አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Friday, 12 May 2017

 በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ

ሳምንታዊ አቋም መግለጫ

በሳዑዲ የሚገኙ ዜጎቻችን የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ከማብቃቱ በፊት ወደአገራቸው እንዲመለሱ ሁላችንም እንረባረብ!

የሳዑዲ መንግስት ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የሁሉም አገራት ዜጎች ካለፈው መጋቢት 21 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በ90 ቀናት እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ይታወሳል። ጉዳዩ እንደታወቀ የኢፌዴሪ መንግሥት ሳይውል ሳያድር ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ ልዩ ልዩ ተግባራትን በማካሄድ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ለተመላሾች በሚወጡበት አገር ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ ወደአገር እስኪመለሱና ብሎም ወደየቀያቸው ሲመለሱ አቅም በፈቀደው መልኩ በዘለቄታ እስከሚቋቋሙበት ድረስ ከክልል መንግሥታት ጋር በመሆን ዝርዝር ጉዳዮችን በማጥናትና ሥርዓት በማበጀት ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል፡፡ 

በሳውዲ ዓረቢያም አንድ ግብረ ሃይል በማቋቋም በዚያ የሚገኙ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎቻችን የመውጫ ቪዛ የሚያገኙባቸው ተንቀሳቃሽ ጽሕፈት ቤቶችን በመክፈት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አስፈላጊውን የጉዞ ሰነድ እና መረጃ እየሰጠም ይገኛል። ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የተለያዩ የመገልገያ ዕቃዎችን ያለቀረጥ እንዲያስገቡም መንግሥት ፈቅዷል፡፡

የመንግስት ፍላጎት ከሳዑዲ ተመላሽ  ዜጎቻችን አንዳችም ዓይነት ጉዳት እና እንግልት ሳይደርስባቸው በተሰጣቸው የእፎይታ ጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ አገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ማስቻል ነው፡፡ በመሆኑም በእስካሁኑ ሂደት የተወሰኑ ዜጎቻችን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፤ አሁንም በየዕለቱ በመመለስ ላይ ናቸው። ይሁን እንጅ የተመላሾቹ ቁጥር ከሚጠበቀው አንጻር ሲታይ አነስተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይህ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ዜጎቻችን የሳዑዲ መንግስት ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ  ወደ አገራቸው ካልተመለሱ  አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ የዜጎቻችን ሰብዓዊ መብቶቻቸው ይጣሳሉ፣ ንብረቶቻቸው ይወረሳሉ፣ ለእንግልት ይዳረጋሉ። በመሆኑም  በሳዑዲ የሚገኙት ዜጎቻችን ይህንኑ ከወዲሁ ተገንዝበው በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ በቀሪዎቹ ቀናት  ፈጥነው ወደ ትውልድ አገራቸው መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡

የጊዜ ገደቡ ሳይጠናቀቅ  ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ  በማድረግ በኩል በተለይ ወላጆች ለልጆቻቸው ደህንነት ሲሉ ከፍተኛ ግፊት ማድረግ የሚገባቸው ሲሆን መንግሥት፣ ሚዲያዎች፣ ማህበራት፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እና መላው ህዝባችን የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ዜጎቻችንን ቶሎ እንዲመለሱ በማድረግ በኩል የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል።

ህገ ወጥ ስደት ዘመናዊ ባርነት በመሆኑ ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን እና ደላሎችን ለመቆጣጠር የሚካሄደውን ጥረት መላው ህዝባችን አጠናክሮ እንዲቀጥል በዚህ አጋጣሚ የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል። ስደት ለአገርና ለወገን ውርደት ነው! በአገር ሰርቶ መለወጥ ግን  ኩራት ነው!

 

ግንቦት 04 ቀን 2009 ዓ.ም

Published in ፖለቲካ

አሶሳ ግንቦት 4/2009 አሶሳ ዩኒቨርሲቲ በሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በተቋሙ ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩ ሃያ የአስተዳደር ዘርፍ ሥራተኞችን ከሥራ አሰናበተ።

ተቋሙ ባካሄድው የማጣራት ሂደት ዋናውን የትምህርት ማስረጃ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማቅረብ ያልቻሉ ተጨማሪ አራት ሠራተኞችንም በቅርቡ ከሥራ እንደሚሰናበት አስታውቋል።

የዩኒቨርሲቲው የሥነ ምግባር መከታተልና ፀረ ሙስና ጽህፈት ቤት እንደገለጸው በደረሰው ጥቆማ መሰረት የሠራተኞችን የትምህርት ማስረጃዎች ለማጣራት ጥረት አድርጓል።  

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ያየህራድ አጥናፉ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ የ216 አስተዳደር ሠራተኞችን የትምህርት ማስረጃ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ወደሚገኙ የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ማዕከላት በመላክ ትክክለኛነቱን የማጣራት ሥራ ተሰርቷል፡፡

በተደረገው ማጣራትም 20 ሠራተኞች ሃሰተኛ የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ አቅርበው በዩኒቨርሲቲው እንደተቀጠሩ መረጋገጡን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ዋናውን የትምህርት ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ ከተጠየቁ ሠራተኞች መካከል ሌሎች አራት ሠራተኞች ማስረጃቸውን ማቅረብ ባለመቻላቸው ከሥራና ከደመወዝ እንዲታገዱ መደረጉን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የትምህርት ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ በመጠናቀቁም ተቋሙ ከሥራ እንደሚያሰናብታቸው አቶ ያየህራድ አስረድተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ባቀረቡ ሠራተኞች ላይ እርምጃ የወሰደው በመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/99 አንቀጽ 82 መሰረት ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ጉቦ ተቀብለው የሠራተኛ ቅጥር ሲፈፀሙ የነበሩ ሁለት የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ጉዳያቸው በክልሉ ጸረሙስና ኮሚሽን መያዙንም አስታውሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው በሌሎችም ጉዳዮች ላይ እያደረገ ያለውን የማጣራት ሥራ ሲያጠናቅቅ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ ግንቦት 4/2009 ልዩ ድጋፍ በሚሹና በአርብቶ አደር አካባቢዎች ከሌሎች ክልሎች ጋር ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ተመጣጣኝ ልማት ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

አምስተኛው ዙር  ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች ፣ የአርብቶ አደር አካባቢዎችና የሚኒስቴሩ  የጋራ ምክክር መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ክልል ተጀምሯል።

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ መንግሰቴ መድረኩን ሲከፈቱ እንደገለጹት ጋምቤላን ጨምሮ በአራቱ ልዩ ድጋፍን በሚሹ ክልሎች እንዲሁም በኦሮሚያና በደቡብ ህዝቦች አርብቶ አደር አካባቢዎች  ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት ያላቸው ናቸው፡፡

ይህንን የተፈጥሮ ሀብት ቀደም ሲል ወደ ልማት ባለመለወጡ በእድገት ወደ ኋላ መቅረታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ክልሎቹ ህገ መንግስቱ የፈጠረላቸውን  የመልማት መብት በመጠቀም ያላቸውን  የመሬትና የውሃ ሃብት ያገናዘበ እቅድ ነድፈው ሀብቱን  ወደ ልማት ለመለወጥ ሰፊ ስራዎችን  እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

የተነደፉ የልማት እቅዶችን እውን ለማድረግም የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴርና ሌሎችም የዘርፍ መስሪያ ቤቶች የተቀናጀ ልዩ ድጋፍ እየሰጡ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

በአራቱ ልዩ ድጋፈ በሚሹ ክልሎች ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ፍላጎትን መሰረት አድረጎ የተካሄደው የመንደር ማሰባሰብ መረሃ ግብር ህብረተሰብ ወደ ተሻለ የልማት እንቀስቃሴ መግባት እንዳስቻለው ጠቁመዋል።

በክልሎቹና በአርብቶ አደር አካበቢዎች የታዩት መልካም የልማት ጅምሮች ተጠናከረው እንዲቀጥሉ በሚኒስቴር መስረያ ቤቱ የተጀመሩት የማስፈጸም አቅም ግንባታና ሌሎች ድጋፎች እንደሚቀጥሉ ጠቅሰዋል፡፡

" በተለይም የተሻሻሉ የግብር ቴክኖሎጂዎችና  የኤክስቴንሽን አደረጃጀቶችን እንዲጠናከሩ በማደረግ በክልሎቹ የምግብ ዋስትና እንዲያረጋግጡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ  ያላሰለሰ  ድጋፉን ይሰጣል" ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት ልዩ ድጋፍ የሚሹና የአርብቶ አደር አካባቢዎችን ከሌሎች ክልሎች ጋር  በልማት ለማመጣጠን የተጀመረው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በዙር እየተካሄዱ ያሉት የምክክር መድረኮች በክልሎች መካከል ያሉትን ከፍተቶች ለመለየትና መልካም ተሞክሮዎችን ለማስፋት የጎላ ፋይዳ እንዳለውም ጠቁመዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ተወካይ አቶ ኡኩኝ ኡቡያ በበኩላቸው ቀደም ሲል  በክልሉ ያለው ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት  በአግባቡ ሳይለማ በመቆየቱ ህዝቡ በተፈለገው ደረጃ የልማት ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ይህንን ሀብት  ወደ ልማት በመለወጥ  ህዝቡን በዘላቂነት ተጠቃሚ ለማድረግ በራስ ኃይልና በፌደራል ድጋፍ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ አበረታች ውጤት እየተገኘ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በክልሉ  በተለይም የመንደር ማሰባሰቡ መረሃ ግብር ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ የተጠናከረ የግብርና ሙያዊ ድጋፍና የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂ ግብዓቶች በማቅረብ ለግብርና ልማቱ ስራ መሻሻል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ጠቁመዋል።

የጋራ የምክክር መድረክ ክልሉ በዘርፉ ያለበትን  ክፍተት ለመለየትና  የተሻሉ ተክሞክሮዎችን ለመውሰድ መልካም አጋጣሚ መሆኑንም  አቶ ኡኩኝ ጠቅሰዋል።

በጋምቤላ ከተማ  ለሶስት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድርክ የክልሎችና አርብቶ አደር አካባቢዎች የእቅድ የአፈፃፀም ሪፖርትና መልካም ተሞክሮች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ተመልክቷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 4/2009 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለአዲሱ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የደስታ መግለጫ መልዕክት አስተላለፉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በደስታ መግለጫ መልዕክታቸው ተመራጩ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያና ፈረንሳይ የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚያደርጉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ለአዲሱ ፕሬዚዳንት መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው መመኘታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የ39 ዓመቱ ኢማኑኤል ማክሮን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ 66 ነጥብ 06 በመቶ ድምጽ በማግኘት ነው ተቀናቃኛቸውን ማሪን ሌፔንን ያሸነፉት።

አዲስ ተመራጩ ፕሬዚዳንት በመጪው እሁድ ቃለ መሐላ በመፈጸም መንበረ ስልጣናቸውን ከአገሪቷ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ሆላንድ ይረከባሉ።

በፈረንሳይ ሪፐብሊክ ታሪክ 25ኛው የአገሪቷ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ማክሮን፤ እ.አ.አ ከ2014-2016 የፈረንሣይ ኢኮኖሚ ኢንዱስትሪና ዲጂታል ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2016 ያቋቋሙት "ኢን ማርች" የሚል መጠሪያ ያለው ፓርቲ በአጭር ጊዜ በፈረንሣይ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ግንቦት 4/2009 በመጪዎቹ አስር ቀናት የበልግ ዝናብ በመጠንና ስርጭት በሰሜን ምሥራቅ እየቀነሰ ወደ ምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፋ እንደሚሄድ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ የበልጉ ዝናብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክፍሎች ከሞላ ጎደል ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጿል።

በዚህም መሠረት በአዲስ አበባና በምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራና ምዕራብ ሸዋ የኦሮሚያ ዞኖች በአብዛኛው መደበኛና አልፎ አልፎም በጥቂት ቦታዎቻቸው ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ። 

የአማራ ምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም፣ የሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞኖችና የባህር ዳር ዙሪያ፤ የትግራይ የምዕራብና የመካከለኛ ዞኖችና የጋምቤላና የቤኒሻንጉል ክልሎችም እንዲሁ በአብዛኛው መደበኛና አልፎ አልፎም በጥቂት ቦታዎቻቸው ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ።

በአንጻሩ የምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ አርሲና ባሌ፣ ቦረናና ጉጂ የኦሮሚያ ዞኖች፤ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፤ ሰሜን ሸዋ የአማራ ዞኖች ደረቃማ ቀናት እያመዘነባቸው በጥቂት ሥፍራዎቻቸው ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙም ጠቁሟል።

ከአፋር ክልል ዞን ሦስትና አምስት፤ ከሶማሌ ክልል ጅግጅጋ፣ ሲቲ፣ ፊቅና ደጋሀቡር ዞኖች ደረቃማ ቀናት የሚያመዝንባቸው ሲሆን በጥቂት ሥፍራዎቻቸው ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል።

የኤጀንሲው መግለጫ እንዳመለከተው በአብዛኛው ተፋሰሶች ላይ የሚኖረው የደመና ሽፋንና ዝናብ የወሩን ሙቀት በመቀነስ በውሃ አካላት ላይ የሚኖረውን የትነት መጠን ይቀንሳል፤ የውሃ እጥረት ለሚታይባቸው ተፋሰሶችም በትንንሽ ወንዞች ውሃ እንዲኖራቸው ያደርጋል።

በአንጻሩ የተቀሩት የአገሪቱ ሥፍራዎች ደረቃማ ሆነው ይሰነብታሉ።

 

 

 

Published in አካባቢ

ከገዛኸኝ ደገፉ /ኢዜአ/

የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ዘርፍ የአለማችንን አጠቃላይ አመታዊ ምርት ወይም ጂዲፒ ሁለት በመቶ በመያዝ 3 ትሪሊየን  የአሜሪካን ዶላር በማንቀሳቀስና ለበርካታ ሚሊዮኖችም መተዳደሪያ መሆን ችሏል፡፡

ሁሉም የዘርፉ ተሳታፊዎች ድርሻቸውን ለማሳደግ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያደርጉት ፉክክርም እየጨመረ መምጣቱን በአልባሳትና በጨርቃጨርቅ ዙሪያ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ላለፉት 100 እና ከዛ በላይ አመታት ታዋቂዎቹ አውሮፓውያንና አሜሪካውያን የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎች በአለማችን ተንሰራፍተው በመቆየታቸው የሌሎች ሃገራት የምርት ውጤቶች ራሳቸውን አስተዋውቀው ወደ ገበያው እንዳይገቡ ትልቅ ተጽእኖ ሲፈጥሩ እንደነበረ አውስቷል፡፡

ፋይበር ቱ ፋሽን ድረ ገጽ እንዳለው ግሎባላይዜሽን የምርትና የሽያጭ ውድድሩን እጅግ ከባድ ከማድረጉም በላይ የዘርፉ ተዋናዮች ሁሌም አርቀው እንዲመለከቱና ለምርቶቻቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስገድዷል።

አፍሪካም ሆነች ሃገራችን ኢትዮጵያ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከአገር ውስጥ ፍላጎት ባሻገር ወደ አለምአቀፉ ገበያ ለመግባት የሚያስችሏቸውን የፖሊሲና የአሰራር መንገዶች አዘጋጅተው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ጎልተው የሚታዩ  በርካታ እርምጃዎችም ተወስደዋል።

ኢትዮጵያ የምታሰፋፋቸው የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ለአውሮፓና አሜሪካ ማሽነሪና መለዋወጫ አምራቾች የገበያ ሲሳይ ይዘው መምጣታቸውን የጣሊያን የጨርቃጨርቅ ማሽኖች አምራቾች ማህበር ፕሬዝዳንት ራፋኤል ካሩቤሊ ዉልን ኒውስ ኔት ለተባለው ድረገጽ ነግረውታል።

እንደ ፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ ከሆነ ኢትዮጵያ የምትከፍታቸው ሰፋፊ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የጨርቃጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ማእከላትን የሚያካትቱ በመሆናቸው ማእከላቱ የሚፈልጓቸውን የመሸመኛ፣ የማቅለሚያ፣ የስፌትና የመሳሰሉትን ማሽኖች ለማቅረብና ለመትከል ዝግጁ ሆነው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቂ የግብአት አቅርቦት

አፍሪካ ለጥጥ ማምረቻ የሚሆን ሰፊ መሬትና የውሃ ሃብት እንዲሁም በቀላሉ ሰልጥኖ ወደስራ ሊገባ የሚችል ወጣት የሰው ሃይል ያላት ሲሆን ይህንን ምቹ የተፈጥሮ ሃብትና ሰፊ የሰው ሃይል ወደ ስራ ለማሰማራት እንዲረዳም የአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያም ከ3 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ለጥጥ አምራቾች ምቹ ማድረጓን ያወሳው ፊውቸር ቴክስታይል ድረ ገጽ ጥቅም ላይ የዋለው ግን ከ30-40 ሺህ የሚሆን ሄክታር ብቻ መሆኑን ጠቅሶ፤ ይሄም ሃገሪቱ ምን ያህል ለጥጥ፣ ለጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች ምቹ የስራ ቦታ እንደሆነች አመላካች ነው ብሏል ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ያደረጋቸው የአሰራር ማሻሻያዎች መንግስት ለጨርቃጨርቃና አልባሳት ልዩ ትኩረት እንዳለው ያመላክታል ያለው ዩሮ ሞኒተሪንግ ዋቢ ያደረገው ጀስት ስታይል ድረ ገጽ በ2016 የምርት ዘመንም አገሪቱ አንድ ቢሊየን ዶላር ለማግኘት በርትታ መስራቷን አስነብቧል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንዉሚ አዴሲና እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በተለያዩ ምእራፎች ከፋፍላ ባስቀመጠቻቸው የእድገትና የሽግግር መረሃግብር አመታት ለዘርፉ በሰጠችው ልዩ ትኩረት ካልቪን ከሌይን እና ቶሚ ሂልፊገር የተባሉ የንግድ ምልክቶች ባለቤት የሆነው  ፒቪኤች ኮርፕ የመሳሰሉ ታዋቂ ኩባንያዎችን ባስገነባበቻቸው ታላላቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሰሩ ማድረጓ ለሌሎች ታዳጊ ሃገራት ምሳሌ ያደርጋታል ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ቴክኖሎጂን ወደ አፍሪካ ለሚያመጡና እንደ ጨርቃጨርቅ ብዙ የሰው ሃይል ለሚያሰማሩ የአፍሪካ ሃገራትና ድርጅቶች ድጋፉን እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

የገበያ አቅም

አንድ ቢሊየን የተጠጋ ህዝብ ያላት አፍሪካ ለዜጎችዋ የምታቀርበው ምርት በአብዛኛው መሰረቱን ያደረገው ከአውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም ከህንድና ከቻይና በሚመጡ አልባሳት ላይ በመሆኑ አፍሪካ ለራሷ ዜጎች ራሷ ያመረተቻቸውን አልባሳት ብታቀርብ ወደውጭ የምታወጣውን ገንዘብ ከማስቀረቷም በተጨማሪ ለዜጎቹዋ አስተማማኝ የሰራ እድል ልትፈጥር እንደምትችል ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡

ምጣኔ ሃብቷና የህዝብ ቁጥሯ በፍጥነት በሚያድገው  አፍሪካ የህጻናትንና ወጣቶችን ቀልብ መሳብ የሚችሉ አልባሳትን ማምረት የሚችሉ አፍሪካውያን ኩባንያዎች ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ተስፋ አድርገዋል።

ምጣኔ ሃብታዊ ለውጦች እየታዩባት ባለችው አፍሪካ ዘመናዊ አኗኗር እየተለመደና እያደገ ካለው የከተሜነት የህይወት ዘይቤ ጋር በተገናኘ ሁሉንም ማእከል ያደረጉ አልባሳት መመረትና ለገበያ መቅረብ መቻላቸው እንዲሁም ምርቶቹን በማከፋፈልና በመቸርቸር የተሰማሩ  አካላት ውጤታማ መሆናቸው  አፍሪካን የቻይናና የህንድ ምርቶች መጣያ እንድትሆን አደርጓታል የሚሉ ዘገባዎች ተደጋግመው ሲሰሙ እንደነበር ይታወቃል።

ብዝሃነትና ፈጠራ

አፍሪካ ያሏትን እምቅ ባህሎችና የአለባበስ ዘይቤዎች ዘመኑን በሚመጥኑ ንድፎች አምረው እንዲቀርቡ ማድረግ ብትችል አህጉሪቱን ከማስተዋወቃቸውም ባሻገር የወጣት የአልባሳትና የፋሽን ንድፍ ባለሙያዎችን አቅም ለመጠቀም እንደሚያስችላት ፋይናንሺያል ታይምስ ጋዜጣ አስነብቧል ።

እንደጋዜጣው ከሆነ አፍሪካውያን ለረጅም ዘመናት ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ራሳቸው እያመረቱ የተጠቀሙባቸው አልባሳት ራሳቸውን ከማሰተዋወቃቸውም ባሻገር ሌሎች አይተው ቢገዟቸው የበለጠ ተጠቃሚ ሊሆኑና አፍሪካ የራስዋ የሆኑ መታወቂያዎች እንዳላት የምታሳይበት  መሆኑንም አመላክቷል።

ብዙ አይነት የአለባበስና የአኗኗር ዘይቤ ካሏቸው ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች የገለጸው አይፒ ኤስ ኔውስ በበኩሉ ኢትዮጵያውያን ሙሉ በሙሉ  የሃገራቸው የሆኑና ባህላዊ የአመራረት መንገዶችን ተከተለው ከተፈጥሮ ግብአቶች የተመረቱ አልባሳት ወደ አውሮፓና አሜሪካ ገበያዎች እየደረሱ ቢሆንም ተገቢው የማስተዋወቅ ስራ ስላልተሰራባቸው አምራቾቹ የሚፈለገውን ያህል ጥቅም እያገኙ አለመሆኑን አትቷል።

ያልተነካው እድል

ኢትዮጵያ ከጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶች ትርጉም ያለው ገቢ ማስገኘት የተለያዩ ፖሊሲዎችን አውጥታ ተግባራዊ ማድረጓንና ለዘርፉ ቀጥተኛ ግብአት የሚሆኑ ወጣት ምሁራንን በልዩ ትኩረት በመመልመል በሃገሪቱ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በጨርቃጨርቅ  አልባሳትና ንድፍ ምህንድስና ዘርፍ እንዲማሩ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ልማት ኢንስቲትዩት ይፋዊ ድረገጽ አስነብቧል፡፡

አሜሪካ ለአፍሪካ ምርቶች የሰጠችውን እድል / AGOA / ለመጠቀም ኢትዮጵያም በርትታ እየሰራች እንደሆነ አስፍሯል። አጎዋ የአፍሪካ ምርቶች ግብኣቶቻቸውን ከአፍሪካ እንዲያገኙ የሚያስገድድ በመሆኑ ሁሉንም ነገሮች ለማሟላት ጥረቶች እየተደረጉና አበረታች ውጤቶች እየተገኙ መሆኑንም ድረ ገጹ አመላክቷል።

ዘርፉ የሚጠበቅበትን ያህል የውጭ ምንዛሪ ማስገባት ባይችልም የሚታዩት እንቅስቃሴዎች ተስፋ ሰጭ መሆናቸውንና የኢትዮጵያ ምርቶችም ትኩረት ቢሰጣቸው አለምአቀፍ ተወዳደሪ መሆን እንደሚችሉ አለምአቀፍ የሚድያ አውታሮች ከሚያወጣቸው  ዘገባዎች መረዳት ይቻላል።

ባሳለፍነው ሳምንት ጃካርታ ፖስት የተባለው ድረ ገጽ እንዳስነበበው ከሆነ ኢትዮጵያ የምታመርታቸው የጨርቃጨርቅና የአልባሳት ውጤቶች ለኢንዶኔዥያ የአልባሳት ኩባንያዎች ፈተና እየሆኑ መምጣታቸው እንዳሳሰበው የኢንዶኔዥያ የጨርቃጨርቅ አምራቾች ማሀበራት ሊቀመንበርን ጠቅሶ አሰነበቧል ።

ብዛትና ጥራት

ሃብታሞቹ የአውሮፓና የአሜሪካ ሃገራት ለሚያመርቷቸው ምርቶችና ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች የጥራትና የደረጃ መስፈርቶችን አዘጋጅተው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ከ50 አመታት በላይ እንዳስቆጠሩ ሃገራቱ ስለጥራትና ደረጃዎች የሚያወጡዋቸውን መረጃዎች መመለከቱ በቂ ነው።

ያደጉት ሃገራት የከባቢ አየር መበከልና የአለም ሙቀት መጨመር እያስከተለባቸው ያለውን ተጽእኖ መቋቋም እንዲያስችላቸው ወደ አህጉራቸው የሚገቡ ምርቶችም ከአካባቢ ጋር የተስማሙና ተመልሰውም ጥቅም ላይ ሊውሉ ከሚችሉ ጥሬ እቃዎች የተመረቱ ሊሆኑ  እንደሚገባ ደጋግመው ሲያስጠነቅቁ ይሰማል።

በመሆኑም ሃገራቱ ይህንን አላማቸውን የሚያስተገብሩባቸው ህግጋትን በማውጣት ወደስራ የገቡ ሲሆን አካባቢያቸው እንዳይበከል ሲባል የተገለገሉባቸውን አልባሳት በመሰብሰብ ወደ አፍሪካ ሃገራት እንደሚልኩና ትንሽ የማይባል ገንዘብ እንደሚያገኙ ሃፊንግተን ፓስት ድረ ገጽ አፍሪካ የአውሮፓ ልባሽ ጨርቆችን አትፈልግም ሲል ባወጣው ጽሁፍ አስነብቧል።

እ.ኤ.አ 2014 ብቻ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ በማውጣት ልባሽ ጨርቆችን እንዳስመጡ ያተተው ጋዜጣው ልባሽ ጨርቆችን መጠቀም ከሚያስከትለው የጤና እክል ባለፈም የአፍሪካ ታዳጊ የዘርፉ አንቀሳቃሾችን አቅም እየተፈታተነ መሆኑንና አፍሪካ ማግኘት ያለባትን ገቢ እንዳስቀረባት አመልክቷል።

በመጪው አዲስ አመት መስከረም ወር ማብቂያ በመዲናችን አዲስ አበባ ከ25 ሃገራት የሚመጡ ከ250 በላይ አለም አቀፍ የጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾችን የመዋቢያ ቁሰቁሶች አቅራቢዎችንና ልዩ ልዩ የዘርፉ አንቀሳቃሾችን የሚያካትት ግዙፍ አውደ ርእይና ባዛር ይካሄዳል፡፡ ይህም አፍሪካ በተለይም ኢትዮጵያ ለዘርፉ ምን ያህል ትኩረት እንደሰጠችው አመላካች መሆኑን ኒቲንግ ኢንዱስትሪ ዶት ኮም አውስቷል፡፡

በአውደ ርእዩ ኢትዮጵያ ያላትን አቅምና ዝግጁነት ለተሳታፊ አካላት የምታሳይበትና ልምድ የምትወስድበት መሆኑንም ጠቅሷል።

 

Published in ዜና-ትንታኔ

አዳማ ግንቦት 4/2009 ፍትሀዊ የመድኃኒት አቅርቦትና ስርጭትን ለማረጋገጥ ከብዙሀን መገናኛ ባለሙያዎች ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሰራ የመድኃኒት ፈንድ አቅርቦት አጄንሲ አስታወቀ።  

ኤጀንሲው ለብዙሀን መገናኛ ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ ያዘጋጀው የሁለት ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

የኤጄንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አየለ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ተቋሙ ፍትሃዊ የመድኃኒት አቅርቦትና ስርጭትን በማረጋገጥ ጤናማና አምራች ሕብረተሰብ ለመገንባት የተቀመጠውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።

ለዚህም "መረጃን ተደራሽ ማድረግና በዘርፉ የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የመቅረፍ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው” ብለዋል ።

በዚህ በኩል የብዙሀን መገናኛ ሚና የጎላ በመሆኑ የተቋማቱና የዘርፉ ባለሙያዎች እገዛ ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል።

ከምዕተ ዓመቱ የጤና ልማት ግቦች መካከል በእናቶችና ሕጻናት ሞት፣ በወባ፣ በቲቢና ኤች አይ ቪ/ኤዴስ እንዲሁም ተላላፊ በሽታዎችን  በመቀነስና በመከላከል በኩል አገሪቱ ላስመዘገበቻቸው ውጤቶች የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ድርሻ የጎላ እንደነበር ለአብነት ጠቅሰዋል።

እንደአቶ ወንድወሰን ገለጻ፣ ኤጀንሲው የሚሰጠውን አገልግሎት ጥራት እውን ለማድረግ በቀጣይ ከብዙሀን መገናኛና ከባለሙያዎቹ ጋር በቅንጅት ይሰራል ።

በኤጄንሲው የመድኃኒት ግዥ ትንበያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ይገዙ  በመድረኩ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ  በሀገሪቱ ጥራትና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ የመድኃኒት ግዥ፣ አቅርቦትና ስርጭት ስርአት እንዲሰፍን ጥረት እያደረገ ነው ።

ይህን የመንግስት ጥረት ከዳር ለማድረስ ከመገኛኛ ብዙሀንና ባለሙያዎች ጋር ቅንጅታዊ አሰራር ለመፍጠር በተያዘው አቅጣጫ መሰረት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል ።

ዛሬ በተጠናቀቀው መድረክ ከፌደራልና ከክልል የተውጣጡ ከ40 በላይ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

Published in ማህበራዊ

 አዲስ አበባ ግንቦት 4/2009 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በመጪው ማክሰኞ በሚጀመረው 46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዝላይና ውርወራ ብቃት ያላቸው አትሌቶች እንደሚያገኝ ተስፋ አድርጓል።

 ከግንቦት ስምንት ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚካሄደው ውድድር 1 ሺህ 265 አትሌቶች ይሳተፋሉ።

 ለሻምፒዮናው 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የተበጀተ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 480 ሺህ ብሩ ለአትሌቶች ሽልማት የሚውል ነው።

 የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ውድድሩን አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ "በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በማትታወቅባቸው የሜዳ ላይ ተግባራት ብቃት ያላቸው አትሌቶች እንደምናገኝ ተስፋ አለን" ብሏል።

 በተለይም በዝላይና ውርወራ አዲስ ክብረወሰን ሊሰብሩና ሊያሻሽሉ የሚችሉ አትሌቶች እንደሚገኙ ነው ኃይሌ የተናገረው።

 በቀጣይም በእነዚህ ውድድሮች ውጤት ለማምጣት ከስፔንና ኩባ አሰልጣኞች በማስመጣት ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁሟል።

 ሻምፒዮናው ተተኪ አትሌቶች ለማፍራት ብሎም በክለቦች፣ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ማሰልጠኛ ማዕከላት ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር ዕድል የመፍጠር ዓላማ አለው።

 በአህጉርና በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች የሚመረጡበትም ነው ብሏል ኃይሌ።

 የሚመረጡ አትሌቶች የተቀመጠውን ሚኒማ የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸውም ጠቁሟል።

 በሻምፒዮናው ታዋቂ አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ክብረወሰን የሚሰብሩ 14 ሺህ ብር ሽልማት ያገኛሉ ተብሏል።

 በውድድሩ አሸናፊ ለሚሆኑ ደግሞ በየደረጃው የሜዳሊያና የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል።

 ለሻምፒዮናው ከ150 በላይ የተለያዩ ባለሙያዎችና 80 የአትሌቲክስ ዳኞችን ማዘጋጀቱን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ግንቦት 4/2009 ኢጣሊያ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በህጻናት የልብ ቀዶ ህክምና ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ተስማማች። 

 የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃኔና በኢትዮጵያ የኢጣሊያ አምባሳደር ጁሴፔ ሚስቴሬታና ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

 ስምምነቱ በህጻናት የልብ ቀዶ ህክምና ለኢትዮጵዊያን የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ከመስጠት ባሻገር ለህክምናው የሚሆን የግብዓት ድጋፍን ያካተተ ነው።

 አምባሳደር ጁሴፔ ሚኒስቴሬታ እንዳሉት ስምምነቱ የአገራቱን የጤና ሚኒስቴሮች በቀጥታ የሚያገናኝ መሆኑ በአይነቱ የተለየና አዲስ ያደርገዋል።    

 "በጤናው መስክ አጋር ከሆኑ አምስት አገራት መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት" ያሉት አምባሳደሩ ለተጨማሪ ሦስት ዓመታት ትብብሩን ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።  

 በአዲስ አበባ የኢጣሊያ ልማት ኤጀንሲ የጤና ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ላውራ ፒኮራሮ በበኩላቸው አገራቸው በህጻናት ልብ ቀዶ ህክምናና ጤና አገልግሎት ትልቅ አቅም መፍጠሯን ገልጸዋል።

 ይህን የካበተ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም ነው ያረጋገጡት።  

 ስምምነቱ ወደ ተግባር ተለውጦ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጣ እኩልነት፣ ሴቶችን ያማከለና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን መሰረት እድርጎ እንደሚከናወን አብራርተዋል።     

 ሚኒስትር ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃኔም ስምምነቱ ኢትዮጵያ በህጻናት ቀዶ ህክምና የምትሰጠውን አገልግሎት ጥራት በማሻሻል ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።

 "አገሪቱ የህጻናት ልብ ቀዶ ህክምናን ተደራሽ በማድረግ ረገድ የሚጠበቀውን ያህል ርቀት አልተጓዘችም" ያሉት ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት 400 ሺህ ህጻናት የልብ ቀዶ ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል። 

 "መንግሥት ህክምናውን ለመስጠት የሚያስችለውን መሰረተ ልማት ይገነባል፤ ዋናው ጉዳይ የባለሙያ እጥረት ነው፤ ስምምነቱ በዚህ ረገድ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል" ብለዋል

Published in ማህበራዊ

ቤጂንግ ግንቦት 4/2009 የመንግስታቱ ድርጅት የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ፕሮግራም (ዩ.ኤን.ኤድስ) በአፍሪካ የሚያከናውናቸውን የፀረ-ኤች አይ.ቪ/ኤድስ ስራዎች በቴሌቪዥን ለማስተላለፍ ከቻይናው ስታር ታይምስ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ።

የዩ.ኤን.ኤድስ ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ሚሼል ሲዲቤና የስታር ታይምስ ብሮድካስት ሚዲያ ፕሬዚዳንት ሚስተር ፓንግ ዢያንግ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ስምምነቱን የፈረሙት በ"ዋን ቤልት ዋን ሮድ ኢኒሼቲቭ ፎረም" ላይ ለመሳተፍ ቤጂንግ በገቡበት ወቅት ነው።

በስምምነቱ መሰረት ዩ.ኤን.ኤድስ በሽታውን አስመልክቶ የሚያዘጋጃቸው ፕሮግራሞች በስታር ታይምስ ሚዲያ ይተላለፋሉ።

የኤድስ መከላከልን አስመልክቶ ተከታታይ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ለአህጉሪቷ ዜጎች ግንዛቤ ማስጨበጥ የስምምነቱ ዋና ዓላማ ነው።

የመንግስታቱ ድርጅት የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ፕሮግራም "በ2030 ዜሮ የኤድስ በሽታ" በሚል ያዘጋጀውን እቅድ ከግብ ለማድረስ መገናኛ ብዙሃንን ለቅስቀሳ እየተጠቀመ ነው።

ዳይሬክተሩ ሚስተር ሚሼል ሲዲቤ እንደተናገሩት አፍሪካዊያን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምርመራ በማድረግ ራሳቸውን እንዲያውቁና ግንዛቤያቸው እንዲያድግ የመገናኛ ብዙሃንና የኮሙኒኬሽን ተቋማት ሚና ወሳኝ ነው።

ዜጎች ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ በማድረግ ረገድ በቂ ግንዛቤ አለመኖሩ የአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ስጋት እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ የቻይናው ስታር ታይምስ የብሮድካስት ሚዲያ ባለው ሰፊ ተደራሽነት ለአህጉሪቷ ዜጎች ግንዛቤ በማስጨበጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በአፍሪካ በኤች.አይ.ቪ ቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቢቀንስም ከሰሀራ በታች ባሉ አገራት አሁንም ከፍተኛ የጤና ስጋት መሆኑን ነው ያስረዱት ሚስተር ሚሼል።

የቻይናው ስታር ታይምስ ብሮድካስት ሚዲያ ፕሬዚዳንት ሚስተር ፓንግ ዢያንግ በበኩላቸው በአፍሪካ ኤድስን ለመዋጋት ከመንግስታቱ ድርጅት የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ፕሮግራም ጋር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በአህጉሪቷ የኤሌክትሪክ ኃይል በሌለባቸውና ደካማ የቴሌቪዥን ሲግናሎች በሚገኙባችው የገጠር አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ሳተላይት በመግጠም ፕሮግራሙን እንዲከታተሉ ይደረጋል ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ በተካሄደው የአፍሪካ-ቻይና የትብብር ፎረም የቻይናው ፕሬዚዳንት ጂን ፒንግ በአፍሪካ የሚገኙ 10 ሺህ መንደሮች የሳታላይት ቴሌቪዥን ፕሮግራም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የገቡትን ቃል አስታውሰዋል።

ስታር ታይምስ በአፍሪካ የቴሌቪዥንና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽ በማድረግ በቴክኖሎጂ ያላትን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የኢዜአ ሪፖርተር ከቻይና የላከው ዘገባ ያመለክታል። 

የሚዲያ ተቋሙ ከመንግስታቱ ድርጅት የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ፕሮግራም ጋር በመሆን ካለፈው ዓመት ጀምሮ በኢቦላ ቫይረስ በተጠቁ የምዕራብ አፍሪካ አገራትን አስመልክቶ በተንቀሳቃሽ ምስል የታገዙ ፕሮግራሞች በመስራት ላይ ይገኛል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን