አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Saturday, 06 May 2017

መቀሌ ሚያዝያ 28/2009 በትግራይ ክልል ሞዴል አርሶ አደሮችን ጨምሮ በግብርናው ዘርፍ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ 386 ባለድርሻ አካላት ዛሬ ተሸለሙ ።

ከተሸላሚዎቹ መካከል 274ቱ ከ1 ነጥብ 5 እስከ 10 ሚሊዮን ብር ያፈሩ ሞዴል አርሶ አደሮች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ለዘርፉ እድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ባለሀብቶች፣ የግብርና ልማት ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድረሻ አካላት ናቸው ።

የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኪሮስ ቢተው እንደገለፁት ለሽልማት የበቁት አርሶ አደሮች ከተወሰኑ አመታት በፊት ምንም ሀብት ያልነበራቸው ናቸው።

"አርሶ አደሮቹ መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍና ጉልበታቸውን በመጠቀም አሁን ለደረሱበት ባለሀብትነት በቅተዋል " ብለዋል ።

አርሶ አደሮቹ ሀብት ከመፍጠራቸው በተጨማሪ በተፈጥሮ ሀብት ስራዎችና ክብካቤ የተሻለ ስራ በማከናወናቸው ለሽልማት እንደበቁ አቶ ኪሮስ ገልፀዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ እንዳስመዘገቡት ውጤት ከምስክር ወረቀት በተጨማሪ የዋንጫ ፣ የገንዘብ ፣ የግብርና መሳሪያዎች ፣ ኮምፒውተሮችና ፕሪንተሮች በሽልማት ተበርክቶላቸዋል ።

ተሸላሚ አርሶ አደሮች የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ሰራዊት ሆነው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ከተሸላሚዎች መካከል ከትግራይ ምዕራባዊ ዞን የወልቃይት ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሃለቃ ግደይ ጥላሁን አንዱ ናቸው፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉት ከሶስት ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ በማልማትና ከ150 በላይ የቤት እንስሳት በማርባት ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማፍራታቸው ለሽልማት በቅተዋል ።

ሽልማቱ ለስራቸው ይበልጥ  እንደሚያነሳሳቸውና ሌሎች አርሶ አደሮች የእርሳቸውን አርአያ እንዲከተሉ የማስተማር ስራ እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል፡፡

ሽልማቱ መንግስት ከአርሶአደሩና ከባለሃብቱ ጎን መሆኑን ያሳያል ያሉት ደግሞ በትግራይ ደቡባዊ ዞን በራያ ዓዘቦ ወረዳ በግብርና ኢንቨስትመንት ስራ ላይ የሚገኙት አቶ አማኑኤል አብርሃ ናቸው።

አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስመጣት ከራሳቸው በተጨማሪ በአካባቢያቸው ለሚገኙ አርሶ አደሮች በማስተላለፍ እንዲጠቀሙበት በማድረጋቸው ለሽልማት መብቃታቸውን ባለሀብቱ ተናግረዋል፡፡

የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ ባለፈው አመት በአካባቢው በተከሰተ ድርቅ ለተቸገሩ አርሶ አደሮች ውሀና መኖ ማከፋፈላቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በክልሉ ማእከላዊ ዞን በአሕፈሮም ወረዳ ነዋሪና አካል ጉዳተኛ አርሶ አደር መኮንን ተኸሉ በበኩላቸው ከግል ባለሃብቶች የመቆፈሪያ ማሽኖችን በመከራየት ሁለት የውሃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶችን በመቆፈር ከሁለት ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ማልማት መቻላቸው ለሽልማት እንዳበቃቸው ተናግረዋል ።

እንደ አርሶ አደር መኮንን ገለፃ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት በአመት እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር ገቢ እያገኙ ነው ።

የእለቱ ክብር እንግዳና የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ "በግብርና ስራዎቻችን በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ በተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች የጀመርነውን ጥረት ለማጠናከርና ለማጎልበት የተቀናጀ ስራ መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል ።

የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ  ለሁሉም የግብርና ስራዎች መሰረት በመሆኑ ካለፉት አመታት በተለየ መልኩ በዘርፉ የተቀናጀ ስራ እንደሚሰራ አመላክተዋል ።

ሞዴል አርሶአደሩቹ ያስመዘገቧቸውን ለውጦች ወደ ሌሎች ከማስፋት በተጨማሪ በእያንዳአንዱ የግብርና ስራ የተፈጥሮ ሃብት ክብካቤን ማእከል አድርጎ ሊካሄድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

"በግብርና ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ለውጥ የሚያበረታታ ቢሆንም ከሚፈለገው  ፈጣን እድገት ጋር ለማጣጣም  ዘርፉን ዘመናዊ ማድረግ ያስፈልጋል "ያሉት ደግሞ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትሩ ዶክተር እያሱ አብርሃ ናቸው፡፡

እንደ ዶክተር እያሱ ገለፃ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ለጥራት፣ ለፍጥነት፣ ለብዛትና ለጊዜ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ።

በአገራችን ከሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል 22 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ወደ ሞዴልነት የተሸጋገሩ መሆናቸውን ያመለከቱት ሚኒስትሩ ቁጥራቸውን ከፍ ለማድረግ በቴክኖሎጂና በምርምር እገዛ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 28/2009 ባለሃብቶቹ የመሰረተ ልማት እጥረት ለሥራቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው ገለፁ።

 የአዲስ አበባ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ በበኩሉ ባለሃብቶቹ የሚደረግላቸውን ድጋፍ በአግባቡ ባለመጠቀማቸው በሚፈለገው ደረጃ ራሳቸውን ሊያሳድጉ አልቻሉም ብሏል።

ይህ የተባለው ቢሮው ከጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሽነት ወደ ባለሃብትነት ከተሸጋገሩ ባለሃብቶች ጋር ባካሄደው ውይይት ነው።

በብረታ ብረት፣ በእንጨት ሥራ፣ በምግብ ዝግጅትና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩት ባለሃብቶቹ በኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ በውሃ እጦትና መሰል ችግሮች ውጤታማ መሆን እንዳልቻሉ ነው የገለጹት።

በተለይም በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምክንያት ማሽኖቻቸው ለብልሽት በመጋለጣቸው ለኪሳራ መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት ወደሚመለከተው አካል ቅሬታ ብናቀርብም በቂ ምላሽ አላገኘንም ሲሉም ወቅሰዋል።

መንግስት በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው እንዲሰሩ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ወደ ባለሃብትነት መሸጋገራቸውን የሚናገሩት ባለሃብቶቹ የመሰረተ ልማት አለመሟላት የበለጠ ውጤታማ እንዳይሆኑ እንቅፋት እንደሆነባቸውና መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በቢሮው የመስሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዲና ኃይለስላሴ እንደተናገሩት የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግር መኖሩ ባለሃብቱን ጎድቶታል፤ መንግስትም ማግኘት ያለበትን ገቢ እንዲያጣ አድርጎታል።

ይሁን እንጂ በፖሊሲ የተቀመጡ የብድር አገልግሎት፣ የገበያ ትስስር፣ ምቹ የመስሪያ ቦታ፣ የአቅም ግንባታና መሰል ድጋፎች እየተደረገላቸውም ማደግ ያልቻሉ ባለሃብቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

አቶ ግዲና እንደሚሉት ባለሃብቶቹ የሚደረግላቸውን ድጋፍ በአግባቡ ባለመተግበራቸውና በሚፈለገው ደረጃ ራሳቸውን ባለመቻላቸው በዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ ውጤት አላመጡም።

ለመስሪያ የሚሆን ቦታ ከመንግስት ተረክበው ቦታውን ያከራዩና የሸጡ መኖራቸውንና በቀላሉ ትርፍ የሚያስገኙ የስራ ዘርፎችን መምረጥ የመሳሰሉ የአመለካከት ችግሮች መኖራቸውንም ገልፀዋል።

ቢሮው የሚያደርገው ክትትልና ድጋፍ አነስተኛ ሲሆን ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት ክፍተት እንዳለበትም አምነዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ ከኢንዱስትሪ ቢሮ፣ ከመብራት ኃይልና ከውሃ ልማት ጋር መድረክ በማዘጋጀት እንደሚመክርና ፈጣን መፍትሄ ለማምጣት እንደሚሰራም ዋና ዳይሬክተሩ ቃል ገብተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 28/2009 የተሻለ አፈጻጸም የተመዘገበባቸው አገራዊ ስኬቶች ቢኖሩም የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ስራዎች ደካማ መሆን ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ተናገሩ።

 የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን መሪዎች፣ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት አገራዊ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በውይይቱ ላይ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በህዝቡና በየደረጃው በሚገኙ ተቋማት የተሰሩ መልካም አፈጻጸሞች ቢኖሩም ሚዲያውና የህዝብ ግንኙነት ተቋማት በሚጠበቀው ልክ እየሰሩ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት።

 የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ተቋማት ኃላፊዎች በበኩላቸው አገራዊ የህዝብ ግንኙነት ስራው የሚፈለገውን ውጤት ላለማምጣቱ ወጥ የህዝብ ግንኙነት አሰራር አለመዘርጋት፣ የመገናኛ ብዙሃንና የመንግስት ተቋማት ህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች አለመግባባትና የአቅም ውስንነትን በምክንያትነት አንስተዋል።

 "የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የተቋማቸውን ዓቢይ ተልዕኮ በመረዳት ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለህብረተሰቡ በፍጥነት ተደራሽ ማድረግ አለባቸው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለስራቸው እንቅፋት የሆኑ አሰራሮችን  እንዲፈታ አሳስበዋል።

 ሁሉም የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የመጀመሪያው የተቋማቸው የህዝብ ግንኙነት ሊሆኑ እንደሚገባና የመረጃ ጥያቄ ከመገናኛ ብዙሃን፣ ከግለሰቦች ወይም ከሌሎች ተቋማት ሲቀርብላቸው ወቅታዊ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸውም አስገነዝበዋል።

 የመረጃ ነጻነት አዋጅ አተገባበርን በሚመለከት አዋጁን ሙሉ ለሙሉ መተግበር የሚያስችሉ የህግ  ማዕቀፎች አለመዘጋጀት፣ የተቋማት የተደራጀ የመረጃ ማዕከል አለመኖር፣ የሰነድ ስራ አመራር ስርዓት አለመዘርጋት፣ ለህዝብ ይፋ መደረግ ያለበትን መረጃ ሚስጥር ማድረግና መሰል ችግሮች አሁንም መቀጠላቸው በውይይቱ ወቅት ተገምግሟል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 28/2009 በስፖርት ትጥቅ አምራቹ ኩባንያ ናይክ አስተባባሪነት የማራቶን ርቀትን ከሁለት ሠዓት በታች ለመጨረስ የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀረ።

በኢጣሊያ ሞንዛ ከተማ በተደረገ ሩጫ በማራቶን ከፍተኛ ብቃት ላይ የሚገኘው ኬንያዊ አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ ማራቶንን ከሁለት ሠዓት በታች ይገባል ተብሎ ቢጠበቅም ሳይሳካለት ቀርቷል።

ማራቶንን በሳይንሳዊ ልምምድ፣ አመጋገብ፣ ስነ ልቦናና በስፖርት ትጥቅ በመታገዝ አትሌቶች ከሁለት ሠዓት በታች እንዲሮጡ ለማድረግ ናይክ ለሰባት ወራት ሲያሰለጥናቸው ቆይቷል።

ስልጠናውን የወሰዱት ኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌ፤ ኢትዮጵያዊው ሌሊሳ ዴሲሳና ኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰ ናቸው።

ዛሬ ለሩጫው የተሻለ ሠዓት ለማስመዝገብ ያግዛል ተብሎ በኢጣሊያ ሞንዛ ከተማ ሩጫው ሲደረግ ኬኒያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌ ርቀቱን 2 ሠዓት ከ25 ሰከንድ በመግባቱ የተያዘው ዕቅድ አልተሳካም።

ኬፕቾጌ ከ2 ሠዓት በታች መግባት ባይችልም በማራቶን ፈጣን ሠዓት ማስመዝገብ ችሏል።

የተመዘገበው ውጤት በ2014 በኬንያዊው ዴኒስ ኪሜቶ የተያዘውን 2 ሠዓት ከ2 ደቂቃ ከ57 ሰከንድ የማራቶን ክብረወሰን በሁለት ደቂቃ ከ32 ሰከንድ አሻሽሎታል።

ሆኖም ሩጫው በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር እውቀና ያልተሰጠውና በናይክ ለሙከራ የተካሄደ በመሆኑ ሠዓቱ በአዲስ ክብረ ወሰንነት አይመዘገብም።

በዚህ ሩጫ ኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰ 2 ሠዓት ከስድስት ደቂቃ ከ51 ሰከንድ ሲያጠናቅቅ፤ ኢትዮጵያዊ ሌሊሳ ዴሲሳ 2 ሠዓት ከ14 ደቂቃ ከ10 ሰከንድ የሆነ ሠዓት አስመዝግበዋል።

ሩጫው በሶስቱ አትሌቶች ብቻ የተካሄደ ፉክክር ቢሆንም የተሻለ ሠዓት እንዲያስመዘግቡ አሯሯጭ አትሌቶች ተሳትፈውበታል።

አትሌት ኪፕቾጌ ከውድድሩ በኃላ በሰጠው አስተያያት ቀደም ሲል ከነበረው ሠዓት በሁለት ደቂቃ ከ33 ሰከንድ በማሻሻሉ መደሰቱንና እንደ ታሪክ የሚዘከር መሆኑን ተናግሯል።

የሰው ልጅ የማራቶን ርቀትን ከ2 ሠዓት በታች መግባት አንደሚችልም ገልጿል።

Published in ስፖርት

ጎባ ሚያዝያ 28/2009 የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጎባ ሪፈራል ሆስፒታል በመደበኛው መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 37 የህክምና ዶክተሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ አስመረቀ፡፡

በእለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የጤና ጥበቃ  ሚኒስቴር ተወካይና የሰው ሀብት ልማት ጄኔራል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር  ጌታቸው ቶሌራ በትምህርታቸው ብልጫ ላመጡ ተመራቂዎች የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት አበርክተዋል ።

ዶክተር  ጌታቸው በወቅቱ እንደተናገሩት  መንግስት በሀገሪቱ የሚታየውን የህክምና ባለሙያዎችን እጥረት በማቃለል ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ነው፡፡

"ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመ ባጭር ጊዜ ውሰጥ  ከፍተኛ ኃብትና ልምድ የሚጠይቀውን በህክምና ሙያ ዘርፍ የድህረ ምረቃ ስልጠና መርሀ ግብር በመክፈት በሀገር ደረጃ የሚታየውን የህክምና ዶክተሮች እጥረት ለማቃለል እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው" ብለዋል ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ ተካ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የጎባ ሪፈራል ሆሰፒታል ያለበትን የህክምና ባለሙያዎች እጥረት ለማቃለልና ክህሎት ለማዳበር እያደረገ ባለው ጥረት ወደ ሌላ አካባቢ በሪፈራል የሚላኩ ህሙማን በራስ አቅም ማከም እየተቻለ መሆኑን ጠቁመዋል ።

"በዚህም ለአካባቢው ማህበረሰብ የህክምና አገልግሎትን በቅርበት በመስጠት ከአላስፈላጊ እንግልትና  ወጭ ማዳን ተችሏል " ብለዋል ።

የጎባ ሪፈራል ሆሰፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አቡበከር ከድር በበኩላቸው ሪፈራል ሆሰፒታሉ በአሁኑ ወቅት ከህክምና ዶክተሮች በተጨማሪ በጤና መኮንንነት በአምስት የጤና ዘርፎች ከ1 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል" ብለዋል ።

እንደ ዶክተር አቡበከር ገለፃ ሆስፒታሉ በቀጣይ በአጠቃላይ የቀዶ ጥገናና በማህጸንና ጽንስ እስፔሻሊስትነት የህክምና ባለሙያዎችን ለማሰልጠን የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናቋል ።

በከፍተኛ ማእረግ ከተመረቁት መካከል ዶክተር አዲሱ ቂጤሳ በሰጡት አስተያየት  “በተማርኩበት ሙያ ቦታን ሳልመርጥ ማህበረሰቡን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ” ብለዋል ።

ሌላዋ ሴት ተመራቂ ዶክተር ስንዱ ተሰፋዬ  በበኩሏ “ራሴን በየጊዜው በማብቃት ህብረተሰቡ ከኔ የሚፈልገውን ጥራት ያለውን የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነኝ” ብላለች፡፡

የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ በ1999 ዓ. ም 742 ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማሩን ሥራ የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ በ62 የትምህርት አይነቶች ከ13 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛውና በተከታታይ  መርሃ ግብር ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንሚገኝ ታውቋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 28/2009 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህጻናት ፓርላማ የምስረታ ደንብና መተዳደሪያ ደንቡን በሙሉ ድምፅ አፀደቀ።

ደንቡ ህጻናቱ በአዕምሮና በአካል ብቁና ዴሞክራሲያዊ ስብዕና ተላብሰው እንዲያድጉ ያግዛል ተብሏል።

ፓርላማው ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ አካሂዷል።

በፀደቀው ደንብ ቁጥር 1/2009 መሰረት ፓርላማው የግንዛቤ መፍጠርና የህጻናትን መብት የማስጠበቅ ሚና ይኖረዋል። 

የህጻናቱ ፓርላማ ለቤተሰብ፣ ለአካባቢ ህብረተሰብና በትምህርት ቤት የህጻናት መብቶች ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ትምህርቶችን መስጠት፤ ህጻናቱ እንዲሟሉላቸው የሚፈልጓቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለሚመለከተው አካል የማቅረብ ኃላፊነት ተጥሎበታል።

የህጻናቱን መብትና ጥቅም ማስከበር፣ የመብት ጥሰት የሚፈጽሙትንም ለአስተዳደርና ለፍትህ አካላት ሪፖርት የማድረግና እርምጃ ስለመወሰዱ የመከታተል ተግባራትም ይኖሩታል።

የፓርላማው ሰብሳቢ ህፃን ኤርሚያስ ታደሰ እንደተናገረው ፓርላማው ለህጻናቱ መብትና ግዴታቸውን አስመልክቶ ስልጠና በመስጠትና ግንዛቤያቸውን በማስፋት በራስ መተማመናቸውን ለማሳደግ ይሰራል፤ በየአካባቢያቸው ያላቸውን ተሳትፎም ያጠናክራል።

በአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት የህግ ባለሙያ አቶ ሙሴ አንበሴ ለኢዜአ እንደተናገሩትም ደንብና መመሪያው የህጻናቱ ፓርላማ የህግ መሰረት እንዲኖረው ያደርጋል።

የፓርላማው መቋቋም ህጻናት አገራቸውንና ህዝባቸውን የሚጠቅሙና መብታቸውንም የሚያስከብሩ በአዕምሮና በአካል ብቁና ዴሞክራሲያዊ ስብዕና ተላበሰው፤ ህገ-መንግስቱን አክብረው እንዲያድጉ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት በአዲስ መልክ የተዋቀረው የህጻናቱ ፓርላማ የመጀመሪያ መደበኛ ጉባዔውን በታህሳስ 2009 ዓ.ም ያካሄደ ሲሆን በከተማዋ ካሉት ወረዳዎች የተውጣጡ 113 አባላት አሉት።

Published in ፖለቲካ

ደብረ ብርሃን ሚያዝያ 28/2009 በደብረብርሃን ከተማ በኢንተርኘራይዝ የተደራጁ ወጣቶች  በብድር ባገኗቸው ማሽኖች ተጠቅመው መስራታቸው ወደ መካከለኛ ባለሃብትነት ለመሸጋገር እንዳስቻላቸው ገለፁ።

የሰንደል ልብስ ስፌት ኢንተርፕራይዝ ባለቤት ወጣት ይመኑ በለጠ  እንደገለፀው ዋልያ የካፒታል እቃ ፋይናስ ንግድ ስራ አክስዮን ማህበር ከተሰኘ መንግስታዊ ተቋም ባገኘው 280 ሺህ ብር ብድር 18 የልብስ መስሪያና መስፊያ ማሽኖች በመታገዝ ስራውን እያከናወነ ነው ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ማሽኖችን በመጠቀም ካመረታቸው ምርቶች ሽያጭ ካገኘው ገቢ ውስጥ 117 ሺህ 600 ብር ብድር መመለሱን ተናግሯል፡፡

እንደ ወጣት ይመኑ ገለፃ ያቋቋመው ኢንተርፕራይዝ ለ30 ሰዎች የስራ እድል ፈጥሯል ።

አጠቃላይ ካፒታሉን ወደ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በማድረሱ በቅርቡ ወደ መካከለኛ ባለሃብት በመሸጋገር ከክልሉ እውቅና ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

ሌላዋ የሶፊ ሸዋ ልብስ ስፌት የግል ኢንተርፕራይዝ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሶፊያ መሀመድ በበኩላቸው ከአክስዮን ማህበሩ 150 ሺህ ብር ዋጋ ያላቸው 13 የልብስ ስፌት ማሽኖችን በብድር በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ማሽኖችን በመጠቀምም የተለያየ ደረጃ ያላቸውና በገበያ ተወዳዳሪ ምርቶችን በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል ።

በማሽኖቹ መጠቀም ከጀመሩ ከሁለት አመት ወዲህ ጠንክረው በመስራት አጠቃላይ ካፒታላቸው ግማሽ ሚሊዮን ብር መድረሱን ጠቅሰዋል ።

በዚህም ከጥቃቅን ወደ ታዳጊ ባለሃብት በማደግ እውቅና እንደተሰጣቸው ገልፀዋል ።

በናትናኤል ሶሎሜና ጓደኞቻቸው የብረታ ብረት ማምረቻ ሽርክና ማህበር የሊዝ ማሽን ባለሙያ  ወጣት አለማየሁ ወርቁ በበኩሉ  አክስዮን ማህበሩ ከመከላከያ ኢጅነሪንግ ጋር በመተባበር ለማህበሩ በብድር በሰጣቸው የሊዝ ማሽኖች አጠቃቀም ተጨማሪ የክህሎት ማዳበሪያ የሶስት ወራት ስልጠና እንዲያገኙ ማድረጉን ጠቅሷል ።

የዋለያ የካፒታል እቃ ፋይናስ ንግድ ስራ አክስዮን ማህበር የደብረብርሃን ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋየ አበበ እንደገለፁት  በእንጨት፣ በጨርቃጨቅርቅ፣  በቆዳ ፣ በወተትና ወተት ውጤቶች ማቀነባበሪያና በሌሎች ዘርፎች ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ማሽኖችን በብድር ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በግልና በጋራ ተደራጅተው ለሚንቀሳቀሱ 11 ኢንተርፕራይዞች 50 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ማሽኖችን ብድር መስጠቱን ተናግረዋል።

አክሲዮን ማህበሩ ኢንተርፕራይዞች ያለባቸውን የማሽን አቅርቦት እጥረት በመፍታት ውጤታማ እንዲሆኑ ለማገዝ የተቋቋመ መሆኑን አቶ ተስፋየ አስታውቀዋል ።

የከተማ አስተዳደሩ ቴክኒክና ሙያ ኢርንተርፕራይዝ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃን ገብረ ህይወት በበኩላቸው አክሲዮን ማህበሩ የኢንተርፕራይዞችን የመስሪያ ማሽን አቅርቦት እጥረት በመፍታት ጉልህ ሚና እየተወጣ ነው።

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር ሚያዝያ 28/2009 የአማርኛ ቋንቋ ሃሳብን በትክክል የመግለፅ ደረጃውን በማሳደግ የሳይንስ ፣ የቴክኖሎጂና የምርምር ቋንቋ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ አስታወቀ፡፡

አምስተኛው የአማርኛ ቋንቋና የባህል ዘርፎች አገር አቀፍ ዓውደ ጥናት ዛሬ ተጀምሯል።

የዩኒቨርስቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙሉነሽ አበበ በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በዩኒቨርስቲው የአማርኛ ቋንቋን ለማበልፀግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው።

ቋንቋው ረጅም እድሜ ያስቆጠረና በርካታ ቁጥር ተናጋሪ ያለው ቢሆንም የእድሜውን ያህል እድገት እያሳየ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ቋንቋውን ተጠቅሞ ሃሳብን በአግባቡ አለመግለፅ፣ ወጥነት የጎደለው የአፃፃፍ ስርዓት መታየት፣ የቃላት አረባብ ስርዓት ችግር ፣ ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር ተደባልቆ መነገር በአማርኛ ቋንቋ የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው።

በቋንቋው ላይ የተጋረጡትን እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ዩኒቨርስቲው ግንባር ቀደም የሆነ የአማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋም ተቋቁሞ ችግሮችን በጥናትና ምርምር በመለየት መፍትሄ የሚሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩን ገልፀዋል።

ለዚህም ለመማር ማስተማሩ የሚያግዙ መጻሃፍትን ማዘጋጀትና አስቸጋሪ ለሆኑ አንዳንድ የእንግሊዝኛ ቃላት አቻ ትርጉም በመስጠት በትክክለኛው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተሰራ ነው።

የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የአማርኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋም ዳይሬክተር አቶ መለሰ ገላነህ በበኩላቸው ''ከጊዜ ወደ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ የመጠቀምና ለነገሮች ስያሜ መስጠት እየቀነስ መጥቷል'' ብለዋል።

በተለዩ ችግሮች ዙሪያ በየደረጃው ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የቋንቋ መምህራን ስልጠና የመስጠትና የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች ክበባትን በማቋቋም ግልፅ ውይይት ማድረግ ፣  ስለ ቋንቋው የተፃፉ መፃህፍትን በማሰባሰብ ለመማር ማስተማር ስራ እንዲውሉ እየተደረገ ይገኛል።

''በሚዲያ ተቋማት የሚስተዋሉ የቋንቋ አጠቃቀም ችግሮችን በመለየትም በቀጣይ ተገቢው የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ እየተሰራ ነው'' ብለዋል።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሒሩት ካሳው በበኩላቸው ''የአማርኛ ቋንቋ ለመግባቢያነት ብቻ የሚያገለግል ሳይሆን የባህልና የማንነት መገለጫ ነው'' ብለዋል።

''የቋንቋውን ደረጃ በማሳደግ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ለምርምር፣ ለመማር ማስተማርና ለሀገር ልማትና እድገት እንዲውል መሰራት አለበት'' ብለዋል።

በሆቴሎችና የንግድ ተቋማት ስያሜ አጠቃቀም ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በጥናትና ምርምር በመለየት ማስተካከያ ለማድረግ ከዩኒቨርስቲው ጋር ተባብረው እየሰሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

በባህር ዳር ከተማ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የአማርኛ ቋንቋና ባህል ቴክኖሎጂ ማዕከል በማቋቋም በቋንቋው በተፃፉ ኮምፒዩተሮች እንዲማሩና እንዲፅፉ ለማድረግ ፕሮጀክት ተቀርፆ ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።

በቋንቋው የተፃፉ የሃገሪቱ ታሪኮችና ባህሎች በፊልም መልክ ተዘጋጅተው እንዲማሩባቸው እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

በባህር ዳር ከተማ የፊታውራሪ ሃብተማሪም 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የአማርኛ ቋንቋ መምህር በድሉ አደመ በበኩላቸው ለቋንቋው ማደግ ምሁራን የሚያደርጉት የጥናትና ምርምር ውጤት ወደ ትምህርት ቤቶች ወርዶ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው 5ኛው ሃገር አቀፍ የአማርኛ ቋንቋና ባህል ዘርፎች ዓውደ ጥናት ላይ  ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችና ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

በአውደ ጥናቱም በተለያዩ ምሁራን የተጠኑ 19 የምርምር ስራዎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

Published in ማህበራዊ

ሚያዝያ 28/2009 የሲንጋፖር ምክትል  ጠቅላይ ሚኒስትር  ቴዎ ቺ   ሂን  ከነገ ጀምረው ኢትዮጵያንና  ደቡብ አፍሪካን  ሊጎበኙ መሆኑን  የገሪቱ  የውጭ  ጉዳይ ሚኒስቴር  አስታወቀ፡፡

ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር  ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከውጭ ጉዳይና ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ከሀገሪቱ ዓለም ዓቀፍ ድርጅት የተውጣጣ የልዑክ ቡድን  አብሯቸው እንደሚጓዝም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ጉብኝቱ ሲንጋፖር ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት አካል መሆኑንም ነው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስታወቀው፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዳስታወቀው ምክትል ጠቅላይ  ሚኒስትሩ   ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ከምክትላቸው ደመቀ መኮንን እንዲሁም ከኢንዱስትሪ፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሮችና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ዶክተር አርከበ እቁባይ ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ፡፡

በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ ትብብሮችን ማጠናከር ደግሞ የውይይታቸው ተቀዳሚ አጀንዳ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የሲንጋፖር  ባለሀብቶች ጋር ተገናኝተው ለመወያየትም  እቅድ ይዘዋል፡፡

የሲንጋፖር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቴዎ ቺ   ሂን   የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን እንዳጠቃለሉ በ20ኛው ዓለም አቀፍ አማካሪ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናሉ፡፡

ምንጭ፡- straitstimes.com

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 28/2009 የስራ ቦታቸው ንፅህና በመዝናኛ ክበብ ተጠቃሚዎች በመጓደሉ በስራቸው ላይ እንቅፋት እየፈጠረባቸው መሆኑን በልደታ ክፍለ ከተማ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ማኅበራት አመለከቱ።

በመዲናዋ አሰብ ሆቴል ጀርባ ተደራጅተው የሚሰሩት ማኅበራቱ በመስሪያ ሼዶቻቸው ቅጥር ግቢ የሚገኘው የሸማቾች ማኅበር መዝናኛ ተጠቃሚዎች በአጥሩ ስርና በቆሙ አሮጌ ተሽከርካሪዎች ውስጥ በመፀዳዳት አካባቢውን እየበከሉት መሆኑን ጠቁመዋል።

ሼዶቹ ከሚገኙበት ህንጻ የመጀመሪያ ወለል በስተቀር ውሃ ባለመኖሩና መጸዳጃ ቤቶቹም የፍሳሽ መውረጃ ያልተገጠመላቸው መሆናቸው ስራቸውን በአግባቡ ለመከወን ተጨማሪ ችግሮች እንደሆኑባቸው ገልጸዋል።

ችግሮቹ እንዲፈቱላቸው ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ቢያመለክቱም መፍትሄ አለማግኘታቸውን ነው ያስረዱት።

በሳይቱ ላይ ከ600 በላይ አንቀሳቃሾች የተመደቡ ቢሆንም ስራ የጀመሩት ጥቂት አንቀሳቃሾች መሆናቸውንም አክለዋል።

ትርፋማ ባይሆኑም የቤት ኪራይና ግብር እየከፈሉ ችግሮቹ ይፈቱልናል በሚል ተስፋ እየተጠባበቁ መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ከመመሪያ ውጪ የተሻለ ገቢ ያላቸው ሰዎች ሼድ ተሰጥቷቸው እየሰሩ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

የልደታ ክፍለ ከተማ የመስሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሐደራ አብርሃ በግቢው ውስጥ የሚገኙት የሸማቾች ክበብና አሮጌ ተሽከርካሪዎች እንዲነሱ መወሰኑን ተናግረዋል።

ሆኖም የወረዳው አመራር አፈጻጸሙ ላይ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ረገድ "ሃላፊነቱን አልተወጣም" ነው ያሉት።

የወረዳ 7 ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፀሀዬ ብርሃኑ በበኩላቸው ከማኅበራቱ የተነሱ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ያሉትን ውስንነቶች በማስወገድ በአንድ ወር ጊዜ መፍትሄ ለመስጠት እንረባረባለን ብለዋል።

በሼዶቹ ቅጥር ግቢ ያለው የሸማቾች ማኅበር እንዲነሳ ተለዋጭ ቦታ ለይተው ለክፍለ ከተማው ማሳወቃቸውንም አክለዋል።

የሸማቾች ማኅበር አመራሮች ከቦታው እንደሚነሳ በመጪው ሳምንት ለአባላቶቻቸው እንዲያሳውቁም "መግባባት ላይ ደርሰናል" ብለዋል።

የውሃ መስመሩ በግፊት ከ1ኛ ፎቅ በላይ እንዲደርስ የሚያደርጉ ማሽኖች መገዛታቸውንና የማኅበራቱ ኮሚቴ እንዲረከብ ማሳወቃቸውንም አቶ ፀሃዬ አስረድተዋል።

ግቢው ከጸዳ በኋላ ማኅበራቱን ማስተዋወቅ የሚያስችል ባዛር በግቢውና ፊት ለፊቱ ባለው አስፋልት ላይ ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

በግቢው የቆሙት አሮጌ ተሽከርካሪዎች እንዲነሱ ለከተማው አስተዳደር የንብረት ማስወገድ ክፍል ማሳወቃቸውንም እንዲሁ።

ሼዶች ለሶስተኛ ወገን እንደተከራዩ በደረሰን ጥቆማ መሰረት አራት ሰዎች እንዲለቁ አድርገናል፤ አሁንም ካሉና መረጃ ከተገኘባቸው "እርምጃ እንወስዳለን" ነው ያሉት።

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን