አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 08 May 2017

አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2009 ዘላቂ የእንስሳት ሀብት ልማት ማካሄድ ለከተማ ነዋሪዎች የሥራ እድል ለመፍጠርና የምግብ አቅርቦትን ለመጨመር እንደሚያስችል ተገለጸ።

የሰባተኛው ዓለም አቀፍ ዘላቂ የእንስሳት ሀብት ልማት አጀንዳ የባለድርሻ አካላት የአጋርነት ጉባኤ በአዲሰ አበባ እየተካሄደ ነው።

የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ በጉባዔው ላይ እንደገለጹት፤ የእንስሳት ሀብት ልማት ማካሄድ ለከተማ ነዋሪዎች የሥራ እድል በመፍጠርና የምግብ አቅርቦትን እንዲጨምር በማድረግ በኩል አስተዋጽኦ አለው።

በተጨማሪም የምግብ ዋጋ ለመቀነስ እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት።

“የእንስሳት ሀብት ልማት በማጠናከር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ ብልፅግናን ለማምጣት ይቻላል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ዘርፉን ለማሳደግና ለማዘመን የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ጠቁመዋል።

አገሪቷ ለተያያዘችው ለአየር ንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ዘርፉ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የእንስሳት ሀብት መሪ እቅድ በማውጣት ላይ መሆኑንም አመልክተዋል።

በዓለምአቀፉ የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የግብርና እና የሸማቾች ጥበቃ ክፍል ረዳት ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ረን ዋንግ፤ ዘላቂ የእንስሳት ሀብት ልማት ረሃብን ለማጥፋት እና ድህነትን ለመዋጋት ለሚደረገው ጥረት ውጤታማነት ትልቅ ሚና አለው።

በዘላቂ የእንስሳት ሀብት ልማትን በዘመናዊ መንገድ ሲተገበር የመሬት መሸርሸርን፣ የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ ለሚመጣው የሕይወታዊ ሀብት መጥፋት ችግርን ለመግታት ሁነኛ መንገድ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ጄኔራል ጂሚ ስሚዝ በበኩላቸው  እንስሳት ለተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት እንዲሁም ለምግብ ዋስትና ማረጋገጥ  አኳያ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ለብዙዎች የስራ እድል በመፍጠርም አስተዋጽኦ እንዳላቸው ነው የገለጹት።

በአዲሰ አበባ እየተካሄደ ባለው ሰባተኛው አለም አቀፍ ዘላቂ የእንስሳት ሀብት ልማት አጀንዳ  የባለድርሻ አካላት ጉባኤ በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን በማገናኘት ልምድና ተሞክሮዎችን እንዲለዋወጡ በማድረግ የዘርፉን ዘላቂነትና ውጤታማነት ለማረጋገጥ ያለመ ነው።

በጉባኤው ከሁሉም አህጉራት የተወጣጡ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሲሆኑ፤ ጉባኤው እስከ ግንቦት 4 ቀን 2009 ዓ.ም እንደሚቆይም ተነግሯል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2009 የፕሬዚዳንት አንድሬ ሴባስቲያን ዱዳ የአዲስ አበባ ጉብኝት የኢትዮ-ፖላንድን ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ። 

የፖላንዱ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ጉብኝት ለማድረግ ትናንት አዲስ አበባ ገብተዋል።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ከፖላንዱ አቻቸው ጋር በአገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ በብሔራዊ ቤተ መንግስት ተወያይተዋል።

የአገራቱን የጋራ ጥቅሞች በሚያስከብር መንገድ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል መስማማታቸውን ፕሬዚዳንቶቹ ከውይይታቸው በኋላ በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ "ኢትዮጵያና ፖላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ከጀመሩ ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠሩ ቢሆንም ያላቸውን አቅም ወደ ጋራ ጥቅም ከመቀየር አንጻር የሚጠበቀውን ያህል አይደለም" ብለዋል።

የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት የአገራቱን የትብብር መስኮች፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር በማሳደግ ግንኙነታቸውን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረውም ተናግረዋል።

የኢትዮ-ፖላንድ የንግድና ኢንቨስትመንት መጠን 35 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን የፖላንድ ባለሃብቶች በግንባታ፣ በኬሚካልና በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ እየተሳተፉ ነው።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ኢትዮጵያ በፖላንድ መዲና ዋርሶው ኢምባሲዋን እንድትከፍት ከፕሬዚዳንት ዱዳ የቀረበላቸውን ጥያቄ መቀበላቸውንና ኢምባሲው እንደሚከፈት አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ አገር ብትሆንም የፖላንድ ባለሃብቶች ተሳትፎ የሚፈለገውን ያህል ባለመሆኑ የፕሬዚዳንት ዱዳ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ፖላንድ በመጪው ዓመት በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ለመሆን ላቀረበችው ጥያቄ ኢትዮጵያ ድጋፍ እንድታደርግም ለፕሬዚዳንት ሙላቱ ከፖላንዱ አቻቸው ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

"ኢትዮጵያ ድጋፍ እንድታደርግ ከፖላንድ መንግስት የቀረበላትን ጥያቄ በአዎንታ ትመለከተዋለች፤ ድጋፉን አስመልክቶ ግን በቀጣይ በዲፕሎማሲ መንገድ መልስ ትሰጣለች" ብለዋል ዶክተር ሙላቱ።   

የፖላንድ ፕሬዚዳንት አንድሬ ሴባስቲያን ዱዳ በበኩላቸው "በአፍሪካ የተለየ ቦታ ያላት ኢትዮጵያ ፖላንድ ከአፍሪካ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ዋነኛ አጋራችን ናት" ብለዋል።

በፖላንድ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ አፍሪካን በመጎብኘት የመጀመሪያው የሆኑት ፕሬዚዳንት ዱዳ በአዲስ አበባ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖላንድ ኩባንያዎች በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስኮች ያላቸው ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው ተጨማሪ ኩባንያዎች እንዲመጡ መንግስታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል ፕሬዚዳንት ዱዳ።

ሁለቱ አገራት "ዓለም አቀፋዊና የሁለትዮሽ የትብብር አጀንዳዎችን ለማሳደግ ፍላጎት አላቸው" ያሉት ፕሬዚዳንት ዱዳ "ከዓለማችን የፈጣን ኢኮኖሚ ባለቤትና ከአፍሪካዋ መዲና ኢትዮጵያ ጋር በፖለቲካና ኢኖሚያዊ ጉዳዮች ይበልጥ መተሳሰር እንፈልጋለን" ነው ያሉት።

ፕሬዚዳንት ዱዳ ትናንት በኢትዮጵያ ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የአዳማ አውሞቲቭ ኢንዱስትሪን የጎበኙ ሲሆን በነገ ውሏቸው ከአፍሪካ ኅብረት የስራ ኃፊዎች ጋር በፖላንድ-አፍሪካ ግንኙነት ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

ፖላንድ በአፍሪካ ያላት የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር በማደግ ላይ ሲሆን ከአምስት ዓመታት በፊት ከነበረበት 300 ሚሊዮን ዶላር አሁን ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል።

አሴኮና ዩረሰስ የተሰኙ የፖላንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በአይሲቲና አውቶሞቭ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተሰማርተዋል።

በአፍሪካ-ፖላንድ ግንኙነት ታሪክ አገሪቱ ከደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዚያ፣ አልጄሪያ፣ ሞሮኮና ግብፅ ጋር በአንጻራዊነት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ያላት ሲሆን አሁን የፖላንድ ኩባንያዎች ትኩረታቸውን ወደ ኢትዮጵያ አድርገዋል።

Published in ፖለቲካ

ሚያዝያ 30/2009 ላለፉት 19 አመታት በኬንያና ታንዛኒያ ሲከናወን የቆየው የኮንስትራክሽን አውደርዕይ ገበያዋ በፍጥነት በማደግ ላይ በሚገኘው ኢትዮጵያ 150 የአገር ውስጥ እና አለም አቀፍ ተሳታፊዎችን በመያዝ  ከግንቦት 4 እስከ 6 በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚዘጋጅ ፒአር ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

ኢትዮጵያ በአለም ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ ጥቂት አገራት አንዷ ስትሆን ባለፉት 12 ተከታታይ አመታት ባለሁለት አሀዝ እድገት ማስመዝገቧን ድረ ገጹ ጠቅሷል፡፡

ቢዩልድ ኤክስፖ 2017 የተሰኘው አውደርዕይ ኢትዮጵያ ውስጥ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ጎብኚዎች ቢታደሙበት ብዙ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡

በኤክስፖው ላይ ከ 22 አገራት የሚመጡ አለም አቀፍ ኩባንያዎች የዘመኑን ቴክኖሎጂ የተላበሱ የግንባታው ዘርፍ ማሽኖችንና መሳሪያዎችን  ለእይታ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡

በኤክስፖው ላይ ተንቀሳቃሽ የድንጋይ መፍጫ በቻይናው ሆንግ ዚንግ ማሽነሪ፣ የእሳት አደጋ መከላከያ ዘዴና የውሃ ቧንቧ በጣሊያኑ ዚጊኦቶ እና ኩባንያው፣ የመሬት ቅየሳና የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች በጀርመኑ ጂኦማክስ ኤጂ፣ የፕላስቲክ ቱቦና የጣራ መስሪያ እቃዎች በእንግሊዙ አሊአክሲስ ኩባንያ የሚቀርቡ ሲሆን የደቡብ ኮሪያ፣ የታይላንድ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ የሳኡዲ አረቢያና የግሪክ ኩባንያዎች በኤክስፖው ላይ እንደሚካፈሉ  አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡

“ኤክስፖውን በኢትዮጵያ እንድናከናውን ደንበኞቻችን በተደጋጋሚ ሲጠይቁን ነበር፡፡ የ 20 አመት ምስረታችንን ምክንያት በማድረግ ኤክስፖውን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማከናወን ስንወስን ያገኘነው አዎንታዊ ምላሽ አስገራሚ ነበር”  በማለት የኤክሶ ግሩፕ የሽያጭ ዳይሬክተር ማክስ ልዊስ ተናግረዋል፡፡

በቢዩልድ ኤክስፖ ኢትዮጵያ ታዋቂ የኢንዱስትሪ ኤክስፐርቶች ባለድርሻ አካላትና ውሳኔ ሰጪ አካላት እንደሚሳተፉም ተነግሯል፡፡በዝግጅቱ አዳዲስ ምርቶች ፣የገበያ ትስስርና አዲስ ግንኙነት ለመፍጠር ከመቻሉ በላይ ተጨማሪ የገበያ እድል  እንደሚገኝበት ድረ ገጹ ጠቅሷል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2009 ለፍትህ አገልግሎት አሰጣጡ ቅልጥፍናና ጥራት የኅብረተሰቡ ተሳትፎ የተሟላና የተዋጣለት እንደሆነ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለጸ።

በፍትህ ሳምንት ከኅብረተሰቡ ጋር የተካሄዱ ውይይቶች የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን ማየት የሚያስችሉ ግብዓቶች ተገኝተውባቸዋል ተብሏል።

7ኛው አገር አቀፍ የፍትህ ሳምንት "የሕግ የበላይነት ለዘላቂ ሠላምና ለሕዝቦች አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 6 ቀን 2009 ዓ.ም የሚከበር ሲሆን ዛሬ በአዲስ አበባ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ተከፍቷል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና የፍትህ አካላት አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዳኜ መላኩ እንደገለጹት በመዲናዋ ከተለያዩ የህብረተሰብ  ክፍሎች ጋር በፍትህ ዙሪያ በተካሄዱ ውይይቶች ጠቃሚ ግብዓቶች እንደተገኙ ተናግረዋል።

ከኀብረተሰቡ የተነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትና የፍትህ ተቋማትን አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የፍትህ ሳምንት መከበሩ "የፍትህ ተቋማትን የተጠያቂነት አሰራር ከሚያጎለብቱበት እንዲሁም በህዝብና በተቋማቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ከሚያጠናክሩ አሰራሮች መካከል አንዱ ነው፡፡’’ ብለዋል፡፡

የፍትህ ሣምንቱ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሰሆን ዛሬ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ኮሚሽኖች እንዲሁም የጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍትህ አካላትና ህብረተሰቡ የተሳተፉበት የእግር ጉዞ ከሜክሲኮ አደባባይ እስከ ልደታ ፍርድ ቤት ተካሂዷል።

በፍትህ ተቋማቱ የተዘጋጀውና በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ የተከፈተው ዓውደ ርዕይም ከሚያዚያ 30 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል።

Published in ማህበራዊ

ሰመራ ሚያዝያ 30/2009 በሰመራ ሎግያ ከተማ ለወጣቶች ተጠቃሚነት ተገቢው ትኩረት ባለመሰጠቱ ጊዚያቸውን በአልባሌ ስፍራ እንዲያሳልፉ ምክንያት መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለፁ ።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን የወጣቶችን በተለያዩ ዘርፎች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሰመራ ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ትናንት ውይይት አካሂዷል ።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በንግድ ስራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ ዘይነብ አብረሃ እንደተናገሩት የክልሉን ወጣቶች በስራ እድል ፈጠራ   ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች ውስን ናቸው፡፡

ለወጣቱ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ያልተገነቡ በመሆናቸው አብዛኛውን የእረፍት ጊዜያቸው በአልባሌ ቦታዎች ሲያሳልፉ እንደሚስተዋሉ  ተናግረዋል፡፡

"የወጣቶች አፍላ ጉልበትና እውቀት ለፀረ- ድህነት ትግሉ ማዋል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ያሉት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ዶጌ ቢዳሮ ናቸው፡፡

"የክልሉ መንግስት ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመረው የምክክር መድረክ ሳይቆራረጥ መቀጠል አለበት" ብለዋል፡፡

ሌላዋ ተሳታፊ መምህርት አለም መንግስቱ በበኩላቸው የወጣቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት  በተናጠል ከመሆን ይልቅ በቅንጅት መስራት ይገባል" ብለዋል፡፡

የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀራረብ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል ።

በተለይም  ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢ እንዲሆኑ በአመለካከትና በእውቀት ለመቅረፅ ወላጅችና በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመላክተዋል ።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ተወካይ አቶ እስማኤል ወልዱ እንደገለፁት በክልሉ የወጣቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።

ወጣቱን በስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ ለማድረግና  የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለማስፋፋት የተጀመሩ ስራዎችን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በክልሉ ወጣቶች ትርፍ ጊዜያቸውን በአልባሌ ስፍራ እንዳያሳልፉ በ13 ወረዳዎች ከ300 በላይ ታዳጊ ወጣቶች በፕሮጀክት ታቅፈው በ12 ስፖርት አይነቶች ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ በክልሉ 32 ወረዳና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ስራ አጥ ወጣቶችን የመለየት ስራ እተካሄደ ነው ።

ወጣቱን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል  አቶ እስማኤል ጠይቀዋል።

Published in ማህበራዊ

አሶሳ ሚያዝያ 30/2009 የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሁለት ወረዳዎችና አንድ ከተማ አስተዳደር የተሳተፉበት የካራቴ ስፖርት ውድድር ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተጀመረ።

በውድድሩ ባምባሲና አሶሳ ወረዳን እንዲሁም አሶሳ ከተማ አስተዳደርን በመወከል 42 ስፖርተኞች ተሳታፊ  ሆነዋል ።

የውድድሩ አላማ በቀጣዩ ወር በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት በቢሾፍቱ ከተማ በሚካሄደው የኢትዮጵያ ካራቴ ሻምፒዮና ክልሉን ወክለው የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ መሆኑን የክልሉ የማርሻል አርት ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ከማለዲን ኡስማን ገልፀዋል፡፡

ውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች፣ በተለያዩ ክብደቶች በነጠላና በቡድን ነፃ ፍልሚያና በአርቱ ዘርፍ በርካታ ግጥሚያ እንደሚካሄድበት ተገልጿል ።

ከሌሎች የቴኳንዶ ስፖርቶች ቀድሞ በ1999 ዓ.ም በክልሉ መዘውተር የጀመረው የካራቴ ስፖርት በአሶሳ ዞን ብቻ ተወስኖ ቢቆይም በአሁኑ ወቅት በሌሎች ዞኖችም እየተጀመረ መሆኑን ተጠቁሟል ።

ስፖርቱን ለማስፋፋት አሰልጣኞች ስፖርቱ ባልተዘወተረባቸው የክልሉ ሁለት ዞኖች ማሰልጠኛዎች እንዲከፍቱ እንዲሁም ስፖርቱን በታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ለማካተትና ለአሰልጣኞች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ማርሻል አርት ፌዴሬሽን አስታውቋል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2009 የንግድ ሚኒስቴር በሥነ-ልክ መሣሪያዎች ላይ የሚያደርገው ቁጥጥርና የሚወስደው እርምጃ ዝቅተኛ መሆን በገቢና ወጪ ንግዶች ላይ ችግሮች እንዲከሰቱ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የንግድ ሚኒስቴርን በገቢና ወጪ ዕቃዎች እንዲሁም የህጋዊ ሥነ-ልክ ደረጃዎች ፍተሻ አፈፃፀም የተከናወነ የኦዲት ግኝት ሪፖርት ዛሬ አዳምጧል። 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንደገለጹት፤ ከጅምላ አከፋፋዮች እስከ ቸርቻሪዎች ድረስ የልኬት መሣሪያዎችን በአግባቡ ባለመጠቀማቸው በገቢና ወጪ ንግዶች ላይ ችግሮች በማስከተል በአገርና ሕዝብ ላይ ጉዳት እያስከተሉ ናቸው።

ለዚህም እንደ ምክንያት ዘርፉ ለኪራይ ሰብሳቢነት መጋለጡ፣ የልኬት መሣሪያዎችን በየወቅቱና በድንገት የሚፈትሹ ባለሙያዎች ገለልተኛ ያለመሆናቸው ተጠቃሽ ናቸው። 

በተጨማሪም የአዋጆች ፣ ደንቦችና መመሪያዎች ያለመጽደቃቸውም በምክንያትነት ያነሱት ሃሳብ ነው።

''ይህ ባለመደረጉ ቁጥጥሩና የሚወሰደው እርምጃ አናሳ እንዲሆን አድርጎታል ነው'' ያሉት።

ሚኒስቴሩ “እስካሁን ጸድቀው ወደ ተግባር መግባት ሲገባቸው የተጓተቱና የዘገዩ አዋጆች፣ መመሪያዎችና ደንቦችን ፈጥኖ በማጽደቅ ወደ ተግባር መግባት ይኖርበታል” ሲሉ አሳስበዋል።

የአዋጆቹ መጽደቅ የልኬት መሣሪያዎችን ሆን ብለው የሚያዛቡ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ ግልጽና አስተማሪ የሆነ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚያስችል ነው አጽንኦት የሰጡት።

አምባሳደር መስፍን እንደገለጹት፤ ኅብረተሰቡ የልኬት መሣሪያዎችን በተመለከተ ማድረግ የሚገባውን እንዲያውቅና እንዲጠይቅ ራሱን ያሳተፈ እንቅስቃሴ ማከናወን ያስፈልጋል።

ህዝቡ ችግሮች ሲያጋጥሙት ለሚኒስቴርና ለሚመለከታቸው አካላት በቀጥታ በማሳወቅ እርምጃ እንዲወሰድ የግንዛቤ ሥራ መስራት አለበት ብለዋል።

የገቢና ወጪ ምርቶች የኅብረተሰቡን ደህንነት፣ ጤንነትና ጥቅም የጠበቁ እንዲሆኑም በትኩረት መስራት እንዳለበት ነው የተናገሩት።

በሪፖርቱ ላይ በቀጣይ መወሰድ ስላለባቸው ጉዳዮች አስተያየት ያቀረቡት የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ ከዋናው ኦዲተር የተሰጡትን የክዋኔ ኦዲት ግኝት ለማስተካከል የሚያደርገውን ጥረት አድንቀዋል።  

በቀጣይም መስሪያ ቤቱ “የአገሪቷ የንግድ አሰራርና ሥርዓት ከአደጋ ለመከላከል፣ የገቢና ወጪ ምርቶች ደረጃቸውንና ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ በዘርፉ ከተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት ይጠበቅበታል” ነው ያሉት። 

የምርቶችን ጥራትና ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚከናወኑ ተግባራትን ማስፋት እንዳለበት ጠቅሰው ፤ ይህም የአገርና የባለኃብቱ ጊዜና ገንዘብ ለመቆጠብ እንዲሁም በገቢዎችና ጉምሩክ አካባቢ የሚፈጠረውን የቦታ ጥበት ለማቃለል እንደሚያስችልም ገልጸዋል። 

በአገሪቷ ደረጃ ያልወጣላቸው ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የታወቀ የሶስተኛ ወገን የብቃትና የጥራት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንዲቀርብ መደረጉ የሚበረታታ ነው።  

ምስክር ወረቀቱ ለህገ ወጥ ተግባር ውሎ በሕብረተሰቡ ጤና፣ ደኅንነት፣ ጥቅምና በአገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት እንዳያስከትል በጥንቃቄ መታየት እንደሚኖርበት አመልክተዋል።   

የንግድ ሚኒስትሩ ዶክተር በቀለ ቡላዶ በበኩላቸው፤ መሥሪያ ቤቱ የደረጃ መሥፈርቱን መሰረት በማድረግ “የምርቶች ጥራትና ቁጥጥርና መለኪያ መሣሪያዎች ትክክለኛነት በማረጋገጥ የሕብረተሰቡን ደኅንነት፣ ጤናና ጥቅም ለማስጠበቅ እየሰራ ይገኛል” ብለዋል።

የአገርን ኢኮኖሚ፣ የሕብረተሰቡን ጤናና ደህንነት የሚጎዱ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ በሚኒስቴሩ፣ በክልሎችና በ15 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የአደረጃጀትና አቅም የመገንባት ሥራ እየተሰራ ነው።  

በተጓዳኝም ወጥ የሆነ አሰራር ሥርዓት እንዲዘረጋ የተለያዩ አዋጆችና ሕጎችን የማውጣትና ግብዓት የማሰባሰብ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በገበያ ላይ የባለሙያዎችና የሥነ-ልክ መሣሪያዎች ችግር መኖሩን ተናግረዋል።

ችግሩን ለማቃለል ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበርና ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ በተግባረዕድ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ሥልጠና መስጠት መጀመሩን አብራርተዋል።     

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሶስተኛ ወገን ምስክር ወረቀት በሐሰተኛ መንገድ ተሰርቶ እንዳይቀርብ በጥንቃቄ የመመርመር ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

በላይነህ ባህሩ /ኢዜአ/

አምና ሰማይ ሲለግም ዘንድሮ ምድር ተመረዘች። በሰማዩ መለገም ዝናብ ሲጠፋ ምድሪቱም በተምች ተመታች - በጋሞ ጎፋ ሰማይና ምድር። አካባቢው በድርቅና በተባይ ተመታ።

በድርቁ ምክንያት በዞኑ ቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ 85 ሺህ ቤተሰቦች ለእለት ደራሽ እርዳታ እንዲጋለጡ አስገድዷል ። ከ11 ሺህ በሚበልጡ የቤት እንስሳት ላይም አደጋ አደርሷል።

በጥምር ግብርና (በሰብል ልማትና እንስሳት እርባታ) ለሚተዳደረው ለጋሞ ጎፋ ዞን ህዝብ ፈታኝ የሆነ የድርቅ ፈተና የመጋፈጥ ዕጣ ፈንታ ተጋረጠበት። መቼም የአየር መዛባት ያመጣው ጦስ ነውና ተስፋ ባለመቁረጥ ወደ መፍትሔው ማምራት የተሻለ አማራጭም ተመራጭም ሆነ።

መንግስት ለችግሩ ሁለት መሠረታዊ መፍትሔዎችን አበጅቻለሁ አለ።  አንደኛው በድርቁ ምክንያት ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ ቤተሰቦችና ለቤት እንሰሳት የአስቸኳይ ጊዜ እህል፣ መኖና ውሃ ድጋፍ ማቅረብ ነው ፤ ሁለተኛው ደግሞ ባለፈው ዓመት በድርቁ ምክንያት  የቀነሰውን ምርት በዘንድሮው የበልግ አዝመራ ማካካስ ልዩ ትኩረት የተሰጠበት አቅጣጫ መሆኑን ይፋ ተደረገ።

በሁለቱም የመፍትሔ አቅጣጫዎች ለውጥ ለማምጣትም ወደ ስራ ተገባ። የእለት ደራሽ እርዳታ የማቅረቡ አማራጭ   በጥሩ ሁኔታ ተሳካ ። በእንስሳት ላይ መጠነኛ ጉዳት ቢደርሰም በሰው ህይወት ላይ ግን የከፋ  አደጋ ሳያደርስ መከላከል ተችሏል።

ሁለተኛውን መፍትሔ ሌላ ፈተና ገጠመው። በበልግ እርሻ የተሸፈነው የበቆሎ ሰብል በተምች ተመታ። በአንድ ጊዜ 25 ሺህ እንቁላሎችን በመጣል ራሱን በፍጥነት የሚያባዛው ይኽው አደገኛ ተባይ በፍጥነት የመዛመትና የመስፋፋት አቅም አለው።

ሴቷ ተምች ከ22 እስከ 37 ሚሊ ሜትር በሚሰፋ ክንፎቿ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከ1 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የመጓዝ አቅም አላት ነው የሚባለው። በተለምዶ ከእሳትራት ጋር ያመሳስላታል።

ተምቹ  በፍጥነት በመብረር በቆሎን በመንጋ የመውረር ባህሪ ያለውና ለቁጥጥር አሰቸጋሪ መሆኑን የዘርፋ ባለሙያ አቶ አክሊሉ አወቀ ይገልፃሉ። አቶ አክሊሉ የካምባ ወረዳ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት የሰብል ልማት ባለሙያ ናቸው። ተባዩ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ሐምሌ 2016 በደቡብ ምዕራብ ናይጀሪያ ፣ ቤኒንና ቶጎ መከሰቱንና ቀጥሎም በታህሳስ ወር አጋማሽ በደቡብ አፍሪካ ዝምቧቡዌ ፣ ዛምቢያ፣ ሞዛምቢክ፣ ማላዊ፣ ናሚቢያ ፣ ቦትስዋና ፣ ኮንጎ፣ ሎሴቶና በቅርቡም ታንዛኒያ መከሰቱን ያስረዳሉ ።

በሀገራችን ከወራት በፊት በተለይ በደቡብ ክልል ምዕራባዊ ዞኖች የታየው ይኽው ፀረ በቆሎ ተባይ በፍጥነት ወደ ደቡብ ምዕራብ ዞኖች በመሰራጨት በጋሞ ጎፋ ዞን 467 ሄክታር የቆሎ ማሳ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመውረር ጥቃት አድርሷል ።

ተባዩ ከኬኒያ በመሻገር በደቡብ ኦሞ ዞን የታየው መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓም ሲሆን  በዞኑ ባሉት 10 ወረዳዎች በ1ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተዘራው የበቆሎ ሰብል ለመወረር የወሰደው ጊዜ ከአንድ ሳምንት ያነሰ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አሸብር ደምሴ ይገልፃሉ ።

ተባዩ ከበቆሎ ሌላ ከ80 በላይ ሰብሎችን የማጥቃት ባህሪ እንዳለውም ያብራራሉ ።  በተለይ በብርዕና አገዳ ሰብሎች(በቆሎ፣ ማሸላ፣ ሰንዴ ገብሰ፣ ጤፍ፣ ዳጉሳና ሩዝን) በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጥፋት ለከፋ የምግብ እጥረት የሚያጋልጥ አደገኛ ተባይ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የእንስሳትን ግጦሸ በማውደም ለመኖ እጥረት ከማጋለጡም በላይ ከፍተኛ የጋማ ከብቶችን ጤና በማወክ ሞትን የሚያስከትል ነው። በዚህም ከ1ሺህ 100 በላይ የዞኑን አርሶ አደሮች የጉዳቱ ሰለባ ከማድረጉም በላይ ጠቅላላ የግብርና ኢኮኖሚውን ጥያቄ ውስጥ እስከ መክተት ደርሷል ።


በጋሞ ጎፋ ዞን በአማካይ በበልግ እርሻ ከሚለማው 150 ሺህ ሄክታር መሬት 36 ከመቶ የሚሆነውን ማሳ የሚሸፈነው በበቆሎ ሰብል ነው ። በቆሎ የዞኑ አርሶ አደሮች የገጠር ስራ እድል ፈጠራ ዋነኛው መስክ መሆኑንም የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ጋሻው ሞላ ይገልጻሉ።

በቆሎ አብዛኛው ሰው በቀላልና በዝቅተኛ ወጪ ኃይል ሰጪ ምግብ  የሚያገኝበት ሰብል በመሆኑ ለምግብ ዋስትና ካለው አሰተዋጽኦ ሌላ ከህብረተሰቡ የዕለት ተለት እንቅሰቃሴ ውሰጥ ያለው ቁርኝት ከፍተኛ ነው ይላሉ - አቶ ጋሻው።

ፍሬው ለምግብነትና ለባህላዊ መጠጦች እንዲሁም አገዳው ለእንሰሳት መኖና ለማገዶም ጭምር ያገለግላል ።


ተምቹን ከመከላከል አንጻር ሲታይ ደግሞ በአንድ ሰብል ላይ ከሁለት በላይና በአንድ ካሬ ሜትር ግጦሽ መሬት ላይ ከ10 በላይ ትሎች ከታዩ የመቆጣጠር እርምጃ መወሰድ እንዳለበት የዘርፋ ባለሙያዎች ይመክራሉ ።

ማላታይን፣ ካርባሊን፣ ሱማታይን፣ ሳይፐርሜትሪንና ዲያዝኖን የተባሉ የፀረ ተባይ ከሚካሎች ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን ማላታይን በገበያ ላይ በቀላሉ የሚገኝና በፍጥነት ለመቆጣጠር የሚያስችል ተመራጭም ነው ይባላል።

ይሁን እንጅ በጋሞ ጎፋ ዞን በኬሚካል ርጭት የተጀመረው የመከላከል ሰራ የተባዩን ፈጣን ስርጭት ሊገታው አልቻለም ነበር።

አቅም የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ተባዩን መከላከል አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን የተገነዘበው የዞኑ አስተዳደር ሌላ ሰትራተጅ መቀየሱ ግድ ሆነበት። አርሶ አደሩ የራሱንና የቤተሰቡን ጉልበት በማስተባበር ተባዩን የመግደል ዘመቻ አዲስ ስትራተጂ ሆኖ ተቀየሰ። በኬሚካል ርጭት መግታት ያልተቻለውን ተባይ በጋራ ማጥፋት የሚያስችል አማራጭ ሁሉ እንዲጠቀም አርሶ አደሩ እድል አገኘ ።

አርሶ አደሩ በዘመቻው ተባዩን መግደል ቀዳሚ አማራጭ አድርጎ ተረባረበ።  በእጅ መጨፍለቅና የተደበቁ ትሎችን በጃንጥላ ሸቦና በጃርት እሾክ መግደል የመጀመሪያው እርምጃ ሆነ። አዛባ በበሬ ሸንት ተበጥብጦም ጥቅም ላይ ውሏል። የተወቀጠ ሚጥሚጣም እንዲሁ።

የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ጨምሮ 3 ሺህ 121 የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፋበት ከኬሚካሉ ርጭት ጎን ለጎን አርሶ አደሩ ይዞ የቀረበውን የመከላከል አማራጭ በመጠቀም በዞኑ በ10 ወረዳዎች ባሉ 72 ቀበሌዎች የተከሰተውን ተምች በሰብሉ ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር እንደተቻለ ከዞኑ እርሻና ተፈጥር ሀብት ልማት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያስረዳል ።

በዘመቻው ተምቹን ከበቆሎ ማሳ መከላከል ቢቻልም አልፎ አልፎ በስኳር ድንች፣ በማሽላ፣ በሰሊጥና በግጦሽ ማሳዎች ላይ እየታየ ነው። የበቆሎ ማሳ ለመከላከል  10 ሺህ 081 ሊትር “ማላታይን” የተባለ ኬሚካል ጥቅም ላይ ቢውልም ለተባዩ መጥፋት ከፍተኛውን ድርሻ ያበረከተው ግን አርሶ አደሩ ይዞ የቀረባቸው የመከላከያ ዘዴዎች መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአርባምንጭ እጽዋት ጤና ክሊኒክ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉዓለም መርሻ ናቸው።

በተለይ በበሬ ሸንት የተበጠበጠው አዛባ ተባዩን የመግደል አቅሙ ከፍተኛ እንደነበረ ይናገራሉ።

በዚህም የተከሰተው የተምች ወረርሸኝ ከባህሪው አንጻር አስቸጋሪ ቢሆንም መከላከል እንደሚቻል ትምህርት የተገኘበት ነው ባይ ናቸው ።

አርሶ አደሮች የተጠቀሙትን ባህላዊ የመከላከል ዘዴ በደቡብ ኦሞ ዞን በማሌ ወረዳም ተሞክሮ ውጤት ማስገኘቱን አብራርተዋል። ተባዩ በተከሰተበት ሌሎች አካባቢዎችም አርሶ አደሮች እንዲጠቀሙበት መክረዋል።

አርሶ አደሩ ተባዩን ለመከላከል የተጠቀማቸውን ኬሚካሎችን ሳይንሳዊ ለማድረግ በክልሉ እየተጠና መሆኑንም  ጠቁመዋል።

አርሶ አደሩ በሰብሉ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመቅረፍ የተጠቀመው የመከላከል ፈጠራ ዘዴ ወራሪውን መጤ አደገኛ ተምች መመከት ችሏልና ሌሎችም ቢጠቀሙበት መልካም ነው እንላለን። በሳይንሳዊ ዘዴ ቢታገዝ ደግሞ ፋይዳው የጎላ ሊሆን ስለሚችል ይታሰብበት መልእክታችን ነው።

Published in ዜና ሓተታ

ደብረ ብርሃን ሚያዝያ 30/2009 በአማራ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ህብረተሰቡ  ለትምህርት ዘርፍ ከ744 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው አስተዋፅኦ ማድረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የክልሉ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች በሰሜን ሸዋዞን በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰሞኑን ጎብኝተዋል ።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለፁት ህብረተሰቡ  ካደረገው ድጋፍ ውስጥ 396 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብሩ በጥሬ ገንዘብ የተለገሰ ነው።

"ህብረተሰቡ ባደረገው ድጋፍ  ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የ1 ሺህ 383 ተጨማሪ ክፍሎች ግንባታ ፣ የ3 ሺህ 342 የመማሪያ ክፍሎች ጥገና ፣ የ169 የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና  የ87 ቤተ-መፅፋት ግንባታ ተጠቃሽ ናቸው" ብለዋል ።

በጉብኝቱ በአጣየ ከፍተኛ መሰናዶና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያለው የመምህራንና የወላጅ መምህራን ህብረት ቅንጅታዊ አሰራር በአርያነቱ ማሳያ እንደሆነም ተጠቅሷል።

የተፈጠረው መልካም ግንኙነትም ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹ በማድረግ ተማሪዎች እውቀታቸውን በቤተ- ሙከራ እንዲያዳብሩና የተሻለ ክህሎት እንዲኖራቸው መደረጉ የሚበረታታ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ዞኑ እየተሰሩ ያሉ የቅንጅታዊ የአሰራር ልምዶች ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች መሸጋገር እንዳለባቸው ዶክተር ይልቃል አስገንዝበዋል ። 

የአጣየ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ የወላጅ መምህራን ህብረት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ከድር ሀጂ እንደተናገሩት ማህበረሰቡና የትምህርት አመራሮች ተቀናጅተው ለትምህርት ፍትሃዊነትና ጥራት መረጋገጥ እየሰሩ ነው።

ባለፉት አመታት የመማሪያ ክፍሎችን በማደስና አካባቢውን ለመማር ማስተማር ሂደት  ምቹ በማድረግ በተሰሩ ተግባራት የተማሪዎች  የጥናትና ምርምር ዝንባሌ መለወጡን አስረድተዋል።

መምህራንና የአካባቢው ህብረተሰብ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማድረግ ትምህርት ቤቱ ያለበትን የመማሪያ ክፍል ጥበት ለመፍታት 12 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ባለ አንድ ፎቅ ህንፃ እያስገነቡ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ 

ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል ከደቡብ ጎንደር ዞን የመጡት ወይዘሪት እመቤት ባዩ በሰጡት አስተያየት በጉብኝቱ ህብረተሰቡ ለትምህርት ተቋማት እያደረገ ያለውን ድጋፍ በተጨባጭ ለመመልከት እንደቻሉ ተናግረዋል ።

በሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ የስርአተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ገበየሁ በላይ  በበኩላቸው የአንደኛ ክፍል  ተማሪዎችን ለማብቃት የሚደረገው ጥረትና መምህራንም ከተማሪዎች ባህሪ ጋር በሚዛመድ አቀራረብ ማስተማር መቻላቸው አርአያ መሆኑን ገልፀዋል።

ከክልሉ የተለያዩ ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች የተውጣጡ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች በሰሜን ሸዋ ዞን ስድስት ወረዳዎች በ15 ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደት ጎብኝተዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2009 የአርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካ የካይዘን ፍልስፍናን ተግባራዊ በማድረጉ ከሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳኑን አስታወቀ፡፡

ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ካባ መርጋ ለኢዜአ እንደገለጹት ፋብሪካው ገንዘቡን ያተረፈው በወጭ ቅነሳ መርሃ ግብር መሰረት የካይዘን ፍልስፍናን ተግባራዊ በማድረጉ ነው ፋብሪካው የተለያዩ ማሽኖችና የማምረቻ እቃዎች ላይ የማሻሻያ ስራዎችን በራስ አቅም በማከናወን ወጪዉን መታደግ የቻለው።

በዚህም በግቢው የወዳደቁ ቁሳቁሶች አሰባስቦ አገልገሎት ላይ በማዋልና የተበላሹ ማሽኖችን በራስ አቅም ጠግኖ በመጠቀም ውጤታማ መሆን መቻሉን ነው ።

በብልሽት ምክንያት ከአገልገሎት ውጪ የሆኑ የአገዳ መገልበጫና የፋብሪካ ተረፈ ምርት ማስወገጃ ማሽኖች በግቢው የሚገኙ ቁሳቁሶችን በመጠቀም በፋብሪካው ባለሙያዎች ተጠግነው ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉን ገልጸዋል።

በተለይ ከፋብሪካው የሚወጣው ተረፈ ምርት ካሁን በፊት በሰው ጉልበት ወደ ተሽከርካሪ የመጫኑ ስራ ከፍተኛ ጊዜና ገንዘብ ይጠይቅ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁን ወቅት ካይዘን ተግባራዊ በመድረጉ ውጤታማ መሆን እንደተቻሉንም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የፋብሪካው ባለሙያዎች የአገዳ ማመላለሻና መገልበጫ ማሽኖችን የመገልበጥና የመጫን አቅማቸውን ለማሳደግ ባከናወኑት ተግባር እስከ ሶስት እጥፍ ማሳደግ መቻላቸውን አስረድተዋል።

ተሽከርካሪዎቹ ሶስትና ከዚያ በላይ ማመላለስ የሚጠበቅባቸውን የአገዳ መጠን በአንድ ጊዜ እንዲጭኑ መደረጉም እንዲሁ።

“ካሁን በፊት ማሽኖቹና ቁሳቁሶቹ ካለቦታቸው ተቀምጠው ለስራ እንቅፋት ሆነው ነበር” ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ ፋብሪካውን ለማስጠገን ይወጣ የነበረውን ገንዘብ ማትረፍ መቻሉንም አብራርተዋል።

የፋብሪካው ማሽኖች ለመጠገን የሚያስችል መሳሪያ ወይም ሌስ ማሽን በራስ አቅም በመጠገኑ የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረት አኳያም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል። 

የአርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካ በ2007 ዓ.ም የማምረት ስራውን የጀመረ ሲሆን፤ ለውጭ ገበያ የሚውል ነጭ ስኳር እንደሚያመርትም ይታወቃል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን