×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Saturday, 10 June 2017

ደሴ ሰኔ3/2009 በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ህጻናትን ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ  የህብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አመለከቱ።

ከዞንና ከወረዳ የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች ፣የመንግታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮችና  የኃይማኖት አባቶች የተሳተፉበት የአፍሪካ የህጻናት  ቀን ትናንት በፓናል ውይይት ተከብሯል።

ዋና አስተዳዳሪው  አቶ እጅጉ መላኬ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ቀኑ የሚከበረው  የሕጻናት መብትና ደህንነትን ለማስከበር ትኩረት እንዲሰጠብት ለማስገንዘብ  ነው።

በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ህጻናትን ለመታደግ የህብረተሰቡ ቅንጅታዊ ተሳትፎ ወሳኝ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወላጆቻቸውን በተለያዩ ምክንያቶች ያጡና ለችግር የተጋለጡ ሕጻናትን በማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና ክብካቤ ጥምረት በኩል  ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ  በተናጠል፣ በቡድንና ተቋማዊ በሆነ መንገድ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት ትኩረት ሰጥቶ ከሚንቀሳቀስባቸው ዘርፎች  መካከል የሕጻናት መብትና ደህንነትን  እንዲከበር የማድረግ ስራ አንዱ መሆኑንም  አቶ እጅጉ ጠቁመዋል::

የህጻናት መብቶችና ደህንነቶች እንዲከበሩ በማህበረሰቡ ውስጥ ግንዛቤ እንዲኖርና ለተፈፃሚነቱ  ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የዞኑ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰሉ ብርሃኑ በበኩላቸው " የዚህ ዓመት በዓል ስናከብር በዞኑ ውስጥ ምን ያህል ህጻናት ለከፋ ችግር እንደተጋለጡ መረጃ በማሰባሰብና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ነው” ብለዋል።

እስከአሁን በዞኑ  ከ18 ሺህ በላይ ህጻናት በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ መለየታቸውን  ጠቅሰው ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የተለያየ ድጋፍ እየተደረገላችው መሆኑንም ገልጸዋል።

ከእነዚህ ውስጥ በተለያየ ምክንያት ለጎዳና ተዳዳሪነት ተጋልጠው የነበሩ 185 የሚሆኑ ህጻናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል እንደኃላፊዋ ገለጻ።

በሌላ መልኩ ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናት በጉዲ ፍቻ ለአሳዳጊዎች ለመስጠትም የመረጃ ማሰባሰብና የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እየተካሂደ መሆኑም አመልክተዋል።

የኮምቦልቻ  ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ህጻናት፣ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ባልደረባ  ወይዘሮ አብነት ብስራት እንዳሉት በከተማዋ ከሁለት ሺህ በላይ ለችግር የተጋለጡ ህጻናት ይገኛሉ።

የህፃናትን መብትና ደህንነት ለማስከበር ህብረተሰቡና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት  ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በዓሉ ሰኔ 9/2009 ዓ.ም  በአፍሪካ ለ27 ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ26 ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ " በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህጻናትን ለመደገፍ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው" በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል።

 

Published in ማህበራዊ

ባህርዳር ሰኔ 3/2009 ህጋዊ የገንዘብ ቼኮችን በማሳሳት   ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ያጭበረበረው ግለሰብና  ሁለት ተባባሪዎቹ በእስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን የአማራ ክልል የስነ -ምግባርና ፀረ -ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ፀሐይ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለፁት ተከሳሾቹ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ባከናወኑት የማጭበርበር ተግባር እያንዳንዳቸው ከ9 እስከ 14 ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጥተዋል ። 

የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ሾፌር የነበረው ተከሳሽ ደጀኔ ተባባል ለሚያሽከረክረው  መኪና የእጥበትና የቅባት መቀየሪያ ያወጣው  450 ብር እንዲወራረድለት በግንቦት ወር 2006 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ጊዜ ይጠይቃል።

ግለሰቡ ባቀረበው ማመልከቻ መሰረት ሰርቪስ ያደረገበት እያንዳንዳቸው 450 ብር የያዙ ሦስት የገንዘብ ቼኮችን በማፃፍ በድምሩ 1ሺህ 350 ብር በህጋዊ ቼክ እንዲከፈለው ተጽፎለታል።

ይሁን እንጂ በተሰጠው ህጋዊ ቼኮች ላይ 450 ከሚለው ጎን በፊደል "ሺህ" በመጨመር እንዲሁም በቁጥር 3 ዜሮዎችን በማከል 450 ብር የነበረውን 450 ሺህ ብር በማድረግ የማጭበርበር ተግባር መፈፀሙ ተደርሶበታል።

በዚህም ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግሽ አባይ ቅርንጫፍ በተፃፈው ቼክ መሰረት 1ሺህ 350 ብር ማውጣት ሲገባው ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ እንዳወጣ መረጋገጡን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

"በዚህም ግለሰቡ በህዝብና በመንግስት ሃብት ላይ ሙስና ፈፅሞ ተገኝቷል " ብለዋል ።

ተከሳሹ የማይገባ ብልፅግና ለማግኘት በማሰብ  በፈፀመው የማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በ14 ዓመት ፅኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር እንዲቀጣ በፍርድ ቤት የተወሰነበት መሆኑን አመልክተዋል።

በግለሰቡ ስም በተለያዩ ባንኮች ተቀምጦ የተገኘ 923 ሺህ ብርና አንድ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ለመንግስት በውርስ ገቢ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግሽ አባይ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን የሆኑት ተከሳሽ ቸርነት ይታየውና በዚሁ ባንክ የደንበኞች አገልግሎት ስራ አስኪያጅ ተከሳሽ አደራጀው ፈንታሁን የባንኩን አሰራር በጣሰ መንገድ ክፍያ እንዲፈፀም በማድረጋቸው  በተባባሪነት ተከሰው ተቀጥተዋል።

ተከሳሾቹ በባንክ ቤቱ አሰራር መሰረት በቼክ ክፍያ ሲከናወን የገንዘቡ መጠን በፊደልና በአሃዝ በትክክል መፃፉን በማረጋገጥ ክፍያ እንዲፈፀም ማዘዝና ክፍያ መፈፀም የሚለውን ህግ ጥሰት ተገኝቶባቸዋል።

በዚህም ግለሰቦቹ በግልፅ አጠራጣሪ ሁኔታ እየተመለከቱ የይከፈል ትዕዛዝ በማስተላለፋቸው ባጠፉት ጥፋት አያንዳንዳቸው የ9 ዓመት ፅኑ እስራትና የ10 ሺህ ብር ቅጣት ተወስኖባቸዋል።

እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን የሙስና ወንጀል እንዲከላከሉ እድል ቢሰጣቸውም ማስተባበል ባለመቻላቸው የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት የቅጣት ወሳኔውን አስተላልፎባቸዋል ።

በአማራ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በህዝብና በመንግስት ሃብትና ንብረት ሙስና ፈፅመው በተገኙ 211 ተከሳሾች  ከሦስት ወር እስከ 14 ዓመት በሚደርስ እስራትና በገንዘብ መቀጣታቸው ታውቋል፡፡

 

 

 

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ ሰኔ 3/2009 በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን የብሄረሰቦች ማንነት መገለጫ የሆኑ ተፈጥሯዊና ባህላዊ እሴቶችን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ  ተጠባባቂ ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ፡፡

አራተኛው የኮሬ ብሔረሰብ የባህል ቋንቋና ታሪክ ሲምፖዝየም ከትናንት በስትያ በአማሮ ኬሌ ከተማ ተካሂዷል፡፡

ተጠባባቂ ዋና አስተዳዳሪው አቶ አልጌዬ ጅሎ እንዳሉት ብሔር ብሔረሰቦች ያላቸውን ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ እሴቶች በማሳደግ ለልማት ለማዋል  እየተሰራ ነው፡፡

ባለፉት ሀያ ስድስት ዓመታት ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ይሁንና ዞኑ ስምንት ብሔረሰቦች የሚገኙበት እንደመሆኑ የብሄረሰቦቹን እሴት ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት ቢከናወኑም  ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ከሰጣቸው መብት አንጻር የተሰሩት ተግባራት በቂ  እንዳልሆኑ ነው አቶ አልጌዬ ያመለከቱት ።

"የኮሬ ብሔረሰብም ከዚህ አንጻር ሲታይ ቋንቋውን፣ ባህሉንና ታሪኩን ለማሳደግ እያከናወነ ያለው ጅምር ስራ ቢኖርም በቂ አይደለም" ብለዋል፡፡

የአማሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሰማ ታምራት በበኩላቸው በኮሬ ብሔረሰብ ህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት በማጠናከር በልማት ላይ የጋራ አስተሳሰብ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን  ተናግረዋል ።

ለዚህም ብሔረሰቡ ያለውን ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ እሴት በማጥናት ጥቅም ላይ ለማዋል እየተካሂደ ያለውን ስራ ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ሶስት ሲምፖዚየሞች በተደረሰ ስምምነት መሰረት ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ያሉ ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዲላ መምህራን ኮሌጅ ዘንድሮ በሚመረቁ የዲፕሎማ መምህራን አማካኝነት በመጪው ዓመት ትምህርቱ በሁሉም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንደሚደረግ አመላክተዋል ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አወቀ አምዛዬ እንዳሉት ብሔር፣ ብሔረሰቦች ያላቸውን ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ እሴት መሰረት ያደረገ ልማት በህዝቦች መካከል ያለውን ትስስር ያጠናክራል፡፡

የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየሞች መዘጋጀታቸው ቋንቋና ባህልን ከማሳደግ ባለፈ በርካታ ፋይዳ እንዳላቸው ገልፀዋል።

"የብሄረሰቡ ምሁራንና የታሪክ ባለሙያዎች ያላቸውን መረጃዎች በማስቀመጥና መጽሀፍትን በማዘጋጀት ልጆች እንዲያውቁና በትምህርት ቤቶች በባህላቸው እንዲቀረጹ ማድረግ ይገባቸዋል " ብለዋል ።

በሲምፖዚየሙ በብሄረሰቡ ምሁራን የተጻፈ የኮሬ ብሔረሰብ ባህላዊ የህግ ስርዓት ላይ ያተኮረ መጽሐፍና የኮረቴ አማርኛ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ተመርቋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ነቀምቴ ሰኔ 3/2009 የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር በ19 ማህበራት ለተደራጁ  መኖሪያ ቤት የሌላቸው ግለሰቦች  የቤት መስሪያ ቦታ ሰጠ፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንት አቶ ለማ መገርሳ  በቦታው ተገኝተው ለግለሰቦቹ የቤት መስሪያ ቦታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት አስረክበዋል፡፡

በከተማው ለሚገነባው የማንጎ እና ቲማቲም ማቀነባበሪያ ፋብሪካም የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡

ፕሬዝደንቱ  የክልሉ መንግስት በማህበር ተደራጅተው ለቤት መስሪያው ከሚያስፈልጋቸው ወጪ  አስር በመቶ የቆጠቡ ሰዎችን  የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አስመራ እጃራ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የክልሉ መንግስት መኖሪያ ቤት የሌላቸውን  የቤት ባለቤት ለማድረግ ባወጣው መመሪያና ደንብ መሰረት  ከተማ አስተዳደሩም ተግባራዊ እያደረገ ነው።

በ19 ማህበራት የተደራጁት 262 ግለሰቦች  ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ መቆጠባቸውንም ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በነቀምቴ ከተማ ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ለሚገነባው የማንጎ እና የቲማቲም  ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት አቶ ለማ መገርሳ እንደገለጹት ፋብሪካውን መገንባት ያስፈለገው  አከባቢው ማንጎና ቲማቲም አብቃይ በመሆኑ እሴት ጨምሮ ለህብረተሰቡ የተሻለ ጥቅም ለማስገኘት ብሎም የስራ እድል ለማስፋፋት ታስቦ ነው ፡፡

ፋብሪካው በአጭር ጊዜ ወስጥ ተገንብቶ ለአገልግሎት እንዲበቃ የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚከታተለውም ጠቅሰዋል፡፡

 

 

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ሰኔ 3/2009 ብዙሃነትን ማጠናከር  ህዝቦች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ያላቸውን ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

"ብዙሃነትና የባህል ግንባታ"  በሚል ሀሳብ  የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ትናንት ባካሄደው አውደ ጥናት ላይ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ክንደያ ገብረህይወት እንደገለፁት ሀገሪቱ እየተከተለች ያለችው የፌዴራሊዝም ስርዓት ለብዙሃነት በሰጠው እውቅና ህዝቦች ማንነታቸው  ተጠብቆ ለሀገራቸው እድገት በጋራ እንዲተጉ አስችሏቸዋል።

"ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የወከሉ ተማሪዎች በትምህርት ተቋማት ባህል ቋንቋና ሌሎች የጋራ እሴቶችን ለመጠበቅ  የሚያደርጉት ትጋት የዚሁ ማሳያ ነው " ብለዋል ።

በኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ተመራማሪ አቶ ፍስሃ ሃብተጽዮን  " የኢትዮጵያ የፌደሬሽን ትርጓሜና የብዙሃነት እይታ"  በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

በዚሁ ጥናታዊ ጽሁፋቸው የፌዴራሊዝም ስርዓቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች በማንነተቻው ኮርተው ለአገራቸው እድገት በጋራ እንዲሰሩ እንዳስቻላቸው አመልክተዋል፡፡

መንግስት የህዝቦችን ማንነትና አንድነት ለማጠናከር የሚያግዙ ህገ -መንግስትና የተለያዩ የህግ ማእቀፎችን በማውጣት ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

"ብዙሃነትና ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ህዝቦች ያስገኙት ጥቅም "  በሚል ጽሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁር  ዶክተር አሰፋ ፍስሃ በበኩላቸው "ለብዝሀነት የተሰጠው እውቅና  በህዝቦች መካከል ያለውን የባህልና የአኗኗር ሁኔታ አጠናክሯል " ብለዋል።

በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ያላቸው ግንኙነት እንዲጎለብትና በሃገሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ እኩልተሳትፎ እንዲኖራቸው ምቹ መደላድል መፍጠሩንም ጠቅሰዋል።

እንደ ዶክተር አሰፋ ገለፃ በአንድ አገር  ለዘመናት የማይተዋወቁ ህዝቦች በፌዴራል ስርዓቱ ግንኙነታቸው እየተጠናከረ መጥቷል ።

የህዝቦች የማንነትና የብዝሀነት መገለጫ የሆኑ ባህሎችና ቋንቋዎች እውቅና ማግኘታቸው በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነትን ለማምጣት የጎላ ሚና እንዲጫወቱ ማስቻሉን የገለጹት ደግሞ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የስነ- ዜጋና ስነ -ምግባር መምህርት ብርነሽ አፅብሃ ናቸው፡፡

"እኛ የኢትዮጵያ ህዝቦች  ባህሎቻችንን ለአገራዊ እድገት በሚጠቅም መልኩ ማጎልበት ይኖርብናል " ብለዋል መምህርት ብርነሽ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ፀጋይ በርሄ "እንዲህ ያለው አውደጥናት በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ለማጠናከር የሚረዳ በመሆኑ ወደ ፖለቲካ አመራሩና ህብረተሰቡ መድረስ ይገባዋል"ብለዋል።

በአውደ ጥናቱ የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን በማንነትና በብዙሀነት እይታ፣ብዙሃነትና ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ህዝቦች ያስገኙት ጥቅም፣ብዙሃነት ለአገር ገፅታ ግንባታ ያበረከተው አስተዋፅኦና በአገሪቱ የሰላም ግንባታ ያሉት ተግዳሮቶችና መፍትሄዎቻቸው የሚሉ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ከክልሉ ምክር ቤቶች፣  ከሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከመቀሌና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲዎች የተወጣጡ ከ300 በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል።

 

 

Published in ፖለቲካ

ሀዋሳ ሰኔ 3/2009 ህብረት ስራ ማህበራት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት መሰረት በመጣል የህዳሴውን ጉዞ እንደሚደግፉ  የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

"የህብረት ስራ ማህበራት ሁሉ አቀፍ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣሉ" በሚል መሪ ሀሳብ ዘጠነኛው ሀገር አቀፍ የአለም ህብረት ስራ ቀን በሃዋሳ ከተማ እየተከበረ ነው፡፡

የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት  ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ እንደገለፁት የህብረት ስራ ማህበራት የሚያከናውኗቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት መሰረት እየሆኑ ነው ።

ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ በግብርና ምርት ማቀነባበር ዘርፍ የማህበራቱ ተሳትፎ እያደገ መጥቷል።

"ማህበራቱ በግብርና ምርቶች ላይ እሴት እየጨመሩ ለሀገር ውስጥና ውጭ ገበያ እያቀረቡ ነው " ብለዋል ።

በከተሞች ገበያን  ከማረጋጋት ጎን ለጎን በብድርና ቁጠባ አገልግሎት ያላቸው ተሳትፎ ኢንቨስትመንትን በመደገፍ ለኢኮኖሚ እድገቱ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

ለዚህም በርካታ የብድርና ቁጠባ ህብረት ስራ ማህበራት መፈጠራቸው ማሳያ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ካባ ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ ያደረጉና ሕይወታቸውን የለወጡ ህብረት ስራ ማህበራት መኖራቸንም ጠቁመዋል ።

አባላቶቻቸው የሚፈልጉትን የግብርናና የፋብሪካ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ምርታማነትን በመጨመር ረገድ ፋይዳ ያለው ተግባር እያከናወኑ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶክተር ካባ ገለፃ ማህበራቱ በተሰማሩባቸው ዘርፎች ሁሉ በርካታ የስራ እድሎችን መፍጠራቸው ሌላው በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸውን ጉልህ ሚና ማሳያ ነው ።

ማህበራቱ ለኢኮኖሚ እድገት እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የመንግስት ድጋፍ እንደማይለያቸውም አረጋግጠዋል ።

የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው  ህብረት ስራ ማህበራት ለአባላት ከሚሰጡት ጠቀሜታ በሻገር በሀገራዊ ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ኡስማን እንዳሉት የህብረት ስራ ቀን ዓላማው ገጠሩን ከከተማው የሚያስተሳስሩ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራትን ከሸማቹና ማህበራት ትብብራቸውን ማጠናከርና ተሞክሮዎቻቸውን እንዲለዋወጡ ለማድረግ ነው።

ከወላይታ ዞን  የሲቋ ገንዘብ ቁጠባና ብድር ዩኒየን  ስራ አስኪያጂ አቶ ተስፋዬ ኩማሎ በሰጡት አስተያየት ዩኒየኑ 19 ሺህ 885 ለሚሆኑ አባላት ለተሻለ ኑሮ እንዲበቁ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ የዩንየኑ ካፒታል 3 ሚሊየን ብር ደርሷል።

የህብረት ስራ ማህበራት ቀን በአለም ለ95ኛ እና በኢትዮጵያ ደረጃ ደግሞ ለዘጠነኛ ጊዜ እየተከበረ ነው ።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ3/2009 ዘመናዊ ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ አስቆጥሯል። ያም ሆኖ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ውድድሮች የምትሳተፍባቸውና ውጤት የምታስመዘግብባቸው የስፖርት ዓይነቶች ውስን ናቸው።

ዕድገቱም ቢሆን በሚፈለገው ደረጃ አይደለም፤ የዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የስፖርቱ አደረጃጀትና አመራር ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው አለመደረጉ ነው።

ይህን ችግር ለመቅረፍ መንግስት በ1990 ዓ.ም ስፖርቱ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረውና በህዝብ እንዲተዳደር ለማድረግ የስፖርት ፓሊሲ አውጥቷል።

ፖሊሲው ስፖርቱ ከመንግስት ድጎማ ተላቆ በራሱ የገቢ ምንጭ እንዲንቀሳቀስ የሚያግዝ ነበር።

ሆኖም አሁንም ድረስ አብዛኞቹ ክለቦችና የስፖርት ማህበራት የሚተዳደሩት በመንግስት ድጎማ ነው፤ መጠነኛ ለውጥ በሚታይባቸው የእግር ኳስ ክለቦች እንኳን አብዛኛዎቹ በመንግስት ድጋፍ የሚተዳደሩ ናቸው። 

ለመሆኑ መንግስት የሚሰጠው ድጎማ እስከ መቼ  ይቀጥላል? ሲል የኢዜአ ሪፖርተር ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ርስቱ ይርዳ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ሚኒስትር ርስቱ እንደሚሉት ህብረተሰቡ በስፖርቱ ልማት እያደረገ ያለው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም በሚፈለገው ደረጃ አይደለም። 

በተለይም ክለቦችና የማዘውተሪያ ስፍራዎች በተወሰነ ደረጃ በባለሀብቶች እየተደገፉና እየተሰሩ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ስፖርቱ ሙሉ በሙሉ በራሱ ገቢ እንዲንቀሳቀስ ግን በቅድሚያ የስፖርት መሰረተ ልማቶች በመስራት ህዝባዊ አደረጃጀት እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። 

"በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በግል ኢንቨስትመንት እንዲንቀሳቀስ የምናደርግበት ደረጃ ላይ አይደለንም" ሲሉም አክለዋል።

ይህ አቅም እስከሚፈጠር ድረስ መንግስት ስታዲየምና የስልጠና ማዕከላትን በመገንባት የስፖርት ስልጠናዎች መስጠት አለበት ብለዋል።

የስፖርት መሰረተ ልማቶች ከተስፋፉና ክለቦች ህዝባዊ አደረጃጃት እየያዙ ከመጡ በአጭር ጊዜ ሳይሆን በረጅም ጊዜ ራሳቸውን የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም አብራርተዋል።

ለውጡ ከአገሪቷ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተያይዞ የሚመጣ በመሆኑ ጊዜ መውሰዱ እንደማይቀር በመጠቆም።

ሆኖም የአገሪቱ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ በመሆኑ ስፖርቱም ከመንግስት ድጎማ የሚወጣበት ጊዜ ሊያጥር እንደሚችል ነው ሚኒስትር ርስቱ የተናገሩት።

"የአገሪቷ ኢኮኖሚ ሲያድግ ስፖርትም ከመንግስት የኢኮኖሚ ድጋፍ ተላቆ መውጣቱ እይቀርም፤ እስካሁን ግን አካሄዱ ጤናማ ነው" ብለዋል።

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ  ሰኔ 3/2009 የኢትዮጵያ መንግሥት ህዝቡን በማስተባበር ድርቁን ለመቋቋም እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለጸ።

ድርጅቱ የሚያስተባብረው የልዑካን ቡድን ዛሬ ከብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ጋር በኢትዮጵያ የድርቅ ሁኔታ ላይ ተወያይቷል።

ከገልፍ አገራት፣ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከመንግስታቱ ድርጅትና ከአፍሪካ ልማት ባንክ የተውጣጣው የልዑካን ቡድን ''ለአፍሪካ ቀንድ አጋርነት'' በሚል መሪ ሃሳብ በድርቅ የተጎዱ የአፍሪካ ቀንድ አገራትን እየጎበኘ ነው።  

ቡድኑ ጉብኝቱን በኢትዮጵያ የጀመረ ሲሆን ሶማሊያ፣ ኬንያና ደቡብ ሱዳን በመርኃ ግብሩ መሰረት በቀጣይ የሚጎበኙ አገራት ናቸው።

የጉብኝቱ ዓላማ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መልዕክት ለማስተላለፍና በድርቁ የተጎዱ የአፍሪካ ቀንድ አገራትን በዘላቂነት ለማቋቋም ኃብት ማሰባሰብ ነው።  

በዚሁ መሰረት ልዑኩ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን የድርቅ ተጎጂዎችን የጎበኘ ሲሆን እየተደረገ ያለውን ሰብዓዊ ድጋፍ ተመልክቷል።  

ቡድኑ በኢትዮጵያ ቆይታውም ከአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር የተወያየ ሲሆን በኢትዮጵያ ያለውን ችግር እንዲያውቅ ተደርጓል።

የልዑካን ቡድኑ መሪና የመንግሥታቱ ድርጀት ዋና ጸሃፊ የሰብዓዊ ድጋፍ ልዩ መልዕክተኛ ዶክተር አህመድ አልመሬይኪ እንደገለጹት ቡድኑ በኢትዮጵያ ድርቁ ያጋጠመበት አካባቢ በመሄድ ተጎጂዎቹ ያሉበትን ሁኔታና እየተደረገላቸው ያለውን ድጋፍ ተመልክቷል። 

የጉብኝቱ ዓላማም ለጋሾችና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን በአካል በማየት ያለውን ሁኔታ እንዲረዱ በማድረግ በቀጣይ እንዴት መደገፍ እንደሚችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት መሆኑን ተናግረዋል።  

በጉብኝቱም ለጋሽ ድርጅቶችና አገራት ድጋፍ ለማድረግ ፍቃደኛ ሆነዋል ብለዋል። 

''ድርቁን ለመቋቋም የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ ከአፍሪካ ህብረትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሚኖራቸው ድጋፍ ዙሪያ ለጋሾችን ለማወያየት መርኃ ግብር ተቀርጿል'' ብለዋል።  

የኢትዮጵያ መንግሥት ህዝቡን በማስተባበር የዜጎቹን ህይወት ለመታደግ እያደረገ ያለው ጥረት ምስጋና የሚያስቸረው መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር አህመድ ጥረቱን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲደግፍ የማድረጉ ተግባር እንደሚጠናከር አረጋግጠዋል።   

የብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በበኩላቸው ድርቁን ለመቋቋም እየተደረገ ስላለው ጥረትና ስለተገኙ ውጤቶች  ለቡድኑ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን እየተጫወተች ካለው ሚና ባሻገር ከ830 ሺህ በላይ ስደተኞችን ተቀብላ ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።

''ኢትዮጵያ መሰል አሁጉራዊ ኃላፊነቷን በአግባቡ እንድትወጣ ኢኮኖሚዋ የተረጋጋ ሊሆን ይገባል'' ያሉት ኮሚሽነሩ በዚህ በኩል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። 

ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የክልል ሴክተር መስሪያ ቤቶችና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የተውጣጣ 19 አባላት ያለው ቡድን ተቋቁሞ በሰብል አብቃይና በአርብቶ አደር አካባቢዎች መሰማራቱን ተናግረዋል።

''ቡድኑ በሰብል አብቃይ አካባቢዎች 15፣ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ደግሞ 21 ቀናት በመቆየት ዶክመንት እንዲዘጋጅ ይደረጋል'' ያሉት አቶ ምትኩ ከመንግስታቱ ድርጅት ጋር በመተባበር በተሰባሰበው መረጃ መሰረት ድጋፍ የማድረግ እንቅስቃሴ ይካሄዳል ብለዋል። 

በአሁኑ ወቅት በድርቁ 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች ተጎጂ ሲሆኑ እነዚህን ለማቋቋም ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል። 

እስካሁንም ክልሎችን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ከኀብረተሰቡና ከባለኃብቶች 200 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኃብት በማሰባሰብ ለተረጂዎች ድጋፍ አድርጓል።

ከለጋሾች 365 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ መሆኑንና ለተረጂዎች ሙሉ ድጋፍ ለመስጠት 600 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

 

 

 

Published in ማህበራዊ

ጎባ ሰኔ 3/2009 ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓትን በጥናትና ምርምር በማጎልበት ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንደለበት ተመለከተ፡፡

የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር " ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት በኢትዮጵያ ! " በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀውን ሶስተኛ ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት ዛሬ በባሌ ጎባ ተጀምሯል፡፡

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ ተካ እንዳሉት የአውደ ጥናቱ  ዓላማ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ስርዓት ላይ የተሰሩ የምርምር ወጤቶች ላይ ምሁራንን በማወያየት የተሻሉ የምርምር ወጤቶች ለተጠቃሚው የሚደርስበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው፡፡

በኮንፈረንሱ ላይም በባህላዊ የግጭት አፈታተ ስርዓት ላይ ያተኮሩ 15 የምርምር ወረቀቶች ቀርበው ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተጋበዙ ምሁራን ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡

ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ስርዓትን በጥናትና ምርምር በማጎልበት ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ጥረታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና የጋራ ባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጌታቸው በበኩላቸው ኢትዮጵያ የበርካታ ሀገር በቀል ባህላዊ ግጭት አፈታት ባለቤት ናት።

"ይሁን እንጂ እነዚህን እሴቶች ሳይበረዙ ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  ተጠቃሽ ስራ ተሰርቷል ለማለት አያስደፍርም "ብለዋል።  

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ሚኒስቴር መሰሪያ ቤቱ ሀገሪቱ ያላት  ተፈጥሯዊና ባህላዊ ሀብቶች ተጠብቀውና ለምተው ለህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም እንዲሰጡ ለማድረግ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር እየሰራ ነው።

በተለይ በዘርፉ የሚሰተዋሉ ተግዳሮቶችንና በጎ አማራጮችን በጥናትና ምርምር በመለየት ለማበልጸግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ አውደጥናቱም የዚሁ ጥረት አካል ነው።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ተሾመ ከበዳ በበኩላቸው " በዩኒቨርሲቲው ተዘጋጅቶ  የተሰጣቸውን  የኦዳ ሮባ ዲዛይን በመንግስት በጀትና በህዝቡ የጋራ ድጋፍ ለማልማት በቅንጅት ይሰራል "ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ተዘንግቶ የቆየው የአርሲ ኦሮሞ ገዳን የሚወክለውን ኦዳ ሮባ ባሀላዊ ፕሮጄክት በነፃ ሰርቶ በማስረከቡም አመስግነዋል፡፡ 

ከኦዳ ሮባ አባገዳዎች መካከል አደም ቲና እንደተናገሩት ዩኒቨርስቲው ለ136 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የኦዳ ሮባ ታሪክ መልሶ ለማጠናከር እያደረገ የለው ጥረት የሚያስመሰግን ተግባር ነው፡፡

እንደ አባ ገዳው ገለጻ  ባለፉት ስርዓት ውስጥ ተቀብሮ የነበረው የኦሮሞ ህዝብ ማንነት ጎልቶ እንዲወጣ መደረጉ አሁን ያለው የፌዴራል ስርዓቱ ለህዘቦች ማንነትና እኩልነት መከበር ያለውን ህገመንግስታዊ ዋስትና ያመለክታል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው አውደ ጥናት ከሀገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ፣ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከቅርስ ጥበቃ ባለሥለጣን፣ ከኦሮሚያ የተውጣጡ ምሁራን፣ የስራ ኃላፊዎችና አባገዳዎች እየተሳተፉ ነው፡፡

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ3/2009 መንግሥት 180 ሺህ ታብሌት ሞባይሎችን ከውጭ ኩባንያ ለመግዛት ያወጣው ጨረታ የአገር ውስጥ ሞባይል መገጣጠሚያ ኩባንያዎችን አላማከለም የሚል ቅሬታ አስከተለ።

ቅሬታቸውን ያቀረቡት የሞባይል መገጣጠሚያ ኩባንያዎች ድርጊቱ አገሪቱ ከምትከተለው የውጭ ገበያ ተኮር ኢንዱስትሪ ጋር የሚጻረር መሆኑን ተናግረዋል።

የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ደግሞ ጨረታው በግዥ ሕግ፣ መመሪያና አዋጅ መሰረት የተከናወነ ነው ይላል።

ለሕዝብና ቤት ቆጠራ ስራ የ180 ሺህ የሞባይል ታብሌት ግዥ በዓለም ዓቀፍ ጨረታ ስርዓት መሰረት አሸናፊው ተለይቶ የግዥ ስምምነት ውል በመጠባበቅ ላይ ነው።

ግዥው እስከ 44 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን ይህም በአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ላይ አሉታዊ ጫና ይኖረዋል ተብሏል።

ጎን ለጎንም አገሪቱ ከግዥው በቀጥታ ታክስ ታገኘው የነበረውን 144 ሚሊዮን ብር እንደሚያሳጣት ተጠቁሟል።

ቅሬታ አቅራቢዎች ምን አሉ?

የቴክኖ ሞባይል መገጣጠሚያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ህላዌ ግርማ ኩባንያው በወር እስከ አንድ ሚሊዮን ሞባይሎችን የማምረት አቅም አለው።

ሞባይሎቹን ከአገር ውስጥ አቅርቦት ባለፈ ለውጭ ገበያም በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ችሏል።

ይሁንና በቅርቡ በመንግሥት የወጣው የ180 ሺህ ሞባይሎች ግዥ የአገር ውስጥ ገበያ በማሳጣት በሥራቸው ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድር ነው የተናገሩት።

የሲኒ ሞባይል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መዝገቡ አለምነህም ኩባንያው በተቋቋመ በሁለት ዓመት ጊዜ ምርቶቹን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ መሆኑን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት ከታብሌት ሞባይል አልፎ ውስብስብ ቴክኖሎጂ ያላቸውን ላፕቶፖችና ዴስክቶፕ ኮምፒዩተር የማምረት አቅም መገንባቱንም ተናግረዋል።

ሆኖም መንግሥት ባወጣው የታብሌት ሞባይል ጨረታ ተሳትፎ ባልታወቀ ምክንያት ከጨረታው መገለሉን ነው ያመለከቱት።

የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ምላሽ

የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በበኩሉ ግዥው የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በላከው ዝርዝር የፍላጎት መግለጫና መመዘኛ መስፈርት የተካሄደ ነው ይላል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ እንደተናገሩት በህጉ መሰረት ግዥው ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ በመሆኑ ዓለም አቀፍ የግዥ ጨረታ እንዲወጣ ተደርጓል።

ጨረታው በሕጋዊ መልኩ እንደተከናወነ ገልፀው ታብሌት ሞባይሉ ሟሟላት ስላለበት ዝርዝር የፍላጎት መግለጫ ግን የሚመለከተው አካል ምላሽ ይስጥበት ብለዋል።

የአርማታ ብረት አጠቃላይ ግዥ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ቢሆንም ከአገር ውስጥ አምራቾች እንዲፈጸም አቅጣጫ መቀመጡን ገልፀዋል።

ይህም የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪውን ለማበረታታት መሆኑን ጠቁመው በሌሎች ምርቶች ላይ ግን ተግባራዊ አለመሆኑን አስታውቀዋል።

የሃገር ውስጥ አምራቾችን ስለማበረታታት

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ደረጃ ካሳ የግዥ ሥርዓቱ የአገር ውስጥ አምራቾችን ከግምት ያስገባ አይደለም ባይ ናቸው።

የአገር ውስጥ አምራቾች አትችሉም የሚባሉት ሥራ ተሰጥቷቸው መስራት ሲያቅታቸው እንጂ በደፈናው መሆን እንደሌለበት ተናግረዋል።

መመሪያና አዋጆችንም ከጊዜው ጋር እንዲሄዱ መከለስ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የሞባይል አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር የሶፍትዌር ፓርት ኃላፊ ዶክተር አማረ ተፈሪ  ወጥ የሆነ የፌዴራል የግዥ ዝርዝር መመርያ መኖር እንዳለበት ተናግረዋል።

ይህ ካልሆነ ግን ተቋማት “በሚፈልጉት መልኩ የግዥ መመሪያ እንዲያወጡና በራሳቸው መንገድ እንዲንቀሳቀሱ እድል ይፈጥራል” ብለዋል።

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ምላሽ

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ ከዚህ በፊት ለሕዝብና ቤት ቆጠራ መረጃ ለመሰብሰብ 800 የሞባይል ታብሌቶችን ለሙከራ መጠቀማቸውን ገልጸዋል።

ዝርዝር  መስፈርቱም እነዚህን ታብሌቶች መነሻ በማድረግ መዘጋጀቱን ነው የተናገሩት።

የታብሌቱ ዝርዝር የፍላጎት መግለጫና መመዘኛ መስፈርት በኤጀንሲውና በዓለም ዓቀፍ ባለሙያዎች መዘጋጀቱንም አስረድተዋል።

መስፈርት ሲያዘጋጁ የአገር ውስጥ የማምረት አቅምን በማገናዘብ መሆኑን ጠቁመው ይህን የሚገልጽ ቴክኒካል ዝርዝር የመመዘኛ መስፈርት ግን በአስረጂነት አላቀረቡም።

በአንጻሩ በተጨባጭ ዓለም አቀፍ መመዘኛ መስፈርት መዘጋጀቱንና በዚህም የአገር ውስጥ አምራቾች የጨረታውን መመዘኛ ባለሟሟላታቸው በጨረታው መሸነፋቸውን ነው ያብራሩት።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 14 የሞባይል መገጣጠሚያ አምራች ኩባንያዎች ይገኛሉ።

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን