×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Thursday, 01 June 2017

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2009 ሁለተኛው አገር አቀፍ የሞዴል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር ዛሬ ተከፈተ።

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ “ዘላቂነት ያለው የገበያ ትስስር ለስራ እድል ፈጠራና ለኢንተርፕራይዞች ልማት መሰረት ነው” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚካሄደው።

በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት ፌዴሬሽን ቅጥር ግቢ የሚካሄደው ኤግዚቢሽንና ባዛር እስከ ግንቦት 30 ቀን 2009 ዓ.ም ይቆያል።

በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ የተገኙት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደምሴ ሽቶ እንደተናገሩት ዘርፉ ባለፉት ዓመታት በተለይም በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደረው የህብረተሰብ ክፍል አማራጭ የስራ እድሎችን አመቻችቷል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሃብት እንዲያፈሩና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻሉም ለአገራዊ የድህነት ምጣኔ መቀነስ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተም ይገኛል።

የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጄንሲ ዋና ዳሬክተር አቶ ዘነበ ኮሞ በበኩላቸው ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር ከመፍጠርና ዘርፉን በሚፈለገው ደረጃ ከማስፋፋት ባለፈ የእርስ በእርስ የልምድ ልውውጥን እንደሚያጎለብት ገልፀዋል።

በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ባህላዊና ዘመናዊ አልባሳት፣ የቆዳ ምርት ውጤቶች፣ የዕደ-ጥበባትና ቅርጻ ቅርጽ፣ የብረታ ብረትና የእንጨት እንዲሁም የኢንጂነሪንግ ውጤቶች ቀርበዋል።

የአግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች፣ የከተማ ግብርና ውጤቶች፣ ፈሳሽ ሳሙናና ዲተርጀንትና የተዘጋጁ ምግቦችን የሚያመርቱ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችም ተሳትፈዋል።

ተሳታፊዎቹ በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ተጠቅመውና በትጋት ሰርተው ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻል በተጨባጭ ያረጋገጡና ከሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 160 ሞዴል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው።

እንዲሁም ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውጭ የሆኑ አስር አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ያስተዋውቃሉ።

በተጨማሪም ከኢትዮጵያና ከአዲስ አበባ ነጋዴ ሴቶች ማህበራት፣ ከሴቶች ኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ፕሮግራም፣ ከፋሽን ዲዛይን አሶሴሽን፣ ከሴቶች ራስ አገዝና ከሥራ ፈጠራ ልማት ማዕከል የተውጣጡ 31 ከአጋር አካላት የተመለመሉ ኢንተርፕራይዞችም ይሳተፋሉ።

የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾቹም የፈጠራ ውጤቶቻቸውንና ምርቶቻቸውን የሚሸጡበትና የሚያስተዋውቁበት መድረክ መዘጋጀቱ የበለጠ ለመስራት እንደሚያበረታታቸው ገልፀዋል።

ከ16 ሺህ 500 መቶ በላይ ሰዎች እንደሚጎበኙት በሚጠበቀው በዚህ ኤግዚቢሽንና ባዛር ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ሽያጭና የገበያ ትስስር ይፈጠራል ተብሎም ይታሰባል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2009 በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ለሚያስጠሩ አትሌቶች የተሻለ ዕውቅናና ሽልማት እንደሚሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስራ አስፈጻሚዎችን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል፡፡

በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ውጤት ያመጡ አትሌቶች ከገንዘብና ሌሎች ሽልማቶች በተጨማሪ መሬት  ይሰጣቸው እንደነበር ይታወሳል።

አሁን ለውጤታማ አትሌቶች መሬት እየተሰጣቸው ባለመሆኑ  መሬት የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻችና የሽልማት መጠኑም እንዲያድግ ኮሚቴው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ከውይይቱ በኋላ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ  ለውጤታማ አትሌቶች በቂ ሽልማት እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡

90 ሚሊዮን ህዝብን ወክለው አገራቸውን በዓለም አደባባይ ለማስጠራት የሚጥሩ አትሌቶችን መሸለምና እውቅና መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንኛውም ስፖርተኛ ሽልማት ለማግኘት ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት ስሜት አገሩን ለማስጠራት ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ መጠቆማቸውንና መሬትን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች ሊደረግላቸው እንደሚገባ መናገራቸውንም አቶ ርስቱ  አብራርተዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሲያስተዳድረው የነበረው በተለምዶ "ሪቼ ሜዳ" ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ለወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ተሰጥቶት ቆይቷል።

አሁን ደግሞ ኦሊምፒክ ኮሚቴው  የሪቼ ሜዳን በባለቤትነት ለማስተዳደርና ማዕከላትን ለመገንባት የካርታ ይዞታ ማረጋገጫ እንዲሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም ለኦሊምፒክ ኮሚቴ የካርታ ይዞታ ማረጋገጫ እንዲሰጠው መመሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በመላ አፍሪካ ጨዋታዎችና በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተሻለ ውጤት እንድታስመዘገብ  ከመንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ የኢትጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብርወልደጊዮርጊስ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታ ከወዲሁ ለሚደረገው ዝግጅት የስፖርቱ እንቅስቃሴ የበላይ ጠባቂ እንዲሆኑ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያቀረበላቸውን ጥያቄም ተቀብለዋል።

ኦሊምፒክ ኮሚቴው በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሰሩ ያሉት ስታዲየሞችና ማዘውተሪያ ስፍራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁና የቴሌቪዥን መብት እንዲኖረውም ጥያቄ አቅርቧል።

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2009 በሳዑዲ አረቢያ ያለ ፈቃድ የሚኖሩ ወገኖችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ከሪያድ ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው የበረራ ምልልስ ሊጨመር ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቃባይ አቶ መለስ ዓለም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ምልልሱን ለመጨመር ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በጋራ እየሰራ ነው።

"ዜጎችን በማስመለስ በኩል በአስመላሽ ግብረ ኃይሉ እንደ አንድ እንቅፋት የተለየውን የትራንስፖር ችግር ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው" ብለዋል፡፡

የማጓጓዝ ስራውን ለማቀላጠፍም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ጽህፈት ቤቶች ብቻ ሲደረግ የነበረውን የትኬት ሽያጭ አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በሳዑዲ አረቢያ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጽህፈት ቤቶች በኩል አገልግሎቱ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በተለያዩ አገራት ያላት ተቀባይነት እየጨመረ መምጣቱንና የዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው መመረጥ የዚሁ ማሳያ መሆኑን አቶ መለስ ተናግረዋል።

በሌላ ዜና በቅርቡ ወደ መጠነ ሰፊ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የተሸጋገረው የኢትዮ ቻይና ወዳጅነት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ሁሉን አቀፍና ጠንካራ ግንኙነት እንደሚያሳይ ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት።

ባለፉት 20 ዓመታት የቻይና ባለሃብቶች በ624 ፕሮጀክቶች ላይ መዋዕለ-ነዋያቸውን በማፍሰስ ከ111 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2009 የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ተማሪዎችና ለፈተናው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አባላት ገለጹ።

ተማሪዎቹ እንደተናገሩት ፈተናውን በተፈቀደው ቦታና ሠዓት በቅድሚያ በመገኘት ያለምንም እንከን እየወሰዱ ነው።

በእስካሁኑ ሂደት የተማሪዎች ስነ-ምግባር መልካም እንደሆነና ፈተናው በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።

በቂ ዝግጅት ማድረጋችን ፈተናው ቀላል እንዲሆንልን አድርጎልናል ያሉት ተፈታኞቹ ጥሩ ውጤት ለማምጣትና ወደ ቀጣዩ ክፍል ለመዘዋወር ሙሉ አቅማቸውን እንደሚጠቀሙ ነው የተናገሩት።

ፈተናውን ለመቆጣጠር የተመደቡ መምህራንና ታዛቢዎች በበኩላቸው ፈተናው በሠላማዊ ሁኔታ እንዲሰጥና ኩረጃ እንዳይኖር ጥንቃቄ የተሞላበት ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን ነው የገለፁት።

የፊውቸር ሆፕስ ትምህርት ቤት ተማሪዋ ማርታ ጌታሁን የፈተና ሂደቱም ሆነ  የመምህራን ክትትልና ቁጥጥሩ እንዳስደሰታት ተናግራለች፡፡

የየካቲት 66 ትምህርት ቤት ተፈታኝ ተማሪዋ ብርቱካን አለማየሁም በፈተና ሂደቱ የስነ ምግባር ግድፈት እንዳላስተዋለች ገልጻ መኮራረጅ እንዳይኖር ጥብቅ ቁጥጥር መደረጉ መልካም መሆኑን ጠቅሳለች፡፡

የአጋዚያን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪው ጴጥሮስ አብርሃም ደግሞ እስከ አሁን የወሰዳቸው ፈተናዎች ብዙም እንዳላስቸገሩት ነው የተናገረው- ሌሎቹም ፊታቸው ላይ የደስተኝነት ስሜት እንደሚታይባቸው በመግለጽ፡፡

የኮማንድ ፖስቱ አባላት በበኩላቸው ፈተናው በታቀደለት ጊዜ ያለምንም እንከን እንዲጠናቀቅ የሚያስችል የሰው ኃይልና ቁሳቁስ ከወዲሁ መዘጋጀቱ የፈተናውን ሂደት መልካም አድርጎታል ብለዋል።

በተለይም ኮማንድ ፖስቱ ከትምህርት ቢሮ፣ ከጸጥታ አካላትና ከአካባቢ ነዋሪዎች መውጣጣቱ ፈተናውን ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲከናወን ማስቻሉን፤ ፈተናውም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮማንድ ፖስቱ አባል አቶ ማናዬ አራጋው እንዳሉት ፈተናው ከተጀመረ እስከ አሁን ያለምንም ችግር እየተካሄደ ነው።

ለፈተናው የተመደበው የሰው ኃይል ሥራውን በአግባቡ እየከወነ መሆኑን በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የኮማንድ ፖስት አባል አቶ ባየው ደርበው ናቸው።

ተማሪዎችና ፈተናውን በበላይነት የሚቆጣጠሩ አካላት በሠዓቱ እየተገኙ ፈተናው በመልካም ሁኔታ እየተካሄደ እንደሆነ አስረድተዋል።

ፈተናው በሶስት ሺህ 500 ጣቢያዎችና 72 ሺህ የትምህርት ባለሙያዎች፣ የፖሊስ አባላትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለደርሻ አካላትን በማሳተፍ እየተካሄደ ነው።

በውጭ አገራትም በሳዑዲ ዓረቢያ፣ ሪያድና ጂዳ እንዲሁም በሱዳን በሚገኙ የኮሚኒቲ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች በተመሳሳይ ፈተናውን እየወሰዱ ነው። 

ከግንቦት 23 እስከ 25 ቀን 2009 ዓ.ም በሚካሄደው የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አንድ ሚሊዮን 206 ሺህ 869 ተማሪዎች የተቀመጡ ሲሆን 46 ነጥብ 74 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸው።

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ግንቦት24/2009 የውሃ ፣መስኖና ኤሌክትሪክ  ሚኒስቴር በትግራይ ክልል ለሚከናወኑ የንፁህ መጠጥ ፣የመስኖና የኤሌከትሪክ  መሰረተ ልማት ስራዎች ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡

 በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በክልሉ መንግስት ትብብር በመገንባት ላይ የሚገኙ የልማት ተቋማት   ተጎብኝተዋል፡፡

 የውሃ ፣መስኖና ኤሌክትሪክ  ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ  በቀለ  በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት በራያ አካባቢ አርሶ አደሮች የከርሰ ምድር ውሃን ተጠቅመው ከ5ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በመስኖ በማልማት ያከናወኗቸው ሥራዎች በመልካም ተሞክሮ የሚወሰድ ነው፡፡

 በመቀሌ ዙሪያ በመገንባት ላይ የሚገኘው የመጠጥ ውሃ ግድብና ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮችና  ፋብሪካዎች ሌላው የተመለከቱት ውጤታማ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 በአክሱም ከተማ ያለው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከኳዌየት መንግስት ብድር መገኘቱን  ጠቁመው "በቂ ባለመሆኑ የፌዴራል መንግስት የገንዘብ ደጋፍ በማፈላለግ ለመስራት ታቅዷል "ብለዋል።

 በክልሉ ከኤሌክትሪክ መብራት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚታየው ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና የመስኖ ልማትን ለማጠናከር  ድጋፍ እንደሚያደረጉም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

 ርዕሰ መስተዳድር አባይ ወልዱ በበኩላቸው በፌዴራል መንግስት የሚደረግላቸው እገዛ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ተለይ  በመጠጥ ውሃና በመስኖ ፕሮጀክት ስራዎች ላይ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

 የፌዴራል መንግስት በክልል የሚያከናውናቸው የልማት ፕሮጀክቶችን  ለማገዝና ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋገጠዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2009 በወተት ኃብት ልማት ዘርፍ ተገቢው የገበያ እሴት ሰንሰለት እንዳልተፈጠረ የእንስሳትና አሳ ኃብት ልማት ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

ሚኒስቴሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ17ኛ ጊዜ የሚከበረውን የወተት ቀን "ለዓለም የወተት ቀን ኩባያችንን እናንሳ" በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከክልሎች፣ በወተት ልማት ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሃብቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር አክብሯል፡፡

በበዓሉ ላይ የተገኙት የእንስሳትና አሳ ኃብት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ገብረእግዚአብሔር ገብረዮሐንስ እንደገለፁት በዘርፉ የተሰራው የገበያ ሰንሰለትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ አነስተኛ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በዓመት አምስት ቢሊዮን ሌትር ወተት የማምረት አቅም ላይ የተደረሰ ሲሆን በ2012 ዓም ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ሌትር ከፍ ለማድረግ እቅድ ተይዟል።

አገሪቱ ያላትን የወተት አቅም በሚገባ እየተጠቀመችበት አይደለም ያሉት ዶክተር ገብረእግዚአብሔር ዘርፉ ለዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ያለው ድርሻ አናሳ መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታት ሚኒስቴሩ አሁን ያለውን የተዛባ የግብይት ሰንሰለት በማስተካከልና በአነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሮች የሚመረተውን ምርት ከገበያ ጋር ለማስተሳሰር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡

ለዚህም የእንስሳት ጤና አገልግሎት፣ የዘርፉ የግል ባለሃብቶች ተሳትፎና የግብይት ስርዓትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ አንድ ሰው በዓመት እስከ 200 ሌትር ወተት መጠጣት ያለበት ሲሆን በኢትዮጵያ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ከ20 ሌትር በታች ነው።

በተጨማሪም የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስፋፋት በዘርፉ የሚያጋጥመውን የመኖ እጠረትና ጥራት፣ የእንስሳት ምርታማነትና ሌሎችንም ለማስተካከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የባለድርሻ አካላት በቅንጅት አለመስራት በዘርፉ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

ለዚህም በመፍትሄነት ከእንስሳትና አሳ ኃብትና ከጤና ጥበቃ  ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ከአምራቾችና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት የሚውጣጡ አባላትን የሚይዝ ቦርድ ለማቋቋም በጥናት ላይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2009 በጤና ተቋማት የሚታየው የመድሃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ችግር በፍጥነት መፈታት እንዳለበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮና የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ባለስልጣንን የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸም ትናንት ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ሒሩት አፅብሃ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የጤና ጣቢያዎችና የሆስፒታሎች የግብዓት አቅርቦት ችግር እየተፈታ አይደለም።

ቢሮው በጤና ተቋማቱ የሚታየውን የመድሃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች የመሳሰሉ እጥረቶችን በመቅረፍ አገልግሎቱን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባውም አሳስበዋል።

በጤና ተቋማት ያለውን የመሰረተ ልማት እጥረት ያነሱት ሰብሳቢዋ በተቋማቱ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችም በተቀናጀ መልኩ መታገል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ቋሚ ኮሚቴው፤ በመዲናዋ የጤና ተቋማት ውስጥ በሚታዩ ውስብስብ ችግሮች ምክንያት የሕክምና አገልግሎት በሚፈለገው ደረጃ እየተሰጠ አለመሆኑንም ጠቁሟል።

የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ባለስልጣን አፈጻጸምን የገመገመው ቋሚ ኮሚቴው የጤና ተቋማት ብቃት ማረጋገጫ አሰጣጥ ችግር አለበት፤ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ምግቦችና መድሃኒቶችንም በፍጥነት እያስወገደ አይደለም ብሏል።

የግል ክሊኒኮችና የባህል ህክምና አዋቂዎች ምዝገባ ችግር እንዳለበት የጠቆሙት የቋሚ ኮሚቴው አባላት የህክምና አሰጣጥ ሂደቱ የህብረተሰቡን ጤናና የኢኮኖሚ ሁኔታ ያማከለ እንዲሆን ሊሰራ ይገባልም ነው ያሉት።

የባለስልጣኑ ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ወረቲ ችግሩ እንዳለ አምነው መድሃኒቶቹ የሚወገዱበት በቂ ቦታ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ሁለቱም ተቋማት የጤናውን ዘርፍ ተደራሽ ለማድረግ በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ቋሚ ኮሚቴው ጠቁሟል።

Published in ማህበራዊ

ጎንደር ግንቦት 24/2009 በሰሜን ጎንደር ዞን የተለያየ የሙስና ወንጀል የፈፀሙ 46 ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን በአማራ ክልል የፀረ ሙስናና ስነምግባር ኮሚሽን የጎንደር ቅርንጫፍ አስታወቀ፡፡

 የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሰጥአርጌ መሰሉ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለቅርንጫፉ ከቀረቡ 165 የሙስና ጥቆማዎች 148ቱ ትክክለኛ ጥቆማ መሆናቸው በመረጋገጡ ምርመራና ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

 በፍርድ ቤት ክስ ከተመሰረተባቸው መካከልም 46 ግለሰቦች በፈፀሙት የሙስና ወንጀል ከሦስት ወር እስከ አራት ዓመት በሚደርስ እስራትና እስከ 15 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጫ ተወስኖባቸዋል፡፡

 ሌሎችም ካለፈው ዓመት የተላለፉና ዘንድሮ ጥቆማ የቀረበባቸው 36 የክስ መዝገቦችም በቀጠሮ ላይ ሲሆኑ 120 መዝገቦች ደግሞ በአቃቢ ህግና ለፖሊስ በተሰጠ ውክልና የሙስና ወንጀሎቹ በመጣራት ላይ ይገኛሉ፡፡

 ቅጣቱ የተላለፈባቸው ግለሰቦች ስልጣንን ያለአግባብ ለግል ጥቅም ያዋሉ፣ የመንግስትን ሃብትና ንብረት የመዘበሩ፣ ህገወጥ ግዢና የጨረታ አሰራር ያካሄዱና የፈቀዱ ናቸው፡፡

 በሙስና ያለአግባብ የተወሰደ 200 ካሬ ሜትር ቦታ ወደ መንግስት የመሬት ባንክ እንዲመለስ የተደረገ ሲሆን 560 ካሬ ሜትር የከተማ ቦታና ሁለት የመኖሪያ ቤቶችም የህግ እገዳ እንዲደረግባቸው ተደርጓል፡፡

 ተመዝብሮ የነበረ 382 ሺህ ብር የመንግስትና 455 ሺህ ብር የማህበራት ገንዘብ ተመላሽ ተደርጓል፡፡

 እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስት ጥሬ ገንዘብ ይዘው የተሰወሩ ግለሰቦችም ኃብታቸው እንዳይሸጥና እንዳይለወጥ በፍርድ ቤት ታግዷል፡፡

 በዞኑ በሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሚቀጠሩ የመንግስት ሠራተኞች ቁጥራቸው መበራከቱን ለቅርንጫፉ የደረሱ ጥቆማዎች ያመላክታሉ፡፡

 ከቀረቡ 76 ጥቆማዎች 15ቱ ተጣርተው 10 የመንግስት ሰራተኞች በሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ መቀጠራቸው በመረጋገጡ ከአንድ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጥተዋል፡፡

 ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ ለመቅረጽ እየተደረገ ባለው ጥረትም ቅርንጫፉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 13 ሺህ ለሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት  መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2009 ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኗን የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርቲንግ ስታንዳርድ /አይ.ኤፍ.አር.ኤስ/ ከ140 በላይ የዓለም አገራት በጋራ የሚጠቀሙበት ዘመናዊ የፋይናንስ ሪፖርት ማቅረቢያ ዘዴ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁርና የኢንስቲትዩቱ ተባባሪ አማካሪ አቶ ወጋየሁ ወልደየሱስ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርቲንግ ስታንዳርድን ለመተግበር የአቅም ግንባታ ስልጠና ጀምራለች።

"አዲሱን አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ ለጥረት ኮርፖሬት የፋይናንስ አመራሮችና ባለሙያዎች የመጀመሪያውን ስልጠና ከግንቦት 17 እስከ 24 ሰጥቷል" ብለዋል።

አዲሱ አሰራር አንድን ንብረት መጀመሪያ በተገዛበት ብቻ ሳይሆን የወቅቱን ዋጋ መሰረት በማድረግ የሚቀርብ መረጃና ትክክለኛ የሀብት መጠን ለማሳወቅ የሚረዳ መሆኑን ስልጠናውን የሰጡት እኚሁ ምሁር ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በዚሁ ስልት ስለሚጠቀሙ ከተለያዩ አገራት ኢንቬስተሮችን ይበልጥ ለመሳብ እንደሚጠቅም አስረድተዋል።

ጥረት ኮርፖሬት ከውጭ ድርጅቶች ጋር ስለሚሰራ አሰራሩን ለማዘመን በጠየቀው መሰረት ስልጠናው እንደተሰጠው ገልፀዋል አቶ ወጋየሁ።

ከአንድ ዓመት ልምምድ በኋላ አዲሱን አሰራር ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። 

በአገር አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ ስልጠና በሶስት ዙር እንደሚሰጥና በመጀመሪያው ዙር የመንግስት የልማት ድርጅቶችና የፋይናንስ ተቋማት እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።

በሁለተኛው ዙር ደግሞ ማህበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፤ በሶስተኛው ዙርም ሌሎች ተቋማት ስልጠናው ይሰጣቸዋል።

በኢንስቲትዩቱ የቢዝነስ ልማትና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ተረፈ ትዜ በበኩላቸው "ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርቲንግ ስታንዳርድ ስርዓትን መጠቀም የግድ ነው" ይላሉ።

ስርዓቱ ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወጥ በሆነ መልኩ የሚጠቀሙበት መሆኑን አመልከተው "ኢትዮጵያም የትልልቅ ኢንቨስትመንቶች መዳረሻ በመሆኗ መስፈርቱን ማሟላት አለባት" ብለዋል።

ቀደም ሲል የነበረው የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ከአሜሪካ በልምድ የተወሰደ ሲሆን የአሁኑ ግን ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በጋራ የሚጠቀሙበት ዘመናዊ አሰራር እንደሆነ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ስታንዳርድን ለመተግበር በ2006 ዓ.ም ስምምነቱን መፈረሟንና ለተግባራዊነቱም የሚቆጣጠረውን የኢትዮጵያ አካውንቲንግና ኦዲት ቦርድ በ2007 ዓ.ም ማቋቁማን አስታውሰዋል።

አዲሱ የፋይናስ ሪፖርቲንግ አሰራር ውስብስብ በመሆኑ ተከታታይ ስልጠና እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይጠቁሟሉ።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 24/2009 ትናንት የተጀመረው ብሔራዊ ፈተና በተረጋጋ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ተማሪዎችና የፈተናው ታዛቢዎች ገለፁ።

ተማሪ ፍሬህይወት ግርማ በደቡብ ክልል የሃዋሳ ከተማ ኮተኒ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ናት።

ትናንት የተጀመረው ፈተና በተረጋጋ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሆነ የምትናገረው ፍሬህይወት በግቢው ውስጥ ያለው የፀጥታና ፈተናው እየተሰጠ ያለበት ሁኔታ የሰከነ እንደሆነ ትናገራለች።

ስለወሰደቻቸው ፈተናዎች ስትናገርም ከተማረችው ትምህርት አንጻር "ያልከበደና ያልቀለለ ፍትሃዊ ነበር" ብላለች።

ከሌሎች ትምህርቶች አንጻር ለሒሳብ ፈተና የተሰጠውን ጊዜ ሙሉ በሙሉ መጠቀሟን የምትናገረው ተማሪዋ ከሌሎቹ አንጻር ጊዜ የወሰደባት እያንዳንዱ ጥያቄ የሚሰራ ሒሳብ ስላለውና የበለጠ ትኩረት ስለሚፈልግ እንጂ ከባድ ሆኖ እንዳልነበር ገልፃለች።

በአዲስ አበባ የጥቁር አንበሳ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪው ኢብራሂም ዓሊም ወደሚፈተኑበት ትምህርት ቤት ግቢ ሲገቡ ጀምሮ ያለው ፍተሻና የተማሪው ግብረገብነት ጥሩ እንደሆነ ተናግሯል።

ተማሪ ኢብራሂም ፤ በግቢው ጥበቃ የሚያደርግ ፖሊስ መኖሩንና የተማሪዎች እንቅስቃሴም የተረጋጋ እንደሆነ ነው የገለጸው።

ፈተናውም ቢሆን ለተዘጋጀ ተማሪ ያን ያህል ከባድ እንዳልነበርና ከሌላው ጊዜ በተለየ ብዙዎች የተሻለ ነጥብ ሊያመጡ የሚችሉበት እንደሚሆን ግምቱን አስቀምጧል።

ባለፈው ዓመት ፈተናው ስለመሰረቁና ተፈታኞች ጋር ስለመድረሱ በመወራቱ ተማሪዎች ላይ ደርሶ የነበረውን ከፍተኛ ጫና አስታውሶ  ዘንድሮ እንደዚያ አይነት ችግር አለመፈጠሩ እንዳረጋጋው ተናግሯል።

በመዲናዋ የአራዳ ክፍለ ከተማ የራስ ደስታ ፖሊስ ጣቢያ ወንጀል መከላከል ፖሊስ አባል ኮንስታብል አስተዋለ ሙላት በቀለመወርቅ ትምህርት ቤት የብሔራዊ ፈተናውን ፀጥታ የሚጠብቀው የፖሊስ ኃይል አስተባባሪ ናቸው።

አንዳንድ ተፈታኞች እያረፈዱ እንደሚመጡ መታዘባቸውን የሚናገሩት ኮንስታብል አስተዋለ ተፈታኞቹ በግቢው ውስጥ የሚያሳዩት ስነ ምግባር ግን ጥሩ እንደሆነ መስክረዋል።

“ተፈታኞቹ ወደ ግቢ ሲገቡ በሰለጠኑ ሲቪል ፈታሾች የሚፈተሹ ሲሆን ፍተሻውን ፖሊስ በቅርብ ይከታተለዋል” ብለዋል።

“አልሰማንም” በሚል ሞባይል የያዙ የግል ተፈታኞች ስልካቸውን አስቀምጠው እንዲገቡ መደረጉንና 13 ተፈታኞችም በራሳቸው ምክንያት መቅረታቸውን ማወቃቸውን ገልጸዋል።

በመላ አገሪቷ ትናንት የተጀመረው የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በታቀደው መልኩ መካሔዱን የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጿል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን