና ትኩረት በመስጠት ሕሙማንን ሊታደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ የካንሰር ሕክምና ማዕከል የካንሰር ህክምና ባለሙያና የጨረራ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ወንድማገኝ ጥግነህ እንደገለጹት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በቅድመ ካንሰር መከላከል ላይ አልተሰራም።

በዚህም ሕክምና ለማግኘት ከሚመጡት ታካሚዎች መካከል 70 በመቶዎቹ የካንሰር ሥርጭቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ የጨረራ፣ የቀዶ ጥገና፣ የኬሞቴራፒ እና የመሳሰሉ የሕክምና አገልግሎቶች ያስፈልጋቸዋል።

ማዕከሉ ባለው የጨረራ መሣሪያዎች እጥረት ታካሚዎቹን በወቅቱ ማስተናገድ ባለመቻሉ ከተመዘገቡት ሕሙማን መካከል ከ23 እስከ 25 በመቶዎቹ ለሕልፈት እንደሚዳረጉ ነው ዶክተር ወንድማገኝ የገለጹት።

በማዕከሉ ካሉት ሁለት የጨረራ መሣሪያዎች አንዱ ከተበላሸ ሁለት ዓመታት እንዳስቆጠረ ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

አንደኛውም ለ3 ሳምንታት ተበላሽቶ የነበረ በመሆኑ ከሕሙማን ቁጥር አንጻር በቂ አይደለም ያሉት ዶክተር ወንድማገኝ፣ ይህም ለካንሰር ሕክምና ትኩረት አለመሰጠቱን ያሳያል ብለዋል። 

በማዕከሉ የጨረር ሕክምና ባለሙያ አቶ ሰለሞን ተሾመ በበኩላቸው “ማዕከሉ ብቸኛው የጨረራ አገልግሎት ሰጭ በመሆኑ በርካታ ዜጎች ከተለያዩ አካባቢዎች በመምጣት አገልግሎቱን ባለማግኘታቸው ሲንገላቱ ይስተዋላል” ብለዋል።

በማዕከሉ የጨረራ ማመንጫ መሣሪያ ብልሽት ሲገጥመው የጥገና ባለሙያ ባለመኖሩ አገልግሎት እንደሚቋረጥና ዘላቂ መፍትሔ እየተሰጠ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በአምስት ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የካንሰር ሕክምና ማዕከል እንደሚቋቋም ከተነገረ ዓመታት ቢቆጠሩም እስካሁን የሕክምና ክፍል ግንባታ ካጠናቀቀው ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ውጭ ሌሎቹ አልጀመሩም።

እ.አ.አ በ2016 የወጣው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ በዓመት 60 ሺህ ሰዎች በካንሰር በሽታ የሚያዙ ሲሆን ከነዚህ መካከል 44 ሺህ ተጠቂዎች ወይም 73 በመቶዎቹ ተገቢውን ህክምና ሳያገኙ ለህልፈት ይዳረጋሉ።

Published in ማህበራዊ

ጎንደር ሰኔ 11/2009 በሰሜን ጎንደር ሦስት ወረዳዎች የተከሰተውን ተምች ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

ጸረ-ሰብል ተባዩ በጎንደር ዙሪያ፣ በጭልጋና አለፋ ወረዳዎች 32 ሄክታር በሚሸፍን የበቆሎና ማሽላ ሰብል ቡቃያ ላይ መከሰቱን በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ እንኳየሁሽ ሙሉ ተናግረዋል፡፡

በወረዳዎቹ ሰባት ቀበሌዎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የተከሰተውን ተምች ለመከላከል በባህላዊና በኬሚካል ርጭት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

እስካሁንም ሦስት ነጥብ አምስት  ሄክታሩን በባህላዊና በኬሚካል ርጭት መከላከል መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ተምቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አርሶአደሩ ከሚያደርገው ባህላዊ የመከላከል ስራ ጎን ለጎን 400 ሊትር ኬሚካልና የመርጫ መሳሪያ ተሰራጭቶ የመከላከል ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል፡፡

የአለፋ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ገበየሁ አለምነህ በበኩላቸው ተምቹ በወረዳው አራት ቀበሌዎች መከሰቱን ተናግረዋል፡፡

22 ሄክታር በሚሸፍን የበቆሎ፣ ማሽላና የግጦሽ ሳር ላይ የተከሰውን ተምች ለመከላከል አርሶአደሩ በባህላዊ መንገድ እየተረባረበ ሲሆን 150 ሊትር ኬሚካልና 1ሺ 720 መርጫ መሳሪያ እየተሰራጨ ነው፡፡

በወረዳው በዘንድሮ የመኸር እርሻ 12 ሺ ሄክታር መሬት በበቆሎና በማሽላ ሰብሎች መሸፈኑም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

ጸረ-ሰብል ተባዩ ሊከሰት እንደሚችል በግብርና ባለሙያዎች አስቀድሞ ትምህርት ተሰጥቶኝ ዝግጅት በማድረጌ የመከላከል ስራውን እያካሄድኩ ነው ያሉት ደግሞ በአለፋ ወረዳ የጫራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር እንዳለው ፍሬ ናቸው፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 11/2009 የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን ያዘጋጀው የመኪና ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ተካሄደ። ውድድሩ በጃንሜዳ ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

በዕለቱ ውድድሩን ሲመለከቱ በነበሩ ስድስት ተመልካቾች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል።

በማወዳደሪያ ችግርና ተወዳዳሪዎች የህግ ከለላ እንዲሰጣቸው በመጠየቃቸው ምክንያት ወጥ የሆነ የሞተር ስፖርት ውድድር ማድረግ አልተቻለም ነበር።

ዛሬ ከአንድ ዓመት በኋላ በአምስት ምድብ በተካሄደው ውድድር 21 የመኪና ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል።

ብርቱ ፍክክር በታየበትና ልምድ ያላቸው ተወዳዳሪዎች በተሳተፉበት አምስተኛ ምድብ  ጣሊያናዊው ኤርነስቶ ሞሊናር አሸናፊ ሲሆን፣ በመኪናና በሞተር ውድድር በርካታ ልምድ ያለው ኢትዮጵያዊው አንተነህ ተጫኔ ሁለተኛ ወጥቷል።

በዚህ ምድብ የተወዳደረው ዮናስ እጅጉ ደግሞ ሶስተኛ ሆኗል።

በአራተኛው ምድብ ጣሊያናዊው ሲሞን ፈራሪ አንደኛ፤ ኢትዮጵያዊው ሄርኩለስ ሙጂ ሁለተኛ በመሆን አሸንፈዋል።

ጣሊያናዊው ሶርጆ ኦሊቨሮ አንደኛ፣ ሀሽም አቦበከር ሁለተኛ በመሆን የሶስተኛው ምድብ አሸናፊዎች ናቸው።

በአንደኛ ምድብ ፋህሚ ግርማ አንደኛ፣ አሚር ሸምሱ ሁለተኛ፣ ፍቃዱ ከበደ ሶስተኛ ሲሆኑ፤ በሁለተኛው ምድብ ፋኑኤል ታምራትና ኩሩቤል ፉፋ በተከታታይ አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ማሸነፍ ችለዋል።

በዕለቱም አሸናፊ ተወዳዳሪዎች የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላችዋል።

የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሚያስ አየለ እንደተናገሩት፤ በማዘወተሪያ ስፍራ እጥረት የመኪና ውድድሮች ሳይካሄዱ ቆይተዋል።

ዛሬ በጃንሜዳ የመኪና ውድድር መደረጉ "ለስፖርቱም ሆነ ለተወዳዳሪዎች መነቃቃት የሚፈጥር ነው" ብለዋል።

በዕለቱ ሁለት ተወዳዳሪዎች ለአሸናፊነት ሲፎካከሩ የአንደኛው መኪና ከውድድር ማብቂያ ቦታ ዘሎ በመውጣት በስድስት ተመልካቾች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል።

ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ተመልካቾች ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ተወስደው ህክምና ከተከታተሉና ምንም ዓይነት የከፋ ችግር እንዳላጋጠማቸው ከተረጋገጠ በኋላ ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።

በውድድሩ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፣ በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታና ሌሎች ኃላፊዎች ተገኝቷል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ሰኔ 11/2009 ኢትዮጵያ  በጅቡቲና ኤርትራ ድንበር መካከል የቆየው የኳታር ሰላም አስከባሪ ኃይል ከቦታው በመልቀቁ ምክንያት የተከሰተውን ውጥረት አገሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው የፕሬስ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ኢትዮጵያ ኳታር የሰላም አስከባሪ ወታደሮቿን ከጅቡቲና ኤርትራ ድንበር ካስለቀቀች በኋላ በአገሮቹ መካከል የተከሰተውን ውጥረት በቅርበት እየተከታተለች ነው።

ኢትዮጵያ ትናንት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት፤ በአገራቱ መካከል የተከሰተውን ውዝግብ ለመፍታት ጉዳዩን የሚያጣራ እውነታን ፈላጊ ልዑክ እንዲሰማራ ያቀረቡትን ሀሳብ እንደምትደግፍ መግለጫው አስታውቋል።

አገራቱ የተነሳውን ውዝግብ ከማባባስ ተቆጥበው ያላቸውን ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እንደምትፈልግ የጠቆመው የቃል አቀባዩ መግለጫ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውጥረቱን ለማርገብ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደምታበረታታ አትቷል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሰኔ 11/2009 በፈረንሳይ ላንግል ትናንት በተካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር  ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀናቸው።

በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የነሐስ ደረጃ ያለው 27ኛው የኮሪዳ ላንግል የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ ሆነዋል።

በሴቶች ምድብ በተደረገው ውድድር አትሌት ብርሃን ምህረቱ በአንደኝነት ስታጠናቅቅ፤ አትሌት በላይነሽ በየነ ሁለተኛ ወጥታለች።

ኬንያዊቷ አትሌት ሱሳን ኪፕሳንግ ሶስተኛ በመሆን ውድድሯን ጨርሳለች።

አትሌት ብርሃን ውድድሩን ለመጨረስ 32 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ ፈጅቶባታል። አትሌት በላይነሽ ደግሞ 32 ደቂቃ ከ34 ሰከንድ በመግባት ነው ውጤቷን ያስመዘገበችው።

በዚህ ውድድር የአምና አሸናፊ የነበረችውና "ክብርዋን ለማስጠበቅ ትሮጣለች "የተባለችው አትሌት መስከረም አማረ ውድድሩን ሳትካፈል መቅረቷ ታውቋል።

አትሌት መስከረም ባለፈው ዓመት 32 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ ከ16 ማይክሮ ሰከንድ በማስመዝገብ በአንደኝነት ማጠናቀቋ ይታወሳል።

በወንዶች ምድብ በትውልድ ኢትዮጵያዊው በዜግነት ባህሪናዊው አትሌት ዳዊት ፍቃዱ በአንደኝነት አጠናቋል።

አትሌት ዳዊት ውድድሩን ለመጨረስ 28 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ ፈጅቶበታል።

ኢትዮጵያዊያኑ አትሌት አምበሳ ተስፋዬና ፍቃዱ ሀፍቱ ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን ውድድራቸውን ጨርሰዋል።

አትሌት አምበሳ በአትሌት ዳዊት በአንድ ሰከንድ ተቀድሞ ነው ሁለተኛ የሆነው። 28 ደቂቃ ከ46 ሰከንድ አትሌት ፍቃዱ የገባበት ሰዓት ነው።

ሌላው ኢትዮጵያዊ አትሌት አየኑ ይስማው አራተኛ ወጥቷል።

 

Published in ስፖርት

አዳማ ሰኔ 11/2009 የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በፖሊሳዊ ሣይንስ የዲግሪ ኘሮግራም እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡

በኮሌጁ የአቅም ግንባታ ስልጠና የተከታተሉ አንድ ሺህ 67 የፖሊስ አባላት ዛሬ ተመርቀዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኮሌጁ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር አበበ ለገሰ በተለይ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ኮሌጁ እስካሁን በፖሊሳዊ ሣይንስ በዲኘሎማ የሚሰጠውን ትምህርት ከመጪው ዓመት ጀምሮ ወደ ዲግሪ ከፍ ለማድረግ የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናቋል።

የዲግሪ መርሃ ግብሩ መከፈት የወንጀል ድርጊትን ለመከላከል  በጥበብ፣ በእውቀትና በክህሎት የበቁ አባላትን በየደራጃው ለማፍራትና ፖሊሳዊ አገልግሎቶችን ለማዘመን  ያስችላል፡፡

''ፖሊስ ማንኛውንም ህብረተሰብና ተቋም የሚያገለግል እንደመሆኑ የትምህርት ኘሮግራሙ መከፈቱ እነዚህን አካላት ለማርካት የሚያስችል ቁመና እንዲኖረው ያስችላል'' ብለዋል፡፡

በተለይ ከተለመደና ኋላቀር አሰራር ፈጥኖ በመውጣት አሁን ካለው ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አብሮ ለመጓዝ አቅም ለመፍጠር እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ኮሌጁ በስራ ላይ ያሉትንና በፖሊሰ ሣይንስ ዲፕሎማ ያላቸውን አባላት በመመልመልና የመግቢያ ፈተና በመስጠት ከ2010 ጀምሮ በዲግሪ ደረጃ ማሰልጠን ይጀምራል።

ኮሌጁ ከመደበኛው ጎን ለጎን የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመው የእለቱ ተመራቂዎችም ለአምስተኛ ጊዜ ለሁለት ወራት የተሰጠውን ስልጠና ተከታትለው ያጠናቀቁ ናቸው፡፡

ስልጠናውን ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ትራፊክ ፖሊሶች፣ የወንጀል መከላከልና ምርመራ ኃላፊዎች እንዲሁም መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች ተከታትለዋል፡፡

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል አዱኛ ደበሌ በምረቃው ላይ እንደተናገሩት ፖሊስ ህገ መንግስቱን በማክበርና በማስከበር የሕዝቡን ሰላምና ጸጥታ በማስከበር ለሀገሪቱ ህዳሴ እውን መሆን እየሰራ ነው።

በየደረጃው ያሉትን አባላት በስልጠናና በቁሳቁስ በማጠናከር በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ደህንነት መስፈን የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ባህር ዳር ሰኔ 11/2009 በደቡብ ጎንደር ዞን ከ184 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት  በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ አዲስ ተፈራ ለኢዜአ እንደገለፁት በዘንድሮው የመኽር እርሻ ለማልማት በዕቅድ ከተያዘው 551 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ከአንደኛ እስከ አራተኛ ጊዜ ተደጋግሞ ታርሶ ለዘር ተዘጋጅቷል፡፡

ከዚህ መሬት ውስጥም 51 ሺህ 821 ሄክታሩ በኩታ ገጠም የእርሻ ማሳ በአራት የሰብል አይነቶች በመስመር፣ ሙሉ የግብርና ፓኬጁንና የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም እንደሚለማ ተናግረዋል።

''እስካሁን ከ184 ሺህ ሄክታር የሚበልጠው መሬት በድንች፣ በቆሎ፣ ገብስ፣ ስንዴና ጥራጥሬ ሰብሎች ዘር ተሸፍኖ እየለማ ነው'' ብለዋል።

ለመኸር እርሻ ልማት ከግማሽ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የቀረበ ሲሆን ከ275 ሺህ ኩንታል የሚበልጠው ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ ውሏል።

ዘንድሮ የማዳበሪያ ዋጋ በመቀነሱም አርሶአደሩ ግብዓት በተሻለ ገዝቶ እንዲጠቀም አስችሎታል።

በቀጣይም በዕቅድ የተያዘውን መሬት ሙሉ በሙሉ በማልማት ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ፋርጣ ወረዳ የሶራስ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታደሰ አያሉ በሰጡት አስተያየት ያላቸውን አንድ ሄክታር መሬት በድንች፣ ገብስና ስንዴ ዘር ሸፍነዋል፡፡

''የማዳበሪያ ዋጋ በመቀነሱም  ሁለት ኩንታል ተኩል ማዳበሪያ ገዝቼ እንድጠቀም አስችሎኛል” ብለዋል።

የግብርና ባለሙያዎች በሚሰጡዋቸው ምክረ ሃሳብ ታግዘው ባለፈው ዓመት የጀመሩትን የቢራ ገብስ ልማት ዘንድሮም አጠናከረው መቀጠላቸውን የተናገሩት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፀጋዬ ተፈሪ ናቸው።

በመኽር ከሚያለሙት ሁለት ሄክታር መሬትም ግማሽ ሄክታር የሚሆነውን በኩታ ገጠም የቢራ ገብስ በመስመር ዘርተው እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቀሪውን ደግሞ በስንዴ፣ ድንችና በሌሎች የጥራጥሬ ሰብል ዘር በመሸፈን እያለሙ ሲሆን ሶስት ኩንታል ተኩል ማዳበሪያም ገዝተው ተጠቅመዋል።

እያለሙት ያለውን የሰብል ምርት ከፀረ-ሰብል ተባይና ፀረ-ሰብል አረም ለመከላከል ክትትል እያደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በ2008/2009 የምርት ዘመን በዞኑ ከለማው መሬት ከ11 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡንም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ ሰኔ 11/2009 የኢትዮጵያ መድኀኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በመድኀኒት አቅርቦትና ጥራት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በኤጀንሲው አዲስ አሰራርና አደረጃጀት ከመዘርጋት ጀምሮ የሪፎርምና የለውጥ መሳሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና በአዳማ ከተማ ትናንት ተጀምሯል።

የኤጄንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሓሪ ተከስተ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት በተቋሙ ውስጥ የአደረጃጀት፣ አሰራርና የአገልግሎት ተደራሽነት ችግር እንዳለ በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት ተለይቷል፡፡

በተለይ የመድኀኒትና የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦትና ጥራት ጉድለት፣ የሠራተኞች ቅጥርና ዝውውር ግልፅነት የጎደለው መሆን፣ በመጋዘኖች መድሃኒቶች ለአገልግሎት ሳይውሉ መበላሸትና የግዥ ሥርዓቱ ለኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና የተጋለጠ መሆን በኤጀንሲው ከሚታዩ ችግሮች ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እነዚህን ችግሮች መዋቅራዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የውስጥ አሰራርና አደረጃጀትን በመፈተሽ ግልፅነትነትና ተጠያቂነት የተላበሰ የልማት ሠራዊት የመገንባት ስራ በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በኤጄንሲው የሪፎርምና መልካም አስተዳድር ዳይሬክተር አቶ ብሩክ አለማየው በበኩላቸው አዲሱ አሰራርና አደረጃጀት ሠራተኞች በውጤት የሚለኩበት፣ የሚበረታቱበት፣ ደካማው የሚማርበትና ራሱን የሚያበቃበት መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም በቡድን የመስራት መንፈስ ይበልጥ ባህል እንዲሆንና በሠራተኞች መካከል ውድድር እንዲኖር የሚያስችል መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ስልጠናውም ከ2010 የበጀት ዓመት ጀምሮ አመራሮች፣ ሙያተኞችና መላው ሠራተኞች በለውጥና በውጤት ለመለካት የሚያበቃ ዝግጅት የሚደረግበት መሆኑን አመልክተዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዘላለም ታረቀኝ እንደገለፁት በኤጂንሲው መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ እየተዘረጋ ያለው አዲስ አሰራርና አደረጃጀት የአቅርቦት፣ የጥራት፣ የአመለካከት፣ የተነሳሽነትና የክህሎት ከፍተቶችን በትክክል የፈተሸ መሆን ይኖርበታል፡፡

ይህን አገራዊ ችግር ለመፍታትና አዲሱን አሰራር ውጤታማ ለማድረግ የአቅም ግንባታ ስልጠናው የጎላ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

በአዳማ ከተማ ከትናንት ጀምሮ በአራት ዙር ለ10 ቀናት በሚካሄደው የሪፎርም መሳሪያዎች ትግበራና የጤና ልማት ሠራዊት ግንባታ ስልጠና ላይ ከ17 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችና ከዋናው መስሪያ ቤት የተወጣጡ ከ2 ሺህ በላይ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሙያተኞችና ሠራተኞች ይሳተፋሉ።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ ሰኔ 11/2009 በእንስሳት ላይ ከሚከሰቱ በሽታዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ወደ ሰው የሚተላለፉና ጉዳት የማድረስ ባህሪያቸው ሰፊ መሆኑን የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴር ገለፀ ።

የበሽታውን መተላለፊያ መንገዶች ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ  ተዘጋጅቶ በአዳማ ከተማ ለውይይት ቀርቧል ።

በሚኒስቴሩ የእንስሳት ልየታ ፣ ክትትልና ደህንነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ሀድጉ ማንደፍሮ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት የእንስሳት በሽታ በአግባቡ ክትትልና ቁጥጥር ካልተደረገበት በሰው ጤና፣ በእንስሳት ተዋፅኦና በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ሰፊ ነው፡፡

ሰፊ የእንስሳት ሀብት ባላት ኢትዮጵያ የህዝቦቿ አኗኗር ከእንስሳት ንኪኪ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ ከእንስሳት ወደ ሰውና ከሰው ወደ እንስሳት የሚተላለፉ በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር አስፈላጊ ነው፡፡

በእንስሳት አረባብ፣ በመኖ አቅርቦትና አጠቃቀም፣ በእንስሳት ጤናና በግብይት ችግር ምክንያት ያልተጠቀምንበትን የእንስሳት ሀብት በአግባቡ ለማልማት አዋጁ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል ።

''የችግሩን አሳሳቢነት ግምት ውስጥ በማስገባት  የእንስሳት ጤና፣ የማህበረሰብ ጤናና የእንስሳት ደህንነት አካቶ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ  በሚመለከታቸውና ባለድርሻ አካላት እየተተቸ ነው'' ብለዋል ።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የእንስሳት ልየታ ፣ ምዝገባና ክትትል  ባለሙያ ወይዘሮ አልማዝ እሸቴ በሰጡት አስተያየት በዓለማችን ከሚገኙ 10 ተላላፊ በሽታዎች መካከል  4ቱ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ ናቸው ።

በተለይም ጥሬ ስጋና ጥሬ ወተት በመመገብ ሳንባ ነቀርሳና ውርጃን ጨምሮ በርካታ በሽታዎች ከእንስሳት ወደ ሰው ይተላለፋሉ ብለዋል ።

አዋጁ  በአገሪቱ እየተስፋፉ የመጡትን  የእንስሳት በሽታዎች ለመከላከል ፣ ለመቆጣጠርና ደረጃ በደረጃ ለማጥፋት ፣ ባህላዊ የእንስሳት አያያዝን ዘመናዊ ለማድረግና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማጠናከር እንደሚረዳ አስረድተዋል ::

የእንስሳት ህክምናና የህብረተሰብ ጤና ዳይሬክተር ዶክተር ወንድወሰን በቀለ በበኩላቸው  የእብድ  ውሻ በሽታን ጨምሮ ለህብረተሰቡ አስጊ የሆኑና ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችንና  ለህብረተሰቡ የሚቀርበውን ስጋ ጥራት ለመቆጣጠር አዋጁ አመቺ የህግ ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል ።

በአዳማ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት በረቂቅ አዋጁ ላይ በሚመክረው ዓውደ ጥናት ላይ የቁም እንስሳት ላኪዎች ፣ የኤክስፖርት ቄራዎች ፣ የህግ ባለሙያዎች ፣ በዘርፉ የሚሰሩ ዩኒቨርሲቲዎችና የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

 

Published in ማህበራዊ

አዳማ ሰኔ 11/2009 ሃገሪቱ ያላትን ሰፊ የውሃ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ የውሃ ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ  መሆኑን  የአዳማ ሣይንስና  ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

በእስራኤል የውሃ አጠቃቀም ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በዩኒቨርሲቲው ተካሂዷል።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዜዳንት ዶክተር ተሾመ አብዶ  እንደገለጹት ኢትዮጵያ ሰፊ የውሃ ሀብት ቢኖራትም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በተገቢው ተጠቃሚ አልሆነችም፡፡

የውሃ ሀብቱን በአግባቡ እንዳትጠቀም ካደረጓት ማነቆዎች መካከል የፋይናንስና የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት፣ደካማ የውሃ ሀብት አስተዳደር በዋናነት ተጠቅሰዋል።

ሀገሪቱ ያላትን የውሃ ሀብት በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል መንግስት የውሃ አስተዳደር ፖሊሲ፣ስትራቴጂና የልማት ፕሮግራም በመቅረፅ ለተግባራዊነቱ በየደረጃው እየሰራ መሆኑን  አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲውም ይህንን  ለመደገፍ  የውሃ ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል።

ዶክተር ተሾመ እንዳሉት በአሁኑ ወቅትም  በውሃ ቴክኖሎጂ የዳበረ ልምድ ካላቸው አገራት ጋር በመተባበር ለመስራት ጥረት ተጀምሯል።

" በዘርፉ ስኬታማ ከሆኑ የዓለም አገራት መካከል እስራኤል ቀዳሚ ናት " ያሉት ዶክተር ተሾመ አውደ ጥናቱ የተዘጋጀውም  በአገሪቱ  እየተሰራበት ያለውን የውሃ አጠቃቀም ቴክኖሎጂ ምንነት እንዲሁም ከዩኒቨርሲስቲው የውሃ ሀብትና መስኖ የልህቀት ማዕከል ጋር ያለውን ግንኙነት በመፈተሽ አብሮ ለመስራት ታስቦ መሆኑን አመልክተዋል።

እንዲሁም በሀገሪቱ የውሃ አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ፣ውሃን በቁጠባ ለመስኖ፣ለኃይል አቅርቦት፣ለኢንዱስትሪና ለሌሎችም አገልግሎቶች ለማዋል የሚቻልበት ዘዴና  ልምድ  ለመቅሰም መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ስፔሻል  ዲን ዶክተር ዘላለም ብሩ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ወጣት ተመራማሪዎችን በማፍራት የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል፡፡

ትናንት በተካሄደው አውደ ጥናት  በውሃ አጠቃቀም ረገድ የእስራኤልን  ውጤታማ ቴክኖሎጂዎች ከእስራኤል የመጡ  ከፍተኛ ባለሙያዎች ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ  ላይ የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና ባለድርሻ አካላት መክረዋል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን