×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Wednesday, 14 June 2017

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2009  የጃፓን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ግብርና ማቀነባበር ጨርቃጨርቅና ኤሌክትሮኒክስ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ አመቺ ሁኔታ መኖሩን የጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት/ጀትሮ/ ገለጸ።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት/ጀትሮ/ ምክትል ፕሬዚዳንት ካትሱሚ ሂራኖ የተመራ 32 የባለሃብቶች ልዑካን ቡድን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት/ጀትሮ/ ምክትል ፕሬዚዳንት ካትሱሚ ሂራኖ እንደገለጹት ሁለቱም አገራት በቢዝነስና ኢኮኖሚ ግኑኝነታቸውን ለማጠናከር ዓላማው ያደረገ ጽህፈት ቤት በአዲስ አበባ ለመክፈት መወሰኑን ገልጸዋል።

የጃፓን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ውጤታማ የሚያደርጉ ዘርፎችን ለመለየት የሚያስችል መረጃ ለመሰብሰብ መምጣታቸውን ነው ምክትል ፕሬዚዳንቱ የገለጹት።

ከዚህ በተጨማሪ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍና የዘርፎቹ አመቺ አማራጮች ላይ በጠቅላይ ሚኒስተሩና ፕሬዚዳንቱ በቂ ማብራሪያ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።

በመሆኑም በግብርና ማቀነባበር ጨርቃጨርቅና ኤሌክትሮኒክስ ኢንዱስትሪዎች የጃፓን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስና ለመወሰን የሚያስችሉ ግንዛቤ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በኢትዮጵያ ያሉ አመቺ የኢንቨስትመንት አማራጮችና መንግስት የሚያደርጋቸውን ድጋፎች በተመለከተ ለልዑካን ቡድኑ ማብራሪያ መስጠታቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በፕሬዚደንት ጽህፈት ቤቱ የፕሮቶኮልና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ተናግረዋል።

በተለይም የጃፓን ባለሃብቶች በጨርቃጨርቅ ፣በምግብና መጠጦች እንዲሁም በሌሎች ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ቢሰማሩ አዋጭ ዘርፎች መሆናቸውን ለልዑካኑ ገልጸውላቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ካለው ሰፊ የገበያና ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ አንፃር መዋዕለንዋያቸውን ቢያፈሱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በፕሬዚዳንቱ ገለጻ ተደርጎላቸዋል ያሉት ዳይሬክተሩ ባለሃብቶቹም በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት አሳይተዋል ብለዋል።

የልዐካኑ በአገራቸው ሌሎች ባለሀብቶችን ለመሳብ እንደሚሰሩ ለፕሬዚዳንቱ ቃል መግባታቸንም አቶ አሸብር ተናግረዋል።

የልዑካን ቡዱኑ ከ20 በላይ የሚሆኑ አባላት በጃፓን ስመ ጥር ከሆኑ ትላልቅ ኩባንያዎች የተወከሉ መሆናቸው ጠቁመው፤ በአንድ ጊዜ በብዛት ወደ አገራችን ሲመጡ “የመጀመርያ ነው” ብለዋል።

ከኢትዮጵያን ባለሃብቶች ጋራ በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ማሳየታቸውን ጠቁመዋል። 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2009 ከተሞችን ከሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ ለመጠበቅ የሚየስችል ለአደጋ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

በዘጠኙ ክልሎች ዋና ዋና ከተሞችና በድሬዳዋ አስተዳደር ላይ የተካሔደው የከተሞችን ደህንነትና ለአደጋ የመጋለጥ ሁኔታ የሚያሳይ ጥናት ዛሬ ይፋ ሆኗል ።

ናቱ በአገሪቷ የሚገኙ ከተሞች በፍጥነት እያደጉ መሆናቸውን ጠቁሞ፤ ቀድመው አደጋን ለመከላከል ለአደጋ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ ተግባራት ማከናወንና የተቀናጀ የመረጃ አያያዝ ስልት መጠቀም እንዳለባቸው አመላክቷል።

በከተሞች በፍጥነት እያደገ ያለውን የሰው ኃይል ፍልሰትን፣ የውሃ እጥረትንና ጎርፍን መቆጣጠር የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ አደጋዎቹን አስቀድሞ ለመከላከል መተግበር ያለባቸው ቁልፍ ጉዳዮች በማለት ካስቀመጣቸው የመፍትሄ ሀሳቦች መካከል ይገኙበታል።

የመሬት መንቀጥቀጥን ለመቋቋም የግንባታ ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋትና በየዘርፍ መስሪያ ቤቱ አደጋን የሚመለከት ቡድን ማቋቋምም ሌላው ችግሩን ለመከላከል እንደ መፍትሄ የተቀመጡ ናቸው።

በአለም ባንክ የከተማ ልማት ባለሙያና የጥናቱ አስተባባሪ አቶ አበባው አያሌው እንደገለጹት፤ ከተሞች ለአደጋ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ አካልን ሊያቋቁሙ ይገባል።

የሚቋቋመው አካልም አደጋ ሲደርስ እርዳታ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከመድረሱ በፊት መረጃ በመሰብሰብ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የሚሰራ መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የከተማና ቤቶች ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ከተሞቹን ምቹና ከአደጋ የፀዱ ለማድረግ ቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች ማካሔድ እንደሚያስፈልግም አመልክቷል ፡፡

ሚኒስትሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን ፤ የአገሪቷ ከተሞች ከኢኮኖሚው ጋር በፍጥነት እያደጉ ቢሆንም "የሰው ሰራሽና ተፈጥራዊ አደጋ እንዳይገጥማቸው ካሁኑ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል" ብለዋል።

መንግስት በፍጥነት የሚያድገውን ኢኮኖሚ ለማስቀጠልና ከዚሁ ጎን ለጎን አደጋን በቅድሚያ ለመከላል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ከተሞችም አደጋን ለመከላከል ለሚደረግ ዝግጅት በጀት ሊመድቡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ሁሉም የክልሎች ከተሞች ለእሳት አደጋ፣ ለጎርፍ፣ ለመኖሪያ ቤትና ለመጠጥ ውሃ እጥረት የመጋለጥ እድል ሊኖራቸው እንደሚችል ጥናቱ ይገልፃል።

የጥናቱ ተሳታፊና የከተማና አደጋ ባለሙያ ወይዘሮ አስሚታ ቲዋሪ በበኩላቸው መንግስትና የከተማ አስተዳደሮች አደጋን ቀድመው ለመከላከል የተቀመጡትን የመፍትሄ ሀሳቦች ሊተገብሩ ይገባል ብለዋል።

ጥናቱ ሚኒስቴሩና የአለም ባንክ  በጋራ ያካሔዱት ሲሆን፤ የሁለት ዓመት ጊዜ መውሰዱም ተገልጿል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥናቱ ቀድሞ የተደረገ መሆኑ ታውቋል።

በ2004 ዓ.ም በተደረገ ጥናት በከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 15 ሚሊዮን አካባቢ ሲሆን፤ በ2026 ዓ.ም 42 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ።

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2009 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር ለመደራደር ያቀረቧቸውን አጀንዳዎች በጋራ ተወያይተው ማጽደቅ ጀመሩ፡፡

አጀንዳዎቹ ከ17ቱም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሰበሰቡ ሲሆን፤ በሚያዚያ 11 ውይይታቸው አጀንዳዎችን ሰብስበው እንዲያዘጋጁ በመረጧቸው ኮሚቴዎች አማካኝነት ቀርበዋል፡፡

የኮሚቴው አባል አቶ ገብሩ በርሄ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፤ የተሰበሰቡት አጀንዳዎች ካላቸው የይዘት ተመሳሳይነት አኳያ በ13 አብይ ክፍል ተደራጅተው የቀረቡ ናቸው። ሁሉም ሃሳቦች ሶስትና ከዚያ በላይ በሆኑ ፓርቲዎች ለመደራደሪያነት የተጠየቁ ናቸው፡፡

በዛሬው የውይይት የምርጫ ህግና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከተው አብይ ክፍልን የቀጣይ መደራደሪያ አጀንዳ እንዲሆን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አጽድቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ( ኢህአዴግ) በአንድ ፓርቲ ብቻ የተነሱ አጀንዳዎችን በሚመለከትም  እንደገለጸው፤ የጋራ የድርድር መድረክ እንደተጠናቀቀ ሃሳቡን ካቀረቡ ፓርቲዎች ጋር የሁለትዮሽ ድርድር ለማካሄድ ፈቃደኛ ነው።

የዛሬውን የውይይት መድረክ የውጭ እና የሃገር ውስጥ ታዛቢዎች እንዲሁም ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የመጡ ጋዜጠኞች በስፍራው ተገኝተው ተከታትለውታል።

ፓርቲዎቹ ሌሎች ቀሪ የመደራደሪያ አጀንዳዎችን ተወያይተው ለማጽደቅ ለሰኔ 12 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ይዘዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ጎባ ሰኔ 7/2009 የመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከአንድ ኢትዮዽያዊ ምሁር ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የማጣቀሻ መጻሐፍት በድጋፍ አገኘ።

ዩኒቨርሲቲው 750 የማጣቃሻ መጻህፍቱን በድጋፍ ያገኘው በተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ  ዛይድ ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግ ትምህርት ክፍል መምህር ከሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አብዮት ምንዳዬ  ነው።

መጸሐፍቱ ለአካውንቲንግ፣ ማርኬቲንግና ቢዝነስ የትምህርት ዘርፎች ለማጣቀሻነት የሚያገለግሉ ናቸው።

የመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሐብታሙ ተካ እንደገለፁት ምሁሩ ለዩኒቨርሲቲው ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለሌሎች በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው ።

"መፃህፍቱ ዩኒቨርሲቲው  የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት እያደረገ ያለውን ጥረት ያግዛሉ " ብለዋል ።

የተቋሙ ተማሪዎች በትምህርት መስኮቹ ዕውቀታቸውን እንዲያሰፉ አስተዋኦ ያላቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል ።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አብዱልአዚዝ ዳውድ በበኩላቸው በድጋፍ የተገኙት የማጣቀሻ መፃህፍት ዩኒቨርሲቲው በግዥ ሊያወጣ የሚችለውን ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ አስቀርቷል "ብለዋል ።

በተለይ መፃህፍቱ የቅርብ ጊዜ እትም መሆናቸው ተማሪዎች ውጤታማ የምርምር ስራ ለማከናወን እንደሚያስችላቸው አቶ አብዱልአዚዝ ተናግረዋል ።

ድጋፉን ያደረጉት ረዳት ፕሮፌሰር አብዮት ምንዳዬ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች የማጣቀሻ መፃሐፍቱ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ላደረጉት ትብብር አመስግነዋል።

በቀጣይም በውጭ ሀገር የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም በቴክኖሎጂ ሽግግርና በትምህርት ጥራት መረጋገጥ ላይ ከመንግስትና ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ረዳት ፕሮፌሰሩ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የምስክር ወረቀትና የእውቅና ሽልማት ከዩኒቨርሲቲው ተበርክቶላቸዋል ።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2009 በአገሪቷ በተለያዩ ተቋማት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንቅፋት የሚሆኑ የአሰራር ክፍተቶች መስተካከል እንዳለባቸው የሴት አደረጃጀቶች ተናገሩ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ የፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተጠሪ ተቋማት ሥር ካሉ 14 የሴት አደረጃጀቶች ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ ላይ የየተቋማቱ የሴት አደረጃጀቶች እንደተናገሩት፤ የሴቶችን የአመራር ሰጪነት ሚና ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት የሚያስተጓጉሉ የአሰራር ክፍተቶች ይታያሉ።

እነዚህን ክፍተቶች ለማስተካከልና ችግሮችን ለማቃለል በቅንጀት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ነው የተመለከተው። 

''የተደራጀ መረጃ አለመያዝ፣ ከፍትህ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር በሥራችን ላይ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው'' የሚል ተመሳሳይ ሀሳብ ነው ከሴት አደረጃጀቶቹ የቀረበው።   

የዘርፉን ጉዳይ የሚያስፈጽም በጀትና የሰው ኃይል እጥረት መኖር የሥርዓተ - ጾታ ዳይሬክቶሬት አለመቋቋም አሰራር ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር መሆኑም  ነው የተገለጸው።

የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን በተመለከተ በአስፈጻሚ አካላት ዘንድ የሚፈለገው አመለካከት አለመኖርም ሌላው ችግር መሆኑ ተወስቷል።

ቋሚ ኮሚቴው በሴቶቹ የተነሱትን ችግሮች በመጋራት ችግሩን ለማቃለል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት የድርሻውን እንደሚወጣ  ገልጿል።

የቁሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት እንደገለጹት፤ በተቋማቱ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን ማስቀጠል ይገባል።

ተቋማቱ ለሴት ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ከመስጠት ባለፈ በተጨባጭ ወደ አመራር ሰጪነት እንዲመጡ ትኩረት ሰጥተው  መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

Published in ፖለቲካ
Wednesday, 14 June 2017 21:54

'የእናት ሆድ ዥንጉርጉር'

ጠዋት በግምት አንድ ሰዓት አካባቢ በኦሮማያ ብሄራዊ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን ዋና ከተማ ሻሸመኔ ላይ ተገኝተናል። የሰኔዋ ጀንበር ያለስስት የማለዳ ሙቀቷን ለሻሸመኔዎች ብቻ የምትለግስ እስክትመስል ድረስ ፍንትው ብላለች። ነፋሻማው የሻሸመኔ የአየር ጸባይ በማለዳዋ ፀሃይ ታጅቦ አካባቢው "አትልቀቁኝ አትልቀቁኝ" ይላል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ  በደቡብ ብሔሮች  ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ያስገነባቸውን ሁለገብ የግብርና ግብዓት አቅራቢ ማዕከሎችን ሥራ ማስጀመሩን አስመልክቶ ለመዘገብ የተገኘነው ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጣን ጋዜጠኞች በከተማዋ የተገኘነው ማምሻውን ነበር።

ወደ ጉዳያችን ከመሄዳችን በፊት ቁርሳችንን እየበላን አንድ ነገር ትዝ አለኝ፤ ራስ ተፈሪያን (ጃማይካዊያን) ሻሸመኔ እንደሚኖሩ በወሬ ደረጃ ነው የማውቀው። ስለዚህ በዚህ አጋጣሚ ያሉበትን ቦታ 'በአካል ማየት አለብኝ' ብዬ አሰብኩና የሆቴሉን ጥበቃ አናገርኩት "እራስ ተፈሪያን የት ነው የሚኖሩት?" ስል ላቀረብኩለት ጥያቄ በቅርብ ርቀት እየጠቆመ "ያ የእነርሱ ሰፈር ነው" አለኝ።

በአካል ሄጄ የአኗኗር ዘይቤአቸውን ስለማየት እያሰብኩ ለሹፌራችን "ጋዜጠኞቹን ቶሎ ይዘህ ና" የሚል መልዕክት ደረሰው። ሻሸመኔ ደርሼ ጃማይካዊያንን ሳላያቸው መንገዴን ብጀምርም የማየው፣ የምገረምበት፣ የምደነቅበት፣ የምኮራበት ነገር አላጣሁም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ነኛ።

"እንኳን ደህና መጣችሁ" ብላ ተቀብላ፣ ያሳደረችንን ሻሸመኔን ተሰናብተን ሁለገብ ማዕከሉ ስራ ወደሚጀምርበት ሃላባ ልዩ ወረዳ ጉዟችንን ስንጀምር ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት ይሆናል።

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሏ ሃላባ ከሻሸመኔ ከተማ በሃምሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ሻሸመኔን ለቀን አንድ ኪሎ ሜትር እንኳ ሳንጓዝ ከፊት ለፊታችን ስፋቱ ከዓይን እይታ ውጭ የሆነ አረንጓዴ ነገር ይታየን ጀመር።

አረንጓዴው ውስጥ አልፎ አልፎ መሃል ላይ  ጉች ጉች ያለ ነገር ይስተዋልበታል። ከአጠገቤ የተቀመጠው ጓደኛዬን "ደስ ሲል እባክህ! አረንጓዴ ማሳ" አልኩት።

"አዎ! በዚህ ወቅት ወደ ደቡብ ክልል ስታቀና የተለመደ ነገር ነው" አለኝ። "ይሄ ደቡብ ነው እንዴ አልኩ ?"

" አይ ይኼስ ኦሮሚያ ክልል ነው" ሲል መለሰልኝ። እየተጠጋን ስንሄድ አይኖቼ ግራ ቀኝ አካባቢውን ማማተር ጀመሩ።

በጣም እየተጠጋን ስንሄድ “እንዴ! ጤፍ ነው እንዴ አንተ?” አልኩት፤ ኤሊያስ ይባላል ከአጠገቤ የተቀመጠው ጓደኛዬ “ኧረ! ነው አንተ!” አለኝ። ይታጨዳል፣ ይከመራልለመታጨድ የደረሰም አለ።

“መቸ ቢዘራ ነው እባክህ! ‘የናት ሆድ ዥንጉርጉር’ ይላል የአገሬ ሰው” አልኩኝ በልቤ። እዚሁ ኦሮሚያ ክልል ወዲያ በድርቅ መጎዳት ወዲህ ጤፍ አጨዳ፣ አርሶ አደሮች እያጨዱ እና እየከመሩ ግራ ቀኝ እየተመለከትን ተሽከርካሪያችን እየከነፈች ነው።

ከሩቅ ስናየው አረንጓዴ ሆኖ ሲታይ የነበረው የጤፍ ሰብል መሃል ለመሃል ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ከተጓዝን በኋላ  ሹፌራችንን “ከጤፉ ከገባን ጀምሮ ምንያህል ኪሎ ሚትር  ተጓዝን? ያለንበትስ አሁንም ኦሮሚያ ነው?" ስል ጠየኩት። 

“ሃያ ኪሎ ሜትር አካባቢ ተጉዘናል፤ አሁንም ኦሮሚያ ነው ያለነው አለኝ” ገና የጤፉን ማሳ አልጨረስንም።

“ ኤጭ! ይኼ ድርቅ የሚባለው ክስተት ሰው በሆነና ያለ ርህራሄ በክልሉ ቦረና እና ጉጅ ዞኖች እንዲሁም በባሌና አካባቢው ተማሪዎችን ከትምህርታቸው እንዲያቋርጡ ሲያስገድድ፣ እንስሳት እንዲሞቱ ያደረገበትን ሴራውን ለመበቀል ከዚህ ጤፍ መሃል አስቀመጦ ነበር ‘እንቁልልጭ’ ማሰኘት” አልኩኝ ለራሴው።

“የታባቱ፤ ድርቅ ለጊዜው ይታገላል፣ ያጉላላል እንጂ በትብብር ከተሠራ መሸነፉ አይቀርም” አልኩኝ መልሼ፤ አንዳንዴ በምናቤ እስለዋለሁ። ከሳምንት በፊት የበልግ ወቅት ሰብል ሽፋንን አስመልክቶ ከእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር መረጃ ስጠይቅ የተሰጠኝ መረጃ ‘በብዛት በበልግ ሰብል የመሸፈን እድል ያለው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ነው’ የሚል ነበር።

አንድ የታዘብኩት ነገር ደግሞ የጤፍ ሰብሉ አምሮና ተውቦ በሚታይበት እርሻ መሀል አልፎ አልፎ ቦዘኔ ወይም በሰብል ያልተሸፈኑ ቦታዎች ይታያሉ፤ ለምን? ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል። አጠገቡ ያለው ቦታ በዓመት ሁለት ጊዜ እያመረተ ለምን እራቁቱን ሰማይን አንጋጦ እንዲመለከት ይፈቀድለታል? ምንስ በወጣው ነው ጎረቤቱ በጤፍ ሰብል ታጅቦ እርሱ እራቁቱን ብርድና እና ፀሀይ የሚፈራረቅበት ወይስ የመሬቱ ባለቤቶች ጤፍ ስለማይወዱ ነው?

ይህንን በዚህ ወቅት ህልም በሚመስል መልኩ የጤፍ ምርትን እንካችሁ እያለ የሚያስደስት የድርቅ ጠላት የሆነውን አካባቢ ማልማትና መንከባከብ ያስፈልጋል።

Published in መጣጥፍ

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2009 የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የጃፓኑ ቶሞኒየስ ኩባንያ የቦሌ ለሚ ሁለት ኢንዱስትሪ ዞንን  ለማልማትና ለማስተዳደር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የፈረሙት በኮሚሽኑ በኩል ኮሚሽነር ፍጹም አረጋ ሲሆኑ፤ በኩባንያው ደግሞ ዳይሬክተሩ ሂሮሺ ኦትሱባ ናቸው፡፡

ኮሚሽነር ፍጹም በስምምነቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ በ31 ሄክታር ላይ ለሚገነባው የቦሌ ለሚ ሁለት ኢንዱስትሪ ዞን  የሚሆን መሬት እየተዘጋጀ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦቱም እየተዘረጋ ነው።

የጃፓኑ ቶሞኒየስ ኩባንያ ዳይሬክተር ሂሮሺ ኦትሱቦ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ባሉት የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችና ምቹ ሁኔታዎች ተስበው እንደመጡ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኘው አምራች የሰው ኃይል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል መኖር መዋዕለ ንዋያቸውን አውጥተው በልማት ለመሳተፍ እንደገፋፋቸው ገልጸዋል። 

በአብዛኛው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ይሳተፉበታል ተብሎ በሚጠበቀው ልዩ ዞን "ከሃያ እስከ ሠላሳ የሚሆኑ ፋብሪካዎችን ለማካተት ታስቧልም" ብለዋል።

ኩባንያቸው በካምቦዲያ ውስጥ ያሉትን በዓለም ግዙፍ የሆኑ ድርጅቶች ያቀፈውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማትና አስተዳደር ልምድ በመቀመር የተሻለ ተሞክሮ እንደሚያመጣም ጠቁመዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ድሬዳዋ ሰኔ 7/2009 ህፃናት መልካም ስብዕና ተላብሰው እንዲያድጉና ሀገር ገንቢ ዜጋ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር አስታወቀ።

በከተማ አስተዳደሩ ላለፉት ሁለት ቀናት የተካሄደ ስድሰተኛው የህፃናት ፓርላማ ጉባኤ ትላንት ተጠናቋል ።

የአስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አብዱልሰላም መሐመድ በወቅቱ እንደገለፁት መንግስት በአለም አቀፍ ደረጃ የወጡት የህጻናት መብቶችን የሀገሪቱ የህግ አካል በማድረግና በመተግበር ህጻናት መልካም ስብዕና ተላብሰው እንዲያድጉ እየሠራ ይገኛል።

በከተማ አስተዳደሩም ተመሳሳይ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የገለፁት አፈ ጉባኤው በተለይ ህጻናት በህገ-መንግስቱ የተረጋገጠላቸው ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው  እንዲከበሩ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

"አስተዳደሩ ከባለድረሻ አካላት ጋር በመሆን በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት በወጡበት አካባቢና ማህበረሰብ ባህል፤ ወግና ሃይማኖት ውስጥ እንዲያድጉ የድጋፍና እገዛ ስራዎች እያከናወነ ነው "ብለዋል ።

በመጠናቀቅ ላይ ባለው በጀት አመት ለችግር ለተጋለጡ 1ሺህ ህፃናት  የምግብ፣ የአልባሳትና የትምህርት መረጃ ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

የአስተዳደሩ የህጻናት ሞዴል ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ተማሪ ሩት ታከለ በበኩሏ ''መንግስት ስለመብቶቻችንና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከልጅነታችን ጀምሮ  አውቀን እንድናድግ ማድረጉ ቀጣዩን ሀገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ እንድንወጣ ያግዘናል'' ብላለች፡፡

በየትምህርት ቤቶች በተቋቋሙ ሚኒ ሚዲያዎች በመጠቀምም  ህጻናት በሥነ-ምግባር እንዲታነፁ፣ ስለመብቶቻቸው እንዲረዱና ኩረጃን እንዲጠየፉ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሰራ በመጭው ዓመት በተጠናከረ መልኩ እንደሚሰራ ህፃን አፈ ጉባኤዋ አመላክታለች ።

በከተማ አስተዳደሩ የ01 ቀበሌ ሞዴል ህጻናት ፓርላማ ፕሬዝዳንት ተማሪ ሃይዶር ከድር በሰጠው አሰተያየት በየቀበሌው የህፃናት ፓርላማ መቋቋሙ የህፃናት መብቶች እንዲከበሩ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ማስቻሉን ተናግሯል ።

እንደ ተማሪ ሀይደር ገለፃ የፍትህ አካላት በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በመከላልና አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ይበልጥ መስራት  አለባቸው ።

በአስተዳደሩ ከገጠርና ከተማ ቀበሌዎች የተውጣጡ 3ሺህ የህፃናት ፓርላማ አባላት መኖራቸው ታውቋል ።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2009 በአገሪቷ በፍጥነት እየተስፋፋና በበቆሎ ምርት ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለውን 'የአሜሪካ መጤ ተምች' ለመከላከል ህዝባዊ ንቅናቄ ማድረግ እንደሚገባ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አሳሰበ።  

ሚኒስቴሩ ተምቹን ለመከላከል በተከናወኑ ስራዎችና በቀጣይ መካሔድ በሚገባቸው እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። 

ተምቹ ከመካከለኛው አሜሪካ የተነሳ ሲሆን፤ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ አውሮፓውያን ዘመን ቀመር በ2016 በናይጄሪያ ታይቷል።

በኢትዮጵያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሶስት ወር በፊት በደቡብ ክልል ተከስቷል።   

ተምቹ ከ100 በላይ እጽዋትን የሚያጠቃ፣ ሰብሎችን ከቡቃያ እስከ ፍሬ ድረስ የሚበላና በከፍተኛ ደረጃ የመዛመት ባህሪም ያለው ነው።

በአሁኑ ወቅት ከደቡብ ክልል በመነሳት ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ጋምቤላና ቤንሻንጉል ክልሎች በመዛመት በቆሎ አምራች አካባቢዎች ላይ ጥቃት እያደረሰ ነው። 

የሚኒስቴሩ ህዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ እንደገለጹት፤ ተምቹን ለመከላከል ከዝግጅት ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ማግኘት አልተቻለም። 

ወጣት አደረጃጀቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመከለከያና ፖሊስ አባላትና ኀብረተሰቡ ከአርሶ አደሩ ጋር በመተባበር ተምቹን  የመግደል፣ የማቃጠልና የመቅበር ስራን በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

''ጸረ ተባይ ኬሚካል ከመጠቀም ይልቅ በባህላዊ መንገድ የመከላከል ዘዴ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል'' ያሉት አቶ ዓለማየሁ፤ ተምቹን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድም ባህላዊ ዘዴን መጠቀምም ወሳኝ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ተምቹ በአገሪቷ በ35 ዞኖች፣ 235 ወረዳዎችና 2 ሺ 900 በላይ ቀበሌዎች መታየቱን የተናገሩት ደግሞ በሚኒስቴሩ የእጽዋት ጤናና ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ወልደሐዋርያት አሰፋ ናቸው። 

ተምቹ በዋናነት በበቆሎ ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁንም በ146 ሺ 320 ሄክታር መሬት ላይ መታየቱን አብራርተዋል። 

ተምቹን ለመከላከል ለክልሎች ባለሙያዎች ስልጠና መሰጡንና ከ100 ሺ ሊትር በላይ ጸረ ተባይ ኬሚካል ለክልሎች መሰራጨቱንም ተናግረዋል።

''አዲሱ ተምች ልክ እንደመደበኛው ተምች በዝናብ ይጠፋል የሚል አመለካከት በአርሶ አደሩ ዘንድ ሊኖር አይገባም'' ያሉት ደግሞ በሚኒስቴሩ የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዮስ ሰላቶ ናቸው።  

ተምቹ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ አርሶ አደሮች ሳይዘናጉ የመከላከል ስራውን እንዲያከናውኑም ጥሪ አቅርበዋል። 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2009 በአገሪቷ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የምርት ጥራትና ደረጃ ጽንሰ ሐሳብ እንዲካተት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲው ይህንን የገለፀው የቀጣይ ዓመት የስራ እቅዱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሳይንስ፣ መገናኛና ቴክኖሊጂ ጉዳች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው።

የኤጀንሲው ዋና ዳሬክተር አቶ እንዳለው መኮንን እንደገለጹት፤ ኤጀንሲው ከመዋለ ሕፃናት አንስቶ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ባሉት የስርአተ ትምህርት የምርት ጥራት ጽንሰ ሐሳብ እንዲካተት እየሰራ ነው።

የምርት ጥራት ጉዳይ በሁሉም ሕብረተሰብ ዘንድ እንደ ባሕል ሊለመድ የሚገባ ጉዳይ ሲሆን፤ ለዚሁ ስኬትም "ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር  በትብብር እየሰራን ነው" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ከምርቶች ጋር ባዕድ ነገሮች ተጨምረው የሚስተዋለው "ስለ ጥራት ያለው ግንዛቤ የተሳሳተና አናሳ በመሆኑ ነው" ብለዋል።

በወተት ፣ በውኃ፣ በቅቤ፣ በሽሮና በመሰል ምርቶች ላይ አለ አግባብ የሚደባለቁት ባዕድ እንዳይቀላቀሉ ለማድረግ ሕብረተሰቡን በጥራትና ደረጃ  ጽንሰ ሀሳብ ላይ ያለውን ግንዛቤ ማስፋት ተገቢ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡

ኤጀንሲው ከ10 ሺ በላይ ደረጃዎችን ተገቢነት ላላቸው ምርቶች የሰጠ ሲሆን፤ እነዚህ ደረጃዎች እያሉም "የምርት ጥራትና ጉድለት ይስተዋላል" ብለዋል።

"ምርቶችን በኃላፊነት ማምረትና መጠቀም እንዲቻል ትምህርት ወሳኝነት አለው" ነው ያሉት ዳሬክተሩ።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን