×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Saturday, 17 June 2017

አምቦ ሰኔ 10/2009 በምዕራብ ሸዋ ዞን ለመኽር አዝመራ  ከሚያስፈልገው ማዳበሪያ ውሰጥ 184 ሺህ ኩንታሉ ለአርሶ አደሩ ደርሶ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡

የዞኑ ሕብረት ሥራ ማስፋፊያና ማደራጃ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ  አቶ አበበ ኦማ እንደገለጹት ለመኸሩ  የሚየስፈልገው የማዳበሪያ መጠን  523 ሺህ 363 ኩንታል ነው።

ከዚህ ውስጥ  እሰካሁን 184 ሺህ ኩንታሉ በመሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሩ ደርሶ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡

የማዳበሪያ ስርጭቱ መቀጠሉን የጠቆሙት  አስተባባሪው ቀሪው ማዳበሪያም  በክልሉ ህብረት ስራ ማስፋፊያ በኩል እስከ ሀምሌ 15 ቀን 2009 ዓ.ም እንደሚቀርብ አመላክተዋል ።

በአምቦ ወረዳ የቆራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፈዬራ ቶለሳ በሰጡት አስተያየት "ለምርት ወቅቱ የሚያስፈልገው ማዳበሪያ ቀድሞ በመድረሱ የበቆሎ ዘር በወቅቱ ለመዝራት ችያለሁ " ብለዋል።

ለምርት ማሳደጊያ የሚያገለግላቸውን ሶስት ኩንታል ማዳበሪያ  ቀድመው መግዛታቸውን የገለፁት ደግሞ በደንዲ ወረዳ የአሰጎሪ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሌንጂሳ ሶቦክሳ ናቸው።

አርሶ አደሩ እንዳሉት ማዳበሪያ በመጠቀም ግማሽ ሄክታር ማሳቸውን በበቆሎ ዘር ሸፍነዋል ።

ባለፈው ዓመት 1 ሺህ አምስት መቶ ይገዛ የነበረው አንድ ኩንታሉ ማዳበሪያ ዘንድሮ የ250 ብር ቅናሽ መሳያቱን አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በምርት ዘመኑ  በተለያየ የሰብል ዘር ከሚሸፈነው 616 ሺህ 748 ሄክታር መሬት 17 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ተቅዷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

መቱ ሰኔ 10/2009 እየተደረገላቸው ያለውን ድጋፍ በመጠቀም ራሳቸውን ለመለወጥ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች ተሰማርተው እየሰሩ መሆናቸውን በኢሉአባር ዞን ያዮና ሁሩሙ ወረዳዎች አስተያየታቸውን የሰጡ  ወጣቶች ገለጹ።

ወጣቶኡ ለኢዜአ እንዳሉት መንግስት እራሳቸውን ለመለወጥ የሚያስችላቸውን  የብድር አገልግሎት ፣ የስልጠና እና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ አድርጎላቸዋል፡፡

በዚህም ተጠቅመው ሙሉ ጊዜያቸውን ስራ ላይ እያዋሉ ነው፡፡

ወጣት ፋንታሁን ጌታቸው በያዮ ወረዳ አጭቦ ቀበሌ ተደራጅተው ዘንድሮ ወደ ስራ ከገቡ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው።

ወጣቱ እንደገለጸው ከሌሎች አስር ጓደኞቹ ጋር በመሆን ባገኙት የብድር ገንዘብና የመስሪያ ቦታ በእንስሳት ማድለብ ስራ  ተሰማርተዋል።

መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍ የገቢ አቅማቸውን በማሳደግ ራሳቸውን ለመለወጥ ተግተው እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡

አካባቢያቸው ለእንስሳት እርባታና ማድለብ አመቺ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውጤታማ እንደሚሆኑ የገለጸው ወጣት ፋንታሁን  በቀጣይነት በገበያ ትስስሩ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቋል።

"መንግስት የወጣቱን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት  የገባውን ቃል በተግባር ማየት ጀምሬያለሁ  የተደረገልንን ድጋፍ በመጠቀም ከሌሎች አስር ጓደኞቼ ጋር በመሆን በከብት ማድለብ ተሰማርቼያለሁ"  ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ የቀበሌው ነዋሪ ወጣት ነጻነት መክብብ ናት።

ሴቶች ከወንዶች እኩል የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ የሚያበረታታ መሆኑን ተናግራለች፡፡

በሁሩሙ ወረዳ የባሮ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ተስፋዬ ታሲሳ በበኩሉ መንግስት  ባደረገላቸው  ድጋፍ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ በማዕድን ማውጣት ስራ መሰማራቱን ገልጿል፡፡

" ወጣቱ ፍላጎትና ተነሳሽነት ካለው በአጭር ጊዜ ወደ ባለሀብትነት የሚሸጋገርበት ጊዜ ላይ ነው "ያለው ወጣቱ፤ እሱም ለሌሎች ወጣቶች አርአያ ለመሆን ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡

የዞኑ  ስራ እድል ፈጠራና ከተማ ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ወይኒቱ በቀለ "በዞኑ በበጀት ዓመቱ በመደበኛና በተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ ድጋፍ  ከ26 ሺህ በላይ ወጣቶች ተደራጅተው ወደ ስራ  ገብተዋል" ብለዋል።

ወጣቶቹ በገጠር ግብርና፣ በማዕድን ማውጣት  እንዲሁም በከተሞች አካባቢ ደግሞ  በማምረቻ፣ በአገልግሎት፣ በግንባታና በሌሎችም የስራ መስኮች ተሰማርተዋል፡፡

ወደስራ ለገቡት  ወጣቶቸ ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር ገንዘብና 1 ሺህ ሄክታር የመስሪያ ቦታ እንደተሰጣቸውም  ወይዘሮ ወይኒቱ አመልክተዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ጋምቤላ ሰኔ 10/2009 የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን በማካሄድ ለሀገሪቱ ልማትና እድገት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ፡፡

ዩኒቨርሲቲው የናይሎቲክ የትምህርትና የጥናት ማዕከል መከፈቱን ይፋ አድርጓል።

ማዕከሉ በተከፈተበት ወቅት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክና ምርምር  ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ቤል ቢቾክ  እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው

የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት በተጓዳኝ  ችግር ፈቺ ምርምሮችን እያካሄደ ነው፡፡

ዩኒቨርስቲው  ባለፉት ሁለት ዓመታት የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢከኖሚያዊ ችግሮች የሚፈቱ ከ40 በላይ የምርምር ስራዎችን  አከናውኗል፡፡

እንደ ዶክተር ቤል ገለጻ ከተከናወኑት የምርምር ስራዎች ውስጥ ግብርና፣ ኢኮ ቱሪዝምና ተፈጥሮ ሀብት ላይ ያተኮሩ ይገኙበታል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው የናይሎቲክ የትምህርትና የጥናት ማዕከል በመክፈት ቋንቋውን የሚናገሩ የክልሉን አምስት ነባር ብሄረሰቦች ጨምሮ በሀገሪቱ የሚገኙ የቋንቋው ተናጋሪ ህዝቦች ባህልና ቋንቋ ላይ ምርምር ለማካሄድ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

" ማዕከሉ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የቋንቋው  ተናጋሪዎች ብቻ ሳይሆን ቋንቋውን የሚናገሩ የአፍሪካ  ህዝቦች ያላቸውን ባህልና የቋንቋ ትስስር ለማጥናት ጭምር ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል" ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው  የጀመረውን የሰው ሀበት ልማት ለማስፋት በመጪው የትምህርት ዘመን አምስት አዲስ የትምህርት ክፍሎችን በመክፈት በ31 የትምህርት ዘርፎች በዲግሪ ፣ በአምስት የትምህርት መስኮች ደግሞ የሁለተኛ ዲግሪ ስልጠና ለመስጠት በዝግጅት ላይ ነው እንደ ዶክተር ቤል ገለጻ፡፡ 

ተቋሙ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራትና  ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማጠናከር ለሀገሪቱ ልማትና እድገት የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል፡፡

ዩኒቨርሲቲው እያካሄደ ያለውን የምርምርና የሰው ኃብት ልማት በተሟላ መልኩ ለማስኬድ የሚያግዘውን  የማስፋፊያ ግንባታም ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ  እያካሄደ መሆኑን ዶክተር ቤል አመልክተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ሳይንስ ፋክሊቲ ዲን መምህር እንዳልካቸው ታየ የናይሎቲክ ቋንቋን አስመልክተው ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ  ኢትዮጵያን ጨምሮ በመካከለኛው አፍሪካ  እስከ 40 ሚሊየን የሚደርስ    ቋንቋው ተናጋሪ ህዝብ እንዳለ ገልጸዋል።

"ማዕከሉ በኢትዮጵያ የሚገኙ የቋንቋውን ተናጋሪዎች ብቻ ሳይሆን የሌሎች የአፍሪካ ህዝቦችን ባህልና ታሪክ ለማጥናት ጭምር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል "ብለዋል። 

የናይሎቲክ የትምህርትና የጥናት ማዕከሉን መከፈት ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ስነስርዓት ላይ  የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው  ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

Published in ማህበራዊ

መቐለ ሰኔ 10/2009 በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ 17 ሺህ ሕጻናት የትምህርት ቁሳቁስና ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

26ኛው የአፍሪካ ህፃናት ቀን በመቀሌ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ንግስቲ ወልደሩፋአኤል በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት ቁጥር ከፍ እያለ መጥቷል።

መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የትምህርት ቁሳቁስን ጨምሮ ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገላቸው ከሚገኙት በተጨማሪ በቀጣይም ከ56 ሺህ በላይ ሕጻናትን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።

የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብረሀ ኪሮስ በመድረኩ ላይ ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ እንዳመለከተው በክልሉ ከ150 ሺህ የሚበልጡ ሕጻናት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ቢገኙም በሚፈለገው ደረጃ ስለመብታቸው የሚሰራ ግለሰብም ሆነ ተቋም አልተፈጠረም።

ለሕጻናቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መገኘት ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል የጋብቻ መፍረስ፣ የወላጆቻቸው በህይወት አለመኖርና ከድህነት ወለል በታች መሆን ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውንም ጥናቱ ያሳያል።

በዚህም ህፃናት በብረታ ብረትና እንጨት ስራ ፣በታክሲ ረዳትነትና በሽመና ስራ አለአግባብ ጉልበታቸው ሲበዘበዝ መብታቸውና ጥቅማቸውን በአግባቡ ማስከበር አልተቻለም።

በመሆኑም በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ህጻናትን መብትና ጥቅም ለማስከበር መንግስትና የዴሞክራሲ ተቋማት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው የጥናቱ አቅራቢ አስረድተዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል የህውነት ደቂ ሰባት የሕጻናት ማሳደጊያ ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቅሬ አሰፋ እንደገለጹት ማዕከሉ ከሚያሳድጋቸው 60 ሕፃናት በተጨማሪ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ላሉ 350 ሕጻናት በየወሩ ለእያንዳንዳቸው የትምህርት ቁሳቁስና የ350 ብር ድጋፍ ያደረጋል።

ሆኖም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሕጻናት ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተሳካ ስራ ለማከናወን የሁሉም እገዛ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ከኤርትራ የመጣችውና በህመም ምክንያት ወላጆቿን ያጣችው ታዳጊ ሕጻን ሳምራዊት ኃይሌ በበኩሏ እንዳለችው  እየተደረገላት ባለው ድጋፍ በተረጋጋ ሁኔታ ትምህርቷን በመከታተሏ አሁን ስድስተኛ ክፍል ደርሳለች።

በቀጣይም ትምህርቷን እስከምታጠናቅቅ ድረስ ይሔው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደምትፈልግ ተናግራለች።

በፓናል ውይይቱ ከ450 የሚበልጡ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ ሰዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዳማ ሰኔ 10/2009 ሃገሪቱ ያላትን ሰፊ የውሃ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ  የውሃ ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ  መሆኑን  የአዳማ ሣይንስና  ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ።

በእስራኤል የውሃ አጠቃቀም ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በዩኒቨርስቲው ተካሂዷል።

የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተሾመ አብዶ  እንደገለጹት ኢትዮጵያ ሰፊ የውሃ ሀብት ቢኖራትም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በተገቢው ተጠቃሚ አልሆነችም፡፡

የውሃ ሀብቱን በአግባቡ እንዳትጠቀም ካደረጓት ማነቆዎች መካከል የፋይናንስና የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት፣ደካማ የውሃ ሀብት አስተዳደር በዋናነት ጠቅሰዋል።

ሀገሪቱ ያላትን የውሃ ሀብት በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል መንግስት የውሃ አስተዳደር ፖሊሲ፣ስትራቴጂና የልማት ፕሮግራም በመቅረፅ ለተግባራዊነቱ በየደረጃው እየሰራ መሆኑን  አመልክተዋል።

ዩኒቨርስቲውም ይህንን  ለመደገፍ  የውሃ ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል።

ዶክተር ተሾመ እንዳሉት በአሁኑ ወቅትም  በውሃ ቴክኖሎጂ የዳበረ ልምድ ካላቸው አገራት ጋር በመተባበር ለመስራት ጥረት ተጀምሯል።

" በዘርፉ ስኬታማ ከሆኑ የዓለም አገራት መካከል እስራኤል ቀዳሚ ናት " ያሉት ዶክተር ተሾመ አውደ ጥናቱ የተዘጋጀውም  በአገሪቱ  እየተሰራበት ያለውን የውሃ አጠቃቀም ቴክኖሎጂ ምንነት እንዲሁም ከዩኒቨርስቲው የውሃ ሀብትና መስኖ የልህቀት ማዕከል ጋር ያለውን ግንኙነት በመፈተሽ አብሮ ለመስራት ታስቦ መሆኑን አመልክተዋል።

እንዲሁም በሀገሪቱ የውሃ አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ፣ውሃን በቁጠባ ለመስኖ፣ለኃይል አቅርቦት፣ለኢንዱስትሪና ለሌሎችም አገልግሎቶች ለማዋል የሚቻልበት ዘዴና  ልምድ  ለመቅሰም መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዩኒቨርስቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ስፔሻል  ዲን ዶክተር ዘላለም ብሩ በበኩላቸው ዩኒቨርሰቲው ወጣት ተመራማሪዎችን በማፍራት የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል፡፡

ትናንት በተካሄደው አውደ ጥናት  በውሃ አጠቃቀም ረገድ  የእስራኤልን  ውጤታማ ቴክኖሎጂዎች  ከእስራኤል የመጡ  ከፍተኛ ባለሙያዎች ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ  ላይ የዩኒቨርስቲው ምሁራንና ባለድርሻ አካላት መክረዋል።

 

አዲስ አበባ ሰኔ 10/2009 የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማጎልበት የሚያስችል ሥርዓተ-ትምህርት ሊቀረጽ ነው ተባለ።
የመለስ ዜናዊ የአመራር አካዳሚ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥትንና የአመራር ክህሎትን የተመለከተ ብሔራዊ ጉባኤ አካሂዷል።

በአካዳሚው በሚንስትር ማዕረግ የጥናትና ምርምር ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አስቴር ማሞ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ የመንግሥት የሥራ

ኃላፊዎችን አቅም ለመገንባት እየሰራ ነው።

በሚሰጣቸውም አጫጭር ሥልጠናዎች በፌደራልና በክልል የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች የአመራር አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ደግሞ ኃላፊዎቹ በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ያላቸውን እውቅትና የአመራር ክህሎት በተደራጀ መልኩ ለማስቀጠል ሥርዓተ - ትምህርት እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም የልማታዊ አስተሳሰብ በሥራ ኃላፊዎች ዘንድ ልዕልና እንዲኖረው እንደሚያስችል በመግለጽ።

በአካዳሚው የሚመሩት ዘርፍም በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች ዙሪያ ከአመለካከት ጀምሮ ያሉትን ችግሮች በጥናትና ምርምር ለመለየት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በዚህም መሰረት ክፍተቶቹን መሰረት ያደረጉ ሥልጠናዎች እንደሚዘጋጁ አመልክተው፤ ሥልጠናው በምን ዓይነት መንገድ መካሄድ እንዳለበት ግንዛቤ ውስጥ እንደሚገባና ትኩረት እንደሚደረግበት ገልጸዋል።

በሥልጠናውም አመራር አባላትን ማዕከል ያደረጉ ጥናትና ምርምሮች እንደሚደረጉ ጠቁመው፤ "የተሰጡት የሥልጠና መርኃ ግብሮች በተጨባጭ የታለመላቸውን ግብ ማሳካታቸውም ግምገማ ይደረግባቸዋል" ብለዋል።

ጎን ለጎን ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የማማከር አገልግሎት በመስጠት የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት አሁን ካለበት ደረጃ እንዲጨምር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ወይዘሮ አስቴር ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ልማት ምርምር ተቋም ምጣኔ ኃብታዊ ተመራማሪ ዶክተር አለበል ባየሩ በበኩላቸው፤ "የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አስታሳሰብ በብሔራዊ ደረጃ ከዚህ በላይ መጎልበት አለበት" ይላሉ።

በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና በመላው ኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት እድገት ያስመዘገበ ቢሆንም፤  አሁንም ተጨማሪ ሥራዎችን በሥፋት በመሥራት አስተሳሰቡ እንዲጎለበት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል። 

"የግንዛቤ ማነስ በራሱ ለብልሹ አሰራር ይዳርጋል፤ በመሆኑም በተለይም የሥራ ኃላፊዎች ለሰፊው ሕዝብ መወገን የሚለውን መርሆ ሊላበሱት ይገባል" ብለዋል። 

በመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ የሚካሄደው ይኸው ጉባኤ ነገ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሰኔ 10/2009 በሳውዲ ዓረቢያ ካለመኖሪያ ፈቃድ የሚኖሩ ዜጎች በአንዳንድ አሰሪዎች በሚቀርብላቸው ድለላ ሳይዘናጉ ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚገባቸው የሳውዲ ተመላሾች ጥሪ አስተላለፉ፡፡

አንዳንድ አሰሪዎች  "አዋጁ ለማስፈራራት እንጂ አይተገበርም እንዲሁም እኛ ደብቀን እናስቀራችኋለን"  በሚሉ መደለያዎች ተመላሾችን እያዘናጓቸው መሆኑንም ነው ተመላሾቹ የጠቆሙት፡፡  

ወይዘሪት ዘውድነሽ ጌታቸው በሳውዲ ዓረቢያ ያለመኖሪያ ፈቃድ አራት ዓመት እንደቆየች ገለጻ፤ አንዳንድ የአገሬው ዜጎች አዋጁ የተለመደና "ምንም ችግር አያመጣም" እንደሚሉ ተናገራለች፡፡

 "ነገር ግን ዜጎች በሚሰሙት የተሳሳተ መረጃ ሳይታለሉ አዋጁን አክብረው ወደ አገራቸው መመለስ አለባቸው" ብላለች፡፡

ወይዘሪት ሃዋ ሙሃመድ በበኩሏ፤ አብዛኛው የመኖሪያ ፈቃድ የሌለው ሰው "እኛ እናስቀራችኋለን" በሚል የአሰሪዎች የተሳሳተ መረጃ ተታለው ለመምጣት አልተመዘገቡም፡፡

ሆኖም ግን አገሪቷ ያሰቀመጠችው ቀነ ገደብ እየቀረበ ሲሄድ አሰሪዎቻቸው ከቤት እያባረሯቸው ለችግር የተዳረጉ እህቶች እንዳሉም ተናገራለች፡፡

መንግስት ከስደት ተመላሾች በአገራቸው ሰርተው የሚለወጡበትን መንገድ በተግባር እንዲያመቻችም ጥሪዋን አስተላልፋለች፡፡

የሳውዲ ዓረቢያ መንግስት የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የሌላ አገር ዜጎች አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ያሰቀመጠው ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ ዘጠኝ ቀን ብቻ ቀርቶታል።

በሳውዲ ዓረቢያ ከ450 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ያለ መኖሪያ ፍቃድ እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን፤ ከ80 ሺ በላይ ዜጎች ወደ አገራቸው ለመመለስ የጉዞ ሰነድ የወሰዱ ቢሆንም እስከአሁን የደረሱት ዜጎች ቁጥር ዝቅተኛ ነው።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሰኔ 10/2009 ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት ለማሳካት የግሉን ዘርፍ መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለፀ።

 የምክር ቤቱ የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኤን. ኤ. ብረታ ብረት ኢንዱስትሪና ኢንጅነሪንግን ጎብኝቷል፡፡

 አገሪቷ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር የግሉ የኢንዱስትሪ ዘርፍ መሰረት ሊሆን እንደሚገባም ተጠቁሟል።

 የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ መሀመድ ቦልኮ በጎብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢንዱስትሪዎቹ አገሪቷ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረት ባለፈ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ገቢ ለማስገኘት ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል።

 ጥራት ያለው ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ገቢን እንዲያሳድጉ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

 መንግስትም ባለሀብቱን ወደ ኢንዱስትሪውና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለማሰማራት የማምረቻ ቦታ በማመቻቸትና ከቀረጥ ነፃ እቃዎችን እንዲያስገቡ በመፍቀድ የሚያደርገውን ድጋፍ መቀጠል እንዳለበት አቶ መሀመድ ገልጸዋል።

 ቋሚ ኮሚቴው የጎበኘው ኤን. ኤ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ኢንጅነሪንግ የከባድ ተሽከርካሪ አካላትን እና ትልልቅ የውሃና የነዳጅ ታንከሮችን የሚያመርት ነው።

 ድርጅቱ በወጣቶች መተዳደሩ አገሪቷ በኢንጅነሪንግ ዘርፉ የምታካሂደውን ትራንስፎርሜሽን ውጤታማ መሆኑን እንደሚያመላክትም በጉብኙቱ ማስተዋላቸውን ነው የገለጹት።

 የድርጅቱ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ አሰፋ በበኩላቸው፤ መንግስት የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለመፍጠር  እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚያስደስት ሲሆን፤ ክትትልና ድጋፉም እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

 ከቻይናው የሲኖትራክ ኩባንያ ጋር ስምምነት በማድረግም ተሽከርካሪውን ገጣጥሞ ወደ ውጭ ለመላክ 10 ሺ ካሬ ሜትር ላይ የፋብሪካ ግንባታ እያካሔዱ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

 ከሶስት ወር በኋላም ግንባታውን አጠናቀው ለአገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ ወደ ምስራቅ አፍሪካ አገሮች የመላክ እቅድ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

 ይሁን እንጅ አሁንም የማምረቻና የምርት ማከማቻ ቦታ እጥረት እንዳለባቸው ገልጾ፤ ለዚህ "መንግስት ድጋፍ ቢያደረግልን" ሲሉ ጥያቄያቸውን ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።

Published in ኢኮኖሚ

 

 ሀዋሳ ሰኔ 10/2009 የአገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ተከትሎ  እየጨመረ የመጣውን የሃይል ፍልጎት ለሟሟላትና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ ለመቋቋም የባዮ ፊውል ልማትን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን  የማዕድን ፣ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ  ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የባዮፊውል ልማት ፎረም የማዕድን ፣ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ  ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ዶክተር ኳንግ ቱትላም እንዳሉት ከ1999 ዓ. ም ጀምሮ 60 ሚሊዮን ሊትር ኤታኖል በማምረት ለቤት ውስጥ ፍጆታና ለትራንስፖርት አገልግሎት ማዋል ተችላል ።

ይህም አገራዊ የባዮፊውል ልማትና አጠቃቀም ስትራቴጂ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን "በዚህም 50 ሚሊየን የአሜርካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል "ብለዋል፡፡  

በተጨማሪም 300 ሺህ ቶን የካርበን ልቀት መቀነስ ተችሏል፡፡

ይሁን እንጂ እየተገባደደ ባለው  በጀት ዓመት 20 ሚሊዮን ሊትር ኤታኖል በማምረት 12 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማዳን ቢታቀድም  ማምረት የተቻለው 2 ሚሊዮን ሊትር መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

"የውጭ ምንዛሪ የማዳን አቅሙ ከግማሽ ሚሊየን የአሜርካን ዶላር አልዘለለም"ብለዋል።

ለዚህም ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የስኳር ፋብሪካዎች በተለያዩ ምክንቶች ኤታኖል ማምረት በማቆማቸው ስራው ለአንድ ዓመት ተኩል ተቋርጦ መቆየቱን በምክንያትነት ጠቅሰዋል ።

"ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከመንግስት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴርና ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር ባደረገው ጥረት ማምረት ተጀምሯል" ብለዋል ።

በአሁኑ ወቅትም ለባዮ ፊውል ልማትን ለማጠናከር ተኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑም  ተመልክቷል፡፡

የደቡብ ህዝቦች ክልል የማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ምክትል ስራ አስኪያጀ አቶ ተከተል ማቲዮስ በበኩላቸው  የክልሉ መንግስት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ እስከ 1 ሚሊዮን ብር በመመደብ በባዮፊውል ልማት ዙሪያ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ኤጀንሲው የባዮፊውል ልማት ከሚያካሂድባቸው የክልሉ አካባቢዎች በተጨማሪ ከሀዋሳ ፖሌ ቴክኒክና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከል ጋር በመቀናጀት የዳሰሳ ጥናት እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ መቅደስ ደረሰ ባዮፊውል ከናፍጣ ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ የሆነ የካርበን ልቀት ስላለው ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ተናግራለች።

እንደ ተማሪ መቅደስ ገለፃ ኢትዮጵያ በ2016 ከውጭ ካስገባችው ሰባት ሜጋ ቶን በካይ ጋዝ ወደ አየር የለቀቀች ሲሆን ባዮፊውል ይህንን በመቀነስ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

ከትናንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደው ፎረም   የማዕድን ፣ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ  ሚኒስቴርና  የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 10/2009 የምጥን ማዳበሪያ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ከውጪ አገር በሚገባ ጥሬ-ዕቃ ጥራት ችግር ሥራቸውን ማቋረጣቸውን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጥሬ-ዕቃውን ግዢ የሚፈጽመው የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን በበኩሉ፤ ግዢው ሚኒስቴሩ ባስቀመጠው ዝርዝር መስፈርትና ጥራት መሰረት መከናወኑን ገልጿል።

የኢትየጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት ደግሞ፤ ለፋብሪካዎቹ ስለሚገቡ ጥሬ-ዕቃዎችም ሆነ ስለምርቶቹ ጥራት መረጃ እንደለሌው አመልክቷል።

ከሦስት ዓመታት በፊት በ175 ሚሊዮን ብር በአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሄራዊ ክልሎች የተገነቡት እነዚህ ፋብሪካዎች ከውጪ አገር በሚገባ ግብዓት እንደየአካባቢው የአፈር ሁኔታ ምጥን ማዳበሪያ እንዲያመርቱ የተቋቋሙ ናቸው።

እነዚህ “የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ያስችላሉ” ተብለው የተቋቋሙት ፋብሪካዎች የተፈለገውን ውጤት ሳያስገኙ ስራቸውን ማቆማቸው ነው የተገለጸው።

በአሁኑ ወቅት በዝቅተኛ አቅም እያመረቱ ከሚገኙትና በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በቾ ወሊሶ እና በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ ከተቋቋሙት ምጥን ማዳበሪያ ፋብሪካዎች ውጪ ሌሎቹ ሥራ ማቆማቸውን ነው የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የሚገልጸው።

በሚኒስቴሩ የግብርና ግብዓት ግብይት ዳይሬከተር አቶ ሠይፉ አሰፋ ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ፋብሪካዎቹ በጥሬ-ዕቃ ጥራት ችግር ምክንያት ማምረት ማቆማቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።  ለዚህ ደግሞ እንደአንድ ችግር የጠቀሱት በተሰጠው ዝርዝር መስፈርት መሰረት ያለመቅረቡን ነበር።

ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት በመከናወን ላይ ስላሉ ጉዳዮች ኢዜአ ያነጋገራቸው አቶ ሠይፉ እንደሚሉት፤ ፋብሪካዎቹ የሠለጠነ የሰው ኃይልና የግብዓት ጥራት ችግር እንዳጋጠማቸው ተገምግሟል።

የግብዓቱን ግዢ የሚፈጽመው የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን በበኩሉ፤ በመጀመሪያው ዙር ከተገዛው ቦሮን የተባለው ማዳበሪያ በስተቀር ግዢው የተፈጸመው ሚኒስቴሩ ባወጣው ዝርዝር መስፈርት መሰረት እንደሆነ ገልጿል።

የኮርፖሬሽኑ የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ስራ አስፈጻሚ  አቶ ብረሃን አወቀ እንደገለጹት፤ ለግብዓትነት የተገዙት ሦስት ዓይነት ማዳበሪያዎች ቦሮን፣ ፖታሽ እና ዚንክ የሚባሉት ናቸው።

በመጀመሪያው ዙር ግዢ ቦሮን የተባለው ማዳበሪያ ከተቀመጠው ዝርዝር መስፈርት ውጪ የተገዛበት ምክንያት አቅራቢው፤ "እንዲህ ዓይነት ዝርዝር መስፈርት የለም" በማለቱ እንደሆነ ያስረዳሉ።

ለፋብሪካዎቹ ስራ ማቋረጥ ግብዓቱ ሚኒስቴሩ ባወጣው ዝርዝር መስፈርት መሰረት ያለመገዛት ችግር አለመሆኑን ነው የገለጹት።

ይልቁንም ከተገዙት 500 ሺ ኩንታል ማዳበሪያዎች ውስጥ 190 ሺ ኩንታል አካባቢ ብቻ አገልግሎት ላይ የዋለ መሆኑን ያመለከቱት፤ ቀሪው “ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የመጋዘን ኪራይ እየተከፈለበት ይገኛልም” ብለዋል።

ለአገልግሎት የሚውሉ ከውጭ የሚገቡና በአገር ውስጥ የሚመረቱ ጥሬ - ዕቃዎችንና ምርቶችን ጥራት የሚቆጣጠረው የኢትየጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት በበኩሉ፤ ለፋብሪካዎቹ ስለሚገቡት ጥሬ-ዕቃዎችና ምርቶች እንደማያውቅ ነው የገለጸው።

የድርጅቱ የኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ በርሄ እንደተናገሩት፤ ፋብሪካዎቹ ስለሚጠቀሙት ጥሬ እቃ መረጃ የለውም። ድርጅታቸውም እየተቆጣጠረና እየተከታተለ ያለው ከውጭ የሚገቡ ያለቀላቸውን ኬሚካል የአፈር ማዳበሪያዎችን ነው።

ድርጅቱ፤ ያለቀለት ማዳበሪያ በተቀመጠው ዝርዝር መስፈርት መሰረት በቤተ-ሙከራው እየተፈተሸ እንዲገባ የማድረግ ሥራ እያከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል።

የመቀሌው እንደርታ፣ የባህርዳሩ መርከብ እና የወራቤው መልህቅ ምጥን ማዳበሪያ ማቀነበበሪያ ፋብሪካዎች በሙከራ ደረጃ የጀመሩትን ምርት ከጥሬ - ዕቃ ጥራት ችግር ጋር በተያያዘ አቋርጠዋል።

ማቀነባበሪያዎቹ በሚቀጥለው ዓመት በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩና አርሶ አደሩ ለአላስፈላጊ የጉልበትና የገንዘብ ወጪ እንዳይዳረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን