×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Sunday, 11 June 2017

አዲስ አበባ ሰኔ4/2009 የምስራቅና የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ነዋሪዎች በአካባቢያቸው የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ባለመገንባቱ በምርታቸው ላይ እሴት በመጨመር ተጠቃሚ ለመሆን አለመቻላቸውን ገለጹ።

 ከሁለቱ ዞኖች የተወጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

 ነዋሪዎቹ  እንደገለጹት፤ በአካባቢው የምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ባለመኖሩ እንደ ቡና፣ በቆሎ፣ አትክልትና ፍራፍሬ  ያሉ ምርቶች በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋሉ አይደለም።

 "መንግስት ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት በአካባቢው የምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪን ሊያስፋፋ ይገባል" ብለዋል።

 በተጨማሪም የመንገድ መሰረተ ልማትና የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግር በስፋት እንደሚስተዋልም ተወካዮቹ ገልጸዋል ።

 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በሰጡት ምላሽ፤ ጥያቄው ትክክለኛና አግባብነት ያለው መሆኑን ገልጸው፤ መንግስት በአካባቢው የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

 ከመንግስት ጥረት ጎንለጎን የአካባቢው ነዋሪዎችም በመቀናጀት የምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ለመመስረት መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው አብራርተዋል።

 ለዚህ ደግሞ መንግስት 15 በመቶ ብቻ ለቆጠቡ 85 በመቶ ብድር ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን አስረድተው፤ የአካባቢው ነዋሪዎች የዚህ ዕድል ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸውም ነው ያመለከቱት።

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁተኛው እድገትና ትራንፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ የተካተቱ የመንገድ ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውሰው፤ በቀጣዩ ዕቅድ የመንገድ መሰረተ ልማት በስፋት እንደሚካተት ነው ያብራሩት።

 የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግር በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ችግሩ የመላ አገሪቷ መሆኑን ጠቁመው፤ በሂደት እንደሚፈታም  ገልጸዋል።

 የህብረተሰቡ ተወካዮች በአካባቢያቸው እየተከናወኑ ስላሉ ልማቶች መደሰታቸውን ለጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል ።

Published in ኢኮኖሚ

ደብረ ብርሃን ሰኔ 4/2009 በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን መጨረሻ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የቅበላ አቅም አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ለማድረስ የያዘውን እቅድ ለማሳካት እየሰራ መሆኑን የትምህርት ሚስቴር አስታወቀ። 

 የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበተን 10ኛ ዓመት በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል። 

 በዝግጅቱ ላይ የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴርን ወክለዉ የተገኙት ዶክተር ከተማ መስቀሌ እንደገለፁት በሃገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ተደራሽ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤት እየተገኘ ነው።

 ከ25 ዓመታት በፊት በሀገሪቱ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ይሰጥ የነበረው የከፍተኛ ትምህርት በአሁኑ ወቅት ከ36 በላይ በመድረሱ ዜጎች በአካባቢያቸው የትምህርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።

 በአሁኑ ወቅትም ከ10 የማያንሱ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ሲጠናቀቅ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመኑ መጨረሻ አሁን ያለው 700ሺህ ዓመታዊ የቅበላ አቅም ወደ አንድ ነጥበ ሁለት ሚሊዮን እንደሚያድግ ተናግረዋል።

 በግል የሚተዳደሩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቁጥርም 116 መድረተሳቸውን አብራርተዋል። 

 የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸዉ ተፈራ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በህዝብና በመንግስት የተጣለበትን የማስተማር ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት በትኩረት እየሰራ ይገኛል። 

 ባለፉት 10 ዓመታት መንግስትና ህዝቡ ባደረጉት ርብርብ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች ዓመታዊ የቅበላ አቅሙን ከ28ሺ በላይ ማድረስ መቻሉን አብራርተዋል። 

 ዩኒቨርስቲው በ80 ሚሊዮን ብር ወጪ በሀገሪቱ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሚያስተሳስረውን የመረጃ ማዕከል አስገንብቶም አስመርቋል።

 "በቀጣይ በግብርና፣ በምግብ ማቀነባበር፣ በታሪክና ቅርሳ ቅርስ መስኮች የልህቀት ማእከል በመሆን ህብረተሰቡን በጥናትና ምርምር ውጤቶች ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል" ብለዋል።

 በዓሉ በፓናል ውይይትና በተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ትላንት ሲከበር የከፍትኛ ትምህርት ምሁራንና ኃላፊዎች እንዲሁም የቀድሞ ተመራቂዎችን ጨምሮ አንድ ሺህ የሚደርሱ እንግዶች ተገኝተዋል። 

 

Published in ማህበራዊ

አዳማ ሰኔ 4/2009 በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ የሚታዩ ችግሮች የሙያ፣ የማስፈፀምና የፋይናንስ አቅም ውስንነት ማሳያዎች መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን ገለጡ።

 በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በአባገዳ አዳራሽ ላለፉት ሦስት ቀናት የተካሄደው ዓለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ ትናንት ተጠናቋል።

 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲት የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮፌሰር ጤናአለም አየነው የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ልማትና አጠቃቀም ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

 ኘሮፌሰሩ በዚሁ ጽሁፋቸው እንደገለፁት በአገሪቱ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ግንባታ ላይ የሚታዩ ችግሮች በዋናነት ከዕውቀት ማነስ፣ ከማስፈፀምና ከፋይናንስ አቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ የሚመነጩ ናቸው ፡፡

 የዘርፉ ምሁራን የዕውቀት መሰረታቸው ውስን መሆን፣ የቁፋሮ ዋጋ መናር፣ የተቆፈሩ ጉድጓዶች ደርቀው መገኘትና ሀብቱን በትክክል ለማወቅ የአቅም ውስንነት መኖሩ በግንባታ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች ናቸው፡፡

 በምስራቅና በምዕራብ የአገሪቷ አካባቢዎች በተለይም ስምጥ ሸለቆን ጨምሮ አፋር፣ ሶማሊ፣ ኦሮሚያና አማራ ክልሎች የሚገኘው የከርሰ ምድር ውሃ ከፍተኛ የፊሎራይድ፣ አይረንና ጨዋማ ይዘት አለው።

 ''በዚህም ከ11 እስከ 14 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ተጠቂ ነው  ያሉት ፕሮፌሰሩ ችግሩን መቅረፍ ያልተቻለው እየተጠቀምን ያለው የዕውቀት ደረጃና የቴክኖሎጂ አቅም ደካማ መሆኑ ነው'' ብለዋል።

 በኦሮሚያና አዲስ አበባ አካባቢ ከኢንዱስትሪ የሚወጡ የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ የግብርና ግብዓት ኬሚካሎች አጠቃቀምም ለከርሰ ምድር ውሃ መበላሸት መንስኤ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

 ለችግሩ መባባስ ሙያዊና ሳይንሳዊ ድጋፍ የሚሰጥ ተቋም ያለመኖር፣ ለዘርፉ ፖሊስና ስትራቴጂ ተግባራዊነት ላይ የግል ሴክተርና መንግስት የተቀናጀ ርብርብ ደካማ መሆንና ጠንከራ ክትትል ያለማድረግ ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 በዚህም በብዛት እየተጎዳ ያለው አርሶ አደሩና ደሃው ህብተረሰብ ነው ያሉት ጥናት አቅራቢው ለዘርፉ ፖሊስና ስትራቴጂ ተግባራዊነት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

 እንዲሁም አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና ከከፍተኛው የደጋ ክፍል ውሃ በቧንቧ በመሳብ ለችግሩ ተጋላጭ የገጠር ቀበሌዎችና ከተሞች ተደራሽ ማድረግን ጥናቱ እንደመፍትሄ አስቀምጠዋል።

 በአዳማ ከተማ በነባሩ ፕላን አተገባበርና ወስንነቶች ላይ ጥናት ያቀረቡት ኢንጂነር ደጀነ ተሰማ በበኩላቸው የከተማዋ ኢንቨስትመንት ተቋማት፣ የቤቶች ልማት፣ የመሬት አጠቃቀምና የአካባቢ ጥበቃ ልማቶች ፕላኑን ተከትሎ ያልተከናወኑና ለህገ ወጥነት በር የከፈቱ ናቸው፡፡

 ለኢንቨስትመንትና ለመኖሪያ ቤት የተሰጠው መሬት ሳይለማ ከ5 እስከ 10 ዓመት መቆየቱ፣ የመሬት ወረራና ህገ ወጥ ግንባታ መስፋፋት፣ በከተማዋ ፍትሃዊነት የመሰረተ ልማት እንዳይስፋፋ ማድረጉንም ገልጠዋል።

 አዲሱ የከተማዋ ፕላን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑ፤ መንግስት ሳይለሙ የተቀመጠ መሬት እንዲመለስ ለማድረግ ጠንካራ ክትትልና ግምገማ በማድረግ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 የውሃ ዘርፉን ጨምሮ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ የቀረቡት ጥናቶች የችግሮቹ አመላካችና የመፍትሄ አቅጣጫ ጠቋሚ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኢትዮጰያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ኢንስቲትዩት ተወካይ አቶ ሁንዴ መልካ ናቸው።

 የውሃ ሀብቱን ለማልማት የሚሰጠው የኢንቨስትመንት ፈቃድ በህብረተሰቡ ጤንነት፣ ደህንነትና በአካባቢና ተፈጥሮ ሀብት ላይ ጉዳት የማያስከትል መሆን አለበት ብለዋል።

Published in ማህበራዊ

ባህር ዳር ሰኔ 4/2009 የብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህል በመጤዎች ከመበረዝ አደጋ ለመታደግ ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የባህል ማዕከል አሳሰበ።

3ኛው ሃገር አቀፍ የባህል ማዕከላት የልምድ ልውውጥ ፕሮግራም በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እልፍነሽ ሃይሌ የልምድ ልውውጥ ፕሮግራሙ ትናንት ሲጀመር እንዳሳሰቡት ባህል የአንድ ህዝብ የማንነት መገለጫ ነው።

ህዝቡ ሃዘኑን፣ ደስታውን፣ ጀግንነቱን፣ ሃገር ወዳድነቱን፣ ተባብሮና ተረዳድቶ መኖርን፣ እንዲሁም ታሪኩንና ማንነቱን የሚያንፀባርቅባቸው ባህሎች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ባህልን በማልማት፣ በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በማስተዋወቅ የሃገሪቱን በጎ ገፅታ እንዲገነባ ለማድረግም አጋዢ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

በተለይም የባህል ማዕካላት ሃገራዊ ገፅታን እንዲያስተዋውቁ የተሟላ አሰራርና አደረጃጀት ኖሯቸው እንዲቋቋሙ እየተደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

በየዓመቱ እየተካሄደ ያለው የልምድ ልውውጥ ፕሮግራምም ክልሎች ልምዶቻቸውን እንዲለዋጡ በማድረግ የተሻለ አቅም ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ብሄራዊ ማዕከሉ ወጣቱ የባህሉ ባለቤት ሆኖ እንዲያድግና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር እንዲሁም ባህልን ከመበረዝ ለመታደግ የሚያደርገውን ጥረት ባለድርሻ አካላት ሊደግፉ ይገባልም ብለዋል።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው የክልሉን ባህል የሚያንፀባርቁ 110 የባህል ማዕከላትን በማቋቋም አቅም በፈቀደ ሁሉ የመደገፍ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም በኪነ ጥበብ ዘርፉ የክልሉ መገለጫ የሆኑ የጎንደር፣ የጎጃም፣ የወሎና ሌሎች አካበቢዎች የኪነጥበብ ቡድን ተቋቁሞ ባህሎቻቸውን እንዲያስተዋውቁ በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የዚህ የልምድ ልውውጥ ኘሮግራምም ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ እንግዶች የክልሉን የምግብ ዝግጅትና መሰል ባህል እንዲያውቁ ለማድረግ እንደሚያግዝ አብራርተዋል።

የባህል ልማት እንደ ሌሎች የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መልማትና ማደግ እንዳለበት የገለፁት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ባህል ማዕከል ዋና ዳይሬክተርና ጥናታዊ ፅሁፍ አቅራቢ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ ናቸው።

እንደ ሃገር ባህል ለልማት አስተዋጽኦ አለው የሚል አስተሳሰብ እየዳበረ ቢመጣም በባህል መበረዝ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ተረድቶ ተቀናጀቶ በመስራትና ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በመግባት በኩል ክፍተት መኖሩን ገልፀዋል።

ትናንት የተጀመረው የልምድ ልውውጥ እስከ ሰኔ 9 ቀን 2009 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን የአማራ ክልል የምግብ አዘጋጃጀት ለታዳሚዎች ይቀርባል።

እንዲሁም በሚቀርቡ ጥናታዊ ፅሁፎች ውይይት የሚካሄድ ሲሆን ቤዛዊት ቤተ መንግስት፣ የጣና ገዳማት፣ ጢስ አባይ ፏፏቴ፣ የጎንደር አብያተ መንግስታትና ሌሎችም በታዳሚዎች ይጎበኛሉ።

 

Published in ማህበራዊ

ሃዋሳ ሰኔ 4/2009 የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግርን በማምጣት ሀገሪቱ ወደ አንደስትሪ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ለምታደርገው ጥረት መሰረት እንደሚሆን ተመለከተ።

ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የተወጣጡ የፌዴራል ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮ-ቴሌኮም የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወይዘሮ ጽጌሬዳ ጋሻው ለኢዜአ እንደገለጹት የሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ከጠበቁት በላይ ግዙፍና ዘመናዊ ሆኖ አግኝተውታል፡፡

ፓርኩ ሀገቱ ወደ ኢንደስትሪ ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር ትልቅ መሰረት እንደሚሆንና ለዕድገቷም እገዛ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ፍሰሀ በቀለ በበኩላቸው እንደገለጹት ከዚህ በፊት በመገናኛ ብዙሀን ከሰሙት አንጻር በአካል ተገኝተው የተመለከቱት ኢንዱስትሪ ፓርኩ ትልቅና ብዙ ተግባራት የሚከናወኑበት ነው።

የቅጥር ስብጥሩም ከዝቅተኛው የትምህርት ደረጃ አንስቶ እስከ ከፍተኛው ድረስ ተዋጽኦ ያለበት መሆኑ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሀዋሳ ኢንደስትሪያል ፓርክ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው የአካባቢው ተወላጆች መካከል ወጣት ማርታ ሰንባቦ እንዳለችው የልብስ ስፌት ዕውቀት ስላልነበራት ስራውን ፈርታው እንደነበር ተናግራለች።

ነገር ግን ከስራው በፊት የተሰጣት የሙያ ስልጠና በራስ መተማመኗን ያሳደገላት ከመሆኑም ባለፈ ከሙያው በምታገኘው ጥቅም እራሷንና ቤተሰቧን መርዳት መቻሏን ተናግራለች።

በፓርኩ በመጀመሪያው ዙር የተገነቡ 37 ሼዶች ለባለሀብት በመተላለፋቸው 12 ባለሀብቶች ወደ ምርት ስራ ሲገቡ ሌሎቹ በማሽን ተከላና በቅድመ ዝግጅት ሰራ ላይ ይገኛሉ።

ወደ ስራ ከገቡት ውስጥ ስድስቱ ምርታቸውን ለውጪ ገበያ ማቅረብ የቻሉ ሲሆን ባጠቃላይ ስራ የጀመሩ አስራ ሁለት የውጪ ካምፓኒዎች ከ6 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የስራ እድል መፍጠራቸውም በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር ሰኔ 4/2009 በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በህዝብ ንቅናቄ የተካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የአፈር ክለት መጠንን  በሄክታር ወደ 34 ቶን ዝቅ ማድረግ እንዳስቻለ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

 በአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ድርጅት በተመረጡ 34 ተፋሰሶች የተካሄደው ጥናት በሚመለከታቸው አካላት ተገምግሟል።

የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው እንግዳየሁ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት ባለፉት ሰባት ዓመታት በተካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የአፈር ክለት መጠንን በመቀነስ ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል፡፡

በ34 የተመረጡ ተፋሰሶች ላለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው ጥናት የአፈር ክለት መጠን በሄክታር ከነበረበት 77 ቶን ወደ 34 ቶን ዝቅ ማለቱ ተረጋግጧል።

የአፈር ክለት መጠን መቀነሱን ተከትሎ የአፈር ለምነት በመጨመሩም ቀደም ሲል በሄክታር ይገኝ ከነበረው ምርት የዘጠኝ ኩንታል ጭማሪ እንዲኖር ማድረግ ተችሏል።

በተጨማሪም በተፋሰሶቹ ውስጥ የደን ሽፋኑ 30 በመቶ እንዲደርስ አስችሏል።

ጥናቱን ያካሄደው የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ውብነህ በለጠ በበኩላቸው በጥናቱ አንድ ሺህ 466 ሄክታር መሬት መሸፈኑን ገልፀዋል፡፡

በጥናቱ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች ቢኖሩም ህብረተሰቡ በልማት ስራው የሚሳተፈውን ያህል ልማቱ የእኔ ነው ብሎ ያለመጠበቅ ችግር በጥናቱ መለየቱን ገልፀዋል።

ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የተፈጥሮ ሃብት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር እንየው አድጎ በበኩላቸው የተፋሰስ ልማት ስራውን በምርምር ለማገዝ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

''ጥናቱ እንደየስነ-ምህዳሩ ተስማሚ የሆኑና የተሻለ ጥቅም የሚሰጡ የደን ዝርያዎችን በምርምር እየለየን እንድናቀርብ ያግዛል'' ያሉት ደግሞ ከአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደን ተመራማሪ ዶክተር ምናለ ወንዴ ናቸው።

በደብረታቦር ከተማ ላለፉት ሁለት ቀናት በተካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ አውደ ጥናት ላይ በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከምርምር፣ ከግብርናና ሌሎች ተቋማት የተጋበዙ ምሁራንና ባለሙያዎች ታሳታፊ ሆነዋል።

Published in አካባቢ

አዳማ ሰኔ 4/2009 በአገልግሎት አሰጣጥ ወቅት የሚታዩ ችግሮች  ከአመለካከት፣ ከክህሎትና ከተጠያቂነት ማነስ ጋር ተያይዞ የሚመነጩ መሆናቸውን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ያካሄደው አገር አቀፍ ጥናት አመለከተ ።

የጥናቱ ግኝት ትናንት በቢሾፍቱ ከተማ ከፌዴራል፣ ከክልልና ከከተማ አስተዳደር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት ቀርቦ  ውይይት ተደርጎበታል ።

በህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም  የቁጥጥርና ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አዱኛ ሙሉነህ እንደገለፁት ጥናቱ በፌዴራል መስሪያ ቤቶች ፣ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉልና በአፋር ክልሎች በሚገኙ የመንግስትና የልማት ድርጅቶች የሚያገለግሉ ሰራተኞችን ያካተተ ነው ።

በጥናቱ መሰረት የአገልግሎት አሰጣጡ ዋነኛ ችግሮች የአመለካከት፣ የክህሎትና የተጠያቂነት ማነስ ሲሆኑ ከአደረጃጀትና ከመዋቅር ጋር የተያየዙ ችግሮችም ተጠቃሾች ናቸው ።

የጥናቱ ግኝት እንዳመለከተው ችግሮቹ ከምቹ የስራ አካባቢ አለመኖር ፣ ከአገልጋይነት መንፈስ መጓደልና ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡

እንዲሁም ከአደረጃጀትና ከመዋቅር ችግር፣ ከእውቀት፣  ከክህሎትና ልምድ ማነስ፣ ከአሰራርና የህግ ክፍተት፣ ከቅንጅታዊ አሰራር መጓደልና ከኪራይ ሰብሳቢነት ችግር የመነጩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የስራ ባህል ያለመዳበር ፣ በመብት ላይ ብቻ በማተኮር ግዴታዎችን አለመወጣት፣ ያልተገባ ጥቅም መፈለግ፣ ሙሉ ጊዜን በስራ ላይ አውሎ  በጥረት ከማደግ ይልቅ ጥቂት ሰርቶ በአቋራጭ ለመክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ  መኖሩ በጥናቱ ተረጋግጧል ።

ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር፣ ከፍትሃዊነት፣ በዘመድ አዝማድና በመሳሳብ ላይ የተመሰረተ ሹመት የአገልጋይነት መንፈሱን እያዳከመው እንደመጣም ጥናቱ ያትታል ።

ስራውን አክብሮ የሚሰራውም ሆነ የማይሰራው በትክክል መዝኖ  ጠንካራ ሰራተኞችን የሚለይበት የማትጊያ ስርዓት አለመኖርም  በችግርነት ተነሰቷል ።

በፌዴራልና በአዲስ አበባ ደረጃ 60 ከመቶ የሚሆኑ  መስሪያ ቤቶች የራሳቸው ቢሮ የላቸውም ያለው ጥናቱ ለቢሮ ኪራይ ባለፈው ዓመት  500 ሚሊዮን ብር ዘንድሮ ደግሞ 800 ሚሊዮን ብር መከፈሉን ገልጿል፡፡

ገንዘቡ በበጀት ላይ ከሚያስከትለው እጥረት በተጨማሪ መስሪያ ቤቶች በርካታ ህንፃዎች ሊሰሩበት ይችሉ እንደነበር ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው በሲቪል ሰርቪሱና በመንግስት የልማት ድርጀቶች ውስጥ የሚገኙ ሰራተኞች ከአገልጋይነት ይልቅ  የተገልጋይነት አስተሳሰብ ሲያመዝንበት ይስተዋላል ።

''የጥናቱ ዓላማም በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በሰራተኛው ዘንድ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት መንስኤዎቹንና የመፍትሄ ሃሳቦችን የያዘ ሰነድ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው'' ብለዋል ።

15 የጥናት ግኝቶችንና 110 ገፅ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘው የጥናት ሰነድ ለውይይት ቀርቦ በምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች ተቀባይነት አግኝቷል።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የምክር ቤት ውሳኔዎች አፈፃፀምና የህዝብ አቤቱታ ማስተናገጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬተር አቶ ሽዋንግዛው ማሞ በሰጡት አስተያየት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር የህዝብ ቅሬታን እያስከተለ በመሆኑ በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የህዝብ ቅሬታ የሚያስተናግድ አደረጃጀት መፈጠሩን ተናግረዋል ።

ጥናቱ 3ሺህ 441 የፅሁፍ መጠይቆች ፣ 195 የቡድን ውይይቶች ፣ 434  ቃል መጠይቆችና 73 ምልከታዎችን በማካሄድ የተሟላ መረጃዎች  ሰብስቦ የተነተነ ነው ተብሏል ።

ከአገልግሎት አሰጣጡ በተጨማሪ በመሬት ልማትና አስተዳደር ላይም ምርመራና ጥናት አካሔዷል ።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 4/2009 "እሬቶ" የሚል ስያሜ የተሰጠውና በተማሪ  ዮሴፍ ከተማ  የተጻፈው አዲስ ልብ ወለድ መጽሐፍ  ዛሬ በሀገር ፍቅር ቴያትር ተመርቋል።

የመጽሓፉ ደራሲ ዮሴፍ ከተማ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዓመት ተመራቂ ተማሪ ነው።

ይሄው የደራሲው የበኩር ስራ የሆነው "እሬቶ" የተሰኘው መጽሐፍ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኃይማኖታዊና የእለት ከዕለት ገጠመኞችን የሚዳስስ መሆኑ ታውቋል።

284 ገጾች ያሉትና በ65 ብር ለአንባቢያን የቀረበው ይህ መጽሃፍ የታሪክ፣ ወቅታዊ ኩነቶችንና ሌሎች አገራዊ ጉዳዩችን ዳሷል።

"እሬቶ" ከሰማይ ቁልቁል የወደቀ ኮከብን ለመጥራት የተሰጠ ስያሜ ሲሆን፤ሥርወ ቃሉ "መራር እሬት" ማለት እንደሆነ ደራሲው ተናግሯል።

በዩንቨርሲቲው የትያትርና ኪነ ጥበብ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ "ከኃይሉ ጸጋዬ ቀጥሎ  ተማሪ ሆኖ መጽሐፍ ሲያሳትም የማውቀው  ዮሴፍ ከተማን ነው" በማለት ጸሃፊውን አበረታተውታል።

"እውነትም አሁን ላይ ያሉ ወጣቶች ቀደም ብለው በወጣትነታቸው መጀመሪያ ዘመን ከአባቶቻቸው የወረሱትን እውቀት አዳብረው የተሻለ ስራ መስራት እንደሚችሉ ይህ በትምህርት ላይ እያለ መጽሐፍ የጻፈው ደራሲ ማሳያ ነው" ብለዋል ተባባሪ ፕሮፌሰር ነብዩ።

"መጽሐፍ መጻፍ ልጅ እንደ መውለድ ነው" ያለችው ደራሲት እምወድሽ በቀለ በበኩሏ ደራሲውን "በስነ ጽሑፉ ዘርፍ ተተኪ ወጣት" ብላዋለች።

በመጽሐፍ ምረቃ ላይ የደራሲው ወዳጆች፣ መምህራንና የሙያ ባልደረቦቹ ተገኝተዋል። በትምህርት ላይ ሆኖ መጽሐፍ ማሳተም በመቻሉ "በርታ ፤እደግ ተመንደግ" ብለውታል።

 

Published in ማህበራዊ

ሃላባ 4/2009 በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሃላባ ልዩ ወረዳና የወላይታ ሶዶ ሁለገብ የእርሻ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ስራ ጀመሩ።

የማዕከላቱን ስራ መጀመር ያስታወቀው የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ  ሲሆን፤ በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልል የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

ማዕከላቱ የተገነቡት ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ የእርሻ መሳሪዎች፣ የእንስሳት መድሃኒትና የፀረ ተባይ ኬሚካሎችን በማቅረብ ለአርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማከፋፈል ነው፡፡ ይህም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ታምኖበታል፡፡

ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው እነዚህ ማዕከላት ከ10 ሺ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሲሆን፤ ማዕከላቱ ተሰርተው የተጠናቀቁት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

ማዕከላቱ በኤጀንሲው መሪ ተዋናይነት፣ በእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴርና በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ በጥምረት በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID ) የገንዘብ ድጋፍና ሲ.ኤን.ኤፍ.ኤ (CNFA) በተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት የቴክኒክ እገዛ መገንባታቸው ታውቋል፡፡

የኤጀንሲው የንግድ አገልግሎት ማዕከል ማስፋፊያ አስተባባሪ አቶ ግዛቸው ሲሳይ እንደሚሉት፤ የአገሪቷ የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርና በግብዓት እጥረትና  ውድነት ምክንያት  ችግሮች ሲስተዋሉ ቆይተዋል።

በዚህም ኤጀንሲው ከተለያዩ ባለሃብቶችና ማህበራት ጋር በመነጋገር በተመጣጣኝ ዋጋ በወቅቱ የማቅረብ ስራውን ጀምሯል፡፡

ችግሮቹን ለማስቀረትም 20  የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በደቡብ፣ በአማራ፣ በትግራይና በኦሮሚያ ክልሎች ለማስገንባት አቅዶ የሃላባንና ሶዶን ጨምሮ ከዚህ ቀደም አገልግሎት መስጠት የጀመሩትን የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል ባኮና ባሌ  አራቱ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡

በዚህ ወር መጨረሻ ድረስ ስምንት ተጨማሪ ተቋማት ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ነው አቶ ግዛው የተናገሩት፡፡

ማዕከላቱ የሚገነቡት አርሶ አደሮች በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ላይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ግዛው፤ ከዚህ ቀደም ሩቅ ቦታ በመሄድ የሚያባክኑትን ጊዜና ወጪ በመቀነስ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ነው የተናገሩት፡፡

ማዕከላቱ በተጨማሪ አርሶ አደሮችን የማሰልጠንና የማማከር ስራም እንደሚያከናውኑ ታውቋል፡፡

አጠቃላይ የታቀዱት 20 አገልግሎት መስጫ ተቋማት ስራ ላይ ሲውሉ 100 ሺ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ  ያደርጋሉ፤ ለ210 ባለሙያዎች የስራ ዕድልይፈጥራሉ፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 4/2009 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ21ኛ ጊዜ በተካሄደው ፔፕሲ አዲስ አበባ የዱላ ቅብብል ማራቶን አሸናፊ ሆነ ።

በአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚካሄደው ይኽው ውድድር ከ16 ክለቦች የተውጣጡ 127 አትሌቶች የተሳተፉበት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል ።

በዚሁ ውድድር ኢትዮ­ጵያ ንግድ ባንክ ቀዳሚ በመሆን የዋንጫ አሸናፊ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።

በተመሳሳይ ባለፈው ዓመትም እነዚሁ ክለቦች እንደቅደም ተከተላቸው አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ውድድሩን መጨረሳቸው ይታወሳል።

በዘንድሮው ውድድር የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ሶስተኛ በመሆን የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።

ውድድሩ ወንድ እና ሴት አትሌቶች በመቀላቀል የተካሄደ ሲሆን፤ ሴቶች 17 ኪሎ ሜትር ሲሸፍኑ ወንዶች ደግሞ 25 ኪሎ ሜትሩን ሮጠዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌት ይከበር ቢያብል እንዳለው፤ ወድድሩ ተተኪ አትሌቶችን ለማግኘት እድል ይፈጥራል።

የክለቡ አትሌቶች ጠንካራ ስራ በመስራታቸው አሸናፊ መሆን እንዳስቻላቸው ገልጾ፤ በቀጣይ በውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆን ሌሎች ክለቦችም መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግሯል።

የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ባለሙያ አቶ አንዱዓለም ያየህይራድ በበኩላቸው፤ በውድድሩ የክለቦች ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብ  ታዋቂ አትሌቶች ከውጭ ውድድሮች ይልቅ ለሃገር ውስጥ ውድድሮችና ክለቡን ለማገልገል ቅድሚያ በመስጠታቸው በዓመቱ ለአሸናፊነት መብቃቱን ገልጸዋል።

ሌሎች ክለቦችም የውድድሩ ፉክክር እንዲጨምርና እንዲደምቅ ታዋቂ አትሌቶች ለአገር ውስጥ ውድድሮች ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

Published in ስፖርት
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን