አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 07 May 2017

አዲስ አበባ ሚያዚያ 29/2009 የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን ዕውቀትና ክህሎት ለማሳደግ ለአቅም ግንባታ ትኩረት መስጠቱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ሚኒስትሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ይህን ያሉት ከፌዴራል፣ ከክልልና ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ የኮሙኒኬሽን አመራሮች እና  ባለሙያዎች በተዘጋጀ ስልጠና ላይ ነው።

"የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር ግንባታ እንዲሁም በሰላም አብሮ የመኖር እና የአገር ገጽታን የሚገነቡ መረጃዎችን በየጊዜው በማምረት በተገቢው መንገድ ለህብረተሰቡ እንዲደርስ በህዝብ ግንኙነቱ በኩል ያሉ የእውቀትና የክህሎት ክፍተቶችን ለመሙላት ስልጠናዎችን በየደረጃው ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቷል፤ የዛሬው መድረክም የዚህ አንድ አካል ነው" ብለዋል።

በተጨማሪም በቀጣዩ ዓመት 50 ባለሙያዎችን ከፌዴራል እና ከክልል አወዳድሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለማስተማር ከስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

የጽህፈት ቤቱ የህዝብና የሚዲያ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሰይድ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት "ስልጠናው መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር ግንኙነት ለመፍጠርና የመረጃ ፍላጎቱን ለማጣጣም በሚያደርገው ሂደት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን እውቀትና ክህሎት ለማሳደግ ያግዛል"።

በቀጣይም በፌዴራል እና በክልል የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት በመፍጠር ለህዝብ ተአማኒና ሚዛናዊ የሆነ መረጃ ለማቅረብ የባለሙያዎችን አቅም የማሳደጉ ስራ በአጫጭር ስልጠናዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ሰልጣኞች ያገኙትን እውቀት እና ግንዛቤ ካላቸው ልምድ ጋር በማጣመር የዘርፉን የሰው ሃይል የማብቃት ስራ መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሉ ዘርፉ ከልማዳዊ አሰራሮች ወጥቶ በእውቀት እና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንዲመራ የስልጠና መድረኮች አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ብርሃኑ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ የተሰሩ ስራዎች ሳይዛቡ ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ ተመሳሳይ ስልጠናዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ጽህፈት ቤቱ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙትን ተፈጥሯዊ ኃብቶች፣ ታሪካዊ ቅርሶችና መስህቦችን የተመለከተ የስዕል አውደ ርዕይ አሳይቷል።

ከዚህ በተጨማሪ በአቶ ተሾመ ተፈራ የተዘጋጀ "የኢትዮጵያ ህዳሴ" የሚል መጽሐፍ በጽህፈት ቤቱ በኩል ታትሞ ቀርቧል።

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 29/2009 የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ቀጣይ አመራሮችን በመምረጥ ተጠናቀቀ።

"አደረጃጀቶቻችንን በማጠናከር የአገራችንን ወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን" በሚል መሪ ቃል ለሶስት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው ጉባኤው ሰባት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና አምስት የኦዲት ቁጥጥር ኮሚሽነሮችን መርጧል።

በዚህም መሰረት ቀድሞ ፌዴሬሽኑን በፕሬዝዳንትነት ሲመራ የቆየው ወጣት ታረቀኝ አብዱጀባር ከኦሮሚያ ፕሬዝዳንት፤ ዓሊ ሁሴን ከአፋር ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን ተመርጠዋል።

ተመራጮቹ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣትና ወጣቱን በታማኝነት ለማገልገል ቃል ገብተዋል።

ጉባኤው ያለፉትን ሶስት ዓመታት አፈጻጸም የገመገመ ሲሆን የቀጣዮቹን ሶስት ዓመታት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ደግሞ ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ወስኗል።

ፌዴሬሽኑ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እስከ ወረዳ ድረስ መዋቅር በመዘርጋት ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ አባላት በማፍራት ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ የወጣቶችን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን ገልጿል።

Published in ማህበራዊ

ማይጨው ሚያዚያ 29/2009 የገበያ ትስስርና የግብዓት አቅርቦት ችግር ከመስኖ ልማት ተጠቃሚ እንዳንሆን እያደረገን ነው ሲሉ በትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮች ገለፁ፡፡

አርሶ አደሮች ያሉባቸውን ችግሮች ለማስወገድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ አስታውቋል።

የራያ አዘቦ ወረዳ አርሶ አደር ሙላት አብርሃ በሰጡት አስተያየት ዘንድሮ የውሃ ጉድጓድ ተጠቅመው በመስኖ ካለሙት ቲማቲም  እስከ 80 ሺህ ብር ገቢ ለማግኘት አቅደው እንደነበር ገልፀዋል፡፡

ይሁንና የገበያ ትስስር ድጋፍ ባለማግኘታቸው ከምርታቸው ሽያጭ 32 ሺህ ብር ብቻ  እንዳገኙና ቀሪው ምርት ለብልሽት መዳረጉን ተናግረዋል።

ያገኙት ገቢም ለጉልበት ሰራተኞች ያወጡትን ወጪ  እንኳ ማካካስ  እንዳልቻለ  አስረድተዋል።

ከሌሎች 60 ወጣቶች ጋር በማህበር ተደራጅተው በተሰጣቸው መሬት የመስኖ ልማት በማካሄድ ላይ መሆናቸውን የገለፀው ደግሞ የራያ አላማጣ ወረዳ አርሶአደር ወጣት ሃፍቱ ነጋሽ ነው።

ወጣቶቹ ከህዳር እስከ መጋቢት አጋማሽ ድረስ ካለሙት የቲማቲምና ቀይ ሽንኩርት ሽያጭ እስከ 37 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን አስታውቋል፡፡

ሆኖም የመስኖ ልማት ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ በመሆኑ ለስራው ማከናወኛ የሚውል የብድር ድጋፍ ቢፈልጉም ማግኘት ባለመቻላቸው ሙሉ አቅማቸውን በመጠቀም ሰርተው የተሻለ ገቢ ለማግኘት እንቅፋት እንደፈጠረባቸው ገልጿል።

አርሶአደር ንግስቲ ሃፍቱ በበኩላቸው የፀረ ተባይ መከላከያ መድሃኒት ባለመቅረቡ በውድ ዋጋ  ከነጋዴ ገዝተው ለመጠቀም መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህ አመት ካመረቱት የአትክልት ምርት ሽያጭ ከ24 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን የገለፁት አርሶ አደሯ በቀጣይ ለሚያካሂዱት የመስኖ ልማት ውጤታማነት ፀረ ተባይ መድኃኒትን ጨምሮ ለልማቱ የሚያስፈልጉ ግብአቶች በወቅቱ እንዲቀርቡላቸው ጠይቀዋል፡፡

በዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የመስኖ ልማት ቡድን አስተባባሪ አቶ አሰፋ አስረስ በሰጡት ምላሽ የዞኑ አርሶአደሮች  በመስኖ ልማት ስራው ያጋጠማቸውን የባለሙያ ድጋፍ ፣ የገበያና  የመድሃኒት አቅርቦት ችግሮች ለማስወገድ ጥረት እየተደረገ ነው።

በተለይ የገበያ ችግርን ለመፍታት ከትግራይ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ ጋር በመተባበር አርሶ አደሮችን በመቀሌ ከተማ ከሚገኙ የአትክልት ነጋዴዎች ጋር የማስተሳሰር ጅምር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

በዞኑ  በእርሻ ልማት የተሰማሩ ባለሃብቶችን  ከአርሶአደሩ ጋር በማገናኘትም የአትክልት ምርጥ ዘርና የተባይ መከላከላያ መድሃኒት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በዞኑ አምስት ወረዳዎች ካለፈው ህዳር ወር እስከ መጋቢት አጋማሽ ድረስ 40 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለምቷል፡፡

በመስኖ ከለማው ከዚሁ መሬት ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የጓሮ አትክልት፣ የተለያዩ ሰብሎች፣ ጥራጥሬና የቅመማ ቅመም ምርት ተሰብስቧል፡፡

በመስኖ ልማቱ ከ78 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

ጎባ ሚያዝያ 29/2009 በባሌ ሮቤ ከተማ የመጠጥ ውኃ እጥረት በመባባሱ ተቸግረናል ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለፁ ።

በከተማው የመጠጥ ውሃ እጥረት ከተከሰተ ወራቶች ቢቆጠሩም መፍሄ የሚፈልግ አካል መጥፋቱን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ።

በከተማው የበሀ-ቢፍቱ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አማኔ አልይ በሰጡት አስተያየት የውሃ እጥረቱ በመባበሱ ወደ ገጠር ቀበሌ በመሄድ ከጉድጓድ ወኃ ለመቅዳት ተገደዋል ።

ይህ ደግሞ ለአላስፈላጊ እንግልትና ውጣ ውረድ እንደዳረጋቸው ገልፀዋል ።

ከውሃ ጉድጓዱ የሚጠቀመው ህብረተሰብ በመብዛቱ ውሃ ሳያገኙ  ወደ ቤታቸው የሚመለሱበት ጊዜ መኖሩንም ወይዘሮ አማኔ ተናግረዋል ።

ሌላዋ የጨፌ ኦዳ ነዋሪ ወይዘሮ የባለወርቅ ንጉሴ በበኩላቸው ንፅሀናው ያልተጠበቀ ውሀ በመጠቀማቸው እሳቸውን ጨምሮ የቤተሰብ አባሎቻቸው በውሃ ወለድ በሽታ ተይዘው ለህክምና ወጪ እንደዳረጋቸው ጠቁመዋል ።

ውሃ ከሩቅ ቦታ ቀድተው ከሚሸጡ ሰዎች ላይ አንዱን ጀሪካን ከስድስት አስከ 10 ብር ሂሳብ ገዝተው እየተጠቀሙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የጨፌ ዶንሳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አልፍያ አብደላ ናቸው።

በከተማው በሆቴል አገልግሎት ስራ የተሰማሩት ወይዘሮ  ሞሚና ሀሰን  በበኩላቸው "በውሀ እጥረት ደንበኞቼን በአግባቡ ማስተናገድ አልቻልኩም " ብለዋል ።

የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንዲፈታ አስተያየት ሰጭዎቹ ጠይቀዋል።

የሮቤ ከተማ የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ  ኃላፊ አቶ ታሪኩ ደመቀ እንደገለፁት የከተማው ህዝብ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ  ፍላጎቱና አቅርቦቱ ባለመጣጣሙ ችግሩ ተከስቷል ።

"ግንባታዎች፣ ሆቴሎች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ የከፍተኛ ትምህርትና የህክምና ተቋማትን ጨምሮ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎች መስፋፋት ደግሞ የውሀ እጥረቱን አባብሶታል" ብለዋል ።

ኢንተርፕራይዙ እጥረቱን ለመፍታት የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

እንደ አቶ ታሪኩ ገለፃ ችግሩን በጊዜያዊነት ለማቃለል ለከተማዋ ነዋሪዎች ውሃ በአምስት ፈረቃ እየታደለ ነው።

በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ የሚጠናቀቅ የአንድ ጥልቅ የወኃ ጉድጓድ ቁፋሮ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት  ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በተገኘ 204 ሚሊዮን ብር በጀት አዲስ የውሃ ማስፋፊያ መሰረተ ልማት ለመገንባት  የፕሮጀክት ቀረፃ መካሄዱን ተናግረዋል ።

ጨረታውን ያሸነፈ ተቋራጭ ግንባታውን ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን አቶ ታሪኩ  አስታውቀዋል ።

Published in ማህበራዊ

ፍቼ ሚያዝያ 29/2009 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በመጪው መኸር ምርታማነትን ለማሳደግ 433 ሺህ ሄክታር ማሳ በመስመር ለመዝራት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ሥራ ሂደት ኃላፊ ወይዘሮ ዘውድነሽ ተስፋዬ እንደገለጹት በመስመር የሚዘራው ማሳ በምርት ዘመኑ ለማልማት ከታቀደው 455 ሺህ ሄክታር ውስጥ ነው ።

በዚህም በምርት ወቅቱ በ13 ወረዳዎች ከሚለማው ማሳ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው 16 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው በእጥፍ ብልጫ እንደሚኖረው አመላክቷል ።

"ለአርሶ አደሩ በዘመናዊ አመራረት ስልጠና ከመሰጠቱ በተጨማሪ የተሻሻሉ የእርሻ መሣሪያዎችና የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በሚፈለገው መልኩ  እንዲጠቀም እየተደረገ ይገኛል" ብለዋል ።

በዚህም ለምርት ወቅቱ የሚያገለግል 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮና 22ዐ ሺህ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እየተሰራጨ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

እንደ ወይዘሮ ዘውድነሽ ገለፃ በምርት ዘመኑ 176 ሺህ 687 አርሶ አደሮች በሰብል ልማት ተሳታፊ ናቸው ።

የግራር ጃርሶ ወረዳ የቶርባን አሼ ቀበሌ አርሶ አደር ገረመው ጫላ በሰጡት አስተያየት "በምርት ወቅቱ ባለኝ ሁለት ሄክታር ማሳ ላይ የበቆሎ ዘር በመስመር ለመዝራት እየሰራሁ ነው " ብለዋል

ከዚህ ቀደም በመስመር ዘርተው እንደማያውቁ የገለፁት አርሶ አደሩ የባለሙያዎችን ምክር በመቀበል ለመጀመርያ ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ መነሳሳታቸውን ጠቅሰዋል ።

ምርታማነትን ለማሻሻል ጥረቴን ከአሁኑ ጀምሬአለሁ ያሉት አርሶ አደሩ  በመስመር ለመዝራት የእርሻ መሬታቸውን ደጋግመው  በማረስና በማለስለስ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

ሥራውን ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ገልጸው ባለሙያዎች የሰጧቸው የተግባር ሥራም በፍጥነት ለመተግበር እንዳነሳሳቸው ይናገራሉ።

ሌላው የወዴሶ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለሙ በዳዳ በበኩላቸው አካባቢያቸው በተደጋጋሚ በድርቅ እንደሚጠቃ ጠቁመው ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን በመስመር ለመዝራት ማቀዳቸውን ተናግረዋል ።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 29/2009 ከ14 አመት በታች ያሉ ህጻናት የሩጫ ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄደ።

ውድድሩ የአውሮፓ ህብረት 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያና በህብረቱ ትብብር የተዘጋጀ ነው።

ውድድሩ ቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተደርጓል።

በአውሮፓ ህብረት የፕሬስና ኢንፎርሜሽን ክፍል ኃላፊ ሳንዲ ዌድ እንደተናገሩት ህጻናት የወደፊት ተስፋ በመሆናቸው ውድድሩ በስፖርቱ እየተዝናኑ እንዲሳተፉ ዕድል ይፈጥራል።

ቀጣይነት እንዲኖረውም ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ ተተኪ አትሌቶችን ከማፍራት ባሻገር የህጻናትን አእምሮ ለማበልጸግ እንዲህ አይነቱ ስፖርታዊ ውድድር የጎላ ሚና ይኖረዋል ብሏል።

በመሆኑም ህጻናትን የሚያሳትፉ ስፖርታዊ ውድድሮች እንዲለመዱ በትምህርት ቤቶችና በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የውድድር መርሃ ግብሮች መስፋፋት አለባቸው ብሏል።

በውድድሩ በሴቶችም በወንዶችም ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት የተሳተፉ ሲሆን ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ይዘው ላጠናቀቁ ተወዳዳሪዎች የምስክር ወረቀትና የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ውድድሩ ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን ሶስት ሺህ የሚሆኑ ህጻናት ተሳትፈዋል።

Published in ስፖርት

ጎባ ሚያዝያ 29/2009 የባሌ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራና የከተሞች ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ18 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶችን በተለያዩ የገቢ ማስገኛ መስኮች ማሰማራቱን ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተሾመ ጣፋ እንዳመለከቱት በመደበኛ መርሃ ግብር ወጣቶቹ በአዋጭ የስራ መስኮች የተሰማሩት በሁለት ከተሞችና በ18 የገጠር ወረዳዎች ነው።

ወጣቶቹ በአነስተኛና ጥቃቅን ማህበራት ተደራጅተው ከተሰማሩባቸው የስራ መስኮች መካከል ግብርና፣ ኮንስራክሽን፣ ማእድን፣ አነስተኛ ንግድ እንዲሁም የእንጨትና ብረታ ብረት ስራዎች ይገኙበታል።

ጽህፈት ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የስራ ብቃት ስልጠናን ጨምሮ 842 ሄክታር የእርሻ መሬትና 396 የመስሪያ፣ የማምረቻና የመሸጫ ሼዶች እንዲሰጣቸው አመቻችቷል።

ከኦሮሚያ ብደርና ቁጠባ አክሲዮን ማህበር ጋር በመቀነጀትም ያለባቸውን የመነሻ ካፒታል እጥረት ለማቃለል ከ12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር እንዲያገኙ ማድርጉን ነው ኃላፊው የተናገሩት።

እንደ አቶ ተሾመ ገለፃ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ከነዚሁ ወጣቶች በተጨማሪ ከ40 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶችን በማደራጀት በስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

በተቀሩት ወራት ወደ ስራ ይገባሉ ተብለው ለሚጠበቁት ለነዚሁ ወጣቶች መንግስት 188 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መመደቡን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቀት አብዛኛዎቹ ወጣቶች ተደራጅተው የቅድመ ቁጠባ ክፍያና የንግድ አዋጭነት ስልጠና በማጠናቀቃቸው ተዘዋዋሪ ፈንዱን የማሰራጨት ስራ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

ከስራ እድሉ ተጠቃሚዎች መካከል በጎባ ከተማ የምስራቅ ቀበሌ ወጣት አብዱልከሪም ማህሙድ በሰጠው አስተያየት በግንዛቤ እጥረት በዲግሪ ተመርቆ ለሶስት ዓመት ያለ ስራ በመቀመጡ ይቆጯል።

በዚህ ዓመት ግን መንግስት ባመቻቸው የስራ እድል በመጠቀም ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመደራጀትና 40 ሺህ ብር ብድር በወስድ በእህል ንግድ ስራ መሰማራታቸውን ገልጿል።

ወጣት አብዱልከሪም እንዳለው የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ በመሆኑ በሚያገኘው ገቢ ከቤተሰብ ጥገኝት ለመላቀቅ እየሰራ ነው።

ከሶስት ጓደኞቹ ጋር በመደራጀትና 20 ሺህ ብር በመቆጠብ ተዘዋዋሪ ፈንድ ወስደው ስራ ውስጥ ለመግባት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የተናገረው ደግሞ በከተማዋ የምእራብ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ተስፋዬ ካሳዬ ነው።

በፍላጎታቸው በመረጡት የስራ መስክ መደራጀታቸውን የተናገረው ወጣቱ በዚህም የስራ ተነሳሽነታቸው እንደሚጨምራና ሙሉ ጊዜያቸውንም ስራ ላይ በማሳለፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ለመሆን እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡

ወጣቶቹ እንዳሉት ያገኙትን አማራጮቹ ሁሉ በመጠቀምና ጠንክረው በመስራት ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋጋጥ ይተጋሉ።

በባሌ ዞን ባለፈው ዓመት ከ21 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሰራ እድል መፍጠር መቻሉንም ለማወቅ ተችሏል።

Published in ኢኮኖሚ

አሶሳ ሚያዚያ 29/2009 በአሶሳ ከተማ የሚገኘው ባምቡ ፓራዳይዝ ሆቴል በ110 ሚለዮን ብር ያካሄደውን የማስፋፊያ ግንባታ አጠናቆ ትላንት አስመረቀ ።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ረመዳን አሸናፊ እንደተናገሩት ሆቴሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚገኝበት ስፍራ መገንባቱ የቱሪስቶችን ምቾትና ቆይታ ለመጨመር አስተዋጽኦ አለው ።

የሆቴሉ ባለቤት አቶ አሰፋ ካሳሁን በበኩላቸው የአሶሳ ከተማ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጎብኚዎች መዳረሻ በመሆኗና የቱሪስት ፍሰቱም  እያደገ መምጣቱ የማስፋፊያ ግንባታውን ለማካሄድ ምክንያት እንደሆናቸው ተናግረዋል፡፡

የአሶሳ ከተማ ከንቲባ ተወካይ አቶ አቡዱሙንጣሊብ ሸምሰዲን እንደገለፁት ከተማው አገራዊ ስብሰባዎችና የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚያስተናግድ በመሆኑ የሆቴሉ የማስፋፊያ ግንባታ የእንግዶች ማረፊያ እጥረትን ያቃልላል ።

በከተማዋ የሚገኙ ሌሎች በሆቴል ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ባለሃብቶችም የማስፋፊያ ስራ የሚያከናውኑ ከሆነ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ሆቴሉ ባካሄደው ማስፋፊያ ከነበረው ባለ አምስት ፎቅ ህንፃ በተጨማሪ አዲስ ባለ አራት ፎቅ ህንፃ ያስገነባ ሲሆን ለሃምሳ ያህል ተጨማሪ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል እንደፈጠረ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 29/2009 በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ በሰብዓዊነት እንዲሳተፍ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጥሪ አቀረበ።

የማህበሩ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሚያዚያ 30 “ለተጎጂዎች በያሉበት’’ በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የዓለም ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ቀን አስመልክቶ የእግር ጉዞ አካሂዷል።

በስነ-ስርዓቱ የማህበሩ የቦርድ ሊቀ-መንበር ዶክተር አህመድ ረጃ በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመርዳት ማህበሩ ከለጋሽ ድርጅቶችና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በመተባበር ምግብና ምግብ ነክ ቁሳቁሶችን ማቅረቡን ገልፀዋል።

በተለይም ህፃናት፣ ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች የአልሚ ምግብ ድጋፍ ስለሚፈልጉ ህብረተሰቡ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ የቦርድ ሊቀ-መንበር ዶክተር ምርጌሳ ካባ በበኩላቸው እስካሁን በደረሱ አደጋዎች ለተደረጉ እርዳታዎች ለጋሾችን አመስግነው ሰብዓዊ እርዳታው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ብለዋል።

ችግሮች ሲከሰቱ ከሚሰጡ ሰብዓዊና ቁሳዊ አገልግሎቶች በተጨማሪ ወደፊት በሚካሄድ አደጋዎችን የመከላከል ስራ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሁሉም ህብረተሰብ ከማህበሩ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

የቀይ መስቀል ማህበር መርሆችን ለማስተዋወቅም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና የማህበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት ነገ ውይይት ይካሄዳል።

የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ71ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለዘጠነኛ ጊዜ ነው የተከበረው።

 

 

Published in ማህበራዊ

አዳማ ሚያዚያ 29/2009 የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት እና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ከ28 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአገልግሎት ዘመኑ ያለፈና ህገወጥ የሆነ መድኃኒት እንዲወገድ ማድረጉን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ የሶስተኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈፃጸም ግምገማ ትናንት በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።  

በባለስልጣኑ የፕሮጀከት ዝግጅትና ማስተባበሪያ ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ልሳነወርቅ ዓለሙበዚህ ወቅት እንዳስታወቁት የአገልግሎት ዘመኑ ያለፈና ህገወጥ የሆነ መድኃኒት እንዲወገድ የተደረገው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ነው።

የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መደኃኒቶች የተያዙት በመግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻና በመደበኛ የቁጥጥር ስራዎች መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይ ባለስልጣኑ ከአለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅትና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በቶጎ ውጫሌ፣ ሞያሌ፣ ቃሊቲ፣ መተማና በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ድንገተኛ ፍተሻ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የምግብ ጥራትና ደህንነት ቁጥጥር ውጤታማነት ለማሻሻል በተደረገው እንቅስቃሴም በ129 የታሸጉ ጭማቂዎች ናሙናዎች ላይ በተካሄደው የላብራቶሪ ምርመራ 20ዎቹ መስፈርቱን ሳያሟሉ በመቅረታቸው ምርቱ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ ተደርጓል።

ለድህረ ገበያ ጥናት የተሰበሰቡ 215 የማንጎ ጭማቂ ናሙናዎች የጥራት ምርመራ የተሰራላቸው ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 103 ናሙናዎች መስፈርቱን ሳያሟሉ ቀርተዋል፡፡

ከ28 የጨቅላ ህጻናት ወተት ናሙናዎች ውስጥ 22ቱ መስፈርቱን ባለሟሟላታቸው ከ94 የዘይት ናሙናዎች ውስጥ ደግሞ 19ኙ መስፈርቱን ሳያማሉ በመቅረታቸው እንዲወገዱ መደረጉን አመልክተዋል።

በተለይ ባለ 20 ሊትር 7 ሺህ 500 ጀሪካን ዘይት የአምራች ስምና አገር " ባች ቁጥር " የተመረተበት ጊዜና መጠቀሚያ ጊዜ እንዲሁም የምርቱ ይዘት ስለማይገልፅ ወደ መጣበት አገር እንዲመለስ ተደርጓል።

የጥራት መስፈርትን አሟልተው ያልተገኙ መድሀኒቶችና የኮንዶም ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ እና ከገበያ ላይ እንዲሰበሰቡ የማድረግ ስራ መከናወኑንም አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በጤና አገልግሎት ግብአቶች  ላይ ቁጥጥርና ፍተሻ በማድረግ  ከ8  ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው መድሀኒትና የህክምና መገልገያ መሣርያዎች ወደ ሀገር ውሰጥ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል።

ህገ-ወጥ የምግብና መድኃኒት ንግድ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያም በ182 የምግብ አምራቾች ላይ በአዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙሪያ፣ በጨው አምራቾችና አከፋፋዮች እንደ ሀገር ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ ጥናት ተደርጎበታል፡፡

የጥናቱ ውጤቱ ለሚመለከታቸው አካላት ቀርቦ አሰፈላጊው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የምግብ፣ የመድኃኒት እና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ በበኩላቸው እንደተናገሩት ባለስልጣኑ በጤና ችግሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

የቁጥጥር ዘርፉን ለማጠናከር አዳዲስ ስትራቴጂዎችን በመቀየስ ሁሉንም የልማት ኃይሎች ለማስተባበርና ለማንቀሳቀስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የጤና ቁጥጥር ስራ በአንድ ተቋም ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ ከህዝብ ክንፍና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የጋራ እቅድ በማውጣት ለውጤታማነቱ መረባረብ  ይገባል ብለዋል። 

ባለስልጣኑ ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው የስራ አፈፃጸም ግምገማ ላይ ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ የሕዝብ ክንፍና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን