አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Wednesday, 17 May 2017

ባህር ዳር ግንቦት 9/2009 የአማራን ህዝብ ማንነት የሚገልፁ ባህሎችን በመጠበቅና በማሳደግ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማዋል እንደሚገባ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ገለፁ።

''ኪነ ጥበብ ለዘላቂ ህይዎት'' በሚል መሪ ቃል 12ኛው የአማራ ክልል የባህል ሙዚቃ ፌስቲቫል ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተጀምሯል።

አፈ ጉባኤው አቶ ይርሳው ታምሬ  በፌስቲቫሉ መክፈቻ ላይ እንደገለፁት የህዝቡ የማንነት መገለጫ የሆኑ ባህሎችን ጠብቆ በማቆየት ለመጭው ትውልድ ማሰተላለፍ ይገባል።

ክልሉ እምቅ የባህል ሃብት ባለቤት መሆኑን ጠቁመው ይህንኑ ሃብት በመጠበቅ፣ በማልማትና በማሳደግ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማዋል እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዓለም አንድ በሆነችበት በአሁኑ ዘመን የህዝቡ መገለጫ የሆነው ባህል በመጤ ባህሎች እንዳይበረዝና እንዳይጠፋ መጠበቅ ይጠይቃል።

ባለፉት 25 ዓመታትም እንደሌሎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች የባህል ዘርፉ እኩል እንዲያድግ የሚያግዙ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመቅረፅ እንዲለማ የማድረግ ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል።

የክልሉን ባህል ለማልማትና ታሪካዊ ይዘቱ ሳይበረዝ ጠብቆ ለማቆየት እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ባህል ቱሪዝም ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሒሩት ካሳሁን ናቸው፡፡

የፌስቲቫሉ ዓላማም የክልሉን ባህል፣ ሙዚቃና የኪነጥበብ ስራዎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግና በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ  እንቅስቃሴ ዘርፉ ሚናውን እንዲወጣ ማድረግ ነው።

ህዝቡ ከቀደምት አባቶች የወረሰውን የአብሮነት፣ የሰላም፣ የመቻቻልና የመተሳሰብ ባህል ለመጭው ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግም ጭምር መሆኑን ገልፀዋል።

እንዲሁም የክልሉ ብሔር ብሄረሰቦች ሙዚቃና ባህላዊ ትውሁፊቶች በማስተዋወቅ እንደ አንድ የቱሪዝም ሃብት ማመንጫ እንዲውል የማድረግ ዓላማ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣይ አምስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ፌስቲቫል ላይ  ከሁሉም ዞኖችና ከባህር ዳር፣ ደሴና ጎንደር ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ300 በላይ የባህል ቡድኖች ተሳታፊ ሆነዋል።

በቆይታውም የሙዚቃና የባህላዊ ትዕይንት የሚካሄድ ሲሆን የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

''ኪነ ጥበብ ለዘላቂ ህይዎት'' በሚል መሪ ቃል ለ12ኛ ጊዜ በሚካሄደው ፌስቲቫል መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የሱዳን የልኡካን ቡድን አባላትን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የባህል ቡድን አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2009 የዓለም ባንክ በአገሪቷ በአጋርነት ለሚያከናውናቸው የተለያዩ የልማት ሥራዎች የሚውል የ4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዓለም ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ  ክሪስታሊና ጂኦርጂቫ ጋር ተወያይተዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ   ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከድህነት ለማላቀቅ ከዓለም ባንክ ጋር በቀጣይ ሦስት ዓመታት በአጋርነት ለምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች የሚውል የ4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ድጋፉ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ ለተፋሰስ ልማት፣ ለሴቶች ሥራ ፈጠራና ለሴፍቲኔት ፕሮግራም እንደሚውልም ገልጸዋል።

በድህነት ቅነሳና በሥራ ፈጠራ ላይ የተሰራውን ሥራ አድንቀው በአገሪቷ ያለውን እምቅ የፈጠራ አቅም መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በተለይም በሴፍትኔት ፕሮግራም እየተከናወነ ያለው ተግባር ዜጎች ከድርቅ እንዲወጡ ብቻ ሳይሆን ህይወታቸው በዘላቂነት እንዲቀየርና እንዲሻሻል ማድረግ መቻሉ የሚደነቅ እንደሆነም ነው የገለፁት።

በቀጣይም የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በጋራ ለመከወን ምክክር እየተደረገ መሆኑንና መግባባት ላይ ሲደረስ የድጋፉ መጠን ሊጨምር እንደሚችል አስታውቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው አገሪቷ ድህንትን ለማሸነፍና መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት ከዓለም ባንክ ጋር መስራቷ ለውጥ ማምጣቱንና ድጋፉ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በሴቶች ተጠቃሚነት፣ በስራ ፈጠራ፣ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲሁም በሴፍትኔት ፕሮግራም የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተናገሩት።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ ግንቦት 9/2009 በሁለተኛው ዙር መስኖ ልማት 12 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የምስራቅ ሸዋ ዞን መስኖ ልማት ባለሥልጣን ገለጸ።

የባለሥልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ሚደቅሳ የመስኖ ልማቱ ስራ እየተካሄደ ያለው በዞኑ 10 ወረዳዎች ውስጥ ነው።

የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ፣  ዘመናዊና  ባህላዊ መስኖ እንዲሁም  ኩሬና በእጅ በሚሰሩ የጉድጓድ ውሃ በመጠቀም 57 ሺህ ሔክታር መሬት እየለማ ይገኛል።

ከሚለማው መሬት 90 በመቶ  ቲማቲም፣ቀይ ሽንኩርት፣ቃሪያ፣ሃባብ፣ ፎሶሊያና ጥቅል ጎመን ሲሆን ቀሪው በጥራጥሬ፣ቦቆሎና ስንዴ ሰብል የተሸፈነ ነው።

በልማቱ ላይ 47 ሺህ 439 አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን ከመካከላቸውም  8 ሺህ 287 ሴቶች ናቸው።

አርሶ አደሮቹ ጥራት ያለው ምርት አምርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በየደረጃው የተመደቡ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች በአቅራቢያቸው የሙያ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውንም  አቶ ጌትነት ጠቅሰዋል።

ከመስኖ ልማቱም 12 ሚሊዮን ኩንታል  ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል።

ስራ አስኪያጁ እንዳመለከቱት በምስራቅ ሸዋ በብዛት ለሚመረተው የአትክልት ምርት  በአፋጣኝ ገበያ ማግኘት ካልተቻለ በቀላሉ ለብልሽት ተዳርጎ በአምራቹ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቷል።

እስከ አሁንም  በኦሮሚያ፣ትግራይ፣ሐረር፣ሶማሌና አፋር ክልል ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣መሰረታዊ ኀብረት ስራ ማህበራትና ከባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ዩኒዬን ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

በዞኑ አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ የዶድቻ መስኖ ፕሮጀክት ተጠቃሚዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ አዩብ በዳሶ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት መንግስት በገነባው ዘመናዊ መስኖ ፕሮጀክት 164 የማህበሩ አባላት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የማህበሩ አባላት በዘንድሮ የመጀመሪያው ዙር መስኖ በ67 ሄክታር መሬት ላይ ፎስሊያ፣ቲማቲም፣ቀይ ሽንኩርትና ጥቅል ጎመን  በማልማት 8 ሺህ 556 ኩንታል ምርት አግኝተዋል፡፡

ምርቱን ለመቂ ባቱ የገበሬዎች ኀብረት ሥራ ዩኒዬንና ለነጋዴዎች በማስረከብ ባገኙት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በ1994 ዓ.ም 119 አባላትን በማቀፍ  በ50 ሺህ ብር ካፒታል የተመሰረተው ማህበሩ ዛሬ ላይ ካፒታሉን ወደ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር አድርሷል።

እንደ ሊቀመንበሩ ገለፃ የአባላቱም ዓመታዊ ገቢ ከ100 ሺህ እስከ 150 ሺህ ብር ነው።

በምስራቅ ሸዋ ዞን  በመጀመሪያው ዙር 75 ሺህ ሄክታር መሬትን በመስኖ በማልማት ከ16 ነጥብ  ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የዞኑ  መስኖ ልማት ባለሥልጣን አመልክቷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር ግንቦት 9/2009 በአማራ ክልል አንዳንድ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በተጭበረበረ የትምህርትና የመንጃ ፈቃድ ማስረጃዎች ቅጥር እንደሚፈጸም በጥናት ማረጋገጡን የክልሉ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ እውነቴ አለነ ለኢዜአ እንደገለጹት ኮሚሽኑ ከክልሉ ስቪል ሰርቪስ ቢሮ ጋር በመተባበር ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በናሙናነት በተመረጡ ተቋማት ጥናት አካሂዷል ።

ጥናቱም በባህር ዳር፣ ደብረታቦር፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ደብረማርቆስ፣ ደብረብርሃንና ቋሪት ከተሞች በሚገኙ 22 መስሪያ ቤቶች በናሙናነት በመምረጥ  የተካሄደ ነው።

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለፃ ከተቋማቱ መካከል የገጠር መንገድ፣ የገቢዎች፣ የትራንስፖርት፣ የፍትህ፣ የትምህርት፣ የንግድና የጤና ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው ።

"በተቋማቱ በናሙናነት ከተፈተሹ 1ሺህ 936 የትምህርትና የመንጃ ፈቃድ ማስረጃዎች ውሰጥ 488ቱ ሀሰተኛና አጠራጣሪ ሆነው ተገኝተዋል " ብለዋል ።

ሀሰተኛና አጠራጣሪ ሆነው የተገኙት ማስረጃዎቹ የ13 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የቴክኒክና ሙያ፣የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች እንዲሁም የግል ጤና ሳይንስ ኮሌጆች ስም የቀረቡ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

"በሃሰተኛ ማስረጃዎቹ  እየተገለገሉ የሚገኙ ግለሰቦች በማይመጥናቸው ደረጃ በመቀመጥ የአሰራር ክፍተት ከመፍጠር በተጨማሪ የመንግስት ሀብትና ንብረት እንዲባክን ምክንያት መሆናቸውን ጥናቱ አመላክቷል " ብለዋል ።

በቀጣይ ጥናቱን መሰረት በማድረግ በሁሉም የመንግስት ተቋማት የቅጥር ማስረጃዎችን በመፈተሽ በህጋዊ አግባብ እርምጃ ለማስወሰድ አቅጣጫ መያዙንም  አቶ እውነቴ አስታውቀዋል ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ለኮሚሽኑ ቀርበው ምርመራና ክስ ከተመሰረተባቸው የሙስ ወንጀሎች ውስጥም 21 በመቶ የሚሆኑት ሃሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀትና መገልገል መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

አክሱም ግንቦት 9/2009 የግዕዝ ቋንቋን ትሩፋቶችና የቅዱስ ያሬድን ስራዎች ለዓለም ህዝብ ለማስተዋወቅ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር "የቅዱስ ያሬድ አስተዋፅኦ ለዘላቂ ቱሪዝም" በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው የሶስት ቀናት አውደ ጥናት በአክሱም ከተማ ዛሬ ተጀምሯል።

በአውደ-ጥናቱ ላይ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ ተወካይ አቶ አለማየሁ ጌታቸው እንደገለጹት መድረኩ የግዕዝ ቋንቋ ትሩፋቶችንና የቅዱስ ያሬድን ስራዎች ለዓለም የሚያስተዋውቁ ጥናቶች የሚቀርቡበት ነው።

"በውይይቱም ላይ በሚገኝ ፍሬ ሃሳብ ተደግፈን ሀገራችንና ህዝባችን በአለም አቀፍ ደረጃ  ተገቢ ስፍራና ጠቀሜታ  እንድታገኝ መስራት አለብን" ብለዋል።

ሚኒስቴር መሰሪያ ቤቱ ተልእኮውን ለማሳካት የማሰፈጸሚያ ስልቶችን እየከለሰ እንደሚገኝ ተናግረው የባህል ፖሊሲው በቅርቡ ተሻሽሎ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም አስረድተዋል።

በቅርቡ የሚጸቅደው የፊልምና የቋንቋ ፖሊሲና በሂደት ላይ ያሉ ሌሎች የማስፈጸሚያ ስልቶችን በመጠቀም የዘርፉ ልማት ውጤታማ እንዲሆን የሁሉንም ጥረት እንደሚሻ ገልጸዋል።

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጸሃየ አሰመላሽ በበኩላቸው፣ "አውደ ጥናቱ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ያበረከተውን ድንቅ ስራ ለዘላቂ የቱሪዝም ልማት እንዲውል የጋራ  መግባባት በመድረስ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው" ብለዋል።

ስራዎቹ የማይዳሰሱና በአንደበት የሚገለጹ እንደመሆናቸው ለታሪኩ ተገቢውን ትኩረት ሳይሰጠውና በተፈለገው መጠን ሳይተዋወቅ መቆየቱንም ዶክተር ጸሐዬ አስረድተዋል።

"ቅዱስ ያሬድ የሰራውን ያህል ክብር አልተሰጠውም" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ሰራዎቹ ተጠንተው በሰነድ እንዲያዙና በቅርስነት እንዲመዘገቡ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

በዜማ ድርሰት፤ በግዕዝ ስነ-ፅሑፍና ድርሰት ባበረከተው አስተዋፅኦ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአለምም ቀዳሚ መሆኑን ገልጸው "ዜማውና የዜማ መሳሪያዎቹ በአለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ማድረግ ይጠበቃል" ብለዋል።

ቅዱሰ ያሬድ የተወለደበትን 1ሺህ 504ኛ ዓመት አስመልክቶ በተዘጋጀው አውደ-ጥናት ላይ እሱ ለኢትዮጵያና ለዓለም ህዝብ ባበረከታቸው ስራዎች ዙሪያ ከአዲስ አበባና ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚካሔድባቸው ይጠበቃል።

በአውደ ጥናቱ ላይ 500 የሚጠጉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን፣የሃይማኖት መሪዎች፣ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ተወካዮችና የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2009 በአማራ ክልል ለሰባት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የትራኮማ መድኃኒት እደላና የሕክምና ድጋፍ መርኃ ግብር ተጀመረ።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የላየንስ ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ክለብና የካርተር ሴንተር ሳይት ፈርስት ኢኒሼቲቭ የልዑካን ቡድን አባላትን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።

18ኛው የትራኮማ መከላከል ዘመቻ መርኃ ግብር ዛሬ በላሊበላ የተጀመረ ሲሆን ላየንስ ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ክለብና ካርተር ሴንተር ሳይት ፈርስት ኢኒሼቲቭ በተሰኙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የጋራ ድጋፍ ነው የሚካሄደው።

የትራኮማ በሽታ መከላከል ዘመቻው በአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ዋግ ኽምራ፣ ሰሜን ሸዋና ኦሮሚያ ልዩ ዞን በሚገኙ 61 ወረዳዎች በ1 ሺህ 330 ቀበሌዎች ለሚገኙ ዜጎች የመድሃኒት ዕደላና ተያያዥ ህክምና ይሰጣል::
በላየንስ ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ክለብ የአፍሪካ ባለአደራ ቦርድ ተወካይ የዓለም ሎሬት ዶክተር ጥበበ የማነብርሃን እንደተናገሩት በዋነኛነት የትራኮማ በሽታ መከላከያ መድሃኒት ዕደላና ብርሃናቸውን ላጡ የቀዶ ሕክምና ይሰጣል።

መርሃ ግብሩ ስለ በሽታው ምንነትና ጉዳቱ ግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችንም ያካትታል።

ላየንስ ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ክለብ ከትራኮማ በተጨማሪ በጊኒዎርም፣ በዝሆኔና ፎከት ወይም ሪቨር ብላይንድነስ በሽታዎችን እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ለማጥፋት የሚሰራ ተቋም ነው።

ፕሮግራሙ ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ በአማራ ክልል ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት የትራኮማ በሽታ ስርጭትን ከ62 በመቶ ወደ 28 በመቶ ዝቅ ማድረግ ሲቻል ከ15 ዓመት በላይ በሆኑት ደግሞ በ25 በመቶ መቀነስ ተችሏል።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው ተቋሙ የትራኮማ በሽታን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ስራው ድሃውን ማኅበረሰብ ያማከለ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጠውና መንግስትም ጥረቱን እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።

ፕሬዚዳንቱ የላየንስ ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን አባል በመሆናቸው ተግባሩን በግላቸውም እንደሚደግፉ መግለፃቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዚዳንቱ የኮሚዩኒኬሽንና ፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

 አዲስ አበባ ግንቦት 9/2009 ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት የሚወዳደሩት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንዲመረጡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የጤና ማህበራት ድጋፋቸውን እየገለጹ ነው።

ማህበራቱ በኢትዮጵያ ህክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ገመቺስ ማሞ በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ዶክተር ቴድሮስ ቢመረጡ ለዓለም ጤና የተሻለ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

ዶክተር ቴድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት አገሪቷን የሚሌኒየሙን የልማት ግብ በጊዜው ማሳካት ከቻሉ ጥቂት አገራት አንዷ እንድትሆን አስችለዋታል ነው ያሉት።

በወቅቱ የህፃናት ሞትን በሁለት ሦስተኛ፣ በወባ የሚከሰት ሞትን በ75 በመቶ፣ በኤች.አይ.ቪ የሚሞቱትን በ70 በመቶ፣ በሳንባ ነቀርሳ የሚሞቱትንም በ64 በመቶ መቀነስ እንዳስቻሉም ነው የተናገሩት።

በአገሪቷ 3 ሺህ 500 የጤና ማዕከላትና 16 ሺህ የጤና ኬላዎችን በማቋቋም የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ መቻላቸውንና የጤና ባለሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላትን ከሦስት ወደ 33 እንዳሳደጉ አስታውሰዋል።

16 ሺህ 500 የነበሩትን የጤና ባለሙያዎች በሰባት እጥፍ ማሳደግ መቻላቸው የጤናውን ዘርፍ የመምራት አቅማቸውን የሚያሳይ በመሆኑ በዋና ዳይሬክተርነት ቢመረጡ ይህንን ልምዳቸውን እንደሚጠቀሙ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ዶክተር ቴድሮስ በተለይ በሚታወቁበት የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም 38 ሺህ ባለሙያዎችን አሰልጥነው ወደ ስራ በማስገባት የጤና አጠባበቅ ስርዓቱ ማህበረሰባዊ መሰረት እንዲኖረው ማድረጋቸውንና ለጤና መድህን ሽፋን መጀመር መሰረት መጣላቸውን አውስተዋል።

ግሎባል ፈንድን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትን የመሩት ዶክተር ቴድሮስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅትም በአፍሪካ ኅብረት በኩል ኢቦላን ለመቋቋም በተደረገው ርብርብ ኢትዮጵያ የበኩሏን ጉልህ አስተዋፅኦ እንድታበረክት አድርገዋል።

በመሆኑም ዶክተር ቴድሮስ ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ቢመረጡ ከሌሎቹ ዕጩዎች የተሻለ ልምድ ያላቸው ስለመሆናቸው ዶክተር ገመቺስ የባለሙያ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።  

Published in ማህበራዊ

ማይጨው ግንቦት 9/2009 በተመቻቸላቸው የብድር አገልግሎትና የስልጠና ድጋፍ  በገቢ ማስገኛ ስራዎች ተሰማርተው እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለመለወጥ መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገራው የደቡባዊ ትግራይ ወጣቶች ገለጹ።

የምልመላ፣የስልጠናና የእቅድ ዝግጅቱ ጊዜ ቢወስድም የብድር ገንዘቡ በመቅረቡ ወጣቶቹ ወደ ስራ እንዲገቡ እንደሚደረግ የዞኑ ንግድና ከተማ ልማት መምሪያ አስታውቋል።

የማይጨው ከተማ ነዋሪው ወጣት ሙሉብርሃን ሐለፎም እንደገለጸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ የቤተሰቡን አነስተኛ የንግድ ስራ ሲያግዝ ቆይቷል።

አሁን ግን በማይጨው ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በፕሪካስት ቢም ማምረት ስልጠና አብረውት ከወሰዱ 18 ጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ በራያ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ላይ ለመሳተፍ የብድር አገልግሎት እየጠበቀ መሆኑን ገልጿል።

የኮረም ከተማ ነዋሪው ወጣት ዘነበ ታደሰ በበኩሉ ባለፈው ዓመት በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪ ቢያገኝም ስራ ባለማግኘቱ ተቸግሮ እንደቆየ ተናግሯል።

በተመቻቸላቸው የብድር አገልግሎት ከጓደኞቹ ጋር በመደራጀት በኮረም ቴክኒክ ኮሌጅ  ባገኙት የብሎኬት ማምረት ስልጠና በመታገዝ ወደ ስራ ለመግባት መዘጋጀታቸውን ገልጿል

የማይጨው ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት የዕቅድና ፕሮጀክት ክትትል ባለሙያ አቶ አሰፋ አርቤ እንዳሉት፣ በከተማው በሁለት ዙሮች በማህበር የተደራጁ 509 ስራ አጥ ወጣቶች በአምስት አይነት የሙያ መስኮች ሰልጥነው የብድር ተጠቃሚ ለመሆን ተዘጋጅተዋል።

የዞኑ ንግድና ከተማ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስመላሽ ረዳ በበኩላቸው እንደገለጹት በዞኑ ሰባት ከተሞች ከ6ሺህ 500 በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እስከ አሁን በማህበር ተደራጅተው የስራ ዕቅድ ያቀረቡ ከ2ሺህ 800 በላይ ወጣቶች በአምስት የሙያ ዘርፍ ሰልጥነው ለስራ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ከምልመላ ጀምሮ፣በስልጠናና በማደራጀት ሒደት መዘግየት ቢታይበትም ወጣቶቹ ከተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ እና ከደደቢት ብድርና ቁጠባ ተቋም ለዞኑ የተመደበውን 304 ሚሊዮን ብር በመጠቀም ወደ ስራ ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

ወጣቶቹ  ለሚሰማሩበት የስራ ዘርፍም በቡድን ዋስትና ተጠቅመው እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የሚደርስ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

ቀደም ባሉት ዓመታት በዞኑ በተፈጠረላቸው የስራ እድል ከ18 ሺህ በላይ ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ተደራጅተው በመስራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ። 

Published in ኢኮኖሚ

ድሬዳዋ ግንቦት 9/2009 የአካባቢያቸውን ልማት ከማጠናከሩ በተጓዳኝ ክራይ ሰብሳቢነትንና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል የድርሻቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለፁጹ፡፡

ሰባተኛው የፍትህ ሣምንት በድሬደዋ አስተዳደር ትናንት በተከበረበት ወቅት ተሳታፊ ነዋሪዎች እንደገለጹት  ከፍትህ አካላት ጋር ተቀናጅተው  የአካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ  የማስከበር ተግባራትን አጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል የሀገር ሽማግሌው አቶ ዜና በየነ በሰጡት አስተያየት "የህግ የበላይነት መስፈን  ለሰላም፣ለልማትና ለሀገር ዘላቂ እድገት መሠረታዊ በመሆኑ የፍትህ አካላት ለዚህ  ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል" ብለዋል፡፡

ቤተሰብ ፣ማህበረሰብና የፍትህ አካላት እርስ በርስ ከተባበሩና ለአንድ ተልዕኮ ከተንቀሳቀሱ  አፍራሽ ድርጊቶች ቦታ እንደማይኖራቸው  የተናገሩት ደግሞ አባገዳ አብዱልማክ ዩኒስ ናቸው፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የኃይማኖት ተቋማት ፎረም ሰብሳቢ ሊቀብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው በበኩላቸው "በየደረጃው በሚገኙ የፍትህ ተቋማትም ሆነ በዘርፍ መስሪያ ቤቶች ለተነሱ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት ይገባል "ብለዋል፡፡

በጥልቅ ተሃድሶ ላይ ለህዝብ ቃል የተገቡ ጉዳዮች በቃል መቅረት እንደሌለባቸው ጠቁመው ሆኖም  በፍርድ ቤቶች አካባቢ  በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻሎች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡

አቶ አብዱልአዚዝ ያሲን የተባሉ ነዋሪ እንዳሉት በየዓመት የፍትህ ሣምንትን ጠብቆ ከህብረተሰቡ ጋር መወያየት ብቻ ሣይሆን በየቀበሌው መድረኮች በመፍጠር ህዝቡ ልማቱና ሠላምን  እንዲጠበቅ መደገፍ ተገቢ ነው፡፡

" ወጣቱ ሰላምና ልማትን የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፤ከፍትህ አካላት ጋር በመሆን የኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል የበኩሌን ጥረት አደርጋለሁ " ያለው ደግሞ ወጣት ሱሌይማን አሊ ነው፡፡

የአካባቢያቸውን ሰላምና ልማት ከማጠናከሩ ጎን ለጎን  ክራይ ሰብሳቢነትንና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አብደላ አህመድ "በሀገሪቱ እየተመዘገቡ የሚገኘው ፈጣን ልማት ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ የፍትህ አካላት ለህግ የበላይነት መከበር ተግተው መስራት ይጠበቅባቸዋል "ብለዋል፡፡

የፍትህ አካላትና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና የመልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ በላቸው አቺሶ በአንዳንድ የፍትህ አካላት ዘንድ የሚስተዋሉ የሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለማጥራት  የተጀመሩ ሥራዎች ስኬታማ የሚሆኑት ህብረተሰቡ የራስን ኃላፊነት ሲወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፍትህ ሣምንት በዓሉ በድሬደዋ  የተከበረው  በህዝባዊ ውይይት ፣  በፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ፣ በተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድሮች ሲሆን የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የአስተዳደሩ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2009 አገር አቀፍ የስፖርት ጨዋታዎች ደረጃቸውን ጠብቀው ባለመካሄዳቸው ተተኪ ስፖርተኞች ማፍራት እንዳልቻለ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ ለስፖርት ማህበራትና ለክልሎች የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊዎች በአገር አቀፍ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ዙሪያ ያካሄደውን መነሻ ጥናት አቅርቧል።

የጥናቱ አቅራቢ አቶ አስመራ ግዛው በአገሪቱ የሚካሄዱ የስፖርት ጨዋታዎች የሚፈለገውን ውጤት ላለመገኘቱ ምክንያቶች ያሏቸውን ዘርዝረዋል።

ከምክንያቶቹ የመጀመሪያው ደረጃቸውን የጠበቁ አለመሆናቸው እንደሆነ ነው የተናገሩት።

የአዘጋጅ ክልልና የስፖርት ማህበራት አለመቀናጀት፣ ከአዘጋጁ በኩል ግልጽ የኮሚቴ አደረጃጀት አለመኖርና የአገር አቀፍ ውድድሮችን ዓላማ በግልጽ አለመረዳትም እንዲሁ።

በተለይም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ የታዳጊዎች የምዘና ውድድሮች ላይ ቀድመው ያልሰሩትን የቤት ስራ ውጤት በአቋራጭ ለማግኘት መሞከር ለውጤቱ መቀነስ በጥናቱ የተለዩ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው።

በቀጣይ ደረጃውን የጠበቀ አገር አቀፍ ስፖርታዊ ጨዋታ ለማዘጋጀት ከእስካሁኑ አሰራር ወጥተው የራሳቸውን ማህበር ወይም ፌደሬሽን ማቋቋም እንደሚገባቸው ተገልጿል።

የፋይናንስ አቅማቸውን ለማጎልበት የስፖንሰር፣ የምስል መብት፣ የትኬት ሽያጭና ሌሎች የገቢ ምንጮችን በመጠቀም ከመንግስት ጥገኝነት መላቀቅ እንዳለባቸው አቶ አስመራ ጠቁመዋል።

በመላ ኢትዮጵያና በአገር አቀፍ የተማሪዎች ጨዋታዎች፤ በታዳጊ ወጣቶች ተሳትፎና አገር አቀፍ የሴቶች ተሳትፎ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ የሚያደርጋቸውን ዝግጅት ማድረግ አለባቸውም ብለዋል፡፡ 

በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ የመነሻ ጥናቱ በስፖርት ማህበራት ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ውይይት ከተደረገበት በኋላ ወደ ስራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዛሬ የተጀመረው የስፖርት ተሳትፎ የውድድር አሰራር ስርዓት አተገባበር ለ3 ቀናት የሚቆይ ሲሆን በማዘውተሪያ ቦታዎች ደረጃ አመዳደብ ደንብ፣ በስፖርት አመራርነት የሴቶች ሚናና የታዳጊ ወጣቶች ስልጠና አፈጻጻም ላይ ውይይት ይካሄዳል።

Published in ስፖርት
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን