አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Thursday, 18 May 2017

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2009 ስምንተኛው ከተማ አቀፍ የባህል ፌስቲቫል ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚጀመር የመዲናዋ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

ኢግዚብሽኑ ከግንቦት 12 እስከ 14 ቀን 2009 ዓ.ም "የባህል ልማት ለዘላቂ ሠላምና አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ  በአዲስ አበባ ኢግዚብሽን ማዕከል ይካሄዳል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ  የባህል እሴቶችና ኢንዱስትሪ ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ አዳነች አሰፋ በአሉን አስመልክቶ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት፤ በከተማው ያሉ አራቱ የአስተዳደሩ ቴአትሮች የተውኔት ውድድር ያደርጋሉ፡፡

ፌስቲቫሉ የአገሪቷን የኪነ ጥበብ ሀብት ለመጠበቅ፣ ለማስተዋወቅ፣ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን ለማበረታታት እና ለጥበቡም ህዝባዊ ወገንተኝነትን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል፡፡

የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል፣ አውደ ርዕይ፣ ሲምፖዚየምና ውድድሮች የባህል ፌስቲቫሉ አካል መሆናቸውን የተናገሩት ወይዘሮ አዳነች፤ “176 የሚሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ይሳተፉበታልም“ብለዋል፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት፤ የኪነ ጥበብ ፌስቲቫሉ በአማተር ቡድኖች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በየክፍለ ከተማው በተቋቋሙ ሙያዊ የባህል ቡድኖች ይሸፍናል። ወጣቱና የኪነጥበብ ባለሙያው ባህሉን እንዲጠብቅና በሥራ ፈጠራው ጭምር እንዲጠቀመበት ለማድረግና ለማበረታታት ትልቅ ሚና አለው፡፡

የባህል ምግብና መጠጦች፣ አልባሳት እና የጥበብ ውጤቶችን ለከተማው ነዋሪና ጎብኚዎች በአውደ ርዕዩ እንደሚቀርቡም ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ አዳነች እንደተናገሩት፤  የከተማው ባህል አዳራሽ፣ ራስ ቲያትር እና አገር ፍቅር ቲያትር የተውኔት ውድድር የሚያደርጉ ሲሆን፤ ህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ተሳታፊ ይሆናል፡፡

ለውድድር የሚቀርቡት ተውኔት  መሪ ቃሉን የሚያጎሉ መሆን ያለባቸው ሲሆን፤ “ይሄንን ማሳካታቸውን የሚታይበት አግባብ ይኖራልም” ነው ያሉት፡፡ 

በክፍለ ከተሞች መካከል፣ በግል እና በቡድን የሚካሄድ የትወና፣ የውዝዋዜ፣ የሥነ ጽሁፍ፣ የመነባንብ እና የልዩ  ተሰጥኦ ውድድርም የፌስቲቫሉ አካል ሲሆኑ፤ ለአሸናፊዎች እስከ ሃያ ሺ ብር  ሽልማትም ተዘጋጅቷል።  የሱዳን የባህል ቡድን በተጋባዥነት ይገኛልም ተብሏል፡፡

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ ግንቦት 10/2009 በጋምቤላ ከተማ ዛሬ የጣለው ከባድ ዝናብ ተከትሎ ባስከተለው ጎርፍ  የተለያዩ መኖሪያ ቤቶች በማጥለቅለቅ በንብረት ላይ ጉዳት  አደረሰ፡፡

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቶማስ ቱት እንደገለጹት በከተማው ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ ያለማቋረጥ ከሶስት ሰዓት በላይ የጣለው ከባድ ዝናብ ጎርፍ በማስከተል ጉዳት አድርሳል፡፡

ጎርፉ በከተማው አራት ቀበሌዎች መኖሪያ ቤቶችን በማጥለቅለቅ ነዋሪዎችን አፈናቅሏል፡፡

እስካሁን ባለው መረጃ ጎርፉ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አለማድረሱ ተረጋግጣል፡፡

ይሁን እንጂ የበርካታ ነዋሪዎችን ቤት በማጥለቅለቅ ንብረት ማጥፋቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎችን ወደ ደረቅ ቦታ ለመውሰድ የቦታ መረጣ እየተካሄደ መሆኑንና የደረሰውንም የጉዳት መጠን የማጣራት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በዜሮ አምስት ቀበሌ ጉዳት ከደረሰባቸው ነዋሪዎች መካከል አቶ ወንዴ ገበየሁ በሰጡት አስተያየት ዝናቡ ባስከተለው ጎርፉ በቤት ንብረታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ጎርፉ ሊከሰት የቻለው ግለሰቦች  በውሃ ማፋሰሻ ቦዮች አፈር እየደፉ በማጣበባቸው ምክንያት ነው ብለዋል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ተስፋነሽ ማቲዎስ በሰጡት አስተያየት ዝናቡ ባስከተለው ጎርፍ ቤት ንብረታቸው ተጥለቅልቆ ችግር ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል።

ስለሆነም መንግስት ጊዚያዊ መጠለያና ለተከሰተው ችግር መፍትሄ እንዲያፈላልግላቸው ጠይቀዋል።

የኢዜአ ሪፖርተር በከተማ የተለያዩ ቀበሌዎች በተዘዋወረበት ወቅት በርካታ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች በጎርፍ ተጥለቅልቀው ተመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

ግንቦት 10/2009 በኢትዮጵያ  ሶማሌ  ክልል  120ሜጋ ዋት  የነፋስ ሀይል  ማመንጫ  ሊገነባ  መሆኑን  የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ  ሚኒስቴር   አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ  የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ  ቶልቻ  ለዥንዋ  እንዳስታወቁት   ግንባታው   በሃምሌ  ወር  ይጀመራል፡፡

ፕሮጀክቱ  ዶንግፋንግ   በተሰኘው  የቻይና  ኤሌክትሪክ   ኮርፖሬሽን   እንደሚገነባ  ተነግሯል፡፡ 

በ257 ሚሊዮን  ዶላር ወጭ   የሚገነባው  ፕሮጀክቱ  በ18   ወራት   ይጠናቀቃል  ተብሏል፡፡

የፕሮጀክቱ  ወጭ  85  በመቶው  በቻይና  ኢምፖርት  ኤክስፖርት  ባንክ  የሚሸፈን   ሲሆን   15 በመቶው  በኢትዮጵያ   መንግስት  እንደሚሸፈን   በዘገባው  ተመልክቷል፡፡  

በአገሪቱ ከዚህ ቀደም  በአሸጎዳ 120 ፣ በአዳማ I 51 እና  በአዳማ II 153 ሜጋ ዋት የሀይል ማመንጫዎች  መገንባታቸው  ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ  እአአ እስከ 2020 ከውሃ  ፣ከነፋስ፣  ከፀሃይና  ከሌሎችም  ምንጮች  በመጠቀም የሃይል መጠኗን ወደ  17,300 ሜጋ ዋት  ለማሳደግ  አቅዳ  እየሰራች  እንደሆነም   ዘገባው አስታውሷል፡፡  

 

Published in ኢኮኖሚ

ነቀምቴ ግንቦት 10/2009 በነቀምቴ ከተማ የሚካሔደው የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ መቋረጥ የመጠለያ ፍላጎታቸውን ለመሟላት ስጋት እንደፈጠረባቸው አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።

በቤት ፈላጊዎች ቁጥር ማነስ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ግንባታ 49 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ወደ ስራ መገባቱን በክልሉ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የምእራብ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

በነቀምቴ ከተማ የ02 ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ማስረሻ ከበደ እንደገለጹት መንግስት የህብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በከተማው ሲያከናውነው የነበረው የጋራ መኖሪያ ሕንጻ ግንባታ መቋረጥ ቤት የማግኘት ፍላጎታቸውን ለስጋት ዳርጎታል።

"የግንባታው መቋረጥ ከግል የኪራይ ቤት ተፅእኖ ለመላቀቅ የነበረንን ተስፋ እንዲጨልም እያደረገው ነው" ያሉት ወይዘሮዋ ግንባታው እንዲቀጥል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተናግረዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ሙሉጌታ ፈይሳ በበኩላቸው የቤቶቹ መገንባት ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ መጠለያ እንዲያገኝ ከማገዙም ባለፈ የከተማይቱን ገጽታም የሚቀይር በመሆኑ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የጋራ መኖሪያ ቤት ያገኙት የከተማው ነዋሪ አቶ አካሉ ተስፋዬ እንደተናገሩት ደግሞ ቤቱን የግላቸው ለማድረግ በወር 900 ብር እየከፈሉ ይገኛሉ።

እስከ 3 ሺህ ብር ድረስ በወር ለቤት ኪራይ ይከፍሉ እንደነበረ ገልጸው የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ እንደሳቸው የተቸገሩ ነዋሪዎችን የሚታደግ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የምእራብ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት የፕሮግራምና እቅድ ባለሙያ  አቶ ተስፋዬ ዳቡሰ እንደገለጹት በ2000 ዓ.ም.የተጀመረው የጋራ መኖሪያ ህንጻ ግንባታ 42 በመቶ ከተሰራ በኋላ በ2005 ዓ.ም ተቋርጧል።

በወቅቱ በነበረው የቤት ፈላጊዎች ቁጥር ማነስና የግንባታ እቃዎች ዋጋ መናር ምክንያት የተቋረጠው ግንባታም "አሁን ላይ የፍላጎት መጨመር በመታየቱና የግንባታው መቀጠል አስፈላጊነት ስለታመነበት 49 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ ወደ ስራ ተገብቷል" ብለዋል ።

በግንባታው 25 ህንጻዎች የተካተቱበት ሲሆን 532 አባወሯዎችና ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2009 በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ድርቅና ሁከቶችን ተቋቁማ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ በዓለም ተጠቃሽ አገር መሆን መቻሏን የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ ሰኔ 7 ቀን 2009 ዓ.ም ለተባበሩት መንግሥታት የማኅበራዊና ፋይናንስ ካውንስል የሚያቀርበውን “የ2017 የዘላቂ ልማት ግቦች የፈቃደኝነት ብሔራዊ ግምገማ” ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ አስገምግሟል።

ድህነትና ረሃብን  ማጥፋት፣ ጤናማ ሕይወት መምራት፣ የመሠረተ ልማት ግንባታና ኢንዱስትሪ ፈጠራ፣ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት እንዲሁም የውሃ ሥነ-ምህዳርን በዘላቂነት መጠበቅ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚገመገሙ የዘላቂ ልማት ግቦች ናቸው።

እነዚህ ዘላቂ የልማት ግቦች ከሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ጋር ተመጋጋቢ ናቸው።

ክምክር ቤቱ አባላት የእቅዱ ዘመን አፈጻጸም ያለበት ደረጃ እንዲቀርብ ጥያቄ ቀርቦ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ይናገር ደሴ እንደገለጹት፤ አገሪቷ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅና ሁከቶች እንዲሁም የዓለም የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ሳይበግራት በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሁለት ዓመታት ውስጥ ፈጣን እድገት አስመዝግባለች።

በ2008 በጀት ዓመት የአገሪቷን ኢኮኖሚ በ11 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ተይዞ ስምንት በመቶ ያደገ ቢሆንም ከዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝና በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ ከነበረው ፈተና አኳያ የተመዘገበው ፈጣን እድገት ነው።

“በዚህም በዓለም ፈጣን እድገት ካስመዘገቡ አገሮች መካከል አንዷ መሆኗን አስመስክራለች” ብለዋል።

በ 2008 ዓ.ም የሸቀጦችና የዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ እንደነበር ጠቁመዋል።

በወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሥራዎች፣  የሥርዓተ ፆታ፣ የሰው ኃብት ልማት፣ ፍትሃዊ የኃብት አጠቃቀም ያሉበት ደረጃ በሪፖርቱ ላይ በዝርዝር እንዲቀርቡም ምክር ቤቱ ጠይቋል።

Published in ኢኮኖሚ

ሶዶ ግንቦት 10/2009 በ28ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪመየር ሊግ እግር ኳስ ጨዋታ ንግድ ባንክ ወላይታ ዲቻን አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት አሸነፈ፡፡

የሁለት ጨዋታዎች ዕድሜ  በቀረው የፕሪምየር ሊጉ ፉክክር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲቻን ያሸነፈው  ዛሬ በወላይታ ሶዶ ሁለገብ ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ ነው፡፡

ንግድ ባንክ ጎላን ያስቆጠረው የጨዋታው ሰዓት አልቆ በባከነው ደቂቃ የዳኛ ፊሽካ በሚጠበቅበት ጊዜ ነው፡፡

ጎላን ያስቆጠረው የዲቻ ተከላካዮችን መዘናጋት የተጠቀመው ሁለት ቁጥሩ ፍቅረየሱስ ገብረ መድህን ነው፡፡

ሁለቱም ቡድኖች የመውረድ ስጋት ውስጥ ሆነው ያደረጉት ጨዋታ በመሆኑ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ለማሳየት የሞከሩ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ወደጎል የቀረቡ ሙከራዎች በማድረግ ባንክ የተሻለ ነበር፡፡

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባለሜዳዎቹ ተጭነው በመጫወት በ78ኛውና 83ኛው ደቂቃ  በፈቱዲን ጀማል ሞክረው የባንኩ በረኛ ያወጣቸው ኳሶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ በ80ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ የዲቻ በረኛም ጭምር የወጣበትን አጋጣሚ ባንኮች መጠቀም ቢችሉ የጎል ልዩነቱ ሊሰፋ ይችል ነበር፡፡

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ዲቻ በኳስ ቁጥጥር በማጥቃትና በማደራጀት ለጎል  የቀረቡ ሙከራዎችን ቢያደርግም ኢላማቸውን ባለመጠበቃቸው ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡

በ54ኛው ደቂቃ ላይ የባንኩ 88 ቁጥሩ ታዲዮስ ወልዴ በዲቻው 19 ቁጥሩ አላዛር ፋሲካ ላይ በፈጸመው ያልተገባ አጨዋወት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ "ተመጣጣኝ ጨዋታ አሳይተናል ኳስ ይዘን በመጫወት ነጥብ ይዘን ለመመለስ ነበር፤ ተሳክቶልናል" ብለዋል፡፡

"የወላይታ ዲቻ በረጃጅም ኳሶችና በፈጣን ሩጫ የሚያስቸግር ቡድን በመሆኑ የተገኙ አጋጣሚዎችን መጠቀም ወሳኝ ነበር "ያሉት አሰልጣኝ ሲሳይ በውጤቱም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የወላይታ ዲቻ ቡድን ዋና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ "በርካታ የጎል ዕድሎችን በሁለቱም የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ብንፈጥርም ለማሸነፍ በነበረን ጉጉት የተነሳ ወደጎል  መቀየር ባለመቻል ተሸንፈናል " ብለዋል፡፡

መሸነፋቸው  በኳስ  ዓለም እንደሚያጋጥም የተናገሩት  አሰልጣኝ መሳይ "ከመውረድ ለመትረፍ ዕድሉ በእጃችን ያለ በመሆኑ ቀጣይ ያሉን ጨዋታዎች የምናሸንፍበት መንገድ ማሰብ ተገቢ ነው "ብለዋል

ዲቻ ቀሪ ጨዋታዎች አንዱን ከሜዳ ውጪ ከአርባ ምንጭ ከተማ የመጨረሻውን ደግሞ በሜዳው ከደደቢት ጋር ይገጥማል፡፡

በተለይ በተጨማሪ ሰዓት ጎል ከገባ በኋላ  የዲቻ ደጋፊዎች ያሳዩት ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለው ተግባር ለታዳጊ ወጣቶችና ለስፖርቱ ዕድገት አሉታዊ ተጽዕኖ ያለው በመሆኑ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2009 የዘንድሮ አገር አቀፍ ፈተናዎች በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠናቀቁ ወላጆች ለልጆቻው የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ።

የወላጅ ተማሪዎች መምህራን ተወካዮች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አንደገለጹት፤ የዘንድሮ አገር አቀፍ ፈተናዎችን የሚወስዱ ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የወላጆች ምክር፣ ቁጥጥርና ድጋፍ ያስፈልጋል።

ለፈተናዎቹ በስኬት መጠናቀቅ ወላጆች ሚናቸው የላቀ መሆኑን ተገንዝበው በቀጧዮቹ ቀናት በንቃት እንዲሰሩም አሳስበዋል።

በአራዳ ክፍለ ከተማ የወላጅ ተማሪ መምህራን ተወካይ ሻምበል እንድሪያስ በሻዳ በሰጡት አስተያየት "ሁሉም ተማሪዎች ተረጋግተው ፈተናቸውን እንዲሰሩ ወላጆች የሚያደርጉትን ክትትል ማጠናከር ይኖርባቸዋል" ብለዋል።

ወላጆች ተማሪዎች ተረጋግተውና በሰከነ ሁኔታ ፈተናቸውን እንዲሰሩ በስነ-ልቦና ሊያዘጋጇቸው እንደሚገባም መክረዋል።

ተማሪዎች በሰከነ ሁኔታ እንዲፈተኑ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ እንደሆንም አመልክተዋል።

የቃሊቲ አቃቂ ክፍለ ከተማ ተወካይ ወይዘሮ አስናቀች አበበ በበኩላቸው  ተማሪዎች መኮረጅ እንደሌለባቸው ወላጆች ለልጆቻቸው ማስረዳትና ማስገንዘብ ይገባቸዋል።

ሌላው የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ተወካይ አቶ ከበደ ፈትሃ  "ፈተና ይሰረቃል" በሚሉ ሐሰተኛ ወሬዎች ተፈታኞች እንዳይደናገጡ ወላጆች አስፈላጊውን የስነ-ልቦና ዝግጅት እንዲያደረጉ መጣር ይጠበቅባቸዋል።

ተማሪዎች የኩረጃ ውጤትን እንዲጠየፉና በራሳቸው እንዲተማመኑ የሚያደርግ ተግባር ወላጆች መስራት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።

የትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከግንቦት 23 እስከ 25  የሚሰጥ ሲሆን፤ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ደግሞ ከግንቦት 28 እስከ 30 ይሰጣል።

ዘንድሮ ሀገር አቀፍ ፈተናዎች 288 ሺ 626 የ12ኛ ክፍልና 1 ሚሊዮን 206 ሺ 839 የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ከሦስት ሺ በላይ በሚሆኑ የፈተና ጣቢያ ፈተናቸውን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2009 ቅዱስ ጊዮርጊስ 20ኛውን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለ14ኛ ጊዜ ሻምፒዮን ሆነ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረገው ጨዋታ 1 ለ ባዶ በማሸነፍ ነው ለ14ኛ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት የቻለው።

28ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ስታዲየም ሰባት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰዓት ተካሂደዋል።

ከሰባቱ የጨዋታዎች  አንዱ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵ ኤሌክትሪክ ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊሱ  አዳነ ግርማ  በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠራት ግብ ለሻምፒዮና በቅቷል።

ክለቡ በ28 ጨዋታዎች በ55 ነጥብ በመሰብሰብ ሻምፒዮንነቱን ያረጋገጠው ተከታዮቹ ደደቢትና ሲዳማ ቡና ነጥብ በመጣላቸው ነው።

ይህም ክለቡ ቀሪዎችን ሶስት ጨዋታዎች ቢሸነፍ እንኳ በሰባት ነጥብ ልዩነት የሊጉ አሸናፊ መሆን ችሏል።

አዳማ ከነማ በሜዳው ደደቢትን 2 ለ 1 በማሸነፍ የደደቢትን የዋንጫ ተፎካካሪነት እድል አምክኗል።

ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ ከመከላከያ ያደረጉት ጨዋታ 3 ለ0 በመሆነ ውጤት ፋሲል ከነማ ማሸነፍ ችሏል።

ወልዲያ ከነማ ከጅማ አባቡና ፣ ሲዳማ ቡና ከአርባ ምንጭ ያለምንም ግብ በተመሳሳት አቻ ውጤት ተለያየተዋል።

ድሬዳዋ ከነማ አዋሳ ከነማን እንዲሁም  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  ወላይታ ድቻን በተመሳሳይ  1 ለ ባዶ መርታት ችለዋል።

ሻምፒዮናው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ55 ነጥብ ፣ ደደቢትና ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ 48 ነጥብ በጎል ልዩነት ተበላልጠው እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

ሃዋሳ ከነማ፣ ወልዲያ፣ አርባ ምንጭ፣ ድሬድዋ፣ ወላይታ ድቻ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክና ጅማ አባቡና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወራጅ ስጋት ውስጥ ሲገኙ አዲስ አበባ ከሊጉ መውረዱን ቀድሞ ያረጋገጠ ክለብ ሆኗል።  

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2009 ኅብረተሰቡ በቤተሰብ ምጣኔ ዙሪያ ያለውን አመለካካት ለመቀየር የሚሰራ "ሼፕ" የተሰኘ የመገናኛ ብዙሃን ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

ፕሮጀክቱ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የሚተገበረው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና በኮሪያ ዓለም ዓቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ኮይካ) አማካኝነት ሲሆን፤ በሶስት ክልሎች ለአንድ ዓመት የሚቆይ ነው።

በአማራ፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ተግባራዊ እንደሚደረግ ታውቋል።

ልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም በሥነ-ተዋልዶ ጤና እንዲሁም አመለካከትና ባህርይ ለውጥ ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያስችል ፕሮጀክት እንደሆ ነው የተገለጸው።

በጤና ጥበቃ የሚኒስትር ደኤታው አማካሪ አቶ ግርማ አሸናፊ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ቁጥርን ለመጨመርና  የሴቶችን ትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ ያስችላል።

በሥነ-ተዋልዶ ጤና የወንዶች ተሳትፎን ለማጎልበት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በተለይም ያለ ዕድሜ ጋብቻና የሴቶች ግርዛት ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሚረዳም ነው የተናገሩት።

ከባህል፣ ከእምነትና ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮችን ለማቃለልም እንዲሁ።

የኮሪያ ተራድኦ ድርጅት ተጠሪ ዶህ ዮንግ አህ በበኩላቸው፤ "አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በሰው ሃብት ልማት፣ በጤናና በገጠር ልማት ላይ በጋራ እየሰራች ነው" ብለዋል።

ኅብረተሰቡ በስነ-ተዋልዶ ጤናና በቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን አስመልክቶ ያለው ግንዛቤ እንዲዳብር አገራቸው እገዛ እያደረገች መሆኑንም ገልጸዋል።

አገሪቷ የያዘችውን ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት እንድትችል ድርጅቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ ተከታታይ የሬዲዮ ድራማዎች ፣ የሬዲዮና የቴሌቪዥን አጫጭር ቀስቃሽ መልዕክቶች፣ የመንገድ ላይ ትዕይንቶች እንዲሁም የተለያዩ በራሪ ጽሁፎች፣ ፖስተሮችና ቢልቦርዶችን በመጠቀም እንደሚከናወንም ተገልጿል። 

Published in ማህበራዊ

አርባምንጭ ግንቦት10/2009 በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ የተፈጠረው የህዝብ መነቃቃት በልማቱም መደገም እንዳለበት የደቡብ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ አሳሰቡ፡፡

በጋምጎፋ ዞን 15 ወረዳዎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች ለአንድ ወር ያህል ሲዘዋወር የቆየው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ማጠቃለያ ፕሮግራም ዛሬ በአርባምንጭ ከተማ ተካሂዷል ፤ 301 ሚሊዮን ብርም ተሰብስቧል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በማጠቃለያ ፕሮግራሙ ላይ  እንደተናገሩት የዞኑ ህዝብ የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የሰጡትን አደራ ጠብቆ በመደገፍ  ያሳየውን አንድነትና የነቃ ተሳትፎ አድንቀዋል፡፡

"ዞኑ በግብርና ፣ በቱሪዝምና በሌሎች የልማት መስኮች እምቅ ሃብት ያለው በመሆኑ የተፈጠረዉን የህዝብ መነቃቃት ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል"፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ ዋንጫው በዞኑ በሚኖረው ቆይታ 270 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በተፈጠረው ህዝባዊ ንቅናቄ ወደ 301 ሚሊዮን ብር ማሳደግ  መቻሉን ተናግረዋል ፡፡

ባለሃብቶች ፣ የመንግስት ሠራተኞች ፣ ነጋዴዎች ፣ አርሶ አደሮች፣መንግሰታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ሌሎችም ነዋሪዎች  ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡                                                                    

በኢትዮጵያ ቃለህይወት ቤተክርስቲያን የደቡብ ምዕራብ ቀጠና አስተባባሪ አቶ ኢያሱ ጦና በሰጡት አስተያየት ተቋማቸው ለግድቡ ግንባታ 1 ሚሊዮን 20 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ እንዲውል የሚገዙት ቦንድ የቁጠባ ባህላቸውን ለማሳደግ እንደረዳቸው የተናገሩት ደግሞ በዞኑ  የኦይዳ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አታርቄ አሎ ናቸዉ ፡፡

በግላቸው የ5 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውንና ድጋፋቸውን ወደፊትም እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን