አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Friday, 05 May 2017

ወጣቱ ከጀግኖች አባቶቹ እና እናቶቹ በወረሰው የአገር ፍቅር ወኔ ዘመኑ የሚጠይቀውን የጸረ ድህነት ተጋድሎ እንዲያደርግ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ጠየቀ።

 ጽህፈት ቤቱ “የጀግኖች አርበኞቻችንን ድል የአሁኑ ትውልድ በጸረ ድህነት ትግሉ ይደግመዋል” እና “ለመገናኛ ብዙሃን መጠናከርና መስፋፋት መንግሥት አበክሮ መሥራቱን ይቀጥላል” በሚሉ  ርእሰ ጉዳዮች  የጀግኖች አርበኞችን ድልና የፕሬስ ቀንን አስመልክቶ ሳምንታዊ መግለጫ ልኳል።

 ለኢዜአ በላከው መግለጫው  አሁን ያለው ትውልድ በተለይም ወጣቱ ከጀግኖች አባቶቹ እና እናቶቹ በወረሰው የአገር ፍቅር ወኔ ዘመኑ በሚጠይቀው ጸረ ድህነት ተጋድሎ እንዲረባረብ ጥሪ አስተላልፏል።

 ይህ በእንዲህ እንዳለ ጽህፈት ቤቱ ለብቁ መገናኛ ብዙሃን መጠናከርና መስፋፋት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ሲባል በኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ዘርፉ ላይ ሁሉን አቀፍ የማሻሻያ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ብሏል።

 ከዚህ አንጻር መንግሥት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የማሻሻያ እርምጃዎችን እንደሚቀርጽና ተገቢውን የሰው ሃይል እና በጀት በመመደብ በጽናት እንደሚያስፈጽም ገልጿል። 

 የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል

 በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ

ሳምንታዊ አቋም መግለጫ

 የጀግኖች አርበኞቻችንን ድል የአሁኑ ትውልድ በጸረ ድህነት ትግሉ ይደግመዋል!

76ኛው የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል በዛሬው ዕለት በአገራችን በልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች ተከብሮ ውሏል። በዓሉን የምናከብረው ፋሽስት ኢጣሊያ በዓድዋ ድል ከተመታች በኋላ  የፈጸመችብንን ዳግም ወረራ  ጀግኖች አባቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት አገራችን ዳግም ነጻነቷን ያረጋገጠችበት ዕለት በመሆኑ ነው። በመሆኑም በዓሉን  ስናከብር ለአገራቸው ነጻነት ቀናኢ የነበሩትንና በዚህም ህይወታቸውን በየጫካውና በየፈፋው ቤዛ ላደረጉት እና ይህቺን አገር ላስረከቡን ጀግኖች አርበኞቻችን ክብርና ምሥጋና እየሰጠን መሆኑ ይታወቃል:: በዚህ አጋጣሚ የኢፌዴሪ መንግሥት ለጀግኖች አርበኞቻችንና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እያስተላለፈ፣ አሁን ያለው ትውልድ በተለይም ወጣቱ ከጀግኖች አባቶቹ እና እናቶቹ በወረሰው የአገር ፍቅር ወኔ ዘመኑ የሚጠይቀውን የጸረ ድህነት ተጋድሎ እንዲረባረብ የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል።

 ለመገናኛ ብዙሃን መጠናከርና መስፋፋት መንግሥት አበክሮ መሥራቱን ይቀጥላል!

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በአገራችን ለ7ኛ ጊዜ ሚያዚያ 25 ቀን 2009  በተከበረበት ወቅት ከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን፣ ማህበራት፣ የመገናኛ ብዙኃን አሳታሚዎችና ባለሙያዎች በዘርፉ ስላሉ ችግሮችና የመፍትሄ ሃሳቦች ተወያይተዋል።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለው ካስመዘገቧቸው በርካታ ድሎች መካከል የፕሬስ ነፃነት አንዱ ነው። ከ25 ዓመታት በፊት የፕሬስ ነፃነት ጉዳይ በኢትዮጵያ ፈጽሞ የማይታሰብ የነበረ ሲሆን የደርግ አምባገነናዊ ሥርዓት እንደወደቀ በሽግግሩ ዘመን ፈጥነው ከተረጋገጡት መብቶች አንዱ የፕሬስ ነጻነት ነበር። ከኢፌዴሪ ምሥረታ በኋላም መረጃ የማግኘት፣ የመናገር፣ የማሳተምና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ተረጋግጦለታል።

ለፕሬስ ነጻነትና መረጃ ነፃነት ቁልፍ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ረገድም መንግሥት በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል። ለአብነትም በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው የሰው ኃይል በአብዛኛው በልምድ ብቻ የሚሠራ እንደነበር በመገንዘብ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የጋዜጠኝነት የትምህርት ተቋማት እንዲስፋፉ አድርጓል። በዚህም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በብዛት እንዲፈጠርና ወደ ኢንዱስትሪው እንዲቀላቀሉ ማድረግ ተችሏል።

የህዝቦቻችንን የመረጃ ፍላጎት ለሟሟላት ሲባልም የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችን ተደራሽነት በመላ አገሪቱ ማስፋፋት ሌላው በዘርፉ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ከተከናወኑት አበይት ተግባራት ውስጥ ተጠቃሽ ነው። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ 10 የህዝብ፣ 10 የንግድ እና 45 የማህበረሰብ ብሮድካስት መሰራጫ ባለቤቶች በአገራችን ይገኛሉ። ይህ ውጤት ዜጎች በመልክአ ምድር ብቻ ሳይሆን በቋንቋ አብዝሃነት ጭምር የሚዲያ ተደራሽ እንዲሆኑ ያስቻለ በመሆኑ ከቁጥር በላይ  ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ለመገናኛ ብዙሃን እና ለዜጎች የመረጃ ፍላጎት መሟላት ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አንጻር መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ሥርዓትን እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ እንዲዘረጋ ማድረጉም ሌላው ቁልፍ ተግባር ነው።

ለመገናኛ ብዙሃን መጠናከርና መስፋፋት እጅግ መሰረታዊ የሚባሉት እነዚህ እና መሰል ተግባራት ያስመዘገቧቸው ትላልቅ ውጤቶች የመኖራቸውን ያህል ግን እድገቱ በሚፈለገው ልክ እንዳይፈጥን ያደረጉ ችግሮች መኖራቸውም ይታወቃል።

በመሆኑም እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ብሎም ለብቁ መገናኛ ብዙሃን መጠናከርና መስፋፋት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ሲባል በኮሙዩኒኬሽንና ሚዲያ ዘርፉ ላይ ሁሉን አቀፍ የማሻሻያ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር የኢፌዴሪ መንግሥት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የማሻሻያ እርምጃዎችን የሚቀርጽ ሲሆን ለተግባራዊነታቸውም ተገቢውን የሰው ሃይል እና በጀት በመመደብ በጽናትና በዲስፕሊን የሚያስፈጽማቸው ይሆናል። 

ሚያዚያ 27 ቀን 2009 ዓ.

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 27/2009 የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ በስልጠና አሠጣጥ የሚፈጠሩ የጥራት መጓደሎችን ለመፍታት የአሠልጣኞችን አቅም ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ።

ኤጀንሲው በአገር አቀፍ ደረጃ ከክልል፣ ዞን እና ወረዳ ለተውጣጡ አመራሮች ስልጠና እየሰጠ ነው።

የስልጠናው ዋና ዓላማ አዳዲስ አመራሮች ወደ ስራ መግባታቸውን ተከትሎ ሥራውን  በአግባቡና በብቃት እንዲያከናውኑ ከማስቻል አንፃር የአቅም ግንባታ ለመፍጠር መሆኑን የኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሰ ገብረ ተናግረዋል።

በቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና የአሠልጣኞች ብቃት ማነስና በቁሳቁስ የተሟላ የስልጠና ማዕከል አለመኖር በስልጠና ወቅት ለሚፈጠሩ የጥራት መጓደል ችግሮች ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ያሉት አቶ ንጉሰ ስልጠናው ተግባር ተኮር እንደመሆኑ ችግሮች መፈታት አለባቸው ነው ያሉት።

ለዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ለማሳደግ ምክር ቤት የተቋቋመ በመሆኑ የኢንዱስትሪው ባለቤት መሆን የሚቻልበትን ስራ ለመስራት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከኢንዱስትሪዎች ጋር  ትስስር በመፍጠርም ለሠልጣኞች የሚሰጠውን ስልጠና ጥራት ለማስጠበቅ ሠፊ ሥራ ስለሚጠይቅ በዚህ ላይ ከኢንዱስትሪዎች ጋር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተመሳሳይም አመራሩ በአሰራርና በቴክኖሎጂ የተደረገፈ ስራ እንዲያከናውን የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የሐሰት የምስክር ወረቀት የማሰራትና በመዛኝና ተመዛኙ መካከል ያለውን አላስፈላጊ ግንኙነት የመሳሰሉ በምዘና ወቅት የሚገጥሙ ብልሹ አሰራሮችን ለመግታት እየተሰራ ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2009 በአገሪቱ የነዳጅ ፍላጎትና ስርጭትን ለማመጣጠን ዘመናዊ የነዳጅ ትራንስፖርት አለመኖር ችግር እንደሆነበት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ገለጸ።

ድርጅቱ ዛሬ 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ታደሰ ኃይለማርያም እንዳሉት ዘመናዊ የነዳጅ የትራንስፖርት ዘዴዎችን መጠቀም ያለመቻል ለነዳጅ አቅርቦት እጥረት አንዱ መንስኤ ሆኗል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ የመጠባበቂያ ዴፖዎች አናሳ መሆን ሌላው የአገልግሎት ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተቋቋሙ የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች ማነስና የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ብቻ በአገልግሎት ዘርፉ በስፋት መዋልን እንደ ችግር ነው ያነሱት።

በተጨማሪ ለነዳጅ እጥረቱ በማደያዎች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋል የብልሹ አሰራር አዝማሚያ በዘርፉ ከሚጠቀስ የአቅርቦት ችግር መካከል ነው ብለዋል።

አቶ ታደሰ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በተለያዩ አገራት የነዳጅ ማጓጓዝ ስራው በቱቦ (ቧንቧ)፣ በባቡርና በመኪና ይከናወናል።

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ጭነት ተሽከርካሪ ማጓጓዣ ብቸኛ ዘዴ በመሆኑና እስካሁን አማራጭ ስላልተፈጠረ ለነዳጅ እጥረት መንስኤ የሚሆንበት አጋጣሚ እንደሚኖር አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ በዘርፉ የሚታዩትን ክፍተቶች ለመሙላት የአገልገሎት ማሻሻያ ስራ መጀመሩንም ዋና ስራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።

የነዳጅ እጥረቱን ለማቃለል በሁለት አካባቢ የአዳዲስ ማጠራቀሚያ ዴፖ ግንባታ ስራ ዕቅድ መኖሩን ገልጸው 30 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር የሚይዝ የነዳጅ መጠባበቂ ዴፖ በአዋሽ በመገንባት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የዚህ ዴፖ ግንባታ በስድስት ወራት ተጠናቆ ለአግልግሎት እንደሚበቃም እንዲሁ።

ድርጅቱ የነዳጅ ማጓጓዝ ስራውን ከተሽከርካሪ ወደ ባቡር ትራንስፖርት የማሸጋገር ዕቅድ እንዳለው ጠቁመው የአዋሽ ዴፖ መስመርን ከአዲስ በአበባ ጅቡቲ ከተዘረጋው የባቡር ሃዲድ ጋር የማገናኘት ስራ እንደሚሰራም ዋና ስራ አስፈጻሚው አመልክተዋል።

በዱከም በ10 ሄክታር ላይ 240 ኪዩቢክ ሜትር የሚይዝ የመጠባበቂያ ዴፖ ለመገንባት እና ከባቡር መስመር ጋር ለማገናኘት እቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።

ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ለመዘርጋት የረዥም ጊዜ ዕቅድ መያዙንም ጭምር።

የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ በበኩላቸው በአገሪቱ የሚፈጠረውን የነዳጅ ስርጭት ችግር ለመፍታት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተነድፈዋል ነው ያሉት።

ለአብነትም በአዲስ በአበባ ከ40 እስከ 60 የሚደርሱ የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎችን ለመገንባት መታቀዱን ገልጸው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቦታ ርክክብ መደረጉን ተናግረዋል።

ግንባታቸውን በ2010 ዓ.ም መግቢያ ተጀምሮ በዓመቱ መጨረሻ ለማጠናቀቅ መታቀዱንም ነው ሚኒስትሩ ያስታወቁት።

ከዚህ በተጨማሪም በክልሎችም አዳዲስ ማደያዎችን ለመገንባትና የትራንስፖርት አገልግሎቱን ምቹ ለማድረግ ከክልሎች ጋር ድርድር መጀመሩን አቶ ሞቱማ ጠቁመዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ሚያዝያ 27/2009 የአፍሪካን ከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ለማሳደግ የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ተገለጸ፡፡

የቻይናው ዓለም ዓቀፍ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ በዩኔስኮ የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ዱ ቶይት ጃኮን አነጋግሮ እንደዘገበው ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠትና ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ ያመች ዘንድ የከፍተኛ ትምህርት የተልዕኮ ትምህርት መስጫ ማእከላትን ለማስፋፋት ለተያዘው እቅድ  የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

አይሲቲ ሁሉንም የህይወት መስክ የሚነካ በመሆኑ  በማህበረሰቡ ውስጥ   እምርታዊ  ለውጥ ያመጣል ያሉት አማካሪው ተፅእኖው በተለይ በትምህርት ቤቶች ጎልቶ እንደሚታይ ነው ያብራሩት፡፡

አይ ሲ ቲ ተማሪዎችና መምህራን እውቀታቸውን የሚያጎለብቱበትን እድል የሚያሰፋ በመሆኑ  ማህበረሰቡ ትምህርት ቤቶች ይህን ወቅታዊ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ግፊት ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ 

አማካሪው ከሚያዝያ 24-26/2009 በጅቡቲ በተካሄደው የከፍተኛ ትምህርት፣ፖሊሲና ምርምር ጉባኤ መሳተፋቸውም ተመልክቷል፡፡

ጉባዔተኞቹ ኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ  ለትምህርት፣ ለከባቢ አየር ለውጥ፣ ለሰላምና ደህንነት እንዲሁም ለከፍተኛ ትምህርት የሚኖረውን ድርሻ የተመለከተ ውይይት አድርገዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ አይሲቲ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ የሚኖረውን ሚና ለማጉላት አካታችና ሁሉን አቀፍ ፖሊሲዎች ከማስፈለጋቸውም በላይ   ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአሁኑ ሰአት እያጋጠማቸው ያለውን ተጨባጭ ችግር ለመፍታት እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡   

በጉባዔው ላይ የሞሪሺየስና የጅቡቲውን ፕሬዝዳንቶች ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነሮች  ምሁራን ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ተማሪዎችና የልማት ድርጅት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

ቀጠናዊ የከፍተኛ ትምህርት፣ፖሊሲና ምርምር  ጉባዔው 13ቱን የምሥራቅ አፍሪካ አባል ሀገራት ያካተተ መሆኑም በዘገባው ተመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 27/2009 'አልቃሽና ዘፋኝ' የተሰኘ በማህበራዊ ህይወት ላይ ያተኮረ የኮሜዲ ቴአትር በድጋሚ በብሔራዊ ቴአትር መታየት ጀመረ።

 ቴአትሩ ከ30 ዓመታት በፊት ለተመልካች ቀርቦ የነበረ ሲሆን በተመልካች አስተያየት እንደገና ለመድረክ በቅቷል።

 የትውፊታዊ ተውኔት ደራሲና መምህር በነበረው ፍሰሐ በላይ ተጽፎ የተዘጋጀው ቴአትሩ በአሁኑ ወቅት በአርቲስት አዳፍሬ ብዙነህ እንደገና ተዘጋጅቷል።

 ቴአትሩ በአንድ ቤት ውስጥ ተከራይተው በደባልነት የሚኖሩ የአንዲት ሴት አልቃሽ፣ አንድ አዝማሪና በልመና የሚተዳደሩን አባት የዕለት ተዕለት ህይወትና ማህበራዊ መስተጋብር የሚያሳይ ነው።

 አዝማሪው የዕለት ጉርሱን ለማሟላት ሰርግና ድግስ ሲያሳድድ አልቃሿ ደግሞ በተቃራኒው ሀብታም ሰዎች በየጊዜው እንዲሞቱና ኑሮዋን እንድታሻሽል ትታትራለች።

 ቴአትሩ ከ30 ዓመታት በፊትም ሆነ ዛሬ ስለማህበራዊ ህይወትና የሰዎች መስተጋብር የሚያስተላልፈው መልዕክት እንዳለው አዘጋጁ ተናግሯል።

''ቴአትሩ በፍልስፍና ላይ የተመሠረተ ሲሆን አሁን በአገሪቱ የሚታየውን ነባራዊ ህይወትና ማህበራዊ ክዋኔዎችን ያንፀባርቃል'' ሲል ገልጿል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 27/2009 የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን በአገሪቱ የልማት ሥራዎች ያላትን ተሳትፎ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለፀች።

 ቤተክርስቲያኗ የ50ኛ ዓመት የኢዮቤልዩ በዓሏን የሃይማኖት አባቶች እና ተከታዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ ስታዲዮም አክብራለች።

 በዚህ ወቅት የቤተክርስቲያኗ ፕሬዝዳንት ፓስተር ይልማ ዋቄ ቤተክርስቲያኗ በመከራ ውስጥ አልፋ ዛሬ ለተገኘው ነፃነት በቅታለች ብለዋል።

 በቀጣይም የበለጠ ወንጌልን ከመሥበክ ባሻገር በአገሪቱ የሚከወኑ የልማት ሥራዎችን በመደገፍና ተሳታፊ በመሆን ያላትን ተሳትፎ አጠናክራ እንደምትቀጥል ፓስተር ይልማ ተናግረዋል።

 ቤተክርስቲያኗ ወጣቶችን፣ ሴቶችን እና በተለያየ መንገድ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ እቅድ አላት ያሉት ፓስተር ይልማ በቀጣይ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎችና የኃይማኖት አካላት ጋር ለአገሪቱ ሠላም እንደምትሰራ ተናግረዋል።

 የቤተክርስቲያኗ አባላት፣ ህዝበ ክርስቲያኑ እና የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ የአገሪቱ ህዝቦች በሙሉ አሁን ያለውን ሠላም ለማስቀጠል ለሠላም ዘብ ሊቆሙ ይገባል ብለዋል።

 የቤተክርስቲያኗ መጋቢ ፓስተር አበራ በላይ ከዚህ ቀደም በነበረው ሥርዓት ቤተክርስቲያኗ ብዙ ችግር እና እንግልት የደረሰባት ሲሆን አሁን ባለው የእምነት ነፃነት የአምልኮ እና የልማቱ ተሳታፊ ሆናለች ነው ያሉት።

 ቤተክርስተያኗ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም በትምህርት እና በሌሎች የልማት ተግባራት ያላትን ተሳትፎ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን በጥቂት የዩኒቨርስቲ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በ1958 ዓም ነው የተመሠረተችው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 27/2009 በመጪው ወር ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ስለሚጠናከሩ በደቡብ ምዕራብና ምዕራብ ኢትዮጵያ የዝናብ መስፋፋት እንደሚኖር   የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

 ኤጀንሲው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች አንጻራዊ ጥንካሬ ይዘው ሊቀጥሉ ይችላሉ።

 ዝናቡ ከወሩ አጋማሽ በኋላ ከደቡብ ምስራቅ፣ ከምስራቅና ከሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ቀስ በቀስ እንደሚቀንስም ነው የገለፀው።

 በመጪው ወር ከኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራና ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ አርሲ ባሌ፣ ቦረና እና ጉጂ፣ አዲስ አበባ፣ የጋምቤላና የቤኔሻንጉል ክልል የተለያየ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።

 ከአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ እንዲሁም ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ ባህርዳር ዙሪያ፣ አገው አዊ፣ የሰሜንና የደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ ከአፋር ዞኖች ደግሞ ሶስት፣ አራት እና አምስት የተለያየ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል።

 እንዲሁም አብዛኛው የትግራይ ክልል ዞኖች፣ ከደቡብ  ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ደግሞ የሀዲያና የጉራጌ፣ የሲዳማ፣ የከፋና የቤንች ማጂ፣ ወላይታ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ኦሞ የሰገን ህዝቦች የሶማሌ ክልል ሁሉም ዞኖች የተለያየ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል ብሏል።

 ከዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች መጠናከር ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ ከባድ ዝናብና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል ጠቁሟል።

 የዝናቡ መጠን በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበና አልፎ አልፎም ከዚያም በላይ ሊሆን እንደሚችል ተንብዩዋል።

 በመጪው ግንቦት በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች በአብዛኛው ዞኖች፣ በአፋር ክልል ዞኖች ደግሞ ሶስት፣ አራት እና አምስት እንዲሁም በሶማሌ ክልል ሁሉም ዞኖች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል ።

 ዝናቡ ዘግይተው ለተዘሩ በተለያዩ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የበልግ ሰብሎች ቀጣይ እድገት የጎላ ጠቀሜታ ሲኖረው፤ መደበኛው የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ ለጀመሩ አካባቢዎች እርጥበት ለማግኘት ያግዛል።

 በሌላ በኩል በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚጠበቀው ከባድ ዝናብና ቅጽበታዊ ጎርፍ በተለያዩ የእድገት ደረጃ ላይ ላሉ ሰብሎች አሉታዊ ተጽዕኖ  ስለሚኖረው ከወዲሁ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ኤጀንሲው ጥሪ አቅርቧል።

 

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2009 በአገሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥና የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆን አለበት አሉ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ።

ፕሬዝዳንቱ ይህን የተናገሩት ሁለተኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን ጉባኤን ሲከፍቱ ነው።

ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መፋጠን ወጣቱ ትውልድ በጊዜ፣ በእውቀት፣ በጉልበትና በገንዘብ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ፓኬጆች ተቀርጸው መተግበራቸውን የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ ''የወጣቶችን የኑሮ ሁኔታ መቀየር የሚችሉ በርካታ የስራ እድሎች ተፈጥረዋል" ብለዋል።

ወጣቶች በድህነት ቅነሳ ፕሮግራም ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ዘላቂ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋገጥ ስራ መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስትር እርስቱ ይርዳ በበኩላቸው ወጣቱ ድህነትን የማስወገድና የአገሪቱን ፈጣን ልማት የማረጋገጥ ኃላፊነቱ የጎላ ነው ብለዋል።

ይህን ከግብ ማድረስና የበለጸገች አገር ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።

እንደሳቸው ገለጻ ወጣቶች የሚጠበቅባቸውን አገራዊ ኃላፊነት በብቃት መወጣት የሚችሉበትን አቅም ለመገንባት ራሳቸውን በእውቀትና በክህሎት ለማሳደግ መጣር ይኖርባቸዋል።

በዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የበኩሉን ለመወጣት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ወጣት ታረቀኝ አብዱልጀባር በበኩሉ ፌደሬሽኑ በአገሪቱ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወጣቱን የኢኮኖሚው ተሳታፊና ፍትሃዊ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል ብሏል።

ፌደሬሽኑ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እስከ ወረዳ ድረስ መዋቅር በመዘርጋት ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ አባላት በማፍራት መንግስታዊ ከሆኑና ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ የወጣቶችን ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ መሆኑንም ገልጿል።

"አደረጃጀቶቻችንን በማጠናከር የአገራችንን ወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን" በሚል መሪ ቃል ነገም ቀጥሎ በሚውለው ጉባኤ የቀጣይ የፌደሬሽኑ አመራሮች ምርጫ ይካሄዳል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 27/2009 በሚያዚያ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 8 ነጥብ 6 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።

 ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መረጃ መሰረት የዋጋ ግሽበቱ ከመጋቢት ወር ጋር ሲነጻጸር የ0 ነጥብ 1 በመቶ ጭማሪ ነው ያሳየው።

 ምግብ ነክ በሆኑ ሸቀጦች ላይ 12 ነጥብ 2 በመቶ ሆኖ ሲመዘገብ ከመጋቢት ወር ጋር ሲነጻጸር የ2 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

 በተያዘው ወር በተለይ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላና ገብስ ላይ ጭማሪ የታየ ሲሆን በእህሎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ጠንከር ያለ በመሆኑ የምግብ ዋጋ ግሽበት ከፍ እንዲል አድርጓል፡፡

 ሆኖም በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በጥራጥሬ፣ ድንች፣ ስራስሮች እና የቡና ዋጋ ላይ ቅናሽ መታየቱን ነው ኤጀንሲው ያስታወቀው።

 ምግብ ነክ ባልሆኑት ላይ በወሩ የ4 ነጥብ 6 በመቶ ቅናሽ ሲታይ ካለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር 2008 ዓም ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የ4 ነጥብ 3 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

 ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍ እንዲል ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ ልብስ፣ መጫሚያ፣ የማገዶ እንጨት፣ የቤት ዕቃዎችና ማስጌጫዎች መሆናቸውን ጠቅሷል።

Published in ኢኮኖሚ

ዲላ ሚያዚያ 27/2009 ህገ-ወጥ ባለሁለት እግር ሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች መበራከት ለአደጋ እያጋለጣቸው መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

የከተማው ፖሊስ በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል ።

ነዋሪዎቹ በሰጡት አስተያየት ህገ-ወጥ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎቹ ለቁጥጥር አመቺ ባልሆኑ የከተማው የውስጥ ለውስጥ መንገዶች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የለት ተለት እንቅስቃሴያችንን ለአደጋ የተጋለጠና ስጋት ላይ የወደቀ አድርጎታል ብለዋል። 

የዲላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህርት ዳንቾ ፀጋዬ በሰጡት አስተያየት በቂ ክህሎት የሌላቸው ሞተረኞች  በመኖሪያ አካባቢዎችና ትምህርት ቤቶች አካባቢ ኃላፊነት በጎደለው ፍጥነት ስለሚያሽከረክሩ ህፃናትና አዛውንቶች ለአደጋው ዋንኛ ተጋላጭ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

"ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ህፃናትና ተማሪዎች ሞተር ሳይክል ሲያሽከረክሩና ሲለማመዱ በስፋት ይስተዋላሉ " ብለዋል።

ለዚሁ ብለው የትምህርት ገበታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱንም ጠቁመዋል ።

ሌላው የሀሴ ዴላ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ጢባ ማልደኢ በበኩላቸው "በከተማው በብዛት የተሽከርካሪ አደጋ የሚደርሰው በባለ ሁለት እግር ሞተር ሳይክል ነው " ብለዋል ።

እንደ አቶ ጢባ ገለፃ ከከተማ ወደ ገጠር መውጫ በሆኑ የውስጥ ለውስጥ  መንገዶች ላይ አደጋው ጎልቶ መታየቱ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል ።

በቂ ችሎታ የሌላቸውና ሕጻናት በባለ ሁለት እግር ሞተር ሳይክል እስከ አራት ሰዎችን ጭነው በፍጥነት በማሽከርከር በተሳፋሪዎችና እግረኞች ላይ አደጋ እያደረሱ መሆኑን ተናግረዋል ።

በከተማው ሰሌዳ የሌላቸው ህገ-ወጥ ሞተር ሳይክሎች እንቅስቃሴ እየጨመረ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሀሮ ወላቡ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ዳንኤል ከተማ ናቸው ።

"በሰዎችና እንስሳት ላይ አደጋ አድርሰው የሚሰወሩ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች በስፋት እየተስተዋሉ በመሆኑ የሚመለከተው አካል መፍትሄ ሊወስድ ይገባል " ብለዋል ።

የዲላ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የትራፊክ አደጋ ቁጥጥርና ክትትል ዋና ሥራ ሂደት አስተባባሪ ሳጅን አድማሱ ኢቲቻ እንደገለጹት በከተማው ከባለ ሁለት እግር  ሞተር ሳይክል መበራከት ጋር ተያይዞ እየደረሰ ያለው የተሽከርካሪ አደጋ አሳሳቢ ሆኗል ።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የህብረተሰቡን አመለካከት መገንባት ተገቢ በመሆኑ ለግንዛቤ ማስጨበጫ ቅድሜያ በመስጠት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በትምህርት ቤቶች የተማሪ ትራፊክ ክበባትና የቀበሌ የመንገድ ደህንነት ኮሚቴዎችን በማቋቋም በመንገድ ዘርፉ ህግና ደንብ እንዲሁም በተሽከርካሪ አደጋ መከላከል ላይ ያተኮረ ትምህርት ለህብረተሰቡ እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል ።

ከዚሁ ጎን ለጎን የመንገድ ደህንነት ደንብ በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት መንጃ ፍቃድ ሳይኖራቸው ደንብ ተላልፈው የተገኙ ከ140 በላይ የባለሁለት እግር ሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች መቀጣታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

እድሜያቸው 18 ዓመት ያልሞላቸው ህፃናትና ታዳጊ ወጣቶች በድብቅ ሞተር ሳይክል እንዳያሽከረክሩ ወላጆች ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደርጉ እንደሚገባ ሳጅን አድማሱ አስገንዝበዋል ።

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን