Items filtered by date: Thursday, 15 June 2017

ጎንደር ሰኔ 8/2009 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጣና ሀይቅ ላይ እየተስፋፋ የመጣውን እምቦጭ አረም ሰብስቦ በመፍጨት የሚያስወግድ መሳሪያ በመፍጠር የሙከራ ስራውን በተያዘው ወር መጨረሻ እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መስፍን ለኢዜአ እንደተናገሩት መሳሪያው በቀን 10 ቶን እምቦጭ አረምን ከሀይቁ ላይ ሰብስቦና ፈጭቶ የማስወገድ አቅም ይኖረዋል፡፡

ደረጃውን ጠብቆ በዩኒቨርሲቲው መምህራንና በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ትብብር የተሰራው ይኸው መሳሪያ በአሁኑ ወቅት 90 በመቶ ተጠናቋል፡፡

ኬንያና ሌሎች ሀገሮች መሳሪያውን ከውጪ ሀገር ገዝተው እየተጠቀሙ መሆናቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ዩኒቨርስቲው ግን በ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ በሀገር ውስጥ እንዲመረት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በሀይቁ ላይ የተስፋፋውን እምቦጭ አረም ለማስወገድ ሌሎች ስድስት ያህል ተጨማሪ መሳሪያዎች እንደሚያስፈልጉ የገለጹት ዳይሬክተሩ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለማሰራት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

በሀይቁና በዳርቻው የተስፋፋውን እምቦጭ አረም በዘንድሮው ክረምት  በመሳሪያው ታግዞ የማስወገድ ስራ ለመጀመር ዩኒቨርሲቲው ዝግጅት ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡ 

ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ በጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተው እምቦጭ አረም አድማሱን በማስፋት የሀይቁ አዋሳኝ በሆኑ አምስት ወረዳዎች ከ29ሺ ሄክታር በላይ የውሃ አካል መውረሩ ታውቋል፡፡

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2009 በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የተገነባው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ምርት ምዕራፍ መሸጋገሩን በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚንስትሩ ልዩ አማካሪ ዶክተር አርከበ እቁባይ ገለጹ።

የፓርኩን ወደ ምርት ምዕራፍ መሸጋገር አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። 

ዶክተር አርከበ እንደገለጹት፤ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአፍሪካ የመጀመሪያ ዘላቂነት ያለውና ዘመኑ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ  እድገት የሚጠቀም የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ፓርክ ነው። 

"የኢንዱስትሪ ፓርኩ ወደ ማምረት መሸጋገሩም መንግስት እያከናወነ ያለውን  የአኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር  ስራ  የሚደግፍ ነው" ብለዋል።

የፓርኩ የመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ከተጠናቀቀ በኋላ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ በዓለም አቀፈ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ 18 አምራቾች እንዲሁም ስምንት የአገር ውስጥ ድርጅቶችን መሳብ እንደተቻል ተገልጿል።

ፓርኩ  በሙሉ አቅሙ ማምረት  ሲጀምር ለ60 ሺ ሰዎች የስራ እድል ከመፍጠሩም በላይ አገሪቷ ከወጪ ንግድ በዓመት ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት እንደሚያስችላት ዶክተር አርከበ ጠቁመዋል።

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የምርት ምዕራፍ  የመክፈቻ ስነ ስርዓት ሰኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ኢኮኖሚ

ነቀምቴ ሰኔ 8/2009 በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ በማህበር ለተደራጁ አንድ ሺህ 100 ወጣቶች የእርሻ መሬት የይዞታ ማረጋገጫ ተሰጠ፡፡

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ቶለሣ እንደገለጹት በ98 ኢንተርፕራይዝ ለተደራጁት ለእነዚህ  ወጣቶች ሰሞኑን የተሰጠው የይዞታ ማረጋገጫ  ካርታና የምስክር ወረቀት ነው፡፡

ወጣቶቹ በተሰጣቸው የይዞታ ማረጋገጫ መሰረት መንግሥት የወሰነውን  1 ሺህ 570 ሄክታር የእርሻ መሬት  እንዲረከቡ ተደርጓል።

ስራ አጥ ወጣቶቹ  በተሰጣቸው የእርሻ መሬት ዝናብና ሌሎችንም የውሃ አማራጮችን በመጠቀም የተለያየ ሰብል ለማልማት በዝግጅት ላይ እንደሚገኙም ተመልክቷል፡፡ 

በወረዳ  የጉቴ-ጉዲና ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ረቢራ ገመዳ በሰጠው አስተያየት 10 ሆነው በመደራጀት  7 ሺህ 300 ብር መቆጠባቸውን ተናግሯል፡፡

ከመንግሥት የተመቻቸላቸውን 70 ሺህ  የብድር ገንዘብ በመጠቀም   ማህበራቸው በተረከበው 10 ሄክታር መሬት አርሰው በቆሎ ፣ አኩሪ አተርና ቦሎቄ ለመዝራት  ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

በምስራቅ ወለጋ ዞን ገጠርና ከተማ በበጀት ዓመቱ  ስራ አጥ የነበሩ  31 ሺህ 225 ወደስራ እንዲገቡ መደረጉን የገለጹት ደግሞ የዞኑ  ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞገስ ኢዳኤ ናቸው፡፡

ወደስራ ከገቡትም  2 ሺህ 382 ወጣቶች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ምሩቃን ናቸው።

ግብርና ፣ እንጨትና ብረታ ብረት ስራ እንዲሁም  ንግድና አገልግሎት መስኮች ወጣቶቹ ከተሰማሩባቸው የስራ መስኮች መካከል ይገኙበታል፡፡

ለወጣቶቹ  ከብድር አቅርቦት ሌላ በሕገ ወጥ መንገድ በባለሀብቶች ተይዞ የነበረ 2 ሺህ 84 ሄክታር መሬት እንዲሁም   56 የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎች በማመቻቸት ድጋፍ መደረጉን  አቶ ሞገስ አመልክተዋል፡፡

ስራ የሌላቸው ወጣቶችን በመለየትና በመመልመል  በተመሳሳይ የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2009 ጃፓናውያን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራት እንደሚፈልጉ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ መንግስትም በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራት ለሚፈልጉ ባለኃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካትሱሚ ሂራኖ የሚመራውን ልዑክ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሁለቱ አገሮች ጃፓናውያን ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ አናሳ በመሆኑ በቀጣይ ተሳትፏቸው ይበልጥ በሚያጎለብቱበት ሁኔታ ላይ መምከራቸው ይታወቃል።

የጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ካትሱሚ ሂራኖ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ያመቻቸውን አጋጣሚ በመጠቀም የጃፓን ባለኃብቶች በአገሪቷ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራት ይፈልጋሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት አገልግሎት ክፍልና የሞጆን ደረቅ ወደብ ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን አመልክተው፤ ባለሃብቶቹ በተለያዩ ዘርፎች መሰማራት እንዲችሉ የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጃፓን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በማውጣት በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎትና ተነሳሽነት ስላላቸው መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል ምክትል ፕሬዘዳንቱ።

በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ መሰማራት ለሚፈልጉ ጃፓናውያን ባለሃብቶችም መንግሥት አስፈላጊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ መናገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቢዝነስ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄኔራል ወይዘሮ ኢየሩሳሌም አምደማሪያም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በቀላልና መንግስት ትኩረት በሚሰጣቸው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በቀጣይ ድጋፍ እናደርጋለን" ብለዋል።

ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ድርጅት ተወካዮችም የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክሩ ተጠቁሟል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2009 የአገር ውስጥ ባለሃብቱ በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን እንዲደግፍ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ወይዘሮ ሮማን ጥሪያቸውን ያስተላለፉት በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ፣ ደብሊው ኤ ዘይት ማምረቻ እና ማከፋፈያ እንዲሁም ኪያ ትራንስፖርት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር ለእናት ወግ ግብረ ሰናይ ድርጅት የሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር እርዳታ ባስረከቡበት ወቅት ነው፡፡

በአዲስ አበባ በሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚካሔደውን የተማሪዎች ምገባ መርሃግብር የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት፣ ትምህርት ሚኒስቴርና የእናት ወግ ግብረ ሰናይ ድርጅት በጋራ ያካሒዱታል።

ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ እሮማን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የአገር ውስጥ ባለሃብቱ ደጋፊ የሌላቸውና የነገ አገር ተረካቢ ሕፃናትን በመርዳት ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ሰብአዊና አገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል፡፡

''ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ነው ለአንድ ሰው ግን ጌጥ በመሆኑ እያንዳንዳችን ከተረዳዳን ነገ ብቁ  ዜጋ አፍርተን አገር እንዲረከቡ እናደርጋለን'' ነው ያሉት፡፡

ለምገባ መርሃ ግብሩ አንድ ሚሊዮን ብር የደገፈው የበላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ ባለቤትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በላይነህ ክንዴ እንደተናገሩት ፤ ድርጅታቸው  የአሁኑን እርዳታ  ጨምሮ ለተከታታይ 10 ዓመት ይለግሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት አገሪቷ እያደገች ልማታዊ ባለሃብቶችም እየተፈጠሩ ሲሆን፤ እነዚሁ አካላት "በማሕበራዊ ስራዎች ላይ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል" ነው ያሉት፡፡

የደብሊው ኤ የዘይት ማምረቻና ማከፋፈያ ዋና ስራ አስፈጸሚና ባለቤት አቶ ወርቁ አይተነው በበኩላቸው፤ ባለሃብቱ ሕጻናቱን በመደገፉና ያለምንም ችግር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረጉ "የሕሊና እርካታን ያመጣለታል" ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት እነዚሁ ሕፃናት ዘላቂነት ያለው ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግም ድርጅታቸው የአዋጭነት ጥናት አጠናቆ ለማስረከብ ቃል መግባቱን ገልፀዋል፡፡

ለምገባ መርሃ ግብሩ በደብሊው ኤ ዘይት ማምረቻ እና ማከፋፈያ አንድ ሚሊዮን እንዲሁም ኪያ ትራንስፖርት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር 500 ሺ ብር ለእናት ወግ ግብረ ሰናይ ድርጅት ዛሬ በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት አስረክበዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ጎንደር ሰኔ 8/2009 በሰሜን ጎንደር በተያዘው ክረምት  ገበያ ተኮር የሆኑ አምስት የሰብል ዓይነቶችን በኩታ ገጠም  የእርሻ ቴክኖሎጂ ለማልማት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ ለኢዜአ እንደገለጹት ሰሊጥ ፣በቆሎ ፣የቢራ ገብስ ፣ ማሽላና ጤፍ ናቸው በኩታ ገጠም እንዲለሙ የተመረጡት፡፡

ቴክኖሎጂውን ፈጥነው መተግበር ለሚችሉ ሞዴል አርሶአደሮች ክህሎታቸውንና እውቀታቸውን ለማጎልበት የሚያስችል ስልጠና በግብርና ማሰልጠኛ ማዕከላት ቀደም ሲል ተሰጥቷል፡፡

አርሶአደሮቹ ከአንድ ሺህ በላይ በሚሆኑ ኩታ ገጠም ቦታዎች እንዲደራጁ የተደረገ ሲሆን በዚህም 215ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬት እንዲያለሙ  ይደረጋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ ቴክኖሎጂው አርሶአደሩ መሬቱን በተበጣጠሰ መንገድ ከሚያለማበት ልማዳዊ አሰራር ተላቆ በጋራ በማረስ፣ በመስመር በመዝራት፣ በማረም፣ ግብአትን በመጠቀምና ምርቱንም በጋራ በመሰብሰብ ጊዜና ጉልበቱን በሚቆጥብ መንገድ ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችለው ነው፡፡

ኩታ ገጠም የእርሻ ቴክኖሎጂ በዞኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጥቂት መሬትና አርሶአደሮች ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑ በመረጋገጡ በተያዘው ክረምት  ገበያ ተኮር ሰብልን በስፋት ለማልማት ወደ ተግባር ተግብቷል፡፡

"ቴክኖሎጂው ምርታማነት ከማሳደግ አንጻር ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በአንድ ለአምስት የተደራጁ 18ሺ አርሶአደሮችን ማሳተፍ ጀምረናል "ያሉት ደግሞ በዞኑ የአለፋ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ተላይነህ ናቸው፡፡

በወረዳው ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ስድስት ሺ 500 ሄክታር የሚጠጋ የእርሻ መሬት ገበያ ተኮር የበቆሎና የጤፍ ሰብል  ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተካሂዱ ናቸው፡፡

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የዳስ ድንዛዝ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለምነው ቻሌ በበኩላቸው "ስለ ኩታ ገጠም የእርሻ ቴክኖሎጂ ተገቢውን እውቀትና ክህሎት በስልጠና አግኝቼ በአሁኑ ወቅት የእርሻ መሬታችንን በጋራ አርሰን ማሽላ ዘርተናል " ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂውን ባለፈው ዓመት በጤፍ ላይ ሞክረውት እንደነበር የገለጹት  የጣቁሳ ወረዳ ነዋሪ  አርሶአደር ታሪኩ ስለአባት ጥቅሙን በመገንዘብ ዘንድሮ በኩታ ገጠም አሰራር ከተደራጁ አርሶአደሮች ጋር ልማቱን አጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል፡፡

በሰሜን ጎንደር በተያዘው የክረምት ወቅት በተለያየ ሰብል ለማልማት  ከታቀደው 961ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን 150ሺህ ሄክታር ታርሶ በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አመልክቷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2009 የጉዞ ሠነድ የወሰዱ በሳዑዲ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከ82 ሺህ መብለጡን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

ለተመላሾቹ ቀደም ሲል ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ከተፈቀዱ ዕቃዎች ተጨማሪ እንዲያስገቡም ተፈቅዶላቸዋል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ መለስ ዓለም ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ እንደገለፁት ወደ አገራቸው መመለስ የሚሹ በሳዑዲ የሚገኙ ዜጎች በብዛት እየተመዘገቡ ነው።

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ሕገ ወጥ ያላቸውን ስደተኞች ወደ የአገሮቻቸው እንዲመለሱ የሰጠው የእፎይታ ጊዜ ሊጠናቀቅ 11 ቀናት ቢቀሩትም ለመመለስ ከተመዘገቡት ወደ አገር የገቡት ግን ግማሽ ያህሉ ብቻ እንደሆኑ ነው የተናገሩት።

የሳዑዲ መንግስት የእፎይታ ጊዜ አዋጅ ይዘትና ትርጓሜ ላይ ግንዛቤ ከመፍጠር የጀመረው ዜጎችን ወደ አገር እንዲመለሱ የመገፋፋት እንቅስቃሴና ከተመለሱም በኋላ ማቋቋሙ ከህብረተሰቡ ጋር እየተሰራበት ነውም ብለዋል።

ቀደም ሲል ከቀረጥ ነጻ የተፈቀዱ ዕቃዎችን በመከለስ ለተመላሾቹ መጠቀሚያ የሚሆኑ ከዓረቢያን መጅሊስ ወይም ሶፋ፣ መጋረጃና ምንጣፍ እስከ 42 ኢንችና ከዚያ በታች የሆነ ቴሌቪዥንና የወጥ ቤት ዕቃዎች ያለቀረጥ እንዲያስገቡ ተፈቅዷል።

ቃል አቀባዩ፤ ወደ አገር እየገቡ ያሉት መክፈል የሚችሉና ጤናሞች መሆናቸውን ጠቁመው፤ በኃይል የማስወጣት ሁኔታው ሲጀመር አቅም የሌላቸው፣ ጤናቸው የተጓደለና ህጻናት ሊመጡ ስለሚችሉ ለዚሁ ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።

አቶ መለስ እንደሚሉት የአዲስ አበባ መስተዳድር 700 የሚሆኑ በጎ አድራጊዎችን፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም 11 ሆስፒታሎችን፣ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንም ብርድ ልብስና ፍራሾችን አዘጋጅተዋል፡፡ 

ተመላሾቹ ችግር እንዳያጋጥማቸው ፖሊስ የራሱን እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ቃል አቀባዩ ከአዲስ አበባ ወደ መንደራቸው የሚያደርሳቸው የህዝብ ትራንስፖርት ጉዳይም እየተሰራበት መሆኑን አስታውቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት ጋር ትናንት ባደረጉት ውይይትም ሚድሮክ አስር ሚሊዮን ብርና 100 ለሚሆኑ ተመላሾች በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዕድል፣ 100 ለሚሆኑት የሥራ ዕድል፣ ለ100 ህጻናትም ከመዋዕለ ህፃናት ጀምሮ እስከ ስምንተኛ ክፍል ለማስተማር ቃል መግባቱን ገልጸዋል።

አቶ መለስ፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ኦሎምፒክ ኮሚቴና ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በጋራ አምስት ሚሊዮን ብር ለመስጠት ቃል እንደገቡም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች ማህበር ለህጻናትና ሴቶች የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለመስጠት፣ አርቲስቶች የማስታወቂያ ስራውን በነጻ ለመስራት፣ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትም ገንዘብ ለማሰባሰብ ቃላቸውን ሰጥተዋል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል “ከስደተኞች ጋር ቆመናል” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረው የዘንድሮው የዓለም የስደተኞች ቀን ሰኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጉኝል የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ይከበራል።

የኢፌዴሪ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች እንደሚገኙም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2009 የኮርያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ /ኮይካ/ በትግራይ ክልል በአራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ያካሄደውን የትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታ አስመረቀ።

በአድዋ ወይንም በቀድሞ መጠሪያው ንግስተ - ሣባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተካሄደው ይኸው የማስፋፊያ ግንባታው 6 ሺ 288 ስኩዌር ሜትር ይሸፍናል ተብሏል።

በማስፋፊያ መርኃ ግብሩ ዘጠኝ ሕንጻዎች የተገነቡ ሲሆን፤  የመማሪያ፣ የአስተዳደር፣ የኮምፒዩተር፣ መመገቢያ ክፍልና የጉባኤ አዳራሽ የግንባታው አካሎች ናቸው። 

በኢትዮጵያ የኮርያ አምባሳደር ኪም ሞን በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ግንባታው መጠናቀቁ በአድዋ ያለውን የትምህርት ሥርዓት ያሻሽላል።

የከተማዋ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት እንዲስፋፋና ተማሪዎቹም በዕውቀት በልጽገው "ለአገሪቷ ልማት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ያስችላቸዋል" ብለዋል።

የአድዋ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ዪኬሎ ለገሰ በበኩላቸው፤ ግንባታው የመምህራንና የተማሪዎች ጥምርታ ምጣኔን ዝቅ ለማደርግና ለማስተካከል ይረዳል።

አሁን ላይ ከተጨማሪ መማሪያ ክፍሎች በተጨማሪ የኮምፒዩተር መማሪያ ክፍል መገንባቱ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተናግረዋል

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2009 ኢትዮጵያ የዓለም ስራ ድርጅት ስራ አስፈጻሚ መደበኛ አባል ሆና ተመረጠች፡፡

በጄኔቭ በተካሄደው ምርጫ አፍሪካን በመወከል ከፍተኛ ድምጽ አግኝታ መመረጧን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው የፕሬስ መግለጫ አስታውቋል።

በአባልነት መመረጧ ከድርጅቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያስችል ያመለከተው የፕሬስ መግለጫው፤ በተለይ በወጣቶች ሥራ ፈጠራ ላይ በማተኮር መንግስት 10 ቢሊዮን ብር በመመደብ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ እንደሚያግዝ ነው የጠቆመው።

በዚህም የቴክኒክ እና የፖሊሲ ድጋፍ ለማጎልበት እንደሚረዳ ታምኖበታል፡፡

በተጨማሪ ድርጅቱ ቀጣይ ራዕይ ለማስቀመጥ ሰፊ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቅሶ፤ ኢትዮጵያ የስራ አስፈጻሚ መደበኛ አባል ሆና መመረጧ የራሷንና የአፍሪካን ጥቅም እና ፍላጎት ለማስጠበቅ ይረዳል፡፡

ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ስራ አስፈጻሚ መደበኛ አባል ሆና ለመጨረሻ ጊዜ ያገለገለችው እ.ኤ.አ ከ1999 እስከ 2002 ነው፡፡

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 8/2009 የፋይናንስ ተቋማት የሙስናና ብልሹ አሰራሮችን የመከላከል ተግባራቸውን ማጠናከር እንዳለበቸው ተነገረ።

የፌደራል ሥነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ከግልና ከመንግሥት ባንኮችና የመድን ድርጅቶች ጋር በጉዳዩ ላይ መክሯል።

በአገሪቱ በተዘረጋው ነጻ የኢኮኖሚ ስርዓት በአሁኑ ወቅት በርካታ የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ዘርፉን ተቀላቅለዋል።

ይህም የአገሪቱ የፋይንናስ ተቋማት ለኅብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት በቁጥርና በጥራት የማሳደግ ሚናው ጉልህ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ይሁንና የፋይናንስ ዘርፉ ከገንዘብ ጋር ባለው ቁርኝት ለሙስናና ብልሹ አሰራር የተጋለጠ እንደሆነ ነው ኮሚሽኑ የሚገልጸው።

ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ኃብት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ በዘርፉ በአመዛኙ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል ተጠቅሰዋል።

እነዚህንና ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል ተቋማቱ የጸረ-ሙስና ትግላቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ነው የፌደራል የሥነ ምግባርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ያሳሰበው።

ኮሚሽነር ዓሊ ሱሌይማን እንደተናገሩት ተቋማቱ ለሙስናና ብልሹ አሰራር ተጋላጭ እንዳይሆኑ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ማስፈን ይገባል።

ተቋማቱ ተመሳሳይ ተግባራትን በማጠናከር የጸረ-ሙስና ትግሉ ግብ አንዲመታ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

ኮሚሽኑ በዘርፉ የሚስተዋለውን ብልሹ አሰራር ለማስወገድ ትኩረት ማድረጉንና በቀዳሚነትም የሙያ ሥነ-ምግባርን ለማስረጽ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የፋይናንስ ተቋማቱ ከኮሚሽኑ ጋር እንዲሰሩም ነው ኮሚሽነር ሱሌማን ጥሪ ያቀረቡት።

የምክክሩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በተቋማቱ የሙስና ተጋላጭነትን ለመከላከል ከኮሚሽኑ ጋር በቅንጅት አንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በፋይናንስ ተቋማት የሚከሰትን ሙስና ለመከላከል የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅና የወንጀል ሕጉ እንዲሻሻል መደረጉ ይታወሳል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን