አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Saturday, 13 May 2017

አዳማ ግንቦት 5/2009 በአርሲ ዞን ዴራ እና ኢተያ ከተሞች መካከል በተከሰተው ጎርፍ የመደርመስ አደጋ የደረሰበትን መንገድ በአስቸኳይ ለመጠገን እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

አዳማ ከተማን ከአሰላ ከተማ በሚያገናኘው በዚህ የአስፋልት መንገድ ላይ የመደርመስ አደጋ የደረሰው ትናንት ሌሊት በአካባቢው የጣለው ኃይለኛ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ምክንያት ነው።  

የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለኢዜአ እንደገለፁት የተከሰተው ጎርፍ በዴራና ኢተያ ከተሞች መካከል በሚገኘው የአስፓልት መንገድ ላይ ጉዳት አድርሷል።

አቶ ሳምሶን እንዳሉት፣ ላጋጠመው ችግር አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፕሬሽን የጥገና ቡድን ዛሬ ወደ ስፍራው ተጉዟል።

የአርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብድላ ኦገቴ በበኩላቸው፣ የዞኑ መንገዶች ባለስልጣን ለችግሩ ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት ዛሬ ጠዋት ላይ ተለዋጭ መንገድ ሰርቶ ለትራፊክ ክፍት ማድረጉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያለው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በትራፊክ ፖሊስ እገዛ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ መንገዱ በአስቸኳይ ካልተጠገነ በቀጣይ የከፋ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል አመልክተዋል።

ዴራና ኢተያ ከተሞች መካከል ትናንት ሌሊት ጉዳት የደረሰበት መንገድ ከአዳማ ከተማ በግምት 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ግንቦት 5/2009 በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የህግ ተማሪዎች መካከል የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች አስመልክቶ በተካሄደ የምስለ ችሎት ክርክር ውድድር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሸነፈ።

በዚሁ በጽሁፍና በቃል ክርክር በተካሄደው ውድድር 20 ዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፈዋል። በመጀመሪያው ዙር የጽሁፍ ውድድር ከተሳተፉት መካከልም ለቃል ክርክር ያለፉት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል እና የአለም አቀፉ ቀይ መስቀል  ኮሚቴ በጋራ ባዘጋጁት ውድድር ለፍጻሜ የደረሱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህግ ተማሪዎች ናቸው። 

አሸናፊውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ክፍልን ወክለው የተወዳደሩት ተማሪ ሊያ መሃሪና ተማሪ አሜን ታዬ ለውድድሩ ከመቅረባቸው በፊት በሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ዙሪያ በርካታ መጽሐፍትና ጥናታዊ ጽሁፎችን ማንበባቸውን ነው የገለጹት።

ተማሪ ሊያ እንደምትለው፤ ዝግጅቱም ሆነ ውድድሩ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችና ህጎችን ላይ ያላትን እውቀት እንድታዳብር አስችሏታል።

የትምህርት ቤት ቆይተዋን አጠናቃ ወደ ስራ አለም ስትገባም አቅም ሊሆናት እንደሚችል ነው ያመለከተችው።

እንደዚህ ዓይነት ተግባርና ክህሎትን ያጣመሩ ውድድሮች በሌሎች የትምህርት ክፍሎችም እየተለመዱ መምጣት እንዳለባቸው ጠቁማ፤ ይህ በስራ ዓለም ውጤታማ ተግባር ለማከናወን እንደሚረዳ ነው የገለጸችው።

ተማሪ አሜን በበኩሉ "ውድድሩ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ያለኝን እውቀት በተግባር እንድፈትሽ አስችሎኛል" ብሏል።

ውድድሩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎችን፣ ግጭቶች በሚፈጠሩበት ወቅት የሰው ልጆች መብቶች መጣስ ችግርን ከማቃለል እና ግንዛቤን ከማሳደግ አኳያ የፈጠራ ታሪኮችን በማቅረብ የተደረገ የምስለ ችሎት ውድድር ነው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ሃላፊ አቶ ዮናስ ቢርመታ እንደተናገሩት፤የውድድሩ መካሄድ በአገሪቷ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነትን ያጠናክራል። ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር አስተዋጽኦ አለው።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል በቀጣይ በታንዛንያ  በሚደረገው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች እውቀት የምስለ ችሎት ውድድር እንደሚሳተፍ ያመለከቱት አቶ ዮናስ፤ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ውድድር የሶስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን አስታውሰዋል።

ባለፈው ዓመት በአገሪቷ ለመጀመሪያ ጊዜ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በተካሄደው የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች የምስለ ችሎት ውድድር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንደኛ መውጣቱ አይዘነጋም።

Published in ማህበራዊ

ደብረ ብርሃን ግንቦት 5/2009 በሀገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ወደ ማህበረሰቡ ወርደው ችግር እንዲፈቱ እየተደረገ መሆኑን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ አራተኛው ዓለም አቀፍ የምርምር ሲፖዚየም "ምርምርና ፈጠራ ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ቃል በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ለሦስት ቀናት ተካሂዷል።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንደገለጹት፣ በሀገሪቱ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ከተጀመሩ ከ70 ዓመታት በላይ ቢቆጠርም ምርምሮቹ ለማህበረሰቡ ችግር መፍቻ ይውሉ እንዳልነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄዱ የምርምር ሥራዎች በቁጥር እያደጉ መምጣታቸውን ጠቁመው፣ የጥናትና ምርምር ውጤቶች  በተግባር የህዝብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአንኮበር አካባቢ የጀመረው የባህላዊ መድኃኒት ጥናትና ምርምር እንዲሁም በሸዋሮቢት አካባቢ የአርሶአደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ያካሄደውን ጥናት በአብነት አንስተዋል።

በተጨማሪም "የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ በጉና ተራራ አካባቢ የአርሶአደሩን ችግር ለመፍታት የገብስና የበቅሎ ዝርያን በማሻሻል ያካሄዳቸው ምርምሮች አርሶአደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ጀምረዋል" ብለዋል።

ከፍተኛ ገንዘብና እውቀት ፈሶባቸው የሚካሄዱ የምርምር ሥራዎች የሕብረተሰቡን ችግሮች መፍታት እንዲችሉና የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የምርምር ግኝቶችን ፈጥነው ወደ ተግባር ለማሸጋገር የጥናትና ምርምር ምክር ቤቶችን ከማቋቋም ባለፈ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።  

የደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት ደክተር አልማዝ አፈራ በበኩላቸው፣ ባለፉት ዓመታት ዩኒቨርሲቲዉ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናትና ምርምሮችን ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጸዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን በድርቅ ተጋላጭ በሆነው ሸዋ ሮቢት ወረዳ በአሳ ማርባት ባካሄደዉ ምርምር 10 ሰዎች የምግብ ዋስትናቸዉን እንዲያረጋግጡ መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የኢኮኖሚ ችግር ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን  በጓሮ አትክልትና  በዶሮ እርባታ እንዲሁም የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸዉ ላለባቸዉ የማህበረሰብ ክፍሎች የሻማ ማምረቻ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲው በምርምር በማውጣት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ነው የገለጹት።

በአንኮበር የተጀመረው የባህላዊ መድኃኒት ምርምር ከፍተኛ ዉጤት የተገኘበት መሆኑን ጠቁመዉ፣ ወደ ተግባር ያልተሸጋገሩ ነገር ግን  ለትግበራ የተዘጋጁ  ተጨማሪ የምርምር ውጤቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

የምርምር ውጤቶቹ የእዉቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ የሚተገበሩ ሲሆን የሕብረተሰቡን የገቢ ምንጭ ለማሳደግ ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ዶክተር አልማዝ አመልክተዋል። 

እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ በየዓመቱ በዩኒቨርሲቲው የሚካሄደዉ የጥናትና ምርምር ሲፖዚየም የወጣት ተመራማሪዎችን ፍላጎት በማሳደግ በኩል መልካም ተሞክሮ ተገኝቶበታል።

የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸዉ ተፈራ በበኩላቸው የምርምር ሲፖዚየሙ የሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲዎችን በተለያዩ አገራት ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ጋር በማገናኘት የምርምር ባህልን ለማዳበር ያግዛል ብለዋል።

በለፉት ዓመታተ በተካሄደ የጥናትና ምርምር ሲፖዚየም የተገኙት ተሞክሮዎችን በመቀመር ዩንቨርሲቲዉ ለሚያካሂዳቸው የማህበረሰብ አቀፍ ጥናቶች ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማግኘቱንም አስታውቀዋል።

ከሲፖዚየሙ ተሳታፊዎች መካከል በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ መምህር ይርጋለም አለሙ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ የሚካሄዱት ጥናትና ምርምሮች የህብረተሰቡን ችግር ከመፍታት ባለፈ የሀገርን ፖሊሲ ለመቅረጽ ፋይዳቸው ከፈተኛ ነው።

ለሦስት ቀናት በተካሄደው ሲምፖዚየም ከ500 በላይ ምሁራን ተሳታፊ ሲሆኑ ከዉጪ ሀገር የመጡ ምሁራን ልምዳቸዉን ለአገር ውስጥ ተመራማሪዎች ማካፈላቸው ተገልጿል፡፡

ጎንደር ግንቦት 5/2009 አስራ አምስት አባላትን ያቀፈው በሱዳን የገዳሪፍ ግዛት የፓርላማ አባላት ቡድን ሰሜን ጎንደርን ለመጎብኘት ዛሬ ጎንደር ከተማ ገባ።

በገዳሪፍ ግዛት የፓርላማ ህዝብ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ዋና ፀሃፊ አብዱል ሀሰን አሊ ለኢዜአ እንደተናገሩት የፓርላማ አባላቱ ጉብኝት ዋና አላማ የሁለቱን ሀገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከር ነው።

በሶስት ቀን ቆይታውም በንግድ፣ በቱሪዝም በኢንቨስትመንትና በባህል ዘርፍ የእርስ በርስ የልምድ ልውውጥ ያካሄዳል።

የፓርላማ አባላቱ በቆይታቸው ከሰሜን ጎንደር አመራሮች ጋር ገንቢ የሆነ ውይይት የሚያካሄዱ ሲሆን ታሪካዊ ስፍራዎችንም ተዘዋውረው ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሦስት ሴቶች ያሉበት ይሔ የፓርላማ አባላት ቡድን የገዳሪፍ ግዛት የሃገር ሽማግሌዎችንም ያካተተ ሲሆን የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስማማው ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች የዞኑ አመራሮች አቀባበል አድርገውለታል።

Published in ፖለቲካ

አሶሳ ግንቦት 5/2009 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውጤታማ የሆኑ አርሶ አደሮችን ጨምሮ በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ 99 ባለድርሻ አካላት ሽልማት ተሰጠ።

ከተሸለሙት 63 አርሶአደሮች መካከል 22ቱ ሴቶች መሆናቸው ተመልክቷል።

ከተሸላሚ አርሷ አደሮች መካከል በአነስተኛ ማሳ ምርታማነታቸውን እያሳደጉ ወደ ባለሃብትነት በመሸጋገር በአገር አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ የሆኑ አርሷ አደሮች ይገኙበታል፡፡

ባላቸው አነስተኛ ማሳ የሚሰጣቸውን የቴክኖሎጂና የባለሙያ ድጋፍ በአግባቡ የተጠቀሙ እንዲሁም የከርሰ ምድርና ገፀ ምድር ውሃን በመጠቀም በአመት ሁለቴና ከዚያ በላይ በማምረት ውጤታማ የሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በሽልማቱ የተካተቱ ወጣት ሴት አርሶ አደሮች እንደሚገኙበትም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪ ለግብርናው ዘርፍ ስኬታማነት ከፍተኛ ድርሻ አበርክተዋል የተባሉ የግብርና ባለሙያዎች፣ ሞዴል የግብርና ማሰልጠኛ ጣቢያዎች፣ የግብርና ምርምር ማዕከላት እና በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃቶች ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ ሙሳ አህመድ እንደገለፁት በግብርናው ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት አርሶ አደሮች ትልቅ ሚና አላቸው፡፡

ለዚህም አርሶ አደሮችን በክህሎትና በአመለካከት በማብቃት፣ ክልላዊ የልማት ሰራዊት በመፍጠርና ምርጥ ተሞክሮዎች የማስፋት ስልት ተቀይሶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ግንባር ቀደም በመሆን ተሸላሚ የሆኑ አርሶ አደሮችና ባለድርሻ አካላትም ለሌሎች አርአያ በመሆን ለተቀየሰው ስልት ውጤታማነት መትጋት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፀሐይ አዳሙ በበኩላቸው ሽልማቱ ምርጥ ተሞክሮዎችን በማስፋት በቀጣይ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ መነሳሳት መፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄዱ የአርሶ አደሮች ሽልማቶች ለስምንት ጊዜ ያህል መሸለማቸውን የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር አልኑር አህመድ ናቸው፡፡

አርሶ አደሩ በዘንድሮ ዓመት በአዳማ ከተማ በተደረገው አገር አቀፍ የአርሶ አደሮች ሽልማት ትራክተር ተሸላሚ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

አጠቃላይ ሃብታቸው ከ10 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱን ተነግረዋል፡፡

ከአምስት አመት በፊት ተቀጣሪ ሰራተኛ እንደነበር የተናገረው ደግሞ ከሃረማያ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ምሩቅ የሆነው ወጣት አርሶ አደር ንጋቱ ደሳለኝ ነው፡፡

በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ላይ አነስተኛ መሬት በመከራየት የጀመረው የግብርና ስራ ዛሬ ላይ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ሃብት እንዲያፈራ እንዳስቻለው ተናግሯል፡፡

የተሰጠው ሽልማትና እውቅና የበለጠ መነሳሳት እንደፈጠረለት በመግለጽ በቀጣይ በክልሉ መንግስት በኩል የተገቡ ቃሎች ተግባራዊ ከተደረጉ የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን ተናግሯል፡፡

ባላቸው አነስተኛ ማሳ በአመት ሁለት ጊዜ እንደሚያመርቱ የገለፁት ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ የኔሰው አዱኛ ናቸው፡፡

መንግስት የስራቸውን ውጤት በመመልከት የተሰጣቸው ሽልማት ከዚህ በላይ ለመስራት መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

ለተሸላሚ አርሶ አደሮችና የግብርና ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ሜዳልያ፣ የእውቅና የምስክር ወረቀት፣ የበቆሎና የለውዝ መፈልፈያ፣ የሁለት ሺህ ብር ቦንድ፣ ገንዘብና ተንቀሳቃሽ ስልክ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 5/2009 የሕብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሪዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ።

ጊፍት ሪል ስቴት ከ850 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በመንደር ቁጥር ሁለት የገነባቸውን ቤቶች ዛሬ ለደንበኞቹ አስተላልፏል።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ በቤቶቹ ምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የመኖሪያ ቤት የመጠለያ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዜጎች አገራቸው ላይ ማግኘት የሚገባቸው ሁለንተናዊ የደህንነት ዋስትና ነው።

በመሆኑም መንግስት በያዘው የቤት ልማት መርሃ ግብር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ከመቶ ሺህ በላይ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን አባዎራዎች ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጎን ለጎንም በሪልስቴት ኢንዱስትሪ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ለግንባታ የሚሆን መሬት ከማቅረብ ጀምሮ የተለያዩ ማበረታቻዎችን እያደረገ ነው ብለዋል።

ባለሃብቶችም ዕድሉን ተጠቅመው የስራ እድል ከመፍጠርና ምቹ መኖሪያዎችን ገንብቶ ዜጎችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ ነው ፕሬዝዳንቱ የገለጹት።

በተቃራኒው ቃል በገቡት ፍጥነትና ጥራት ቤቶቹን ካለማቅረብ ጀምሮ የደንበኞችን ገንዘብ ለሌላ ዓላማ የሚያውሉ ህገ ወጦች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ህገወጥ ተግባሩን በሚፈፅሙት ላይ መንግስት ጥብቅ ክትትል እንደሚያደርግ ጠቁመው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች በሃላፊነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ጊፍት ሪል ስቴት በመንደር ቁጥር ሁለት ከ850 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የገነባቸውን መኖሪያ ቤቶች ለደንበኞቹ አስተላልፏል።

መኖሪያ ቤቶቹ በ90 ሺህ 229 ካሬሜትር መሬት ላይ ያረፉ ሲሆን 350 የተለያየ ዲዛይን ያላቸው ቪላና አፓርታማ ናቸው።

በፕሮጀክቱ ከ1 ሺህ 500 በላይ ዜጎች የቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ከድርጅቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የሪል ስቴቱ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ገብረየሱስ ኢጋታ የቤቶቹ ግንባታ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በአንዳንድ ተቋማት ያለው የቢሮክራሲ ችግርና ከውጭ ባለሃብቶች ጋር መወዳደር አለመቻልን ከችግሮቹ መካከል ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የሕብረተሰቡ ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ መንግስት የፋይናንስ አቅርቦትና አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን በመደገፍ አገር በቀል ኩባንያዎችን እንዲያበረታታ ጠይቀዋል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ቤጂንግ ግንቦት 5/2009 የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ኢትዮጵያን በአባልነት ተቀበለ።

ባንኩ በእስያ - ፓስፊክ ቀጣና የሚካሄደውን የመሰረተ ልማት ለመደገፍ የተቋቋመ ነው።

የባንኩ ፕሬዚዳንት ጂን ሊቹን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በተወያዩበት ወቅት “ኢትዮጵያ የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ (ኤ.አይ.አይ.ቢ) አባል በመሆኗ በጣም ደስተኞች  ነን። ከዛሬ ጀምሮ የባንኩ አባል መሆኗን ስናፀድቅም በጣም ደስ እያለን ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ እኤአ 2015 ለተመሰረተው የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ አባል ለመሆን ከሁለት ዓመት በፊት ጥያቄ ማቅረቧ የሚታወስ ሲሆን፤ ባንኩ በአባልነት የተቀበላት ሶስተኛዋ አፍሪካዊት አገር ናት።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በመጪው ሰኔ በደቡብ ኮርያ ''ጄጁ'' በሚካሄደው የባንኩ ሁለተኛ ዓመታዊ የዳይሬክተሮች ቦርድ ጉባኤ ላይ እንድትሳተፍ ተጋብዛለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የባንኩ አባል መሆኗ አገሪቷ ለጀመረቻቸው ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች የሚያግዝ በቂ የብድር አቅርቦት ማግኘት ያስችላታል።

ለመሰረተ ልማት ግንባታ ከሚገኘው ብድር በተጨማሪ እንደ ማኑፋክቸር እና ማዕድን ለመሳሰሉ አዋጪ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲሁም ለአቅም ግንባታ ተግባራት ድጋፍ ማግኘት እንደሚያስችላትም ነው የተናገሩት።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ለልማት ፕሮጀክቶች "ተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭ ማግኘት መቻሏ መልካም እድል ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤  ከባንኩ የሚገኘው ብድር አነስተኛ ወለድ ያለው እና ለግብርና፣ ለማኑፋክቸሪንግ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለመሳሰሉ አዋጭ ፕሮጀክቶች ለማዋል እንደሚቻልም ገልፀዋል።

የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ በቻይና ሃሳብ አመንጭነት የተመሰረተ ሁለገብ የፋይናንስ ተቋም ሲሆን፤ በእስያ ያለውን የመሰረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት አገሮችን የማስተባበር ዓላማ አለው።

Published in ኢኮኖሚ

ጊምቢግንቦት 5/2009 በጊምቢ ከተማ በህገወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 58 የቀበሌ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች እንዲመለሱ ማድረጉን የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት አስታወቀ።

የማዘጋጃ ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ  አቶ ተመስገን ምሬሳ እንደገለጹት ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ በተከናወነ የማጣራት ሥራ በህገ ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 43 የንግድ ቤቶችና 15 የቀበሌ ቤቶች እንዲመለሱ ተደርጓል።

ቤቶቹ እንዲመለሱ የተደረገው ግለሰቦቹ  የመንግስት ቤቶቹን ያለአግባብ አከራይተውና ከውል ውጭ ቤቶቹን ለሌላ ግለሰብ አሳልፈው በመስጠት ሲጠቀሙ በመገኘታቸው ነው።

ቤቶቹ ከቀበሌ መስተዳድር አካላትና ከማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል በተውጣጣ ግብረ ኃይል በተደረገ ክትትልና የማጣራት ሥራ እንዲመለሱ መደረጉንም አስታውቀዋል።

ግብረ ኃይሉ ወደሕብረተሰቡ በመሄድ አስቀድሞ የማሳመን ሥራ በመስራቱ አብዛኞች ባለሃብቶችና ቤቶቹን የያዙ ግለሰቦች በሙሉ ፍቃደኝነት ቁልፍ ማስረከባቸውን ገልጸዋል።

አቶ ተመስገን እንዳሉት፣ በከተማው በሚገኙ አራት ቀበሌዎች ለማስመለስ በዕቅድ ከተያዙት 20 መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 15ቱ እንዲሁም ከ53ት የንግድ ቤቶች 43ቱን ለማስመለስ ተችሏል።

በአሁኑ ወቅት የተመለሱ የንግድ ቤቶች ሥራ አጥ ለሆኑ ወጣቶች በእጣ የተከፋፈሉ ሲሆን የመኖሪያ ቤቶቹንም ለችግረኛና አቅመ ደካሞች ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የመንግስት ቤት የያዙትን ግለሰቦች ለማስለቀቅ የተጀመረው ጥረት በቀጣይም በሁሉም ቀበሌዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ተመስገን አስታውቀዋል።

የጊምቢ ከተማ ነዋሪ ወጣት ደሱ ገዛህኝ በበኩሉ በሰጠው አስተያየት፣ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በማህበር ቢደራጅም የመስሪያ እና የመሸጫ ቦታ በማጣት ሲቸገሩ መቆየታቸውን አስታውሷል።

በአሁኑ ወቅት በህገ ወጥ መንገድ ተይዞ የነበረ የንግድ ቤት በእጣ በማግኘታቸው የማህበሩ አባላት የተሻለ ሥራ ለመስራት ተነሳሽነት እንደፈጠረባቸው አስታውቋል።

የማህበሩ አባል የሆነው ወጣት ሳሙኤል ገለታ በበኩሉ፣ "ለሥራችን የሚሆን ቤት ማግኘታችን ለቤት ኪራይ የምናወጣውን ወጪ ከማስቀረቱም በላይ ሥራችንን ተረጋግተን እንድንሰራ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል" ብሏል።

የጊምቢ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እመቤት ዱጋሳ ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ በከተማዋ ብዙ ለውጥ እየታየ መሆኑን ነው የገለጹት።

በተለይ የመስሪያ ቦታ አጥተው ያለስራ በቤት ውስጥ ለተቀመጡ ወጣቶች እየተደረገ ያለው ድጋፍ መልካም በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

 

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ ግንቦት 5/2009 የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት ጎን ለጎን ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን ለተጀመረው የልማትና የፀረ- ድህነት ትግል መሳካት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው " ሳይንሳዊ ፈጠራና አገር በቀል እውቀትን ማበረታታት ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ ከትናንት ጀምሮ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኦፒዮው ኡሞድ በምርምር ኮንፈረንሱን ላይ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት ጎን ለጎን ችግር ፍቺ ምርምሮችን በማካሄድ ለአገሪቱ የልማት ዕቅዶች መሳካት የድርሻውን አስተዋጽኦ ለማድረግ እየሰራ ነው።

መንግስት የቀየሳቸው የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና የፀረ-ድህነት ስትራቴጂዎች ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምርምር ሥራዎች ሲታገዙ ጭምር መሆኑንም ገልጸዋል።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲም የሕብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በሚፈቱ፣ በመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ያተኮሩ የምርምር ሥራዎችን በማካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ ዩኒቨርሲቲው በአገሪቱ የተቀየሰውን የሕዳሴ ጉዙ የሚያሳካ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ማፍራት እንዲችል መምህራንና ተማሪዎች በምርምር ሥራዎች ላይ በስፋት እንዲሳተፉና ተግባራዊ እውቀትና ልምድ እንዲኖራቸው እየተደረገ ነው።

በዩኒቨርሲቲው የተዘጋጀው አገር አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስም የምርምር ውጤቶችን ይፋ ለማድረግና ከሌሎች አቻ ተቋማት ልምድና ተሞክሮዎችን የመቅሰም አላማ እንዳለው ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባልና የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አከኔ ኦፖዶ በኮንፋረሱ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፣ ከፋተኛ የትምህርት ተቋማት ብቃት ያለው የሰው ሀብት ከማፈራት ባለፈ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን ማካሄዳቸው ለልማት እቅዶች ስኬት የጎላ ድርሻ አለው።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ተማሪዎችን ተቀብሎ ከማስተማር ጎን ለጎን የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግሮች የሚፈቱ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን ውጤቶችን ወደ ሕዝቡ ሲያደርስ መቆየቱን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው  የጀመራቸውን የምርምርና ጥናት ሥራዎች በቀጣይ በማጠናከር የሕብረተሰቡን የቴክኖሎጂ ችግሮች ለመፍታትና በአካባቢው የተነደፉ የልማት እቅዶች ስኬታማ እንዲሆኑ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በጋምቤላ ከተማ ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው አገር አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ በአገሪቱ ካሉ ከሃያ በላይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን የተገኙ ሲሆን፣ በመድረኩ የተለያዩ የምርምር ውጤቶችና ሥራዎች መቅረባቸው ተገልጿል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 5/2009 የተማሪ ትራፊኮች በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚደርሰውን አደጋን በመከላከል ውጤት እያስገኙ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ። 

ኮሚሽኑ ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን አንድ ሺህ የተማሪ ትራፊኮች ዛሬ አስመርቋል።

በአስፋልት መንገዶች ዳርቻ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተመልምለው ስልጠና የወሰዱ ተማሪዎች የትራፊክ አደጋ እንዲቀነስ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆኑን ዋና ኮሚሽነር ይህደጎ ስዩም ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ በትራፊክ ምልክትና ማመልከቻዎች እንዲሁም በማስተናበርና በመሠረታዊ የደንብ ጥሰቶች ላይ ነው የሚሰሩት።

የዛሬዎቹን ጨምሮ በዚህ ዓመት ከአንድ ሺህ 600 በላይ የተማሪ ትራፊኮች ስልጠና እንደተሰጣቸው ነው የተገለጸው።

እንደ ኮሚሽነር ይህደጎ ገለፃ በሰው ልጆች ላይ አካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያደረሰ ያለው የመንገድ ትራፊክ አደጋ በመዲናዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።

አደጋውን ለመከላከል ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ቢሆንም የመከላከሉ ተግባር የመንገድ ተጠቃሚዎችን ሙሉ ትብብርና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ በመሆኑ በሚፈለገው ልክ ውጤት እንዳልተገኘ ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከል የተማሪ ትራፊኮች እያከናወኑት ያለውን ተግባር ቀጣይነት እንዲኖረው ኮሚሽኑና ባለድርሻ አካላት በትኩረት እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተመራቂው ተማሪ ደጀን ሀሰን ሥራው በበጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተና በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ መታደግ የሚያስችል መሆኑን ገልጿል።

ከትምህርት ቤቱ በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎችም የትራፊክ ህግ የሚተላለፉ አሽከርካሪዎችን መረጃ ለትራፊክ ፖሊስ በመስጠት እንደሚሰራ ነው የተናገረው።

የተማሪ ትራፊኳ ዓለምፀሀይ መሰለም ፆታና ዕድሜ እንዲሁም ሃይማኖት ሳይለይ ጉዳት እያደረሰ ያለውን አደጋ ለመከላከል በራሷ ፍላጎትና ተነሳሽነት መሰልጠኗንና ሥራውንም ያለመሰልቸት እንድምትሰራ ገልፃለች።

በመዲናዋ ባለፉት አምስት ዓመታት በመንገድ ትራፊክ አደጋ 1 ሺህ 982 ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ፣ 7 ሺህ 603 ከባድና 5 ሺህ 474 ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን