አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 02 May 2017

አዲስ አበባ ሚያዝያ 24/የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ረቂቅ አዋጆችን አፀደቀ፤ አንድ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ።

በኢትዮጵያና ቻይና መንግስታት መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳይ ግለሰቦችን አሳልፎ የመስጠትና በፍትሃብሄርና በንግድ ጉዳዮች ላይ የተደረጉ የትብብር ስምምነቶችን በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።

የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት እንደገለፁት በወንጀል ጉዳይ ግለሰቦችን አሳልፎ ለመስጠት የተደረገው ስምምነት በአገራቱ ሠላም፣ ፀጥታና መረጋጋትን ለማረጋጋጥ አስተዋፅኦ አለው።

አገሪቷ የጀመረችውን የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አጠናክራ ለማስቀጠል የሕግ የበላይነት መከበር ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑና ወንጀል ፈፅመው ከአገር የሚሸሹ ሰዎችን ለፍርድ ለማቅረብም ያስችላል።

የፍትሃብሄርና የንግድ ጉዳዮች ስምምነቱም በአገራቱ መካካል እያደገ በመጣው የንግድና የፍትሃብሔር ግንኙነት አለመግባባቶች ቢፈጠሩ በቀላሉ መፍታት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በአገራቱ መካከል ያሉ ተዋዋይ ወገኖች በውላቸው መሰረት ባይፈፅሙና ክርክር ቢነሳ መረጃዎች እንደ አስፈላጊነቱ ከሁለቱም አገራት በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑም ያደርጋል።

የፍርድ ሂደትን ለማፋጠን በተጨማሪም የሚሸሹና የሚደበቁ የአገርና የግለሰብ ንብረቶችን ለማስጠበቅ ታስቦ የተደረገ ስምምነት መሆኑንም አቶ ጴጥሮስ አክለዋል።

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወስን የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ መርምሮ ረቂቅ አዋጅ 26/2009 በማድረግ ለሕግ፣ ፍትህና አስተዳደርና ለንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አማኑኤል አብርሃ ረቂቅ አዋጁ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የነበረውን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ተጠሪነት ለንግድ ሚኒስቴር እንዲሆን ያደርገዋል ሲሉ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ባለስልጣኑ አግባብነት ካላቸው የዘርፉ መስሪያ ቤቶች ጋር ለመቀናጀት ምቹ ያለመሆኑን በመገንዘብ ተጠሪነቱ ለንግድ ሚኒስቴር እንዲሆን የማሻሻያ አዋጁ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 24/2009 በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መሳካት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ቀጥለዋል።

በሲዊዲን፣ በኖርዌይ፣ በፊንላንድ፣ በአውስትራሊያና በፈረንሳይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት ስድስተኛ ዓመት ክብረ በዓል "ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የአገራችን ህብረ ዜማ የህዳሴያችን ማማ" በሚል መሪ ሀሳብ  አክብረዋል።

በዓሉን ባከበሩበት ወቅት በኖርዌይ ኦስሎና ፊንላንድ ሄልሲንክ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተከናወነ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ የሚውል ከሰላሳ ስድስት ሺ ዶላር  በላይ መገኘቱ ነው የተገለጸው።

በተመሳሳይ በአውስትራሊያ በሜልበርንና በካራቤራ ከተማ በተካሄዱ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች ደግሞ አስራ አምስት ሺ ዶላር የቦንድ ሽያጭ ተከናውኗል።

በኖርዲክ አገሮች ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ፤ "የህዳሴ ግድቡ ታላቅ አገራዊ ተስፋን ያነገበና መጪው ትውልድም የሚኮራበትና የሚመካበት ነው" ብለዋል።

"የአገሪቷ ልማትና ዕድገት እውን የሚሆንበትና አገሪቷ የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ በተግባር የሚረጋገጥበት ፕሮጀክት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በአውስትራሊያ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ትርፉ ኪዳነማርያም እንደገለጹት፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ በአገሪቷ እየተሰሩ ለሚገኙ ፕሮጀክቶች የሃይል ፍላጎት ከማማላቱም ባሻገር የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት ትልቅ ሚና የሚጫወት ነው።

ለዚህ ታላቅ ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቦንድ በመግዛት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በተመሳሳይ በፓሪስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተከናወነው ስነ ስረዓት ላይም ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል።

በፈረንሳይ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ነጋ ጸጋዬ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በፈረንሳይና በስፔን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቦንድ በመግዛትና ስጦታ በማበርከት ተረባርበዋል።

በዚሁም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በእለቱ ከቦንድ ሽያጭና ከስጦታ 10 ሺ ዩሮ ለማሰባሰብ ተችሏል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙ ተሳታፊዎችም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት በላከልን የፕሬስ መግለጫ አስታውቋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 24/2009 የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የሠብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዘይድ ራድ አል ሁሴን ከአገር አቀፍ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያዩ።

ኢትዮጵያን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት ኮሚሽነሩ ከ11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተወያዩት በሠብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ የሠብዓዊ መብት ጉዳዮች ጉድለቶች መኖራቸውን ገልጸውላቸዋል።

የአገሪቷ ህገ-መንግስት ለሠብዓዊ መብት ትልቅ ሥፍራ መስጠቱን ጠቅሰው አተገባበር ላይ የሚታዩ ጉድለቶች የሠብዓዊ መብት ጥሰት እያስከተሉ መሆኑን ተናግረዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያን ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን አቅምና ገለልተኝነት ለማጎልበት ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ገዥው ፓርቲ በአሁኑ ወቅት ችግሮችን በመቀራረብ ለመፍታት ፍቃደኛ ሆኖ የድርድር ሂደት መጀመሩን በጎ ጅምር ሲሉ ገልፀውታል።

ህገ-መንግስቱ ለዜጎች የሰጠው ሙሉ የሠብዓዊ መብት ዋስትና በገዥው ፓርቲ የተጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው ሆኖም የአገሪቷ ዴሞክራሲ ታዳጊ በመሆኑ የአፈፃፀም ክፍቶች መኖራቸውን አብራርተዋል።

ችግሮችን ለመፍታት ከችግሩ እየተማረና በሂደት እያስተካከለ የዳበረ ዴሞክራሲ ለመገንባት እየሰራ መሆኑንም ለኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽነር ዘይድ ራድ በበኩላቸው የሚስተዋሉት ችግሮች የሚፈቱት በኢትዮጵያውያን መሆኑን ገልፀው ከፓርቲዎቹ የቀረቡላቸውን ጥያቄዎችና አስተያየታቸውን አስመልክተው በጉብኝታቸው ማጠቃለያ መግለጫ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

በውይይቱ ሰማያዊ ፓርቲ፣ ኢዴፓ፣ አንድነት፣ ቅንጅት፣ መኢአድ፣ አትፓ፣ ኢዴህ፣ ኢፍዴኃግ፣ መኦህዴፓ፣ ኢራፓ እና ገዥው ፓርቲ ተሳትፈዋል።

Published in ፖለቲካ

አዳማ ሚያዝያ 24/2009 በኮንስትራክሽን ኢንቨስትመንት ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በመከላከል በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ  እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ልዩ ድጋፍ ከሚሹ ክልሎች ለተውጣጡ የኮንስትራክሽን ዘርፍ አመራሮችና የምህንድስና ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ ያዘጋጀው ተግባር ተኮር  ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል።

የኢንስቲትዩቱ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አርጋው አሻ በተለይ ለኢዜአ እንዳስታወቁት መንግስት ለአገሪቱ ከሚመድበው አጠቃላይ በጀት ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት የሚውል ነው።

"ይህን ሰፊ ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ከአፈፃፀምና ከጊዜ አንፃር ለላቀ ውጤት ለማብቃት ዘርፉን በአቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ስራዎች ለማገዝ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ዘርፉን በአቅም ግንባታ ለመደገፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት ከ5 ሺህ ለሚበልጡ የስራ ተቋራጮች፣ ባለሞያዎች፣ አማካሪዎችና አስፈጻሚዎች ስልጠና መሰጠቱን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በጥናትና ምርምር ረገድም በአገር ውሰጥና በውጭ አገር ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ወደ መሬት ሊወርዱ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን የመለየት፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን የመቀመርና የመተግበር ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡

እስካሁንም 12 ጥናቶች ተመርጠው ምርምር እየተካሄደባቸው መሆኑንም አመልክተዋል።

ዶክተር አርጋው እንዳሉት በኮንስትራክሽን ዘርፉ ወጥ የሆነ አሰራር ለማስፈንም 14 ዓይነት የአሰራር ስርዓት በማንዋል ደረጃ እየተዘጋጀ ነው።

"በዘርፉ ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ለማስወገድ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል" ያሉት ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተሩ በተለይ ከጨረታ ጋር ተያይዞ የሚታየውን የተዘበራረቀና  የተጋነነ ዋጋ ስርአት ለማስያዝ የስነ -ምግባር ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

በኮንስትራክሽን ዘርፉ እያጋጠመ ያለውን የሞትና የአካል ጉዳት ችግር ለመፍታት የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አወል መገሪስ በበኩላቸው "የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ክፍተቶችን ለመሙላት ለዘርፉ ተዋንያን እየተሰጠ ያለው ተግባር ተኮር ስልጠና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል።

በተለይ በዘርፉ በርካታ የማስፈጸም ውስንነት ያለባቸው ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ክልሎች የሚደረገው ድጋፍ አንድ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት ልዩ ትርጉም እንዳለው አስታውቀዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ አዳነች ጋይናሞ በበኩላቸው በኮንስትራክሽን ዘርፍ በአፈጻፀም ሂደት የሚስተዋሉ የጥራት መጓደል፣ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ወጪና ጊዜ ያለመጠናቀቅ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

መንግስት ችግሮቹን ለመፍታት ትኩረት መሰጠቱን የገለፁት ወይዘሮ አዳነች ዘርፉን የሚመራና የሚከታተል ተቋም ማቋቋሙን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ለቀጣዮቹ አምስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ላይ ከጋምቤላ፣ ከቤንሻንጉል፣ ከአፋር፣ ከሶማሌና ከሀረሪ ክልሎች የተውጣጡ ባለድረሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 24/2009 ትምህርት ሚኒስቴር በተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት ስልጠናና ፕሮግራም የሚስተዋሉ ክፍተቶችን እንዲያስተካክል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የሰው ሃብትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የ2009 ዓ.ም በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጻም ሪፖርት አድምጧል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሻምበል ነጋሳ እንደገለፁት ፕሮግራሙ ቅንጅታዊ የአመራር ጉድለትና የቁጥር መረጃዎች ጥራት ጉድለት ይታይበታል።

በአደረጃጀቱና በፕሮግራሙ ላይ ባለው የአመለካከት ችግር በአንዳንድ ጣቢያዎች ከልማዳዊ የማንበብ፣ የመፃፍና የማስላት ትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ወጥቶ የጎልማሶችን ክህሎት ሊያሳድግ የሚችል የተቀናጀ ተግባር ተኮር ትምህርት መሆን አልቻለም።

ስለሆነም ሚኒስቴሩ በተቀናጀ የተግባር ተኮር ትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሙ የሚታዩትን ችግሮች ለመቅረፍ በትኩረት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተሳትፎ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ተደራሽነት፣ የበጀት አጠቃቀም፣ በቴክኒክና ሙያ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽንና ቴክኖሎጂም የሚኒስቴሩን ትኩረት የሚሹ ተብለዋል።

በዩኒቨርሲቲ ሴቶችን ወደ አመራርነት የማምጣት፣ የመምህርነትና ተመራማሪነት ተሳትፏቸውን የማሳደግና ሴት ተማሪዎች በትምህርት እንዲዘልቁ ማድረግ ላይም ውስንነቶች ታይተውበታል ሚኒስቴሩ።

የመንግስትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነትን ከማስጠበቅና ለትምህርት ጥራት ወሳኝ የሆኑ ግብዓቶችን ከሟሟላት አኳያም የበለጠ መስራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት አቶ ሻምበል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሺፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው ከምክር ቤቱ የተሰጡ አስተያየቶችና ግብረ መልሱ ገንቢና በግብዓትነት የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።

የጎልማሶችን ትምህርት በተቀናጀ መንገድ አለመምራት፣ የምልመላ፣ ስልጠናና ስምሪት ችግር፣ ፕሮግራሙ ከጎልማሶች የኑሮ ክህሎት ጋር ተቀናጅቶ ያለመሰጠቱና ስራውን የትምህርት ዘርፍ ብቻ አድርጎ ማየት ከሚታዩ ችግሮች መካከል ጠቅሰዋል።

ፕሮግራሙን ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ የተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርትና ስልጠና ቦርድ ሚናውን እንዲወጣ የማስተካከያ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት እንዲቻል ትምህርት ቤቶችን የትራንስፎርሜሽን ማዕከል ማድረግ የሚያስችል ፓኬጅ ተቀርፆ ወደ ተግባር ለመግባት ለክልሎች ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ በብዛት ከአምስተኛ ክፍል በላይ እንደሚስተዋልም ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

ችግሩን ለማስወገድ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽነት ማስፋት፣ ለሴቶችና ህጻናት ምቹ የትምህርት አካባቢ መፍጠር፣ መምህራንን ሟሟላትና በትምህርት ቤት ምገባ ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የዘንድሮ የ12ኛ እና የ10 ክፍሎች ብሔራዊ ፈተና ከህትመት እስከ ስርጭት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተሟላ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

Published in ማህበራዊ

ሰመራ ሚያዝያ 24/2009 የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና የዘላቂ ልማት ግቦችን የበለጠ ስኬታማ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በ2008 የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅድና የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም ላይ የሚወያይ የሁለት ቀናት  መድረክ ዛሬ በሰመራ ከተማ ተጀምሯል፡፡

በኮሚሽኑ የአምራች ዘርፍ ዳሬክተር ዶክተር ተፈሪ መኳንንቴ በውይይቱ ላይ እንደገለፁት የሃገሪቱን ዘላቂ የልማት ግቦችን በማካተት ተዘጋጅቶ በትግበራ ላይ የሚገኘዉ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅድ ልማትን በማፍጠን የዜጎችን ተጠቃሚነት የበለጠ ለማረጋገጥ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡

በተለይም ባለፈው ዓመት ተከስቶ የነበረውን የድርቅ ተጽእኖ በመቋቋም የተመዘገበው የ8 በመቶ እድገት ሃገሪቱ የአየር ንብርት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያላትን አቅም ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አመታት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተካሄደው  የተፋሰስ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ስራ የተገኘው ውጤት አስተዋፆ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

እድገቱ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት እንዲያስመዘግቡ ከሚጠበቀው የ7 በመቶ አመታዊ እድገት አንጸር የተሻለ ቢሆንም በ2008 ከተቀመጠው አገራዊ የእድገት ምጣኔ አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑን አስታውቀዋል፡ 

በቃጣዮቹ አመታት በአቅድ አፈጻጸም ላይ ስኬታማ ውጤት ለማስመዝገብ ከፌዴራል እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን የሚገኙ አስፈጻሚ አካላት በመናበብ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

እንዲሁም ''በልማቱ ላይ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ እንደ አንድ ቁልፍ ተግባር ተደርጎ መያዝ ይኖርበታል'' ብለዋል፡፡

የእንስሳትና አሳ ሃብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ገብረ እግዚያብሄር ገብረ ዩሃንስ በበኩላቸው መድረኩ ባለፈው አመት በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም በቀጣይ ክፍተቶችን አርሞ የተሸለ ሃገራዊ ስኬት ለማስመዝገብ የጋራ መግባባት ለመፍጠር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአፋር ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ  ኃላፊ አቶ ኡስማን መቅቡል እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የልማት ስራዎች የክልሉን አርበቶ አደር ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ።

"ከእድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅዱ ጋር  ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙትን የድህነት ቅነሳ መርሀ ግብሮች  የአርብቶ አደሩን የልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል የጎላ ፋይዳ አላቸው " ብለዋል ።

ለእቅዶቹ ስኬት በየደረጃው የሚገኘው አመራር ፣ ህብረተሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በውይይቱ ላይ  የክልሉ የቢሮ ሀላፊዎች፣ የወረዳ አመራሮች ጨምሮ ከተለያዩ የሕዝብ አደረጃጀቶች የተውጣጡ ከ100 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል ።

ተሳታፊቹ በሁለት ቀን ቆይታቸው በ2008 በጀት አመት በአገር አቀፉ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅድና የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም ላይ ይወያያሉ፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ሶዶ ሚያዝያ 24/2009 በወላይታ ዞን በየደረጃ የተካሄደውን የጥልቅ ተሀድሶ ተከትሎ የተመዘበረውን የህዝብና የመንግስት ሀብት የማስመለስና ከኪራይ ሰብሳቢነት ያልፀዱ አመራሮች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለፀ።

ከሚያዝያ 17 ቀን 2009 አ.ም ጀምሮ በዞኑ በሁለት ከተማ አስተዳደርና በ13 ወረዳዎች በመንግስት መስሪያ ቤቶችና  አደረጃጀቶች ከተሀድሶ በኋላ በመጡ ለውጦችና ተግዳሮቶች ዙሪያ እየተካሄደ ያለው ግምገማ እንደቀጠለ ነው ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስራት ጤራ  ለኢዜአ እንደገለፁት በጥልቅ ተሀድሶ መድረኮች የተነሱ የህዝብ ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ ኪራይ ሰብሳቢነትን የመታገልና መልካም አስተዳደርን የማስፈን ጥረቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል ።

ግምገማውን መሰረት በማድረግ እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች በሁለት የከተማ አስተዳደሮችና በ13 ወረዳዎች ሊፈፀሙ የነበሩ 62 ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውሮች እንዲቀሩ መደረጉን ጠቅሰዋል ።

በድርጊቱ ተሳታፊ ሆነው የተገኙ 55 አመራሮች ላይ ድርጅታዊ እርምጃ ተወስዶ ጉዳያቸው ለህግ መቅረቡን ተናግረዋል ።

“ሌሎች 31 አመራሮች ላይ ደግሞ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል” ብለዋል ።

በገጠርና በከተማ ከተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በግለሰቦች ከተመዘበረ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የመንግስት ገንዘብ ውስጥ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር  እንዲመለስ ተደርጎ ቀሪው በህግ አግባብ እንዲያዝ መደረጉን ተናግረዋል።

እንዲሁም በህገ-ወጥ ወረራ ተይዞ የነበረ ከአራት ሺህ  ሄክታር በላይ የገጠርና  ከ17 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬት  እንዲመለስ መደረጉንም ጠቅሰዋል ።

በሌላ በኩል በዞኑ በሚገኙ መስሪያ ቤቶችና አደረጃጀቶች በአገልግሎት አሰጣጥና በአመለካከት የተሻለ ለውጥ እየታየ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ውጤት አያመጣ አይደለም” ብለዋል ።

የዞኑ ደኢህዴን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘብዴዎስ ኤካ በበኩላቸው በቀጣይ በየደረጃው ከሚገኙ አደረጃጀቶችና  ከህብረተሰቡ ጋር የሚደረጉ ውይይቶችን በማስቀጠል ኪራይ ሰብሳቢነትነ በመታገል የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የመመለስ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡ 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 24/2009 የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬ መደበኛ ስብሰባው በሁለት ረቂቅ አዋጆችና አንድ ስትራቴጂ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።

ምክር ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው የዓለም አቀፍ ስምምነቶች መዋያያና ማፅደቂያ ሥነ-ስርዓትና የባቡር ትራንስፖርት አስተዳደር ረቂቅ አዋጆች እንዲሁም የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ረቂቅ ስትራቴጂ ላይ ነው።

ምክር ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳለው የባቡር ትራንስፖርት ተስፋፍቶ የአገሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚደግፍ አማራጭ የትራንስፖርት ንዑስ ዘርፍ እንዲሆን የሚያደርግ ምቹ ሁኔታን መፍጠር አስፈልጓል።

የባቡር መሰረተ ልማቶች የሚገነቡበትና አገልግሎት ላይ የሚውሉበት አገር አቀፍ ደረጃ የሚወሰንበትን ሥርዓት መዘርጋትም እንዲሁ።

በአገሪቱ ውስጥ ወደ ሥራ የሚሰማሩ ባቡሮች ዓይነትና መጠንን የሚወስን ህግ ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ በመታመኑ የባቡር አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበትና ማሻሻያዎች ታክለውበት ይፀድቅ ዘንድ ተወስኗል።

የገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ ስትራቴጂ ከአገሪቷ አጠቃላይ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ጋር ተጣጥሞና የገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ ዕይታዎች፣ አቅጣጫዎች፣ ዓላማዎች፣ ስልቶችና አማራጮች ጋር በማስተሳሰር ተዘጋጅቷል።

የስትራቴጂው ዓበይት ዓላማም በገጠር የሥራ ዕድልን ለማስፋፋት እንዲሁም ሥራ ፈላጊ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆን ለማስቻል የሚደረጉ ጥረቶችን ማጎልበት ነው።

ምክር ቤቱም በቀረበው ስትራቴጂ ላይ ከተወያየ በኋላ ማሻሻያዎችን በማከል ተቀብሎ ሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

በተመሳሳይ መንግሥት ከተለያዩ አገራት ጋር ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የሚፈጽም በመሆኑ፤ ስምምነቱን የመደራደር፣ የመዋዋል፣ የማፅደቅና ቀሪ የማድረግ ሥነ-ሥርዓትን ከህገ መንግስቱና ከሌሎች ተዛማጅ ህጎች ጋር ማጣጣም አስፈልጓል።

በመሆኑም ምክር ቤቱ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መዋዋያና መፅደቂያ ሥነ-ስርዓት ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ማሻሻያዎችን በማድረግ ተቀብሎ እንዲፀድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል። 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 24/2009 የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለሚያከናውኑት ኢንቨስትመንት መጎልበት አገራቱ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ደርሰዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የጀርመኑን ምክትል መራሄ መንግስትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲግማር ጋብርኤል በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ እንደገለጹት አገራቱ በልማት ትብብር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ጠንካራ ግንኙነት አላቸው።

የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ በተሻለ መልኩ እንዲቀጥል የአገራቱ መንግስታት መደገፍ በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ሰፊ የሀሳብ ልውውጥ ተደርጓል።

በተለይም በማምረቻው ዘርፍ የተሰማሩ የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እንዲሰሩ አገራቱ በጋራ በሚከውኗቸው ተግባራት ዙሪያ ተነጋግረዋል ነው ያሉት አምባሳደሩ።

የጀርመኑ ምክትል መራሄ መንግስትና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በሶማሊያ ጉብኝት አድርገው መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጋር በሶማሊያ የተገኘውን ሠላምና መረጋጋት በማስቀጠል፣ በመልሶ ግንባታ ስራዎችና በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር መስራት ስለሚቻልባቸው ጉዳዮች መክረዋል።

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በሌሎች አህጉራዊ ጉዳዮች በተለይም በደቡብ ሱዳን ሠላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በጋራ ለመስራትም ተነጋግረዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲሳ አበባ ሚያዝያ 24/2009 ጀርመን ከአፍሪካ ጋር በሰላምና ደህንነት ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል የጀርመን ምክትል መራሄ መንግስት እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሲግማር ጋብርኤል ገለፁ።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሲግማር ጋብርኤል ከአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ  መሃመት ጋር በአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚሁ ወቅት ጀርመን ከአፍሪካ ጋር በሰላምና ደህንነት ላይ ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው የገለጹት።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋብርኤል እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት በሶማሊያና እና በሌሎች አፍሪካ አገሮች በድርቅ ምክንያት የተከሰተው ረሃብ ጉዳት ሳያስከትል ለመከላከል ድጋፍ ለማድረግ ለሰላምና ደህንነት ቅድሚያ መሰጠት አለበት።

የስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ የአገሮቹን ሰላም ከማረጋጋት በተጨማሪ "ለአፍሪካውያን ወጣቶች ብዙ የሥራ እድሎች መፍጠር ያስፈልጋል" ብለዋል።

ከሰላምና ደህንነት ጉዳዮች በተጓዳኝ "ዘመናዊ እና በኢንዱስትሪ የበለጸገች አፍሪካን ለማየት ቁርጠኛ መሆናችንን በውይይታችን ወቅት አንስተናል" ብለዋል።

ጀርመንም ሆነች አውሮፓ ህብረት በቅርብ ጊዜ ውስጥ የበለጸገች አፍሪካን የማየት ምኞት እንዳላቸው ነው የገለጹት።

"ጀርመን ጠንካራ የአፍሪካ ህብረት የማየት ፍላጎት አላት" ሲሉ ነው የገለጹት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ።

የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ አፍሪካ ህብረት ከጀርመን ጋር ሰላምና ደህንነትን አስመልከቶ ጠንካራ ግንኙነት አለው።

እንደ ሕገወጥ ስደትና ድርቅ የመሳሰሉ ቀውሶችን  ለመግታትም አፍሪካ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ጀርመን እጅ ለእጅ ተያይዘው መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያስገነዘቡት።

ጀርመን በህብረቱ ዋና መስሪያ ቤት የጁሌስ ኔሬሬ ሰላምና ደህንነት ቢሮ በ31 ሚሊዮን ዮሮ  እንዲገነባ ድጋፍ ማድረጓን አውስተው፤ ይህም የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ጠንካራ መሠረት እንዲኖረው እንዳደረገ ገልፀዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት አፍሪካ ህብረት ከጀርመን ጋር ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንኳን ህብረቱ ከጀርመን የሚያገኘው ዓመታዊ ድጋፍ ወደ 74 ሚሊዮን ዩሮ መድረሱን ነው የሚያመለክቱት።

ጀርመን የምትሰጠው ድጋፍ በህብረቱ ለሰላምና ደህንነት፣ ለእርሻ፣ ለትምህርት፣ ለመሰረተ ልማትና ለመልካም አስተዳደር ዲፓርትመንቶች እንደሚውል ነው የሚገለጸው።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን