አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Sunday, 14 May 2017

አዲስ አበባ ግንቦት 6/2009 ቻይና ለታዳጊ አገሮችና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ስምንት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ ፕሬዝዳንት ዢ ጃንፒንግ ቃል ገቡ።

ድጋፉ የሚደረገው አገሮችን በመሰረተ ልማቶች ለማስተሳሰር በነደፈችው የ"ቤልት ኤንድ ሮድ" ልዩ መርሃ ግብር መሰረት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የ29 አገራት መሪዎች በተሳተፉበት በዚሁ መድረክ ላይ ፕሬዝዳንቱ የ"ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ" ዝርዝር እቅድን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነው ቃል የገቡት።

ፕሬዝዳንቱ እኤአ በ2014 የታዳጊ አገሮች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ለተመሰረተው የ"ሲልክ ሮድ ፈንድ" 14 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚደረግም ነው ያስታወቁት።

በተጨማሪ ቻይና በ"ቤልት" ስር ባሉ አገሮች መካከል ትብብሩን ለማጠናከርና ፈጠራን ለማነቃቃት ሃምሳ ላብራቶሪዎችን በጋራ እንደምታቋቁም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ጃንፒንግ  ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እስያ፣ አውሮፓ እና አፍሪካ በኢኮኖሚው ዘርፍ በትብብር እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የጋራ ራዕይ በመያዝ በተቀናጀ፣ በተባበረና ዘላቂ ደህነነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ዘላቂ ሰላም ያለበትን አካባቢያዊ ሁኔታ በመፍጠር ሽብረተኝነትን መዋጋት እንደሚያስፈልገ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

የ"ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ" ከደቡብ ፓስፊክ አንስቶ ደቡብና መካከለኛ እስያና አውሮፓን እንዲሁም አፍሪካን የሚሸፍን ሲሆን፤ 60 አገሮችን ያቅፋል።

በኢኒሼቲቩ ቻይና የመሠረተ ልማት ግንኙነቱን ለማሻሻል በበርካታ ዋና ዋና ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ተሰማርታለች። ከነዚህ መካከል ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የተገነባው የባቡር መስመር የሁለቱን አገሮች ከተሞች በማገናኘት ረገድ ተጠቃሽ ነው።

በተጨማሪም ከጃካርታ - ባንዶንግ፣ ከቻይና - ላኦስ እና ከሀንጋሪ - ሰርቢያ የተገነባው የባቡር መስመርን ጨምሮ በጓዳርና በፔሩስ የተገነቡት ወደቦች የኢኒሼቲቩ እውነታነት ማሳያ ተደርገው ይጠቀሳሉ።

በቀጣይም የሕዝቦችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በምድር፣ በባህርና በአየር የመጓጓዣ መስመርና በመረጃና ኮሙኒኬሽን ስርዓት በአካተተ መልኩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንደሚጀመሩ ይጠበቃል።

ከዚሁ መድረክ ጎን ለጎን በተካሄደ የከፍተኛ ባለስልጣናት ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ቻይና ለዓለም እድገትና ብልጽግና ወሳኝ ሚና እየተጫወተች መሆኑን ገልጸዋል። 

ታዳጊ አገሮች በተለይም አፍሪካውያን ለእድገትና ብልፅግና በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቻይና ታላቅ አጋር መሆኑዋን ነው ያብራሩት። 

አብዛኛዎቹ ታዳጊ አገሮች በተለይም አፍሪካውያን ከድህነት ለመውጣት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቻይናን እንደ ስኬታማ የኢኮኖሚ አርአያ እየተከተሏት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም "ኢኒሼቲቩ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ግጭት አልባ የሆነ ግዙፍ የኢኮኖሚ ትብብር ራዕይ መገለጫ ነው። የቻይና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እና ምርጥ ልምዶችን ለመቅሰምም አቅም የሚሰጥ ነው" ብለዋል።

"ቻይና በዓለም አቀፍ ትብብር ላይም ግንባር ቀደም በመሆን  ቁርጠኝነቷን እያሳየች ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ ኢኒሼቲቩ አካባቢያዊ ትብብርን በማጠናከር ረገድና ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት በማምጣት እንዲሁም የ2030 የልማት አጀንዳን ለማሳካት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል። 

ኢንሼቲቩ የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካውያን ራዕይ ለማሳካት ካወጣው አጀንዳ 2063 ጋር የተጣጣመ መሆኑን ነው የገለጹት።   

''የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ'' በቻይናው ፕሬዝዳንት ጃንፒንግ እ.ኤ.አ በ2013 የመነጨ ልዩ መርሃ ግብር ነው።

ይህ ልዩ መርኃ ግብር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ2030 ይደረስባቸዋል ብሎ ያቀዳቸውን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት ያስችላል ተብሎ ይታመናል። 

ኢኒሼቲቩ በተለይ በአፍሪካ ለሚተገበሩ የልማት ሥራዎች አማራጭ የገንዘብ፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢንቨስትመንትና ሰፊ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥር እምነት ተጥሎበታል።

Published in ኢኮኖሚ

ጎንደር ግንቦት 6/2009 የኢትዮጵያና የሱዳን ህዝቦችን የቆየ ወዳጅነትና ግንኙነት በማጠናከር በኩል የሁለቱ ሀገራት  የፓርላማ አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የንግዱ ማህበረሰብ ወሳኝ ድርሻ እንዳላቸው ተገለጸ፡፡

በሱዳን የገዳሪፍ ግዛት የፓርላማ አባላት የሀገር ሽማግሌዎችንና የንግዱን ማህበረሰብ  ያቀፈ የልኡካን ቡድን ከሰሜን ጎንደር አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የንግዱ ማህበረሰብ ጋር ዛሬ በጎንደር ከተማ ተወያይተዋል፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየልኝ ሙሉአለም በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የቆየ ወዳጅነት መጠናከር  የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ የጎላ ሚና ይጫወታል፡፡

በሱዳን ገዳሪፍ ግዛት የልኡካን ቡድን አባላት ወደ ጎንደር መምጣታቸው በተለይ የድንበር አካባቢ ህዝቦችን በንግድ ፣በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምና በባህል ዘርፍ የሚኖራቸውን ትስስር የሚያጠናክር ነው፡፡

"ለሁለቱ ሀገራት  ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣት የነዳጅ፤ የሃይል አቅርቦትና የወደብ አጠቃቀም  ግንኙነቱ ማሳያ ነው "ያሉት አቶ አየልኝ ይህም ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

"ይህን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትና ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር በኩልከሱዳን ገዳሪፍ ግዛት የመጣው የፓርላማ የልኡካን ቡድን ወሳኝ ሚና አለው " ብለዋል፡፡

በቅርቡ የሰሜን ጎንደር አመራሮች ከገዳሪፍ ግዛት አመራሮች ጋር ገዳሪፍ  ባካሄዱት የጋራ ምክክር መድረክ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ተፈጻሚ እየሆነ መምጣቱንም ጠቅሰዋል፡፡

የገዳሪፍ ግዛት የልኡካን ቡድን መሪ አብደላ ረሃምተላ በበኩላቸው ለልኡካን ቡድን የተደረገው አቀባበል አባላቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው ኢትዮጵያ ለሱዳናውያን ሁለተኛ ሀገራቸው እንደሆነች ተናግረዋል፡፡

"ከጉርብትና ባለፈ የኢትዮጵያን ህዝብ ከሱዳን ወንድሞቻችን ነጥለን አናያቸውም፤  በዘመናት የዳበረ የህዝብ ለህዝብ ታሪካዊ ግንኙነት አለን" ብለዋል፡፡

የአሁኑ አመጣጣቸውም የሁለቱን ሀገራት  የቆየ ወዳጅነት በባዛርና በንግድ ትርኢቶች ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታችን ይበልጥ የሚጠናከርበትን መንገድ ለማመቻቸት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"የገዳሪፍና የጎንደር ከተማ የህዝብ ምክር ቤቶች ለሁለቱ ሀገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጠናከር ተቀራርበው ይሰራሉ" ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ መነን አሰፋ ናቸው፡፡

በተለይ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያም ከሱዳን የገዳሪፍ ግዛት ሴት አመራሮች ልምድ መለዋወጥና በጋራ መስራት  እንደሚፈልጉ ጠቅሰዋል፡፡

የጎንደር ከተማ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካይ ኢንጂነር መላኩ እዘዘው "በተለይ የንግዱ ማህበረሰብ በጎንደርና በገዳሪፍ ግዛት መካከል ዓመታዊ የንግድ ትርኢትና ባዛር እንዲዘጋጅ በማድረግ የሁለቱን ህዝቦች ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ማጠናከር አስፈላጊ ነው "ብለዋል፡፡

የሱዳን ባለሀብቶች ጎንደር መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ  በማበረታታት በኩል የገዳሪፍ ግዛት የልኡካን ቡድን ጥረት እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

" በጎንደር የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትም ግንኙነታቸው እንዲጠናከር በጋራ እንሰራለን" ብለዋል፡፡

ከገዳሪፍ ግዛት ባሶንዳ ዞን የመጡት የልኡካን ቡድኑ አባል ጃፋር አህመድ በበኩላቸው ሰሜን ጎንደር ዞናቸውን የሚያዋስን በመሆኑ በንግድ ፣ባህልና በስፖርት ዘርፍ ግንኙነት መፍጠር ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከፓርላማ አባላት ከሀገር ሽማግሌዎችንና ከንግዱ ማህበረሰብ የተውጣጡ 15 አባላትን ያቀፈው የገዳሪፍ ግዛት የልኡካን ቡድን በጎንደር ከተማ ለሶስት ቀናት ይቆያል፡፡

ዛሬ የሁለቱን ሀገራት  የድንበር አካባቢ ህዝቦች ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የጋራ ምክክርና የልምድ ልውውጥ ያደረጉ ሲሆን የልኡካን ቡድኑ የፋሲል ቤተ- መንግስትንም ጎብኝቷል፡፡        

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ግንቦት 6/2009 የወጣቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ መልካም አስተዳደር የማስፈን ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ።

 የፌዴራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር አካባቢ ልማት ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ካሳ ተክለብርሃን በበኩላቸው፤ ወጣቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚ ማድረግ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል። 

 ሚኒስትሩ አቶ ካሳ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን "ወጣቶችና ኢትዮጵያዊነት" በሚል መሪ ሃሳብ አወያይተዋል።

 በውይይቱ ወቅት ተማሪዎቹ ኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለማጎልበትና ለማጠናከር የሚቻልበትን ነጥቦች አንሰተዋል። ኢትዮጵያዊነት ስሜትን ከማጎልበት ባሻገር የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ፣ የግጭት መንስኤዎች እንዲወገዱ ለማድረግ ይበጃሉ ያሉዋቸውን ሀሳቦችም ሰንዝረዋል።

 በዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዓመት የህግ ተማሪ ሙስጠፋ መሃመድ በወቅቱ በሰጠው አስተያየት፤ በአገሪቷ የመልካም አስተዳደር እጦት መኖሩ ወጣቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ነው። በአገራቸው ሰርተው የመቀየር እምነታቸውን እየሸረሸረውም መጥቷል።

 "ወጣቶች ከአገራቸው ጠባቂ ብቻ መሆን የለባቸውም" ያለው ተማሪ ሙስጠፋ፤ ነገር ግን በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ያለው ውስብስብ ቢሮክራሲና የተንዛዛ አሰራር ወጣቱን በአገሩ ላይ ሰርቶ የመቀየር እምነት እንዳይኖረው እያደረገ መምጣቱን ነው ያስረዳው።

 አንዳንድ ወጣቶች “ከዩኒቨርሲቲ፣ ከኮሌጅም ሆነ ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ተመርቀው ስራ አጥተው ሲጉላሉና ስደትን እንደአማራጭ ሲጠቀሙ ይስተዋላል” ብሏል።

 በመሆኑም መንግስት የወጣቶችን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት መልካም አስተዳደር ማስፈን ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባው ነው የጠቆመው።

 የሦስተኛ ዓመት የኢኮኖሚክስ ተማሪ  ወጣት ሄኖክ ካሳሁን በበኩሉ እንደገለጸው፤ የመልካም አስተዳደር እጦት ዛሬም ያልተፈታ የወጣቶች ጥያቄ ነው።

 የአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያዊ አንድነት መፍጠር የመንግስት ብቻ እስኪመስል ድረስ እንደሚሰብኩ ጠቁሞ፤  ይህም ወጣቶች በአገራቸው ጉዳይ የራሳቸው ድርሻ የሌላቸው እያስመሰለ መምጣቱን ተናግሯል።

 ወጣቶች በአገሪቷ ጉዳይ የኃላፊነትና ውሳኔ ሰጭነት እድል እየተሰጠው ያለመሆኑን ነው በውይይቱ ወቅት ያነሱት።

 በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት መንግስት በየአካባቢው የሚገኙትን ወጣቶችን ያለማወያየቱም ትክክል ያለመሆኑን አመልክተዋል።

 የፌደራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር አካባቢ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ካሳ ተክለብርሃን በበኩላቸው እንደተናገሩት፤  መንግስት የወጣቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

 ዘላቂ መፍትሄዎችን በማምጣት ሂደት የሚከሰቱ ጊዜያዊ ችግሮችን እንደሚኖሩ አመልክተው፤ ለዘላቂ መፍትሄው “ወጣቶች ወደ ራሳቸው ማየትና በሰከነ መንፈስ መታገል አለባቸው” ብለዋል።

 የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሁንም እንዳልተፈቱ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ወጣቶችም የሚጠበቅባቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

 የመልካም አስተዳደር እጦት እየተወሳሰበ ሲመጣ የተሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ስለሚያፈርስ ወጣቶች ከመንግስት ጎን እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

 የአንድ አገር ዘላቂ ሰላምና ቀጣይነት ያለው እድገት የሚለካው በወጣቶች ንቁ ተሳትፎ በመሆኑ ስደትን ከመመኘት በአገራቸው ሰርቶ የመለወጥ ስሜት ሊያዳብሩ እንደሚገባም ነው አጽንኦት የሰጡት።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 6/2009 ያዩ ማዳበሪያ ኮምፕሌክስ ፕሮጀክት አፈፃፀም ከገንዘብ አጠቃቀሙ ጋር ተጣጥሞ ያለመሄዱን በግምገማ ማረጋገጡን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

የቋሚ ኮሚቴ አባላት የፕሮጀክት ሄደቱን በተመለከተ የመስክ ምልከታ ባካሄዱበት ወቅት አፈፃፀሙ ከበጀቱ ጋር ያለመጣጣሙን በመገምገም እንዲስተካከል መመሪያ ሰጥተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ገብረእግዚያብሄር አራዓያ እንደተናገሩት፤ የፕሮጀክቱ ሂደት በመጓተቱ ተጨማሪ ወጪ እንዲወጣ መንስዔ እየሆነ ነው።

ስለዚህ ግንባታውን የሚያከናውነው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት ይጠበቅበታል።

ፕሮጀክቱ በ2004 ዓ.ም ሲጀመር የአገሪቷን የግብርና ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግና የእድገቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ተስፋ ተጥሎበት እንደነበር አስታውሰው፤ ለዚህ ፕሮጀክት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ለፕሮጀክቱ የዘጠኝ ነጥብ ሰድስት ቢሊዮን ብር ውል ሲፈጸም በ2006 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ታስቦ ነው።

በአሁኑ ወቅት የግንባታ ሂደቱ የደረሰው 46 በመቶ ላይ ሲሆን፤ የገንዘብ አጠቃቀሙ 60 በመቶ መሆኑ ታውቋል።

ኮርፖሬሽኑ በጀቱ ወደ 14 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ጥያቄ ማቅረቡም ተገልጿል።

በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ያዩ ማዳበሪያ ኮምፕሌክስ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ባያብል ይሁኔ በሰጡት ማብራሪያ፤ ለፕሮጀክቱ ግንባታ መዘግየት የካሳ ክፍያ በወቅቱ ያለመድረስና መጓተቱ እንዲሁም ህብረተሰቡን የማግባባት ስራዎች ጊዜ መውሰዳቸው ዋነኛዎቹ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ አፈፃፀምና ለግንባታው የወጣው ወጪ ልዩነት ያሳየው ለፋብሪካው የሚተከሉ መሳሪያዎችና ግብዓቶች በአገር ወስጥና በውጪ ተመርተው የሚጓጓዙ በመሆናቸው ነው ያሉት ሻለቃ ባያብል፤ መሳሪያዎች ሲተከሉ የፕሮጀክቱ ግንባታ አፈፃፀምና የገንዘብ ወጪ እንደሚጣጣም ተናግረዋል። 

የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ፕሮጀክቱን በ2010 መጨረሻ ላይ ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

የያዩ ማዳበሪያ ኮምፕሌክስ ፕሮጀክት በኢሉ አባቦራ ዞን በያዩ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን፤ የድንጋይ ከሰል በጥሬ እቃነት በመጠቀም የዩሪያ ማዳበሪያ ለማምረት የተቋቋመ ፕሮጀክት ነው።

በፕሮጀክቱ የዩሪያ ማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ መትከል፣የድንጋይ ከሰል ማልማትና የሃይል ማመንጫ ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

Published in ኢኮኖሚ

ጎንደር ግንቦ  6/2009 ባህላዊ የእጽዋት መድኃኒት በዘመናዊ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማስቻል የቤተ ሙከራ ሳይንሳዊ ምርምር እያካሄደ መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

 ተቋሙ ምርምሩን እያካሄደ ያለው ህብረተሰቡ ለቁስል ፣ ለጉበት ለወባና ካንሰር በሽታዎች በሚጠቀምባቸው የእጸዋት መድኃኒት ላይ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የፋርማሲ ትምህርት ቤት መምህር  ረዳት ፕሮፌሰር አብዮት እንዳለ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

 የእጽዋት መድኃኒት ለዘመናት በባህላዊ መንገድ ህብረተሰቡ ሲጠቀምባቸው የቆየ ቢሆንም ፈዋሽነታቸውና መርዛማነታቸውን በሳይንሳዊ ምርምር በማረጋገጥና በዘመናዊ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ በኩል የተከናወነ ተግባር የለም፡፡

 ረዳት ፕሮፌሰሩ እንዳሉት ዩኒቨርሰቲው በተለይ ለወባና ለጉበት በሽታዎች የሚውሉ የእጽዋት መድኃኒት ላይ ትኩረቱን በማድረግ በአሁኑ ወቅት ፈዋሽነትና መርዛማነት በአይጦች ላይ በቤተ-ሙከራ ምርምሩን እያካሄደ ነው፡፡

 ለወባ በሽታ ተብለው በባህላዊ መድኃኒት  አዋቂዎች የሚታዘዙት ላይ  ላለፉት ሁለት ዓመታት የተደረገውን ሳይናሳዊ ምርምር በማጠናቀቅ በመጪው ዘመን  ውጤቱን ይፋ ለማድረግ የምርምር ክፍሉ መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል፡፡

 በእጽዋት መድኃኒት  ላይ የሚካሄዱ ምርምሮችን ከማጠናከር አኳያም የባህል መድሃኒት አዋቂዎችን ከማሰልጠን ጀምሮ አብሮ በመስራትና የእውቀት ሽግግር የሚፈጠርበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኩል ዩንቨርሲቲው እየሰራ ነው፡፡

 ተቋሙ  በዘርፉ የምርምር አድማሱን ከማስፋት አንጻርም እንግሊዝና አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት ለመመስረት ጥረት እያደረገ ነው፡፡

 ዝርያቸው ተመናምኖ በመጥፋት ላይ የሚገኘው የእጸዋት መድኃኒትን ጠብቆ ለማቆየትም ዩኒቨርሲቲው ከወንዶ ገነት የእጸዋት ጥበቃና ልማት ተቋም ጋር ግንኙነት በመመስረት የእጸዋት መድኃኒት እያለማ መሆኑንም ረዳት ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡

 በዩኒቨርሲቲው በቅጥር ግቢው ውስጥም የእጽዋት መድኃኒት የማልማት ስራ ካለፈው ዓመት ወዲህ መጀመሩን ጠቁመው  "ለመድኃኒትነት የሚውሉ 75 ያህል የእጸዋት ዝርያቸው አደጋ ላይ እንደሚገኝ በጥናት መለየት ተችሏል "ብለዋል፡፡

 እነዚህን ዝርያዎች ለመታደግ ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

 እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አብዮት ገለጻ ለመድኃኒትነት የሚጠቅሙ  የእጸዋት ዝርያዎችን  በመንከባከቡና በማልማቱ ስራ ላይም የባህል መድኃኒት  አዋቂዎች ሰፊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግም እያስተባበሩ ይገኛሉ፡፡

 ዩንቨርሲቲው ለመጥፋት የተቃረቡና ለመድኃኒት የሚውሉ  የእጸዋት ዝርያዎች ጠብቆ ለማቆየት የሚያከናውናቸውን ተግባራት በመደገፍ  ተቋሙ እንዲያለማቸው በችግኝ መልክ አዘጋጅተው መስጠታቸውን የተናገሩት ደግሞ በባህል ህክምና ላይ የተሰማሩት  አቶ ካሴ ገነት ናቸው፡፡

 የዘርአብሩክ የባህል ህክምና አዋቂዎች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ነጋ አናኒያ በበኩላቸው ማህበሩ ከጎንደር ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለመድኃኒትነት የሚውሉ የእጽዋት ዝርያቸው ተቋሙ ባዘጋጀው ቦታ ላይ በማልማት እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 በባህል መድኃኒት አቀማመጥ ፣ቅመማና ህክምና አሰጣጥ ላይም ተቋሙ በዘመናዊ አሰራሮች  የተደገፈ የተግባር ስልጠና ለማህበሩ አባላት በመስጠት ድጋፍ ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ግንቦት 6/2009 የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ  አድሃኖም   ከምርጫ    ቅስቀሳው ጋር  በተያያዘ  ለሁለት  ቀናት የስራ   ጉብኝት   ካይሮ   ገብተዋል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ  ካይሮ  አለም አቀፍ  አየር  ማረፊያ   ሲደርሱ  የሀገሪቱ  የውጭ  ጉዳይ   የአፍሪካ  ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር  ሞሃመድ   ኢድሪስ    አቀባበል   አድርገውላቸዋል፡፡

ከውጭ  ጉዳይ  ሚኒስትሩ  ሳሜህ  ሹክሪ   በሞሃምድ   ኢደሪስ   በኩል ለቴወድሮስ  አድሃኖም  ሰላምታ  ማድረሳቸው ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ  አፍሪካን  ወክላ  ለአለም ጤና  ድርጅት  ዋና  ጸኃፊነት   ለምታደርገው  የምርጫ  ፉክክር  ሀገራቸው  ግብጽ  ድጋፍ  እንደምታደርግም ለቴድሮስ  አድሃኖም  መልዕክታቸውን  አስተላልፈዋል፡

የውጭ  ጉዳይ  ሚኒስትሩ  ከምርጫው  ጋር  በተያያዘ  ወደ  ጀኔቫ  ለሚያቀናው  የግብጽ  ልዑክ ለኢትዮጵያ  ድምጽ   እንዲሰጥም  አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ   አፍሪካን   ወክላ  ለአለም  ጤና  ድርጅት ዋና  ፀኃፊነት  ከተመረጠች   የአህጉሪቱን  ጥቅም  እንደምታስከብር  ተናግረዋል፡፡ 

የመጨረሻው  ምርጫ  በጀኔቫ  ግንቦት  15 እንደሚደረግም ታውቋል፡፡

ምንጭ፡- http://www.egyptindependent.com           

Published in ፖለቲካ

ደብረ ብርሃን ግንቦት 6/2009 የደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በህክምና  እና በሒሳብ ትምህርት በዶክትሬት ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 51 ባለሙያዎችን ዛሬ አስመረቀ።

 ተቋሙ በጤናውና በሒሳብ  ዘርፍ የሚስተዋለውን  የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ለማሟላት የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን  የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ተፈራ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ገልጸዋል፡፡

 ለዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት በዶክትሬት ዲግሪ ለህክምናው የሚመጥናቸውን እውቀትና ክህሎት የያዙ 46 የጤና ባለሙያዎችን አሰልጥኖ   ለምረቃ ማብቃታቸውን ተናግረዋል።

 ቀሪዎቹ አምስት ባለሙያዎች ደግሞ በሒሳብ ትምህርት  የዶክትሬት ዲግሪ  የሰለጠኑ ሲሆን አጠቃላይ ከተመረቁትም ውስጥ ዘጠኙ ሴቶች ናቸው፡፡

 ተመራቂዎቹ  ቀደም ሲል በሙያቸው ከሦስት ዓመት በላይ ያገለገሉና በዩኒቨርስቲው የተሰጠውን ትምህርት ያጠናቀቁ መሆናቸውን ጠቁመው  ሰልጣኞቹ  በቀሰሙት  እውቀት ህዝቡን ከአድሎና ከሙስና በፀዳ መንገድ ማገልገል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

 የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶከተር አሚን አማን በበኩላቸው ባለፉት 25 ዓመታት በተደረገው ጥረት በጤናው ዘርፍ የተማሪዎች የዩኒቨርስቲ  የቅበላ አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።

 የጤና አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግም 16ሺ ጤና ኬላዎች፣ ከ3ሺ 500 በላይ ጤና ጣቢያዎችና ከ300 በላይ ሆስፒታሎች መገንባታቸውንም አመልክተዋል፡፡ 

 በዚህም መከላከል መሰረት ያደረገውን የጤና ፖሊሲ ግቡን እንዲመታ ከማገዙም በላይ የተሻለ የህክምና አገልግሎት መስጠት እንዳስቻለም  ጠቁመዋል።

 ከተመረቂ ተማሪዎች መካከል ዶክተር ህይወት ደበበ በቆይታቸው  ያገኙትን  እውቀትና ልምድ በመጠቀም ህብረተሰቡን በቅንናትና በታማኝነት ለማገልግል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

 ሌላው  ተመራቂ ዶክተር ተወደደው ባልከዉ "ሀገሪቱ  በጤናው ዘርፍ ያለባትን  የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት ለማሟላት ያገለገሉ ሙያተኞችን በማሰልጠን ማብቃት መጀመሯ መንግስት ዘርፉን  ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል "ብሏል።

 በቀጣይ በዘርፉ ለማገልገል መንግስት በሚመድበው  ስፍራ ሄዶ በሙያው ህዝብ ለማገልገል ዝግጁ መሆኑም ገልጿል፡፡ 

 የደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ዓመታዊ የተማሪ የቅበላ አቅሙን 25 ሺህ ማድረሱም ተመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

 ሐረር ግንቦት 6/2009 በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የአፍረን ቀሎ ማህበረሰብ የገዳ ስርዓት ዳግም ተቋቋመ።

 በሐረር ከተማ ትናንት በተከናወነው በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ እንደተገለጸው  የገዳ ስርዓት የዴሞክራሲ  ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

 ጥልቅና ሰፊ ሐሳብን ይዞ በኦሮሞ ህዝብ የመነጨው የገዳ ስርዓት ለበርካታ መቶ ዓመታት የማህበረሰቡ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ አቅጣጫ ጠቋሚ ሆኖ አገልግሏል።

 ሆኖም በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ በአገሪቱ በተፈጠሩ ወረራዎች የተነሳ ስርዓቱ ከቦረናና ጉጂ በስተቀር ጸንቶ መቆየት አልቻለም ነበር።

 ለመቶ ዓመታት ተዘንግቶ በቆየባት ምስራቅ ሐረርጌ ዞን የአፍረን ቀሎ ማህበረሰብ ውስጥ ስርዓቱ ዳግም እንዲቋቋም ተደርጓል።

 በኦሮሚያ ክልል ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳይ ኃላፊ ወይዘሮ አልፍያ ሐጂ ዩስፍ እንዳሉት  የገዳ ስርዓት በሀገሪቱ  በነበረው  የፖለቲካ መዛባት የተነሳ ከቦረናና ጉጂ ጎሳዎች በስተቀር በሌሎች አካባቢ ተዘንግቶ ቆይቷል።

 በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ እየታወሰ የሚገኘውን የገዳ ስርዓት ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ለማስፋፋት የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ኦሮሞዎችን የሚወክል አፍረን ቀሎ የሚል መጠሪያ የተሰጠውን የገዳ ስርዓት መቋቋሙን ነው ያስረዱት።

 የድሬዳዋ ባህል ቡድን አባል አባ ቦኮ አብዱልአዚዝ ሱፍያን በበኩላቸው  ከዚህ ቀደም ተበታትነው ይኖሩ የነበሩ ጎሳዎች በአንድ ስርዓት ስር መሰባሰባቸው ለአካባቢው ልማትና እድገት የሚያበረክተው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 እንዲሁም በአካባቢው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር የአባ ገዳ ስርዓቱ መቋቋም የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።

 የገዳ ስርዓት በዞኑ መመስረት በአካባቢው ላይ የሚታዩ ግጭቶችን በማስወገድ ቀጣይና ዘላቂነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ  እንዳለው የገለጹት ደግሞ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው፡፡ 

 የአካባቢው ነዋሪ  አቶ ናስር መሀመድ በሰጡት አስተያየት ተዘንግቶ  የቆየው የገዳ ባህላዊ ስርዓት ዳግም መቋቋሙ መደሰታቸውን ገልጸው ለዚህም አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 በዕለቱም  የአፍረን ቀሎና ሁምበና የአባ ገዳዎች ሰብሳቢ አበገዳ ሙሳ አሊ የተመረጡ ሲሆን የአባ ገዳ ምክር ቤትም ተመስርቷል።

 በኦሮሚያ ሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ አባ ገዳዎች በተገኙበት የምረቃ ስነ ስርዓት በቅርቡም እንደሚካሄድም ተመልክቷል።

 የአፍረን ቀሎ ማህበረሰብ የገዳ ስርዓት ዳግም በተቋቋመበት ስነስርዓት ላይ  የሀገር ሽማግሌዎች፣  የሐይማኖት አባቶች፣  አባ ቦኩዎችና የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

 የገዳ ስርዓትበተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት ፣የሳይንስና  የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ  ቅርስነት  በተያዘው ዓመት መመዝገቡ ይታወሳል።

Published in ማህበራዊ

ባህርዳር ግንቦት 6/2009 በአማራ ክልል ደጋው አካባቢ አርሶ አደሩ በኩታገጠም ተደራጅቶ የቢራ ገብስን  በስፋት እንዲያለማ ተገቢውን ድጋፍ መደረግ እንዳለበት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሳሰቡ።
 
በቢራ ገብስ ልማት ላይ በሚስተዋሉ ችግሮችና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ በደብረታቦር ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በውይይቱ ወቅት " የቢራ ገብስ ልማት ለደጋው አርሶ አደር  በምግብ ራሱን እንዲችል ወቅቱ የፈጠረለት አዲስ የኢኮኖሚ ተስፋ ነው" ብለዋል።

የቢራ ገብሱን በቋሚነት መጠቀም የሚችሉ የቢራ ፋብሪካዎች በሃገሪቱ በፍጥነት መስፋፋትና ማደግ ለምርቱ አስተማማኝ ገበያ የተፈጠረለት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ይህንን እድል ለመጠቀም አርሶ አደሩን በኩታገጠም በማደራጀትና የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በወቅቱ በማመቻቸት ሰብሉ በስፋት እንዲያለማ ተገቢው ድጋፍ መደረግ  እንዳለበት አሳስበዋል።

በተለይም አርሶ አደሩ ለገበያ ብሎ ጥራቱን የጠበቀ የቢራ ገብስ እንዲያመርት ግንዛቤውን በማሳደግና ክህሎቱን በማዳበር የግብርና ባለሙያዎች በቁጭት መሰራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የቢራ ገብስ ልማት አርሶ አደሩን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር  ለቢራ ፋብሪካዎች ብቅል ከውጭ  ለመግዛት ሃገሪቱ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረትም የላቀ ሚና እንደሚጫወትም አቶ ገዱ አመልክተዋል።

ባለፈው የመኸር ወቅት የተመረተ 85 ሺህ ኩንታል የቢራ ገብስ ምርት ለጎንደር ብቅል ፋብሪካ አርሶ አደሮች ማቅረባቸውን የገለጹት ደግሞ  የክልሉ  ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መልኬ ታደሰ ናቸው።

ለፋብሪካው ካቀረቡት የቢራ ገብስ ምርትም 100 ሚሊዮን የሚጠጋ  ብር  ለአቅራቢ አርሶ አደሮች መከፋፈሉንም አመልክተዋል፡፡

ነገር ግን አርሶ አደሮቹ ያመረቱትን የቢራ ገብስ ምርት ለቤት ውስጥ ፍጆታ በማዋል ሙሉ በሙሉ ወደ ብቅል ፋብሪካው  እንዳላቀረቡም ጠቁመዋል፡፡  

ችግሩን በቀጣይ ለመፍታት በግብርና ባለሙያዎች እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በሚቀጥለው የምርት ወቅት ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም ጠቅሰዋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን ላይ የጋይንት ወረዳ ነዋሪው  አርሶ አደር ቄስ መልኬ ነጋሽ  ባለፈው የመኸር ወቅት ካለሙት አንድ ሄክታር ከሩብ መሬት ከሰበሰቡት 47 ኩንታል ምርት  ሽያጭ  52 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

አሲዳማ መሬትን በኖራ በማከምና ማዳበሪያ በመጠቀም በመስመር መዝራት በማልማታቸው የተሻለ ምርትና ጥቅም ማግኘት እንደቻሉም ጠቅሰዋል፡፡

በዚሁ ዞን እስቴ ወረዳ የአጉና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ውለታው ተሾመ በበኩላቸው በሁለት ሄክታር ተኩል መሬት ላይ ባለፈው የመኸር ወቅት አልምተው ከሰበሰቡት ምርት ሽያጭ ከ96 ሺህ ብር በላይ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የዳሽን ቢራ ፋብሪካ የማህበራዊ ግብይት ስራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው አበበ እንዳሉት ተገቢውን የብቅል ግብዓት ለማግኘት  አርሶ አደሮችን ለማሰልጠን ከሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በመመደብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ ነው።

በተለይም የቢራ ገብስ የተሻለ ምርጥ ዘር እንዲገኝ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ለምርምር ተቋማት በመስጠት የተሻለ አማራጭ ዘር ለማሰባሰብም ጥረት እየተደረገ መሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

በቢራ ገብስ ልማት ላይ የሚስተዋሉ  ችግሮችና በመፍትሄዎች ዙሪያ በተደረገው ውይይት ከምርምር ተቋማት፣ ቢራ አምራች ከሆኑ አካባቢዎች የመጡ አርሶ አደሮች፣ ባለሙያዎችና አመራሮች ተሳትፈዋል።

አርሶ አደሩን በመደገፍና የተሻለ የቢራ ገብስ ልማትና ግብይት ላካናወኑ ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ቀበሌዎችና የህብራት ስራ ማህበራት የዋንጫ፣ የሰርተፍኬትና የኮምፒዩተር  ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ግንቦት 6/2009 የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ አጓጊ ለሆነው አዲሱ ሲልክ ሮድ ዕቅድ 124 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገቡ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ዕቅዱ በባላንጣነትና በበላይነት የመኖር እሳቤን በማስቀረት የሰላም፣የአብሮነትና  የጋራ ንግድን ለማጠናከር  የሚያስችል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በቤጂንግ ለሁለት ቀናት የሚካሄደውን ስብሰባ ሲከፍቱ እንደተናገሩት ለጋራ ልማት የትብብር መንገዶችን የመገንባትና ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚን ክፍት ማድረግ ይገባናል ብለዋል፡፡

በአገሮች መካከል ልማትን ለማፋጠን ትክክልና ግልጽ የሆነ ዓለም አቀፍ ንግድና የኢንቨስትመንት ህግ እንዲኖር ማበረታታት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

"ንግድ ለኢኮኖሚ ልማት አስፈላጊ የሆነ ሞተር ነው" ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡

ቻይና በኤሺያ፣ አፍሪካና አውሮፓ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማስፋት ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ የተሰኘውን አዲስ ዕቅድ እአአ በ2013 በይፋ ጥሪ ማድረጓ የሚታወስ ነው፡፡

ሁሉ አቀፍ የንግድ ስርዓት፣ የነጻ ንግድ ቀጠናና ነጻ ንግድ እንዲፈጠር መላው ዓለም ጉልህ ሚና ሊጫወት እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ ማሳሰባቸውን የዘገበው ሮይተርስ ነው፡፡

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን