Items filtered by date: Friday, 16 June 2017

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2009 የአገሪቷን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር በኅብረት መሥራት እንደሚገባ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ ለኢዜአ በላከው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ እንዳስታወቀው አገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር በሚደረገው ጥረት የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

ከተሞች እንዲለሙ፣ ሥራ አጥነት እንዲቀረፍ፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲስፋና የአገር ውስጥ ምርት እንዲጨምር ሚናው የጎላ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው አንደሚገባ ጠቁሟል።

ዘርፉ የቴክኖሎጂና ዕውቀት ሽግግር ለማቀላጠፍ አመቺ መሆኑንም ገልጿል።

በመሆኑም በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን በዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ የበኩላቸውን ሚና እንዲጨወቱ ጥሪውን አቅርቧል።

በዚህም የአገሪቷም ህዳሴ ማረጋገጥ እንደሚቻል ነው መልዕክቱን ያሰተላለፈው።

የውጭ ባለሃብቶች በአገሪቷ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉም በመግለጫው ጥሪውን አስተላልፏል።

በአሁኑ ወቅት በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የውጭ አገሮች ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳም ከቪዬትናም ቀጥላ ሁለተኛ ተቀዳሚ አገር መሆኑዋን መግለጫው አመልክቷል።

በ2017 የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን ራዕይ ሰንቃ እየገሰገሰች መሆኑዋንም ጠቅሷል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

የአገራችን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር የሚያደርገውን ሽግግር በማፋጠን የኢትዮጵያን ህዳሴ ዕውን እናደርጋለን!

አገራችን ኢትዮጵያን ከምትታወቅበት አስከፊ ድህነት አላቅቀን ወደ ቀድሞ ሥልጣኔዋና ታላቅነቷ ለማሸጋገር የህዳሴ ፕሮጀክት ነድፈን መንቀሳቀስ ከጀመርን ውለን አድረናል፡፡ የምንመኘው ህዳሴም ዕውን ይሆን ዘንድ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር፣ ሰፊ የኢንዱስትሪ መሠረት ያለን እና ዓለምን የሚያስደምም የምርቶች መፍለቂያ አገር ለመሆን ራዕይ ሰንቀን፣ በትልቁ አቅደን በመስራት ላይ እንገኛለን።

ከተሞች እንዲለሙ፣ ስራ አጥነት እንዲቀረፍ፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲፋፋ፣ የአገር ውስጥ ምርታችን እንዲጨምር፣ የቴክኖሎጂና ዕውቀት ሽግግር እንዲስፋፋ፣ በአጠቃላይ የአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ከማድረግ አንጻር የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የሚያስገኘውን ፋይዳ በመገንዘብ ለዚሁ የሚያግዙ በርካታ ዘመናዊ እና ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገነቡ ተደርገዋል፤ እየተገነቡም ይገኛሉ፡፡ የጥረቱ ፍሬም ከወዲሁ መጎምራት ጀምሯል።

በአገሪቱ እየተገነቡ ካሉ በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮች አንዱ የሆነው የሃዋሳው ኢንዱስትሪ ፓርክ የዛሬ ዓመት መሰረቱ ተጣለ፤ ግንባታው በዘጠኝ ወራት ውስጥ ተጠናቅቆ ሃምሌ 6 ቀን 2008 ተመረቀ፤ እነሆ ዛሬ አንድ ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት እና ኤክስፖርት ሂደት መሸጋገር ቻለ፡፡ ይህ ለአገራችን ትልቅ ድል ነው። ሂደቱ ቀጣይ ከመሆኑ አንጻርም ትልቅ ተስፋ የሚሰጠን ነው። በቅርቡ እንደሚጠናቀቁ ከሚጠበቁት የኮምቦልቻና የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም ተመሳሳይ ውጤት እንጠብቃለን። ግንባታቸው በመካሄድ ላይ ካሉት የቦሌ ሊሙ 2፣ የድሬዳዋ፣ የአዳማ፣ የባህር ዳር ወዘተ ፓርኮችም እንዲሁ።

የሃዋሳው ፓርክ ከአሁኑ ለ10 ሺህ ወገኖቻችን የስራ ዕድል ፈጥሯል። ወደፊትም ከዚያ በላይ ሥራ ይፈጥርልናል። ወደ ውጭ የምንልካቸውን ምርቶች በዓይነት እና በመጠን በማሳደግም ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ አምራችነት ያሸጋግረናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የውጭ አገራትን ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ከቪዬትናም ቀጥላ ሁለተኛዋ ተቀዳሚ የዓለማችን አገር የኛዋ ኢትዮጵያችን ናት። በ2017 ዓ.ም. የአፍሪካ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን ራዕይ ሰንቃ ወደድል እየገሰገሰች ያለችውም ይህቺው የእኛዋ ኢትዮጵያ ናት።

እርግጥ ስለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ስናነሳ ስለውጭ ኢንቨስትመንት ብቻ እያነሳን አይደለም። የምናነሳው ስለስራ ዕድል ብቻም አይደለም፡፡ ይልቁንም ስለአገር ውስጥ ባለሃብቶቻችን ሚናም ነው። ለአብነት በሃዋሳ ፓርክ ወደ ተግባር የተሸጋገሩት 18 ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የዓለም ሥመጥር ኩባንያዎች ሲሆኑ ሌሎች ስምንት ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶችም ተቀላቅለዋቸዋል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ልማታዊው መንግሥታችን በያንዳንዱ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከ15 እስከ 30 በመቶ ያህሉ የማምረቻ ቦታ ለኢትዮጵያውን መተዉ እንዳለበት አስቀድሞ በዕቅድ ያካተተው ጉዳይ ሲሆን ይህም ለዜጎቹ የሚሰጠውን ትኩረት አመላካች ነው። ከአገር ውስጥ ባለሃብት ተሳትፎ ባለፈ ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምሁራንን እያፈራች ባለችው አገራችን በጊዜ ሂደት ከተቀጣሪነት አስተሳሰብ እየወጡ ራሳቸውን ለስራ ፈጣሪነት በሚያበቁ የአገር ዋልታና ምሰሶ ዜጎቻችንንም ውጤቱ ሊታይ የሚገባው ነው።

የውጭ ባለሃብቶች በአገራችን በተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ተጠቅማችሁ መዋዕለ ንዋያችሁን በማፍሰስ በማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪው ልማት ውስጥ አሁንም በስፋት እንድትሳተፉ የኢፌዴሪ መንግሥት ግብዣውን ያቀርብላችኋል።

የአገር ውስጥ ባለሃብቶቻችንም የአገራችን ዕድገት መሠረቷ እናንተ የአገር ውስጥ ባለሀብቷ መሆናችሁን በውል አጢናችሁ ከጥቃቅን የንግድ ሥራ እየወጣችሁ ወደማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በመግባት የአገራችንን የኢኮኖሚ ነጻነት በማወጅ በኩል የድርሻችሁን እንድትወጡ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥራችሁ እየሰራችሁ ላላችሁ ውድ ኢትዮጵያውያን ዜጎቻችን ሁሉ፦ ዛሬ እናንተ እያከናወናችሁት ያለው ሥራ ራሳችሁን በመጥቀም የታጠረ ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዳሴ ከማረጋጋገጥ አንጻር ትልቅ ፋይዳ ያለው ተግባር በማከናወን ላይ መሆናችሁን መገንዘብ ይኖርባችኋል። በመሆኑም ሥራችሁን በትልቅ ሃላፊነት ማከናወን ይጠበቅባችኋል።

አገራችን በጥንት ጊዜ ታላቅ አገር እንደነበረች እና በኋላ ላይ ግን ዝቅተኛ የሚባለውን መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎት እንኳ ለማሟላት የተሳናት ተረጅ አገር ሆና ነበር ። ዛሬ ሁኔታውን መለወጥ ጀምረናል።
ኢትዮጵያችን ልታድግና ወደ ቀድሞ ታላቅነቷ ትመለስ ዘንድ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የምታደርገው ጥረት የህብረሰቡን ሁለገብ ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡

በመሆኑም በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አገራችንን ወደ ከፍተኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አምራችነት እና ላኪነት ለማሸጋገር ብሎም ህዳሴዋን ለማረጋገጥ እጅ ለእጅ ተያይዘን ተግተን እንድንሰራ የኢፌዴሪ መንግስት ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አለባበሳችሁን ለማስተካከልና ለሌሎች ጉዳዮች ይረዳችሁ ዘንድ የሰኔ 10/2009 ዓ.ም የአገራችን ዋናዋና ከተሞች እለታዊ የአየር ሁኔታ ትንበያ የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ አጄንሲ ከወዲሁ አድርሶናል፡፡

No automatic alt text available.

Published in አካባቢ

አክሱም ሰኔ 9/2009 ኢትዮጵያ የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በምታከናውናቸው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የደቡብ ኮሪያ መንግስት የሚያደርገውን እገዛ እንደሚያጠናክር አስታወቀ።

በአድዋ ከተማዋ የኮሪያ አለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ /ኮይካ/ በ80 ሚልዮን ብር ያስገነባውን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስመርቋል።

በምረቃው ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሙን ዋ ኪም እንደገለጹት ሃገራቸው በትምህርትና በሰው ሃይል ልማት ያላትን ልምድና ድጋፍ መስጠቷን ትቀጥላለች።

ትምህርት ቤቱም በክልሉ ለሚሰጠው ትምህርት ጥራትና ተደራሽነት የተሻለ እገዛ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በታሪካዊቷ የአድዋ ከተማ መገንባቱም የአድዋ ጦርነት የአለም የጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት እና የተስፋ ተምሳሌትነቱን እንደሚያጎላ ገልጸው "በዚህ ቦታ መዋእለ ንዋያችንን ማፍሰሳችን የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋገር ነው" ብለዋል።

የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር አረጋዊ ሓጎሰ በበኩላቸው "የተደረገው ድጋፍ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እና የልማት ትብብር እያደገ መምጣቱን ማሳያ ነው" ብለዋል።

"ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት መገንባቱ በከተማዋ እና አከባቢዋ የነበረውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እጥረት በማቃለል በእውቀት የተገነባ የሰው ሃይል ለማብቃት አስተዋጽኦ ይኖረዋል " ብለዋል።

ቀደም ሲል የተማሪዎች የመማሪያ ክፍሎች እጥረት እንደነበረ ገልጸው ከ40 ክፍሎች በላይ የያዘው ትምህርት ቤት መገንባቱ የተረጋጋ የመማር ማስተማር እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑንም አስረድተዋል።

"ትምህርት ቤቱ የኢትዮጵያ መንግስት ፍትሐዊና ምቹ የትምህርት እድል ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት ለማሳደግ ያግዛል" ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ አፍሬም ወልደጊዮረጊስ ናቸው።

"የኮሪያን መንግስት ላደረገው ትብብር ምስጋና ለማቅረብ  እወዳለሁ ያሉት" አቶ ኤፍሬም የልጆቻቸውን የወደፊት እድል በተሻለ መስመር ለመምራት የትምህርት ቤቱ እገዛ ከፍተኛ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

"ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች፣የኮምፒዩተር ማዕከል፣ቤተ ንባብና ሌሎችንም ያሟላ መሆኑ  ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ያግዛል" ያሉት ደግሞ የከተማው አስተዳደር ተወካይ አቶ ይከአሎ ለገሰ ናቸው።

ትምህርት ቤቱን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ የከተማ አስተዳድሩ ከህዝቡ ጋራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በከተማዋ የቀድሞ መጠሪያ በነግስተ ሳባ ስም የሚጠራው ትምህርት ቤቱ ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን በዘጠኝ ህንፃዎች ከ40 በላይ መማሪያ ከፍሎች፣የአስተዳደር፣የቤተ-ንባብ፣ የኮምፒዩተር ማእከልና ሌሎችንም አሟልቶ የያዘ ነው።

Published in ማህበራዊ

መቀሌ  ሰኔ 9/2009 በሃይማኖቶች  መካከል  አብሮ የመኖርና የመከባበር  እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ  የሀይማኖት አባቶች አስተምህሮ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመለከተ፡፡

 ጉባኤውና  የፌደራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር  በመተባበር  በሀይማኖት አክራሪነት መታገያ ስልቶች ላይ  ያዘጋጁት  የሁለት ቀናት የአሰልጣኞች ስልጠና በመቀሌ ከተማ ተካሂዷል፡፡

 የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ  ምክትል ጠቅላይ ፀሐፊ አቶ ሕሉፍ ወልደስላሴ በዚህ ወቅት  እንደገለፁት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ ያለውን የሀይማኖት አክራሪነትና ፅንፈኝነት  በፅኑ መታገል ይገባል፡፡

 "ሀይማኖትን ሽፋን አድርገው የሚቀሳቀሱ ፅንፈኛና አክራሩ  ቡድኖች  ቀዳሚ ስራቸው  ለዘመናት የቆየውን አብሮ የመኖርና የመከባበር እሴትን ማፍረስ ነው "ብለዋል፡፡

 የዚሁ አስተሳሰብ ሰለባ እየሆኑ ያሉትን ወጣቶች በአስተምህሮ ለመመለስ  የሀይማኖት አባቶች ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመው በሀገሪቱ ለዘመናት የቆየ በሃይማኖቶች መካከል መከባበርና አብሮ የመኖር እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ  ከቤተሰብ ጀምሮ ልጆችን  ማስተማር እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

 "የሀገሪቱን  ሰላም በማስጠበቅ  የልማትና እድገትን ጉዞውን ለማሳካት ብዝሃነትን በአንድነት በማቀፍ  የግድ ነው " ያሉት ደግሞ  በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖትና እምነት ጉዳዮች ጄነራል ዳይሬክተር አቶ ጌታዋ ደስታ ናቸው።

 የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የጸጥታና አስተዳደር ጉዳዮች አማካሪ አቶ ፈረደ የሺወንድም  በበኩላቸው  "በህገመንግስቱ የተቀመጡ  የሀይማኖት እኩልነት ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ልማትና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ  መንግስት ይሰራል "ብለዋል፡፡

 የወቅቱ እንቅፋቶች የሆኑት ትምክህት፣ጠባብነት፣ አክራርነትና ፅንፈኝነት መታገል ወሳኝ በመሆኑ  ሰልጣኞች ያገኙትን ትምህርት ለሌለውም ህብረተሰብ በማካፈል የድርሻውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

 በተለይ ወጣቱን በአክራሪዎችና ፅንፈኞች ሰለባ እንዳይሆን የሃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን እንዲወጡ ስልጠናው ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የስልጠናው ተሳታፊ መልአከ መዊእ ሰለሞን አባይ ናቸው፡፡

 ሌላው የስልጠናው ተሳታፊ ሐጂ ኑሩ ሁሴን በበኩላቸው የሀይማኖት አባቶች አብሮ ለመስራት እንዲችሉ ከስልጠናው  የተሻለ እውቀት ገልጸዋል፡፡

 ዛሬ በተጠናቀቀው ሰልጠና ከትግራይ ክልል የተወጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣የመንግስት ስራ ሃላፊዎች፣ የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀት አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2009 በተሽከርካሪዎች ላይ ለሙከራ የገጠመው ዘመናዊ የቁጥጥር መሳሪያ ቀልጣፋ የስምሪት አገልግሎት መስጠት እንዳስቻለ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጂፒኤስ የተሰኘው የቁጥጥር መሳሪያው በጽህፈት ቤቱ፣ በትራፊክ ማኔጅመነት ኤጀንሲ፣ በመንገዶች ባለስልጣንና በሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ተቋማት ውስጥ ለሙከራ ተተግብሯል።

መሳሪያው በሳተላይት አማካኝነት በሶፍትዌር ከኮምፒዩተር ጋር በማገናኘት የአንድን ተሽከርካሪ ሙሉ እንቅስቃሴ መከታተል የሚያስችል ነው።

የጽህፈት ቤቱ የከተማ የጭነት ትራንስፖርት የስራ ክፍል ኃላፊ አቶ ኢሳያስ አየለ እንደገለጹት፤ የቁጥጥር መሳሪያው 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን እስካሁን በ125 ተሽከርካሪዎች ላይ ተገጥሞ ክትትል እየተደረገበት ይገኛል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ የቁጥጥር መሳሪያው ተግባራዊ መሆኑ ቀደም ሲል በነበሩ የማሽከርከር ጥንቃቄ ጉድለቶች ላይ መሻሻል በማሳየቱ የተሸከርካሪውን ደህንነት መጠበቅ አስችሏል።

በጽህፈት ቤቱ የጠቅላላ አገልግሎት ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ አንተነህ ጌትነት በበኩላቸው መሳሪያው ተግባራዊ በመደረጉ ቀልጣፋ ስምሪት ለመስጠትና የነዳጅ አጠቃቀምን ለመቆጣጠር በማስቻሉ የመንግስትና የህዝብ ሀብት ከብክነት እንዲጠበቅ አድርጓል።

ቴክኖሎጂው ተሽከርካሪዎች ያሉበትን ቦታ ማወቅ የሚያስችል በመሆኑ የጉልበትና የጊዜ ብክነትን በማስቀረት ከግምታዊ አሰራር የተላቀቀና በመረጃ የተደገፈ ስራ መስራት ማስቻሉንም አክለዋል።

ቴክኖሎጂው በጽህፈት ቤቱ መተግበር ከጀመረ ወዲህ ከአሁን ቀደም በአሽከርካሪዎች የጥንቃቄ ጉድለት አልፎ አልፎ ይከሰቱ የነበሩ የተሽከርካሪ ግጭቶች መቀነሳቸውንም ነው ያብራሩት።

እስከዚህ ወር መጨረሻም መሳሪያው በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፣ በአንበሳ የከተማ አውቶቡስ፣ በአሽከርካሪ ተሸከርካሪ ትራንስፖርት ባለስልጣንና መሰል ተቋማት ስር በሚገኙ ተሽከርካሪዎች እንደሚገጠም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

በጽህፈት ቤቱ የሚገኙ አሽከርካሪዎች የመከታተያ ስርዓቱ ለአሽከርካሪውም ሆነ ለተሽከርካሪው ደህንነት ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ ቢሆንም የመንቀሳቀስ መብት በሚነፍግ ሁኔታ ተግባራዊ መደረግ እንደሌለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የአሽከርካሪውን የመንቀሳቀስ መብት የሚገድብ ከሆነ ቁጥጥሩ በአሽከርካሪው የባለቤትነት ስሜት ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድርም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ የቁጥጥር መሳሪያውን በግል የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የህግ ማዕቀፍ እንደሚዘጋጁ ጽህፈት ቤቱ ለኢዜአ  በላከው መግለጫ አመልክቷል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2009 "የካዳባ የጨው አቅራቢ አክሲዮን ማህበር እየጠቀመን አይደለም፤ የምናመርተው ምርት እና የምናገኘው ገቢ ተመጣጣኝ አይደለም" ሲሉ የአፍዴራ የጨው አምራቾች ቅሬታ አቀረቡ። 

የካዳባ የጨው አቅራቢ አክሲዮን ማህበር በበኩሉ "ችግሩ የማህበሩ ሳይሆን መንግስት ከአፍዴራ 282 ሺ ኩንታል ጨው ብቻ እንዲወጣ ባወጣው ኮታ መሠረት እየተሠራ በመሆኑ ነው" የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

'የካዳባ የጨው አቅራቢ አክሲዮን ማህበር' የአፍዴራ የጨው አምራቾችን መብትና ጥቅም ለማስከበር በአምራቾቹ በራሳቸው በ2006 ዓ.ም. የተቋቋመ ማህበር ነው።

ቅሬታቸውን ያቀረቡት አምራቾች፤ የአክሲዮን ማህበሩ በሚያመርቱት ጨው የሚጣለው ግምት "ፍትሃዊ አይደለም" እንዳልሆነ ተናግረዋል። ይህም ለእነርሱ ተጠቃሚነት የተቋቋመው ማህበር እየጎዳቸው መሆኑን እንደሚያሳይ ነው ያመለክቱት።

የኢዜአ ሪፖርተር ለዘገባ በተንቀሳቀሰበት ወቅት በየቦታው የጨው ምርት ተከምሮ አስተውላል። ግምቱም "አስራ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ያህል" እንደሚሆን ነው የተነገረው።

አምራቾቹ በአስቸጋሪ ሙቀት ውስጥ ሆነው ያመረቱትን ጨው የሚሸጡት በ257 ብር ሲሆን፤ ለእነርሱ የሚደርሳቸው 151 ብር ነው። የጨው ምርቱ ፋብሪካ ገብቶ ተጨማሪ እሴት ተጨምሮበት የሚሸጠው ደግሞ 529 ብር ነው።

አምራቾቹ ባለተመቸ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ከሚያመርቱት ጨው ተጠቃሚ ያለመሆናቸው ለቅሬታቸው መንስኤ ነው። አክሲዮን ማህበሩ የመደለል ተግባር እያከናወነ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በአፍዴራ የጨው አምራች አቶ አብደላ ረጂድ፣ አቶ ሳዲቅ አህመድ እና አቶ ኃይላይ በርሄ የሚያመርቱት ምርት ብዙ ቢሆንም የሚያገኙት ገቢ ግን አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የጨው አምራቾቹ በአክሲዮን ማህበሩ "ተሰፋ ቆርጠን ሞራላችን ተነክቷል" የሚል ሀሳብ ነው ያላቸው።

አቶ ኃይላይ በርሄ "የሚገመተው ግምት ፍትሃዊ ባለመሆኑ ትንንሽ አምራቾች አየተጎዱ በመሆኑ ተጠቃሚ አይደለንም" ብለዋል።

ለማምረቻ መሣሪያ  የሞተር ፓምፕና  የነዳጅ  ዋጋ፣ የመቆፈሪያ ዶማና የሠራተኛ ዋጋ እንዲሁም ሌሎች ግብዓቶችን ለመሸፈን የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ ቢሆንም "የምናገኘው ገቢ ግን ዝቅተኛ ነው" በማለት ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።

የካዳባ የጨው አቅራቢ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዋሴ ሳዲቅ መሃመድ እንዳሉት፤ ማህበሩ አምራቾችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ አበክሮ እየሰራ ነው።

አምራቾቹ ላነሱት 'ፍትሃዊ ግምት እየተገመተ አይደለም'  ለሚለው ጥያቄ አቶ ዋሴ ዘንድሮ "የተገመተው ግምት ትክክለኛ ነው" በማለት መልሰዋል።

አምራቾቹ ያመረቱት ምርት 'ከተገመተ በኋላ ለምን አይነሳም'  ለሚለው ጥያቄያቸው፤ "ይሄ ካለማወቅ የሚነሳ ጥያቄ ነው። ምክንያቱም ከክምሩ የሚነሳው ምርት በወር ሁለት በመቶ ብቻ ነው ማንሳት የምንችለው" ብለዋል አቶ ዋሴ።

የዚህ ችግር ምክንያትም ማህበሩ ሳይሆን መንግስት ከአፍዴራ 282 ሺ ኩንታል ጨው ብቻ እንዲወጣ ባወጣው የኮታ አሰራር መሠረት መሆኑን ነው ገልጸዋል።

አምራቾች የሚያነሱትን ቅሬታ ለመፍታት "መንግስት ለአፍዴራ ያወጣውን ኮታ እንዲያሻሽልና ኮታውን ከፍ እንዲያደርግ የሚመለከተውን አካል እያነጋገረን ነው" ያሉት አቶ ዋሴ፤ አሁን እየተነሳ ያለው ችግር "በዚህ መንገድ ይፈታል" የሚል እምነት አላቸው።

ኢዜአ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት በጉዳዩ ዙሪያ ለማነጋገር  በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ጥረቱ አልተሳካም።

ነገር ግን የንግድ ሚኒስቴር ኀዳር 30 ቀን 2009 ዓ.ም ባስተላለፈው ውሳኔ ለፋብሪካዎች ብቻ ጥሬ ጨው  ተጨማሪ እሴትና ኤክሳይዝ ታክስን ጨምሮ በኩንታል 257 ብር ከ95 ሳንቲም እንዲሸጥ ያዛል።

ፋብሪካዎቹም በማጠብና በአዮዲን በማበልፀግ ለጅምላ አከፋፋዮች ተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ በኩንታል 529 ብር ከ68 ሳንቲም እንዲሸጡ እንዲሁ።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2009 በኢትዮጵያ የተጀመረው የኢንተርኔት ቪዛ አገልግሎት ወደ አገሪቱ የሚመጡ ኢንቬስተሮችና ቱሪስቶች ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻል የንግድ፣ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ መነቃቃት እንደሚፈጥር ተገለፀ።

የኢንተርኔት ቪዛ አገለግሎቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መምሪያ በጋራ አዘጋጅተውታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም አገሪቷ በቱሪስት መስህቦች የበለጸገች ብትሆንም በሎጂስቲክ ቅልጥፍና ማነስ ምክንያት ማግኝት የሚገባትን ገቢ እያገኝች እንዳልሆነ ጠቁመዋል።

''በመሆኑም የአገልግሎቱ መጀመር አገሪቱን በአፍሪካ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ይደግፋል" ብለዋል።

አገልግሎቱን ለማመልከት፣ በክሬዲት ካርድ አማካኝነት ተገቢውን ክፍያ ለመክፈልና የቪዛ ፈቃድ ለማግኘት በተከፈተ አንድ ድረ ገጽ አማካኝነት ይሰጣል።

ፎርሙን ሞልተው ተቀባይነት ያገኙ አመልካቾችም ተቀባይነት ማግኘታቸውን የሚያሳይ መልእክት የሚደርሳቸው ሲሆን አዲስ አበባ ቦሌ አየር መንገድ እንደደረሱም ቪዛቸው ተዘጋጅቶ ይጠብቃቸዋል።

ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኘ አየር መንገድ ባለቤት ስትሆን ባለፉት ሰባት ዓመታት በዘርፉ በአማካይ የ25 በመቶ እድገት አስመዝግባለች።

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2009 የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬ መደበኛ ስብሰባው በሁለት የስምምነት ፍቃዶችና በሶስት አዋጆች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።

ምክር ቤቱ በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኦጋዴን አካባቢ ካሉብና ሂላላ በመባል የሚታወቁትን የጋዝ ልማት ስፍራዎች ቀደም ሲል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ጅቡቲ ወደብ ማጓጓዝ የሚያስችል ቧንቧ ለመዘርጋት መብት የሚያሰጠው ስምምነት እንዲፈረም ወስኗል።

ስምምነቱ የሚፈረመው ፖሊ.ጂሲ.ኤል ፔትሮሊየም ኢንቨስትመንት ሊሚትድ ከተባለውና በብሪትሽ ቨርጅን አይላንድስ ከተመሰረተው ኩባንያ ጋር ነው።

በተመሳሳይ ዋይ.ኤም.ጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የአነስተኛ የጽንሰ ወርቅ ማዕድን ማምረት ፍቃድ ላይም ከተወያያ በኋላ ዘርፉ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ረገድ ጠቃሜታው ከፍተኛ በመሆኑ ስምምነቱን እንዲፈረም ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤቱ የኤሌክትሮኒክስ ፊርማን ለመደንገግ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተም በአገሪቷ ኤሌክትሮኒክስ ንግድና በኢንፎርሜሽን ቴክናሎጂ የታገዙ የመንግስት አገልግሎቶችን ለማበረታታት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በቀረበለት ረቂት አዋጅ ላይም ተወያይቷል።

ረቂቁ ምቹ የሕግ ማዕቀፍ መፍጠር፣ የኤሌክትሮኒክ መልዕክት ልውውጥን ህጋዊ እውቅና መስጠት፣ የተሳታፊዎችን መብትና ግዴታ በግልጽ የሚደነግግ ነው ተብሏል።

በተጨማሪም በኤሌክትሮኒክ መልእክት ልውውጥ ወቅት የተሳታፊዎችን ማንነት፣ የመልእክቶችን ትክክለኛነትና አለመካካድን በማረጋገጥ መተማመን ለመፍጠር የሚያስችል በመሆኑ ሕጉን ማውጣት እንዳስፈለገ ተገንዝቦ ረቂቅ አዋጁ እንዲፀድቅ ለሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የወሳኝ ኩነት ምዝገባና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅም ተመልክቷል።

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ከተጀመረ ወዲህ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያጋጠሙትን የአሰራር ክፍተቶች ለመቅረፍና አገልግሎቱን የተሟላ ለማድረግ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 760/2004ን በማሻሻል ይጸድቅ ዘንድ ለምክር ቤቱ አስተላልፏል።

ስለ ዕፅዋት አዳቃይ መብት የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይም በመወያያት አንዳንድ ማስተካከያዎችን አክሎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  እንዲያፀድቀው መወሰኑን ምክር ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

Published in ፖለቲካ

ማይጨው ሰኔ 9/2009 በተያዘው የመኽር ወቅት የማዳበሪያና የውሃ አጠቃቀማቸውን በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን በትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

አርሶ አደሮቹ ለምርት ዘመኑ 36 ሚሊዮን ብር እጅ በእጅ በመክፈል ማዳበሪያ ገዝተዋል።

የእንዳመሆኒ ወረዳ አርሶ አደር ታደሰ በርሄ  እንደገለጹት የአፈር ለምነትን ለመጨመር  ከፍግና ብስባሽ ያዘጋጁትን የተፈጥሮ  እንዲሁም ምጥን ማዳበሪያ በመጠቀም ግማሽ ጥማድ ማሳቸውን በስንዴ ምርጥ ዘር ሸፍነዋል፡፡

ለዘመኑ የምርት ወቅት የሚያስፈልጋቸውን ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እጅ በእጅ በመክፈል ገዝተው ስራ ላይ አውለዋል።

እየጣለ ያለውን ዝናብ ተከትሎ የሚመጣውን ጎርፍ  ጠልፈው ወደ እርሻቸው ለማስገባት ቦይና የአፈር እርከን እየሰሩ መሆናቸውን አርሶ አደር ታደሰ ተናግረዋል።

"በስልጠና ባገኘሁት ግንዛቤ ለመጀመሪያ ጊዜ ምጥን ማዳበሪያና ዩሪያን በመጠቀም የስንዴ ምርጥ ዘር ለመዝራት የማሳ ዝግጅት አድርጊያለሁ " ያሉት ደግሞ ሌላው የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ሃለፎም መረሳ ናቸው።

እርሶ አደሩ እንዳሉት የዝናብ እጥረት ቢያጋጥም ሰብላቸውን ከጉዳት ለመታደግ የጎርፍ ውሀ ለማጠራቀም የሚያስችላቸውን ኩሬ ቆፍረው አዘጋጅተዋል፡፡

በዞኑ የራያ አዘቦ ወረዳ አርሶአደር ሃፍቱ ንጉሰ በበኩላቸው ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ምጥን ማዳበሪያን በመጠቀም ሁለት ጥማድ ማሳቸውን በማሽላ ዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል፡፡

ማሳቸው ውስጥ የዝናብ ውሃ ለመያዝ እርከን መስራታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ዝናብን ብቻ ሳይጠብቁ ያለውን የውሃ አማራጭ ስራ ላይ በማዋልና የማዳበሪያ አጠቃቀማቸውን በማሻሻል ምርታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ሃይለ ካሳ እንዳሉት ለምርት ዘመኑ ከ36 ሺህ ኩንታል በላይ  ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።

ከዚህም ውስጥ 27 ሺህ ኩንታሉ ለአካባቢው የአፈር አይነት የሚስማማ ምጥን ማዳበሪያ ሲሆን ቀሪው ዩሪያ ነው፤ ምጥን ማዳበሪያ እንደየአካባቢው የአፈር ሁኔታ እየተለካ ከተለያዩ ንጥረ ነገሮች የሚዘጋጅ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

እንደ ቡድን መሪው ገለፃ ለምርት ዘመኑ የቀረበው የማዳበሪያ ግዥ አርሶ አደሩ ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ እጅ በእጅ ክፍያ ፈፅሟል፤ በገበሬው የተዘጋጀ ከ6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ።

በምርት ዘመኑ የአፈር እርጥበትን ጠብቆ ለማቆየት በ103 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የአዲስ እርከን ፣ የነባር ጥገናና የጎርፍ ውሀ ቅልበሳ ስራ በአርሶ አደሩ ተሳትፎ እየተካሄደ ነው ።

በዞኑ ለመኽሩ እርሻ ከተዘጋጀው 143 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን 36 ሺህ ሄክታር በአገዳ ሰብል  መሸፈኑን ቡድን መሪው ጠቁመው ቀሪውንም እስከተያዘው ወር  ማብቂያ ድረስ በተመሳሳይ እንደሚሸፈን አመልክተዋል፡፡

በምርት ዘመኑ ከ40 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በሰብል ልማቱ እየተሳተፉ ሲሆን ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማሰባሰብ ታቅዷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2009 በስፖርት ዘርፍ ብቁ ባለሙያዎች ለማፍራት ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ የስፖርት ሳይንስ ተማሪዎች ክህሎት ሊመዘን እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።

የመግቢያ ውጤት አስመዝግበው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች በስፖርት ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ የሚመደቡት ባላቸው የስፖርት ክህሎት ሳይሆን በፍላጎታቸው ነው።

ይህ መሆኑ ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ከሚወጡ የመስኩ ባለሙያዎች አብዛኛዎቹ የስፖርት እንቅስቃሴ ክህሎት ይዘው እንዳይወጡ  ማድረጉን ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናግረዋል።

ምሩቃኑ ለአገሪቱ ስፖርት እድገት በሙያቸው እገዛ ማድረግ ቢጠበቅባቸውም በክህሎት የበለጸጉ ባለመሆናቸው እዚህ ግባ የሚባል አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳልቻሉ ነው የስፖርት ምሁራኑ የገለጹት።

የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ አካዳሚ ዲን ዶክተር አብነት አያሌው እንደተናገሩት ብቃት ያላቸው ሙያተኞች ማፍራት ያልተቻለው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲገቡ ተሰጥኦና ክህሎትን መሰረት ያደረገ ምዘና ባለመኖሩ ነው።

ስፖርት በተግባር የሚታይ በመሆኑ ሰልጣኞቹ በዘርፉ ያላቸው ክህሎትና ተሰጥኦ በተግባር ተመዝኖ እንዲገቡ በማድረግ ሳይንሳዊ እውቀትና ክህሎት ይዘው እንዲወጡ ማድረግ ይቻላል ነው ያሉት።

"ይህ ባለመሆኑ ምሩቃኑ የሚጠበቅባቸውን ያህል ሙያዊ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም" ያሉት ዶክተር አብነት በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ዘርፍ የሚሰለጥኑ ተማሪዎች የክህሎት ፈተና እንዲወስዱ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።

"በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በስፖርት ዘርፍ የሚሰጠው ስልጠና ወጥ እንዲሆን የጋራ የመመዘኛ መስፈርት ቢወጣ መልካም ነው" ሲሉም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

"ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የሚወጡ የስፖርት ባለሙያዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ችግር ይስተዋልባቸዋል" ያሉት ደግሞ የአዳማ ዮኒቨርሲቲ የስፖርት መምህር ይገርማል ንጉሴ ናቸው።

እንደ እሳቸው ገለፃ በስፖርት ሳይንስ ከሚሰለጥኑ ተማሪዎች አብዛኞቹ ፍላጎት የሌላቸውና ከአንድ የአካል ብቃት ባለሙያ የሚጠበቀውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ አይደሉም።

የስፖርት ፍላጎትና ክህሎት ያላቸውን ተማሪዎች በማሰልጠን በዘርፉ በማሰማራት የአገሪቱ ስፖርት ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር አስጨናቂ ታደሰ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በ1994 ዓ.ም የራሱን ስርዓተ ትምህርት ቀርጾ የተግባር ፈተና በመስጠት የስፖርት ስልጠና መጀመሩን አስታውሰዋል።

ሆኖም ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ የትምህርት ክፍሉ እንደ ሌሎች ትምህርት ክፍሎች በአገር አቀፍ የስርዓተ ትምህርት በመካተቱ ያለ ተግባር ፈተና የፍላጎት ምደባ መጀመሩን ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ በስፖርት ሳይንስ ሰልጥነው ለሚወጡ ተመራቂዎች የተግባር ክህሎት ደካማ መሆን ምክንያት እንደሆነ ነው የገለጹት።

በቀጣይ በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ከተመደቡ ተማሪዎች መካከል በተግባር ፈተና በመለየት በስፖርት ሳይንስ ስልጠና ለመስጠት መታቀዱን ዶክተር አስጨናቂ ተናግረዋል።

 

 

 

Published in ስፖርት
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን