×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Monday, 12 June 2017

አዳማ ሰኔ 5/2009 የወባ በሽታን ከአገሪቱ ለማጥፋት ለተያዘው እቅድ ስኬታማነት የሚያግዝ የዳሰሳ ጥናት መጀመሩን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ለጥናቱ አጋዢ የሆነ መረጃ በማሰባሰብ ለሚሳተፉ የዘርፉ ባለሙያዎች የተዘጋጀ ስልጠና ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

የኢንስቲትዩቱ ተወካይ አቶ ገዘኸኝ ተስፋዬ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት የህብረተሰብ የጤና ችግር ከሆኑት በሽታዎች መካከል አንዱ የሆነውን የወባ በሽታ እስከ 2020 ዓ.ም ከአገሪቱ ለማጥፋት ታቅዷል፡፡

ለዚሁ እቅድ ስኬታማነት የሚያግዝ የዳሰሳ ጥናት መጀመሩን ጠቁመዋል።

ለጥናቱ ቁልፍ ግብዓት የሆነ መረጃ የማሰበሰብ ተግባር የሚያከናውኑ ቡድኖችን በተመረጡ ስደስት ክልሎችና 239 ወረዳዎች ለማሰማራት አጋዢ የሆነ እውቀት ለማስጨበጥ የሚያስችል ስልጠናው መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የስልጠናው ተሳታፊ የጤና ባለሙያዎችም ትክክለኛ መረጃ በማሰባሰብ ለጥናቱ ስኬታማነት የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ለአዲሱ ብሔራዊ የወባ ማጥፋት ስትራቴጂክ ዕቅድ ስኬት ለሚሰበሰበው መረጃ ውጤታማነት ህብረተሰቡ፣ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የሆስፒታሎችና ጤና ኬላ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ትብብር እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የወባ ማስወገድ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ደረጀ ድሉ በበኩላቸው በአገሪቱ ባለፉት ስድስት ዓመታት የወባ ህሙማን ቁጥር በ50 በመቶ መቀነሱን አመልክተዋል።

ይህ ውጤት ሊመዘገብ የቻለው ህብረተሰቡ  በበሽታ መከላከልና መቆጣጠር፣ በፀረ ወባ ኬሚካል ርጭትና የአልጋ አጎበር አጠቃቀም ዙሪያ እያገኘ ያለው ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ ነው፡፡

በዚህ ዓመት የተጀመረው የዳሰሳ ጥናት እየተካሄደ ያለውም ከዚህ በፊት የወባ ስርጭትን በመግታት አመርቂ ውጤት ባስመዘገቡ ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ሐራሪ ክልሎችና ድሬደዋ ከተማ አስተዳድር መሆኑን አቶ ደሳለኝ አስታውቀዋል።

በኢንስቲትዩቱ ትኩረት የሚሹ በሽታዎች የጥናትና ምርምር ቡድን አስተባባሪ አቶ ስንዴው መካሻ እንዳመለከቱት ወባን ከአገሪቱ ለማጥፋት የቅኝት ሥርዓትን የማጠናከር ስራ እየተካሄደ ነው፡፡

እንዲሁም የመድሃኒት ፈዋሽነት፣ የላቦራቶሪ መሳሪያዎች፣ የአልጋ አጎበርና ፀረ ወባ ኬሚካሎች ጥራት ላይ የጥናትና ምርምር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአምስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ስልጠና ላይ የዳሰሳ ጥናቱ ከሚካሄድባቸው ክልሎችና የከተማ አስተዳደሩ የተወጣጡ ከ100 በላይ የጤና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  ሰኔ 5/2009 የእናት ወግ የተማሪዎች ምገባ መርኃ ግብር በፖሊሲ ደረጃ እንዲተገበር ተቀባይነት ማግኘቱን ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ ገለጹ። 

 ቀዳማዊት እመቤቷ በቁስቋም ጣይቱ ብጡል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት የተማሪዎች ምገባ መርኃ ግብሩን አተገባበር  ተመልክተዋል። 

 የተማሪዎች ምገባ መርኃ ግብር በበጎ ፍቃደኛ መምህራን፣ በለጋሾችና በህብረተሰቡ ድጋፍ ውጤታማ እንቅስቃሴ እየተደረገበት መሆኑንም ገልፀዋል።     

 ''በቀጣይ መርኃ ግብሩን መንግስት እንደሚረከበው እምነት አለን'' ያሉት ወይዘሮ ሮማን መርኃ ግብሩ በፖሊሲ ደረጃ ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

 መንግስት እስከሚረከበው ድረስ የመርሃ ግብሩን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ከባለኃብቶችና ለጋሾች ድጋፍ የማሰባሰቡ ተግባር እንደሚቀጥል አብራርተዋል።  

 መርኃ ግብሩ ስኬታማ እንዲሆን የበጎ ፍቃደኛ መመህራን ድርሻ የላቀ መሆኑን የጠቀሱት ቀዳማዊት እመቤቷ ተግባራቸው የሚያስመሰግናቸው መሆኑን ተናግረዋል። 

 ተማሪዎችን ከመመገብ ባለፈ በመልካም ስነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ የተጀመረው ተግባር ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።

 በአዲስ አበባ በመርኃ ግብሩ ከታቀፉ ትምህርት ቤቶች መካከል የቁስቋም ጣይቱ ብጡል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ሲሆን 279 ተማሪዎች ተጠቃሚ ናቸው።

 ተማሪ ፍቅሩ ተመስገን የምገባው ተጠቃሚ ሲሆን ወላጆቹን በሞት ያጣ በመሆኑ በምግብ እጥረት ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገዶ እንደነበር ያስታውሳል።

 የምገባ መርሃ ግብሩ በመጀመረ ትምህርቱን መቀጠል ከመቻሉ ባሻገር ውጤታማ እንደሆነም ገልጿል።

 ''በትምህርት ቤቱ ልጃቸው የምገባው ተጠቃሚ በመሆኗ ዝቅተኛ የነበረው የትምህርት ደረጃዋ ከፍ እንዲል ሆኗል'' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ማርታ አይደፍሩህ ናቸው።

 የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ደብረወርቅ ልዑልሰገድ በኩላቸው የትምህርት ቤት ምገባ ከተመጀረ ወዲህ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

 በዕለቱ ብሩህ ተስፋ በጎ አድራጎት ማህበር በመርሃ ግብሩ ለታቀፉ ተማሪዎች የጫማ እንዲሁም የመምህራን መርጃ መጽሃፍት ድጋፍ አበርክቷል።

 የምገባ መርኃ ግብሩ በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተተገበረ ሲሆን ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችም ተጠቃሚ ናቸው። 

 መርኃ ግብሩ በ2007 ዓ.ም 5 ሺህ 100 ተማሪዎችን በመመገብ ነበር

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  ሰኔ 5/2009 የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ በደቡብ ሱዳን የጸጥታ ጉዳይ ለመምከር ባዘጋጀው ስብሰባ ለመሳተፍ የአባል አገራቱ መሪዎች ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል።

 የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ታባን ዴንጋይ፣ የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር፣ የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒና የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓሊ ሀሰን ካይሬ አዲስ አበባ ከገቡት መሪዎች መካከል ናቸው።

 የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስ አሚና ሞሐመድን ጨምሮ ባለስልጣናቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል።

 በወቅቱ የኢጋድ ሊቀ-መንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተጠራው ስብሰባ በደቡብ ሱዳን የፀጥታና ደኅንነት እንዲሁም እየተካሄደ ባለው ሠብዓዊ ድጋፍ ዙሪያ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚመክር ተነግሯል።

 የጅቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ዓሊ ዩሱፍ በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ ትናንት ምሽት አዲስ አበባ መግባታቸው ታውቋል።

 

Published in ፖለቲካ

 

 አዲስ አበባ ሰኔ 5/2009 ኢትዮጵያ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ መሆኗን የዓለም ኢንቨስትመንት ሪፖርት አመለከተ።

 በ2017ቱ የዓለም ባንክና የገንዘብ ድርጅት ተቋም /አይ.ኤም.ኤፍ/ የኢኮኖሚ ትንበያ ሪፖርት ደግሞ ኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ እድገቷ የአፍሪካ ኮኮብ እንደምትሆን አመላክቷል።

 በጎርጎሮሳዊያኑ 2016 በአፍሪካ አገራት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ያሽቆለቆለ መሆኑን የገለጸው ሪፖርቱ፤ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ግን ጠንካራ ስኬት ማስመዝገባቸውን ጠቅሷል።

 በዚህም 46 በመቶ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እድገት በማሳየት ኢትዮጵያን በአህጉሩ ቀዳሚዋ መዳረሻ አገር አድርጓታል። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰቱም 3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድረሱን አስነብቧል።

 በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በየብስ በተከበቡ አገሮች ቅናሽ ቢያሳይም ኢትዮጵያ ግን ለአራት ተከታታይ ዓመታት ጭማሪ ማሳየቷን ሪፖርቱ አመልክቷል።

 ኢትዮጵያም በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር 2015 በየብስ ከተከበቡና ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ታዳጊ አገሮች መካከል 5ኛ ደረጃ የነበረች ሲሆን ሪፖርቱ ወደ 2ኛ ደረጃ ማደጓን ጠቅሷል።

 እንደ ሪፖርቱ ገለጻ የመሰረተ ልማትና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች አገሪቷን በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስኬታማ አድርገዋታል።

 የአይ.ኤም.ኤፍ የ2017 የኢኮኖሚ ትንበያ ደግሞ "ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ካጋጠማት ድርቅ በማገገም በ7 ነጥብ 5 በመቶ እድገት የአፍሪካ ኮከብ ትሆናለች" ብሏል።

 የሰሃራ በታች ዓመታዊ እድገት 2 ነጥብ 6 በመቶ እንደሚሆን የጠቆመው ሪፖርቱ ቡርኪና ፋሶ፣ አይቮሪኮስት፣ ሴኔጋል፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ ከ6 በመቶ በላይ ዓመታዊ እድገት ሊኖራቸው እንደሚችል ነው የተነበየው። 

 የዓለም ባንክ ባወጣው የሰኔ 2017 የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ትንበያ ደግሞ ኢትዮጵያ 8 ነጥብ 3 በመቶ በማስመዝገብ በዓለም በፍጥነት እያደገች ያለች አገር እንደምትሆን አመላክቷል።

 ባንኩ በዓለም ምጣኔ ሃብት ትንበያ ቀውስ እንደሚገጥመው የተነበየ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ የቀጠለው ድርቅ የኬንያ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳንን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ክፉኛ መጉዳቱን ገልጿል።

 ያም ሆኖ ግን ክፍለ አህጉሩ አዎንታዊ እድገት እንደሚኖረው ነው የጠቆመው።

 ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች በ2017 የ2 ነጥብ 6 በመቶ፤ በ2018 ደግሞ የ3 ነጥብ 8 በመቶ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ይኖራል ብሏል።

 በተፈጥሮ ማዕድን ባልበለጸጉ አገሮች በመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት፣ በታዳሽ አገልግሎት ዘርፍ እንዲሁም በግብርና ምርታማነት ታግዘው እድገታቸውን እንደሚያስቀጥሉ ነው የገለፀው።

 በትንበያ ሪፖርቱ ታንዛኒያ በ7 ነጥብ 2 በመቶ፣ ኮትዲቯር በ6 ነጥብ 8 በመቶ እንዲሁም ሴኔጋል በ6 ነጥብ 7 በመቶ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት በማስመዝገብ ኢትዮጵያን የሚከተሉ አገራት ናቸው።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 5/2009 በአካባቢያቸው የተገነቡ ሁለገብ የግብርና ግብዓት ማቅረቢያ ማዕከላት ከእንግልትና ተገቢ ካልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንደታደጓቸው አስተያየት የሰጡ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የደቡብ ክልል ሃላባ ልዩ ወረዳና ወላይታ ሶዶ  አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለፁት የግብርና ግብዓቶችን ለመግዛት ለረጅም ርቀት ጉዞና ለተጨማሪ ወጪ ሲዳረጉ ቆይተዋል።

መንግስት ይህን ችግራቸውን ለመፍታት በአቅራቢያቸው ሁለገብ የግብርና ግብዓት አቅራቢ ማዕከላት እንዲገነቡ ማድረጉ ከሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳዳናቸውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አርሶ አደሮች በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች የአንድ መስኮት የግብርና ግብዓት መስጫ ማዕከላትን እያስገነባ ነው።

የሃላባ እና ወላይታ ሶዶ ማዕከላትም ግንባታቸው ተጠናቆ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩት መካከል ይገኙበታል።

የሃላባ ልዩ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ፎራ ጌቲሶ እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም ረጅም ርቀት ከመጓዛቸው በተጨማሪ ምርጥ ዘር ከአንድ ቦታ፣ ማዳበሪያ ደግሞ ከሌላ ስፍራ ለመግዛት ይገደዱ ነበር።

ግብዓቶቹ አሉ ከተባለበት ስፍራ ሲደርሱ "አልቋል" የሚባሉባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩና ከፍተኛ እንግልት እንደሚደርስባቸው ፤ አማራጭ ስሌላቸውም የተጠየቁትን ዋጋ በመክፈል ለአላስፈላጊ ወጪ ሲዳረጉ እንደነበረ አስታውሰዋል።

አሁን በአቅራቢያቸው በተገነቡላቸው ማዕከላት ጥራታቸው በምርምር የተረጋገጡ ግብዓቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡላቸው በመሆኑ ችግራቸው እንደተቃለለ ገልፀዋል።

በአቅራቢያቸው የእንስሳት መድሃኒት ባለማግኘታቸው ታመው ከሚድኑት ይልቅ የሚሞቱ ከብቶቻቸው ይበዙ እንደነበረ የገለፁት ደግሞ ሌላው አርሶ አደር ተስፋዬ ወልቁ ናቸው።

"ማዕከላቱ አስፈላጊውን መድሃኒትና ባለሙያ በማጣመር በአቅራቢያችን መገኘታቸው የሚሞቱ እንስሳትን ህይወት ለመታደግ የጎላ ድርሻ ይኖራቸዋል" ብለዋል አርሶ አደሩ።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ከ100 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሃያ ሁለገብ የግብርና ግብዓት መስጫ ማዕከላትን ለማቋቋም እየሰራ ነው።

እስካሁን አራት ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን በተያዘው ወር መጨረሻ ተጨማሪ ስምንት ማዕከላት ወደ ስራ እንዲሚገቡ ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

Published in ኢኮኖሚ

ነገሌ ሰኔ 5/2009 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ባለሀብቶች 5 ሺህ 600 ኩንታል የምግብ እህል በድርቅ ለተጎዱ አርብቶ አደሮች ድጋፍ አደረጉ፡፡

እነዚህ 12 ባለሀብቶች ያደረጉት የእህል ድጋፍ  ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት እንዳለው በዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት የዕርዳታ ስርጭት አስተባባሪ አቶ መንግስቱ ዘለቀ  ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

በግል ባንክና ኢንሹራንስ ዘርፍ የተሰማሩት ባለሀብቶቹ ለጽህፈት ቤቱ በማስረከብ ድጋፉን ያደረጉት ባለፈው ቅዳሜ  ነው፡፡

ከእነዚህም መካከል የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፣ የአሮሚያ ህብረት ስራ ባንክና እንዲሁም የአዋሽ ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያ ይገኙበታል።

በርክክቡ ስነስርዓት የተገኙት  የጉጂ ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ ነጋሽ ቡላላ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው በድርቅ የተጎዱ ወገኞችን ለመደገፍ እየተደረገ ያለውን ጥረት በማገዝ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ወደፊትም እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡

የባለሀብቶቹ ተወካዮች  በበኩላቸው ችግሩ እስኪቃለል ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል፡፡

በጉጂ ዞን ካለፈው ዓመት ወዲህ በአምስት የአርብቶ አደር ወረዳዎች በተከሰተው ድርቅ ከ171 ሺህ በላይ ህዝብ ለምግብ እህል እጥረት መጋለጡን ከዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ማህበራዊ

ሃዋሳ ሰኔ 5/2009 በደቡብ ክልል ሁለት ዞኖች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በመከላከል ላይ ያተኮረ የትብብር ፕሮጀክት ተግባራዊ መሆን መጀመሩን የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ አስወቀ።

የፕሮጀክቱን በይፋ መጀመር የሚያበስር የትውውቅ መድረክ ትላንት በሀዋሳ ተካሄዷል ።

የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን በወቅቱ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በወላይታና ሃዲያ ዞኖች አራት ወረዳዎች ውስጥ ለቀጣዮቹ 16 ወራት ተግባራዊ ይደረጋል።

ፕሮጀክቱ በክልሉና በወረዳዎቹ  ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮዎችና በተባበሩት መንግስታት የስነ- ህዝብ ፈንድና በጣሊያን የልማት ትብብር ኤጄንሲ ትብብር ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል ።

በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ የሴቶችን ግንዛቤ ማሳደግና በተለይም በአካባቢዎቹ ጎልተው የሚታዩ ያለእድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት ለማስቀረት በተሰሩ ስራዎች፣ የተገኙ ውጤቶችና ተሞክሮችን ማስፋፋት በፕሮጀክቱ የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው ።

እንዲሁም በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጠቂ የሆኑ ሴቶችና ቤተሰቦችን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ ማሻሻልና የስነ- ተዋልዶ ጤና ትምህርት ማስፋፋት ሌላው የፕሮጀክቱ የትኩረተ አቅጣጫዎች መሆናቸውን ኃላፊዋ ገልፀዋል ።

በፌዴራል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር የህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ሞዲ በበኩላቸው በወረዳዎቹ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የተገኘው ውጤት አበረታች ቢሆንም ተጨማሪ ስራ የሚጠይቁ ተግባራት መኖራቸውን ጠቁመዋል ።

ቀሪ ተግባራትን ለማከናወን የአጋር ድርጅቶች እገዛ አሰፈላጊ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታዋ ፕሮጀክቱ በተለይ ወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አመላክተዋል ።

በጣሊያን ልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ ሚስ ጄኒቬራ ሎቲዛ በበኩላቸው መንግስታቸው ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ 500 ሺህ ዩሮ መመደቡን ተናግረዋል ።

እንደ ተጠሪዋ ገለፃ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት ሴቶች ላይ መስራት ያስፈልጋል።

በትውውቅ መድረኩ ላይ በፕሮጀክቱ ትግበራ የሚሳተፉ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተጠሪዎችና የሚመለከታቸው የክልል፣ የዞንና የወረዳ አስተዳደር አካላት ተሳትፈዋል።

Published in ማህበራዊ

ደሴ ሰኔ 5/2009 በአማራ ክልል በተመረጡ 16 ከተሞች ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የክልሉ ከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ፡፡

ዘመናዊ የመሬት ይዞታ ምዝገባና ማረጋገጥ ስራው ትናንት በደሴ ከተማ አስተዳደር ተጀምሯል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሷልህ አቡ ለኢዜአ እንደገለፁት በከተሞች ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርአት ባለመዘርጋቱ መሬት የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡

መሬትን ያለአግባብ የመጠቀም አዝማሚያን ለማስቀረት በክልሉ በተመረጡ 16 ከተሞች የዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

ከተሞቹ ፤ ባላቸው የህዝብ ብዛት፣ የንግድ እንቅስቃሴና እድገት ግምት ውስጥ በማስገባት መመረጣቸውን ተናግረዋል፡፡

ከተመረጡት ከተሞች ውስጥም ደሴ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን፣ ኮምቦልቻና ቡሬ ከተሞች በመጀመሪያው ዙር ዘመናዊ የመሬት ይዞታ ምዝገባና ማረጋገጥ ስራን ተግባራዊ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

የፌዴራል የከተማ መሬትና መሬት ነክ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ባደረገው ድጋፍ ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የቅየሳ መሳሪያዎች የመሬት ይዞታና ምዝገባ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች መሰራጨታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በመጀመሪያ ዙር የመሬት ይዞታ ምዝገባና ማረጋገጥ ስራ ተግባራዊ ከሚደረግባቸው ከተሞች ውስጥ በደሴ ከተማ ትናንት ስራው ተጀምሯል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ትዕዛዙ እንግዳ እንደገለጹት በከተማው ዘመናዊ የአሰራር ስርአት ባለመዘርጋቱ መሬት የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ችግሩን ለመከላከልም በዘመናዊ መረጃ ስርአት የተደራጀ የከተማ መሬት ምዝገባና ማረጋገጫ የመስጠት ስራ በዳውዶ ክፍለ ከተማ መገናኛ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ትናንት ተጀምሯል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 5/2009 በመጪው ሐምሌ መጨረሻ በለንደን በሚካሄደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ለመምረጥ የሠዓት ማሟያ ውድድር በኔዘርላንድስ ሄንግሎ ተካሄደ።

ውድድሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከኤፍ.ቢ.ኬ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች በተደረገው የሠዓት ማሟያ ውድድር አትሌት ገለቴ ቡርቃ 30 ደቂቃ ከ40 ሰከንድ ከ87 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት አንደኛ ወጥታለች።

ሰንበሬ ተፈሪ 30 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ ከ68 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ ስትሆን፤ በላይነሽ ኦልጅራ ከሰንበሬ በሶስት ሰከንድ ዘግይታ ሶስተኛ በመውጣት ሚኒማ አሟልተዋል።

በወንዶች 10 ሺህ ሜትር አትሌት አባዲ ሀዲስ 27 ደቂቃ ከ08 ሰከንድ ከ26 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት አንደኛ ወጥቷል።

ጀማል መኮንን 27 ደቂቃ ከ9 ሰከንድ ከ8 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ፤ አትሌት የኔዋላ አመራው በ27 ደቂቃ ከ19 ሰከንድ ከ86 ማይክሮ ሰከንድ ሶስተኛ ወጥቷል።

በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሴቶች አትሌት ሶፊያ አሰፋ ውድድሩን በ9 ደቂቃ ከ07 ሰከንድ ከ06 ማይክሮ ሰከንድ በማጠናቀቅ የራሷን ክብረወሰን በመስበር ጭምር አሸንፋለች።

አትሌት ብርቱካን አዳሙ በ9 ደቂቃ ከ28 ሰከንድ ከ67 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ ሆናለች።

በወንዶች አትሌት ጌትነት ዋሌ በቀዳሚነት ለማጠናቀቅ 8 ደቂቃ ከ12 ሰከንድ ከ28 ማይክሮ ሰከንድ ፈጅቶበታል።

ታፈሰ ሰቦቃ 8 ደቂቃ ከ13 ሰከንድ ከ22 ማይክሮ ሰከንድ በሁለተኝነት ሲያጠናቅቅ ጫላ በዮ በ8 ደቂቃ ከ13 ሰከንድ ከ24 ማይክሮ ሰከንድ ሶስተኛ ወጥቷል።

በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ወንዶች ውድድር ከአንደኛ እስከ አራተኛ የወጡ አትሌቶች የራሳቸውን ምርጥ ሠዓት በማስመዝገብ ጭምር ነው ያሸነፉት።

በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች አትሌት ሳሙኤል ተስፋዬ በ3 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ ከ78 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት አሸናፊ ሆኗል።

አማን ወጤ ሁለተኛ፤ ተሬሳ ቶሎሳ ሶስተኛ በመሆን አሸንፈዋል።

በ1 ሺህ 500፣ በ3 ሺህ እና በ10 ሺህ ሜትር ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት ያሸነፉና በሌሎች ርቀቶች ሚኒማ ማምጣት የቻሉ አትሌቶች በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

በለንደን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በወንዶች ቀነኒሳ በቀለ፣ ታምራት ቶላና ጸጋዬ መኮንን፤ በሴቶች ጥሩነሽ ዲባባ፣ ብርሃኔ ዲባባ፣ ማሬ ዲባባና ሹሬ ደምሴ ኢትዮጵያን የሚወክሉ የማራቶን ሯጮች መሆናቸውን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ሰኔ 5/2009 ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ትናንት በቻይና ላንዙ በተደረገው የማራቶን ውድድር በሁለቱም ጾታ አሸነፉ።

በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የብር ደረጃ ባለው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊያኑ የበላይነታቸውን አሳይተዋል።

በሴቶች በተደረገው ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አሸንፈዋል።

አሸቴ በከር 2 ሠዓት ከ32 ደቂቃ ከ3 ሰከንድ በመግባት አንደኛ ሆና ስታጠናቀቅ ሶስተኛ ፕሮፌሽናል የማራቶን ውድድሯን ያደረገችው ትዕግስት ግርማ የግል ምርጥ ሠዓቷን በ29 ሰከንድ በማሻሻል ሁለተኛ ወጥታለች።

አትሌት አበባ ገብረ መስቀል 2 ሠዓት ከ32 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ በመግባት የሶስተኝነት ደረጃን ይዛለች።

ባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ የነበረችው ፀሐይ ደሰላኝ ስድስተኛ ደረጃን ያገኘች ሲሆን የአምናውን ድሏን ማስጠበቅ ሳትችል መቅረቷን የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስነብቧል።

በተመሳሳይ በወንዶች በተካሄደው ውድድር ከልክሌ ገዛኸኝ 2 ሠዓት ከ11 ደቂቃ ከ54 ሰከንድ በመግባት በአንደኝነት አጠናቋል።

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 2015 በኢትዮጵያዊው አትሌት አባይነህ አየለ የተያዘውን የቦታውን ሪከርድ ለማሻሻል ያደረገው ጥረት ግን አልተሰካለትም።

ሌላው ኢትዮጵያዊ አትሌት ፍቃዱ ከበደ ከከልክሌ በ12 ሰከንድ ዘግይቶ በመግባት 2ኛ ሲሆን፤ ኬንያዊው አርነስት ንጌኖ 2 ሠዓት ከ12 ደቂቃ ከ24 ሰከንድ በመግባት ሶስተኛ ወጥቷል።

የውድድሩ አሸናፊ ከልክሌ ገዛኸኝ "የቦታውን ሪከርድ ለመስበር አቅጄ ብሮጥም በውድድሩ አጋማሽ ላይ የነበረው ሙቀት ሪከርዱን እንዳልሰብር አድርጎኛል" ሲል ከውድድሩ በኋላ ተናግሯል።

Published in ስፖርት
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን