አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 04 May 2017

አዲስ አበባ ሚያዝያ 26/2009 የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ባካሄደው ምርመራ መርካታቸውን የመንግስታቱ ድርጅት የሠብዓዊ መብት ኮሚሽነር ተናገሩ ።

በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት ኮሚሽነር ዘይድ ራድ አል ሁሴን በጉብኝታቸው ማጠቃለያ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነሩ የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት የተፈፀመውን የሠብዓዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ ባካሄደው ምርመራ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ይፋ ያደረገችው የሠብዓዊ መብት መርሀ ግብር ብዙ ቸግሮችን እንደሚያስወግድ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል ኮሚሽነሩ።

የአገሪቱ የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተከሰተው አለመረጋጋት በፀጥታ ኃይሎች ስለተወሰደው እርምጃና ስለ ጠፋው የሰው ህይወት ይፋ ማድረጉ ጥሩ ነው ብለዋል።

የተመድ የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ሁኔታውን ለመመርመር ፍቃድ ባያገኝም የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያደረጋቸው ምርመራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር "በአዲስ አበባ የሚገኘውን ፅህፈት ቤታችንን ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመናል፤ ይህም ለባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ድጋፍ መስጠት ያስችለናል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ፣ የዜጎቿን የመማርና ጤንነት የማግኘት መብቶች ማረጋገጥ እንደቻለች ተናግረዋል።

ባልተረጋጋ ቀጣና ውስጥ ያለችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜ የአምባገነን ሥርዓት ወጥታ ያካሄደችው ሰፊ የመሰረተ ልማት ማስፋፋትና የፀረ ድህነት ትግል የሚደነቅ መሆኑንም ኮሚሽነር ዘይድ ራድ ገልፀዋል።

የአካባቢውን ሠላምና መረጋጋት በማስፈንና በርካታ የዓለም አገራት ለስደተኞች ጀርባቸውን በሰጡበት ወቅት ተቀብላ በማስተናገድ እያደረገች ያለውን አስተዋፅኦም አድንቀዋል።

ይሁን እንጂ አገሪቱ በዴሞክራሲና የሲቪክ ተቋማትን በማጠናከር ረገድ የሰራችው ሥራ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የዴሞክራሲና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በዘርፉ እንዲሰራም መክረዋል።

ኮሚሽነሩ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ለማጠናከር የሲቪክ ማህበራትና የበጎ አድራጎት እንዲሁም የፀረ ሽብር አዋጆችና የሚዲያ ህጎችን መልሳ ብታያቸው የሚል አስተያየትም ሰንዝረዋል።

በርካታ ዓለም አቀፍ ህጎችን ያፀደቀችው ኢትዮጵያ ቁርጠኝነቷን ወደ ተግባር ለመቀየር ፈተናዎችን ተቋቁማ ልትገፋበት ይገባልም ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት ከተቃዋሚዎችና ከሲቪክ ማህበራት ጋር የተጀመረውን ችግሮችን ለመፍታት ተቀራርቦ የመሥራት መርህ አጠናክሮ በመቀጠል ዴሞክራሲን ለማጎልበት እንዲሰራም መክረዋል።

ኮሚሽነሩ ከአፍሪካ ኅብረት አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ኅብረቱ በራሱ አቅም የሠብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር የሚያስችል አቅም ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን እንደተረዱ ጠቁመዋል።

የሠብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀምንና ግጭቶችን ለመከላከል ከኅብረቱ ጋር ለመስራትና ትብብራችንን ለማጠናከር ተስማምተናል ነው ያሉት።

የተባበሩት መንግስታት የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን የሠብዓዊ መብት ጉዳዮችን ለመመርመር የኢትዮጵያ መንግስት ፈቃድ እንዲሰጠውም ጥሪ አቅርበዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 26/2009 ወጣቱ ትውልድ ለአገራዊ ልማቱ በአንድነት ሊነሳ እንደሚገባ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አሳሰበ።

ማኅበሩ 76ኛውን የአርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል ከመዲናዋ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ከአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ ጋር በመተባበር አክብሯል።

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ወጣቱ ፍፁም አገራዊ ፍቅርን በመላበስ ለአገሩ ልማት መነሳት ይኖርበታል።

በተለይም ለልማቷ ቀጣይነት መረጋገጥ ወሳኝ የሆነውን ሠላም የማስፈን ኃላፊነት የወጣቱ ድርሻ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአገሪቷን የኢኮኖሚ ነፃነት በማስከበር የጀግኖች አርበኞችን ድል መድገም ከትውልዱ የሚጠበቅ የቤት ስራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ሌሎች የማኅበሩ አባላትም ወጣቱ ትውልድ ለአገሩ ሠላምና የልማት ጉዳይ አፅንኦት ሊሰጥ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ወጣቶች በትምህርታቸውና በተሰማሩበት የስራ መስክ በመትጋት አገር የሚያኮራ ተግባር መፈፀም እንዳለባቸውና ለዚህም እርስ በእርስ መዋደድና መከባበር አስፈላጊ እንደሆነ መክረዋል።

ከጀግኖች አያቶቻቸው የአገር ፍቅርን በመውረስም የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ማስቀጠልና ዳር ማድረስ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

76ኛው የአርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል ነገ በመላ አገሪቷ ይከበራል።

የድል በዓሉ "ኢንተርፕርነራዊ አርበኝነት ለአፍሪካ ኅብረት ኢኮኖሚ ነፃነትና ዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተከበረው።

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ ሚያዝያ 26/2009 በምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች የተመዘገበው ውጤት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ገለጹ፡፡

የዘላቂ ልማት ግቦች የ2017 የፈቃደኝነት ብሔራዊ ግምገማና የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም የምክከር መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።

የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች በመተግበር የታየው ቁርጠኝነትና ስኬት በዘላቂ የልማት ግቦች ለመድገም አጀንዳዎቹን ከሀገሪቱ የልማት እቅድ ጋር  በማጣጣም ወደ ትግበራ ምዕራፍ  ተገብቷል፡፡

ባለፉት ዓመታት የተካሄዱ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ውጤት በሀገሪቱ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ምቹ ሁኔታና መልካም ጅምር እንዲታይ ማስቻሉንም ገልፀዋል፡፡

በጋምቤላ ክልል በመረሃ ግብሩ የግምገማ መድረክ የታየውም የዘላቂ ልማት ግቦችም ሆነ ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማሳካት የሚያስችል አቅም መኖሩን ነው ፡፡

በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተፈጠረውን የባለቤትነት ስሜት ይዞ ከሰራ እንደ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ሁሉ ዘላቂ የልማት ግቦችንም ማሳካት እንደሚቻል  ወይዘሮ ብዙነሽ ገልጸዋል ።

"በክልሉ የተፈጠረውን ምቹ የልማት አጋጠሚ በመጠቀም ዘላቂ የልማት እቅዱን ለማሳካት ከአመራሩ ከፍተኛ ቁርጠኝነትና አቅም ይጠበቃል" ያሉት ደግሞ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ዋና ዳሬክተር አቶ ተመስገን ዋለልኝ ናቸው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ኡኩኝ ኡበያ  እንደገለፁት በክልሉ ባለፉት ዓመታት የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦችና የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማሳካት የተከናወኑት ስራዎች አበረታች ናቸው።

ይሁን እንጂ በጀትን በአግባቡ አሟጦ በመጠቀምና የገቢ አቅም በማሳደግ የልማት እቅዶችን  በተሟላ መልኩ እንዲተገበሩና የሴቶች እኩልነት እንዲረጋገጥ በማድረግ በኩል ውስንነቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በቀጣይ የታዩ ክፍተቶችን በማረም ዘላቂ የልማት ግቦችንና ሁለተኛውን የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት እያንዳንዱ አመራር ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ላክደር ላክባክ በበኩላቸው ክልሉ ባለፈው የበጀት ዓመት ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር መጠነኛ የልማት ክፍተት ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም  በዘንድሮው ዓመት በተሻለ መልኩ እየተተገበሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በጋምቤላ ከተማ  ላለፉት ሁለት ቀናት በተካሄደው የግምገማ መድረክ ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በመድረኩም በ2017 የሚተገበሩ ዘላቂ የልማት ግቦችና የ2008 ዓ.ም የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም ቀረቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 26/2009 የበጎ ፈቃደኞቹ ተግባር የኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክረዋል ተባለ።

ይህ የተባለው የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ስምንት በጎ ፈቃደኞችን በሶስት ክልሎችና በአዲስ አበባ ለማሰማራት ባደረገው የሽኝት ፕሮግራም ነው።

በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር የእስያና መካክለኛው ምስራቅ ቡድን መሪ አቶ ደረጀ ግርማ ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ ስላላቸው የረዥም ጊዜ ጠንካራ ወዳጅነት አውስተዋል።

ደቡብ ኮሪያውያኑ በኢትዮጵያ በተለያየ ሙያ የሚሰጡት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም የአገራቱን ግንኙነት ይበልጥ ያሳድገዋል ብለዋል።

"የበጎ ፈቃደኞቹ ተግባር የአገራቱን የህዝብ ለህዝብ መቀራረብና መደጋገፍ ያጠናክረዋል" ነው ያሉት።

በተጨማሪም "ደቡብ ኮሪያ በፈጣን እድገት ላይ የምትገኝ በመሆኗ ኢትዮጵያውያን የበጎ ፈቃደኞቹን ልምድና ተሞክሮ መቅሰም ያስችላቸዋል" ብለዋል አቶ ደረጀ።

በኢትዮጵያ የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ኮይካ ዳይሬክተር ማዳም ዶህ ዩንጋህ በጎ ፈቃደኞቹ በአማራ፣ ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎችና በአዲስ አበባ እንደሚሰማሩ ተናግረዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ የነርስ፣ የክሊኒካል ፓቶሎጂ፣ የሶሻል ወርክ፣ የመምህርነትና የኪነ-ጥበብ ምሩቃን መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርናና በማህበረሰብ ልማት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግና በኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ እንደሚከወንም አስታውቀዋል።

በጎ ፍቃደኞቹ በተለያዩ የስራ መስኮች ለሁለት ዓመት የነጻ አገልግሎት ስራዎችን ለመተግበር መዘጋጀታቸውንም አክለዋል።

እስካሁን በኢትዮጵያ ከ470 በላይ በጎ ፈቃደኛ ደቡብ ኮሪያውያን በተለያየ ጊዜ የነፃ አገልግሎት እንደሰጡ ተገልጿል።

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ሚያዝያ 26/2009 ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገቻቸው ያሉ የልማት ስትራቴጅዎች የተባበሩት መንግስታት የያዛቸው የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት መሰረት መሆናቸው ተገለፀ።

በሁለተኛው የእድገትና ትራስፎርሜሽን እቅድ የመጀመሪያው አመት አፈፃፀምና በተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦች አስመልከቶ ላለፉት ሁለት ቀናት በመቀሌ ከተማ የተካሄደ ውይይት ተጠናቋል ።

በብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን የኢኮኖሚ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ውብሸት ካሳ በወቅቱ እንደገለፁት በሀገሪቱ ተግባራዊ እየተደረጉ ካሉ የልማት ስትራቴጂዎች መካከል የማህበራዊ አገልግሎቶችና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ መርሀ ግብሮች ተጠቃሽ ናቸው ።

የልማት ስተራቴጂዎቹ የተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦች ከያዛቸው እቅዶች ጋር በቀጥታ የሚዛመዱ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ድህነትና ረሃብን ማጥፋት፣ጤናማ ህይወትና ደህንነቱ የተጠበቀ ዜጋ እንዲኖር ማድረግ ዋናዎቹ የዘላቂ የልማት ግቦች መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።

እንደ አቶ ውብሸት ገለፃ የስርአተ ፆታ እኩልነትን ማረጋገጥ፣ የመሰረተ ልማት ግንባታና የኢንዱስትሪ ፈጠራ ማስፋፋትና የውሃ ስነ-ምህዳር በማጎልበት ዘላቂ ልማትን መጠበቅ የሚሉት ሌሎቹ ግቦች ናቸው ።

በትግራይ ፋይናንስና እቅድ ቢሮ ከፍተኛ የእቅድ ባለሙያ አቶ አማሃ ሃይሉ በበኩላቸው በክልሉ በግበርና ፣ በኢንዱስትሪና በማህበራዊ ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ለዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ መሰረት እጣሉ ነው ።

በተጠናቀቀው በጀት አመት ብቻ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከ190 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የስራ እድል መፈጠሩንና 18 ነጥብ 55 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ  1 ሺህ 457 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የእቅድ ባለሙያ ወይዘሮ መአዛ ታደለ  በበኩላቸው ''የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተፅእኖዎች ለልማት እቅዱ ትግበራ ተግዳሮት ናቸው'' ብለዋል ።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲን በመወከል በውይይቱ የተሳተፉ አቶ ብርሃኑ አቻሜ  በሰጡት አስተያየት በአገሪቱ የተጀመሩት የልማት ስራዎችና የዘላቂ ልማት ግቦች ውጤታማ እንዲሆኑ በየዘርፉ የሚካሄዱ የምርምር ስራዎች አገራዊ የልማት ስትራቴጂና ፖሊሲን መሰረት ያደረጉ ሊሆኑ ይገባል ።

በወርልድ ቪዥን የትግራይ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባልደረባ አቶ ገብረህይወት መዝገቦ በበኩላቸው "ኢትዮጵያ ተግባራዊ የምታደርጋቸው የልማት ስትራቴጂዎች ለዘላቂ የልማት ግቦቹ መሰረትና መልካም ተሞክሮዎች ናቸው " ብለዋል ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አለማ እንየው እንደገለፁት በአገሪቱ  በመካሄድ ላይ ያሉ ትላልቅ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ሲጠናቀቁ ለድህነት ቅነሳ መርሀ ግብሩ ስኬታማነት የላቀ አስተዋፆ ይኖራቸዋል ።

ከህገ- መንግስቱ ጀምሮ ህዝቡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች እያሳየ ያለው ተሳትፎ ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬታማነት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ከክልሉ ምክርቤት ቋሚ ኮሚቴዎች፣ ከሲቪክ ማህበራትና ከባለድርሻ አካላት የተውጣጡ 300 የሚሆኑ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 26/2009 የህብረተሰቡን ጤና፣ ስነ-ልቦና ፣ ወግና ባህል ከማስጠበቅ አንፃር የማስታወቂያ ስራን ሊቆጣጠር የሚችል ረቂቅ ፖሊሲና ስትራቴጂ ተዘጋጀ።

ረቂቁ በአገሪቱ ክትትልና ድጋፍ አልባ የሚባለውን የማስታወቂያ ስራ የሚያስተካክል ነው ተብሏል።  

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በተዘጋጀው ረቂቅ ላይ ከማስታወቂያ ስራ ድርጅቶች፣ ከመገናኛ ብዙሃንና ከማስታወቂያ አሰሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

ሚኒስትር ዴኤታው ዛዲግ አብርሃ እንዳሉት የማስታወቂያ አዋጅ በ2004 ቢወጣም የዘርፉን አጠቃላይ አቅጣጫ የሚያመላክት ፖሊሲ ባለመኖሩ የዘርፉ ዕድገት በሚፈለገው መልኩ መጓዝ አልቻለም።

ዘርፉ ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረለት ብዙዎችን የሚቀጥርና ከፍተኛ መዋዕለ-ነዋይ የሚያንቀሳቅስ ምርታማ ኢንዱስትሪ መሆን የሚችል ነው ብለዋል።

ይህ ካልሆነና አሁን ባለበት ከቀጠለ ተጠያቂነትን ማዕከል ያላደረጉና ፍትሃዊ ያልሆኑ ሂደቶች ተበራክተው በማህበረሰቡና በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ከባድ መሆኑን ገልፀዋል።

እየተሰሩ ያሉ ማስታወቂያዎች የህብረተሰቡን ጤና፣ ወግና ባህል፣ ብሄር፣ ፆታና ሃይማኖት ያላገናዘቡ ከመሆናቸው በተጨማሪ በማዕከላዊነት የማይመሩና ፍትሃዊነት የጎደላቸው በመሆናቸው ይህን ረቂቅ ማዘጋጀት አስፈልጓል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።

አስተያየት ሰጪዎችም በአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡ ማስታወቂያዎች ስነ-ምግባርን ያልተከተሉ፣ የህፃናትና ወጣቶችን አመለካከት በአሉታዊ የሚበርዙ፣ የመገናኛ ብዙሃን ይዘት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ናቸው ሲሉ ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪ አልኮል መጠጣትን የሚያበረታቱ፣ ስነ-ልቦናን የሚጎዱ፣ ከእውነታ የራቁ፣ ግነት የበዛባቸው፣ ከአገሪቱ ባህልና ወግ ጋር የማይሄዱ ናቸው ሲሉም አክለዋል።

በተጨማሪም ዘርፉን ከማሳደግና ህዝቡን ማስታወቂያ እንዲያገኝ ከመስራት ይልቅ "የአገሪቱን ታሪክና እሴት ያለአግባብ በመጠቀም ለራሳቸው የግል ጥቅም የሚያውሉ  ናቸው" ይላሉ።

የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ፍሬው አበበ "የዘገየ ቢሆንም ጥያቄያችን መሰረት ተደርጎ ረቂቁ በመዘጋጀቱ ደስ ብሎኛል፤ ቶሎ ወደ ስራ መግባቱ ልማዳዊ የሆነውን የማስታወቂያ ስራ የሚለውጥ ነው" ብለዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን የወከሉት አቶ አሸናፊ ጅማ በበኩላቸው በሌላ አገር ማስታወቂያ ከመሰራጨቱ በፊት የስነ ልቦና፣ የጤናና የማስታወቂያ ባለሙያዎች ቅድሚያ እንዲያዩት ይደረጋልና ተሞክሮ መወሰድ ቢችል በማለት ሃሳብ ሰንዝረዋል።

የማስታወቂያ ባለቤቶች ግነት ስለሚወዱ መገናኛ ብዙሃን ማስተናገድ ያለባቸውን ለይተው ቢያሰራጩ ጥሩ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ፖሊሲው ፀድቆ ወደ ስራ ሲገባ የተባሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ያስችላል ያሉት ደግሞ ረቂቁን ያቀረቡት በመንግስት ኮሙኒኬሽን የሚዲያ ልማትና ብዝሃነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ደጀኔ ናቸው።

እንደ ረቂቅ ፖሊሲና ስትራቴጂው የህፃናትና ወጣቶችን ተጋላጭነት ለመከላከል የአልኮል ማስታወቂያ ከአራት ሰዓት በፊት አይተላለፍም።

ማስታወቂያዎች በመገናኛ ብዙሃን ይዘትና የጊዜ ሰሌዳ ላይ ተፅዕኖ እንዳይኖራቸው ያላቸውን ሰዓት የመቀነስ ስራም ይሰራል።

የማስታወቂያ ዘርፍ ብሔራዊ ካውንስል በማቋቋም ተዋናዮች ሙያዊ ስነ-ምግባር ጠብቀው እንዲሰሩም ያደረጋል።

ከጤና፣ ከምግብና ከህክምና ጋር የተገናኙ ማስታወቂያዎች ከተቋማቱ ጋር በመሆን የክትትልና ቁጥጥር ስራ ይደረግባቸዋል።

የገበያውን ተዋዳዳሪነት ከማሳደግ ጎን ለጎን አቅም ላልገነቡ መገናኛ ብዙሃን የተለየ ማበረታቻ እንደሚደረግላቸውም ነው የተገለጸው።

ሌላው ፖሊሲና ስትራቴጂው ከሚያስተካክላቸው ሁኔታዎች መከካከል ማስታወቂያዎች በአገር ውስጥ ቋንቋ ይዘጋጁ የሚለው አንዱ ነው።

Published in ማህበራዊ

ሀረርሚያዝያ 26/2009 በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በመጀመሪያው በጀት ዓመት ለተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት የማኑፋክቸሪንግና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው  የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን አስታወቀ።

የዘላቂ ልማት ግቦች የ2017 የፍቃደኝነት ብሔራዊ ግምገማና የ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የ2008 አፈጻጸም የምክክር ጉባዔ በሐረር ከተማ ተካሂዷል።

በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን የመሪ ፕላን ዝግጅትና ክትትል ባለሙያ አቶ ሐብታሙ አስፋው እንደገለፁት በእቅድ ዘመኑ በመጀመርያው በጀት ዓመት ኢኮኖሚው በ8 በመቶ አድጓል።

በተለይ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ከነበረበት የ4 ነጥብ 9 በመቶ ወደ 5 ነጥብ 4 በመቶ እንዲሁም የኮንስትራክሽን ዘርፉም ከ8 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 9 ነጥብ 5 በመቶ ማደጉ ለተመዘገበው ሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የጎላ ድርሻ መያዙን ተናግረዋል ።

የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢም ከ691 የአሜሪካን ዶላር ወደ 794 ዶላር ከፍ ማለቱን ጠቁመው ከዋጋ ንረት አኳያ በነጠላ አሀዝ ለመገደብ የታሰበው በእቅዱ መሰረት እየሄደ መሆኑን ጠቁመዋል ።

በጤናው ዘርፍ የእናቶችን ሞት በመቀነስ፤ በትምህርት ዘርፉም በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ፣ በመሰናዶና  በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ተሳትፎ የተከናወኑት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባንፃሩ በኤክስፖርት ሴክተርና ከሀገር ውስጥ ምርት አኳያ የታክስ አሰባሰብ ክንውን ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ አፈጻጸም መታየቱን አቶ ሐብታሙ ጠቅሰዋል ።

እንደ አቶ ሐብታሙ ገለፃ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በተከሰተው ድርቅ የግብርና ዘርፉ በታሰበው ደረጃ አላደገም ።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው "የ2008  እቅድ አፈጻጸም በተወሰኑ ዘርፎች ላይ የአፈጻጸም ክፍተት ቢታይም በአብዛኛው ስኬታማ ሆኗል" ብለዋል።

በጉባኤው የአፈጻጸም ክፍተት የታየባቸውን ዘርፎች በመለየት በፌዴራልና በክልል ደረጃ በቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች የጋራ አቅጣጫ መያዙን ተናግረዋል ።

በተለይ ታቅደው ያልተከናወኑ ተግባራትን ከዘላቂ ልማት ስድስት ግቦች ጋር አቀናጅቶ መስራት የቀጣይ አቅጣጫ ነው ።

በእቅዱ ትግበራ ለታዩ ክፍተቶች ምክንያት የሆኑ የቅንጅታዊ አሰራር እጦትና የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባርን በጋራ ማስወገድ እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል ።

የሐረሪ ክልል የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ አብዱልባሲጥ አቡበከር በበኩላቸው ጉባዔው በእቅድ ትግበራ ሂደቱ  ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን እንዴት መቅረፍ እንደሚቻል ተሞክሮ የተገኘበት ነው።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምክክር ጉባኤ  የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የከተማና ገጠር ነዋሪዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 26/2009 የኩላሊት እጥበት (ዲያሌሲስ) ሕክምና በዳግማዊ ምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ አስታወቀ።

የኮሌጁ ምክትል ፕሮቮስት ዶክተር ብርሃኔ ረዳኢ እንደገለፁት ኮሌጁ በሚቀጥለው ሣምንት በሆስፒታሉ ለሚጀመረው የኩላሊት እጥበት ሕክምና የማሽን ተከላና የህንፃ እድሳት አከናውኗል።

ለሆስፒታሉ ለስድስት ወራት የሚያገለግል የአላቂ እቃዎች ድጋፍ እንደተሰጠውም ገልጸዋል።

ኮሌጁ ቀደም ሲል ለዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ድጋፍ በማድረግ የሕክምና አገልግሎቱን ማስጀመሩን አስታውሰዋል።

በተመሳሳይ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ለማጠናከር የስምንት ማሽኖች ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

በቀጣይም በባህርዳር፣ ጎንደር፣ መቀሌ፣ ደሴ እና ድሬዳዋ ከተሞች በሚገኙ ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት አገልግሎቱን ለማስጀመር ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ ዶክተር ብርሃኔ ገለፃ በአሁኑ ወቅት ታማሚዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ እስኪሰራላቸው ድረስ የእጥበት አገልግሎት እያገኙ እንዲቆዩ እየተደረገ ነው።

ኮሌጁ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ444 ሰዎች የኩላሊት እጥበት፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮም ለ36 ሰዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና መስጠቱን ዶክተር ብርሃኔ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና በተሳካ ሁኔታ የተካሄደው መስከረም 11 ቀን 2008 ዓ.ም ነው።

የንቅለ ተከላ አገልግሎቱ ከአሜሪካው ሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑንና የእውቀትና ክህሎት ሽግግር ለማድረግ አራት የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች ስልጠና ላይ መሆናቸውን ዶክተር ብርሃኔ ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 26/2009 ሆስፒታሎቹ ያሉባቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመቅረፍ ተገልጋዮቻቸውን ለማርካት መስራት እንዳለባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአለርት የህክምና ማዕከል፣ የቅዱስ ዼጥሮስ ቲቢ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅና የአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ ሆስፒታሎቹ የሚነሱባቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለማስወገድ የጤና ልማት ሰራዊቶቻቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ለዚህም የልማት ሠራዊት አደረጃጀት፣ የክህሎትና የግብዓት ችግሮችን በጋራ በመለየትና በመወያየት በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የተደራጀ ሠራዊት በመገንባት ሠራዊቱ ችግሩን ነቅሶ በማውጣትና መፍትሄውን በማቅረብ ሚናውን እንዲወጣ ማድረግ አለባቸውም ነው የተባለው።

ሆስፒታሎቹ ከኀብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የጀመሯቸውን ስራዎች አጠናክረው በመቀጠል የተገልጋይ እርካታ መፍጠርም ይጠበቅባቸዋል።

ቋሚ ኮሚቴው የአለርት የህክምና ማዕከል የህሙማን አስተኝቶ ህክምና ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመቀነሱ በቀጣይ ሊታይ እንደሚገባ ጠቁሟል።

የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን ቡሳ ቀደም ሲል የመለስተኛ ቀዶ ህክምና በሚሰጥበት ወቅት የታካሚዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሰው አሁን ከፍተኛ ቀዶ ህክምና መስጠት በመጀመሩና የታካሚዎች ቆይታ በመራዘሙ ቁጥሩ መቀነሱን አስረድተዋል።

የቅዱስ ዼጥሮስ ቲቢ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በበኩሉ የቲቢ ህክምና ጀምረው የሚያቋርጡ ህሙማን ህክምናቸውን እንዲያጠናቅቁ በማድረግ ረገድ ያለበትን ክፍተት እንዲያስወግድ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ያዕቆብ ሰማን በምላሹ ሆስፒታሉ ታካሚዎችን ከማስገንዘብ ባሻገር ለአስታማሚዎቻቸው ስልክ በመደወል ህሙማኑ ህክምናቸውን እንዲያጠናቅቁ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅም ህክምናውን ከማስተማርና ከምርምር ስራው ጋር በማቀናጀት ረገድ የተጠናከረ ተግባር ሊያከናውን እንደሚገባው ነው ከቋሚ ኮሚቴው የተነገረው።

የኮሌጁ ባለሙያዎች ከዕቅድ በላይ ምርምሮችን በሳይንስ ጆርናሎች ማሳተማቸውና ኮሌጁም ለባለሙያዎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የኮሌጁ ምክትል ፕሮቮስት ዶክተር ብርሃኔ ረዳኢ ገልጸዋል።

ቋሚ ኮሚቴው የአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተግባራቱን በጤና ልማት ሠራዊት በመምራት ውጤታማ ስራ ማከናወን አለበት ብሏል።

የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ዳዊት አሰፋ በሆስፒታሉ የጤና ልማት ሠራዊት መዋቅር ቢኖርም ውጤታማነቱ ላይ ያለውን ክፍተት ለመቅረፍ እንሰራለን ነው ያሉት።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዚያ  26/2009 ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ እጅ ኳስ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ  ከነገ በስቲያ እንደሚጀምር ፌዴሬሽኑ አስታወቀ።

 ፌዴሬሽኑ የውድድሩን መርሃ ግብር አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

 የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ፍትህ ወልደሰንበት እንዳሉት ውድድሩ ስፖርቱን ለህብረተሰቡ ከማስተዋወቅ ባሻገር ወጣቶች በስፖርቱ እንዲዝናኑ እድል በመፍጠር አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

 ለስፖርተኞች የውድድር ዕድል በመፍጠርና ተተኪዎችን በማፍራት ረገድም የጎላ ሚና አለው ሲሉ ተናግረዋል።

 የመጀመሪያው ዙር ውድድር ከጥር 14 እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን 11 ክለቦች ተሳትፈውበታል።  

 ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤት፣ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ሐዋሳ፣ ቡታጅራ፣ ከንባታ ዱራሜ፣ ባህርዳር፣ አላማጣና ሃዲያ ከተሞች ተወዳዳሪ የነበሩ ቢሆንም ሃዲያ ራሱን ከውድድሩ ማግለሉ ተገልጿል።

 በመሆኑም በሁለተኛው ዙር ውድድር ሃዲያ የማይሳተፍ በመሆኑ በ10ሩ ክለቦች መካከል ውድድሩ እንደሚደረግ ተገልጿል።

 በመጀመሪያ ዙር በተደረጉ ጨዋታዎች መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስና ኮልፌ ቀራንዮ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ውድድሩን እየመሩ ይገኛሉ።

 እንደ አቶ ፍትህ ገለጻ በመጀመሪያ ዙር ውድድር የሜዳ፣ የፋይናንስ፣ በተመልካቾች መካከል የተስተዋለ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደልና የዳኞች ቁጥር ማነስ ችግሮች ነበሩ።

 ፌዴሬሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቀጣይ ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት ያደርጋል ብለዋል።

 ውድድሩን በአንደኝነት የሚያጠናቅቀው ክለብ ብሄራዊ ቡድኑን ወክሎ በአፍሪካ ተወዳዳሪ ይሆናል።

 ሁለተኛ ዙር የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሚያዚያ 28 እና 29 ቀን 2009 ዓም በአዲስ አበባና በባህርዳር ከተሞች ይጀመራል።

 የፌዴሬሽኑ የውድድር መርሃ ግብር እንደሚያመለክተው ፕሪሚየር ሊጉ እስከ ሐምሌ 9 ቀን 2009 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

Published in ስፖርት
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን