አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Wednesday, 10 May 2017

አዲስ አበባ ግንቦት 2/2009 በዱባይ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።

ኢትዮጵያዊያኑና ትውልደ ኢትዮጵያዊኑ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ ማሰባሰቢያ የሎተሪ ድጋፍ የሚውል አንድ ራቫ ፎር ተሽከርካሪ  በስጦታ አበርክተዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤትም የተሽከርካሪ ቁልፍ ተረክቧል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ እንደቀጠለ መሆኑ ይታወቃል።

በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በገንዘብ፣ በእውቀትና ቦንድ በመግዛት የሚያደርጉት ድጋፍ የግድቡን ግንባታ ከመጨረሻው እስኪደርስ እንደሚዘልቅ በተደጋጋሚ ቃል እየገቡ ነው።

በተለያዩ መንገዶች ከኀብረተሰቡ  ዘጠኝ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን በቅርቡ ከግድቡ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በተመሳሳይ መልኩ በዱባይ እና በሰሜን ኢምሬትስ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ድጋፋቸውን አጠናክረው በመቀጠል የቦንድ ግዥ አከናውነዋል።

በዱባይ የኢትዮጵያ ቆንፅላ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ይበልጣል አእምሮ እንደገለጹት፤  የግድቡ መሠረት ድንጋይ የተጣለበትን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድርግ በዱባይና አካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን 152 ሺ ዶላር  የቦንድ ግዢ ፈጽመዋል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት እስካሁን በዱባይና በአካባቢው ስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር የቦንድ ግዢ ማድረጋቸው ነው ያመለከቱት።

በዱባይ ነዋሪ የሆኑት የአል ሀበሻ ሬስቶራንት ባለቤት ወይዘሮ ሳራ አራዲ በቤተሰቦቻቸውና በድርጅታቸው ስም የ250ሺ የአሜሪካ ዶላር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያውሉትን ድጋፍ አጠናክረው ለመቀጠል መወሰናቸውን ነው የገለጹት።  

በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ ከ57 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን፤ የግድቡ አርማታ ሙሌት ሥራም 72 በመቶ ያህል መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በተደረገለት የማሻሻያ ሥራዎች ኃይል የማመንጨት አቅሙ ወደ 6 ሺ450 ሜጋ ዋት ከፍ ማለቱ ይታውቃል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ግንቦት 2/2009 የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን ለምግብነት በሚዘጋጅ እህል ውስጥ ባዕድ ነገር በመጨመር ለገበያ የሚያቀርቡ ግለሰቦችን የመለየትና ለፍትህ አካላት የማቅረብ ስራውን በአግባቡ ያለመወጣቱን አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

ባለስልጣኑ ከተለያዩ ክፍለከተሞች ከተውጣጡ ነዋሪዎች ጋር በተወያየበት ወቅት ከተሳታፊዎቹ እንደተገለጸው፤ ለምግብነት በሚዘጋጅ እህል ውስጥ ባዕድ ነገሮች በመጨመር ለገበያ ሲያቀርቡ እየታየ ትኩረት ሰጥቶ አልሰራም ፤ ተገቢውን ክትትል አላደረገም ፤ አጥፊዎችንም በተገቢው ለፍትህ እያቀረበ አይደለም።

ከልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ፎረም የተወከሉት አቶ ገብሬ ታደሰ እንደተናገሩት፤ ህገ ወጥ ተግባሩን በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ ተገቢውን ቁጥጥር  እያደረገ አይደለም።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፎረም የመልካም አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጌታቸው የሻነው በበኩላቸው፤ የዚህ ዓይነት "ህገ- ወጥ ድረጊት የሚፈጽሙ አካላት ላይ  ተገቢ የፍትህ ውሳኔ እንዲሰጥ መስሪያ ቤቱ ትኩረት አላደርገም" ብለዋል።

ከአዲስ አበባ ነጋዴዎች ፎረም የተወከሉ አቶ እንዳለ አንለይ እንደሚሉት ከሆነ ባለስልጣኑ በአዋጅ የተሰጠውን የማስጠንቀቅ፣ የመቆጣጠር የማሸግ እና የማገድ ኃላፊነትም በሚፈለገው ደረጃ እየተወጣ አይደለም።

የዚህ ዓይነቱን ሕገወጥ ተግባር በሚፈጽሙት ላይ በሚሰጠው ፍርድ ልዩነት ይስተዋላል። ለተመሳሳይ ድርጊት የተለያየ ፍርድም ይሰጣል። ይህም መስሪያ ቤቱ ተገቢውን ስራ እያከናወነ አለመሆኑን ያመለክታል።

በአሁኑ ወቅት በጤፍ እና በስንዴ ላይ የጄሶ እና ሰጋቱራ ቀላቅሎ በማስፈጨት፣ እንጀራ እየጋገሩ በመሸጥ በዜጎች ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትል ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦች መኖራቸው ይስተዋላል።

ይህን ህገ-ወጥ ተግባር መቆጣጠር ከመቻል እና በተያዙት ላይ አስተማሪ የፍትህ ውሳኔ እንዲያገኙ ከማስቻል አኳያ በርካታ ክፍተቶች መኖራቸውን ነው ነዋሪዎች በምሬት የገለጹት።

መስሪያ ቤቱ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ከታች ከቀጣና ጀምሮ የተናበበ ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት እንደሚገባው ነው ምክረ ሀሳባቸውን የሰጡት።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ወረቲ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት   ቀደም ብሎ ባዕድ ነገሮችን ለምግብነት ከሚውል እህል ጋር የሚቀላቅሉ ግለሰቦች ብዙዎቹ የብቃት ማረጋገጫም ሆነ የንግድ ፍቃድ የሌላቸው ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ግን ንግድ ፍቃድ እና የብቃት ማረጋገጫ ያላቸው አካላት በተመሳሳይ ተግባር ውስጥ በስፋት ስለመሳተፋቸው በመረጃ መረጋገጡን አመልክተው፤ ይህን ችግር ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በዚህ ዓይነቱ ህገወጥ ተግባር የሚሳተፉ ግለሰቦች ንብረታቸውን የማስወገድ እና ለፍትህ አካላት የማቅረብ ተግባር እንደሚከናወን አቶ ጌታቸው ተናግረው፤ "በአጥፊዎቹ ላይ የሚወሰደው አስተዳደራዊም ሆነ ፍትሃዊ እርምጃዎች አስተማሪ እና ፍትሃዊ መሆን ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን አረጋግጠናል" ብለዋል።

Published in ማህበራዊ

ግንቦት 2/2009 የሚያዝበት በቂ ገንዘብ ሳይኖረው ለባንክ ቼክ ያቀረበ አንድ ተከሳሽ በሶስት ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሶስተኛው ወንጀል ችሎት ጃፈር አብዱሰላም በተባለው ግለሰብ ላይ ነው የቅጣት ውሳኔ ያሳለፈው፡፡

ተከሳሹ ቅጣቱ የተጣለበት በአካውንቱ የሚያዝበት በቂ ገንዘብ አለመኖሩን እያወቀ ለግል ተበዳይ አቶ ዳዊት ገብረእግዚአብሄር ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓመተ ምህረት በግምት ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 03/09 ውስጥ የ600 ሺህ ብር ቼክ ፈርሞና ስሙን ፅፎ መስጠቱ በመረጋገጡ ነው፡፡

የግል ተበዳይም የተሰጣቸውን ቼክ ይዘው ተክለሃይማኖት አካባቢ ወደሚገኘው አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ቀርበው ሲጠይቁ በአካውንቱ በቂና የሚያዝበት ገንዘብ እንደሌለ ስለተገለጸላቸው ክስ መመስረታቸውን የክስ መዝገቡ ያብራራል፡፡

ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የአራዳ ምድብ ችሎትም ግንቦት 1 ቀን 2009 ዓ.ም  የሰው፣ የሰነድና የኢግዚቢት መረጃዎችን በመመርመር ፤ የተከሳሹን የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆን ከግምት በማስገባት የቅጣት ማቅለያዎችን በመያዝ በሶስት ዓመት ፅኑ እስራትና በብር አምስት ሺህ እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

Published in ማህበራዊ

ጊምቢ ግንቦት 2/2009 ያሉበትን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች በየጊዜው በጥናት እየለየ በሚያደርጋቸው ማስተካከያዎች አሰራሩን ማሻሻሉን የጊምቢ ሆስፒታል አስታወቀ ። 

የሆስፒታሉ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሃይሉ እንደገለጹት ሆስፒታሉ የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድና አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት ህብረተሰቡ ፈጣንና የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኝ እያደረገ ነው።

አገልግሎቱ በተለይም ከከተማና ከገጠር ለሚመጡ ህሙማን በዱቤ የሚታከሙበትንና መድኃኒቶችንም በፍጥነት የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸቱንም ገልጸዋል።

ቀደም ሲል ከካርድ አወጣጥ ጀምሮ በእያንዳንዱ አገልግሎት ላይ የነበረውን የተጓተተ አሰራር ለመለወጥ ሁሉንም ሰራተኛ በማቀናጀት ባደረገው ጥረት ወደ ተሻለ ደረጃ ማምጣቱን ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ደሳለኝ አበበ እንደገለጹት ሆስፒታሉ የተጠቃሚዎችን ፍላጎት ለማርካት የጥናት ቡድን አቋቁሞ በየጊዜው አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

ቀደም ሲል በሆስፒታሉ በቀን ከ100 እስከ 150 ህሙማንን ብቻ ይስተናገዱበት የነበረውን አሰራር በማሻሻል አሁን ላይ እስከ 500 ህሙማንን እያስተናገደ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በተለይ በሆስፒታሉ የማህጸን በር ካንሰር ህክምና አገልግሎት መጀመሩ ታካሚዎችን በአቅራቢያቸው ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ከአላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት እንደታደገም ገልጸዋል።

ወይዘሮ ኤቢሴ አሳና የተባሉ የሆስፒታሉ ተገልጋይ እንደገለጹት ቀደም ሲል የህክምና ካርድ ለማውጣት ብቻ ከአምስት ቀን በላይ ወረፋ ለመጠበቅ ይገደዱ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ግን ሆስፒታሉ ይህንን አሰራር በመቀየሩ የህክምና አገልግሎቱን በሰዓታት ውስጥ ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።

"በተለይም ለእናቶች እና ህጻናት ቅድሚያ ለመስጠት የሚያስችል አዲስ አሰራር በመተግበሩ ተጠቃሚ ሆኛለሁ" ብለዋል።

ከምእራብ ወለጋ ዞን እናንጎ ወረዳ ላንጆ ቀበሌ ለህክምና የመጡት ወይዘሮ ሰናዬ በቀለ በበኩላቸው በግማሽ ቀን ውስጥ የምርመራና የመድሃኒት አገልግሎት ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 2/2009 የፍትህ አካላት ያሉባቸውን ክፍተቶች አሁንም ማስተካከል አልቻሉም ተባለ።

 ሰባተኛው አገር አቀፍ የፍትህ ሳምንት ''የህግ የበላይነት ለዘላቂ ሰላምና ለህዝቦች አንድነት'' በሚል መሪ ቃል በባለሙያዎች ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

 በተለይም ችግሩ በፍርድ ቤቶች ላይ በጉልህ እንደሚስተዋል ከተለያዩ የፍትህ አካላት የተውጣጡ በውይይቱ የተሳተፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።በውይይቱም በፍትህ ተቋማት በተለይም በፍርድ ቤቶች ዘንድ ሰፊ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙሰኝነት፣ የፍርድ ማዛባትና ማጓተት ችግሮች በስፋት እንደሚስተዋሉ ነው ተወያዮች የጠቆሙት።

በዚህም ፍርድ ቤቶች ከአገሪቱ የእድገት ደረጃ ጋር ተመጣጣኝ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ተብሏል፤ ራሳቸውን በዘመናዊ አሰራርን ማደራጀትም ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ችግሮቹ ከአቅም ውስንነት፤ ከባለሙያው የሙያ ብቃት ማነስ፤ አንዳንድ ባለሙያዎች  በስነ-ምግባር የታነጹ አለመሆንና በጥፋተኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አናሳ መሆን በተጨማሪም በፍርድ ቤቶች ያለው የሰው ሃይል እጥረት ለችግሮች መነሻ ምክንያቶች መሆናቸውን ነው ተወያዮቹ የጠቀሱት።

የፍትህ ተቋማት ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት ከመስራት አንጻርም ክፍተቶች መኖራቸውን አንስተዋል።

 የፍትህ አካላት የህዝቦችን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥተው  በመስራት  በህብረተሰቡ ዘንድ አመኔታን  አሳድረው  ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

 በፍርድ ቤቶችና በፍትህ ተቋማት ላይ የህግ ስርዓቱን በሚጥሱት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ በመውሰድ ለተገልጋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባም አንስተዋል።

 የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዳኜ መላኩ በበኩላቸው በፍትህ አካላት ላይ ከህብረተሰቡ ቅሬታዎች ይነሳሉ በተለይም ደግሞ ፍርድ ቤቶች ላይ የፍርድ መዘግየት፣ በአንዳንድ ዳኞች የሚታየው ብልሹ ስነ ምገባር፣ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በስፋት እንዳሉ ከቅሬታ አቅራቢ ተገልጋዮች መረዳት መቻላቸውን  ነው  የገለጹት።

 እኛም ከህብረተሰቡ የመጡ ቅሬታዎችን በመመርምር ተገቢውን ማስተካከያ እያደረግን አገልግሎቱን ቀልጣፋ ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል።

 በዚህም በተቋሙ የሚታየውን የፍርድ የጊዜ ገደብ መጓተት ለማስተካከል ቀጠሮዎች በምን ያህል ጊዜ መጠናቀቅ እንዳለባችው የቀጠሮ ፖሊሲ የሚል ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑንና በቀጣይ ወደ ተግባር እንደሚገቡ ጠቁመዋል።

 የፍርድ ስርዓቱን የሚያዛቡ ባለሙያዎችና ዳኞች ላይ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ እርምጃ እንደሚወሰድም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

 የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ በላቸው አንሽሶ እንደሚሉት ደግሞ በፍርድ ቤቶች ከሚታዩ መጓተቶች በቃል የተደረጉ ክርክሮችን ከድምጽ ወደ ጽሁፍ የሚቀይር መሳሪያ ያለመኖር ትልቁ ችግር መሆኑን ያነሳሉ።

 ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ድምጽን ወደ ጽሁፍ የሚቀይር መሳሪያ ሶፍትዌር ለማዘጋጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

 እንደ አቶ በላቸው ገለጻ የሚሰራው መሳሪያ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከኮምፒተር ሳይንስ ዲፓርትመንት ጋር በመተባባር ሲሆን ሲጠናቀቅም የአገር ውስጥ ቋንቋን ወደ ጽሁፍ በመቀየር የሚታየውን መጓተት እንደሚቀንስ እምነት ተጥሎበታል።

 ሚያዚያ 30 መከበር የጀመረው ሰባተኛው የፍትህ ሳምንት እስከ ግንቦት 6 ቀን 2009 ዓም ድረስ ይቆያል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ግንቦት 2/2009 የጀግኖች አባቶችን ታሪክ በመገንዘብ አባላቱን በሙያቸው ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰራ በአዲስ አበባ የትግራይ ወጣቶች ማህበር ገለጸ።

ማህበሩ የጀግኖች ሰማዕታት ቀንን ለማሰብና ወጣቶችን ለማነቃቃት ''እኛ ወጣቶች የጀግኖች ታጋይ ሰማዕታትንን አደራ እንጠብቃለን'' በሚል መሪ ቃል ግንቦት 19 በሚሌኒየም አዳራሽ ፌስቲቫል አዘጋጅቷል።

የማህበሩ ሊቀ-መንበር ወጣት ሰለሞን ገብሩ ፌስቲቫሉን አስመልክቶ እንደተናገረው ''ማህበሩ ከተመሰረተ ጀምሮ በአገሪቱ ባሉ የልማት ስራዎች የራሱን ድርሻ ሲወጣ ቆይቷል''።

በመዲናዋ በሚከናወኑ የልማት ስራዎችም የማህበሩ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ በ1997 ዓ.ም ከተመሰረተ አንስቶ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጿል።

ወጣቱ የአባቶቹን ታሪክ ተከትሎ ለከተማዋም ሆነ ለአገሩ እንዲሰራ የሚያነቃቃ ፌስቲቫል ማዘጋጀቱንም አስታውቋል።

በፌስቲቫሉ ከ20 ሺህ በላይ ወጣቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ያለው ሰብሳቢው በዝግጅቱ ላይ የትግራይ ህዝብን የትግል ታሪክና ባህል የሚያሳዩ የፎቶ አውደ ርዕይ፣ ወጣቶቹ አሁን ያሉበትን ሁኔታ የሚያሳይ የፓናል ውይይት እንደሚቀርብም ገልጿል።

ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ምን እየሰራ ነው ተብሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበው ጥያቄም መንግስት ለወጣቶች ባዘጋጀው ፈንድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራን ነው ብሏል።

የትግራይ ወጣቶች ማህበር በ1983 ዓም የተመሰረተ ሲሆን ከ400 ሺህ በላይ አባላት አሉት።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ግንቦት 2/2009 ዓመታዊው የቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንት ሰልጣኞች ከንድፈ ሃሳብ ባለፈ ተግባር ተኮር ትምህርት እንዲያገኙ እገዛ እንዳለው የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ገለፀ። 

የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር አቶ አሸብር ተክሌ "ሰላም ለቱሪዝም-ቱሪዝም ለህዳሴያችን" በሚል መሪ ሃሳብ ከግንቦት 6 እስከ 10 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ በሚካሄደው አምስተኛው የቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንት ሁነት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። 

አቶ አሸብር እንደተናገሩት በዘርፉ ተገቢውን ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት 30 በመቶ የንድፈ ሃሳብ ቀሪው ደግሞ በተግባር ስልጠና መደገፍ አለበት።

 ይህ ሁነት መዘጋጀቱ በተለያዩ የሆቴልና ቱሪዝም ሰልጣኞች በክፍል የተማሩትን የንድፈ ሃሳብ ትምህርት በተግባር ለተጋባዥ እንግዶችና ለጎብኚዎች እንዲያቀርቡ ያስችላል ብለዋል።

 እስካሁን በተደረጉ አራት ዝግጅቶችም ይሄንን ውጤት ማግኘት እንደተቻለና በዘርፉ የሚያሰለጥኑ ተቋማት ከኢንዱስትሪው ጋር እንዲተሳሰሩ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

 የዘንድሮው ዝግጅት በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ዙሪያ ጥናታዊ ፅሁፎችን በማቅረብ፣ በእግር ጉዞ፣ በፓናል ውይይት፣ ኤግዚብሽን፣ በአዝናኝ ትዕይንቶችና መሰል ውድድሮችን በማካሄድ እንደሚከበር አቶ አሸብር ገልጸዋል።

 ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የክልል ባህልና ቱሪዝም መሪዎች፣ የሆቴልና አስጎብኚ ድርጅት ባለቤቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ መገናኛ ብዙሃንና ምሁራን በሁነቱ ይሳተፋሉ።

 በ2007 ዓ.ም በተደረገ ጥናት በኢትዮጵያ ሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከተሰማሩ ባለሙያዎች ተዛማጅ ትምህርት የተከታተሉት 23 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው።

 ከ48 አመታት በፊት በአራት ተማሪዎች ስልጠውን የጀመረው የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ኢንስቲትዩት በአሁኑ ሰዓት በመደበኛና በማታ መርሃ ግብር ከሁለት ሺህ በላይ ሰልጣኞችን እያስተማረ ይገኛል።

Published in ማህበራዊ

አምቦ ግንቦት 2/2009 በአምቦ ከተማ በህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የተሰማሩ አካላትን በመከታተል ወደ ግብር መረቡ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን የከተማው ንግድና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽሕፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ታሪኩ ቱራ ለኢዜአ እንደገለፁት በተሀድሶ መድረኮች ከህዝቡ በተነሱ ጥያቄዎች መሰረት ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በመለየት የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ጥናት ተካሂዷል።

በጥናቱ በህገ-ወጥ መንገድ እንደሚሰሩ ከተለዩት 1ሺህ 262 መካከል 963ዎቹ ያለ ንግድ ፈቃድ የሚነግዱ፣ 183ቱ ደግሞ ከተፈቀደላቸው ውጭ የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም 116ቱ የንግድ ፈቃዳቸውን አባዝተው በተለያየ ቦታ የተለያየ ንግድ የሚያከናውኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"በዘርፉ ከንግድ ፍቃድ አሰጣጥ ጀምሮ ከአገልገሎት አሰጣጥ ችግር ፣ከመልካም አስተዳደር መጓደልና ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሁም በተሳሳተ ግንዛቤ ግብር ላለመክፈል መፈለግ ለህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ መስፋፋት ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው " ብለዋል ።

ድርጊቱን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ንግድ ፈቃድ የሌላቸው ነጋዴዎች ፍቃድ አውጥተው ህጋዊ ግብር ከፋዩን እንዲቀላቀሉ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል ።

ከተፈቀደላቸው ውጭ ምርት አቀላቅለው የሚሸጡ ነጋዴዎች የተፈቀደላቸውን ምርት ብቻ እንዲሸጡ እንዲሁም ፍቃድ ካወጡበት ዘርፍ ውጭ በተለያየ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎችም የማስፋፊያ የንግድ ስራ ፍቃድ እንዲሰጣቸው መደረጉን አስረድተዋል ።

በሌላ በኩል ወደ ህጋዊ ንግድ ስርዓቱ ለመምጣት ፍላጎት በሌላቸው ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ የንግድ ቤቶቻቸውን እስከማሸግ የደረሰ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።

"በተመሳሳይ የችርቻሮ ንግድ ፈቃድ ምርት በማከማቸት በገበያ ላይ እጥረት እንዲከሰት ያደረጉ ስድስት ነጋዴዎች የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል" ብለዋል።

በከተማው አጠቃላይ ሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ስራ የተሰማራው ወጣት ፍጹም ከበደ በሰጠው አስተያየት "የህገ-ወጥ ነጋዴዎች መስፋፋት ግብር ከፋዩን ከገበያ እንዲወጣ እያስገደደው ነው " ብሏል።

ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ትክክለኛነቱና የጥራት ደረጃው ያልተረጋገጠ ምርት ለገበያ በማቅረብ በሸማቹም ሆነ በህጋዊ ነጋዴው ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆኑን በመግለፅ ህገ-ወጦችን ወደ ህጋዊነት ለማምጣት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ተናግሯል ።

ሌላው ወጣት ስንታየሁ ምንዳዬ በበኩሉ በተሽከርካሪ ጋሪ አልባሳትን በማዘዋወር በጎዳና ላይ ንግድ መሰማራቱን ገልጿል ።

ንግድ ፍቃድ አውጥቶ ህጋዊ ለመሆን ቢፈልግልም ለግብርና ለቤት ኪራይ የሚጠየቀውን ገንዘብ መክፈል ያቅተኝ ይሆናል በሚል ስጋት የጎዳና ላይ ንግዱን ሲሰራ እንደቆየ ተናግሯል።

ከዚህ በኋላ ፍቃድ አውጥቶ በህጋዊነት ለመንቀሳቀስ የሚያስችለውን አማራጭ ለመጠቀም እራሱን ማዘጋጀቱን ገልጿል።

Published in ኢኮኖሚ

መቐለ ግንቦት 2/2009 የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ "በአፍሪካ ለሚያጋጥሙ ግጭቶች አፍሪካዊ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል" በሚል ርዕስ ለሚያስተናግደው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ።

በዩኒቨርሲቲው የስነ ህዝብ ጥናት ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር ዶክተር ክንፈ አብርሃ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት አፍሪካውያን በየጊዜው የሚያጋጥማቸውን ግጭት እራሳቸው የመፍታት አቅም አላቸው።

ኢንስቲትዩቱ በደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ የአፍሪካ የግጭቶች አፈታት ኢንስቲትዩት ጋር  በመተባበር ላለፉት ሶስት አመታት በአፍሪካ የሚያጋጥሙ ግጭቶችንና የህዝቦቹን የአፈታት ስርዓቶች  ሲያጠና ቆይቷል፡፡

በጥናቱም የአፍሪካውያን የችግር አፈታት ዘዴ ከራሳቸው አልፎ ለሌሎችም እንደሚጠቅም የተቀመሩ ልምዶች በኮንፈረንሱ ላይ እንደሚቀርቡ አስረድተዋል።

“ግጭቶችን የምንከላከልበትና ካጋጠሙም የምንፈታባቸው ዘይቤዎች” በየብሄሮችና ብሄረሰቦች መኖራቸውንም ዶክተር ክንፈ  አስረድተዋል።

አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ስር መቆየታቸው  ባህላዊ የግጭት አፈታትና ሌሎች እሴቶቻቸውን እንዲያጡ ቢያደርጋቸውም በአሁኑ ወቅት ወደ ቀደመው ማንነታቸው እየተመለሱ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለባእዳን ወረራ እጅ ባለመስጠቷ በግጭት አፈታት ላይ ያላትን የተሻለ ተሞክሮ ከነገ ጀምሮ በመቀሌ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ኮንፈረንስ ላይ እንደምታቀርብም ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ የውጭ  ግንኙነት ጥናት ኢንስቲትዩትና ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር  በመተባበር በሚያስተናግደው ኮንፈረንስ ላይ 32  የሚሆኑ ጥናቶች  የሚቀርቡ ሲሆን ከ200 በላይ የአፍሪካና የዓለም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ማህበራዊ

ከሰለሞን ተሰራ /ኢዜአ/

የኢትዮጵያና የፖላንድ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት በ 17 ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ እንደተጀመረ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡የፖላንድ ንጉስ የነበሩት ጃን 3ኛ ሶቤስኪ አገራቸው ከኦቶማን ኢምፓየር የገጠማትን ጦርነት በድል ለመወጣት ከጎረቤት አገራት ያጡትን አጋርነት ከአቢሲኒያው ንጉስ እያሱ 1ኛ ለማግኘት የተሳካ ባይሆንም ሙከራ አድርገው እንደነበር በኢትዮጵያ የሚገኘው የፖላንድ ኤምባሲ ባወጣው መረጃ ተጠቅሷል፡፡

ከዚያ በኋላም በሚቀጥሉት ሁለት ክፍለ ዘመናት የፖላንድና የኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ተዳፍኖ ነበር፡፡ፖላንድ ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የተወሰኑ ተጓዦች ፣ ምሁራን እና የሐይማኖት አባቶች ኢትዮጵያን በመጎብኘት ስለአገሪቱ ባህል ፣ ህዝብ፣ ቋንቋና አስተዳደር መረጃዎችን ወደ አገራቸው ወስደዋል፡፡

ፖላንድ በ1930 አካባቢ ከኢትዮጵያ ጋር የተሟላ ሊባል የሚችል የዲፕሎማቲክና የንግድ ትስስር ለመፍጠር ሞክራለች፡፡በመጀመሪያ እርምጃዋ ካይሮ ላይ የነበረውን ቆንስላዋን በኖቨምበር 1930 ወደ አዲስ አበባ በመላክ በቀዳማዊ ሐይለስላሴ የንግስና በአል ላይ እንዲታደም አድርጋለች፡፡

በመቀጠል ፓሪስ ላይ መቀመጫውን ያደረገው የኢትዮጵያ ቆንስላ ፖላንድ ጎብኝቷል፡፡በዚህ ወቅት የሁለቱ አገራት ግንኙነት አንድ እርምጃ ፈቅ በማለት ኢትዮጵያ በጣሊያን የደረሰባትን ወረራ ፖላንድ እንድትቃወም እስከ መጠየቅ ደርሳለች፡፡ፖላንድ ትኩረቷን በኢኮኖሚ ግንኙነት ላይ በማድረግ የአገሯን ገበሬዎች በኢትዮጵያ ለማስፈር ስትሰራ ነበር፡፡በተጨማሪ የኢትዮጵያን መንግስት በኢኮኖሚ ፣በፖለቲካና በጦር ሐይል የሚያግዙ ኤክስፐርቶችን ለመላክ በትኩረት መንቀሳቀሷ ተገልጿል፡፡

የሁለቱ አገራት ዲፕሎማቶች ያደረጓቸው  ጉብኝቶች  የንግድ እንቅስቃሴያቸውን የማሳደግ ፍላጎታቸውን አሳድጎታል፡፡በዚህ በመታገዝ የኢትዮጵያ መልእክተኛ የነበሩት ተክለ ሐዋርያትና በፓሪስ የፖላንድ አምባሳደር አልፍሬድ ቻላፖውስኪ ስምምነት ለመፈራረም በቅተዋል፡፡

የሁለቱ አገራት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት የሶሻሊዝም ርዕዮተ አለምን መሰረት በማድረግ በደርግ ዘመንም ቀጥሏል፡፡በዚህ ወቅት ፖላንድ በስኮላር ሺፕ ተማሪዎችን ከኢትዮጵያ በመቀበል አስተምራለች፡፡የሶሻሊዝሙ ግንብ ከፈረሰበት ወቅት አንስቶ የአገራቱ ግንኙነት ቢቀጥልም ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸው የላላ ነበር፡፡

ባለፉት ሁለት እስርት አመታት ኢትዮጵያ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ባደረገችው ጥረት አገሪቱን በአማራጭነት ከተመለከቱት የአውሮፓ አገራት አንዷ ፖላንድ ነበረች፡፡በአውሮፓ ተወዳዳሪ የሆኑ የፖላንድ ኩባንያዎችም ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ያላቸውን ፍላጎት ማሳየት የጀመሩት በዚሁ ወቅት ነበር፡፡የፖላንድ ኩባንያዎች በአይሲቲ ፣በማምረቻው ዘርፍና በግብርና ማቀነባበር እምቅ አቅም ያላቸው ናቸው፡፡

ብዛት ያላቸው የአውሮፓ አገራት በቀውስ በተመቱበት ጊዜ ፖላንድ እድገት በማስመዝገብ ላይ ነበረች፡፡በመካከለኛው እና በምዕራብ አውሮፓ እየሰራ የሚገኘው የፖላንዱ የአይሲቲ ኩባንያ አሴኮ በኢትዮጵያ በቅድሚያ ስራ ከጀመሩ አለም አቀፍ ተቋማት አንዱ መሆኑን ጁላይ 1-2013 የወጣው ካፒታል ጋዜጣ ጽፎ ነበር፡፡

በወቅቱ በፖላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ፍስሐ አስገዶም ዋርሶ ላይ ከ 40 የኩባንያ ተወካዮች ጋር መወያየታቸውም በጋዜጣው ተገልጿል፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል የነበረውን የንግድ ልውውጥ በተመለከተ 2012 ላይ የወጣ ሪፖርት 13 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደነበር ገልጿል፡፡ኢትዮጵያ 8 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የግብርና ምርቶችን በተለይ ቡናን ወደ ፖላንድ ስትልክ ፖላንድ በበኩሏ የእንስሳት መድሐኒቶችን በብዛት ትልክ ነበር፡፡

የፖላንድ ፕሬዝዳንት አንድሬ ሴባስቲያን ዱዳ ይህንኑ ግንኙነት ለማሳደግ ያለመ ጉብኝት በኢትዮጵያ አከናውነዋል፡፡የኢትዮጵያና ፖላንድ የንግድ ልውውጥ መጠን 35 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን የፖላንድ ባለሃብቶች በግንባታ፣ በኬሚካልና በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪዎች እየተሳተፉ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖላንድ ኩባንያዎች በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስኮች ያላቸው ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን እና ተጨማሪ ኩባንያዎች ወደ አገሪቱ እንዲመጡ መንግስታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ለኢዜአ ተናግረዋል።

አሴኮና ዩረሰስ የተሰኙ የፖላንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በአይሲቲና አውቶሞቭ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተሰማርተዋል። ይህንኑ የትራክተር ፋብሪካ የጎበኙት የፖላንድ ፕሬዘዳንት የፋብሪካው ግንባታ ሁለቱ አገራት በ 2013 የደረሱበትን ስምምነት ተከትሎ የተገነባ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ትብብሩ የፖላንድ ንግድ ወደ አፍሪካ መጓዝ በማለት የያዘችው ፕሮግራም አካል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያና የፖላንድ የኢኮኖሚ ፎረም ሚያዚያ 30 አዲስ አበባ ላይ የተከናወነ ሲሆን የተዘጋጀው በፖላንድ የንግድና ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ነው፡፡ ፎረሙ ሲከፈት ንግግር ያደረጉት የፖላንድ የንግድና ኢንቨስትመንት ምክትል ፕሬዝዳንት ክራይዝስቶፍ ሴንገር የወጪ ንግድ አካሔዳችንን በመቀየር የፖላንድ ኩባንያዎች በአፍሪካ ገበያ በስፋት እንዲገቡ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

 

 

Published in ዜና-ትንታኔ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን