አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 03 May 2017

 

አዲሰ አበባ ሚያዚያ 25/2009 ኢትዮጵያ በሶማሊያ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ከገቡት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት መሃመድ አብዱላሂ መሃመድ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነትና በአካባቢ ጉዳዮች ላይ በቤተ መንግስት ተወያይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶማሊያ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ኢትዮጵያ እያበረከተችው ያለውን አስተዋፅኦ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት በአገራቱ መካከል አዲስ ምዕራፍ ይከፍታልም ብለዋል።

በአገሪቱ ሠላምና ደህንነት እንዲሁም የሁለቱ ሃገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲዳብር ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሶማሊያ ድህነትን ለመዋጋት በምታደርገው ጥረት በጋራ ለመስራትና ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላትም አክለዋል።

በሶማሊያ መልካም ፈቃድ አገሪቱ ለምትመሰርተው ፌዴራላዊ መንግስት ሙያዊ እገዛ በኢትዮጵያ በኩል ይደረግላታል ነው ያሉት።

በቅርቡ በለንደን በሚካሄደው ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ እንደ ኢጋድ ሊቀመንበርነቷ በሶማሊያ ወጥና የተቀናጀ ድጋፍ እንዲኖር፣ አልሸባብ ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ ፣ ሶማሊያ እንድታገግምና ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግላት ትሰራለች ብለዋል።

ፕሬዝዳንት መሃመድ አብዱላሂ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ውይይታቸው አልሸባብ ከሶማሊያ ሙሉ ለሙሉ በሚወገድበት፣ በድህነት መዋጋት፣ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲና በገንዘብ አስተዳደር ስርዓት ላይ ትኩረት ማድረጉንም ጠቁመዋል።

አልሸባብ በሶማሊያ በመንቀሳቀስ በአገሪቱ ላይ ጥፋትና ውድመት ሲያስከትል የቆየና ለዓለም አቀፍ ሠላምና ደህንነትም ስጋት መሆኑን አመልክተዋል ፕሬዚዳንቱ

አገራቸው በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያና ኬንያ እንዲሁም ከአሚሶም በቂ ድጋፍ በመኖሩ አልሸባብን እየተዋጋች መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጉዳይ እየከፈለች ያለውን መስዋዕትነት ጠቅሰው ምስጋና አቅርበዋል። 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 25/2009 የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ የምክር ቤቱ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን የህዝብ ተወካች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ተናገሩ።

አፈ ጉባዔው በአዲስ አበባ የስራ ጉብኝት ላይ ያሉትን የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዘይድ ራድ አል ሁሴንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ኮሚሽነር ዘይድ ራድ ትናንት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን የጎበኙ ሲሆን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋርም ተወያይተዋል።

በዛሬ ውሏቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ መክረዋል።

ኮሚሽነር ዘይድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰብዓዊ መብት አጀንዳን እንዴት እየከወነው ነው? ሲሉ አፈ ጉባኤ አባዱላን ጠይቀዋል።

አፈ ጉባዔ አባዱላም የዜጎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ በምክር ቤቱ ከሌሎች ጉዳዮች ቅድሚያ ተሰጥቶት በተቀናጀ መንገድ የሚተገበር ዓብይ አጀንዳ መሆኑን ገልጸውላቸዋል።

"ምክር ቤቱ ለዜጎች ህይወት መሻሻል፣ ህገ-መንግስታዊ መብት መረጋገጥና ሌሎች መሰረታዊ ድጋፎችን ማሟላት የሚያስችል የአሰራርና የክትትል ስርዓት ዘርግቷል" ብለዋቸዋል።

ባለፈው ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከት የዜጎች በሠላም የመኖር መብት እንዳይጣስ ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ሠላም ማስፈን መቻሉንም ገልጸዋል።

አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ባለችበት ጊዜም የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ምክር ቤቱ በየጊዜው  በመገምገም የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰዱንም አብራርተዋል።  

"የዴሞክራሲና ሰብዓዊ ተቋማት ግንባታ ስራው በሂደት ላይ ነው" ያሉት አባዱላ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአቅም ግንባታ ስራውን እንዲደግፍ ጠይቀዋል።

ኮሚሽነር ዘይድ ራድ አል ሁሴን በበኩላቸው ስለ ምክር ቤቱ የዜጎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ በአፈ ጉባዔ አባዱላ ለተሰጣቸው ማብራሪያ ምስጋና አቅርበዋል።

ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ተቋማት ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ዘይድ ራድ አልሁሴን ነገ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ጀኔቫ እንደሚያመሩ ይጠበቃል።

Published in ፖለቲካ

ባህር ዳር ሚያዚያ 25/2009 የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአገሪቱ የሚስተዋለውን ኋላቀር የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓት ለማዘመን በሚደረግ ጥረት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን አስታወቀ።

''የመሬት አስተዳደር ለዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደር'' በሚል መሪ ቃል 2ኛው ዓመታዊ የመሬት አስተዳደር ጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተጀምሯል።

በዩኒቨርሲቲው የመሬት አስተዳደር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር አቻምየለህ ጋሹ በኮንፈረንሱ ላይ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው የአገሪቱ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም በዘመናዊ መንገድ የተደራጀ እንዲሆን በትኩረት እየሰራ ነው።

ዩኒቨርስቲው በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ለመፍታት በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስልጠን ላይ ይገኛል፡፡

ባለፉት ዓመታትም አንድ ሺህ 250 ተማሪዎችን አሰልጥኖ በማስመረቅ የሰው ሰሃይል እጥረቱን በመፍታት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።

እንዲሁም በየደረጃው በስራ ላይ የሚገኙ የመሬት አስተዳደር ባለሙያዎችን የአጫጭር ጊዜ ስልጠና በመስጠት የአቅም ክፍተታቸውን የመሙላት ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ በመስራት በጥናትና ምርምር  የተደገፈ የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዓመታዊ ኮንፈረሱም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የበለጠ ተቀራርቦ በመስራት እንደሃገር ወጥ የሆነ ስርዓት እንዲገነባ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የዩኒቨርስቲው የምርምርና  ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው በሃገር አቀፍ ደረጃ በከተማም ሆነ በገጠር የሚገኘው የመሬት ሃብት በአግባቡ ተለይቶ ያልተመዘገበና በባህላዊ መንገድ የሚተዳደር ነው።

በዘርፉ ብቃት ካለው የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረትና ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጉድለት ጋር ተያይዞ የሚታየውን ይህንኑ ችግር በጥናትና ምርምር በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የከተሞችን የመሬት አጠቃቀም በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደርና መረጃ ላይ መሰረት ያደረገ የከተማ ልማት ለማካሄድ የሚያስችል ስትራቴረጂ ተነድፎ እየተተገበረ እንደሚገኝ የገለፁት ደግሞ በከተሞችና ቤቶች ልማት ሚኒስቴር የከተማ መሬትና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ከበደ ናቸው።

በዚህም አዲስ አበባን ጨምሮ 23 ከተሞችን ካደስተርን መሰረት ያደረገ የካርታ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

''እስከ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጨረሻ 91 ከተሞችን ለመድረስ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል'' ብለዋል።

በእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ዮሐንስ ረዳ በበኩላቸው የገጠሩን የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም በዘመናዊ መንገድ የመመዝገብ ስራ እየተከናወነ ነው።

ባላፉት ዓመታት በተካሄደ የምዝገባ ስራ አንደኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ምዝገባ 98 በመቶ ማጠናቀቁን ጠቁመዋል።

የአገሪቱን የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲና እቅድ ለማውጣት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

''የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የሚያዘጋጀው አውደ ጥናትም ባለድርሻ አካላት በጋራ በጉዳዩ ዙሪያ በመምከር በአጭር ጊዜ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የጎላ ጠቀሜታ አለው'' ብለዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው አውደ ጥናት ላይም ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች፣ ዘርፉን የሚደግፉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የፌዴራል ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ሀረር ሚያዚያ 25/2009 የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ድርቅንና በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የቲማቲም ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ መሆኑን ገለፀ።

የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ከበደ ወልደ ጻዲቅ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው አርሶ አደሮች እያስተዋወቀ የሚገኘው ከአሜሪካ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ እስራኤልና አውስትራሊያ ያስመጣቸውን አራት የቲማቲም ዝርያዎች ነው።

ዩኒቨርሲቲው በምርምር ጣቢያ ለሁለት ዓመታት ባደረገው የዝርያ ማላመድ ለአካባቢው የአየር ሁኔታ ተስማሚ መሆናቸው መረጋገጡንም ተናግረዋል ።

በተጨማሪም በሐረማያ ወረዳ፣ በድሬዳዋ አስተዳደርና በሐረሪ ክልል በ610 አርሶ አደሮች ማሳ ዝርያዎቹን የማለማመድና የማስተዋወቅ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል ።

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ የቲማቲም ዝርያዎቹ በአርሶ አደሩ ማሳ በሄክታር እስከ 500 ኩንታል ምርት እንደሚሰጡ ተረጋግጧል ።

"በዚህም ከነባሩ ዝርያ ከሚገኘው 100 ኩንታል አብላጫ ምርት የሚሰጡ በመሆናቸው በአካባቢው አርሶ አደሮችና የግብርና ቢሮዎች ተቀባይነት አግኝተዋል " ብለዋል ።

ዩኒቨርሲቲው ከአጋር አካላትና ከዘር አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመሆን በቀጣይ በሽንኩርትና ቃርያ ዝርያዎች ላይ የማላመድና የማስፋፋት ስራ ለመካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑን ፕሮፌሰር  ከበደ አስታውቀዋል ።

በድሬዳዋ ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የግብርና ኤክስቴንሽን አብይ የስራ ሂደት መሪ አቶ መሐመድ አብዱላሂ በበኩላቸው ከሁለት አመት በፊት በሁለት ቀበሌዎች የተጀመረው የቲማቲም ዝርያ የማላመድና የማስተዋወቅ ስራ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል ።

የዝርያ ማላመድና ማስተዋወቅ ልማቱ 95 ነጥብ 5 ሄክታር የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ውሀን በቁጠባ በመጠቀም  የተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል ።

እንደ አቶ መሐመድ ገለፃ በልማቱ ተሳታፊ የሆኑ 540 አባወራ አርሶ አደሮች በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስርም ተጠቃሚ ሆነዋል ።

"ዝርያዎቹ በሽታና ሙቀትን  የሚቋቋሙና በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ ሊመረቱ የሚችሉ በመሆናቸው የአርሶ አደሩን በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል " ብለዋል አቶ መሀመድ።

በሐረሪ ክልል የሐዋዩ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ከዲር ሙሳ በሰጡት አስተያየት "ቀደም ሲል የምጠቀመው የቲማቲም ዘር ፀሀይና በሽታን መቋቋም ስለማይችል የተፈለገውን ምርት ሊሰጠኝ አልቻለም" ብለዋል።

አሁን እየዘሩት ያለው "ሻንቲ" የተሰኘ የቲማቲም ዝርያ ፀሀይና በሽታን ተቋቁሞ በሶስት ወራት ጊዜ  የሚደርስ መሆኑን ተናግረዋል ።

በሩብ ሄክታር ማሳቸው ላይ ከዘሩት የቲማቲም ዝርያ 30 ሳጥን ምርት ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል ።

እንደ አርሶ አደሩ ገለፃ ከቲማቲም ምርት ሽያጭ ያገኙት 22 ሺህ ብር ገቢ ከዚህ ቀደም በማሳው ላይ ከሚያለሙት ጫት ከአንድ ጊዜ ሽያጭ ያገኙ ከነበረው ገቢ የተሻለ ነው ።

ሌላው የሀረማያ ወረዳ ቱጂ ገቢሳ ቀበሌ አርሶ አደር መሀመድ አደም በበኩላቸው " በአነስተኛ ማሳዬ ላይ የዘራሁት አዲሱ የቲማቲም ዝርያ ፈጥኖ የሚደርስና በመጠንና በክብደቱም ቀድሞ ከምዘራው የተሻለ ነው " ብለዋል ።

በዚህ አመት በመጀመሪያ ዙር መስኖ ከዘሩት የቲማቲም ዝርያ ከሰበሰቡት ምርት ሽያጭ 30 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደር መሀመድ ተናግረዋል ።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ 56 የቲማቲም፣ የሽንኩርትና የቃሪያ ዝርያ አይነቶችን በተለያዩ አካባቢዎች በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ እያላመደና እያስተዋወቀ መሆኑ ታውቋል ።

 

መቱ ሚያዚያ 25/2009 ባገኙት  ብድርና በተመቻቸላቸው  የገበያ ትስስር ተጠቅመው ራሳቸውን ለመለወጥ እየሰሩ መሆናቸውን በዚህ አመት በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ አንዳንድ የበደሌ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

በቡኖ በደሌ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ36ሺ በላይ ስራ አጥ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የስራ መስኮች መሰማራታቸውን የዞኑ ስራ እድል ፈጠራና ከተማ ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ወጣት ከድር ድልገባ በበደሌ ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ ነው፡፡ ወጣቱ እንዳለው በዚህ አመት ከሌሎች ሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን በግንባታ መስክ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

“በተሰማራንበት የግንባታ መስክ በቂ ስልጠና ተሰጥቶናል” የሚለው ወጣቱ በከተማው ከመንግስት መስሪያ  ቤት ጋር በተፈጠረላቸው 80ሺ ብር የሚጠጋ የገበያ ትስስር ወደ ስራ መግባታቸውን  ተናግሯል፡፡

''ለመነሻ ያህል የ10 ሺ ብር ብድር አግኝተናል'' የሚለው ወጣቱ የጀመሩትን የግንባታ ስራ በአብዛኛው በማጠናቀቃቸው 50ሺ ብር የሚጠጋ ክፍያ እንደተፈጸመላቸው ገልጿል፡፡

መንግስት የወጣቶችን የስራ አጥነትችግር ለመቅረፍ እያደረገላቸው ያለው ድጋፍ ሙሉ ጊዜውን ለስራ በመስጠት ራሱን እንዲለውጥ ተነሳሽነት እንደፈጠረለት የሚናገረው ደግሞ ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ወጣት ዳዊት ሙሉጌታ ነው፡፡

ከሌሎች ሁለት ጓደኞቹ ጋር በዚህ አመት በማህበር ተደራጅተው  በግንባታው መስክ መሰማራታቸውን ገልጾ  የወሰዱትን የግንባታ ስራ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ለማስረከብ መዘጋጀታቸውን አመልክቷል፡፡

በዚህ አመት የጀመሩትን አነስተኛ የግንባታ ስራ በማጠናቀቅ በቀጣዩ አመት  ወደ ተሻለ ደረጃ ለመሸጋገር አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን ወጣቶቹ  ተናግረዋል፡፡

የቡኖ በደሌ ዞን ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር ወጣት ሀብታሙ ፈቃዱ በበኩሉ በዞኑ እስከ ገጠር ቀበሌ ድረስ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከተለያዩ የወጣቶች አደረጃጀቶች ጋር  በጋራ እየተሰራ ነው፡፡

የቡኖ በደሌ ዞን የስራ እድል ፈጠራ እና የከተማ ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ግርማ በፈቃዱ እንደገለጹት የበደሌ ከተማን ጨምሮ በዞኑ ዘጠኝ ወረዳዎች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ36ሺ በላይ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡

ከወጣቶቹም ከ10ሺ በላይ የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑ ነው የተናገሩት፡፡

''ወጣቶቹ በ2ሺ 400 ማህበራት በመደራጀት በገጠር ግብርና፣  በማምረቻ፣ በአገልግሎት፣ በግንባታና የመሳሰሉት የስራ መስኮች ተሰማርተዋል'' ነው ያሉት፡፡

ለወጣቶቹ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር  የተሰጣቸው መሆኑን ገልጸው፤ ከአካባቢው መለስተኛና ትላልቅ የልማት ፕሮጄክቶች ጋር ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸው አብራርተዋል፡፡

በዞኑ እስከ ዓመቱ መጠናቀቂያ ድረስ እስካሁን ወደ ስራ የገቡትን ጨምሮ ከ44 ሺ በላይ ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ለወጣቶቹ  ለማከፋፈል  2ሺ ሄክታር የሚሆን መሬት መለየቱንና ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር  ለመስጠት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ሚያዝያ 25/2009 ስድስተኛው  ዓለም  አቀፍ   የሃይድሮ ፓወር  ኮንፈንስ    ከግንቦት  1-3/2009  በአዲስ አበባ  ይካሄዳል፡፡

 ኮንፈረንሱ  በየሁለት  አመቱ   የሚካሄድ  ሲሆን     በአፍሪካ   ሲካሄድ   የመጀመሪያው ነው ፡፡

ጉባዔው በመላ ዓለም አስተማማኝና ቀስ በቀስ ያሉበትን ችግሮች እያቃለለ የሚሄድ የውሃና የሀይል ስርዓት ለማስፈን በቀጣዮቹ አስር አመታት የሚተገበር የሀይድሮ ፓወር ልማት አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኮንፈረንሱ  የሃይድሮ  ፓወር  ፕሮጀክቶች   ሲነደፉ   አካባቢያዊ፣ ማህበራዊና   ተያያዥ   ጉዳዮችን  ከግምት  ውስጥ  ማስገባት  በሚቻልበት መንገድም ይመክራል፡፡      

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮኒሽን ኮንፈረንሱ በአህጉሪቱ ታዳሽ ሃይልን ለማስፋፋት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ገልጾ  ለጉባዔው መሳካትም የድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቋል፡፡

በአዲስ  አበባ  በሚካሄደው  ስድተኛው አለም  አቀፍ  የሃይድሮ  ፓወር   ኮንፈንስ   የሀገራት  መሪዎች  የዘርፉ  ባለሙያዎች፣ ተመድ ፣  የትምህርትና የሲቪል  ማህበራት ተቋማትና  ሌሎች  ባለድርሻ  አካላት  እንደሚሳተፉ  ይጠበቃል፡፡

 

ምንጭ፡-APO

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2009 የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት 13 አዳዲስ የሰብልና የእንስሳት መኖ ዝርያዎችን በማውጣት ለተጠቃሚዎች እያደረሰ ነው።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በዚህ ዓመት ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋሉ ተብለው በብሔራዊ ዘር አፅዳቂ ኮሚቴ ተቀባይነት ካገኙት ቴክኖሎጂዎች መካከል 11ዱ የምግብ ሰብል ዝርያዎች ናቸው።

ሁለቱ ለእንስሳት መኖነት የሚያገለግሉ መሆናቸውንና የባኮና ሲናና የምርምር ማዕከላት ያበለፀጓቸው ቴክኖሎጂዎች መሆናቸውን ጠቁሟል።

አዳዲሶቹ ዝርያዎች የምርታማነትን ደረጃ በማሳደግ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው አስታውቋል ኢንስቲትዩቱ።

በሁለቱ ማዕከላት በአንድ ዓመት ጊዜ በርካታ ቁጥር ያላቸው የምርምር ቴክኖሎጂዎች ሲለቀቁ በአገሪቱ ታሪክ ቀዳሚ ነው ብሏል።

ከምግብ ሰብል ቴክኖሎጂ የምርምር ውጤቶች የፓስታና ማካሮኒ ስንዴ ዝርያ አንዱ ሲሆን እስካሁን ከነበረው ዝርያ 12 ነጥብ 9 በመቶ የምርት መጠን ብልጫ ያለው ነው።

አዲሱ የአጃ ስንዴ ዝርያም በ14 ነጥብ 63 በመቶ ብልጫ ያለው ምርት የሚሰጥ ሲሆን በዳጉሳ ላይ በተሰራ ምርምርም ከቀደመው በ18 ነጥብ 22 በመቶ የሚበልጥ ምርት የሚሰጥ ዝርያ መለቀቁን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

በምርምር የወጣ አንድ የባቄላ ዝርያም ከነባሩ በ20 ነጥብ 38 በመቶ ብልጫ ያለው ምርት እንደሚሰጥ ጠቁሞ አራት የአተር ዝርያዎች በተለያዩ ስነ-ምህዳሮች ሲመረቱ ከ13 ነጥብ 39 እስከ 28 ነጥብ 28 በመቶ ብልጫ ያለው ምርት እንደሚሰጡ አብራርቷል።

ከቲማቲም ዝርያዎች የ38 እና የ28 በመቶ ብልጫ ያለው ምርት የሚሰጡ ሁለት ዝርያዎች በምርምር የተገኙ ሲሆን፤ ከነባሩ ሰሊጥ 22 ነጥብ 2 በመቶ ብልጫ ያለው ምርት የሚያስገኝ አንድ ዝርያም ለተጠቃሚዎች ተለቋል።

በእንስሳት መኖ ዘርፍ ጥምር ጥቅም ያላቸው ሁለት የፒጋን ፒ ዝርያዎችም ለተጠቃሚዎች መቅረባቸው ተጠቁሟል።

አዲሶቹ ቴክኖሎጂዎች ለተለያዩ የስነ-ምህዳር አካባቢዎች ተስማሚ በመሆናቸው በዘር ብዜት ላይ የተሰማሩ መንግስታዊና የግል ተቋማት እንዲያባዟቸውና ለተጠቃሚዎች እንዲያሰራጯቸው ጠይቋል ኢንስቲትዩቱ። 

አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2009 የመንግስታቱ ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦች ለሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ዋነኛ መሳሪያዎች ሆነው እንደሚያገለግሉ ብሄራዊ የፕላን ኮሚሽን ገለፀ።

ኮሚሽኑ ይህን የገለጸው የ2017 ዘላቂ የልማት ግቦችን በአገር አቀፍ ደረጃ ሲገመግም ነው።

ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው አደም እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት ብሄራዊ ግምገማ እንዲያደርጉ ከተመረጡ 44 አገራት አንዷ በመሆን የዕቅዱን የልማት ግቦች አፈፃፀም ገምግማ ታቀርባለች።

ይህም ዘላቂ የልማት ግቦቹን "ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር በማጣጣም መተግበር ያስችላል" ነው ያሉት።

ግምገማው ዘላቂ የልማት ግቦች "ለአገራችን የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ የሚኖራቸውን አጋዥነት የምናስገነዝብበትና ተጨማሪ ግብዓቶችን የምንወስድበት መድረክ ነው" ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ በአዲስ አበባ በተካሄደው ውይይት ከተለያዩ ተቋማትና ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የአመራር አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።

ተሳታፊዎቹ ድህነትንና ረሃብን ማጥፋት፣ ጤናማ ህብረተሰብ መፍጠር፣ የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ማረጋገጥ እንዲሁም የመሰረተ ልማት ግንባታና የውሃ ስነ-ምህዳርን መጠበቅ የሚሉትን የድርጅቱን ግቦች መነሻ በማድረግ ሃሳብ ሰጥተዋል።

በተለይ የልማት ግቦቹ በመላ አገሪቱ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋትና የክልሎችን የወጪ ንግድ ሚና በማሳደግ ረገድ ዕቅድ ተይዞ ቢሰራ የሚሉ ሃሳቦችን አንስተዋል።

በተጨማሪም ዕቅዱ ወጣቶችን በማብቃት፣ ስራ ፈጠራን በማገዝና ወደ ስራ በማሰማራት ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባልም ተብሏል።

ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው ከተሳታፊዎች የተነሱ ሃሳቦችና ጥያቄዎች በግብዓትነት እንደሚወሰዱና በመጨረሻም ግምገማው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሲጸድቅ ለመንግስታቱ ድርጅት እንደሚገለፅ ተናግረዋል።

የዘላቂ ልማት አጀንዳ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2015 የመንግስታቱ ድርጅት አባል አገራት በኒውዮርከ ባካሄዱት ስብሰባ የፀደቀና በሁሉም አገራት የሚተገበር መርሃ ግብር ነው።

አጀንዳው በኢትዮጵያም ከ2008-2022ዓ.ም ተግባራዊ የሚሆን ነው።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2009 በ400 ሚሊዮን ብር ከውጭ አገር ተገዝቶ የገባ 379 ሺህ 702 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ የሚረከበው ማጣቱ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ይህን ያሳወቀው ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን ሲያቀርብ ነው።

ኮርፖሬሽኑ ማዳበሪያዎችን ከውጭ እየገዛ ለክልሎች የሚያቀርብ ቢሆንም በ2007 ዓ.ም የተገዛ 336 ሺህ 702 ኩንታል እና በ2008 ዓ.ም ተገዝቶ የገባ 43 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ክልሎች ሊወስዱት ባለመቻላቸው በመጋዘን ተቀምጧል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ከፍያለው ብርሀኑ ሪፖርቱን ሲያቀርቡ ‘‘ማዳበሪያው ከባንክ በተገኘ ብድር በመገዛቱ ወለዱ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመሆኑና ለመጋዘን ኪራይ በሚከፈለው ገንዘብ መንግስት ከፍተኛ ኪሳራ ላይ እየወደቀ ነው’’ ብለዋል።

ይህ በምን ምክንያት ሊፈጠር እንደቻለ ከመንግስት ልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ለቀረበላቸው ጥያቄ በግዥ ስርዓቱ ውስብስብነት እንደሆነ ተናግረዋል።

ማዳበሪያው የተገዛው በእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር በኩል ከአርሶአደሮች በመጣ ፍላጎት ቢሆንም ማዳበሪያው ከደረሰ በኋላ ግን "ከአፈራችን ጋር አይስማማም በሚል ሊገዙን አልቻሉም" ብለዋል።

በኮርፖሬሽኑ የግብዓት ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ታፈሰ ገብሩ በበኩላቸው የተገዙት ቦሮን፣ ዚንክና ፖታሽ ማዳበሪያዎች ከየአፈር አይነቱ ጋር ተስማሚ መሆናቸው በጥናት የተረጋገጠ ቢሆንም ምርቶቹ አዲስ በመሆናቸው ተቀባይነት አላገኙም ነው ያሉት።

ይህ የአገር ኃብት እንዳይባክን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ለአርሶአደሩ የሚደርስበት መንገድ እየተመቻቸ ነው ብለዋል።

ለወደፊቱ ግን ከክልሎች ጋር ባለው የግዥ ግንኙነት አስቀድሞ ውል እንዲፈራረሙ የሚያደርግ ህግ እየረቀቀ መሆኑን አቶ ከፍያለው አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ኮርፖሬሽኑ ከተጠቃሚዎች ጋር በቀጥታ ቢገናኝ ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረገ ግዥ ሊፈፅም እንደሚችልም ነው ያስረዱት።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ችግሩን በፍጥነት ሊፈታ እንደሚገባ አሳስቧል።

Published in ኢኮኖሚ

ሚያዝያ 25/2009 ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም ለዓለም ጤና ድርጅት የሚያስፈልጉ መሪ መሆናቸውን የዩ ኤስ አይ ዲ የቀድሞ አማካሪ ገለጹ ፡፡

የዩ ኤስ አይ ዲ የቀድሞ አማካሪና በአሁኑ ጊዜ ደግሞ  ዓለም ዓቀፍ የልማትና ማህበራዊ ጉዳይ ፕሮጀክቶችን  በግላቸው የሚያማክሩት ኒኮሌ ሺይግ ሁፊንግተን በተሰኘው ድረ ገጽ ባሰፈሩት ጽሁፍ የቀድሞው የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትርና  የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት የሚመጥኑ ተወዳዳሪ ናቸው ብለዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በታሪኩ  እንደ እርሳቸው በተሻለ መልኩ ሊመራ የሚያስችል እውቀት፣ ክህሎትና የስራ ልምድ ያለው መሪ  ሊያገኝ እንደማይችል  ነው አማካሪዋ በጽሁፋቸው ያሰፈሩት፡፡

ምርጫው ሊካሄድ ከሶስት ሳምንታት ያነሰ ጊዜ መቅረቱን የጠቆሙት አማካሪዋ የዓለም መሪዎች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀድሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስትርና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሆኑትን አፍሪካዊ መሪ የመምረጥ እድል እንዳላቸው በጽሁፋቸው ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም ለስራ ጉዳይ ወደ ኢትዮጵያ በተመላለሱበት ጊዜ  በዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም አመራር ሰጪነት የተከናወኑ  ስራዎችንና በአይናቸው የተመለከቷቸውን ለውጦች በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡

አማካሪዋ ዶክተር ቴድሮስን ያወቋቸው እኤአ በ2005 ዓ.ም ለአሜሪካው ግሎባል ኤድስ ይሰሩ በነበረበት ወቅት አዲስ አበባ ተዘጋጅቶ በነበረ ጉባኤ ላይ እንደ ነበር ያስታውሳሉ፡፡

በጉባዔው ላይ ዶክተር ቴድሮስ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አማካኝነት በሀገራቸው ላይ ሊያመጡ ባሰቡት ለውጥ መማረካቸውንም ይገልጻሉ፡፡

ለዚህ ደግሞ ሴቶችን በጤና ልማት ሰራዊትነት ግንባር ቀደም አድርገው ማሰለፋቸውን አድንቀዋል፡፡

እኤአ በ2010 የዩ ኤስ አይ ዲ ከፍተኛ አማካሪ በነበሩበት ጊዜ የአሜሪካ ዓለም ዓቀፍ የጤና ኢንቨስትመንትን እንቅስቃሴ ለመመልከት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶስት ሀገራት ጉብኝት አድርገዋል ፡፡

በጉብኝታቸውም ፕሮግራሙ በተለይ በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል፣ ወረርሽኖችንና ድንገተኛ የጤና እክሎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከቱን በአካል ተዘዋውረው ለመመልከት መቻላቸውን መስክረዋል፡፡

አማካሪዋ እአአ በ2016 ስልጠና ለመስጠት ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን ገልጸው በዚህኛው ጉብኝታቸው ደግሞ በሀገሪቱ የተተገበረው የጤና ፕሮግራም የህጻናትን ሞት በሁለት ሶስተኛ፣ የኤች አይ ቪ ኤይድስ ስርጭቱን በ90 ከመቶ፣ ከወባ ጋር በተያያዘ የሚከሰትን ሞት በ75 ከመቶ አንዲሁም በሳንባ ነቀርሳ የሚከሰትን ሞት በ64 ከመቶ ለመቀነስ ማስቻሉን ስለመረዳታቸውም አብራርተዋል፡፡

በሁለቱም ጉብኝታቸው ከዶክተር ቴድሮስ ጋር መነጋገራቸውን የገለጹት አማካሪዋ ግብረ መልሶችን በጥንቃቄ የማድመጥ ክህሎታቸውንና  ስለጎበኟው አካባቢዎች የነበራቸውን እውቀት አድንቀዋል፡፡

ዶክተር ቴድሮስ ያካበቱት ልምድና እውቀት ድርጅቱን ለመምራት የሚያስፈልጉ ወሳኝ ሰው መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ስለመሆኑ በጽሁፋቸው አስፍረዋል፡፡

የሁሉንም ዜጋ ጤንነት ለማረጋገጥ ዶክተር ቴድሮስን መምረጥ የተሻለ አማራጭ መሆኑንም ነው አማካሪዋ ኒኮሌ ሺይግ የጠቆሙት፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ