አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 09 May 2017
Tuesday, 09 May 2017 23:36

ፕሬስና ተግዳሮቶቹ

Published in ቪዲዮ

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2009 ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ትኩረት ሰጥቶ እያከናወነ ያለውን ተግባር ማጠናከር እንደሚጠበቅበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

ቋሚ ኮሚቴው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸምን ዛሬ ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ ተላላፊ የሆኑና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል በሚያስችል መልኩ እያከናወነ ያለው ተግባር  በመልካም ደረጃ የሚጠቀስ ነው።

ተላላፊ የሆኑትን በሽታዎች ለመከላከል የክትባት አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ማዳረሱን ያስታወሱት ሰብሳቢዋ፤ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች በተለይም የማህጸን በር ካንሰርን ለመከላከል የተከናወነው ልየታና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ ተናግረዋል።

በቅድመ ወሊድና በድህረ ወሊድ ወቅት የሚከሰተውን የፌስቱላና የማህጸን ወደ ውጪ መውጣት ልየታና ህክምና በስፋት መሰራቱ “ለእናቶች ሞት መቀነስ ያለው አስተዋጽኦ ከፍ እንዲል አድርጎታል” ሲሉም አብራርተዋል።

ስለዚህም ተላላፊ የሆኑና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ የጀመራቸውን ተግባራት "አጠናክሮ መቀጠል አለበት" ብለዋል።

በሌላ በኩል ሚኒስቴሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመለየት ያደረጋቸው  ጥረቶች ቢኖሩም አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያከናውናቸው አሳስበዋል።

ከልማት ሠራዊት ግንባታ አኳያ ባለሙያዎችን  ለማብቃት ብሎም የአመለካከት፣ የእውቀትና የክህሎት፣ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ረገድ  የተሰራው ሥራ አበረታች  መሆኑን ነው ወይዘሮ አበባ የገለጹት።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤  ቋሚ ኮሚቴው የሰጣቸውን ግብረ መልሶች መሰረት በማድረግ ሚኒስቴሩ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት በትኩረት ይሰራል።

ክፍተቶችን ለማስተካከል ለአስተዳደሮች፣ ለቦርድ አባላትና ባለሙያዎች ሁሉን አቀፍ የሆነ ስልጠና በመስጠት ትኩረት የሚሹ ስራዎችን በተገቢው መልኩ በማከናወን አፈጻጸሙን ለማሻሻል ጠንክሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2009 ኢትዮጵያ ለምርታማ ሴፍቲኔት መርሃግብር የሚውል ሁለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ከዓለም ባንክ በብድር አገኘች።

የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ተወካይ ዳይሬክተር ካሮለይን ተርክ ስምምነቱን ፈርመዋል።   

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ  እንደተናገሩት፤ የብድር ስምምነቱ ለምርታማ ሴፍቲኔት መርሃግበር ማስፈጸሚያ የሚውል ነው።

የብድር ስምምነቱ "በድርቅ የተጎዱና በኑሮ የተጎሳቆሉ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል" ነው ያሉት።

የምርታማ ሴፍቲኔቱ ተጠቃሚ የገጠር ነዋሪዎች በጥሬ ገንዘብ ወይም በምግብ መልክ እንደሚሰጣቸው ነው የተመለከተው።

በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ተወካይ ዳይሬክተር ካሮለይን ተርክ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የብድር ስምምነቱ በምርታማ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር የዜጎችን የምግብ ዋስትና  ለማረጋገጥ ይውላል።

ባንኩ እ.ኤ.አ ከ2005 ጀምሮ በምርታማ ሴፍቲኔት መርሃግብር የሚሰጠው ድጋፍ ያጠናከረ ሲሆን፤ ይህ የብድር ስምምነት የመርሃግብሩ አራተኛውን ምዕራፍ ለማስፈፀም የሚውል መሆኑ ታውቋል።

የምርታማ ሴፍቲኔት መርሃግብር በድርቅ የተጎዱ ዜጎችን  ተጠቃሚ በማድረግ በኑሯቸው ለውጥ እንዲያመጡ ያለመ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች በራስ አቅም ከጉዳት ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት አድንቀዋል።

ባንኩ መንግሥት ለሚያደርገው ጥረት የሚሰጠው ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2009 አፍሪካ  በበቂና በተመጣጣኝ ዋጋ የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት ሳይኖራት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ማሰብ እንደማይቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ያለው ስድስተኛው የ2017 የዓለም ውሃ ሃይል /ሃይድሮ ፓወር/ ጉባኤ አዲስ አበባ ውስጥ እየተካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጉባኤውን ሲከፍቱ እንደተናገሩት፤ አፍሪካ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦትን በበቂ መጠን ማሟላት ይጠበቅባታል።

የኤሌትሪክ ሃይል በተመጣጣኝ ዋጋና  በአስተማማኝ ሁኔታ ካልተገኘ ዘላቂ ልማት ሊታሰብ እንደማይችል ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ አፍሪካ ከውሃ ሀብቷ ታዳሽ የኤሌትሪክ ሃይል ለማልማት ጥረት እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።

ከውሃ ሀብት የኤሌትሪክ ሃይል ለማልማት የገንዘብ እጥረት መኖሩን ጠቁመው፤ ይህን ችግር ለማቃለል አፍሪካ የግሉን ዘርፍ ልታሳትፍ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ዘርፉን ለማልማት ትኩረት መስጠቷን ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ዘላቂ የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት እንዲኖራት ለማድረግ እንደሚያስችል አመልክተዋል።

የውሃ፣ መስኖና ኤሌትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው፤ አፍሪካ ካላት እምቅ የውሃ ሀብት ታዳሽ ኃይል በማመንጨት ለመጠቀም መዋለ ንዋይ በማውጣት "በልማቱ የመሳተፊያ ወቅት አሁን ነው" ብለዋል።

አፍሪካ ከውሃ ሀብት የኤሌትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችላት እምቅ አቅም እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከዓለም የውሃ ሀብት አኳያ 12 በመቶ የኤሌትሪክ ኃይል የማምረት አቅም ቢኖራትም እስካሁን አገልግሎት ላይ ያዋለችው ሦስት በመቶ ብቻ ነው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የዘርፉን እምቅ አቅም ለማልማት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ ሲሆን፤ ለዚህም የገንዘብ፣ የቴክኖሎጂና የአቅም ግንባታ እንዲሟላላቸው ይፈልጋሉ።

ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በወቅቱ እንዳሉት፤ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የፖሊሲ፣ የተቋምና አጋርነት መድረኮችን ምቹ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ  የማሻሻያ ተግባራትን እያከናወኑ ናቸው።

ስለሆነም አፍሪካ ካላት እምቅ የውሃ ሃብት ታዳሽ ኃይል ለማልማት መዋለ ንዋይ ማውጫ ወቅቱ አሁን መሆኑን ነው ሚኒስትሩ አጽንኦት የሰጡት።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ለመጠቀምና ለጎረቤት አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል የማቅረብ ስራዎች እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት 97 በመቶ የሚሆነው ከታዳሽ ኃይል የሚመነጭ ሲሆን፤ 89 በመቶ ደግሞ ከውሃ የሚመነጭ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

አገሪቷ ከውሃ ማመንጨት ከምትችለው 45 ሺ ሜጋ ዋት እስካሁን ሦስት ነጥብ ስምንት በመቶ የተጠቀመች ሲሆን፤ ይህን በእጥፍ ለማሳደግ በግንባታ ሂደት ላይ ትገኛለች።

የአፍሪካ ህብረት ምክትል ሊቀ መንበር ዶክተር ኪዊሲ ካርተሪ በበኩላቸው፤ ከታዳሽ ኃይል በተለይም ከውሃ የሚመነጭ የኃይል አቅርቦት ለአፍሪካ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል።

የውሃ ሃብትን በአግባቡ መጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለማዳረስ፣ የካርበን ልቀት መጠን ለመቀነስና ቀጣናዊ ትስስር ለማፋጠን እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

በሌሎች የመሰረተ ልማት ዘርፎች የውሃ ሀብት አቅርቦት፣ የመስኖ ልማት፣ የጎርፍ መከላከልና ድርቅን ለመቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመስራት ያስችላል።

ስለሆነም የፋይናስ ተቋማት፣ የግልና የመንግስት ዘርፎች፣ የሲቪክ ማህበራትና የምርምር ተቋማት በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ጉባኤው ዓለም አቀፉ የሃይድሮ ፓወር  ማህበር፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንና የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር በጋራ የተዘጋጀ ነው።

በጉባኤው ከ80 አገሮች የተውጣጡ ተመራማሪዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የመጀመሪያው ዓለም ዓቀፍ የዓለም ውሃ ሀብት ሃይል /ሃይድሮ ፓወር/ ጉባኤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2007 በቱርክ አንታሊያ የተካሄደ ሲሆን፤ አምስተኛው ጉባኤ በቻይና ርዕሰ መዲና ቤጂንግ ከሁለት ዓመት በፊት መካሄዱ ይታወሳል።

ጉባኤው ለቀጣዮቹ ሦስት ቀናት እንደሚቀጥል ታውቋል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ጋምቤላ ግንቦት 1/2009 ባለፉት ዘጠኝ ወራት በጋምቤላ ክልል በተከናወኑ የዘላቂ ልማትና የድህነት ቅነሳ የልማት ስራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ።

የክልሉ የዘጠኝ ወራት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈፃፀም ግምገማ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና የጋህአዴን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡኩኝ ኡቡያ በግምገማ መድረኩ ላይ እንደገለጹት በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመልካም አስተዳደር፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የተሻሉ ስራዎች ተከናውነዋል።

በተለይም በሰላምና ጸጥታ ፤በግብርና ፣በትምህርት ተደራሽነት፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና በሌሎችም ሴክተሮች ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውንም አስረድተዋል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም በቀደመው መኸርና እርጥበትን በማቆየት ከለማው ወደ 93ሺህ ሔክታር የሚጠጋ መሬት ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡንና ለመጪው መኸር ዝግጅት መጀመሩን ተናግረዋል።

የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ በተካሄደው የንቅናቄ ስራም በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ115 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምርህታቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

በተመሳሳይም በከተማና በገጠር የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲሁም በእናቶችና ሕጻናት ጤና አጠባበቅ ዙሪያ አበረታች ውጤት መገኘቱን አስረድተዋል።

የወጣቶችንና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ከሰባት ሺህ የሚበልጡ ስራ አጦች ተለይተው ወደ ስልጠና የሚገቡበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ባለፉት ዘጠኝ ወራት የአፈጻጸም ክፍተት የታየባቸው የገቢ አሰባሰብ ፣የመንገድና ሌሎችም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፕሮጀክቶች በቀሪዎቹ ወራት ለመፍታት የተቀናጀ ጥረት ለማድረግ በግምገማው ላይ የጋራ አቋም መወሰዱን አስረድተዋል።

የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ላክደር ላክባብከ በበኩላቸው ባለፉት ወራት የልማት እቅዶችን ወደ ተግባር ለመለወጥ ጅምር ስራዎች ቢኖሩም በተወሰኑ ሴክተሮች ክፍተት መታየቱን ተናግረዋል።

በክልሉ በተለይም የገቢ አቅምን በማሳደግ የተጀመሩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት እቅዶችን  ለማሳካት የተደረገው ጥረት የሰፋ ክፍተት የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

"ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የኪራይ ሰብሳቢነት፣አመራሩ ቁርጠኛ ያለመሆንና ያለን የገቢ አቅም አሟጦ ያለመጠቀም ችግሮች ናቸው" ብለዋል።

በጋምቤላ ከተማ ለሦስት ቀናት በተካሔደውና ትላንት በተጠናቀቀው የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ የአመራር አካላትና ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2009 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ  በ"2017 ሶማሊያ ጉባዔ" ላይ ለመሳተፍ ለንደን ገብተዋል።

"የ2017 ሶማሊያ ጉባዔ" አገሪቷ ላለፉት አምስት ዓመት ያስመዘገበችውን ለውጥ ለማስቀጠል የሚያስችል ድጋፍ ለማሰባሰብ ያለመ ነው።

ጉባኤው የምስራቅ አፍሪካ አገሮች መሪዎች እና ሌሎች ዋነኛ  አጋር አካላትን በጋራ ያገናኛል::

በሶማሊያ እየታየ የመጣውን የሰላምና ደህንነት ለውጥ በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል ባተኮሩ ጉዳዮች ላይ ይመክራል።

በ2020 የአገሪቷን ሰላምና ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አዳዲስ ዓለማቀፋዊ የአጋርነት ስምምነቶች ላይ ያተኮሩ ጉዳዮች የጉባኤው ዋነኛ አጀንዳዎች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጉባኤው በሶማሊያ የፌዴራሉና የአባል መንግስታቱ በጋራ በሚስማሙባቸው ጉዳዮች ላይም ትኩረት ይሰጣል።

በአገሪቷ የሴት ወታደሮችን የወደፊት ሁኔታ እንዲሁም ሰብዓዊ መብቶች ሳይጣሱ ሽብርተኝነትን መዋጋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያም ውይይት ይካሄዳል።

እ.ኤ.አ 2011 ሶማሊያ ካለመረጋጋቷም በላይ አብዛኛው የአገሪቷ ክፍል በአል ሽባብ ቁጥጥር ስር ነበር። በአገሪቷ በተከሰተው ረሃብም ወደ 250 ሺ የሚጠጉ ዜጎቿ ተቀጥፈዋል:: በአገሪቷ  የባህር ላይ ውንብድና በሰፊው ከመንሰራፋቱ የተነሳ በተመሳሳይ ዓመት ብቻ በዓለማቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የሰባት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር  ኪሳራ አድርሷል።

ይህን ተከትሎ ለንደን በ2012 ሶማሊያን የተመለከተ የመጀመሪያውን ዓለምአቀፍ ጉባዔ ያካሄደች ሲሆን፤ ከጉባኤው ማግስት ጀምሮ የሶማሊያ ሰላም መሻሻል ጀምሯል።

እኤአ በ2012 በሶማሊያ የፌዴራል መንግስት ስርዓት ማዋቀር ተችሏል። በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ሰላም አሰከባሪ ሃይልም በአገሪቷ  ሰላም ከማስፈን ባለፈ አልሸባብን ዋና ዋና ከሚባሉ ከተሞች ለማስለቀቅ ችሏል::

ሶማሊያ በ2017 የተሳካ ምርጫ በማካሄድ የአገሪቷን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መሃመድ አብዱላሂ መሃመድ በፕሬዚዳንትነት ወደ ስልጣን አምጥታለች።

በሶማሊያ በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶችን  ለማሰቆም እና በድንበሮች አካባቢ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማፋጠን በአገሪቷ ያለውን ደህንነት  ማሻሻል ወሳኝ በመሆኑ ጉባኤው ይህንን ለውጥ ለማፋጠን በሚያስችሉ ዘዴዎቸ ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ግንቦት  1/2009 ሲንጋፖር ከኢትዮጵያ ጋር በአዳዲስ የኢኮኖሚ የትብብር መስኮች በጋራ ለመስራት እንደምትፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዲዮ ጂ ሂያን ገለጹ።

በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ዛሬ የጀመሩት የሲንጋፖር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዲዮ ጂ ሂያን ቀደም ብሎ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተነጋግረዋል።

ሚስተር ዲዮ ጂ  ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር በኢትዮ - ሲንጋፖር የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ከተወያዩ በኋላ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከዚህ ቀደም ሲንጋፖርና ኢትዮጵያ በትምህርት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በንግድ ዘርፎች ስምምነት አድርገው  ተግባራዊ ማድረግ መጀመራቸው ይታወቃል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዲዮ ግንኙነቱን ማሰደግ አስመልክቶ ሲገልጹ፤ “አሁንም በሌሎች አዳዲስ ጉዳዮች በጋራ የመስራት ፍላጎት አለን" ብለዋል።

ኢትዮጵያና ሲንጋፖር የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስራቸውን ለማጠናከር በ2008 ዓ.ም መስከረም ላይ በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢትዮ - ሲንጋፖር የንግድ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት የተደራራቢ ቀረጥን ለማስቀረት ስምምነት መፈረማቸው ይታወሳል።

"የሁለቱ አገሮች የኢኮኖሚ ትስስር እያደገ መጥቷል" ያሉት ሚስተር ዲዮ፤ ከአንድ ወር በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ - ሲንጋፖር የሚጀመረው የቀጥታ በረራም ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

እንደምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዲዮ፤ የአገራቷ የሁለትዮሽና ዓለምአቀፍ የትብብር አጀንዳዎች እየጨመሩ ይሄዳሉ፤''ከኢትዮጵያ ጋር በተለይም በቱሪዝም፣ በግብርና ማቀነባበሪያ፣ ኢንዱስትሪና ሰው ሃብት ልማት ላይ በስፋት እንሰራለን'' ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከደቡብ ምስራቅ እስያ አገሮች ከሆኑት ማሌዥያ፣ ኢንዶኔዥያና ሲንጋፖር ጋር ያላት ግንኙነት እየተሻሻለ መጥቷል።

በአካባቢው በሰለጠነ የሰው ሃይልና በከተሞች ዘመናዊነት በዓለም ቀዳሚ ከሆነችው ሲንጋፖር ጋር በንግድ፣ በቱሪዝምና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ኢትዮጵያ ተባብራ ለመስራት እንደምትፈልግ አቶ ደመቀ አክለዋል ።

የሲንጋፖር ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ በሁለቱም አገሮች መካከል ተሳትፎውን ለማሳደግ ፍላጎት አለ።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2009 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከውጭ አገር ከተላከ ገንዘብና ከምንዛሬ አገልግሎት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገለፀ፡፡

ባንኩ ያዘጋጀው 8ኛው ዙር የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማበረታቻ የሽልማት ዕጣ አወጣጥ ስነ-ሥርዓት ዛሬ በብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ተካሂዷል።

የባንኩ የውጭ ሃዋላዎችና ኤን.አር.ኤን.ቲ ሂሳቦች ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ታምራት ማሞ እንደተናገሩት የሽልማት ፕሮግራሙ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ከማሳደግ አንጻር አበረታች አፈጻጸም እያሳየ ነው።

የሽልማት ፕሮግራሙ ባንኩ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ከሚያካሂዳቸው ፕሮግራሞች ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፕሮግራሙ በአዲስ ዓመት፣ በገና፣ በፋሲካና በረመዳን በዓላት ወቅት ነው የሚካሄደው።

ዓላማውም ከውጭ ምንዛሬ ግኝት በተጨማሪ ከውጭ የሚላክ ገንዘብና የምንዛሬ አገልግሎት በባንኮች በኩል እንዲከናወን ሕብረተሰቡን ማበረታታት ነው።

ባንኩ በመንግስትና በግል ተቋማት ለሚከወኑ ኢንቨስትመንቶች ለሚያደርገው ድጋፍ ከገንዘብ ማሰባሰቢያ ስራዎች አንዱ የውጭ ምንዛሬ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ነው።

በውጭ ሃዋላዎች ከወጪ ንግድ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ እየተገኘ መሆኑንም ነው አቶ ታምራት የተናገሩት።

በስነ-ስርዓቱ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ዕጣዎች የአንድ ሚሊዮን ብር ዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል፣ 15 ዕጣዎች እያንዳንዳቸው አንድ ላፕቶፖ፣ 30 ዕጣዎች እያንዳንዳቸው አንድ የውሃ ማጣሪያና 60 ዕጣዎች እያንዳንዳቸው አንድ ስማርት የሞባይል ቀፎዎች በድምሩ 106 ሽልማቶች እንደ ቅደም ተከተላቸው ወጥተዋል።

9ኛው ዙር ፕሮግራም በመጪው ሰኔ የሚከበረውን የረመዳን በዓል ምክንያት በማድረግ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2009 የስኳር ምርቱን ለማሳደግ የተከላቸው አዳዲስ የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎች ውጤታማ በመሆናቸው እያስፋፋቸው መሆኑን የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ገለፀ።         

በፋብሪካው የመስክ ምልከታ ያደረገው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዲሶቹን ዝርያዎች የማስፋፋቱን ሂደት አበረታች ነው ብሎታል።

የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ስለሺ ዳጋ እንዳሉት የስኳር ምርቱን ለማሳደግ አምስት የኩባ ሸንኮራ አገዳ ዝርያዎች እየተስፋፉ ነው።

አዳዲሶቹ የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎች ከነባሮቹ የተሻሉ በመሆናቸው የፋብሪካውን ምርታማነት እንደሚያሳድጉትም ጠቁመዋል።

ፋብሪካው ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1 ሚሊዮን 166 ሺህ 898 ኩንታል ስኳር ያመረተ ሲሆን አዳዲሶቹን የአገዳ ዝርያዎች መጠቀም ሲጀምር ምርቱ ከ35 እስከ 40 በመቶ ጭማሪ ሊያመጣ እንደሚችል አክለዋል።

በሌላ በኩል ፋብሪካው በተደጋጋሚ የመስኖ ውሃ መጠን መቀነስ ሳቢያ የሸንኮራ አገዳ ምርት ማሳደግ ስራው ችግር እንደገጠመው ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

ከፊንጫ የኤሌክትሪክ ማመንጫ የሚለቀቅለት የመስኖ ውሃ በቂ አለመሆኑን ነው የተናገሩት።

ችግሩን ለመፍታት በፋብሪካውና በስኳር ኮርፖሬሽን ጭምር ጥረት ቢደረግም መፍትሄ አለመገኘቱን አስታውቀዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ፋብሪካው አዳዲስ የሸንኮራ ዝርያዎችን ለማስፋፋት የጀመረው ጥረት አበረታች መሆኑን ገልጾ የመስኖ ውሃ ችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ የሚሻ መሆኑን አመልክቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ገብረእግዚያብሄር አርዓያ ከፋብሪካው አቅም በላይ የሆነው ችግር ለሚመለከተው አካል እንደሚቀርብና  የቁጥጥርና ክትትል ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ከፋብሪካው የሚወጡ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች አወጋገድ፣ ከህብረተሰቡ ለሚነሱ የልማት ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠትና ከንብረት አያያዝና አወጋገድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጣቸውም አሳስበዋል።

በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎችን በህግ አግባብ ከፋብሪካው ክልል የማስለቅቅ ስራ ሊሰራ እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል።

Published in ኢኮኖሚ

አማረ ኢታይ /ኢዜአ/

ገና ለግላጋ ወጣት ነው።ወደ ዚች ምድር ከመጣ 25 ዓመታትን አስቆጥሯል። ስራው ግን እንደ ወጣትነት እድሜው ሳይሆን እደግ ተመንደግ የሚያሰኙ ታላላቅ ተግባራትን አከናውኗል ።  ባከናወናቸው መልካም ተግባራትም ስሙን ከትውልድ ስፍራው አልፎ በመላው ኢትዮጵያ ከዚያም በአፍሪካ አህጉር በሚገኙ ሃገራት ጭምር መጠራት ጀምሯል - የመቀሌ ዪኒቨርሲቲ።

ከዛሬ 25 ዓመት በፊት በመቀሌ ከተማ በአንድ ትልቅ ዋርካ ጥላ ስር የማስተማር ስራውን እንደጀመረ ታሪኩን ያትታል።ዛሬ ዩኒቨርሲቲው በስሩ በርካታ ስራዎች የሚከወንበት የባለ ትላልቅ ስመ ጥር ምሁራንና የዘመናዊ ህንጻዎች ባለቤት ሆኗል።

ተቋሙ በመደበኛ የትምህርት መርሀ ግብር ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የስልጠና ዘርፎች ተቀብሎ ያስተምራል ። ዛሬ በአካዳሚክ ዘርፍ ብቻ በ89 የትምህርት መስኮች የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ይሰጣል።በ126 የትምህርት መርሃ ግብሮች ሁለተኛ ዲግሪ እና በ11ዘርፎች ደግሞ የሦስተኛ ዲግሪ/የዶክትሬት/ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከመማር ማስተማር ስራው በተጨማሪ በሚያካሂዳቸው የምርምርና ጥናት ስራዎቹም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።በተለይ የትግራይ ክልል አርሶ አደሮች ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ በሚያደርጋቸው የምርምር ስራዎች ይበል የሚያሰኙ ውጤቶችን እንደተቀዳጀ ራሳቸው ተጠቃሚ አርሶአደሮቹ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ ።

ዩኒቨርሲቲው ከሚያከናውናቸው ታላላቅ ስራዎቹ መካከል ዛሬ ትኩረቴንና ቀልቤን ወደ ሳበው ጉዳይ ላምራ።የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሃገራችን የስፖርት ልማት ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ ከሚኳትኑ ተቋማት መካከል አንዱ ነው።ዘርፉን ካለበት ደረጃ አንድ እርምጃ ወደ ፊት እንዲራመድ በርካታ ስራዎችን ሰርቷዋል ።እየሰራም ይገኛል።

ዩኒቨርሲቲው በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን እርስ በራሳቸው ተገናኝተው የስፖርት ልማት ዘርፉን እንዲያሳድጉና በመካከላቸው ፍቅርና መልካም መስተጋብርን እንዲጋሩ ለማድረግ በ2000 ዓ.ም የስፖርት ፌስቲቫል በማዘጋጀት ፈር ቀዳጅ ሚናውን ተጫውቷል ።

ዛሬ ደግሞ ሁለት ትላልቅ የስፖርት ፌስቲቫሎችን በጥምረት ለማዘጋጀት ሽርጉድ እያለ ይገኛል።10ኛውን የመላው ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫልና የመጀመሪያው  የመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫልን በ2010 ዓ/ም ለማዘጋጀት ታጭቷል።

የዩኒቨርሲቲው የስፖርት ልማት ዘርፉ ስኬት ሲነሳ የዶክተር ከሰተ ለገሰ ስምም አብሮ ይነሳል።ዶክተር ከሰተ ለበርካታ አመታት የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ዲን ሲሆኑ የስፖርቱን ዘርፍ በበላይነት ይመራሉ ። ያስተባብራሉ ።

በስፖርት ዘርፉ ጥልቅ ፍቅር ያላቸው፣ትሁትና ሰው አክባሪ ታላቅ ምሁር መሆናቸውን በርካቶች ይመሰክርላቸዋል። ለሚሰሩት ስራ የማይለግሙና በትጋት የሚፈጽሙ ታታሪ ምሁር እንደሆኑም በተደጋጋሚ ይነሳል ።

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሊደረጉ የታሰቡት የስፖርት ፌስቲቫሎችም አሁንም በሳቸው የበላይነት ነው የሚመራው ።በመሆኑም የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ እያደረገ ስላላው አጠቃላይ ዝግጅት  ዶ/ር ከሰተ ተናግረዋል ።

የስፖርት ዘርፉን በሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲመራ ለማድረግ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በመጀመሪያ፣በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራም እያሰለጠ መሆኑን ገልጸዋል።ከዚህ ባለፈ በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢና በስሩ በሚገኙ ሌሎች አምስት ካምፓሶች ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ  የእግር ኳስ ሜዳዎች ግንባታ በማጠናቀቂያ ምእራፍ ላይ ይገኛሉ ።

በተጨማሪም የዋና፣የእጅ፣የቅርጫት፣የዳርት የውስጥና የውጭ የስፖርት ውድድሮችን የሚያስተናግዱ ሜዳዎችና ዘመናዊ ስታዲዮሞች ግንባታ ተጠናቀዋል ። ለውድድርም ዝግጁ ሆነዋል።የግንባታ ስራዎቹ ከዛሬ ትውልድ አልፎ ወደ ቀጣይ ትውልድ የሚሸጋገሩ ውድ እሴቶች እንደሆኑም ነው የተናገሩት።

በሚቀጥለው ዓመት የካቲትና ሐምሌ ወር ላይ በዩኒቨርሲቲው አስተናጋጅነት ለሚካሄዱ የመላው አፍሪካና የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫልን ለማስተናገድ ሙሉ ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ዶክተር ከሰተ አስታውቀዋል።

 በፌስቲቫሉ ዝግጅት ለሚሳተፉ አንድ ሺህ በጎ ፈቃደኛ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣የመቀሌ ከተማ ወጣቶችና የስፖርት ኮሚቴ አባላት ስልጠና ሰጥቷል።  በዩኒቨርሲቲው  ምክትል ፕሬዝዳንቶች የሚመሩና የተለያዩ ተቋማትን በአባልነት ያቀፈ ዓብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ለዝግጅቱ ድምቀት የሚያገለግሉ ተግባት እየተከናወኑ ይገኛሉ ባይ ናቸው ።

ዩኒቨርሲቲው  በዓለም አቀፍ ደረጃ የዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል ዝግጅት ላይ በጎ ፈቀደኛ ወጣቶችን በማሳተፍ መልካም ተሞክሮ ካለው አንድ  የኮሪያ የበጎ ፈቃደኛ  ግብረ ሰናይ  ድርጅት ጋር በጋራ ለመስራት ተስማምቷል።

የመላው ኢትዮጵያ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫልን ለመጀመሪያ ጊዜ አስተናግዶ በስኬት ማጠናቀቁን የተናገሩት ደግሞ የመላው ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት  ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አባይ በላይነህ ናቸው።

"የመቀሌ    ዩኒቨርስቲ ከራሱ አልፎ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ነው"ያሉት አቶአባይ ለመላው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች  የስፖርት  ፌስቲቫል  እያደረገ ያለው ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሃገራችን የስፖርት ልማት ዘርፉን ወደ ላቀ ምእራፍ እንዲሸጋገርና ለሃገር በጎ ገጽታ ግንባታ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ እያሳየ ያለው ቁርጠኝነትና እያደረገ ያለው የስራ ትጋት ይበል የሚያሰኝ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ሁለት ታላላቅ የስፖርት ፌስቲቫሎች እንዲያስተናግድ እጩ ካደረጉት ምክንያቶች መካከልም በአካባቢው ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ባለቤት መሆኑን፣ታሪካዊ ቅርሶችና የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች መኖራቸውን፣በሃገሪቱ ውስጥ ያለው አስተማማኝ ሰላምና በስፖርት ፌስቲቫሎቹ ለሚሳተፉ ስፖርተኞችና እንግዶችን የሚያስተናግድባቸው በቂ ዘመናዊ ሆቴሎች መኖራቸውን በመረጋገጣቸው ጭምር መሆኑን ተገልጸዋል።

ይህም በአጠቃላይ ሃገራችን በተለይ ደግሞ መቀሌ ከተማን ይበልጥ ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ጋር እንድትተዋወቅ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥራላት  በመሆኑ መላው የከተማ ነዋሪዎችም የስፖርት ፌስቲቫሎቹ ተጀምረው እስኪጠናቀቁ ድረስ የተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት ባህሉን ማሳየት ይጠበቅበታል።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ እየታየ ያለው መነሳሳትም በሌሎች አቻ ዩኒቨርሲቲዎች አርአያነቱ እንዲደገም መትጋት ያስፈልጋል መልእክቴ ነው።የስፖርት እድገት የአንድ ግለሰብና ተቋም ጥረትና ትጋት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ወገን ርብርብ የሚጠይቅ ነውና የየድርሻችንን እንወጣ ።

Published in ዜና-ትንታኔ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን