አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Tuesday, 16 May 2017

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2009 የመንግስታቱ ድርጅት የሠላም ማስከበር ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሃፊ አተል ከሃር ኢትዮጵያ በሠላም ማስከበር ተልዕኮ ላበረከተችው አስተዋፅኦ ምስጋና አቀረቡ።

ምክትል ዋና ፀሃፊው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ኃይሎች በዓለም ሠላምና መረጋጋት እንዲኖር ለከፈሉት መስዋዕትነት ምስጋና ማቅረብ የውይይቱ አጀንዳ እንደነበር ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነቷ እያደረገችው ያለው አስተዋጽኦም ሌላው የውይይቱ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ሂሩት ዘመነም ኢትዮጵያ በዓለም ሠላምና መረጋጋት እንዲኖር ከመንግስታቱ ድርጅት ጋር ለመስራት ቁርጠኛ አቋም እንዳላት መግለጻቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። 

በሶማሊያ ሠላምና መረጋጋት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ከአገሪቷ መከላከያ ኃይል፣ ፖሊስና የፀጥታ መዋቅር ጋር ተባብራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸውንም አቶ መለስ አብራርተዋል።

ምክትል ዋና ፀሃፊው በበኩላቸው ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት ሠላም ማስከበር ተልዕኮ የተጫወተችው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በሌሎች አገራት ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ኢትዮጵያዊያን ሠላም አስከባሪ ኃይሎች ለከፈሉት መስዋዕትነትም ምስጋና አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮችን በማሰማራት ቀዳሚ ከሆኑት አገራት መካከል ነች።

በአሁኑ ወቅትም በመንግስታቱ ድርጅት ስር በሚገኙ የተለያዩ የሠላም አስከባሪ ዕዞች ከስምንት ሺህ በላይ ሠላም አስከባሪ ወታደሮችን አሰማርታለች።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2009 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሦስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ብር አበረከተ።

ፌዴሬሽኑ በቀድሞ ሥራ አስፈጻሚ አባላት አማካኝነት በተለያዩ ጊዜያት በተዘጋጁ የገቢ ማሰባሰቢያ ህዝባዊ ሩጫ የተገኘውን ገንዘብ  ነው ዛሬ ያስረከበው።

ቼኩን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ተረክቧል።

ለዚህ አንዱ ተጠቃሽ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ግንባታው እየተካሄደበት ባለበት አካባቢ በተደረገው ሁሉን ያሳተፈ የሩጫ ውድድርና በተለይ ደግሞ ለሴቶች በተዘጋጀ ሩጫ የተሰበሰበ መሆኑ ነው።

የርክክቡ ስነ ስርዓት የተካሄደው ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም 46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተጀመረበት ወቅት ነው።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ ቼኩን ባስረከበበት ወቅት እንደገለጸው፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር እስከሚደርስ ፌዴሬሽኑ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ የቼክ ስጦታውን ተቀብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ሮማን እንደገለጹት ፤ ፌዴሬሽኑ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል።

በፌዴሬሽኑ ስም ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል 70 ሚሊዮን ብር ገቢ መደረጉን ያስተዋሱት ወይዘሮ ሮማን፤ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል። 

ፌዴሬሽኑ ለገቢ ማሰባሰቢያ የሚካሄዱ ህዝባዊ ሩጫዎችን በማስተባበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑ ታውቋል።

Published in ኢኮኖሚ

ጊምቢ ግንቦት 8/2009 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ  በምዕራብ ወለጋ ዞን  አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።

ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ የሚውል በዞኑ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ተለግሷል፡፡

በዞኑ የጊምቢ ከተማ ነዋሪ አቶ መንግስቱ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት  የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ለመጎብኘት በርካታ እንግዶች አካባቢውን አቋርጠው ሲልያልፉ  እግረ መንገዳቸውን የንግድ ልውውጥ እንዲያካሄዱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

ይህም ለከተማው እድገት መፋጠን እገዛ ማድረጉን ጠቁመው  በእሳቸው በኩልም ለግድቡ ግንባታ እስካሁን  የ7 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ ማከናወናቸውንና  እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

አቶ  ቸሩ ጫሊ የተባሉ የነጆ ከተማ ነዋሪም  ባለፈው ዓመት በራሳቸውና በልጆቻቸው ስም የ22ሺህ ብር ቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን ጠቅሰው የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ወዲህ  በከተማው የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እንቅስቃሴ እየተሟሟቀ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበር ተደራጅተው በመስራት ከሚያገኙት ገቢ በማህበራቸው ስም ከ10 ሺህ ብር በላይ ቦንድ መግዛታቸውን የተናገረው ደግሞ  ወጣት ማርቆስ አለማየሁ ነው፡፡  

የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስም  ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጧል።

የዞኑ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ አብዮት ዳንኤል ባለፈው አንድ ዓመት ከዞኑ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ 30 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

እስካሁንም ከዞኑ የመንግስት ሰራተኞችና ከተለያዩ  የህብረተሰብ ክፍሎች ከ100ሚሊየን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ መለገሱን አመልክተዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2009 ግንባታቸው የተጓተቱ ሜጋ የመስኖ ፕሮጀክቶች በአፋጣኝ እንዲጠናቀቁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ። 

ምክር ቤቱ ማሳሰቢያውን የሰጠው ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴርን የበጀት ዓመቱን የ10 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም አድምጦ ነው። 

የአርጆ ዴዴሳ፣ የመቂ ዝዋይ፣ የከሰም ተንዳሆና የአድአ በቾ የመስኖ ልማትና የከርሰ ምድር ፕሮጀክቶች ግንባታቸው በመጓተቱ ተጨማሪ ወጪ እየጠየቁ መሆኑንም ገምግሟል። 

በምክር ቤቱ የተፈጥሮ ኃብት ልማትና ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ጀምበርነሽ ክንፈ እንዳሉት በ2006 ዓ.ም መጠናቀቅ የነበረባቸው ሜጋ የመስኖ ፕሮጀክቶች አልተጠናቀቁም።

"ይህም በአገሪቱ ሌሎች ፕሮጀክቶችን መገንባት የሚያስችል ተጨማሪ ወጪ እንዲወጣ እያደረገ ነው" ብለዋል።   

"ፕሮጀክቶቹ በጊዜው ተጠናቀው ቢሆን ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ እድል ከመፍጠር በሻጋር አገሪቷ ከዝናብ ጥገኝነት ለመላቀቅ የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ ትልቅ ፋይዳ ይኖራቸው ነበር" ነው ያሉት።

የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለማምረት የተያዘውን ግብ ለማሳካት የተጓተቱ ሜጋ የመስኖ ፕሮጀክቶች ፈጥነው መጠናቀቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።  

በድሬድዋ፣ ደምቢ ዶሎና ወላይታ ሶዶ ከተሞች እየተገነቡ ያሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለኀብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ባለፉት ዓመታት የመስኖ ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ፍጥነት አዝጋሚ እንደነበር ሲገመገም መቆየቱን አንስተዋል። 

ለፕሮጀክቶቹ መጓተት የፋይናንስ እጥረት፣ የአቅም ውስንነት፣ የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያና በሚሰፍሩባቸው አካባቢዎች የመሰረተ ልማት በወቅቱ አለመሟላት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን ሥራዎች የጥራት ጉድለትም ከምክንያቶቹ መካከል እንደሆኑ አመልክተዋል። 

"ችግሩን ለመፍታት በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከግንባታ በፊት የጥናት ዲዛይንና ሰነዶች ተደጋግመው እንዲፈተሹ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ተቋራጮችና አማካሪ ድርጅቶችም አስፈላጊውን ግብዓት በውሉ መሰረት እንዲያሟሉና በተቻለ መጠን ቀንና ሌሊት በፈረቃ እንዲሰሩ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በውሉ መሰረት በማይሰሩ ተቋራጮችና የፕሮጀክት ኃላፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ ለልማት ተነሺዎች የሚከፈለው ካሳ ወቅቱን የጠበቀ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የተሻለ ሥራ ተከናውኗል።

በቀጣይ የሚተገበሩ ትልልቅ የውሃ፣ የመስኖና የኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ኃብት በመፈለጋቸው ከነባሩ የበጀት ድልድል በበለጠ መጠን ቅድሚያ ትኩረት እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል ሚኒስትሩ።  

ምክር ቤቱ ያነሳቸውን የፕሮጀክቶች መጓተት ችግሮች ለመቅረፍ ሚኒስቴሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ግንቦት 8/2009 በሰሜናዊ ኮንጎ ዳርቻዎች የኢቦላ ወረርሽኝ መቀስቀሱን ለማረጋገጥ   በተደረገ ምርምራ ቫይረሱ በሁለት ሰዎች ላይ መገኘቱን  የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡

በበሽታው ተጠርጥረው ምርመራ ከተደረገላቸው  20 ሰዎች መካከል ነው ሁለቱ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው፡፡

እኤአ ከ2013-2016 በምዕራብ አፍሪካ የተቀሰቀሰው ኢቦላ የ11 ሺህ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ይታወሳል፡፡

ኮንጎ  ለሰባት ጊዜያት ያህል አነስተኛ የኢቦላ ወረርሽኞችን ማስተናገዷን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

እስካሁን ከመዲናዋ ኪኒሻሳ  አንድ ሺህ ሶስት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዋ ባስ-ኡዌሌ ግዛት የሶስት ዜጎቿን ህይወት በወረርሽኑ ማጣቷም   ተመልክቷል፡፡

በሰውነት ፈሳሾች ለሚሰራጨው ቫይረስ ራሱን የቻለ ህክምና/መድሃኒት ባይገኝለትም በቅርቡ በምርምር የተገኘው መከላከያ ክትባት አበረታች ውጤት ታይቶበታል፡፡

የምርት መጠኑ አናሳ መሆን ግን ስጋት ፈጥሯል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2009 በፈጻሚዎችና አመራሮች የተመዘበረ 96 ሺህ 200 ካሬ ሜትር መሬትና ከ105 ሚሊዮን ብር በላይ ማስመለሱን የኦሮሚያ ክልል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ100 ሺህ በላይ የፈጻሚና የመንግሥት ባለስልጣናትን ኃብት መዝግቤያለሁ ብሏል።

የኮሚሽኑን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም የተመለከተ መግለጫ የሰጡት ኮሚሽነር ሂሩት ቢረሳ እንደተናገሩት በአሰራር ግድፈት ጥቅም ላይ ሊውል የነበረ 30 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ማዳን ተችሏል።

በተመሳሳይ መልኩ ተገቢውን አሰራር ባልተከተለ ሁኔታ ሊወጣ የነበረ 51 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በተወሰደ የቅድመ መከላከል እርምጃ በማዳን ለመንግሥት ገቢ መደረጉንም ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።

በሙስና የተገኘ ሰባት ሚሊዮን ብር ደግሞ ከባንክ እንዳይንቀሳቀስ ነው የተደረገው።

እንደ ኮሚሽነር ሂሩት ገለጻ ከአነስተኛ እስከ ፎቅ የሚደርሱ 40 መኖሪያ ቤቶች ሲታገዱ በሙስና የተገኙ ስድስት ተሽከርካሪዎችም በኤግዚቢትነት ተይዘዋል።

ከጨረታ ሂደት ጋር የተያያዘ ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይም ከሙስና ማዳን ተችሏል።

በክልሉ የሙስና መረጃ ተገኝቶባቸው ጉዳያቸው በህግ እየታየ ከሚገኙ 600 ሰዎች መካከል ፅኑ የእስራት ቅጣት የተላለፈባቸው መኖራቸውን ፤ ከእነዚህ መካከልም የሦስት ከተሞች ከንቲባዎች እንደሚገኙበት ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።

ከጥልቅ ተሃድሶው በኋላ በተፈጠረው መነቃቃት የፀረ-ሙስና ስትራቴጂ ሰነድ ተዘጋጅቶ መተግበር በመጀመሩ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንደተቻለም አክለዋል።

በዚህም በህገ-ወጥ መንገድ የተወሰደ 96 ሺህ 200 ካሬ ሜትር መሬት እንዲመለስ መደረጉን ነው የገለጹት።

ኮሚሽኑ በቀጣይም በሌሎች የሙስና ተግባራት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።

ክልሉ የፀረ-ሙስና ትግሉን ለማጠናከርና በሕብረተሰቡ ዘንድ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ከቀበሌ እስከ ዞን  ከነገ ጀምሮ ለአንድ ሣምንት የሚቆይ ሕዝባዊ ውይይት ያካሂዳል።

በውይይት መድረኩ ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተሳታፊ እንደሚሆንም ይጠበቃል።     

Published in ማህበራዊ

ጎንደር ግንቦት 8/2009 በአትሌቲክሱ ዘርፍ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር የነበሩትን አቶ እንዳልክ ቀለመወርቅ ለመዘከር የተዘጋጀ የመታሰቢያ ሲፖዚየም ተካሄደ፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ትናንት በተካሄደው ሲምፖዚየም ላይ ኢንስትራክተር እንዳልክ ቀለመወርቅ በአትሌቲክሱ ዘርፍ የነበራቸውን አስተዋጽኦ የዳሰሰ ጽሁፍ በዩኒቨርሲቲው መምህር በዶክተር ሙሉቀን አዳነ ቀርቧል፡፡

አቶ እንዳልክ በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በስፖርት ትምህርት ተመረቀው ከ1981 ጀምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመምህርነትና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እስከ ጽህፈት ቤት ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡

ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት መጎልበትና አሰለጣጠን በሳይንሳዊ መንገድ እንዲመራ በማድረግ በኩል ፈር ቀዳጅ ተግባር ካከናወኑ የስፖርቱ ባለሙያዎች ግንባር ቀደም እንደሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ተመስገን ሃይሌ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲውን የስፖርት አካዳሚ በስማቸው ለመሰየም በትምህርት ክፍሉ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል አትሌቲክስ ፌደሬሽን የስራ አስፈጻሚ አባል ኮሚሽነር ሰይድ ሁሴን እንደተናገሩት ለስፖርቱ ማደግ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በክልልም ሆነ በብሄራዊ ደረጃ የመታሰቢያ ዝግጅት  እንዲደረግላቸው ፌዴሬሽኑ ተልእኮ ወስዶ ተገቢውን ስራ ያከናውናል፡፡

በመታሰቢያ ሲፖዚየሙ ላይ የስፖርት ባለሙያዎች የስፖርት አመራሮችና የስፖርት ቤተሰቦችን ጨምሮ አብሮ አደግ ጓደኞቻቸው ተካፋይ ሆነዋል፡፡

በመጪው እሁድ "ተተኪዎችን እናፍራ"  በሚል መሪ ሀሳብ የኢንስትራክተር እንዳልክን ህልፈት 10ኛ ዓመት የሚዘክር የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በጎንደር ከተማ እንደሚካሄድ አዘጋጅ ኮሚቴው በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

Published in ስፖርት

ቤጂንግ ግንቦት 8/2009 የቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር የታዳጊ አገራት የፀረ ድህነት ትግልን እንደሚደግፍ የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ቃል ገቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ 30 የሚጠጉ አገራት መሪዎች ዓለም አቀፍ ንግድና ኢኮኖሚን ለማጠናከር ያስችላል የተባለውን ባለ 18 ነጥብ የአቋም መግለጫ ይፋ አድርገዋል።

በፎረሙ አፍሪካ የቻይና ቁልፍ አጋር በሆኑት አገራት መሪዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝና በኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተወክላለች።

ቻይና ሁለተኛውን የቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2019 እንደምታስተናግድም ይፋ ሆኗል።

ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ቤጂንግ አቅራቢያ በሚገኘው ያንቺ ሐይቅ ሪዞርት የአገራት መሪዎች ያደረጉትን የክብ ጠረጴዛ ውይይት አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "ሁሉም አገራት በተለይም ታዳጊዎቹ ድህነትን በማጥፋት አቅጣጫና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማምጣት ረገድ አሁንም የጋራ ፈተና ተጋርጦባቸዋል" ብለዋል።

"ዘመኑ አገራት ለሠላም፣ ለልማትና ለትብብር አብረው የሚሰሩበት መልካም አጋጣሚ ነው" ሲሉም የዓለም አቀፋዊ ትብብርን አስፈላጊነት ተናግረዋል።

የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ታዳጊ አገራት ድህነትን ለመቀነስና ለማጥፋት የሚያደርጉትን ጥረት መልካም አጋጣሚ በመፍጠር የሚደግፍ እንደሚሆንም አረጋግጠዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የባህር በር የሌላቸውና በእድገት ወደኋላ የቀሩ አገራትና ትንንሽ የደሴት መንግስታት በቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም ኢኒሼቲቭ የተለየ ትኩረት የሚሰጣቸው ይሆናል ብለዋል።

ኢኒሼቲቩ የመንግስታቱ ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦች ማሳኪያ ስልት ከሆነው የአዲስ አበባ የድርጊት መርሃ ግብርና ከዓለምአቀፋዊ፣ አህጉራዊና ብሄራዊ ማዕቀፎች ጋር አጣጥሞ ገቢራዊ ማድረግ ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

የመንገድ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የወደቦች፣ የባህርና የሌሎች የውሃ መጓጓዣዎች፣ የአቪዬሽን፣ የኢነርጂ፣ የፋይበር ኦፕቲክ ዝርጋታ፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስፋፋትና እድገትን የሚደግፍ እንደሆነም አክለዋል።

በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ 60 አገራት የተካፈሉ ሲሆን ትብብሩን እንደ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት፣ የኢትዮ-ጅቡቲ አገር አቋራጭ የባቡር መስመርና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ላይ ያደረገ ነው።

በተጨማሪም የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር በትምህርት፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በጤና በምሁራን፣ በሚዲያ፣ በአቅም ግንባታና በሌሎችም ዘርፎች የጋራ ልውውጥ ይደረጋል ብለዋል።

በቅርቡም ኢትዮያ የአፍሪካ አገራትን ለማስተሳሰር የሚዘረጋው የብሮድባንድ ፋይበር ኦፕቲክ ማዕከል እንድትሆን መመረጧ የኢኒሼቲቩ ሌላው ገጽታ ነው።

በኢኒሼቲቩ ማዕቀፍ ዙሪያ ቻይና ከ68 አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በትብብር መስራት የሚያስችላት ስምምነት መፈራረሟን ፕሬዚዳንቱ ይፋ አድርገዋል።

ቻይና ለሁለት ቀናት ባስተናገደችው የቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የቱርኩ ጣይብ ኤርዶጋንና የፊሊፒንሱ ፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዲዮትሬት ተሳትፈዋል።

በአንፃሩ እንደ አሜሪካ ያሉ ምዕራባዊያን አገራትና ህንድ ፎረሙን የቻይናን የበላይነት የሚያነግስ ነው በሚል በስጋት እየተመለከቱት ነው።

Published in ፖለቲካ
Tuesday, 16 May 2017 20:45

አፉርታማን በወፍ በረር

                                              ሚፍታህ አህመድ /ጅማ ኢዜአ/

ጥንታዊው የአባጅፋር ቤተመንግስት ወደሚገኝበት ጅሬን ስንጓዝ ታሪካዊው የአፉርታማ መስጊድን እናገኛለን፡፡ መስጊዱን ታሪካዊ የሚያደረገው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የእስልምና፣ የእኩልነት፣ የአንድነትና የመቻቻል አስተምህሮት ማዕከል ከመሆኑም በላይ የሩቅ ተጓዥ ነጋዴዎች በስፋት የሚያርፉበት፤ በጥንት ጊዜ በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ መንደራ ተብሎ የሚጠራበት አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ጥንታዊና ህብራዊ  መስጊድ አፉርታማ በመባል ይታወቃል፡፡ አፉርታማ የኦሮምኛ ቃል ሲሆን ትርጎሚውም አርባዎቹ እንደማለት ነው፡፡

 40ዎቹ እነማን ናቸው?

ከመስጊዱ አጠገብ ታሪክን የሚናገር  ጥንታዊ የመካነ-መቃብር ስፍራ ይገኛል፡፡ በስፍራውም ንጉስ አባቦቃ አሊይ፣ ንጉስ አባጉቡልና ንጉስ አባ ጅፋር፣ የአባ ጅፋር ቤተሰቦች ፣የአባጅፋር አገልጋዮች እንዲሁም ከሃረር፣ ከጎንደር፣ ከወሎ፣ ከትግራይ፣ ከጉራጌና፣  ከተለያዩ የኢትዮጵያ አከባቢዎች በሚከተሉት ሃይማኖት ምክንያት ህልውናቸው አደጋ ላይ በመውደቁ የተነሳ የሰላም አየር ወደሚነፍስበት የአባጅፍር አገር አርባ  ኡለማዎች(የእስልምና ሃይማኖት ልሂቃን) ይሰደዳሉ፡፡

ኡለማዎችም ያገኙትን ሰላም በመጠቀም ኃይማኖታቸውን በተሰደዱበት አገር ጅማ ማስተማር፣  ማስፋፋትና ማሳደግ የቻሉ መሆኑ በስፋት ይነገራል፡፡

ስለአፉርታማ ስያሜ

ስለ አፉርታማ ስያሜ የሚቀራረቡ ግን የተለያዩ አስተያየቶች በአከባቢው እድሜ ጠገብ አዛውቶች ይነገራል፡፡ አርባዎች ኡለማዎች በህልፈታቸው ጊዜ ግበአተ መሬታቸው የሚፈጸመው በአንድ አከባቢ ሲሆን ቦታውም አፉርተማ መቃብር በመባል ይታወቃል፡፡ በመካነ መቃብሩ ስፍራ አጠገብ የሚገኘውን ታሪካዊው መስጊድ ደግሞ የአከባቢው ነዋሪዎች  አፉርተማ መስጊድ በማለት ይጠሩታል፡፡

በሂርማታ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አብዱልሰመድ የሱፍ የአፉርታማ መሰጊድ ስያሜ ንጉስ አባጅፋር ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የእስልምና ሃይማኖት አዋቂዎችን በማሰባሰብ በጅሬን ባሰሩት መስጊድ ውስጥ በሳምንት አንድ ቀን  የጁመዓ ሶላት ሲሰገድ ከአርባ ሰው በታች እንዳይሆን በማሳብ ለኡለማዎቹ ሁሉን ነገር አሟልተውላቸው በመስጊዱ ውስጥ ሀይማኖታዊ ስርዓታቸውን እየፈጸሙ እንዲኖሩ ከማድረጋቸው ጋር ተያይዞ የተሰጠ ስያሚ ነው ይላሉ፡፡

በጣሊያን ወረራ ጊዜ ብስክሌት በመጋለብ አብዛኛውን ጊዜዬን አሳልፍ ነበር ያሉት አቶ አባፊራ አባዋሪ በወቅቱ የነበሩትን ኡለማዎችን ያስታውሱ እንደነበር ይናገራሉ፡፡

በወቅቱ የነበሩት ሰዎች የጅማ ንጉስ አባጅፋር ያደረጉላቸው እንክብካቤ እንዳስደሳታቸውና በደል የማይፈጽሙ ፍትህ አዋቂ እንደነበሩ ከእንግዳዎች አንደበት እሰማ ነበር ይላሉ፡፡ ኡለማዎቹ በስደት ሳይሆን በአባጅፋር ጥሪ የመጡ ናቸው ፡፡

ከሁለት ሜትር በላይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አባጅፋር፣ የንግስና ካባቸው  ግርማ ሞገስ ያለው፣ የንግስና ክብር የተሰጣቸው፣  የንግስና አርማቸው ደማቅ፣  እንግዳ አክባሪ፣ ቃላቸው አስታሪቂ፣ እንደሆነ በብላቴና እድሜቸው በእንግድነት ከመጡ ኡለማዎች  ይሰሙ እንደነበር ይናገራሉ እድሜ ጠገቡ አዛውንት፡፡

በአሁኑ ሰአት የመስጊዱ አዛን አውጪ (ሙአዚን) ጀማል አባተማም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የመጡ አርባ ኡለማዎች በመስጊዱ ውስጥ በመሆን ቁርአን ይቀሩ ዱዓ(ጸሎት) ያደርሱ ስለነብር ነው አፉርታማ የተባለው ሲሉ የሌሎችን ሃሳብ ያጠናክሉ፡፡

አቶ ጀማል መከነ-መቃብሩና መስጊዱ ከውጭ አገር ጭምር በሚመጡ ሰዎች በመጎብኘት ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡  የአፉርታማ መስጊድ ኮሚቴ አባላት መስጊዱንና የመካነመቃብር ስፍራውን የሚቆጣጠሩ መሆኑን ሙአዚን ጀማል እየነገሩኝ ባሉበት ሰዓት በርካታ ከብቶች ወደ መከነ-መቃብሩ ስፍራ ገብተው በቀብሩ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ ተመልክቻለሁ፡፡ በመካነመቃብሩ  አጠገብ በሚገኘው ለምለም ሜዳ ላይ ቁጭ ብላው በቀዝቃዛ አየር እየተዝናኑ ቁልቁል ጅማ ከተማን በመመልከት ላይ የነበሩ ወጣቶች  ወደመካነ-መቃብሩ  ዘልቀው የገቡትን ከብቶች ሲያባርሩም ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ የአፉርታማ መስጊዲ አልፎ አልፎ የተተከሉ የቅንጭብ አጥር ሲኖረው መካነመቅብሩ ግን ያለምንም አጥር በሰማይ ጠቀስ ጽዶች ተከቦ ይገኛል፡፡

 

የመካነ-መቃብሩ ስፍራ ከአፉርታማ መስጊድ ኮሚቴ አባላት በተጨማሪም የአባጅፍር ቤተሰቦች እየተንከባከቡትና እየጠበቁት ይገኛሉ፡፡ ከአባጅፋር ቤተሰቦች አንዱ የሆኑት የጅማ አባቡና እግር ኳስ ክለብ መስራች አቶ አብዱልከሪም አባገሮ ሲሆኑ አፉርታማ በመባል የሚታወቁት ኡለማዎች ወደ ጅማ ለመሰደድ የመረጡት የተረጋጋ ሰላም የሰፈነበት፣ ንጉሱ ፍትህን የማያጓድሉ፣ በንጉሱ ግዛት ውስጥ በኃይማኖት፣ በዘር፣በሃብትና በመሳሰሉት ልዩነቶች የሰብአዊ መብቶች የማይጣሱበት መሆኑን በማወቃቸው ነው ይላሉ፡፡

ኡለማዎች  በጊዜው በነበሩ ነገስታት ይደርስባቸው የነበረውን የሀይማኖት ተጽዕኖ ምክንያት ከትውልድ  ቀያቸው ሰላም በማጣታቸው ምክንያት ወደ ጅማ ግዛት እንደተሰደዱ ይናገራሉ፡፡

በወቅቱም ለስደት የተዳረጉ ኡለማዎችም "ተብሎ ተብሎ ካልሆነ ነገሩ፣ ጅማ አባ ጅፋር ነው የሰው ልጅ አገሩ" በማለት መግጠማቸው ይነገራል፡፡

ንጉስ አባጅፋር ከተለያዩ አካባቢዎች በስደትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ግዛታቸው የሚገቡ ዜጎችን ወንጀለኛ አለመሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ በተገቢው መንገድ ተቀብለው በሰላም እንዲኖሩ ሁኔታዎችን ያመቻቹላቸው እንደ ነበር አቶ አብድልከሪም ይገልጻሉ፡፡

አበጅፍር በግብጽ አሌክሳንድሪያ ዩኒቭርሲቲ አጠገብ ለኢትዮጵውያን ተማሪዎች እደዚሁም በሳወዲ አረቢያ ደግሞ ለሃጃጅ እንግዶች ማረፊያ እዲሆን በማሰብ ህንጻ ያሰሩ ሲሆን ሳወዲ አረቢያው የሚገኘው ህንጻ እስካሁን ድረሰ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ዶክተር ከተቦ አብዲዮ በጅማ ዩኒቭርሲቲ ባሳተሙት የጥናት መጸሃፋቸው ላይ እንደገለጹት አሁን የአባጅፋር ቤተመንግስት የሚገኝበት የጅሬን አከባቢ የደቡብ ምዕራብ የእስልምና አስተምህሮት ማዕከል እንደነበር  ይጠቅሳሉ፡፡

በተለይ በአጼ ዮሃንስ 4ኛ እና በአጼ ሚሊኒክ 2ኛ ዘመን ከወሎ አካባቢ የእስልምና ሊቃውንት በሚደርስባቸው በደል ምክንያት ወደ አባጅፋር ግዛት ይሰደዱ እንደነበር  በመጸሃፋቸው ላይ አመላክተዋል፡፡

አባ ጅፍር በግዛታቸው 60 የቅዱስ ቁርዓንና የአረብኛ ቋንቋ ማስተማሪያ ማዕከላትን የሰሩ ሲሆን በስደት ወደ ግዛታቸው የመጡ በርካታ የእስልምና ሊቃውንት  ያስተምሩ እንደነበር በጥናት መጸሃፉ ላይ ተጠቅሷል፡፡

የጅማ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዊዳድ አባፊጣ  ጥንታዊ የጊቤ ግዛት አካባቢዎች የገዳ ስርዓትና የዋቄፈታ ኃይማኖትን ይከተሉ ነበር በሂደትም የእስልምና ኃይማኖት ከተጠናከረባቸው ከጎንደር፣ ከወሎ፣ ከይፋት፣ ከደዌይ፣ አካባቢ የእስልምና ኃይማኖት ወደ ጅማ ግዛት ሊስፋፍ በመቻሉ ምክንያት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሊያድግ እንደቻለ ያስረዳሉ፡፡

 በተለይ በ1830 ዓ.ም አካባቢ ከጎንድር የመጡት ሼህ አበዱልሃኪም በጎንደርና በጅማ የእስልምና ሀይማኖት እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ በታሪክ ሰነዶች ላይ ሰፈሮ ይገኛል ፡፡

ጅማ በ18ኛው ክፍለዘመን አጋማሽ የሩቅ ተጓዝ ነጋዴዎች ማዕከል ነበረች፡፡ ነጋዴዎች ከጅማ ሂርማታ ገበያ እንደወርቅ፣ የዝሆን ጥርስ፣ ዝባድ፣ ቡና፣ ብረት የመሳሰሉ ተፈላጊ ምርቶችን ያገኙ ስለነበር የውጭ አገር ነጋዴዎች ጭምር ወደ ሂርማታ ገበያ በስፋት ይመጡ ነብር፡፡

የአፉርታማ መስጊድ የተሰራውም በዚሁ ዘመን በአባጅፋር አባት በአባቦቃ 7ኛ የንግስና ጊዜ በ1862 ዓ.ም ነው፡፡ አፉርታማ የጥንታዊ ጅማ ማሳያ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መጠበቅ ባለበት ልክ አለመጠበቁ የኛ ድክመት ነው ብለዋል፡፡

በመስጊዱ አጠገብ የሚገኘው ሰፊ ነፋሻማ ቦታ  በጅማ ዩኒቨርሲቲ አጠገብ ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ በርካታ ተማሪዎች ለማንበቢያና ለመዝናኛ አገልግሎት እይተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች አካባቢውን ይጎበኙታል፡፡

የቱሪስት መደራሻው በጅማ ከተማ ውስጥ እንደመገኘቱ መሰረተ ልማት ችግር አይሆንበትም፡፡ የአካባቢ ነዋሪዎችን በተለይ ወጣቶችን በማስተባበር መዳረሻውን ማልማት ይቻላል፡፡

የጅማ ከተማ የባህልና ቱሪዝም ኃላፊም የቱሪስት መዳረሻውን አሁን ባለበት ደረጃ እንዲገኝ ያደረገነው ለማልማት ከባድ ሆኖ ሳይሆን ተዘናግተን ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም በአካባቢው ሀብት ብቻ መዳረሻውን ለማልማት እንሰራለን፡፡

በጅማ ዞንና ከተማ አገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው 78 የቱሪስት መዳረሻ ካርታ ሲዘጋጅ በዩኒቨርሲቲው አፍንጫ ስር የሚገኘውን የአፉርታማ መሰጊድና መካነ መቃብር ስፍራ ያለማካተቱ እና ያለመጠናቱ ለቅርሱ መረሳት ማሳያ አይሆንም ትላላችህ?

 

Published in መጣጥፍ

ጋምቤላ ግንቦት 8/2009 ልዩ ድጋፍ በሚሹና አርብቶ አደር አካባቢዎች የህዝቡን የግብርና አሰራር በማሻሻል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ።

ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች፣የአርብቶ አደር አካባቢዎችና የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በጋምቤላ ከተማ ለሶስት ቀናት  ያካሄዱት አምስተኛው ዙር የጋራ ምክክር መድረክ ትናንት የመስክ ጉብኝት በማካሄድ ተጠናቋል።

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ  አቶ ተስፋዬ መንግስቴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ልዩ ድጋፍ በሚሹና አርብቶ አደር አካባቢዎች  ሰፊ የመሬትና የውሃ ሀብት ይገኛል፡፡

ሆኖም ህዝቡ ከነባሩ የግብርና አሰራር ዘይቤ ባለመላቀቁ በተፈለገው ደረጃ ከዘርፉ ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል፤ ለዚህም  የሚደረገው የክትትል፣የቴክኖሎጂና  የሙያ ድጋፍ ዝቅተኛ መሆኑ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

"በጋራ የምክክር መድረኩ ላይም በክልሎች ሆነ በፌደራል ከቀረቡት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርቶች መገንዘብ እንዳተቻለው ቀደም ሲል ከነበረው መሻሻል ቢኖርም ካለው አቅምና ምቹ ሁኔታ አኳያ የተፈለገውን ያህል ርቀት አልተሄደም "ብለዋል።

ህዝቡን  ወደ ተሻለ የግብርና አሰራር ዘይቤ በማሸጋገር  የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ በየደረጀው የሚገኙ የአመራር አካላት፣  ባለሙያዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ጠንክረው ለሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡  

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በክልሎችና አርብቶ አደሮች አካባቢዎች በተለይም  በአቅም ግንባታና ግብዓት አቅርቦት ላይ የተጠናከረ ድጋፍ ለመስጠት መዘጋጀቱንም  አቶ ተሰፋዬ ገልጸዋል።

የጋራ የምክክር መድረኩ  በክልሎችም ሆነ በፌደራል የታዩ ጥንካሬዎችና እጥረቶችን በመለየት ለቀጣይ እቅዶች የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ  የጋራ አቋም የተወሰደበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኤክስቴንሽን አደረጃጀት ስርዓቱ ትኩረት ካልተሰጠው ቴክኖሎጂዎችን ማስፋትና ምርታማነትን  ማሳደግ እንደማይቻል የገለጹት ደግሞ የጋምቤላ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ ናቸው።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዳቹ እንዳመለከቱት  በክልሎች የምርጥ ዘር የጥራትና የአቅርቦት እጥረት ፣ነባር ምርጥ ዘሮችን በአዳዲስ ያለመተካት ፣ የውሃ አጠቃቀም ችግሮች አሉ።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈንታሁን መንግስቴ የሚያጋጥመው የምርጥ ዘር ጥራትና የመጠን ችግር በምርምር፣ በብዜትና በስርጭት ወቅት ተቀናጅቶ ያለመስራት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የክልሎች፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት  ሚኒስቴርና የአርብቶ አደር አካባቢዎች የአፈፃፀም ሪፖርትና  ተሞክሮዎች የቀረቡ ሲሆን የክልሉ የግብርና እንቅስቃሴም በተሳታፊዎች ተጎብኝቷል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን