አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 15 May 2017

መቀሌ ግንቦት 7/2009 በትግራይ ክልል 800 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ 14 ቦታዎችን ተደራሽ የሚያደርግ የገጠር መንገድ ለመገንባት የሚያስችል ዛሬ ስምምነት ተደረገ፡፡ 

የመንገዶችን ግንባታ ለማካሄድ የትግራይ ክልል ኮንስትራክሽን መንገድና ትራንስፖርት ቢሮና ከክልሉ መንገድ ስራዎች ኢንተርፕራይዝ ጋር ዛሬ ስምምነት ተፈፅሟል።

የክልሉ ኮንስትራክሽን፣መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ተስፋይ ገ/ኪሮስ በስምምነቱ ወቅት ላይ እንደተናገሩት፣የመንገዶቹ ግንባታ የሚካሄዱት በአከባቢው መልከአምድር አቀማመጣቸው አስቸጋሪ የሆኑና እስከ አሁን የመንገድ መሰረተ ልማት ተጠቃሚ ሳይሆኑ በቆዩ አከባቢዎች ነው ብለዋል።

154 ኪሎ ሜትር አጠቃላይ ርዝመት ላላቸው ለእነዚሁ መንገዶች ግንባታ ከ794 ነጥብ 9ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን ተናግረዋል።

የመንገዶቹ ግንባታ እንደየርዝመታቸው ስምምነት ከተፈረመባቸው ቀን ጀምሮ ከአንድ አመት ተኩል እስከ ሁለት አመት ተኩል ባለው ጊዜ  ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ይሆናሉ ብለዋል፡፡

መንገዶቹ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆኑ፣ በቀን እስከ 50 ተሽከርካሪ የማስተናገድ አቅም ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል አቶ ተስፋይ፡፡

በዚህም ህብረተሰቡ የዘመናዊ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ለግብርና ስራዎቻቸው የሚያስፈልጋቸው ግብአት በቀላሉ ለማስገባት ይጠቅማቸዋል፡፡

መንገዶቹ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ልምድና ማሽነሪዎችን እንደላቸው የተናገሩት የክልሉ መንገድ ስራዎች ኢንተርፕራይዝ ምክትል ስራ አስክያጁ  አቶ አብረሀ በርኸ  ናቸው፡፡

በመንገድ ፕሮጀክቱ በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች ሊሰርዋቸው የሚችሉ ስራዎችን በመለየት ተሳታፊ እንደሚያደርጉዋቸው ተናግረዋል፡፡

በዚህም በእያንዳንዱ የመንገድ ፕሮጀክት ከሁለት ሺህ500 በላይ ህዝብ ተጠቀሚ እንደሚሆን ይገመታል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ሀረር ግንቦት 7/2009 የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ለዘላቂ የኢንዳስትሪ ሰላምና ልማት መረጋገጥ  የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር እንዳለበት ተመለከተ፡፡

የፌዴሬሽኑ 20ኛ ዓመት ዳግም የምስረታ በዓል በሐረር ከተማ የጨለንቆ ሰማዕታት መታሰቢያ አዳራሽ ዛሬ መከበር ጀምሯል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ በበዓሉ መክፈቻ ስነስርዓት ላይ እንደገለጹት  ኢንቨስትመንትን ከማስፋፋት አኳያ መንግስት ከፍተኛ በጀት መድቦ  የኢንዳስትሪ ፓርኮችን በመገንባት የዘርፉን ልማት እያሳደገ ይገኛል።

ህገ መንግስቱ ባጎናጸፈው መብት መሰረትም ዜጎች ተደራጅተው በኢንዱስትሪውና በሌላውም የልማት ዘርፍ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የተመሰረተው  የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽንም የአሰሪውንና የሰራተኛውን  መብት እያስከበረ ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳመለከቱት  ፌዴሬሽኑ የምርት አገልግሎት ጥራትና የሰራተኛውን የስራ ላይ ደህንነት  በመጠበቅ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ጥረቱን ማጠናከር አለበት፡፡

የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትና የሰላም አምባሰደር አቶ ታደለ ይመር በበኩላቸው የዛሬ 20 ዓመት በሰባት ማህበራት ዳግም የተመሰረተው ፌዴሬሽኑ አሁን ላይ  ከ25ሺ የሚበልጡ አባላት እንዳሉት ገልጸዋል፡፡

የአሰሪና ሰራተኛ መብትና ጥቅም እንዳይሸረሸር ፌዴሬሽኑ ከመንግስት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ በአሰሪና ሰራተኛ መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችን  በመፍታት ረገድ ከኮንፌዴሬሽኑ ጋር ውጤታማ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ  ሰራተኞች ማህበር ኮንፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አያሌው አህመድ ናቸው፡፡

በህብረት ስምምነት ድርድርና በምርት ውጤት ክፍፍል ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን  በጋራ ለመመለስ  ስራቸውን በጋራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል፡፡

በዓሉ በስፖርታዊ ውድድሮች ፣በሲምፖዚየም እንዲሁም 65 አምራች ድርጅቶች ፣አከፋፋይዎች፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በሚሳተፉበት የንግድ ትርኢትና የባዛር ዝግጅት እስከ ግንቦት 20/2009ዓ.ም ይቆያል፡፡ 

የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን በ1945 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ከደርግ ውድቀት በኋላ በ1989ዓ.ም ዳግም እንደተቋቋመ ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ማህበራዊ

መቀሌግንቦት 7/2009 በትግራይ ክልል በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አስታወቁ፡፡

ክልል አቀፍ የጤና መድህን ኮንፈረንስ ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተካሄዷል፡፡

ርእሰ መስተዳድሩ አቶ አባይ ወልዱ በኮንፈረንሱ ላይ እንደገለፁት በክልሉ 18 ወረዳዎች በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ሞዴል ማድረግ ተችሏል።

በሞዴል ወረዳዎቹ ውስጥ የሚገኙ 255 ሺህ ቤተሰቦች በነብስ ወከፍ በዓመት 240 ብር እየከፈሉ ሙሉ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ርእሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

በሞዴል ወረዳዎች የተመዘገበው አበረታች ውጤት በክልሉ በሚገኙ ሌሎች 34 ወረዳዎች ለማስፋት ቢታቀድም በአመራሩ የቁርጠኝነት ማነስና በሌሎች ችግሮች ሳይሳካ መቅረቱን ተናግረዋል፡፡

በሚቀጥለው ዓመት ግን ችግሮቹን ለይቶ በማስተካከል ሁሉንም ወረዳዎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በትጋት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው  በአገሪቱ 13 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ ተጀምሮ ውጤታማ የሆነው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ፕሮጀክት ወደ 374 ወረዳዎች ማስፋት መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ አሁን ያለውን 33 በመቶ የጤና መድህን ሽፋን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ወደ 50 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

''ለተግባራዊነቱም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ቁርጠኝነትና ጤና ተቋማቱ ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት መስጠት ይጠይቃል'' ብለዋል።

በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሞዴል ተብሎው ቀደም ሲል የሞተር ሳይክልና የዲጅታል ካሜራ ሽልማት ከተበረከተላቸው ወረዳዎች መካከል የራያ ዓዘቦና የሀውዜን  ወረዳዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የራያ ዓዘቦ ወረዳ ተወካይ  ወይዘሮ ገነት መንገሻ በሰጡት አስተያየት በወረዳው ቀደም ሲል አንዳንድ የቤተሰብ መሪዎች ለህክምና በአመት ከአምስት ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር  ወጪ ያደርጉ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

በወረዳው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ ግን አባላት በዓመት 240 ብር በመክፈል ሙሉ የጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎት የማግኘት መብታቸው መረጋገጡን ተናግረዋል።

የሀውዜን ወረዳ ተወካይ  አቶ ሃይላይ ገብረማርያም በበኩላቸው፣  የወረዳው ነዋሪዎች የማህበረሰብ ጤና መድህን አባል በመሆናቸው በጤና ተቋማት በቀላል ወጪ የህክምና አገልግሎት እያገኙ ነው፡፡

ወረዳቸውም በክልል ደረጃ በዘርፉ ሞዴል ተብሎ ለሽልማት መብቃቱን አመልክተዋል።

ዛሬ በመቀሌ ከተማ በተካሄደው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ኮንፈረንስ ላይ ከፌዴራል፤ ክልል፤ ዞን፤ ወረዳና ቀበሌ የተወጣጡ ከ300 በላይ አመራሮችና የጤና ባለሙያዎች  ተገኝተዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2009 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሄኒከን ኢትዮጵያ ኩባንያ ጋር የ30 ሚሊዮን ብር የስፖንሰር ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ነው።

ስምምነቱን የፈረሙት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ እና የኩባንያው ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሄሪት ቫንሎ ናቸው።

በፊርማ ስነ ስረዓቱ ላይ አትሌት ኃይሌ  እንደገለጸው፤ የኩባንያው  ምርት የሆነውን 'ሶፊ ማልት'ን ፌዴሬሽኑ በሚያካሂዳቸው ውድድሮችና ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ  እንዲተዋወቁ ይደረጋል።

ይሁን እንጂ ኩባንያው ከ"ሶፊ ማላት" ውጭ ያሉ ሌሎች የአልኮል መጠጦችን ማስተዋወቅ እንደማይቻል ነው የተናገረው።

የኩባንያው ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሄሪት ቫንሎ "በኩባንያችን በኩል የኢትዮጵያ አትሌቶችን ለመደገፍ እድሉን በማግኘታችን ኩራት ይሰማናል" ብለዋል።

ኩባንያው ይህን ስምምነት ማድረጉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስን አንድ እርምጃ ወደ ፊት ለማራማድ የሚችለውን ሁሉ ለመስራት እድል እንደሚሰጠው ነው የተገለጸው።

አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ወደ ፌዴሬሽኑ ሲመጣ አንዱ ግቡ አድርጎ ለመንቀሳቀስ ያቀደው የፌዴሬሽኑን የገንዘብ አቅም በሀገር ውስጥ ከሚሰሩ የተለያዩ ኩባንያዎች ጋር በጋራ መስራት ነው።  ዛሬ ባደረገው ስምምነትም አንዱን እቅድ ማሳካት መቻሉ ነው የታየው።

ፌዴሬሽኑ የገንዘብ አቅሙን ለማጠናከር ከሌሎች ድርጅቶች ጋር እንደሚሰራ ነው የተገለጸው።

 

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2009 የአማርኛና ስፖርት ሳይንስ ትምህርቶችን የቅድመ ዝግጅት /ሞዴል/ ፈተና እንዳይወስዱ መደረጋቸውን የወይዘሮ ቀለመወርቅ ጥሩነህ መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ገለፁ።

የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የመሰናዶ ትምህርት ማጠናቀቂያ ሞዴል ፈተና ካለፈው ዓርብ ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሰጠ ነው።

ቅሬታቸውን ለኢዜአ ያቀረቡት ተማሪዎች ያለበቂ ምክንያት የአማርኛና ስፖርት ሳይንስ ትምህርቶች ፈተና ላይ እንዳይቀመጡ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቱ በ2009 ዓ.ም 472 ተማሪዎችን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ሞዴል ፈተና እንዲወስዱ አድርጓል።

ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል 43 ያህል ተማሪዎች ፈተና አለመውሰዳቸውን በፊርማቸው በማረጋገጥ ቅሬታቸውን ለኢዜአ አቅርበዋል።

የቅሬታ አቅራቢዎቹ ተማሪዎች ተወካዮች በፈተናው ላይ እንዳይቀመጡ የተደረጉበትን ምክንያት እንደማያውቁ ነው የተናገሩት።

ተማሪዎቹ ዛሬ ጠዋት በተሰጡት የአማርኛና የስፖርት ሳይንስ ትምህርቶች ፈተና ላይ ያለአግባብ እንዳይቀመጡ መደረጉን ነው የሚገልጹት።

የፈተና ሠዓት አክብሮ መገኘት የተማሪዎች ግዴታ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች አርፍዶ የሚመጣ ተማሪ መኖሩንም ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ዛሬ እንዳይፈተኑ የተደረገው አርፍደው በመምጣታቸው አለመሆኑን ነው የሚናገሩት።

ኢዜአ የወይዘሮ ቀለመወርቅ ጥሩነህ መሰናዶ ትምህርት ቤትን ርዕሰ መምህር በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ቢሞክርም ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑም።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት በበኩሉ ጉዳዩ ለሚዲያ ፍጆታ የሚሆን አይደለም በማለት ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥቷል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2009 የአክሱም ሐውልት በሁለት ሚሊዬን ዩሮ እድሳት ሊደረግለት ነው።

ይሄው 24 ሜትር ርዝመት ያለውና "ሦስት ሐውልት" ተብሎ የሚጠራውን የአክሱም ሐውልት ለማደስ የሚያሰችል ስምምነት ዛሬ በአክሱም ከተማ ተካሂዷል።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለ ስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ እንደገለጹት፤ ሐውልቱን ማደስ ያሰፈለገው የተገጠመለት የንዝረት መቆጣጠሪያ በጊዜ ብዛት በፀሀይና በዝናብ ምክንያት ብልሽት ስለገጠመው ነው ።

ሁለት ሚሊዮን ዩሮ ወጪ የሚደረግበት የሐውልቱ እድሳት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የትግራይ ማዕከላዊ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሚካኤሊ አብርሓ እንዳስረዱት፤ የአካባቢው ኅብረተሰብ ለዓመታት ሐውልቱን የማደስ ጥያቄ ቀርቦ ነበር። በዚሁ መሰረት ስራው ጥንቃቄን የሚፈልግ በመሆኑ ጥናት ሲደረግበት ቆይቷል።

የሐውልቱ እድሳት የሚያከናወነው ኤም ኤች ኢንጂነሪንግ በተባለ አገር በቀል ድርጅት እና ከጣሊያን የተመለሰውን ሐውልት የዳግም ተከላ ስራ ባከናወነው  ስቱዲዮ ክሮቺ በተባለ የጣሊያን አማካሪ ድርጅት ነው።

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ እና የአካባቢው ማህበረሰብ የሃውልቱን እድሳት ከሚያከናውኑት ድርጅቶች ጋር እንደሚተባበሩም ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ዶክተር ጁሲፒ ኮፕላን በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ታሪካዊ ቅርሶችን ለማደስ በሚያከናውናቸው ሥራዎች አገራቸው የሙያ እና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ጣሊያን "የበርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ባለቤት ናችው" ያሉት አምባሳደሩ፤ ይህም የሁለቱን አገሮች የእርስ በእርስ ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።

አክሱም ሐውልት ከ1ሺ 700 ዓመት በላይ እድሜ ያለው ሲሆን፤ 160 ቶን ይመዝናል። ሐውልቱ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት እ.ኤ.አ በ1980 ተመዝግቧል።

Published in ኢኮኖሚ

ነፃነት አብርሃም (ኢዜአ)

በዓለማችን ላይ አዝናኝ ከሚባሉ ስፖርታዊ ክንውኖች መካከል አንዱ እግር ኳስ ነው። ከዚህም በላይ በብዙ የስፖርት ቤተሰቦች ህይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና ለመዝናኛነትም ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ይኸው የስፖርት ዘርፍ በተለይም በምዕራባዊያን ዘንድ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ የእድገት ግስጋሴው ዘላቂ በሚባል ሁኔታ ላይ መሆኑን ሁላችንም እንረዳዋለን። ይህንንም ተከትሎ በአውሮፓም ሆነ በሌሎች ክፍለ-ዓለማት አስደናቂና እጅግ አዝናኝ የሆኑ የእግር ኳስ ጥበቦችን የሚያሳዩ ተጫዋቾችና ቡድኖችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸውም ሌላው የምናስተውለው ጉዳይ ነው። ስፖርት ወዳዱ ኅብረተሰብም እነዚህን የሜዳ ላይ ክስተቶች ለመመልከት ከያለበት ተነስቶ አንድም በስታዲየም አልያም ደግሞ በቴሌቭዥን መስኮት ለመከታተል ሲዋትት ማየት ልማድ ሆኗል።

በተለይም በሁለት ተቀናቃኝ የስፖርት ቡድኖች መካከል የሚካሄደውን የ"ደርቢ" የእግር ኳስ ግጥሚያ የብዙኃኑን የስፖርት ተመልካች ቀልብ የሚስብ መሆኑንም ልብ እንላለን። እንዲህ ያሉ የደርቢ ጨዋታዎች ተመልካቾችን ከማዝናናነት በተረፈ ለእግር ኳስ እድገት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው የብዙዎች ግምት ነው፡፡ በተለይም በእግር ኳስ ወዳዱ ማኅበረሰብ መካከል ባለው ተፈላጊነት የተነሳ በእያንዳንዱ የእግር ኳስ የውድድር ዘመን የሚጠበቅ የጨዋታ መርኃ ግብር መሆኑንም ልብ እንላለን። የደርቢ ጨዋታዎች ሲካሄዱም፤ ስታዲየሞች ጢም ብለው ሲሞሉ፣ ከፍተኛ የትኬት ሽያጭ ሲመዘገብ፣ በማልያ ሽያጭና በቴሌቭዥን የአየር ሰዓት ስርጭትም ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ መሆናቸው ይታወቃል። 

በዓለማችን ላይ በተለይም እግር ኳስ በመደበኛነት በሚዘወተርባቸው አገሮች ታላላቅ ደርቢዋች የሚገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ ደርቢዎች መካከል ለምሳሌ ያክል በእንግሊዝ ሜርሲሳይድ ደርቢ ሊቨርፑል ከኤቨርተን፣ በሰሜን ለንደን ደርቢ አርሴናል ከቶትንሃም ማንሳት እንችላለን። በሌላ በኩል በማንችስተር ከተማ ክለቦች ማንችስተር ዩናይትድ ከማንችስተር ሲቲ፣ በጣሊያን ሚላን ደርቢ(ሳንሲሮ ደርቢ) ኤሲ ሚላን ከ ኢንተር ሚላን፣ በስፔን ማድሪሊያኖ ደርቢ ሪያል ማድሪድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ፣ በአርጀንቲና ሱፐርክላሲኮ ደርቢ ቦካ ጁኒዬርስን ከሪቨር ፕሌት፣ ፣ በቱርክ ፌነርባቺ ከጋላታሳራይ፣ በስኮትላንድ ሰልቲክ ከረንጀርስ፣ በጀርመን ቦርስያ ዶርትመንድ ከሻልካ 04፣ በፖርቱጋል ሊዝበን ቤነፊካ ከ ስፖርቲንግ ሊዝበን፣ በጣሊያን የሮም ደርቢ ሮማ ከላዚዮ፣ በግሪክ የአቴና ደርቢ አቴንስ ኦሎምፒያኮስ ከፓነትኒያኮስ፣ በብራዚል ሳኦፓውሎ ደርቢ ኮረንቲያስ ከፓልሚሬስ እንዲሁም በሪዮ ዲጄኔሮ ከተማ ፍላ ፍሉ ደርቢ የፍላሚንጎ ከየፍሉሚንዜ ክለቦች የደርቢ ጨዋታ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በሁለት የተለያዩ ከተሞች ተወካዮች የሚደረጉ ታላላቅ የደርቢ ጨዋታዎችንም ብንመለከት አንዱ በኤል ክላሲኮ ደርቢ የሪያል ማድሪድ እና የባርሴሎና ክለቦች ፍልሚያ መጥቀስ ይቻላል። የአፍሪካ አገራትን ደርቢዎች ብንመለከት በግብጽ የካይሮ ደርቢ አል አሃሊን ከዛማሌክ የሚያገናኘው በአፍሪካ ትልቁ የደርቢ ጨዋታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ስዌቶ ደርቢ ኦርላንዶ ፓይሬትስ ከካይዘር ቺፍ፣ በቱኒዚያ ቱኒዝ ደርቢ ክለብ አፍሪካን ከኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ዴስ ቱኒስ የመሳሰሉት ክለቦች ይገኙበታል። ወደ አገራችን “ኢትዮጵያ” ስንመለስ ደግሞ የበርካታ ዓመታት ታሪክና ዝና ካለቸው ክለቦች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ወይንም "የሸገር ደርቢ" ሁነኛ ምሳሌዎች ናቸው።

በአገሪቷ ቀደምት ታሪክ ካላቸው የእግር ኳስ ክለቦች ተርታ የሚሰለፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ቡድን ከምስረታው አንስቶ በፕሪሚየር ሊግ፣ በጥሎ ማለፍ፣ በሱፕር ካፕ፣ በአሸናፊዎች አሸናፊና በሌሎችም ውድድሮች ከ50 በላይ ዋንጫዎችን በመሰብሰብ ገናና ለመሆን የቻለ ቡድን ነው። በአንጻሩ የኢትዮጵያ ቡና በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ታሪክ አንድ ጊዜ ዋንጫ ያገኘ ሲሆን፤ በጥሎ ማለፍ፣ በአሸናፊዎች አሸናፊና በሱፕር ካፕ ፣ በራን አዌይ ሊግ በርካታ ዋንጫዎችን በማግኘት በለስ ቀንቶታል፡፡ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው የደርቢ ጨዋታ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ካሉት 16 የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል በተመልካች ዘንድ ትኩረትን ማግኘት ችሏል። በብዙዎች ግምትም በርካታ ደጋፊ ያላቸውና በከፍተኛ ደረጃ የፉክክር ስሜት ታጅቦ የሚካሄድ ደርቢ መሆኑንም የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮችም ለጨዋታው የሚያገኙት ትኩረትም ላቅ ያለ መሆኑን እናስተውላለን።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በሚኖርበት ወቅት በየደረጃው ያሉ ህጻናትና ወጣቶች ሴቶችና ወንዶች፣ አዛውንቶች ሁሉ በጨዋታው ለመታደም በስታዲየሙ ይገኛሉ። እኔም የሁለቱን ክለቦች ጨዋታና የድጋፍ ሁኔታ ለመመልከት ወደ ስታዲየሙ ከሚያመሩት መካከል አንዷ በመሆኔ ጨዋታው በሚደረግበት ወቅት የሚኖረው ድባብ ትኩረቴን ስለሳበውና ስላስደመመኝ በጥቂቱ ላወጋችሁ ወደድኩ ።

ሁለቱም የአንድ ከተማ ክለቦቹ ለፕሪሚየር ሊጉ ድምቀት እያበረከቱ ያሉት አስተዋፅኦ የጎላ ነው። ጨዋታውን በስታዲየሙ ለመከታተል የሚጓጉ ፀሀይና ዝናብ የማይበግራቸው የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ጨዋታው በሚኖርበት ወቅት ከንጋት ጀምሮ ሰልፍ በመያዝ በስታዲዩሙ ዙሪያ የሚያገኟትን ሳምቡሳ ችብስና ብስኩት እየቀማመሱ የጨዋታውን ሰዓት በጉጉት የሚጠብቁ ደጋፊዎችን እግር ጥሎት ለሚመለከት ሰው የተለየ ስሜት ይሰማዋል። ጨዋታቸውን ውስጥ ገብቶ ለሚመለከት በስታዲየሙ የሚገኘው ተመልካች ብቻ ሳይሆን ከውጪ ሆኑ የድጋፉን ድምጽ ለሚሰማው እንኳን ምነው እኔም የዚህ ድባብ ታዳሚ በሆንኩኝ የሚያሰኝ ነው።

እነዚህ ሁለቱ ክለቦች ሲገናኙ የክለቦቹ ደጋፊዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመምጣቱ በወንበር 25 ሺ እንዲሁም ከወንበር ውጪ እስከ 35 ሺ ተመልካቾችን መያዝ እንደሚችል የሚነገርለት የአዲስ አበባ ስቴዲየም ከምን ጊዜውም በበለጠ ከሚችለው በላይ እንዲሞላ ይገደዳል። አያሌ ደጋፊዎች ደግሞ ቲኬት በማለቁ የተነሳ አስፋልቱ ላይ ሲተራመሱና ወደ ቤታቸው እንደሚመለሱ ያለፉት ዓመታት የስታዲየም አካባቢ ትርክቶች ይመሰክራሉ፡፡

በዚህም በፕሪሚየር ሊግ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል የሸገር ደርቢ የካምቦሎጆ ድምቀት በመሆን "ቀዳሚ ናቸው" ብንልም የማያሻማና ብዙዎችን የሚያስማማ ይመስለኛል። የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎቹ በኅብረት፣ በሚያምርና በሚስብ መልኩ ተደርድረው ቆመው ተቃቅፈው እያዜሙ ሲንቀሳቀሱና ሲወዛወዙ እጅግ ቀልብ በሚስብ ትዕይንት ክለቦቻቸውን ሲያበረታቱ 90 ደቂቃ ያልቃል። ከዚህ ድምቀት ጀርባ በእስካሁኑም ሂደት፤ የአንድ ከተማ ክለቦቹ የደርቢ ትንቅንቅ ለ36ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፤ 20 ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ሰባት ጊዜ ረቶቷል፡፡ በዘጠኝ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ተለያይተዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን በተለያዩ ጊዜያት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አንደኛው በአንዱ ላለመሸነፍ በሚያደርጉት ትንቅንቅ የተነሳ እንከን የማያጣው መሆኑን እዚህ ጋር ለመጥቀስ እወዳለሁ። በተለያዩ መድረኮች ላይ ስለ ስፖርታዊ ጨዋነትና የእግር ኳስ ደጋፊዎች ሥነ-ምግባር ቢነገርም አሁንም ድረስ ግን  አንዳንድ ነውጠኛ ደጋፊዎች በካምቦሎጆ ሜዳ ላይ አላስፈላጊ ተግባር ሲፈጽሙ ይስተዋላሉ። እንዲህ ያሉ ችግሮች በተለይም በእነዚህ ሁለት የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል በሚካሄዱ ጨዋታዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚስተዋል ክስተት መሆኑ የማይካድ ሐቅ ነው። 

ለዚህ ችግር ግን በዋነኝነት የሚጠቀሰው ደግሞ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የእግር ኳስ ፍቅር ከልብ ያልገባቸው ውስን ደጋፊዎች ያልተገባ ተግባራት ስለሚፈጽሙ እንደሆነ ይነሳል። ደጋፊዎቹ ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ፣ የቡድኖችን ስም በአሉታዊ መልኩ በመጥቀስ ወይንም ደግሞ የተጫዎችን ስም በማጉደፍ አልፎም ተርፎ በተቃራኒ ተጫዋቾች ላይ ጉዳት ለማድረስ የተለያዩ ቁሶችን እንደሚወራወሩ ነው የሚስተዋለው። በዚህም አላስፈላጊ ክስተቶች እንዲከሰቱና ለጸብ የሚዳርጉ ድርጊቶችን በመፈጸም ሰላማዊውን የእግር ኳስ መድረክ ሲያውኩ ማየት የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡

በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በተለይም በሶሻል ሚዲያ የሚናፈሱ ውሃ የማያነሱና ለብጥብጥ የሚጋብዙ ወሬዎችም በስታዲየሙ ለሚከሰተው ሁከት ሁነኛ ምክንያት ስለመሆናቸው አምናለሁ። በተጨማሪ ደግሞ አንድ ሁለት በማለት መጠጥ ጎንጨት እያሉ የሚገቡ ደጋፊዎችም አንዱ የጥፋቱ ሰለባ ናቸው።

ጥቂት ደጋፊዎች ደግሞ ሲበሻሻቁ፣ ሲሰዳደቡና ከዚያም ባለፈ ወንበር እየነቀሉ በመወራወር ነገ ትውልድ ሊገለገልባቸው የሚችሉ ግብዓቶችን በማጥፋት የክለቦቻቸውን ስም ሲያጎድፉና በርካታ ደጋፊዎችን ሲፈነከቱ እና አደጋ ሲደርስባቸው እየተመለከትን ነው፡፡ በዚህ ሁከትና ብጥብጥ ሳቢያ "ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ" ነውና የፖሊሶች ዱላ እንዳያርፍባቸው በሚመስል መልኩ በፍርሃት በተዋጠ መንፈስ ሲሯሯጡ ለሚመለከት እንኳን ለመደገፍ በስታዲየሙ የገባውን ቀርቶ መንገደኛውንም የሚያስደነግጥ ነው።

ሆኖም በተለያዩ ጊዜያት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከመካሄዱ አስቀድሞና ከጨዋታውም በኋላ ስለ ስፖርታዊ  ጨዋነት በተደጋጋሚ የፌዴሬሽን አመራር አባላት፣ አሰልጣኞች፣ የቡድን መሪዎች፣ ተጨዋቾችና የክለብ ደጋፉዎች የሚነጋገሩ ቢሆንም እንኳን ችግሩ ሊቃለል ያልቻለ ተግባር እየሆነ መጥቷል። በተጨማሪም አንዳንድ የክለቦቹ ነውጠኛና ጸብ አጫሪ ደጋፊዎችም በሚፈጥሩት ስነ ምግባር የጎደለው ተግባር የተነሳ ክለቦቹ በተለየዩ ጊዜያት ቅጣት ሲጣልባቸው ይስተዋላል።  

ለአብነት ያህል በዚህ ዓመት በሚያዚያ 7 ቀን 2009 ዓ.ም በተደረገው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የተከሰተውን ሁከትና ብጥብጥ ማንሳት ይቻላል። በፕሪሚየር ሊጉ 23ኛ ሳምንት መርኃ ግብር የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። በወቅቱ ቡናማውን እና ቡርቱካናማውን ማሊያ ለብሰው ባሸበረቁ የሁለቱ ደጋፊዎች የደመቀው ጨዋታ በሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች የሚያምር ህብረ ዜማና ቀልብ በሚስብ የድጋፍ ድምጽ የደመቀና በሚያምር የድጋፍ ስሜት የዘለቀ ነበር። ይሁንና  ልዩ ስሙ ካታንጋ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ላይ በጥቂት ጸብ አጫሪ ደጋፊዎች አማካኝነት የእርስ በእርስ አለመግባባት የተነሳ ወደ አላስፈላጊ ሰጣ ገባ ውስጥ በመግባት ቡድናቸውን ከማበረታታት ይልቅ ለስድብና አልፎም ለድብድብ ሲጋበዙ ተመልክቻለሁ።

በዚህም የሁለቱም ክለብ በካታንጋ ቦታ ላይ የነበሩ ደጋፊዎች መቀመጫ ወንበሮችን በመስበርና በመወራወር ሰላማዊ የሆነው ደጋፊ ላይም ጭምር ጉዳት ሲደርስበትና ጨዋታውን አቋርጦ ሲወጣም ተመልክቻለሁ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በዕለቱ በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች ባሳዩት የስነምግባር ጉድለቶች በክለቦቹ ላይ የገንዘብ ቅጣት አስተላልፏል። ይሁንና ክለቦቹ በእነዚህ ጸብ አጫሪ ደጋፊዎች ምክንያት ክለቦቹ ሲቀጡ የመጀመሪያ አይደለም፤ ነገር ግን ቅጣቱ ምን ያህል አስተማሪና ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ ስለመሆኑ እንዲሁም ደግሞ "ደጋፊዎችን ምን ያህል ያስተምራል?" ለሚለው ግን አሁንም ጥያቄ አለኝ።

ታዲያ እንደዚህ ያለው አላስፈላጊና ጸያፍ ተግባር መፈጸሙ የአገሪቷን ስፖርት እንዳያድግ ከማድረግና ስፖርቱን ከማቀጨጩም በላይ በርካታ ሰላም ወዳድና እግር ኳስ አፍቃሪ የስፖርት ቤተሰብን ከካምቦሎጆ እንዲርቅ ምክንያት ይሆናል። በስታዲየሙ ታድሞ በሰላማዊ መልኩ የሚከታተለው የእግር ኳስ ማኅበረሰብ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደር በስታዲየሞች የሚከታተለውን የህዝብ ቁጥር እንዲያሽቆለቁል ምክንያት ሊሆን የሚችል ተግባር ነው። ይህም የአገራችንን እግር ኳስ ገጽታ ጥላሸት ከመቀባት በዘለለ እድገቱን ወደ ኋላ እንደሚጎትተው መገንዘብ እንችላለን።

ታዲያ ችግሩን ማቃለል ይቻል ዘንድ ምን ቢደርግ ይሻል ይሆን? እንደ እኔ ሃሳብ፤ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ማንኛውም የስፖርት ቤተሰብ ውድድሮችን በነጻነትና በሰላማዊ መንገድ ተመልክቶ ወደ ቤቱ የሚጓዝበት ሁኔታ መፍጠር ቀዳሚ መሆን የሚገባው ተግባር ነው። በተለይም ሁለቱም ቡድኖች የካምቦሎጆ ድምቀት እንደመሆናቸው መጠን ደጋፊዎች ባላቸው ውብ ቀለም የራሳቸውን ቡድን ብቻ መደገፍ፣ ጨዋታውን ስነ ምግባር በተላበሰ መልኩ መመልከትና የዳኛን ውሳኔ በጸጋ መቀበል አስፈላጊ ይመስለኛል። ሌሎች ለብጥብጥ መንስኤ የሚሆኑ ተግባራትን ለምሳሌ ተጫዋቾችን፣ ዳኞችንና ደጋፊውን የሚዘልፉ ቃላትን በማስወገድ በኩል የበኩላቸውን አሰተዋፅኦ ማድረግ መቻል ተገቢ ነው። በመሆኑም ካምቦሎጆ ሁሌም ደምቆ እንዲታይና ሁከት የራቀበት ይሆን ዘንድ ተጫዋቾች፣ ዳኞች፣ የክለብ አሰልጣኞች፣ አመራር አባላት እና የክለቦቹ ደጋፊዎች "የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል" የሚል ምክረ ሀሳብ አለኝ። ችግሮቹን ሊያቃልሉ በሚችል መልኩ ለችግሩ መንስኤ የሚሆኑትን ደጋፊዎች የተለያዩ መድረኮች በአባል ደጋፊዎቻቸው አማካኝነት በመፍጠርና ስፖርቱን የሰላም መንደር በማደረግ "ማስተማር ቢቻል ችግሩ ይቃለላል" የሚል ጽኑ እምነት አለኝ

Published in ዜና ሓተታ

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2009 በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 5 ነዋሪዎች የሚመጣላቸው ውሃ ንፅህናው የተጓደለ በመሆኑ መቸገራቸውን ተናገሩ።

የመዲናዋ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በበኩሉ በአካባቢው የውሃ መበከል ማጋጠሙንና ችግሩን ለመፍታት እየሰራ እንደሆነ ገልጿል።

በተለምዶ ዮሃንስ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደተናገሩት በቧንቧ የሚመጣላቸው ውሃ ንጽህናውን ያልጠበቀ በመሆኑ መጠቀም አልቻሉም።

ወይዘሮ ፀሐይ አበጋዝ የአካባቢያቸው ውሃ መጥፎ ሽታ ያለው በመሆኑ ለመጠጥም ሆነ ለሌላ አገልግሎት ለማዋል መቸገራቸውን ይናገራሉ።

ውሃው ንጽህናውን የጠበቀ ባለመሆኑ ለጤናችንም አስጊ እየሆነብን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

"በአካባቢው በተደጋጋሚ ውሃ ይጠፋል፤ በሚመጣበት ወቅት ደግሞ ንጹህ ውሃ አይደለም የሚመጣልን" ያሉት ደግሞ አቶ አያሌው ረጋሳ ናቸው። 

ወይዘሮ አበበች ጎዳና በበኩላቸው ውሃው ቆሻሻና ንጽህናውን የጠበቀ ባለመሆኑ የጤና እክል እየገጠመን ነው ይላሉ።

"ንጹህ ውሃ ባለማግኘታችን ውሃ እየገዛን ለመጠቀም ተገደናል" ያሉት ደግሞ ሌላዋ የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሮ ወርቅነሽ ሚጻ ናቸው።

ነዋሪዎቹ የሚመለከተው አካል ችግራቸውን ተመልክቶ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የሥራ ሂደት መሪ አቶ እስጢፋኖስ ብስራት ችግሩ በአካባቢው መከሰቱ ትክክል መሆኑን ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ ለችግሩ እልባት ለመስጠት እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ችግሩ በተመሳሳይ በሌሎች አካባቢዎችም ሊከሰት እንደሚችልና በሂደት ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ ተመሳሳይ ችግር ሲያጋጥመው በ906 ነጻ የስልክ መስመር እንዲሁም በ0911 86 86 27 በመደወል ማሳወቅ እንደሚችል ነው ያስረዱት።

እንደ አቶ እስጢፋኖስ ገለጻ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 36 ኪሎ ሜትር መለስተኛ የውሃ መስመሮችን የመቀየር ስራ ተከናውኗል። 

በቀጣይም 189 ኪሎ ሜትር የመለስተኛ መስመርና የ24 ኪሎ ሜትር ከፍተኛ የውሃ መስመር ለመቀየር ባለስልጣኑ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2009 የአልጀሪያ ኩባንያዎች የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ የገበያ መዳረሻዎችን ለመጠቀም ኢትዮጵያ ትክክለኛዋ አገር መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የመጀመሪያው የኢትዮ-አልጀሪያ ቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ሲሆን የሁለቱ አገራት ባለሃብቶች፣ዲፕሎማቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል በፎረሙ መክፈቻ ላይ እንዳሉት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ እድሜ ያለው የኢትዮ- አልጀሪያ ግንኙነት በፖለቲካዊ ጉዳዮች ተወስኖ ቆይቷል።

"ይህን ግንኙነት ወደ ሁለትዮሽ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ለመቀየር ሁለቱ አገራት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ናቸው" ያሉት ዶክተር አክሊሉ ተደራራቢ ቀረጥን ማስቀረት፣ የኢንቨስትመንት ጥበቃ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በባህልና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ስምምነት ተፈራርመናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ባላት ምቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ለአልጀሪያ ባለሃብቶች ምቹ ናት ብለው ኢትዮጵያም ምርቶቿን ወደ አውሮፓ ገበያዎች ለመላክ አልጀሪያ ጥሩ መሸጋገሪያ እንደምትሆናት ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር አክሊሉ ገለጻ ኢትዮጵያ ከአለማችን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ አገራት መካከል አንዷ ስትሆን የእርሻ ማቀነባበሪያ፣ የኬሚካል ኢንዱስትሪ፣ የመድሃኒት፣ የጨርቃጨርቅ ልማትና ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ መሆኗን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአልጀሪያ ኤምባሲ ተወካይ ሚስ አፌፍ ቡቶባ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት የነበራቸውን ጠንካራ የፖለቲካ ግንኙነት ወደ ኢኮኖሚ ትስስር መቀየር የሚያስችላቸውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የሁለትዮሽ ቢዝነስ ፎረምና ሌሎች ስራዎችን በማከናወን ላይ ናቸው ብለዋል።

"ኢትዮጵያ በቅርቡ በአልጀርስ ኤምባሲዋን መክፈቷ፣ የአዲስ አበባ-አልጀርስ ቀጥታ በረራ አገልግሎትና የአገራቱ ከፍተኛ መሪዎች እርስ በርስ ጉብኝት ማድረጋቸው ግንኙነቱን ለማሻሻል ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል።"

በሁለትዮሽና አለም አቀፍ የፖለቲካ አጀንዳዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ የቆየው የኢትዮጵያና አልጀሪያ ወዳጅነት ወደ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከጊዜ ወደ ጊዜ በማደግ ላይ ሲሆን ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት ዜሮ የንግድ ልውውጥ አሁን የስምንት ሚሊዮን ዶላር በላይ ዕድገት አሳይቷል።

ለአንድ ቀን በሚቆየው የኢትዮ-አልጀሪያ ቢዝነስ ፎረም የሁለቱ አገራት ባለሃብቶች የምርትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚረዳቸው ሲሆን የአልጀሪያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር ያግዛቸዋል ተብሏል።

 

 

Published in ፖለቲካ

ደብረ ብርሀን ግንቦት 7/2009 በሰሜን ሸዋ ዞን ባለፉት ዓመታት የፍትህ ሳምንት መከበሩ የፀረ ሙስና ትግሉን የሚያግዙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉ ተጠቆመ።

ሰባተኛው የፍትህ ሳምንት " የህግ የበላይነት ለዘላቂ ሰላምና ለሕዝቦች አንድነት" በሚል መሪ ቃል ትናንት በደብረብርሃን ከተማ በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በፀረ ሙስና ኮሚሽን የደብረ ብርሃን ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ አበበ ባለፉት ዓመታት የፍትህ ሳምንት ትኩረት ተሰጥቶት መከበሩ ሕብረተሰቡ ስለፍትህ ያለው ግንዛቤ እንዲያድግ አድርጓል።

ይህም የፀረ ሙስና ትግሉን የሚያግዙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከጊዜ ወደጊዜ ቁጥራቸው እንዲጨምር ማድረጉን ነው የገለጹት።

አቶ ደረጀ እንዳሉት፣ ጽህፈት ቤቱ በየዓመቱ የሚከበረውን የፍትህ ሳምንት ምክንያት በማድረግ ከ22 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥቷል።

በዚህም በአንድ ዓመት ብቻ 1 ሺህ 112 ጥቆማዎች ከሕብረተሰቡ እንደደረሳቸውና ከዚህ ውስጥ ተጨባጭ ማስረጃ የተገኘባቸውን 767 የሙስናና ሌሎች የወንጀል ጥቆማዎች ክስ እንደተመሰረተባቸው አስረድተዋል።

ክስ ከተመሰረተባቸው መካከል 117ቱ ከሁለት ወር እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ተደርጓል።

በተጨማሪም ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስትና የሕዝብ ሃብት እንዲሁም 5 ሺህ 984 ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ ለማስመለስ መቻሉን ነው የገለጹት።

በቀጣይም የሀሰተኛ ማስረጃዎችና ምስክሮችን ለመቀነስ ሕብረተሰቡ ጥቆማውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ደረጀ ጠይቀዋል። 

የዞኑ ፖሊስ  መምሪያ ተወካይ ምክትል ኮማንደር እሸቱ ጌታቸው፣ ሕብረተሰቡ በገንዘቡና በጉልበቱ ለማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አደረጃጀት የቢሮና የመኖሪያ ቤት ገንብቶ በመስጠት ድጋፉን እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

"በየቀበሌው ለሚመደቡ ፖሊሶችም በቅሎ፣ ሞተርና ሌሎች የመጓጓዣ ዓይነቶችን በመግዛት እያገዘ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ከወረዳ እስከ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የውሳኔ መዘግየት እንደነበር የገለጹት ደግሞ በባሶና ወራና ወረዳ የቃይት ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሙላቷ ተክሌ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በየደረጃው ያለው አካል ተናቦ በመስራቱ የፍትህ ውሳኔ ፈጣን በሆነ መንገድ እየተሰጠ  መሆኑን አስረድተዋል።

የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ አወቀ ዘነበ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ የዞኑ ሕዝብ ለፍትህ ስርዓቱ መጎልበት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለውጥ እንዲመጣ አግዟል።

የፍትህና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱና የፀረሙስና ትግሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በፍትህ ሳምንት የተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን