አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Thursday, 11 May 2017

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2009 በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት መገናኛ ብዙሃን አጀንዳቸው አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ።

ሚኒስቴሩ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ የሳዑዲ መንግስት ካለፈው መጋቢት 21 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የሁሉም አገራት ዜጎች በ90 ቀናት ከአገሪቱ እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ የሚታወስ ነው።

ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግስት በሳውዲ ዓረቢያ የሚገኙ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች የመውጫ ቪዛ የሚያገኙባቸው ተንቀሳቃሽ ጽሕፈት ቤቶችን ከፍቶ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እያደረገ ይገኛል።

መግለጫውን የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንዳሉት መንግሥት በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚያደርገውን ጥረት ለማሳካት መገናኛ ብዙሃን አጀንዳቸው አድርገው ሊሠሩ ይገባል።

በሚኒስቴሩ በኩል ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ በማዋቀር የዜጎቹ ደህንነት ተጠብቆ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ እየሰራ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ “ከተሰጠው የጊዜ ገደብ አሁን 48 ቀናት የቀሩ በመሆናቸው በነዚህ ቀናት ውስጥ ዜጎችን በሰላም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው" ብለዋል።

ነገር ግን ''አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በህገ-ወጥ መንገድ ባህር አቋርጠው የሄዱ በመሆናቸው ምን ያህል ኢትዮጵያዊያን በስፍራው እንደሚገኙ ለማወቅ አልተቻለም” ሲሉም ተናግረዋል።

በጅዳ እና ሪያድ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንፅላ ፅህፈት ቤቶቹ ይህንን ሥራ እየሠሩ የሚገኙ ሲሆን በሳዑዲ ገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በመኖራቸው አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የምዝገባ ጣቢያዎች ተቋቁመው እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

የምዝገባ ስራውን ሊሠሩ የሚችሉ የኢምግሬሽን ባለሙያዎች ወደ ስፍራው ተልከው እየሰሩ መሆኑንና በአሁኑ ወቅትም የተመዝጋቢዎች ቁጥር እየጨመረ ፤ ከ20 ሺህ በላይ ዜጎች ተመዝግበው የጉዞ ሰነድ መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።

በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ከአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እና  መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ሚሲዮኖች ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑንም ቃል አቀባዩ አስረድተዋል።

በጉዳዩ ላይ ለኅብረተሰቡ መረጃ እንዲደርስ ከመገናኛ ብዙሃን ጋራ ሰፊ ሥራ የተሠራ ቢሆንም በቂ ባለመሆኑ ከዜና በዘለለ ፕሮግራም እና ሌሎች ዘገባዎችን በተከታታይ በመስራት መገናኛ ብዙሃን በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ አጀንዳቸው አድርገው መሥራት አለባቸው በማለት አሳስበዋል።

በተጨማሪም ቀነ ገደቡ ከተጠናቀቀ በኋላ በወገኖች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት በሚደረገው ብሔራዊ ዘመቻ ላይ ሁሉም አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

Published in ፖለቲካ

ባህርዳር ግንቦት 3/2009 በህዝብና በመንግስት ሃብትና ንብረት ላይ ሙስና ፈጽመዋል ያላቸውን 211 ግለሰቦች በፅኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ማድረጉን የአማራ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ እውነቴ አለነ ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ግለሰቦቹ የተቀጡት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተደረገ ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ስራ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ነው።

በ121 መዝገቦች ክስ ተመስርቶባቸው ተገቢውን ማስረጃ በማሰባሰብ ቅጣቱ የተወሰነባቸው 182 ወንድና 29 ሴቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ግለሰቦቹ በተመሰረተባቸው በስልጣን ያለ አግባብ መጠቀም፣ በግዢና ጨረታ ሙስና ፣ በተጭበረበረ ሰነድ መገልገል፣ በግብር መሰወርና መሰል የወንጀል ክስ ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውንም አስረድተዋል።

ግለሰቦቹ በፈፀሙት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸውም ከሦስት ወር አስከ 14 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ300 እስከ 30 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት የተጣለባቸው መሆኑን ገልፀዋል።

በእጃቸው የተገኘና የሙስና ፍሬ የሆነ ከ14 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ገንዘብና አንድ ሺህ 400 ካሬ ሜትር ቦታም ለመንግስት ገቢ መደረጉን አስታውቀዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን በተሰራ የአስቸኳይ የቅድመ ሙስና መከላከል ተግባርም በጨረታ፣ በእቃ ግዢ፣ በምግብ ዋስትናና በሌሎች እንቅስቃሴዎች ሙስና ሊፈፀምበት የነበረ 18 ሚሊዮን ብር ማስቀረት እንደተቻለ አብራርተዋል ።

ለሙስና በተጋለጡ የከተማ መሬት፣ የንብረት ግዢና ጨረታ፣ የግንባታ፣  የግብር አሰባሰብና አወሳሰን፣በሰነድና መሰል ተግባራት ዙሪያ በተለየ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ህብረተሰቡ ለኮሚሽኑ ስራ መሳካት የሚያደርገውን ጥቆማ አጠናከሮ እንዲቀጥል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተው፤ ባለፉት ወራትም የሙስና ባህሪ ያላቸው አንድ ሺህ 100 ጥቆማዎች ለኮሚሽኑ እንደደረሱት አቶ እውነቴ አስታውቀዋል።

በክልሉ በቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ሙስና ፈፅመው የተገኙ 190 ግለሰቦች በህግ ፊት ቀርበው እንዲቀጡ መደረጉን ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2009 ምቹ የኢንዱስትሪ ሁኔታ የመፍጠር፣ የአሠሪዎችን ችግር የመፍታት፣ የማማከርና የህግ ከለላ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ገለፀ።

ፌዴሬሽኑ 20ኛውን ዓመት የዳግም ምስረታ በዓሉን ከግንቦት 6 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ሐረር ላይ ያከብራል።

የአሠሪው የነቃ ተሳትፎና ተቀናጅቶ መስራት ለኅብረቱ ዓላማ ከግብ መድረስ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው የጠቀሰው ፌዴሬሽኑ አሠሪ ባለሀብቶች በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ጥሪ አቅርቧል። 

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር በአሠሪና ሠራተኛው መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን በመፍታትና በጥሬ እቃ አቅራቢውና በአምራቹ መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የገበያ ትስስር መፍጠር እንደተቻለ ተናግረዋል።

ፌዴሬሽኑ የአሠሪውን መብትና ጥቅም ከማስከበር ባሻገር የሠራተኞች ደህንነት እንዲጠበቅ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተቋማት የግንዛቤ ለውጥ በማምጣት ለሴት ሠራተኞች እኩል ክፍያ እንዲኖር ማድረጉን፣ የወሊድ ፈቃድና የልጆች ማቆያም በተወሰኑ አሠሪዎች እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።

በእርሻ አካባቢዎች ለሚገኙ ሠራተኞች ትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች እንዲገነቡና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉንም አክለዋል።

እንደ አቶ ታደለ ገለጻ በበዓሉ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ባለሃብቶች፣ የውጭ አገራት አሠሪ ድርጅቶች ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይታደማሉ።

ከፌዴሬሽኑ 16 ቅርንጫፎች መካከል የሐረሪው 518 አባላትን ያፈራና የተሻለ በመሆኑ 20ኛ ዓመት የዳግም ምስረታ በዓል እንዲያዘጋጅ መመረጡን አስታውቀዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ከክፍያ ነጻ የሆነ የአዲስ አባላት ምዝገባ እንደሚካሄድም አቶ ታደለ ጠቁመዋል።

ለሁለት ቀናት የሚካሄደው በዓሉ በሲፖዚየም፣ በንግድ ትርዒትና ባዛር፣ በፎቶግራፍ ኤግዚቢሽንና በሌሎች ፕሮግራሞች ይከበራል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2009 ብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት 706 የምርት ደረጃዎችን አፀደቀ፡፡

ምክር ቤቱ በስምንት ዘርፍ ተዘጋጅተው የቀረቡ ብሔራዊ የምርት ደረጃዎችን ነው ያጸደቀው።

ከጸደቁ ብሄራዊ የምርት ደረጃዎች መካከል 293ቱ አዲስ ሲሆኑ 150 የተከለሱ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ደረጃ ተሰጥቷቸው የጥራት ደረጃቸው ተስማሚ በመሆኑ እንዲቀጥሉ የተደረጉ ናቸው።

ከፀደቁት መካከል የኢትዮጵያ ደረጃ ስታንዳርድ ፎር ስታንዳርድ፣ ኮንስትራክሽንና ሲቪል ኢንጂነሪንግ፣ በመሠረታዊ አጠቃላይ የደረጃ ዝግጅት፣ በአካባቢና ጤና ደኅንነት እና የጨርቃጨርቅ የደረጃ ዝግጅት ዘርፍ ቀዳሚ ደረጃ ያገኙ ናቸው።

እንዲሁም በግብርናና ምግብ ዝግጅት፣ በኤሌክትሮ መካኒካል፣ በኬሚካልና ኬሚካል ውጤቶች በስምንት የደረጃ ዘርፎች የተከፈሉ 706 ደረጃዎችን አጽድቋል።

የጸደቁት ደረጃዎች የምርቶችን ጥራት፣ የኢንዱስትሪና የንግድ ተወዳዳሪነት አቅምን የሚያጎለብቱ ናቸው ብለዋል የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለው መኮንን።

እንዲሁም የሕብረተሰቡን ጤናና ደኅንነት፣ የሸማቾችን ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር ፋይዳቸው የጎላ ይሆናል ነው ያሉት። 

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጄንሲ ብሔራዊ ደረጃዎችን በማዘጋጀት አምራችና አገልግሎት ሰጪዎች ደረጃዎችን በመጠቀም ውጤታማ እንዲሆኑ መረጃና ግንዛቤ በመስጠት የክህሎት ሥልጠናዎችን በመስጠት ይሠራል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2009 ኢትዮጵያ በፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነቷ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ሰላምና ደህንነት በትኩረት እየሠራች መሆኑን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በሆነችበት በአራት ወራት ውስጥ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት አራት ወራት ቆይታዋ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ሰላም እና ደህንነት ሠርታለች።

በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ግጭቶችን በሰላም እንዲፈቱ በማድረግና አሸባሪነት እንዲዳከም ያደረገችው ጥረት ውጤታማ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ ከአፍሪካ ተወካዮች ግብፅና ሴኔጋል ጋር በመሆን የአፍሪካ ህብረት ውሳኔዎችን በማስፈፀም ረገድ እየሠራች መሆኑን ገልጸው፤ ከተወካይ አገሮቹ ጋር የጋራ አቋም ለማራመድም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።

አገራቱ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድም ጠንካራ የሆነ የጋራ አቋም እንዳላቸው በመጠቆም።

የአፍሪካ ጉዳዮችን በተመለከተ በተለይም የደቡብ ሱዳን ግጭት በሚፈታበት ሁኔታ ዙሪያ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ለሚያደርጋቸው ጥረቶች የፀጥታው ምክር ቤት  ጠንካራ ድጋፍ እንዲያደርግ በምክር ቤቱ ስብሰባዎች ላይ ግፊት የሚያደርጉ ተግባራት መከናወኑን ተናግረዋል።

በኢጋድ፣ በአፍሪካ ህብረትና በተመድ መካከል የደቡብ ሱዳንን ግጭት ለመፍታት የሚያስችል ቅንጅታዊ ሥርዓት እንዲፈጥሩ የማድረግ ስራ መሰራቱምን እንዲሁ።

በደቡብ ሱዳን ችግር አፈታት ዙሪያ አንድ አቋም በመያዝ በአገሪቷ ላይ ሊጣል የነበረው ማዕቀብ ውዝግቡን የበለጠ እንደሚያወሳስበው በመግለፅና “ተቀናቃኞችን ማወያየት” የሚለው ሃሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ መደረጉንም አስረድተዋል።

እንደ ቃል አቀባዩ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ ሶማሊያን በተመለከተ በአገሪቷ ዘላቂ ሰላም እንዲሠፍንና የተረጋጋ መንግሥት እንዲኖር በአሚሶም ጥላ ሥር እንዲሁም በተናጠል የምታደርገውን የሰላም ማስከበር ሥራ የበለጠ ማስገንዘብ ችላለች። በዚህም የፀረ ሽብር እርምጃዋ በፀጥታው ምክር ቤት ይሁንታ እንዲያገኝ አድርጋለች።

የሶማሊያ የፖለቲካ አቅጣጫ በትክክለኛው መንገድ እንዲጓዝ ምክር ቤቱ ድጋፍ እንዲሠጥ ማድረግ መቻሉን ያስረዱት አቶ መለስ፤ ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል የቆየው የሶማሊያ ምርጫ ተካሂዶ ህብረተሰቡ መሪዎቹን መምረጡን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የሶማሊያ የፀጥታ ሃይል እንዲጠናከር እንዲሁም የሰብዓዊ ዕርዳታና ድጋፍ እንዲደረግ ያቀረበችው ሃሳብ ተቀባይነት ማግኘቱንም ገልጸዋል።

የኤርትራ መንግስት የተጣለበትን ማዕቀብ በመጣስ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በማጋለጥ የምታከናውናቸው ተግባራት በምክር ቤቱ ተቀባይነት ማግኘታቸውንም ነው ያብራሩት።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የምክር ቤቱን ትኩረት ከወሰዱ ግጭቶች አንዱ የሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት መሆኑን አውስተው፤ ኢትዮጵያ በግጭቱ አፈታት ረገድ በፀጥታው ምክር ቤት የምታራምደው አቋም ''የአገሮች የአስተዳደር ተቋማት መፈራረስ የለባቸውም '' የሚል መሆኑን ነው የገለጹት።

የእነዚህ ተቋማት መፈራረስ በሚፈጥረው ክፍተት የሽብር ቡድኖችና አክራሪዎችን እንደሚያጠናክሩ የገለጹት አቶ መለስ፤ “ኢትዮጵያ የእነዚህን ተቋማት ህልውና ባረጋገጠ መልኩ ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን ማፈላለግ ጠቃሚ እንደሚሆን የሚገልጹ መልዕክቶችን በትኩረት ታራምዳለች” ብለዋል።   

ኢትዮጵያ የሰሜን ኮሪያ የኒውክለር ጦር መሳሪያ ሙከራን በተመለከተ ሰሜን ኮሪያ የፀጥታው ምክር ቤት ላስተላለፋቸው ውሳኔዎች ተገዢ እንድትሆን ጥሪ ማስተላለፏንም ገልፀዋል።

በተጨማሪም ሰሜን ኮሪያ ከምታካሂዳቸው የኒውክለርና የሚሳይል ሙከራዎች እንድትታቀብ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በኩል ጥሪ ማስተላለፏን ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።

ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ በአካባቢው የሚያደርጉትን የጦር ልምምድ ወደ ባሰ ፍጥጫ የሚያመራ በመሆኑ ከዚሁ እንዲቆጠቡና በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሠፍን በኒውክለር አጠቃቀም ዙሪያ በሰሜን ኮሪያና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተቋርጦ የነበረው ድርድር እንዲቀጥል ጥሪ ማስተላለፏንም  አክለው ተናግረዋል ።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2009 በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የተተገበረው የባለጉዳይ ወረፋ ማስጠበቂያ ዘመናዊ ስልት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንዳስቻለ ተገለጸ።

ፍርድ ቤቶቹ የተገበሯቸውን ዘመናዊ አሰራሮች የፍትህ ሳምንትን ምክንያት በማድረግ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ልደታ የሚገኘውን መስሪያ ቤት አስጎብኝተዋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋና ሬጀስትራር ወይዘሮ ህይወት ማሙሸት እንዳሉት፤ በፍርድ ቤቶች አካባቢ ከሚነሱ የባለጉዳይ ቅሬታዎች መካከል ከምዝገባ ጀምሮ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ውስብስብ ቢሮክራሲ መንገድ ስለመከተሉ ነው።

የፍርድ ቤቶቹን አገልግሎት ፈላጊዎች ጉዳያቸውን በቀላሉ ለማስፈጸም ችግር ያጋጥማቸው እንደነበር የገለጹት ወይዘሮ ህይወት፤ ባለጉዳይ መስለው ወደ ፍርድ ቤቶች በሚገቡ ደላሎች ለመጭበርበር ተጋላጭ እንደነበሩ አውስተዋል።

ይህን ችግር ለማቃለል በፌዴራል የመጀመሪያ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች አካባቢ ዘመናዊ የባለጉዳይ ወረፋ ማስጠበቂያ ዘመናዊ ስልት በ2009 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጓል።

የወረፋ ማስጠበቂያ ዘመናዊ ስልት ወደ ፍርድ ቤቶች የመጡ ደንበኞች እንደአመጠጣቸው በሚፈልጉት የአገልግሎት ክፍል ቀጥታ እንዲስተናገዱ የሚያስችል የትኬት አገልግሎት ነው።

የመረጃ ዴስክ፣ የፋይል ከፈታ፣ የገንዘብ ክፍያ፣ የፍትሀ ብሄር ይግባኝና መሰል በፍርድ ቤቱ ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ባንድ መስኮት በማሰባሰብ ባለጉዳዮች ሲመጡ በተሰጣቸው የትኬት ቁጥር አማካኝነት በፍጥነት ለማስተናገድ ያስችላል።

ይህ የባለጉዳይ ወረፋ ማስጠበቂያ ዘመናዊ ስልት ባለጉዳዮች በፍርድ ቤቶች ይደርስ የነበረውን እንግልት በማቃለል ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዳስቻለም አብራርተዋል።

በመስሪያ ቤቱ በአካል መገኘት ያልቻሉ ባለጉዳዮች ደግሞ በ8394 ነጻ የስልክ መስመር  አገልግሎት እያገኙ ነው።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2009 የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በእግራቸው መስራት የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረገ በእጅ ብቻ የሚሰራ የሽመና መሳሪያ እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡

መሳሪያው በሚቀጥለው ዓመት አገልግሎት ላይ ይውላል ተብሏል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሲሳይ ሸዋአማረ እንደገለጹት መሳሪያው አሁን የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የደረሰ ሲሆን በቀጣይ ወራት የማጠናቀቂያ ስራዎች ተሰርተው በመጪው ዓመት ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ ይውላል፡፡

ለዚህም ዩኒቨርሲቲው ከጉራጌ ዞን ጋር በመተባበር አካል ጉዳተኞችን በማደራጀት መሳሪያው እንዲደርሳቸው እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

ይህም በእግራቸው ላይ ጉዳት ላለባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የስራ ዕድል በመፍጠር እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት፡፡

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በጋርመንት፣ በፋሽን ዲዛይን ዘርፎች ለሚያደርገው እንቅስቃሴ አጋዥ ነው ብለዋል፡፡ 

የመጀመሪያው መሳሪያ ከአልሙኒየምና ከሌሎች ውድ ግብዓቶች የተሰራ ሲሆን ከ180 እስከ 200 ሺህ ብር ወጥቶበታል፡፡

በቀጣይ ያገለገሉ ግብዓቶችን በመጠቀም ከ100 ሺህ ብር ባነሰ ወጪ 20 መሳሪያዎችን ለማምረትና በቅናሽ ዋጋ እንዲገኝ ለማስቻል እንደሚሰራ ዶክተር ሲሳይ ገልፀዋል፡፡

ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር በመተባበር ሌሎች መሳሪያዎችን በማምረት ምርቱንና ተሞክሮውን ወደ ሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ለማሰራጨትና አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም ጠቁመዋል፡፡

 

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2009 ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ የህዝብ አውቶቡሶች የጥራት ደረጃ እንደወጣላቸው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ፕሮግራም ማኔጅመንት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

በአገር ውስጥ ለሚገጠሙና ከውጭ ለሚገቡ ለአውቶቡሶች ደረጃ ያወጣላቸው የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ነው።

ፅህፈት ቤቱ ስለደረጃው ግንዛቤ ለመፍጠር ከፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣንና ከትራንስፖርት ማህበራት ጋር ባደረገው ውይይት ከአሁን በኋላ ወደ ከተማዋ የሚገቡ አውቶብሶች የጥራት ደረጃቸውን ያሟሉ መሆን አለባቸው ብሏል።

የፅህፈት ቤቱ የደረጃና አግባብነት የስራ ሂደት ኃላፊ አቶ ሲሳይ አሊ ደረጃ የወጣላቸው መካከለኛ፣ ባለ ሙሉ መጠንና ተጎታች ያላቸው የህዝብ አውቶቡሶች እንዲሁም የትምህርት ቤት ሰርቪስ አውቶቡሶች ናቸው ብለዋል።

የወጣው ደረጃ የአየር ብክለትን ከመቀነስ፣ ለተሳፋሪዎች ምቾት ያለው እና የትራፊክ መጨናነቅን የሚቀንስ ሆኖ የተዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት አዳዲሶቹ አውቶቡሶች ለአካል ጉዳተኞች የተመቹ፣ የካርቦን ልቀታቸው ዝቅተኛ የሆነ፣ ረጅም ጊዜ ማገልገል የሚችሉና በሌሎችም መስፈርቶች ይለካሉ።

በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የደረጃዎች ዝግጅት ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይልማ መንግስቱ ለአውቶቡሶቹ ደረጃ ማውጣት ያስፈለገው የትራንስፖርት ጥራትና እጥረትን ለመቅረፍ፣ የተሳፋሪዎችን ምቾት ለመጠበቅና ከተማዋን የዘመናዊ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ለማድረግ ነው ብለዋል።

የወጣው ደረጃም ከከተማዋ የወደፊት ገፅታ ጋር ተስማሚ እንዲሆን ታስቦ ነው።

እንደ አቶ ይልማ ገለጻ በአሁኑ ወቅት ስራ ላይ ያሉ አውቶቡሶች በዚሁ ስራቸው ቀጥለው የአገልግሎት ጊዜያቸው ሲያበቃ ብቻ ከገበያ እንዲወጡ ይደረጋል።

ከአውቶቡሶቹ በተጨማሪ ወደፊት የመንገዶችን፣ የትራፊክ መብራቶችና አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻዎች ደረጃ እንዲወጣላቸው እየሰራን ነው ብለዋል።

ከግል ትራንስፖርት የመጡ ተሳታፊዎች አዳዲስ ለሚገቡ አውቶቡሶች ደረጃ መውጣቱን አድንቀው የመለዋወጫ ዕቃዎች ደረጃ እና የዋጋ ንረት ላይ ትኩረት እንዲደረግ ጠይቀዋል። 

Published in ኢኮኖሚ

ግንቦት 3/2009 የኢትዮዽያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (INSA) ኢዩቴል ሳት ከተሰኘው ድርጅት ጋር ባደረገው ስምምነት ኢትዮ ሳት የተባለ የሳተላይት ቲቪ ለትግበራ አመቺ እንዲሆን ማድረጉን ራፒድ ቲቪ በዜና ዘገባው አመልከቷል።

ኢትዮ ሳት ሳተላይት ቲቪ ዘጠኝ ብሄራዊ ቻናሎችን እንደያዘም በዘገባው ተመልክቷል።   

የትብብር ስምምነቱ ኢዩቴል ሳት በ7/8 ዲግሪ ዌስት በመካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ ለማሰራጨት አቅምን ይፈጥርለታል ተብሏል።

የኢትዮዽያ ብሄራዊ ሳተላይት ቴሌቪⶵን ከበርካታ ሳተላይቶች ተቀብለው የሚያሰራጩ ከ30 በላይ ቻናሎችን በውስጡ አቅፎ መያዙን ያመለከተው ዘገባው በስምምነቱ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የስራ ፈቃድ ያላቸውን ቻናሎች እውን እንዲሆኑ በማድረግ የዲጂታል ስራውን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳ ዘግቧል።

በስምምነት ዕድሉ የኢትዮዽያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንና ኦሮሚያ ቲቪ የመጀመሪያዎቹ በመሆን መረጃዎቻቸውን እያሰራጩ ይገኛሉ።በቀጣይም የብሄራዊ፣የክልላዊና የንግድ ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃንን ወደ ኢትዮሳት የማስገባት ስራ እንደሚሰራ ኤጀንሲው ጠቁሟል።  

“የኮንትራት ስምምነቱ በኢትዮዽያ የዲጂታል ቴሌቪⶵን ገበያ ውስጥ አዲስ የለውጥ ማዕበል ሊፈጥር ይችላል፤የመረጃ ይዘቶች በነፃ አየር በተለያየ አግባብ የሚተላለፉባቸው ከ1200 በላይ ጠንካራ ቻናሎች ያሉበት ነው።” በማለት የኢዩቴል ሳት የገበያ ልማት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚሼል አዚበርት ተናግረዋል።   

የኢትዮዽያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ገ/መስቀል ተክለማርያም በበኩላቸው ኢትዮሳት የሃገራችንን የሚዲያ መልክዓ ምድር እንደሚለውጠው ተናግረዋል።

“የኢዩቴል ሳትን የካበተ ልምድ በመጠቀም ኤጀንሲው በሃገሪቱ ዘርፈ ብዙ የብሮድካስት አገልግሎት በጥራትና ተወዳዳሪ ይዘት ይሰጣል”በማለት አክለዋል።

ለንደን ግንቦት 3/2009 በሶማሊያ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሠላምና ደህንነት ዘላቂ ለማድረግ አገሪቱ ከቀጣናውና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተጠናከረ ድጋፍ እንደምትሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ። 

የምስራቅ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) መሪዎችና የሚመለከታቻው አጋር አካላት በሶማሊያ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሠላምና ደህንነት ዘላቂ ለማድረግ በሚቻልበት በእንግሊዝ እየመከሩ ባሉበት ጉባዔ ላይ የወቅቱ የኢጋድ ሊቀ-መንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። 

“ለሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ኃይል እንሁን፤ በዚህ ጉዳይ አንድ ድምጽ ይኑረን፤ ትኩረትም እንስጠው፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብርና እርምጃ ለመውሰድ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይኑረን፤ ይህ ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ይሰማኛል፤ ይህ ካልሆነ በእርግጠኝነት በዚህ ጉዳይ ለውጡ ውጤታማ ሊሆን አይችልም” ነው ያሉት። 

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ በሶማሊያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት፣ ለድርቅ ቅነሳና የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ማገገሚያ እንዲሁም ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን እንዲውል ጠይቀዋል።  

አልሸባብ አሁንም በዋና ከተማዋና በሌሎችም አካባቢዎች ከባድ የሽብር ጥቃት ለማድረስ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም “ለዚህም አፅንዖት ሊሰጠው ይገባል” ነው ያሉት።     

በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሠላም አስከባሪ ጦርን በማጠናከር በተለይ በአልሸባብ ላይ የሚደረገውን ዘመቻ መደገፍ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።  

“እኛ እንደ ቀጣናው አገር መሥዋዕትነት መክፈሉን እንቀጥልበታለን፤ በሶማሊያ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነን፤ ከዚህ በላይ ድጋፍ የለም፤ ይህም ለጋራ ጥቅም የሚደረግ ነው” ብለዋል።

በቀጣናው በአሁኑ ወቅት ድርቅ ተከስቷል፤ የተከሰተውን ድርቅና ስደት የፖለቲካና ደኅንነት ጉዳይ ሆኖ እየታየ በመሆኑ በአፋጣኝ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

በሶማሊያ የተከሰተው የኮሌራ ወረርሺኝ አፋጣኝ መፍትሔና ድጋፍ የሚሻ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል። 

የሶማሊያን ኢኮኖሚ እንዲያገግምም የተሻለ መተዳደሪያና የሥራ ዕድል እንዲሁም የአገር ውስጥ የገቢ ማስገኛ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘላቂነት ያለው ልማት ለማምጣት መሥራትም ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ በበኩላቸው ለዴሞክራሲ ግንባታ ትኩረት ለመስጠት፣ ሽብርተኝነትና ሙስናን ለመዋጋት እንዲሁም የአገሪቱን ዘላቂነት ያለው ልማት ለማምጣት ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ በጉባዔው ላይ ቃል ገብተዋል።

“ሶማሊያ በሁሉ ረገድ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትደርስ የዴሞክራሲ ተቋማቶቻችንን ማጠናከር መሠረታዊ መንገድ መሆኑን እናምናለን፤ ከዚህ በኋላ ሦስት የሶማሊያ ዋና ጠላቶች የሆኑ ሽብርተኝነት፣ ሙስና እና ድኅነት ላይ እንዘምታለን” ብለዋል።

የአገሪቱ ተፈጥሯዊ ኃብት ፍትሃዊ ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ የተጀመረ ነገር መኖሩን የገለጹት ፕሬዚዳንት አብዱላሂ በቀጣይም መንግሥት በዘርፉ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ዘላቂነት ያለው ሥራ ይሰራል ነው ያሉት።   

አዲሱ ብሔራዊ የፀጥታ መዋቅር የሶማሊያን ብሔራዊ ጦር ለማጠናከርና በአገሪቱ ለውጥ ለማምጣት ጥሩ አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል።

ሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሠላም አስከባሪ ጦርን በማገዝ በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በአልሸባብ ላይ ድል እንደምትቀዳጅ ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ተናግረዋል።  

ለዚህ ስኬት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።  

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን