Items filtered by date: Tuesday, 13 June 2017

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2009 በኔዘርላንድስ ሄንግሎ በተካሄደው የሠዓት ማሟያ ውድድር እስከ አራተኛ ደረጃ የያዙ አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮና ውድድር ለመሳተፍ ከነገ በስቲያ ልምምድ ይጀምራሉ።

የኢትዮጵያ አትሌቲከስ ፌደሬሽን የሄንግሎ የሠዓት ማሟያ፣ የዓለም አቀፍ፣ የአህጉርና አገር አቀፍ ውድድሮች ላይ እየተደረገ ባለው ዝግጅት ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።

የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገብረእግዚአብሄር ገብረማሪያም እንደገለፀው በዓለም ሻምፒዮና ውድድር የሚሳተፉ አትሌቶች  ከመጪው ሐሙስ ጀምሮ ሆቴል በመግባት ልምምዳቸውን ይጀምራሉ።

በማራቶን ውድድር አገሪቱን ወክለው በዓለም ሻምፒዮና የሚካፈሉ አትሌች ተመርጠው ስልጠና እየተሰጣቸው ነው።

ከነገ በስቲያ ደግሞ በሄንግሎ የሠዓት ማሟያ ውድድር የሶስት ሺህ መሰናክልን ጨምሮ ከስምንት መቶ እስከ 10 ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድር ተሳትፈው እስከ አራተኛ የወጡ አትሌቶች ሆቴል ይገባሉ ብሏል።

የፌዴሬሽኑ የስፖርት ማልማትና ማስፋፋት ዓብይ የስራ ሂደት መሪ አቶ ዱቤ ጅሎ በበኩላቸው በሄንግሎ የተካሄደው የሠዓት ማሟያ ውድድር ስኬታማ እንደነበር ገልፀዋል።

በሠዓት ማሟያ ውድድሩ ከተሳተፉት 55 አትሌቶች መካከል 35ቱ ሚኒማውን ማሟላት እንደቻሉም ተናግረዋል።

በውድድሩ ሚኒማውን ያሟሉት አትሌቶች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን በሠዓት ደረጃም ፈጣን የሚባሉ ውጤቶች የተመዘገቡበት በመሆኑ ውድድሩን ስኬታማ ያስብለዋል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ሄንግሎ ላይ በነበረው የሠዓት ማሟያ ውድድር በ800 ሜትር ከተወዳደሩት ወንድ አትሌቶች መካከል አንድም አትሌት ሚኒማውን ማሟላት አልቻለም።

አትሌቶቹ በቀጣይ ውድድሮች ሚኒማውን ሊያሟሉ ስለሚችሉ ካሟሉት አትሌቶች ጋር ሆቴል ገብተው ስልጠና የሚያገኙ ይሆናል ተብሏል።

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2009 ወጣቶች በክረምት ወራት በሚካሄደው የደም ልገሳና የንቅናቄ መርሃ-ግብር በመሳተፍ የሕይወት ማዳን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ብሔራዊ የደም ባንክ ጥሪ አቀረበ።

የዓለም ደም ለጋሾች ቀን “ምን ማድረግ ይፈልጋሉ? ደም መለገስ! አሁን ይጀምሩ! መደበኛ ደም ለጋሽ ይሁኑ!” በሚል መሪ ሃሳብ ከሰኔ 7 እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2009 ዓ.ም ይከበራል።

ለሶስት ወራት በሚቆየው የበዓሉ አከባበር ሕብረተሰቡ ደም እንዲለግስ የንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች ይከናወናሉ።

ከነገ ጀምሮም "በድንገተኛ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ደም በመለገስ ሕይወት እንታደግ" በሚል መሪ ሃሳብ የእግር ጉዞና ለደም ለጋሾችና ባለድርሻ አካላት የሚዘጋጅ የምስጋና መርሃ ግብር ይካሄዳል።

የባንኩ የደም ለጋሾች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ዘለቀ የዓለም ደም ለጋሾችን ቀን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ከሚሰበሰበው ደም ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ከሁለተኛ ደረጃና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሚለገስ ነው።

በተለይም በክረምት ወራት ከትምህርት ተቋማት ወደየአካባቢያቸው የሚመለሱ ወጣቶች ደም ለጋሽ እንዲሆኑ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና ከወጣት አደረጃጀቶች ጋር የክረምት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ እየተሰራ ነው።

በክረምት ወራት የደም እጥረት ያጋጥም እንደነበረ አስታውሰው ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ልገሳው በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስር በመካተቱ እጥረቱ መቀነሱን ገልፀዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ ሕብረተሰቡ በልገሳው ላይ ያለው ግንዛቤ እንዲጎለብት በማድረጋቸውም ችግሩ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንዲቃለል ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።

በትምህርት ቤቶች የተጀመረው የደም ልገሳ ተግባር አበረታች ውጤት እያመጣ ያለና መጠናከር የሚገባው መሆኑንም አመልክተዋል።

ባለፈው ዓመት ብዙ ዩኒት ደም የተሰበሰበው በክረምት እንደነበረ ገልፀው ወጣቶች ከነገ ጀምሮ ለሶስት ወራት በሚቆየው የልገሳና የንቅናቄ መርሃ ግብር በመሳተፍ ሕይወት የማዳን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

"የሰው ልጅ ያለውን ገንዘብም ሆነ ንብረት ቢሰጥ ህይወት መታደግ አይችልም የደም ጠብታ ግን የወገን ህይወት ይታደጋልና ሁሉም ሰው ደም በመለገስ ሕይወት ይታደግ" ያሉት ደግሞ የበጎ ፍቃድ አምባሳደሩ አርቲስት ውብሸት ወርቃለማሁ ናቸው።

ከ70 ጊዜ በላይ ደም የለገሱ ዜጎች መኖራቸውን ጠቅሰው ወጣቱ ትውልድ የእነዚህን በጎ ፈቃደኛ ለጋሾች ዓርአያነት ተከትሎ ሕይወት በማዳን ተግባር እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።

ለ78 ጊዜ ደም የለገሱት አቶ ሰለሞን በየነ በበኩላቸው "የዓለም ደም ለጋሾች ቀን ሰዎች ከእኛ ጋር እንዲኖሩ የፈቀድንበትና ያገዝንበት ቀን በመሆኑ እንደ ልደት ቀናችን የምንቆጥረው የደስታ ቀናችን ነው" ብለዋል።

ባለፋት 11 ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ 160 ሺህ ዩኒት ደም የተሰበሰበ ሲሆን ይህም የዕቅዱ 87 በመቶ እንደሆነ ነው የተገለፀው።

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2009 የማህፀን በር ካንሰርን ለመከላከል የቅድመ ካንሰር ምርመራ ሊዘወተር እንደሚገባ ተገለጸ።

ወጣቶች የሱስ ተገዥ እንዲሆኑ የሚገፋፉ መጤ ጎጂ ባህሎች መበራከታቸውም ተነግሯል።

የአዲስ አበባ አስተዳደር የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ በማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራና የሕክምና አገልግሎት ዙሪያ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ ሴቶች ጋር ተወያይቷል።

በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ ክፍል ባለሙያ ሲስተር ጽጌ ተከስተ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በሽታው በሴቶች ላይ እስከሞት የሚያደርስ ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ ትኩረት ያሻዋል።

በኢትዮጵያ በሽታው በየዓመቱ ስድስት ሺህ የሚሆኑ ሴቶችን ህይወት እንደሚቀጥፍ የተናገሩት ሲስተር ጽጌ የቅድመ ካንሰር ምርመራና ህክምና አገልግሎቱን በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል በነጻ ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በለጋ ዕድሜ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መጀመርና ከበርካታ ወንዶች ጋር ግንኙነት መፈፀም ለበሽታው ተጋላጭ እንደሚያደርግ ባለሙያዋ ተናግረዋል። በቤተሰብ ውስጥ የማህፀን በር ካንሰር ተጠቂ ካለ ሊተላለፍ ይችላልም ብለዋል።

ሲስተር ጽጌ፤ በኢትዮጵያ ሴቶች ለጤና ተቋማት ያላቸው ተደራሽነትና የአገልግሎት ተጠቃሚነት ዝቅተኛነት ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው ቅድመ ካንሰር ምርመራ በማዘውተርና ክትባት በመውሰድ በሽታውን መከላከል እንደሚቻል ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሴቶች የማህጸን በር ካንሰር ተጠቂ ሲሆኑ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በሽታው ሂዩማን ፓፒሎማ በተሰኘው ቫይረስ አማካይነት በሚከሰተው የረጅም ጊዜ ኢንፌክሽን የሚፈጠር መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ የሚመክሩ መድረኮች ጠቃሚ በመሆናቸው ቀጣይነት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

በሌላ በኩል ወጣቶች የሱስ ተገዥ እንዲሆኑ የሚገፋፉ መጤ ጎጂ ባህሎች መበራከታቸው አሳሳቢ መሆኑን የስብሰባው ታዳሚዎች ጠቁመዋል።

ተወያዮቹ፤ የጭፈራ፣ የጫት፣ የሺሻና የመጠጥ ቤቶች መስፋፋት ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚይዝና በትምህርት ቤቶች የሚደረገው ቁጥጥር መላላትን አንስተዋል።

የውጭ ባህልን መሰረት ያደረገ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባና የኢንተርኔት ኢ-ሥነምግባራዊ መልዕክቶችን እንደ አባባሽ ምክንያቶች ጠቅሰዋል።

ተወያዮቹ፤ በርካታ ወጣቶች ለከፋ የጤናና የሥነ-ልቦና ቀውስ መዳረጋቸውን አንስተው ችግሩን ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ በኃላፊነት ስሜት መሥራት አለበትም ብለዋል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2009 ኢትዮጵያና ሶማሊያ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ የሕዝቦቻቸውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ገለጹ። 

የሁለቱ አገሮች ሁለንተናዊ ግንኙነት እንዲጠናከርም ለአገራቱ የጋራ ኮሚሽን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተስማምተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ከሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አብዱልቃድር መሐመድ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

አገራቱ የፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸው ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ እንደምትሰራ ወይዘሮ ሂሩት እንዳረጋገጡላቸው ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በርካታ ሶማሊያዊያን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን እየተካታተሉ ሲሆን፤ በመጪው የትምህርት ዘመንም ተጨማሪ 500 የሶማሊያ ዜጎች ዕድሉን እንዲያገኙ ከወራት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል መግባቱም ይታወሳል።

ይህም ወደ ተግባር እንዲለወጥ ሁለቱ አገሮች ከስምምነት መድረሳቸውን አቶ መለስ ገልጸዋል።

የሶማሊያ ዲፕሎማቶችም በኢትዮጵያ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙና በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የድንበር አካባቢ ንግድም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አብዱልቃድር መሐመድ እንደገለጹት፤ አዲሲቷ ሶማሊያ ለአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት አስተዋጽኦ ማድረግ ትፈልጋለች።

አንጻራዊ ሠላምና መረጋጋት በአገሪቷ እንዲሰፍንም የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ኃይል ለከፈለው መስዋዕትና ላደረገው ተጋድሎ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በአቅም ግንባታው መስክ ትብብሯን አጠናክራ እንድትቀጥልም ጠይቀዋል።

"ሶማሊያ በቀጣይ በንግድ፣ በትምህርት፣ በፖለቲካና በደኅንነት ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጋር አብራ ለመሥራት ፍላጎት አላት" ነው ያሉት።

31ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (የኢጋድ) ልዩ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ በሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሰን ዓሊ ካይሬ የተመራው ልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ አመራር አባላት ጋር በተለያዩ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ እ.አ.አ 1991 ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ለዓመታት ሠላምና መረጋጋት ርቋት የቆየችው ሶማሊያ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና በአፍሪካ ኅብረት ሠላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ጥረት አንጻራዊ ሠላምና መረጋጋት እያገኘች መምጣቷ መረጃዎች ያመለክታሉ።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2009 የአዕምሯዊ ንብረት ረቂቅ ፖሊሲው የቅጂ መብት፣ የንግድ ምልክት ፣ የፈጠራ ስራና መሰል የአዕምሮ ሃብት የፈጠራ ስራዎችን አቅጣጫ ሊሰጥ በሚችል መልኩ በዝርዝር ሊቀመጥ እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ።

በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ከዚህ ቀድሞ የተሰጡ ሃሳቦች እንደ ማሻሻያ አለመወሰዳቸውንም ነው የገለፁት።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የአዕምሯዊ ንብረት ፖሊሲና ስትራቴጂ የመጨረሻ ረቂቅ ላይ ከምሁራንና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል። 

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአዕምሯዊ መብት ስምምነት ብትፈርምም ያላትን የባለቤትነት መብት ማስጠበቅ ላይ ችግሮች መኖራቸው እንደሚስተዋል ምሁራኑ ገልፀው፤ ችግሩን ለመፍታት ግን በፖሊሲው ሊሰራ የታሰበን ጉዳይ በዝርዝር አለመካተቱን ጠቁመዋል።

ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ዶክተር ብሩክ ኃይሌ ከዚህ በፊት በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ውይይት ሲደረግ የተገኙ መሆኑን ገልፀው፤ ቀድሞ የቀረቡ ሃሳቦችና ጥያቄዎች አሁንም እየተነሱ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት።

ይህም ቀድሞ የተሰጡ ግብዓቶች ተወስደው በማሻሻያነት ጠቀሜታ ላይ አለመዋላቸውን እንደሚያሳይ ነው የገለጹት።

እንደ እርሳቸው ምልከታ ፖሊሲው አሁንም ከለላ የሚደረግባቸውን የቅጂ መብት፣ የንግድ ምልክት፣ የፈጠራና የመሳሰሉት ስራዎች ተለይተው አቅጣጫዎች አለመቀመጣቸው ግልፅ እንዳይሆን ያደርገዋል።

አእምሯዊ ንብረት ለልማቱ፣ ለሳይንስ፣ ለንግድ፣ ለባህልና ለተያያዥ ጉዳዮች የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለይቶ ከማሳየት ይልቅ መረጃ መስጠት ላይ ትኩረት ያደረገ እንደሆነም ነው የሚናገሩት።

ሌላው የመቀሌ ዩንቨርሲቲን ወክለው የተገኙት አቶ ካሰዬ ደበሱ በበኩላቸው፤ ከውጪ አገራት ጋር የቴክኖሎጂ ሽግግርና የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደሚደረግ ፖሊሲው ቢያወሳም አፈፃፀማቸው በምን መልኩ እንደሆነ ያስቀመጠው ነገር አለመኖሩን አመላክተዋል።

የባለሃብቱ፣ የምርምርና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በፖሊሲው ባለድርሻ አካላት ተደርገው ቢቀመጡም "ይደራጃል" የተባለው የዘርፉ ምክር ቤት የመንግስት አካላትን ብቻ የያዘ መሆኑንም አስረድተዋል።

ይህ ደግሞ በዘርፉ በሚደረጉ ምርምሮችና የፈጠራ ስራዎች ላይ የምሁራን ድርሻ እንዳይኖር ያደርጋል ባይ ናቸው።

ፖሊሲው ላይ ሃሳቦች በዝርዝር አለመቀመጣቸው የተለያዩ አካላት በሚመቻቸው መልኩ እንዲተገብሩት በር እንደሚከፍት እና በዓለም አቀፍ ደረጃም እንዲሁ በሚደረጉ ስምምነቶች ላይ ተግዳሮቶች ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመዋል።

ፅህፈት ቤቱ በበኩሉ የተነሱ ሃሳቦችን በአብዛኛው በመውሰድ በተወሰኑ ጥያቄዎችና ሃሳቦች ላይ ምላሽ ሰጥቷል።

በፅህፈት ቤቱ የንግድና ምልክት ጥበቃና ልማት ዳይሬክተር አቶ ኤርምያስ የማነብርሃን በበኩላቸው፤ ፖሊሲው ላይ ተደጋጋሚ ውይይት መደረጉን አምነው፤ የተሰጡ ሃሳቦች ያልተካተቱት ፖሊሲውን በማርቀቅ ስራ ላይ ተሳታፊ የነበሩ አካላት በመልቀቃቸው እንደሆነም አሳውቀዋል።

"የዛሬው ውይይትም ሃሳቦቹን መልሶ በማንሸራሸርና በማስገንዘብ ተጨማሪ ግብዓት ለመውሰድ ያለመ ነው" ብለዋል።

የተነሱ ሃሳቦችም እንደ አስፈላጊነታቸው በፖሊሲው ከመካተታቸው ባለፈ እንደ ተቋም አሰራሩን ለማሻሻል የሚያግዙና ለሚወጡ ህጎችም አጋዥ እንደሚሆኑም ተናግረዋል።

የማህበረሰብ እውቀት ልማት ቡድን መሪ አቶ ታደሰ ወርቁ በበኩላቸው፤ ፖሊሲው ከሌሎች አገሮች ተጨምቆ በረቂቅ ለውይይት የቀረበው ከተሳታፊዎች ግብዓት ለመውሰድ መሆኑን ተናግረዋል።

በፖሊሲው "ሁሉም ነገር በዝርዝር ያልተካተተው ደግሞ በማስፈፀሚያ ስልት የሚመለሱ በመሆናቸው ነው" ብለዋል።

ፖሊሲው አዕምሯዊ ንብረትን ለዘላቂ ፣ ውጤታማና ፈጣን ዕድገትና ልማት በግብዓትነት ለመጠቀም፤ ፍትሃዊ ውድድርን ለማስፈን፣ ለሃብት ፈጠራ ፤ ማኅበራዊ ፣ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን እንዲያፋጥን ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።

የውጭ ቴክኖሎጂ ሽግግርና የክምችት መጠንን የማሳደግ፤ ለአዕምሮ መብት ባለቤቶች አስተማማኝ የጥበቃ ሥርዓት መፍጠርና የዘርፉን ባለሙያዎች አቅም ማጎልበት በረቂቅ ፖሊሲው  ተካቷል።

ረቂቁን ለማዘጋጀት አመላካች መነሻዎችና የማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎችን ለመለየት ከአውስትራሊያ፣ ከቻይና፣ ከጋና፣ ከሩዋንዳ፣ ከሞዛንቢክ፣ ከህንድ፣ ከጃፓንና ከሌሎች አገሮች ልምድ መወሰዱን ሰነዱ ያትታል።

 

 

 

 

  

 

 

 

 

ድሬዳዋ ሰኔ 6/2009 ሀገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር የምታደርገው ጉዞ ለማሳካት መንግስት ለማምረቻው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ሚነስቴሩ በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዕድገት፣ ተግዳሮትና ቀጣይ የውጤት ተግባራት ላይ ከድሬዳዋ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ትናንት ተወያይቷል፡፡

ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ውጤታማነት የማምረቻው ዘርፍ የማይተካ ሚና እንዳለው ውይይቱን የመሩት  በሚኒስቴሩ  የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ  ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ ገልጸዋል፡፡

ለዘርፉ አነስተኛና ጥቃቅን በሚል ጥልቅ አካሄድ ሲሰጥ የነበረው ድጋፍ ውጤት አለማምጣቱን ተናግረው ችግሩን በመለየት ሁሉን አቀፍ ዕድገት ለማስመዝገብ መሠረት ለሚሆነው ለማምረቻው ዘርፍ መንግስት የተለየ ትኩረት ሰተጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ዘርፉ በተለይ ሀገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር የምታደርገው ጉዞ መሳካት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ተመልክቷል፡፡

ለዚህም በ2010 በጀት ዓመት ለዘላቂ ልማት የሚመደብ በጀት ሙሉ በሙሉ ለዚህ ዘርፍ ድጋፍ እንደሚውል ጠቁመዋል፡፡

ዘርፉ የምጣኔ ሃብት መዋቅራዊ ሽግግሩን ለማሳካት እንዲያስችል ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ  በ200ሺህ ዶላር ጥናት እንደሚካሂድ አቶ አስፋው ገልጸዋል፡፡ 

"በጥናቱ መሠረት ለአነስተኛና መካከለኛ ማምረቻዎች  ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ ፣ ዘላቂነትና ተመጋጋቢ ያላቸው የአምራች ኢንዱስትሪ መንደር  ይቋቋማል " ብለዋል፡፡

የሚቋቋመው  የአምራች ኢንዱስትሪ መንደር እንደየክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ በዋና ዋና ከተሞችና በወረዳ መስተዳድሮች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በጥናቱ መሰረት ተግባራዊ በማድረግም በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ  የተቀመጠውን ዘርፉ ለ758ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ነው፡፡

እንዲሁም ዘርፉ በሀገራዊ ዕድገት ላይ የነበረውን ድርሻ ከአምስት ወደ ስምንት  በመቶ ከፍ ያደርጋል፤ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርትን 25 በመቶ ይሸፍናል፤ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬም  ያስገኛል፡፡

ኤጀንሲውም ለተግባራዊነቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

በድሬዳዋም አመራሩ ለዘርፉ የሚሆን  መንደር ማዘጋጀትና  ቀደም ሲል ለዘርፉ አንቀሳቃሾች  የተገነቡ የማምረቻ ስፍራዎች ሥራ ማስጀመር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የድሬዳዋ ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው የአነስተኛና መካከለኛ የማምረቻ ዘርፉን ለድሬዳዋ ዋናው የምጣኔ ሃብት መሠረት መሆኑን ጠቅሰው ዘርፉ በአስተዳደሩ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ላይ 40 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የማምረቻ  መንደር ለማቋቋም የቦታ መረጣ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው "የዘርፉን እንቅስቃሴ የሚከታተል አብይ ኮሚቴ በማቋቋም የተቀናጀና የማያቋርጥ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል፡፡

በድሬዳዋ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታ ቢኖሩም ለዘርፉ አንቀሳቃሾች የተሟላ ድጋፍ በመስጠት በኩል የሥራና የኃላፊነት ክፍፍል ባለመኖሩ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ የተናገሩት ደግሞ  የአስተዳደሩ የንግድና ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብደላ አህመድ ናቸው፡፡                       

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃይሉ ፊጣ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ ባንኩ ከ5ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ እንደ ሀገር መመደቡን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ለድሬዳዋ የተመደበው 200 ሚሊዮን ብር ውስጥ የዘርፉ አንቅሳቃሾች የተጠቀሙት 70 ሚሊዮን ብር መሆኑን ጠቁመው ችግሩን ለመፍታት  ከአስተዳደሩ ጋር  የግንዛቤ ሥራ በስፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱም  የካቢኔ አባላት፣ በየደረጃው የሚገኙ የድርጅት አመራሮችና የጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2009 ከሚያዚያ 17 እስከ ግንቦት 30 ቀን 2009 ዓ.ም የተካሄደውን አማካይ የቀን ገቢ ግምት ውጤት እሰከ ሰኔ 15 ባሉት ቀናት ለደረጃ 'ሐ' ግብር ከፋዮች ብቻ እንደሚገለጽ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አስታወቀ።

በባለስልጣኑ የአዲስ አበባ ከተማ ደንበኞች አገልግሎትና ትምህርት ዳይሬክተር አቶ ቶሎ ፊጤ እንደገለጹት፤ ባለስልጣኑ የተሰበሰበውን  መረጃ የማጣራት ሂደት አጠናቆ ውጤቱን ይፋ ለማድረግ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

''ከደረጃ 'ሐ' ውጭ ያሉ ግብር ከፋዮች በአዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ መሰረት ገቢያቸውን በሚጠቀሙት የሂሳብ መዝገብ ማወቅ ስለሚቻል የቀን ገቢ ግምት ውጤቱ አይገለጽላቸውም'' ብለዋል።

ከቀን ገቢ ግምት ውጤት ጎን ለጎን ከደረጃ 'ሐ' ወደ ደረጃ 'ለ' ከፍ ላሉና በተለያዩ ምክንያቶች ከደረጃ 'ለ' ወደ ደረጃ 'ሐ' ዝቅ ላሉ ግብር ከፋዮች የደረጃ ለውጣቸውን የማሳወቅ ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል። 

አማካይ የቀን ገቢ ግምት ውጤቱ ይፋ ሲሆንም የደረጃ 'ሐ' ግብር ከፋዮች ከዚህ ቀደም ግብር በሚከፍሉባቸው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በመሄድ ማወቅ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ግምቱ ይፋ ከሆነ በኋላ የሚነሱ ቅሬታዎችን በሚመለከት ባለስልጣኑ ቅሬታ ተቀብሎ መፍታት ላይ ብቻ የሚሰራ የሰው ኃይል በየወረዳው ማዘጋጀቱንም አቶ ቶሎ አስታውቀዋል።

በሌላ ዜና በተከናወነው የቀን አማካይ ገቢ ጥናት በመዲናዋ ያለ ፈቃድ ሲነግዱ የተገኙ ከ8 ሺህ በላይ ድርጅቶች ከከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ ጋር በመቀናጀት ወደ ህጋዊ ስርዓት እንዲገቡ ተደርጓል።

ከሚያዚያ 17 እስከ ግንቦት 30 ቀን 2009 ዓ.ም በተካሄደው የቀን አማካይ ገቢ ጥናት የ147 ሺህ የንግድ ድርጅቶችን ገቢ መገመት ተችሏል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2009 የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ማሳደግ እንደምትፈልግ አስታወቀች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ሚስ ሪም አል ሃሺሚን አነጋግረዋል።

ሚኒስትሯ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ፣ በሰው ሃይል፣ በኢንቨስትመንትና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ጠንካራ ወዳጅነት አላት።

"የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች በአፍሪካ ያላት ፍላጎት እያደገ መጥቷል፤ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ዋነኛ አጋራችን ናት" ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሁለቱ አገሮች ቀደም ሲል በጋራ ሲሰሩ ከቆዩባቸው አጀንዳዎች በተጨማሪ መተባበር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

በተለይም በታዳሽ ኃይል ልማት፣ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ፣ በሽብርተኝነት መከላከልና ሌሎች አለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር መስራት እንደምትሻ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጋር በነበራቸው ቆይታ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ አበባና የቁም እንስሳት የምትልክ ሲሆን ነዳጅ፣ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች፣ ማሽነሪዎችና ማዳበሪያ ከአገሪቷ ታስገባለች።

የአገሪቷ 20 ኩባንያዎች ባለፉት አምስት ዓመታት በ263 ሚሊዮን ብር ካፒታል በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራታቸውን ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘ መረጃ ያሳያል።

ሚኒስትር ዴኤታ ሚስ ሪም አልሀሺሚ ከቀትር በፊት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋርም ውይይት አካሂደዋል።

 

Published in ፖለቲካ

ሽሬ እንዳስላሴ ሰኔ 6/2009 እራሱን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ብሎ የሚጠራው ቡድን ኢትዮጵያን የማተራመስ ዓላማ ያለውና የሻእቢያን ተልዕኮ የሚያስፈጽም መሆኑን በቅርቡ እጃቸውን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሰጡ የቡድኑ አባላት ገለጹ።

ከቡድኑ አባላት መካከል የጋንታ መሪ የነበረው አዘናው ንጉሴ እንደገለጸው ቡድኑ በውጭ ሃገራት ተደላድለው የሚኖሩ መሪዎችንና የሻዕቢያን ተልዕኮ ከማስፈጸም የዘለለ ዓላማ የለውም።

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን ፍላጎት አባላቱን ለጥፋት በማሰማራት የቡድኑ መሪዎች በውጭ አገር የሚመሩትን የተደላደለ ኑሮ ከማሳካት ውጭ እዚሀ ግባ የሚባል የትግል አላማም እንዳላየበት ተናግሯል።

ተስፋሁን ፋንታ የተባለ ሌላው የቡድኑ የጋንታ መሪ በበኩሉ "የቡድኑ አላማ የሻእቢያን መንግስት ኢትዮጵያን የማተራመስና የሽብር ተግባር ማስፈጸም ነው" ብሏል።

"እዚህ ግባ በማይባሉ ጥቃቅን የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች በስሜት ተገፋፍቼ ወደ አሸባሪው ቡድን  ከአራት ዓመታት በፊት የተቀላቀልኩበት ቀን ሳስበው ያንገብገበኛል" ያለው ደግሞ በረከት ካሳ የተባለው የቡድኑ አባል ነው።

በዚህ ቆይታውም ከስቃይና ከእንግልት ውጭ ያተረፈው አንድም መልካም ነገር እንደሌለም ተናግሯል።

የምዕራባዊ ትግራይ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ ኮማንደር ኃይለ ኪዳነ ማርያም እንደገለጹት ከግንቦት 27 እሰከ ሰኔ ሁለት 2009 ዓ.ም.ባሉት አምስት ቀናት የጥፋት ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ 48 ታጣቂዎች በቡድንና በተናጠል በመግባት ለኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት እጃቸውን  ሰጥተዋል።

የጥፋት ቡዱኑ ሦስት የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት የነበሩትን ዘገየ ሺበሺ፣ታድሎ አለሙና ቴዎድሮስ ሙሉጌታ የተባሉትን አመራሮች ጨምሮ 22 ታጣቂዎች በአንድ ላይ በመግባት እጃቸውን መስጠታቸውንም ተናግረዋል።

"ቀሪዎቹ ሃያ ስድት ታጣቂዎች ደግሞ በተናጠልና በቡድን በቡድን በመሆን ቀን ቀን በጫካ እየተኙ በሌሊት እየተጓዙ በሰላም እጃቸውን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰጥተዋል" ብለዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ከገቡበት ቀን ጀምሮም አስፈላጊው እንክብካቤና ወንድማዊ ፍቅር እንዳልተለያቸው ኮማንደሩ ተናግረዋል።

ባለፉት አስራ አንድ ወራት የጥፋት ቡድኑ አባላት የነበሩ 164 ታጣቂዎች የሻእቢያን የጥፋት ተልእኮ አንፈፅምም በማለት ለኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት በሰላም እጃቸውን መስጠታቸውን ከዞኑ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ፖለቲካ

ባህር ዳር ሰኔ 6/2009 ለደቡብ ጎንደር ዞን የተመደበውን 302 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብን በመጠቀም ስራ አጥ ወጣቶችን  ወደ ስራ እንዲገቡ እያደረገ  መሆኑን የደቡብ ጎንደር ዞን ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ገለጸ።

የመምሪያው ምክትል ሃላፊ አቶ ይትረፍ አየለ ለኢዜአ እንደገለጹት እስካሁን ተለይተው የተመዘገቡ ከ3 ሺህ በላይ ወጣቶችን በ635 ኢንተርፕራይዞች እንዲደራጁ ተደርጓል ።

ከተደራጁትም መካከል 311 ኢንተርፕራይዞች ያቀረቡት የስራ እቅድ ተገምግሞ  ወደ ስራ እንዲገቡ  ካለፈው ወር አጋማሽ ጀምሮ የብድር አገልግሎት እየቀረበ ይገኛል፡፡

"እስካሁን በ45 ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ 225 አንቀሳቃሽ ወጣቶች  9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ብድር ተሰጥቷቸው ወደ ስራ ገብተዋል " ብለዋል፡፡  

ቀሪው ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብም በተመሳሳይ ስራ አጥ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን ማምረቻ ፣ ግንባታ፣ ግብርና፣ አገልግሎትና ንግድ ወጣቶቹ እየተሰማሩባቸው ካሉት የስራ መስኮች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ለወጣቶች የተመደበውን ገንዘብ የማይመለከታቸው ሰዎች ሰርገው በመግባት እድላቸውን እንዳያጣብቡ መምሪያው ከአጋር ኣካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑም አቶ ይትረፍ አመልክተዋል፡፡

በደብረታቦር ከተማ የቁም እንስሳት ማድለብ ሽርክና ማህበር  ሊቀመንበር ወጣት እናናው ፀጋው በሰጠው አስተያየት ከእሱ ጋር አምስት ሆነው ከተደራጁ በኋላ የስራ አመራር ስልጠናና የመስሪያ ቦታ እንደተሰጣቸው ተናግሯል፡፡

እንደ ወጣቱ ገለፃ ባለፈው ሳምንት በተሰጣቸው 629 ሺህ ብር ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብን በመጠቀም ወደ ስራ ለመግባት የሚደልቡ እንስሳትና የመኖ ግዥ እያከናወኑ ናቸው።

ከተደራጁ በኋላ ዘግይቶም ቢሆን ባለፈው ሳምንት ገንዘቡ በመለቀቁ 450 ሺህ ብር ብድር ወስደው የከብት ማደለብ ስራ ለመጀመር እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የተናገረው ደግሞ  የእስቴ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ዘነበ ታምራት ነው።

በደቡብ ጎንደር ዞን  ባለፉት 11 ወራት በመደበኛው ፕሮግራም  የተደራጁ 59 ሺህ ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ መደረጉን  ከመምሪያ የተገኘ መረጃ ያመላክታል ።

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን