አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Saturday, 20 May 2017

ሀዋሳ ግንቦት12/2009  የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች በሀገሪቱ ያለውን  ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲጎለብት የጎላ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የኢትዮጵያ ብርድካስት ባለስልጣን  አስታወቀ።

 በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች  ጋር በሀዋሳ ከተማ ውይይት በተካሄደበት ወቅት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርአይ አስገዶም በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ህብረተሰብ የተሟላና  ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኝ ሬዲዮ ጣቢያዎቹ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

 ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ህብረተሰቡ በሚረዳው የአካባቢ ቋንቋ ከመንግሰት የሚወርዱ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ዙሪያ የተሟላ እውቀት እንዲኖረው እያገዙ ናቸው፡፡ 

 ጣቢያዎቹ የሽፋን ውስንነት ፣ የጥራት ፣ የቴክኒክ አቅምና የፋይናንሰ  ችግሮች ቢኖርባቸውም  በሀገሪቱ ያለውን  ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲጎለብት የጎላ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን አቶ ዘርአይ ተናግረዋል፡፡

 ችግሮቹን በመፍታት የሬዲዮ ጣቢያዎቹ የተሟላ ስርጭት እንዲኖራቸው ለማገዝ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሰራም አመልክተዋል፡፡ 

 የከምባታ ማህበረሰብ ሬዲዮ  ጣቢያ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ በፀጋ በቀለ  እንዳሉት ጣቢያው አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት 2001 ዓ. ም ጀምሮ በከንባትኛ ቋንቋ በዞኑ ሰባት ወረዳዎች  መረጃ ለህዝብ እያደረሰ ይገኛል።

 የዞኑ አስተዳደር የሚሰራጨው ጣቢያው የሚሆን ቢሮ ሰርቶ የሰጠ ቢሆንም የተገነባው ስትዲዮ ድምፅ የሚያስገባ በመሆኑ ለስርጭቱ እንቅፋት መሆኑን ጠቁመዋል።

 የአርጎባ ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ስራ አስኪያጅ አቶ እስማኤል ጦሀ በበኩላቸው  ጣቢያው አብዛኛውን ስርጭት   የሚከናውነው በበጎ ፍቃደኞች እንደሆነ ተናግረው በቅጥር የሚሰሩ ሰራተኞች የሚከፈለው ክፍያ አነስተኛ በመሆኑ እንደሚለቁ ገልጸዋል፡፡

 በሀገሪቱ በአዲስ አበባና በስምንት ክልሎች  ፈቃድ ከተሰጣቸው 45 የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች መካከል 26  ወደስራ በመግባት በአማርኛና  በአካባቢ ቋንቋዎች ስርጭት እያካሂዱ መሆናቸውን በባለስልጣኑ የመገናኛ ብዙሃን ፍቃድና ምዝገባ  ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡

 በሀዋሳ ከተማ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ውይይት ዛሬ የተጠናቀቀ ሲሆን ዓላማውም  የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎቹ ችግሮቻቸውን በመለየት ለመፍትሄው አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ 

Published in ማህበራዊ

አዳማ ግንቦት 12/2009 በሃይማኖት ሽፋን ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳን ለማራመድ የሚደረገውን እንቅስቃሴና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል ህዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን አጠናክሮ ሊታገለው እንደሚገባው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አሳሰበ።

ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚፈፀሙ የአክራሪነትና ፅንፈኝነት ድርጊቶችን ለመከላከል ህዝበ ሙስሊሙን ያሳተፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል ።

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሐጅ መሀመድ አሚን ጀማል ስልጠናውን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ እስልምናን በቀዳሚነት በሰላምና በፍቅር የተቀበለች የፍትህ አገር መሆኗን በታላቁ ነቢይ ተመስክሮላታል ።

" እኛ ኢትዮጵያዊያን የመከባበር ባህላችን በዓለም ህዝቦች የታሪክ መዝገብ ላይ ጎልቶ የሚታይ ፀጋችን ነው " ያሉት ፕሬዚዳንቱ ሀገሪቱ  ልታድግ የምትችለው ቀድሞ የነበሩት አኩሪ እሴቶቻችን በማጠናከር ለልማትና ለሰላም በፅናት በመቆም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ያዓለም ዋነኛ የስጋት ምንጭ የሆነው አክራሪነትና ፅንፈኝነት በሁሉም ሀገራት ለማስፋፋትና በህዝቦች ላይ በጉልበት ለመጫን የሚንቀሳቀሱና ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ሃይሎች መኖራቸውን ተናግረዋል ።

ሐጅ መሀመድ እንዳመለከቱት  በሀገሪቱ ያለ መንግስትና ያለ እስልምና ምክር ቤቱ እውቅናና ፈቃድ ህዝቡን በማሳሳት ገንዘብ የማሰባሰብ ህገ ወጥ ድርጊት የሚፈፅሙ የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ሃይሎች መኖራቸው ተደርሶበታል፡፡

ድርጊቱ በኦሮሚያ ፣ በቤንሸንጉል ጉሙዝ ፣ በአማራ ፣ በደቡብ ህዝቦችና በሌሎችም አካባቢዎች እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል ።

" የሀገሪቱን  ህግ በመጣስ ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ወደ ጎን በመተውና በማን አለብኝነት ተግባር ህዝቡን እየሰበሰቡ መስጊድና መድረሳ እንሰራላችኋለን በሚል የማሳሳቻ ቃል  የሚያካሄዱትን ገንዘብ የመሰብሰብ ዘመቻ በቸልታ አንመለከተውም "ብለዋል ።

በሃይማኖት ሽፋን አክራሪ አስተሳሰቦችን በማራመድ የግል ፍላጎቶችንና የፖለቲካ ዓላማን በህዝቦች ጫንቃ ላይ በሃይል ለመጫን የሚደረገው እንቅስቃሴ ለመከላከል ህዝበ ሙስሊሙ በፅናት ሊታገለው እንደሚገባም  አሳስበዋል ።

መንግስትም ሀገር ለማተረማመስ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በመቆጣጠር የህዝቡን ሰላም የማስጠበቅና የሀገሪቱን  ህጎች ለማስከበር ሃለፊነቱን በብቃት መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ተወካይ  አቶ ሀዱሽ ካሱ በበኩላቸው  በኢትዮጵያ  እየታየ ያለው እድገት ፌዴራላዊ ስርዓቱን ያጎናጸፈው የማንነትና የሃይማኖት እኩልነት ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ትምክህተኝነትና ጠባብነት ፣ አክራሪነትና ፅንፈኝነት ባስከተሉት ችግር በርካታ ወገኖች  የስነ ልቦና ጉዳት ሰለባ እንዲሆኑ ማድረጋቸውን ጠቁመው  መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን ያለምህረት በፅናት እንደሚታገላቸው አረጋግጠዋል ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሃፊ መጋቢ ዘርይሁን ደጉ በበኩላቸው አክራሪነትና ፅንፈኝነት ሁሉ ጊዜ መነሻው በሃይማኖት ሽፋን የሚካሄድ ድብቅ አጀንዳ መሆኑን ገልዋል፡፡

" እኔ ከምከተለው ሌላ ሃይማኖት መኖር የለበትም የሚለው ደግሞ መገላጫው ነው " ያሉት  ዋና ፀሃፊው ሁሉንም የሃይማኖት ተቋማት አክራሪነትና ጽንፈኝነት በፅናት ለመታገል በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በየቦታው እያካሄደ ያለው የስልጠና መድረኮች  ሙስሊሙ ህብረተሰብ ፀረ አክራሪነትና ፅንፈኝነት ትግሉን በእውቀት ላይ ተመስርቶና ሰፊ ንቅናቄ ፈጥሮ እንዲረባረብ የሚያግዝ ነው ተብሏል ።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ  ህዝበ ሙስሊሙ በእውቀት ላይ ተመስርቶ  አክራሪነትና ፅንፈኝነት እንዲታገል በቅርቡ በጎንደር ፣ በአሶሳና በሀዋሳ የፀረ አክራሪነት ግንዛቤ ማጎልበቻ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡

በአዳማ ከተማ ለሶስት ቀናት የሚቆየው ስልጠናም  ተመሳሳይ መሆኑንና በመጪው ረዕቡ ደግሞ  በደሴ ከተማ እንደሚቀጥል  ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

Published in ማህበራዊ

ጊምቢ ነቀምቴ ዲላ ግንቦት 12/2009 የማዳበሪያ ዋጋ ዘንድሮ ቅናሽ በማሳየቱ  የተሻለ ግብአት ተጠቅመው ከአምናው የበለጠ ሰብል ለማምረት እንዳነሳሳቸው  በምዕራብ ወለጋ ዞን  አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡  

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አርሶ አደሮች ከሰብል በተጓዳኝ ቡና በማልማት ገቢ ምንጫቸውን ለማሳደግ እየሰሩ ሲሆን በጌዴኦ ዞን ደግሞ  የበልግ እርሻ ስራው ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው፡፡

ከምዕራብ ወለጋ ዞን አርሶ አደሮች መካከል የላሎ አሳቤ ወረዳ ነዋሪው አቶ  ሁሴን መሀመድ ለኢዜአ እንደገለጹት የሚፈልጉትን ዓይነት ማዳበሪያ መጠን በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት እየቀረበላቸው ነው፡፡ 

ዋጋው ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በኩንታል እስከ 400 ብር ድረስ ቅናሽ እንዳለው ጠቁመው በዚህም ተጠቅመው በገበያ አዋጭነት ያላቸውን ሰብሎች ለማምረት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የላሎ አሳቤ ወረዳ  አርሶ አደር  አያና ዲሳሳ በበኩላቸው ዘንድሮ የማዳበሪያ ዋጋ መቀነሱ ወጪ ከመቀነስ አልፎ ግብኣቱን በበቂ ሁኔታ በመጠቀም ምርታማነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል፡፡

 የግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብርሃም ደሜ እንዳመለከቱት በመኸሩ ወቅት 357 ሺህ 498 ሔክታር መሬት በዘር ለመሸፈን እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

ግብኣትና የተሻሻሎች አሰራሮችን በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ከ219 ሺህ ለሚበልጡ የዞኑ አርሶ አደሮች ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰው  " 236 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እየተሰራጨ ነው" ብለዋል ።

በመኸሩ ወቅት ከሚለማው መሬት ከዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማግኘት ታቅዷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አርሶ አደሮች  ከሰብል በተጓዳኝ ቡና በማልማት ገቢ ምንጫቸውን ለማሳደግ እየሰሩ   ናቸው፡፡

በዞኑ አቤ ዶንጎሮ ወረዳ የኮትቻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር  ጅረኛ ጀና በሰጡት አስተያየት በሰብል ልማት ላይ ተወስነው እንደነበርና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግብርና ባለሙያ ታግዘው  ቡናንም በተጓዳኝ እያለሙ መሆናቸውን  ገልጸዋል፡፡

" ባለፉት ሰባት ዓመታት በቡና ልማት በመሳተፍ ውጤታማ በመሆኔ ዛሬ ላይ ከግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ተርታ ተሰልፌያለሁ" ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ገበየሁ ገመቹ ናቸው።

የዞኑ ቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ ከተማ ገለታ እንደገለጹት በግልና በመንግስት ከ730 በላይ የቡና ችግኝ ጣቢያዎች ዘንድሮ ከ11 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ ተዘጋጅቷል።

የተዘጋጀው ችግኝ ከ12 ሺህ 300 በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በመኸሩ ወቅት እንደሚተከልም አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል በጌዴኦ ዞን በዘንድሮው በልግ ወቅት ከከታረሰው 10ሺህ 369 ሄክታር መሬት ውስጥ 8ሺህ 333 ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን በዞኑ  እርሻና ተፈጥሮ ሃብት መምሪያ የሰብል ልማት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ሠላማዊት ያሬድ ገልጸዋል፡፡

የቀረውም በተያዘው ወር በዘር ለመሸፍን ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው የምርት ማሳደጊያ ግብአት በመጠቀም በበልግ እርሻው ከተዘራው ሰብል ውስጥ በቆሎ በሄክታር 40 ኩንታል ከድንች በሄክታር 261 ኩንታል ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ 

በዞኑ ገደብ ወረዳ የገደብ ጉበታ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ከበደ ደረሶ እንዳሉት የተሻሻሉ የግብርና ዘዴዎችን ከመጠቀማቸው በፊት በሄክታር የሚያመርቱት በቆሎ ከሰባት ኩንታል የማይበልጥ ነበር፡፡

አሁን ላይ የተሟላ የምርት ግብአት በመጠቀም በመስመር መዝራታቸውን አመልክተው በዚህም እስከ 40 ኩንታል የበቆሎ ምርት ይጠብቃሉ፡፡

በበልጉ ወቅት ያላቸውን ሶስት ሄክታር ላይ በማረስ ከዘሩት የበቆሎ ዘር ከቀድሞ የተሻለ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በወናጎ ወረዳ ቱማታ ጭረቻ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር አሰፋ ፈለቀ ናቸው፡፡

በጌዴኦ ዞን ባለፈው ዓመት የበልግ ወቅት ከለማው 8ሺህ 294 ሄክታር መሬት 722ሺህ 695 ኩንታል ምርት መገኘቱን ከዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡   

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ ግንቦት 12/2009 ለአረጋዊያን የሚደረገው ድጋፍ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ባሳተፈ መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

በከተማው ከ12 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባው የአረጋዊያን ማዕከል ዛሬ ተመርቋል።

ማእከሉን መርቀው የከፈቱት የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ እንደተናገሩት በስድስት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባው ማዕከሉ የበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ያረፈበት መሆኑ ከተማዋ የብዙዎች ማዕከል መሆኗን ማሳያ ነው ።

የከተማ አስተዳደሩም ለአረጋዊያን ማዕከሉ የሚያስፈልገውን ድጋፍ በቀጣይ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ሀዋሳ ከተማ ለሃገር ዋጋ የከፈሉ አረጋዊያን የሚታሰቡበት ማዕከል እንድትሆን በእውቀት በገንዘብና በጉልበት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

ግንባታውን ያስተባበረው የሜሪጆይ ልማት ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በበኩላቸው "ማዕከሉ በመላው ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ የተገነባ የህዝብ ሃብት ነው"ብለዋል።

በቀን 300 አረጋዊያንን የማስተገናገድ አቅም ያለው ማዕከሉ ጂምናዚየም፣ የእጅ ጥበብ ውጤቶች መስሪያ ፣ ማሳያና መሸጫ ሱቆች፣ ጊዜያዊ ማረፊያና ቤተ መጽሃፍትን ጨምሮ ከ13 በላይ አገልግሎቶች የሚሰጥበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በየዓመቱ ሃምሳ ለሚደርሱ አረጋዊያን በማዕከሉ የገቢ ማስገኛ ስራ እድል እንደሚፈጠር በመግለጽ በአቅም ማነስና በህመም ቤት ውስጥ ላሉ አረጋዊያን የቤት ለቤት ድጋፍና እንክብካቤ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

የደቡብ ክልል አረጋዊያን አንድነት ማህበር ፕሬዝዳንት ኮሎኔል አምደመስቀል መገርሳ የማእከሉ ግንባታ በዓላማ ጥንካሬና በቁርጠኝነት የተጠናቀቀና የኢትዮጵያዊያን አንድነት የታዬበት መሆኑን ገልጸዋል።

የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን በመወከል በስነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኘው አርቲስት ችሮታው ከልካይ "በማዕከሉ ሁለገብ አገልግሎቱን በመስጠት በሙያቸው አገልግለው የእድሜ ባለጸጋ ለሆኑ አረጋዊያን ያለንን ክብር በተግባር ማሳዬት ይኖርብናል" ብሏል፡፡

በሥነ-ስርዓቱ ላይ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች፣የመገናኛ ብዙሃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም አረጋዊያን ተገኝተዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 12/2009 በግንባታ ላይ የሚገኙት የውሃ አቅርቦትና ፍሳሽ መሰረተ ልማቶች ሲጠናቀቁ የመዲናዋ ነዋሪዎች ደረጃውን የጠበቀ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የፍሳሽ ማስወገድ ስርዓት ተጠቃሚ ይሆናሉ።

የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በመዲናዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የመካኒሳ ቆጣሪና የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች፣ የኮዬ ፈጬ ያልተማከለ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያና የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቶችን ጎብኝቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አብዱልሃሚድ አብዱላሂ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ነዋሪዎች ደረጃውን የጠበቀ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገድ ስርዓት ተጠቃሚ ይሆናሉ።

የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎቹ ቆሻሻ ውሃን በማከምና በማጣራት በድጋሚ መጠቀም የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋአለም ባዬ በግንባታ ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ከተማዋ የተሻለ የመስመር ፍሳሽ የማንሳት አቅም እንደሚኖራት ገልፀዋል።

ፕሮጀክቶቹ በትልልቅ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የህብረተሰቡን የፍሳሽ ማንሳት ጥያቄ በማስተናገድ ተጣርቶ የሚወጣው ውሃም ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ይህም ለተለያዩ አገልግሎቶች ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን ንጹህ የመጠጥ ውሃ መቆጠብ የሚያስችል በመሆኑ በመዲናዋ የሚስተዋለውን የውሃ አቅርቦት ችግር እንደሚያቃልል አክለዋል። 

እንደ አቶ ተስፋአለም ገለፃ የፍሳሽ ውሃ ማጣሪያዎቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ የመዲናዋን 70 በመቶ ነዋሪ ሙሉ በሙሉ ከዘመናዊ የፍሳሽ መስመር ጋር በቀጥታ በማገናኘት በቦቴ የሚሰጠውን አገልግሎት ያስቀራል።

ግንባታው 80 በመቶ የደረሰው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያና የፍሳሽ መስመር በቀን 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ የማጣራት አቅም ሲኖረው  በ2010 ዓ.ም ይጠናቀቃል፤ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በጀትም ተመድቦለታል።

በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የሚከናወነው ያልተማከለ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች ግንባታም በቀን 27 ሺህ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም ይኖረዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ማስፈፀሚያ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በመንግሥት የተመደበ ሲሆን ግንባታው በ2009 ዓ.ም መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የተመደበለት የኮዬ ፈጬ ያልተማከለ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያም በቀን 33 ሺህ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም ያለው ሲሆን በመገንባት ላይ የሚገኙ ከ50 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የዘመናዊ የፍሳሽ መስመር ተጠቃሚ ያደርጋል።

በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመስመርም ሆነ በተሽከርካሪ የሚሰበሰበው 18 ሺህ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ በሰባት ማጣሪያ ጣቢያዎች እየተጣራና እየተወገደ እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ማህበራዊ

ባህርዳር ግንቦት 12/9/2009 በአማራ ክልል ያለው የባህል እሴት ተጠብቆ ለመጭው ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

 12ኛውን የአማራ ክልል የባህል ሙዚቃ ፌስቲቫል ምክንያት በማድረግም ዛሬ ባህርዳር ከተማ አውደ ጥናት ተካሒዷል።

 የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዋ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳሁን በአውደ ጥናቱ ላይ እንደገለጹት ክልሉ ያለውን ዕምቅ ባህልላዊ ሃብት በማልማትና በመንከባከብ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በየወረዳው የባህል ቡድን እንዲቋቋም እየተደረገ ነው።

 ቢሮው የባህል ቡድኖች ስልጠና እንዲያገኙ እያደረገ ሲሆን ያሉባቸውን የቁሳቁስና መሰል ችግሮችም በቀጣይ ለይቶ ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

 ባህልን የማልማት፤ የመከባከብና የማሳወቅ ዕድል እየተፈጠረ በመምጣቱም ባለድርሻ አካላት ለክልሉ የባህል ሙዚቃ ዕድገት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

  በቢሮው የቲያትር ባለሙያ አቶ አብቹ ኃይለማርያም "የአማራ ክልል የባህል ሙዚቃ ቡድኖች እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታዎች፤ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አማራጮች" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት እንዳለመከቱት የክልሉ የባህል ሙዚቃ ቡድን ከተቋቋመ 40 ዓመታትን አስቆጥሯል።

 "በተለይም ከ1983 ዓ.ም በፊት በተለያየ ጊዜ ተቋቁመው የነበሩት የጎንደር ፋሲለደስ፤ የጎጃም ግሽ አባይና የወሎ ላሊበላ የባህል ቡድኖች ለዘርፉ ዕድገት ጉልህ ድርሻ ነበራቸው" ብለዋል።

 ከ1985 እስከ 1999 ዓ.ም በቲያትርና በስነጽሁፍ ዘርፍ መነቃቃት የታየበት ወቅት ቢሆንም የክልሉ የባህል ሙዚቃ ቡድኖች እንቅስቃሴ ጎልቶ መውጣት እንዳልቻለ አስረድተዋል።

 "ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ የባህል ቡድኖች ከክልል ባለፈ በዞን፤ በወረዳና በከተማ አስተዳደሮች እንዲቋቋሙ መደረጉ የባህል ሙዚቃ ቡድኖች እየተበራከቱ እንዲመጡ አስችሏል"ብለዋል።

 ከአውደ ጥናቱ ከተሳታፊዎች መካከል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የመጡት አቶ ዮሐንስ መንግስቱ የክልሉ ቱባ ባህል ሳይበረዝ እንዲያድግ እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸዋል።

 ከክልሉ የተውጣጡ ከ300 በላይ የባህል ቡድን አባላትም ከግንቦት ዘጠኝ ጀምሮ በፌስቲቫሉ እየተሳተፉ እንደሚገኙም ታውቋል። 

  "ኪናጥበብ ለላቀ ህይወት" በሚል መሪ ቃል ላለፉት አራተ ቀናት ሲካሄድ የቆየው 12ኛው የአማራ ክልል የባህል ሙዚቃ ፌስቲቫልና ዝክረ ኪነ-ጥበብ ዝግጅትም በነገው ዕለት ይጠናቀቃል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 12/2009 በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ስነ ልክን ተግባራዊ ካለማድረግ እንደሚፈጠሩ የብሄራዊ ስነ ልክ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።    

 ኢንስትቲዩቱ በኢትዮጵያ ለዘጠነኛ ጊዜ የሚከበረውን የስነ ልክ ቀን "ልኬት ለትራንስፖርት" በሚል መሪ ሀሳብ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ አክብሯል።

 ስነ ልክ የተለያዩ ቁሶችን ይዘት፣ ግዝፈት፣ ኃይል፣ ግፊት፣ ሙቀትና የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን የመለካትና የማረጋገጥ ተግባር ነው።

 የኢንስቲትዩቱ የሳይንሳዊ ስነ ልክ ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው በትሩ እንደገለጹት፤ ባለፈው አመት በአገሪቷ በሌሊት ከተከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች መካከል 52 በመቶ የሚሆኑት ከስነ ልክ ውጪ በመሆናቸው ምክንያት የተፈጠሩ ናቸው።

 ይህም በ2008 ዓ.ም በትራፊክ አደጋ ሳቢያ ከተከሰቱ 4ሺ 350 የሞት አደጋዎች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚወስድ መሆኑን ነው  የሚያመለክተው።

 በትራንስፖርት የሚጓጓዝ ሰው ወይም ቁስ፣ አጓጓዡ ተሽከርካሪ እና መንገዶች ደረጃቸውን ስለመጠበቃቸው በልኬት ተመርምረው ቢያልፉ በየጊዜው የሚፈጠሩ የትራፊክ አደጋዎች ሊቀንሱ እንደሚችሉ ነው የተመለከተው።

 እንደ አቶ ግዛቸው ገለፃ፤ ይህ እንዲሆን የተሽከርካሪው የመጫን አቅም፣ አጠቃላይ ቁመናና የአካል መሳሪያዎች በዓለም አቀፍ መለኪያ መስፈርት ሊፈተሹና ሊረጋገጡ ይገባል።

 በተጨማሪም ተሽከርካሪዎቹ የሚንቀሳቀሱባቸው መንገዶች ጥራትን ለማስጠበቅ ከዲዛይን ጀምሮ እስከሚሰሩበት ቁስ ድረስ በተገቢው ልኬት መታየት ይኖርባቸዋል።

 “የተወሰኑ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች በትክክለኛው ስነ ልክ ያላለፉና የተገጣጠሙበት መንገድ በመሳሪያ ያልተፈተሸ በመሆኑ አደጋዎች ይከሰታሉ” ያሉት ዳይሬክተሩ አቶ ግዛቸው፤ ከተመረቱበት ፋብሪካ የተሰራላቸው መሪ ዱባይ ላይ የሚቀየርላቸውን ተሽከርካሪዎች ለአብነት ጠቅሰዋል።

 የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱ አባጊቤ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የአሁኑ ዘመን ባህላዊ ልኬቶችን የሚፈቅድ አይደለም። የሰውን ጤንነትና ደህንነት ለመጠበቅ ደረጃውን የጠበቀ ስነ ልክ በሁሉም ዘርፍ ሊኖር ይገባል።

 ብሄራዊ ስነ ልክ ኢንስቲትዩት በአሁን ወቅት በይዘት፣ በግዝፈት፣ በኃይል፣ በግፊት፣ በሙቀትና የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን የመለካትና የማረጋገጥ ዓለም አቀፋዊ እውቅና አግኝቶ እየሰራ ይገኛል።

 በኮንስትራክሽን፣ በጤና፣ በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ የአፈር፣ የብረት ጥንካሬ፣ የጤና ሁኔታ መለኪያ መሳሪያዎች ላይ ልኬት እያከናወነ ቢሆንም፤ አሁን ካለው የኢንዱስትሪ እድገትና ከሚፈጠሩ የጤና እክሎችና አደጋዎች አኳያ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ተገልጿል።

 ኢንስቲትዩቱ ከመንግስት ከሚያገኘው በጀት በተጨማሪ 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 12/2009 የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለመደገፍ የሁለት ሚሊዮን ብር ቶምቦላ ሎቶሪ ገዛ።

ለግድቡ ግንባታ ገቢ ለማሰባሰብ 'አንድ ቶምቦላ ሎተሪ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ' በሚል መርህ ከሚያዚያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ የቶምቦላ ትኬት በገበያ ላይ ውሏል።

የህዳሴው ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ከብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳደር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ቶምቦላ ሎተሪ ሽያጭ የተለያዩ ተቋማትና ሰራተኞች እየተሳተፉ መሆኑን ገልጿል።

በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የሁለት ሚሊዮን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾች የ30 ሺህ እንዲሁም አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ የ44 ሺህ 100 ብር የቶምቦላ ሎቶሪዎችን ገዝተዋል።

የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋከቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ሠራተኞችና የአመራር አባላትም የ10 ሺህ 625 ብር ሎቶሪ በመግዛት ለፅህፈት ቤቱ ገቢ አድርገዋል።

በተመሳሳይ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ባለአደራ ቦርድ ሰራተኞቹ እንዲገዙ በማድረግ 3 ሺህ 325 ብር ለጽህፈት ቤቱ አስረክቧል።

በእለቱ የአዲስ ትውልድ ፓርቲ የአንድ ሺህ ብር የቶምቦላ ሎተሪ ገዝቷል።

የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ደነቀ "ከገዥው ፓርቲ ጋር በፖሊሲ ብንለያይም የህዳሴው ግድብ ግንባታ የመላው ኢትዮጵያውያንና የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች በመሆኑ እኛም የራሳችንን ድርሻ ለመወጣት ድጋፍ እናደርጋለን" ብለዋል።

ፓርቲው በአገራዊ ልማት ድርሻውን ለመወጣት በጋራ እንደሚሰራና በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለጹት።

የቶምቦላ ሎቶሪ ግዥው ለሌሎች ተቋማት መነሳሳት የሚፈጥር መሆኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታገል ቀኑብህ ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ እያደረገ ያለው ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው የቶምቦላ ሎቶሪው ሽያጭ ግንቦት 30 ቀን 2009 ዓ.ም ከመጠናቀቁ በፊት ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

የተለያዩ ድርጅቶች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግልና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሎቶሪውን በመግዛትና ለሠራተኞቻቸው በመሸጥ እያደረጉት ያለው ድጋፍ አበረታች መሆኑንም ገልፀዋል።

የገቢ ማሰባሰቢያ ቶምቦላ ሎቶሪ ዕጣ ግንቦት 30 ቀን 2009 ዓ.ም በብሄራዊ ሎቶሪ አስተዳደር አዳራሽ ይወጣል።

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር ግንቦት 12/2009 በኃይማኖት ሽፋን የሚከናወኑ የአክራሪነትና የሽብር እንቅስቃሴዎችን መንግስት ማህበረሰቡን በማሳተፍ ጠንክሮ መከላከል መቻሉን የፌዴራል አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የፌዴራሊዝም አስተምህሮና ስርፀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛህኝ ጥላሁን በባህር ዳር ከተማ በተሰጠው የሰላም እሴት ግንባታ ስልጠና ላይ እንደገለፁት የአክራሪ ሃይሉን ሃገሪቱን የማተራመስ ዓላማ ማክሸፍ ተችሏል።

ከአራት ዓመታት በፊት ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ይታይ የነበረው የአክራሪዎች እንቅስቃሴ ከፍተኛ አንደነበር አስታውሰው ፤ በተጠና መንገድ መንግስትና ህዝቡ በጋራ ባደረጉት እንቅስቃሴም ስጋቱ መወገዱን አስረድተዋል።

"የየሃይማኖቱ መሪዎች እውነተኛና ትክክለኛ ሃይማኖታዊ አስተምህሮን በመስበክ ሰላምን የሚያስፍኑ የጋራ እሴቶችን የመገንባት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካይ አቶ መሱድ አደም ናቸው።

ሃይማኖቶች አብሮነትን፣ መቻቻልን፣ ሰላምን፣ መፈቃቀርን፣ መተጋገዝን እንዲያጠናክሩና በህዝቡ ዘንድ ለዘመናት የዘለቁ የጋራ እሴቶች የበለጠ ጎልብተውና ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚፈፀሙ አክራሪነትንና ሽብርተኝነትን ለመከላከል ህዝቡ ትክክለኛውን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ አንዲያውቅ በማድረግ ችግሩን በራሱ እንዲከላከል እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

"ሰላም የሁሉም የጋራ አቋም ነው"ያሉት አቶ መሱድ በተለይም ወጣቶችና ሴቶች በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ አብሮነታችንን የሚሸረሽሩና የማይጠቅሙ መልዕክቶችን ባለመቀበል የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ አንደሚገባ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ተወካይ አቶ የማነ ታደሰ በበኩላቸው የፌደራል ስርዓቱ የሁሉንም ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የመልማትና የማደግ መብት በእኩል ያረጋገጠ ነው።

"የልማትና የሰላም ጉዳይ የቀጣይ የወጣቶችንና የሴቶችን እጣ ፈንታ የሚወስን በመሆኑ በሁሉም ተግባራት ግንባር ቀደም ሊሆኑ ይገባል" ያሉት ደግሞ የስልጠናው ተሳታፊ ወይዘሮ አስረስ ተረፈ ናቸው።

በስልጠናውም ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የፀጥታ አካላት ፣ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል።

Published in ፖለቲካ

 አዲስ አበባ ግንቦት 12/2009 የአገሪቷን ታሪክ ፣ባህል፣ ወግና ትውፊቶች ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ለዘላቂ ሠላምና አገራዊ ልማት የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተገለፀ።

 ስምንተኛው ከተማ አቀፍ የባህል ፌስቲቫል ''የባህል ልማት ለዘላቂ ሠላምና አንድነት'' በሚል መሪ ሃሳብ በኤግዚቢሽን ማዕከል ተጀምሯል።

 የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ረመዳን አሸናፊ "የአገሪቷ ዘመን ተሻጋሪ ባህል፣ ታሪክ፣ ወግና ትውፊቶች ሳይበረዙ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ለዘላቂ ሠላምና ልማት ያለው ፋይዳ የላቀ ነው'' ብለዋል።

 የባህል ሀብቶች እንደ ተፈጥሯዊ መስህቦች ሁሉ ለቱሪዝም ኢኮኖሚው እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ በመሆናቸው ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

 በመሆኑም የአገሪቷ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶቻቸውን የልማት ቁልፍ መሳሪያ የማድረጉን ተግባር ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

 የባህል ፌስቲቫሉ ባለፉት ሁለት ወራት በየወረዳዎች በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱን የአዲስ አበባ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረጻዲቅ ሀጎስ ተናግረዋል።

 ዓላማውም ጎጂ መጤ ባህሎችና የባህል ወረራን በመከላከል ነባርና ጠቃሚ ባህሎችን ማስተዋወቅ ነው።

 በዘንድሮው ፌስቲቫል የሱዳን የባህል ልዑክ ተሳታፊ መሆኑን የገለጹት አቶ ሀጎስ፤ በጎረቤት አገራት ወንድማማች ህዝቦች መካከል የባህል ልውውጥ ለማድረግ መልካም አጋጣሚ መሆኑን አውስተዋል።

 ለሶስት ቀናት በሚቆየው ፌስቲቫል የብሔር ብሔረሰቦችን ባህላዊ አልባሳትና አመጋገብ የሚያሳይ ዓውደ ርዕይ፣ የኪነ-ጥበብ ውድድሮች፣ የተሰጥኦ ትርኢቶችና ጥናታዊ ፅሁፎች ይቀርባሉ።

 ጥናታዊ ፅሁፎቹ "የአሉታዊ መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተፅዕኖና የመከላከል ስትራቴጂ" እንዲሁም "የባህል ልማት ለዘላቂ ሠላምና አንድነት" በሚል ርዕስ ነው የተዘጋጁት።

   ፌስቲቫሉን የአዲስ አበባ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮና የኢትዮጵያ ባህል ማዕከል በጋራ አዘጋጅተውታል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን