አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Friday, 19 May 2017

አክሱም ግንቦት 11/2009 የቅዱስ ያሬድ ስራዎች ለሀገሪቱ  የቱሪዝም ልማት  እንዲውል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ  ተመለከተ፡፡

በአክሱም ከተማ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ በቆየው አውደ ጥናት "የቅዱስ ያሬድ ሰራዎች"  በማስመልከት የአዲስ አባባ፣የመቀሌና የአክሱም ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች አቅርበዋል።

" ቅዱስ ያሬድ ለቱሪዝም ልማት ያበረከተው አስተዋጽኦ" በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተማራማሪ ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሃ እንዳሉት፣የቅዱስ ያሬድ ስራዎች ለኢትዮጵያዊያን የፅናት፣የትዕግስትና የአዋቂነት ተምሳሌት ናቸው።

የቅዱስ ያሬድ መጽሐፍት፣የማህሌት ዜማ ፣የዜማ መሳሪያዎችና ትምህርት የሰጠባቸው ስፍራዎች ለቱሪዝም ልማት እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው ውድ ቅርሶች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

እነዚህን ቅርሶች ይበልጥ ለቱሪዝም መስህብነት እንዲውሉና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉመው በሰነድ መያዝ ይገባል፡፡ 

ከፍልስፍናዎቹ  የዓላማ ጽናትን፣ከውድቀት መነሳትን፣ ማደግና ምኞት ማሳካት መቻልን በተግባር መማር  እንደሚቻል ያመለከቱት ዶክተር ሙሉጌታ " ስራዎቹና ቅርሶችንም አጣምሮ የሚይዝ ዘመናዊ ሙዚየም  መገንባት ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተወካይ አቶ አለማየሁ ጌታቸው በበኩላቸው፣ ቅዱስ ያሬድና ስራዎቹን ለማስተዋወቅ የተጀመረው ጥረት ከግብ ለማድረስ ትኩረት እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡

" የቅዱስ ያሬድ ያስተማረባቸው ስፍራዎች፣የዜማ ስልቶችና የዜማ መሳሪያዎች መሰባሰብ  ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰፊ ስራ ይጠበቃል"  ያሉት አቶ አለማየሁ ስራዎቹ እንዲጠበቁና  ዘመናዊ ሙዚየም እንዲገነባ  መስሪያ ቤታቸው  አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ይህንን አኩሪ ታሪክና ስራዎች  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማስተዋወቅ ለቱሪዝም ልማት እንዲውሉ መስራት እንዳለባቸው ያመለከቱት ደግሞ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቅዱስ ያሬድ፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ስነ ጽሑፍና ብራና ጥናቶች ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ሐጎስ አብርሃ ናቸው።

"የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቅዱስ ያሬድ ጽሑፎችን በመሰብሰብና ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በመተርጎምና በሰነድ በመያዝ ጥቅም ላይ እንዲውል እየሰራ ነው" ብለዋል፡፡

የቅዱስ ያሬድ ስራዎችና የግእዝ ቋንቋን ለሀገሪቱ  የቱሪዝም ልማት  ጥቅም ላይ እንዲውሉ መነቃቃት ለመፍጠር በአክሱም ከተማ የተዘጋጀው አውደ ጥናት ዛሬ የተጠናቀቀ ሲሆን ምሁራን፣ ተዋቂ  አርቲስቶች፣የሃይማኖት አባቶችና የመንግስት አካላት ተሳትፈዋል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2009 የፓስፖርት እደላን በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በኩል ማድረጉን የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያውና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ስራውን በጋራ ለመከወን ተስማምተዋል።

ተቋማቱ የፓስፖርት እደላ ስራውን በደረሱበት ስምምነት መሰረት እያከናወኑ ስለመሆኑ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚሁ መሰረት ፓስፖርት የማውጣት ሂደቱ በኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ የሚፈጸም ሲሆን እደላውን የኢትዮጵያ ፖስታ  አገልግሎት ድርጅት ያከናውነዋል።

የመምሪያው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዘላለም መንግስቴ የስምምነቱ ዋና ዓላማ ደንበኞች ጥራት ያለውና ተደራሽ አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም “የዋና መምሪያው ግቢ ካለበት የቦታ ጥበት የተነሳ እደላው ለፖስታ አገልግሎት ድርጅት መሰጠቱ በተገልጋዮች ላይ ይደርስ የነበረውን እንግልት ያስቀራል” ብለዋል።

የድርጅቱ የድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደለ አሰፋ በበኩላቸው የፓስፖርት እደላ ስርዓቱን ቀልጣፋ ለማድረግ ድርጅቱ አዲስ አደረጃጀት ማዋቀሩን ተናግረዋል።

የፓስፖርት እደላ አገልግሎቱ ከግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ዋናው ፖስታ ቤት በሙከራ ደረጃ የተጀመረ ሲሆን በቀጣይም በመዲናዋ ለደንበኞች አመቺ በሆኑና በተመረጡ የድርጅቱ ጣቢያዎች ጭምር ይደረጋል።

የኢዜአ ሪፖርተር በአገልግሎት መስጫ ማዕከሉ ለፓስፖርት እደላ ብቻ የሚያገለግል ቢሮና የእንግዳ ማረፊያ መገንባቱንና ለተገልጋዮችም ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተመልክቷል።

በማዕከሉ የፓስፖርት እደላ አገልግሎት ያገኙት ወይዘሮ ታምሬ ሙህዲንና አቶ ዳዊት ፈቃዱ አገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ መሆኑንና ቀደም ሲል የነበረውን መንገላታት እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።

አገልግሎቱን በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ተደራሽ ለማድረግ ጥናት መደረጉ በመግለጫው ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በአገር አቀፍ ደረጃ በ940 መደበኛና በአንድ ሺህ ወኪል ፖስታ ቤቶች አማካኝነት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2009 ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራልነት የሚወዳደሩት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንዲመረጡ ድጋፍ እንደሚያደርግ የስሎቫኪያ መንግስት ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው የፕሬስ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የስሎቫኪያ ሪፐብሊክ መንግስት ለዓለም አቀፍ ጤና ደርጅት ዳይሬክተር ጄኔራልነት በመወዳደር ላይ ያሉትን ዶክተር ቴድሮስ እንዲመረጡ ድጋፍ ያደርጋል።

በቅርቡ የአፍሪካ ካሪቢያንና ፓስፊክ ቡድን አባል አገሮች ሙሉ በሙሉ ድጋፋቸውን ለዶክተር ቴድሮስ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።

በእናቶችና ሕጻናት ሞት ቅነሳ፣ የወባና የልጅነት ልምሻ በሽታዎችን ከአገሪቷ ለማጥፋት ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተደማጭነትን አግኝተዋል። በዚህ ምክንያትም የተለያዩ ሽልማቶችን ተበርክቶላቸዋል።

ዶክተር ቴድሮስ በዚህ ምርጫ አሸናፊ ከሆኑ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስቸጋሪ የሆኑትን የዓለም ጤና ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ምርጫው ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ዋና ከተማ ጄኔቫ የሚካሄድ ሲሆን፤ ድጋፍ ለማጠናከር የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በቅርቡ ወደዚያው ያቀናል።

ዶክተር ቴድሮስ በምርጫው ካሸነፉ የመጀመሪያው አፍሪካዊ የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ይሆናሉ።

የኢትዮ - ስሎቫኪያ የሁለትዮሽ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1947 ሲሆን፤ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር ድርጊቱን ካወገዙ አገሮች መካከል ስሎቫኪያ አንዷ ነች።

የሁለቱን አገሮች የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ተደራራቢ ቀረጥ ለማስወገድና የኢንቨስትመንት ጥበቃ አስመልከቶ መስከረም 2009 ዓ.ም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2009 በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ላስጠሩ ሴት ስፖርተኞችና የአመራር አባላት ዕውቅና ተሰጠ። 

የዕውቅና ፕሮግራሙን ኢ-መልቲ ሚዲያ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከኦሊምፒክ ኮሚቴና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር አዘጋጅቶታል።

በስፔን ባርሴሎና በተካሔደው የኦሊምፒክ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በ10 ሺህ ሜትር ሩጫ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው የአፍሪካ ቀዳሚዋ እንስት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ እውቅናው ከተሰጣቸው መካከል ነች።

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 1996 በአሜሪካ አትላንታ በተካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር በማራቶን በኢትዮጵያ ታሪክ ወርቅ ያስገኘችው አትሌት ፋጡማ ሮባም ተካታለች።

በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የፕሪሚየር ሊግ የወንዶች ክለብ በማሰልጠን የመጀመሪያዋ፤ ድሬዳዋ ከነማ ከብሄራዊ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲያድግ ያደረገችው አሰልጣኝ መሰረት ማኔም ዕውቅና አግኝታለች።

ኢትዮጵያን በመወከል የአፍሪካና የዓለም እግር ኳስ የዋንጫ ውድድሮችን በዳኝነት የመራችው ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰም ዕውቅና የተሰጣት ሌላዋ እንስት ነች።

በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በቴኳንዶ ስፖርት ወርቅ ያስገኘችው ዮርዳኖስ ሲሳይ፣ የብስክሌት ስፖርት ተወዳዳሪዋ ኢየሩሳሌም ዲሮ ዕውቅና ከተሰጣቸው ወጣት ሴት ስፖርተኞች መካከል ናቸው።

በሚኒስትር ማዕረግ የመለስ አካዳሚ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ማሞና የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስራ አስፈጻሚዋን ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማይን ጨምሮ በአመራርነት ደረጃ የኢትጵያን ስፖርት ለማሳደግ ጉልህ ሚና የተጫወቱ እንስቶችም የዕውቅናው ባለቤቶች ሆነዋል።

በዕውቅና ፕሮግራሙ የህጻናትና ሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርስን ጨምሮ በርካታ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ ስፖርትና የሴቶች ሚና በሚል ርዕሰ ጉዳይም ውይይት ተካሂዷል።

 

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2009 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኤሌክትሮ ሜካኒካል ሙያ ያሰለጠናቸውን 138 ቴክኒሺያኖች አስመረቀ።

ተቋሙ በኮተቤ ማሰልጠኛ ተቋም በመሰረታዊ ኤሌክትሮኒክስ፣ ኢንዱስትሪያል ዋየሪንግ፣ የንፋስ ኃይል ማመንጫ፣ በኃይል ማከፋፈያ ኦፕሬሽንና ተያያዥ የትምህርት አይነቶች ለስድስት ወራት ያሰለጠናቸውን 138 ተማሪዎች ነው ያስመረቀው።

የተቋሙ የውጭ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ተሾመ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተመራቂዎቹ መካከል 63ቱ ሴቶች ናቸው።

ተመራቂዎቹ "በባለሙያ ዕጥረት ምክንያት የሚፈጠረውን የኃይል መቆራረጥና ብክነት ችግር ለመፍታት ትልቅ አቅም ይሆናሉ" ብለዋል።

ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በተግባርና በንድፈ ሃሳብ ታግዞ የተሰጠው ስልጠና ምሩቃኑን የበቁና ለስራ ዝግጁ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተያዘው ዓመት ያስመረቃቸው 303 ሙያተኞች በኃይል ማመንጫዎችና በኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ይመደባሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኤሌክትሮ ሜካኒካልና መሰል ሙያዎች ስልጠና መስጠት ከጀመረ 50 ዓመታትን አስቆጥሯል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2009 የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር የኅብረተሰቡን የስነ-ተዋልዶ ጤና ግንዛቤ ለማሳደግ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለፀ።

ማኅበሩ "ሚድዋይፎች፣ እናቶች፣ ቤተሰብና አጋር አካላት ለሕይወት" በሚል መሪ ሃሳብ 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ዛሬ አክብሯል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ማኅበሩ የኅብረተሰቡን የስነ-ተዋልዶ ጤና ግንዛቤ በተለይም በትምህርት ተቋማት ለተማሪዎች ስልጠና በመስጠት ለዘርፉ እድገት ሚናውን በመወጣት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ጎን ለጎንም የሙያተኞችን ስነ-ምግባር ለማጎልበት እየሰራ እንደሆነ ተመልክቷል።

ሚኒስቴሩ በቀጣይ የሚድዋይፎችን የሙያ ብቃትና ቁጥር ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚጠበቅበት ነው ያስታወቁት።

የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚደንት ሲስተር አዜብ አድማሱ በበኩላቸው ማኅበሩ ዋና ትኩረቱን በስነ-ተዋልዶ ጤና ላይ በማድረግ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከአሜሪካው ሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አዲስ አበባና ጎንደርን ጨምሮ በሌሎች ስምንት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።

በቀጣይም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአገሪቷ በአንድ የጤና ተቋም ቢያንስ ሦስት ሚድዋይፎች እንዲኖሩ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር በ1984 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ከ11 ሺህ በላይ አባላትም አሉት።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2009 የኢትዮጵያ አብያተ ክርስትያናት በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያና በየመን የተከሰተውን ረሃብ አስመልክቶ ግንቦት 13 ቀን 2009 ዓ.ም የፀሎት ቀን እንዲሆን አወጁ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊትና የኢትዮጵያ መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስትያናት በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት የፀሎት መርሃ ግብሩ አብያተ ክርስትያናቱ አባል በሆኑበት በዓለምና በአፍሪካ አብያተክርስትያናት ምክር ቤቶች በኩል መወሰኑን ተናግረዋል።

ተወካዩ መልአከ ሠላም አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ እንደተናገሩት በዓለም ላይ የተከሰተው ረሃብ ብዙዎችን እየጎዳ በመሆኑና በተለይ በአራቱ አገራት አደገኛ ሁኔታ ላይ መድረሱ ቤተ ክርስትያናቱን አሳስቧል።

በእነዚህ አገራት ስላለው አስከፊ ረሃብና ችግር የዓለም ህብረተሰብ እየሰጠ ያለው ምላሽ በቂ ባለመሆኑ የዓለምና የአፍሪካ አብያተ ክርስትያናት በፀሎት እንዲያግዟቸው በምክር ቤቶቹ በኩል መወሰናቸውን ተናግረዋል።

የመላው አፍሪካ አብያተ ክርስትያናት ምክር ቤት ለአፍሪካ ህብረት ተጠሪ አቶ ተድላ ተሾመ እንዳሉትም ምክር ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው የተባበሩት መንግስታት ከሃያ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአስከፊ ረሃብ ውስጥ መሆናቸውን ጠቅሶ ሠብዓዊ እርዳታ መጠየቁን ተከትሎ ነው።

በተለይ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያና በየመን ከሃያ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በአስከፊ ረሃብ የሚገኝና ለተለያዩ በሽታዎችና ሞት እየዳረገው መሆኑን አስታውሰው የአብያተ ክርስትያናቱ ምዕመናን ፈጣሪ ምህረት እንዲያወርድ በምህላና ፀሎት እንዲማፀኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በተባበሩት መንግስታት እ.አ.እ. ከ1945 በኋላ እጅግ ከባድ የተባለለትን ይህን የረሃብ አደጋ ለመቀልበስ አራት ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባግንቦት 11/2009 የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከሳዑዲ ዓረቢያ ለሚመለሱ ወገኖችና በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገለጸ። 

እንደ ውሃና ቢራ የመሳሰሉ ሸቀጦች ላይ ሸማቹን የማይጎዳ ጭማሬ በማድረግ ገቢው ለተጎጂዎች እንዲውል ይደረጋል ብሏል።

ምክር ቤቱ ከሳዑዲ ተመላሾችን ማቋቋም ስለሚቻልበትና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የግሉ ዘርፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ በሚያደርግበት ሁኔታ ላይ ዛሬ ተወያይቷል።

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ምክር ቤቱ ከሳዑዲ ተመላሾችን ለማገዝ የፈለገው ኢኮኖሚያዊ ስጋታቸውን በመረዳት ነው።

እንደሚመለሱ ከሚጠበቁት ከ400 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ አገር እየገቡ ያሉት ጥቂቶች መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ሰለሞን ቢመለሱ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የሥራ አጥነትና ማህበራዊ ችግር ለመቀነስ ዘርፉ የበኩሉን ለማድረግ እንደሚፈልግ ነው የተናገሩት።

እርሳቸው እንደሚሉት የግሉ ዘርፍ ከዚህ ቀደም የስደተኞችን ችግር መፍታት የሚችለው መንግስት ብቻ እንደሆነ በማሰብ ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲገቡና የሥራ እድል አንዲፈጠርላቸው በማድረግ በኩል ምንም አስተዋፅኦ አልነበረውም።

"አሁን ግን ወገኖቻችን አገራቸውን እየወደዱ፤ ‘ሥራ አይገኝም’ በሚል ፍራቻ የሳዑዲን መንግስት ከባድ አዋጅ መርጠው ሲቀሩ ዝም ማለት የለብንም" ነው ያሉት።

ተመላሾቹ ወደ አገር ቤት ሲገቡ ከመንግስት ጎን በመሆን በሚፈልጉት ሙያ እንዲሰለጥኑና በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች እንዲሰማሩ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ገልፀዋል።

በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ስለመርዳት ሲናገሩም እነዚህን ወገኖች በመርዳት ረገድ የተለያዩ የግል ተቋማት በተናጠል ድጋፍ እያደረጉ ቢሆንም ስርነቀል መፍትሄ ለማምጣት በጋራ ለመስራት መነጋገራቸውን አስታውቀዋል።

የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች በሚያመርቷቸው እንደ ውሃና ቢራ የመሳሰሉ ሸቀጦች ላይ ሸማቹን የማይጎዳ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ከዚያ የሚገኘውን ገቢ ለተጎጂዎቹ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2009 የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከገዥው ፓርቲ ጋር ለመደራደር ያቀረቧቸው ሃሳቦች ለአጀንዳ ኮሚቴው መድረሱን አረጋገጡ።

ፓርቲዎቹ እያንዳንዳቸው ሁለት ታዛቢ እንዲያቀርቡም ስምምነት ላይ ተደርሷል።

አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያካሄዱት ድርድር፣ ክርክርና ውይይት ላይ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እየተወያዩ ናቸው።

በዛሬው ዕለት እያንዳንዱ ፓርቲ ባለፉት 15 ቀናት ያቀረባቸውን ሃሳቦች ለአጀንዳ ኮሚቴው መድረሳቸውን አረጋግጠዋል።

የአጀንዳና የሚዲያ ኮሚቴ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት ፓርቲ /ኢዴህ/ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ ከውይይቱ በኋላ እንዳሉት ፤ የአጀንዳ ኮሚቴው ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ከ17 ፓርቲዎች የተቀበላቸውን የመወያያ ሃሳቦች ሳይጨመርና ሳይቀነስ ለፓርቲዎቹ አቅርቧል።

ፓርቲዎቹ እያንዳንዳቸው ከ1 እስከ 34 የሚደርሱ የመወያያና የመደራደሪያ ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ በይዘታቸው ከፖለቲካ ምህዳር መጥበብ እስከ ህገ መንግስታዊ ጥያቄ ድረስ የሚሸፍኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በዛሬው ስብሰባቸው ምንም ዓይነት ልዩነት እንዳልነበራቸው ነው የገለጹት።

ከቀረቡት ሃሳቦችና አጀንዳዎች መካከል የአጀንዳ ኮሚቴው ለድርድርና ለውይይት የሚቀርቡትን ሃሳቦች ጨምቆ ለቀጣይ ስብሰባ እንዲያቀርብ መስማማታቸውም ተመልክቷል።

ፓርቲዎቹ በቀጣይ በሚካሄዱት የድርድር፣ ክርክርና ውይይት መድረኮች ላይ የሚሳተፉ ታዛቢዎች ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን፤ እያንዳንዱ ፓርቲ ሁለት ታዛቢዎች እንዲያቀርቡ ተወስኗል።

ፓርቲዎቹ በራሳቸው ከሚያመጧቸው ታዛቢዎች በተጨማሪ በሁሉም ፓርቲ ስምምነት መሰረት ገለልተኛ የሆኑ 12 የውጭና የአገር ውስጥ ድርጅቶች በታዛቢነት እንዲሳተፉ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በዚሁ መሰረትም አምስት የሚሆኑት ከውጭ እንደሚሆኑም ታውቋል።

ታዛቢ ድርጅቶቹ ከኢምባሲዎች፣ ከሲቪክ እና ከሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶች የተውጣጡ እንደሚሆኑም ተጠቁሟል። እንደድርጅቶቹ ነባራዊ ሁኔታ ከአንድ እስከ አምስት ተወካዮች የሚኖሯቸው ሲሆን፤ በመንግስት በኩል ጥሪ እንደሚደረግላቸው ታውቋል።

ዋናው ድርድር ሲጀመር እስከ ታዛቢዎቹ ከአንድ መቶ በላይ ተሳታፊዎች የሚኖሩት ይሆናል። ከአንድ ወር በማያንስ ጊዜ ውስጥ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባደረገው የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ማጠቃለያ ላይ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች ውስጥ በአገሪቷ በህጋዊ መንገድ ከተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት፣ ክርክርና ድርድር ማድረግ ነው። በአሁኑ ወቅትም ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ 17 ፖለቲካ ፓርቲዎች ህግና ደንቡን ተከትለው በቅድመ ሁኔታዎቹ ላይ  እየተወያዩ ይገኛል።

 

 

Published in ፖለቲካ

ጎባ ግንቦት11/2009 በኦሮሚያ ባሌ ዞን የሮቤ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት በዞኑ አርብቶ አደር ወረዳዎች ለሚገኙ የድርቅ ተጎጂዎች 1ሺህ 236 ኩንታል የምግብ እህልና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

የሮቤከተማከንቲባ ተወካይና የእርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል አቶ አብዱልሀኪም አልይ እንደገለጹት ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ የተደረገው በዋናነት ለሰዌና ፣ ለገሂዳ ፣ ዳዌ ቃቸንና ዳዌ ሰረር ወረዳዎች የድርቅ ተጎጂዎች ነው።

ድጋፉን ያደረጉት የከተማው ነዋሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ፣ የሮቤ መምህራን የትምህርት ኮሌጅ ሰራተኞችና መንግስታዊ  ያልሆኑ  ድርጅቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ለተጎጂዎቹ የተሰጠው ድጋፍ አንድ ሺህ 236 ኩንታል ስንዴ፣ሩዝ፣ ዱቄትና ጥራጥሬን ጨምሮ 200 አንሶላና ብርድ ልብስም የተካተተበት መሆኑን አስረድተዋል።

የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ሀይሌ እንደገለፁት ድጋፉ የተጎጂዎችን ችግር ለማቃለል እየተደረገ ያለውን ጥረት ያግዛል ።

በዞኑ አስራ ስምንት ወረዳዎች ውስጥ በድርቅ ለተጋለጡ ወገኖች ከሀምሌ ወር 2008 ዓ.ም.ጀምሮ አስከ አሁን ድረስ መንግስት ከ285 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል፣ጥራጥሬና አልሚ ምግብ እንዲሰራጭ አድርጓል ።

በሰዌና ወረዳ ትናንት በተካሄደው የድጋፍ ርክክብ ላይ የተገኙት የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶአደም ቃሲም "መንግስት ለድርቅ ተጎጂዎች ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር የዞኑ ህዝብ  እያደረገ ያለው ድጋፍ ወገን ለወገን ደራሽ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ነው" ብለዋል።

ችግሩ እስኪያልፍ ድረስ ድጋፉ ለወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

የሰዌና ወረዳ የድርቅ ተጎጂዎች ተወካይ ሼህ መሐመድ ኢብራሂም በበኩላቸው የሮቤ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎችና ተቋማት ላደረጉት ድጋፍ በድርቁ ተገጂ ወገኖች ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በባሌ ዞን በተከሰተው ድርቅ ምክንያት 400 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ለምግብ እህል እጥረት የተጋለጡ መሆናቸውን ከዞኑ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን