አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 01 May 2017

ጎንደር ሚያዚያ 23/2009 ከከተሞች ልማት ጋር በተያያዘ ከይዞታቸው ለሚነሱ ዜጎች የሚሰጠው ካሳ በዘላቂነት እንዲያቋቁማቸው በህግ ድጋፍ መታገዝ እንዳለበት አንድ ጥናት አመለከተ።

በ7ኛው የከተሞች ፎረም ላይ በኢፌድሪ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማእከል “የከተሞች የጎንዮሽ መስፋፋት ምክንያቶች ተጽእኖዎችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል።

የጥናቱ አቅራቢ ዶክተር ዘመንፈስ ገብረእግዚአብሄር እንዳመለከቱት የልማት ተነሺዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በፓኬጅ የተዘጋጀና የከተሞችን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የህግ ማእቀፍ ሊኖር ይገባል፡፡

“ፓኬጁ የተነሺዎችን የእድሜ ሁኔታ፣ የትምህርት ዝግጅት፣ የስራ ዝንባሌና ፍላጎት፣ የካፒታል አቅም መሰረት በማድረግ በሰልጠና፣ በብድር፣ በምክር አገልግሎት፣ በገበያ ትስስር፣ በማምረቻና መሸጫ ቦታ አቅርቦት መደገፍ አለበት” ብለዋል፡፡

አረጋውያንንና አካል ጉዳተኞችን ደግሞ በማህበራዊ ዋስትና እንዲታቀፉ የሚያደርግ ሊሆን እንደሚገባም ተናግረዋል።

የካሳ አዋጁ መመሪያና የደንቦች ማጠንጠኛ የተፈናቃይ ዜጎችን የቀጣይ የኑሮ ዘይቤ መሰረት ያደረገና ዘላቂ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው በማድረግ በኩል በግልጽ መደንገግ እንዳለበት ጥናቱ አመልክቷል።

ተነሺዎች የመሬት ይዞታቸውን ሲለቁ የሚሰጣቸው የመፈናቀያ ክፍያ ቀድሞ የነበራቸው የመጠቀም መብት በመቋረጡ ሌላ የገቢ ምንጭ እስኪያገኙ ድረስ የሚቀጥል ድጋፍ መሆኑ በግልጽ በህግ መደንገግ እንደሚኖርበት ጥናቱ አመላክቷል፡፡

“ከተሞች አቅም በፈቀደ መጠን የልማት ተነሺዎችን የማቋቋም ድጋፍ ያደርጋሉ” የሚለው አስገዳጅነት የሌለው የህግ አንቀጽ አስገዳጅ ሆኖ መደንገግ እንዳለበትም ጥናቱ አመላክቷል፡፡

የከተሞች መስፋፋት የመጨረሻ ግብ ለከተማ እና ለኢንደስትሪ ልማት የሚሆን መሬት የማግኘት ብቻ ሳይሆን በአከባቢው የሚገኙ ዜጎችን ህይወት በዘላቂነት መቀየርንም በተሟላ መንገድ የሚተገብር መሆን እንዳለበትም በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

ከድሬዳዋ የመጡት ተሳታፊ አቶ ጌታቸው ወርቃለማሁ “ጥናቱ በካሳ ክፍያ ላይ ያለውን ወጥ ያልሆነ አሰራርና ተፈናቃዮችን በዘላቂነት በማቋቋም በኩል የታዩ ክፍተቶችን ያመላከተ ነው” ብለዋል፡፡

በከተሞች ከህዝብ ቁጥር መጨመርና ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መስፋፋት ጋር ተያይዞ እየጨመረ የመጣውን የመሬት ጥያቄ በማስተናገድ በኩል ተፈናቃዮችን በዘላቂነት በማቋቋም በኩል ነባር ህጎቹ ሊፈተሹና ሊሻሻሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

“ጥናቱ በተጨባጭ የከተሞችን ችግር ያሳየ ነው ያሉት” የመቀሌ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ብርሃነ ገብረእየሱስ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ከማቋቋም አኳያ በጥናቱ መፍትሄ መጠቆሙ ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሌላው ተሳታፊ አቶ ተስፋ ተክሉ “የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ በክልሎችና በፌደራል ጭምር ወጥ አለመሆን የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኗል ጥናቱ መፍትሄ ማመላከቱ ተገቢና ወቅታዊ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“ጥናታዊ ጽሁፉ ለከተሞች እድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በመለየት በጋራ ለመፍታት ትልቅ ግብአት የሚሆን ነው” ያሉት ደግሞ ከአማራ ክልል ቡሬ ከተማ የመጡት አቶ ይታያል ብርሃኑ ናቸው፡፡

“አሁኑ እየተሰራበት ያለው የካሳ ክፍያ ስርአት በተለይ ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ከእርሻ ስራቸው የሚፈናቀሉ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት ማቋቋም የሚችል አይደለም”ብለዋል።

“ጥናቱ ወሳኝ ጉዳዮችን የዳሰሰና ያመላከተ ሲሆን የመንግስትም ቁርጠኛነት ሊታከልበት ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የፓናል ውይይቱን የመሩት በሚኒስቴር ማእረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ አቶ በረከት ስምኦን "በፍጥነት እያደጉና እየተስፋፉ የመጡ ከተሞች ዘላቂ እድገታቸውን ከማስቀጠል አኳያ የሚገጥሟቸውን ችግሮች  በጥናትና ምርምር መለየት ተገቢ ነው" ብለዋል፡፡

በኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማእከል ለከተሞች ፎረም ተብሎ የተዘጋጀው የመነሻ ጥናትም ከተሞች በችግሮቻቸው ዙሪያ ጥናቱን መነሻ በማድረግ እንዲወያዩ እንዲመክሩና ጠቃሚ ግብአቶችን ማሰባሰብ አንዲቻል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ በፎረሙ ተሳታፊ ከሆኑ 231 ከተሞች የተጋበዙ የከተማ ማዘጋጃ ቤት ሃላፊዎች ከንቲባዎችና ባለሙያዎችን ጨምሮ የፌዴራል ከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር እንዲሁም የክልል ቢሮ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 23/2009 የሰራተኞች የመደራጀት መብት በግል ባለሀብቶች እንቅፋት እንደገጠመው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፈደሬሽን አስታወቀ።

አለም አቀፉ የላብ አደሮች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ128ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ42ኛ ጊዜ “የኢንዱስትሪ ሰላምና ምርታማነት በተደራጀ ሰራተኛ ይረጋገጣል” በሚል ሃሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

ውይይቱን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፈደሬሽን የሰራተኞች መደራጀት መብት ውስን የግል ባለሀብቶች ባላቸው የተዛባ አመለካከት ሳቢያ እንቅፋት እንደገጠመው ገልጿል።

የኮንፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው አህመድ እንደገለፁት የሰራተኞች የመደራጀት መብት ላይ ህገወጥ ተግባር የሚፈፅሙ ባለሀብቶች አሉ።

የግል አሰሪ ተቋማት የቀጠሯቸው ሰራተኞች እንዲደራጁ የማይፈቅዱና ፈቅደውም የተደራጁ ማህበራት አመራሮችን ማዋከብና ሌሎች ጉዳቶችን ያደርሳሉ ብለዋል አቶ አህመድ።

ከዚህ በተጨማሪ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን የሚገዙ ባለሀብቶች ነባር ሰራተኞችን ያለአግባብ ከስራ መቀነስና የሥራ ዋስትና ማሳጣት ተግባራት እየተፈፀሙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ከመንግስት ወደ ግል በሚዛወሩ የልማት ድርጅቶች በገዙ ባለሀብቶች ላይ ክትትል ማድረግ የሰራተኞችን የሥራ ዋስትና እንዲከበር መንግስት ሚናውን እንዲጫወት ጠይቀዋል።

አቶ አያሌው እንደገለፁት አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ድርጅቶች ራሳቸው የማያሰሯቸውን ሰራተኞች በመቅጠር ለሌሎች ድርጅቶች በማከራየት  የጉልበት ብዝበዛ እየፈጸሙ በመሆኑ ለዚህ ህገ ወጥ ድርጊት ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ አዋጆች እንዲሻሻሉም ጠይቀዋል።

በሥራ ላይ በሚፈጠሩ አደጋዎች የሚሞቱና ለአካል ጉዳት የሚጋለጡ ሰራተኞች ቁጥር እየጨመረ ነው ያሉት አቶ አያሌው መንግስት የሙያ ደህንነትና የጤንነት ፖሊሲ የሚጥሱ ተቋማት ላይ  እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር በበኩላቸው በግሉ ባለሀብት የሰራተኞች መደራጀት አሰሪዎች ይጎዳል የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመቅረፍ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህ መሰረት በርካታ አሰሪዎች የሰራተኞች መደራጀት ጥቅም በመገንዘብ ሰራተኞችን እየደገፉ ማደራጀት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ፌዴሬሽኑም የአሰሪዎችን መብት ከማስጠበቅ በተጨማሪ የሰራተኞች አደረጃጀቶች ማበረታታትና መብታቸው እንዲጠበቅ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አብዱልፋታህ አብዱላሂ እንዳሉት መንግስት የተደራጀ ኃይል ለምርትና ምርታማነት ወሳኝ በመሆኑ ሰራተኞች መብታቸውን የሚያስከቡሩበትና የሚደራጁበት አሰራር ተዘርግቷል።

መንግስት በተዘረጉ አሰራሮች የሚነሱ ችግሮችን ሲፈታ ቆይቷል አሁን በፌደሬሽኑ የተነሱ ጥያቄዎችንም ህግን መሰረት አድርጎ ምላሽ ያገኛሉ ብለዋል አቶ አብዱልፋታህ።

በውይይቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በኢትዮጵያ የአለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ጆርጅ ኦክቶ ኢትዮጵያ  የሰራተኞችን መብት በማስከበር ለአፍሪካም ተምሳሌት መሆን ትችላለች ብለዋል።

ሰራተኞች የአገር ዕድገት የጀርባ አጥንት ናቸው ያሉት ጆርጅ ኦክቶ በሥራ አካባቢ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በወጡ ህጎችና በሰለጠነ መንገድ መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እያደገ እየመጣ በመሆኑ ምቹ የሥራ ሁኔታ እና የሰራተኞች መብት እያስጠበቁ መሄድ ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

ሚያዝያ 23/2009 የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሀሰን ኦማር አል በሽር በደቡብ ሱዳን ያለውን የማያቋርጥ ግጭት ለመፍታት እንደተዘጋጁ ሲጂቲን ዘገበ፡፡ 

እንደ ዘገባው ደቡብ ሱዳን ከሶስት አመታት በላይ በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ ያለች ሲሆን በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ሞተዋል፣ ሚሊዮኖችም ወደ ጎረቤት ሃገራት ተሰድደዋል ፡፡

አል በሽር እንዳሉት በአንድ ወቅት ህዝባቸው ለነበረው  የደቡብ ሱዳን ህዝብ ችግሮቻቸውን ለመፍታት መንግስታቸው ትኩረት አድርጎ ይሰራል ፡፡

“ስለደቡብ ሱዳን ህዝቦች እንጨነቃለን ምክንያቱም አንድ ሃገር በነበርንበት ጊዜ ዜጎቻችን ነበሩ፤ በሰላማዊ መንገድ ለመለያየት የበቃነውም  የሁለቱ ሃገራት መንግስታትና ፖለቲካ ፓርቲዎች በደረስነው ስምምነት ነው፡፡ በመሆኑም ጦርነቱና ረሃቡ እንዲቆም  ጥረት እናደርጋለን” ሲሉም በካርቱም ተደምጠዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት በደቡብ ሱዳን ያሉ አንዳንድ ፓርቲዎች በሃገሪቱ ያለውን አውዳሚ ግጭት እንዲያስቆሙላቸው የሱዳን መንግስት አስተዳደርን  ይጠይቃሉ፡፡

“ከተለያዩ ወገኖች በሚደርሰን የሚስጥር መልእክት በደቡብ ሱዳን ያለውን ግጭት ለማስቆም ከየትኛውም አካል በበለጠ የእኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ እየጠየቁን ነው” ብለዋል አልበሽር፡፡  ስለዚህም የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የደቡብ ሱዳን መሪዎች ጦርነቱን አቁመው ወደ ሃገሪቱ ግንባታ እንዲያተኩሩ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

Published in ፖለቲካ

ባህር ዳር ሚያዚያ 23/2009 አሰሪዎችና ሰራተኞች ተቀራርበው እንዲሰሩና የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

 “የኢንዱስትሪ ሰላምና ምርታማነት በተደራጀ ሰራተኛ ይረጋገጣል” በሚል በሪ ቃል ዓለም አቀፍ የላብ አደሮች ቀን /ሜይ ደይ/ ዛሬ በክልል ደረጃ በባህር ዳር ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡

 የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መኮነን ታከለ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ሰራተኛው መብትና ጥቅሙን ለማስከበር ተደራጅቶ መንቀሳቀስ አለበት።

 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱም በክልሉ በ282 መሰረታዊ ማህበራት ለተደራጁ ከ50 ሺህ በላይ ሰራተኞች በግጭት አፈታት፤ በህብረት ድርድርና ሌሎች ርዕሶች ላይ ያተኮረ ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

 ይህም የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍንና የሚከሰቱ ችግሮች በሁለትዮሽ እንዲፈቱ፤ ሳይፈቱ ሲቀሩ በአካል በመገኘት ችግሮችን በመቀራረብ እንዲፈቱ በማድረግ ለሰራተኛው መብትና ጥቅም መረጋገጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

 የሰራተኞች መደራጀት ህገ-መንግስታዊ መብት መሆኑን አሰሪዎች ተረድተው መብታቸው ሳይሸራርፍ እንዲተገበር ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

 “መደራጀት ሰራተኛው መብትና ግዴታውን አውቆ ውጤት ለማምጣት ተግቶ እንዲሰራ ያስችለዋል” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል የአሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ወርቁ ታምራት ናቸው።

 ይህም አሰሪዎችና ሰራተኞች በመካከላቸው የሰመረ፤ በውጤት የታጀበና ቀጣይነት ያለው ጤናማ ግንኙነት እንዲኖራቸው እንደሚያስችላቸውም ገልጸዋል።

 የአማራ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሞላ ጀምበሬ በበኩላቸው ሰራተኞች ማህበር መስርተው የህብረት ድርድር እንዲያደርጉ አሰሪዎች  ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለባቸው።

 ሰራተኛው ህገ-መንግስቱ የሰጠውን መብት ተጠቅሞ በማህበር እንዲደራጅ፤ የሙያ ደህንነትና ጤንነቱ እንዲጠበቅ፤ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲረጋገጥና ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ቢሮው በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

 “መደራጀታችን ጥቅማችንን አስከብረን የተጣለብንን ግዴታ እንድንወጣ አስችሎናል” ያሉት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ከብር ሸለቆ እርሻ ልማት የሰራተኛ ማህበሩ ተወካይ ወይዘሮ አለሰው አገኘሁ ናቸው።

 ከአዊ ዞን አየሁ እርሻ ልማት መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ወርቁ አልማው በበኩላቸው ሰራተኛው መደራጀቱ ከእርሻ ጀምሮ እስከ ምርት አሰባሰብ ጠንክሮ በመስራት በሚያስመዘግበው ውጤት የጋራ ተጠቃሚ እንዲሆን እያስቻለው ነው።

 በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ128ኛ ጊዜ፤ በሀገሪቱ ደግሞ ለ42ኛ ጊዜ በዓሉ ዛሬ ሲከበር ከ400 ያላነሱ የአሰሪና ሰራተኛ ተወካዮች፤ ሲቪክ ማህበራትና ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

Published in ማህበራዊ

 አዲስ አበባ ሚያዚያ 23/2009 ወንጀለኛን አሳዶ ለፍርድ ማቅረብ አለመቻልና የውሳኔ መዘግየት በፍትህ ስርዓቱ ላይ በተደጋጋሚ የሚታዩና አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች መሆናቸውን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

 የፍትህ አካላቱ በበኩላቸው ''እነዚህ ችግሮች የሚፈቱት በህብረተሰቡ ተሳትፎ ነው'' ባይ ናቸው።

 በኢትዮጵያ ለ7ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፍትህ ቀን በማስመልከት በከፍለ ከተማው ዛሬ በተካሄደ ውይይት ነዋሪዎች እንደገለጹት ወንጀለኞችን እጅ ከፍንጅ ይዘን ለሚመለከተው የፍትህ አካል ስናስረክብ መረጃ አልተገኘም በማለት ይለቀቃሉ።

 በተመሰከረባቸውም ሰዎች ላይም ፈጥኖ ብያኔም ሆነ ውሳኔ አለመስጠት ችግር በፍትህ በኩል እንደሚስተዋል ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

 ''በችሎት የሚሰጠውም ቅጣት ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ወንጀለኞች ከጥፋታቸው እንዲታረሙ የማያደርግ ነው '' ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

 በክፍለ ከተማው የወረዳ ዘጠኝ ነዋሪ አቶ ኤልያስ ገድሉ በሰጡት አስተያየት “መስቀል አደባባይ አንዲት ሴት የ3 ወር ልጇን ወደ መኪና ወርውራ ህፃኑ ጉዳት ደርሶበት የፖሊስ ድጋፍ ብንጠይቅ ምንም አልተደረገልንም። በዚህ ምክንያት የህፃኑ ህይወት አልፏል ብለዋል።

 ለየፓሊስ ጣቢያው የተመደቡ መኪናዎችን ለወንጀል መከላከል ስራ ከመዋል ይልቅ ለኃላፊዎችና ሰራተኞች መጓጓዣነት ይገለገሉባቸዋል ሲሉም ወቅሰዋል።

 የፍርድ ቤት ሬጅስትራሮች በር ላይ ካሉ በክፍለ ከተማው የተደራጁ ራፖር ፀሃፊዎች ጋር የጥቅም ግንኙነት አላቸው የሚሉት ነዋሪዎቹ እነዚህ ያልፃፉት ማመልከቻ የህግ ባለሙያ እንኳን ቢያረቀው ተቀባይነት እንደማያገኝ ተናግረዋል።

 ደሃው ህብረተሰብ ለአንድ ገፅ ማመልከቻ 200 እና 300 ብር እየተጠየቀ መሆኑን የተናገሩት ተሳታፊዎች በጥልቅ ተሃድሶው ያልታረሙ ወገኖች አሁንም በፍትህ አካላት ውስጥ መኖራቸውን ጠቁመዋል።

 የወረዳ 11 ነዋሪ ወይዘሮ ሳባ መሃሪ በበኩላቸው የሞባይል መሸጫ ሱቃቸው ሊዘርፉ የነበሩ ሌቦችን ከሁለት ሌላ ሰዎች ጋር እጅ ከፍንጅ በመያዝ ለህግ ማቅረባቸውን ጠቁመው የወንጀለኞች ክስ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ተላልፎ እስካሁን መፍትሄ አለማግኘቱን፣ በኢግዚቢት የተያዘው ንብረት አለመመለሱን ተናግረዋል።

 የተለየ አቋም ያንጸባረቁ ነዋሪዎች በበኩላቸው የፍትህ ስርዓቱን ለማስተካከል ህብረተሰቡ ለሕግ የበላይነት መሰለፍ አለበት ብለዋል።

 ''የጫትና የሺሻ ቤት የሚያከራየው ሕዝብ እየተባለ የሚጠራው የሕብረተሰብ ክፍል ራሱነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ለፖሊስ መረጃ ለፍርድ ቤት ምስክር ስጥ ሲባል እምቢ የሚለውም ራሱ ህዝቡ በመሆኑ ራሳችንን ብናይ'' ብለዋል።

 በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ሽመልስ ሽፈራው የፍትህ ስርዓቱ አምጪም ተቀባይም ህብረተሰቡ መሆኑን ጠቁመዋል።

 ህብረተሰቡ ፍትህን ለማረጋገጥ ትልቁን ድርሻ ካልወሰደ ችግሩን መፍታት አለመቻሉንም ከህብረተሰቡ የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት በማድረግ ምላሽ ሰጥተዋል።

 በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቂርቆስ ምድብ ዳኞች አስተባባሪ አቶ አርአያ በየነ በበኩላቸው የተሰጠው ሃሳብ ትክክል መሆኑን ገልፀው ለፍርዱ መጓተት ከዳኞች በተጨማሪ የባለጉዳዩ እጅ እንዳለበት ተናግረዋል።

 በፍርድ ሂደት ጣልቃ መግባት፣ እገዳ መጠየቅና ምስክር በተባለው ቀን አለማቅረብ በሶስት እና አራት ቀጠሮ ውሳኔ የሚያገኙ መዝገቦችን ከ20 በላይ ቀጠሮ እንዲወስዱ የሚያደርግ መሆኑን አቶ አርአያ ተናግረዋል።

 ባለሙያዎችና አመራሮች ለሚያደርሱት በደል ተጠያቂነት ለማስፈን ለዳኞችና ለአቃብያነ ህግ የስነምግባርና መመሪያ ተዘጋጅቶ እየተሰራበት መሆኑን አስረድተዋል።

 ባለፉት ዘጠኝ ወራት በቀረበባቸው 38 አቤቱታዎች መሰረት 1 የከፍተኛ 3 የመጀመሪያ ደረጃ ዳኞች መባረራቸውን የቀረበው ሪፖርት አትቷል።

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ሚያዚያ 23/2009 በሚቀጥለው ዓመት የመላው አፍሪካና ኢትዮጵያ  ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫልን በጥምረት ለማስተናገድ የሚያስችለውን ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

 ዩኒቨርስቲው በፌስቲቫሉ ዝግጅት ለሚሳተፉ 1 ሺህ በጎ ፈቃደኛ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣የመቀሌ ከተማ ወጣቶችና የስፖርት ኮሚቴ አባላት የሁለት ቀን ስልጠና ሰጥቷል።

 የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ዲንና የመላው ኢትዮጰያ ዩኒቨርስቲዎች ስፖርት ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር  ከሰተ ለገሰ ለኢዜአ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው በመጭው ዓመት ለሚያስተናግደው አህጉራዊና ሀገራዊ የዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል እየተዘጋጀ ነው።

 በዩኒቨርሲቲው ዋና ጊቢና በስሩ በሚገኙ አራት ካምፓሶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ኳስ ስታዲሞች ግንባታ በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

 የእጅ ኳስ ፣የቅርጫት ኳስና የዋና ስፖርት ውድድሮችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የስፖርት ዓይነቶችን የማስተናገድ ዓቅም ያላቸው አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የውስጥና የውጭ ሜዳዎችና የዘመናዊ ህንጻዎች ግንባታም በአብዛኛው መጠናቀቁን ተናግረዋል።

 በዩኒቨርሲቲው  ምክትል ፕሬዝዳንቶች የሚመራና የተለያዩ ተቋማትን በአባልነት ያቀፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ ለዝግጅቱ ድምቀት የሚያገለግሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልፀዋል ።

 ዩኒቨርሲቲው  በዓለም አቀፍ ደረጃ የዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል ዝግጅት ላይ በጎ ፈቀደኛ ወጣቶችን በማሳተፍ መልካም ተሞክሮ ካለው አንድ የኮሪያ የበጎ ፈቃደኛ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በጋራ ለመስራት መስማማቱንም ተናግረዋል።

 የመላው ኢትዮጰያ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫልን ለመጀመሪያ ጊዜ አስተናግዶ በስኬት ማጠናቀቁን የተናገሩት ደግሞ የመላው ኢትዮጰያ ዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አባይ በላይነህ ናቸው።

 "የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ከራሱ አልፎ የኢትዮጰያን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ነው"ያሉት አቶ አባይ፣ለመላው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል እያደረገ ያለው ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

 ዩኒቨርሲቲው በመጪው ዓመት ከሚያዘጋጀው የመላው ኢትዮጰያ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል ባለፈ የመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫልን የሚያዘጋጀው በተደረገው የምረጡኝ ውድድር በማሸነፉ ነው።

Published in ስፖርት

ሚያዝያ 23/2009 በአገሪቱ በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች 15 ዞኖች የተከሰተውን የተምች ወረርሽኝ ለመከላከል የክትትልና የድጋፍ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በሚኒስቴሩ የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ሰላቶ ለኢዜአ እንደገለጹት የተባዩን መከሰት ተከትሎ ባለድርሻ አካላትን የማስተባበር፣ ግንዛቤ የማስጨበጥና አስፈላጊውን ግብዓት የማቅረብ ስራ እየተሰራ ነው፡፡

በተወሰደው እርምጃም ተገቢ የመከላከል እንቅስቃሴ በተደረገባቸው አካባቢዎች ሁሉ ጥሩ ውጤት መመዝገቡን በባለሙያዎችና አርሶ አደሮች እየተገለጸ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

መጀመሪያ በተከሰተባቸውና ቀድሞ መከላከል በተደረገባቸው ማሳዎች የበቆሎ ሰብል እንደገና አቆጥቁጦና አዘርዝሮ ራስ አውጥቶና በደንብ ሸጉጦ መታየቱን በመስክ ሱፐርቪዢንና ክትትል ድጋፍ ቡድን ለመመልከት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የአዲሱ መጤ የአሜሪካ ተምች ተባይ አሰሳና መከላከል በሃገራችን

አዲሱ መጤ የአሜሪካ ተምች (Fall Army worm ) ተብሎ የሚጠራ አደገኛ ተዛማችና ወረርሽኝ ነፍሳት ተባይ ነው፡፡

በደቡብ ብ/ብ/ህዝቦችና በኦሮሚያ ክልሎች ተከስቶ የአሰሳ፣ መከላከል፣ ክትትል ድጋፍና የግብዓት አቅርቦት ሥራ እየተካሄደ ነው፡፡

የተባዩን መከሰት ተከትሎ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር፣ ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ ለመከላከል አስፈላጊውን ግብዓት የማቅረብ፣ የአሰሳ፣ መከላከልና ክትትል ድጋፍ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ በእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴርየእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር ያደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡

የአሜሪካ መጤ ተምች ተባይ (Fall army worm) አመጣጥ

አዲሱ መጤ የአሜሪካ ተምች (Fall Army worm ) ተብሎ የሚጠራ አደገኛ ተዛማችና ወረርሽኝ ነፍሳት ተባይ ነው፡፡

 የተባዩ ክስተት ሁኔታ

የአሜሪካ መጤ ተምች / ፎል አርሚ ዎርም/ Fall army worm (Spodoptera frugiperda) መነሻው ከመካከለኛው አሜሪካ ሲሆን በለፒዶፕተራ ምድብ በኖክቱዴ ቤተሰብ ውስጥ የሚመደብ የሳትራት ትል ነው፡፡

ወደ አህጉራችን እንዴት እንደገባ እስከ አሁን ድረስ ግልፅ ባይሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 2016 በናይጄሪያ ሪፖርት መደረጉ ታውቋል፡፡

ነፍሳቱ በመቀጠልም ከምዕራብ ወደ መካከለኛውና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገሮች በመስፋፋት እ.ኤ.አ. በህዳር 2016 በደቡብ የአፍሪካ ሀገራት በወረርሽኝ ደረጃ ተከሰተ፡፡

ቀጥሎም የነፋስን አቅጣጫ በመከተል የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በመውረር ታንዛኒያ፣ ኬኒያና ኡጋንዳ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ በተለይም በቆሎን በተመሳሳይ ወቅት በሚያለሙ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ስጋቱ ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱ  ነው ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ የሚያመላክተው፡፡

 

በኢትዮጵያ የተምች መከሰት ሁኔታ

በሀገራችን ነፍሳት ተባዩ መጀመሪያ የታየው በየካቲት 25/2009 ዓ.ም በደቡብ ክልል ሸካ ዞን የኪ ወረዳ ሾሻ ቀበሌ በመስኖ የተዘራ በቆሎ ሰብል ላይ 1100 ሜትር የባህር ከፍታ ባለበት አካባቢ ነው፡፡

ቀጥሎም በሼ/ቤንች ወረዳ ኩካ ቀበሌ በቅድመ በልግ በተዘራ በቆሎ ላይ በመጋቢት 04/2009 ዓ.ም በ2030 ሜትር የባህር ከፍታ ላይ በድጋሚ መገኘቱ ተረጋግጧል፡፡

 

ተባዩን ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራት

በአሁኑ ወቅት ተባዩ  በደቡብ ክልል በ12 ዞኖች (ሸካ፣ ቤንች ማጂ፣ከፋ ፣ ጋሞጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ከምባታ ጠምባሮ፣ ዳውሮ፣ ስልጢ፣ ሀዲያ፣ ሰገንና ሲዳማ ዞኖች)ና 2 ልዩ ወረዳዎችን (ኮንታና ባስኬቶ) ጨምሮ በአጠቃላይ በ71 ወረዳዎች በ1 ሺህ 53 ቀበሌዎች ተከስቷል፡፡

በዚህም በበቆሎ ሰብል ከተሸፈነው  171 ሽህ 446 ሄክታር ውስጥ በ18 ሽህ 446 ሄክታር የበቆሎ ማሳ ላይ ተከስቶ 11ሽህ 71 ሄክታር በፀረ-ተባይና 3 ሽህ 574 ሄክታር በባህላዊ መንገድ በድምሩ በ14 ሽህ 645 ሄክታር ላይ የመከላከል ሥራ ተሰርቷል፡፡

የመከላከል ሥራው በቆሎ ከማሳ እስከሚታጨድ ወይም ተባዩ ጨርሶ እስከሚጠፋ እንደሚቀጥል  የገለጹት በሚኒስቴሩ የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ሰላቶ ለመከላከል ስራው 18 ሽህ 585 ሊትር ፀረ-ተባይ ኬሚካል ጥቅም ላይ ውሏል፡፡

በመከላከሉ ተግባር 45 ሽህ 594 አርሶ አደሮች የበቆሎ ሰብላቸውን ከተባዩ ጥቃት ለመከላከል በሚደረገው ተግባር ተሳትፈዋል ብለዋል፡፡

እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በሶስት ዞኖች (ጅማ፣ ቡኖ በደሌና ኢሊአባቦራ ) በ28 ወረዳዎችና በ259 ቀበሌዎች በበቆሎ ከተሸፈነው 34 ሽህ 162 ሄክታር ውስጥ  በ5 ሽህ 214 ሄክታር ላይ ተባዩ ተከስቶ 1 ሽህ 724 ሄክታር በፀረ-ተባይ መከላከል ተደርጓል፡፡ ለዚህም 2 ሺህ 767 ሊትር ፀረ-ተባይ ኬሚካል ጥቅም ላይ መዋሉን ነው ያስታወቁት፡፡

የአሰሳ ሥራ በሁለቱም ክልሎች ተባዩ በተከሰተባቸው ወረዳዎችና ቀበሌዎች በተቋቋመ የቴክኒክ ኮሚቴ፣ በቀበሌ ሙያተኞችና  በአርሶ አደሩ በቡድን እየተካሄደ ሲሆን  የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የባለሙያዎች ቡድንም በክልሎቹ የማስተባበር፣ የቴክኒክ እገዛና ድጋፍ እየሰጡ  እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

ነፍሳት ተባዩ አዲስ በመሆኑ የአሜሪካ ተምችን ከሌሎች ነፍሳት ተባዮች ጋር ያለውን ተመሳሳይነትና ልዩነት የልማት ሠራተኞቹና በየደረጃው የሚገኙ ባለሙያዎች ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግና የልየታና የመከላከሉ ሥራ በአግባቡ መከናወን እንዲያስችል የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ይገኛሉ ተብሏል፡፡

ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብዓቶች የፀረ-ተባይ ኬሚካሎች፣ መርጫ መሳሪያዎች፣ መከላከያ ትጥቅ ድጋፍ ተደርጓል፡፡

እስካሁን ለደቡብ ክልል 26 ሽህ 600 ሊትር ፀረ-ተባይና  ለኦሮሚያ ክልል  10ሽህ ሊትር ባጠቃላይ 36ሽህ600 ሊትር ተባዩ ወደ ተከሰተባቸው ወረዳዎች እንዲደርስ በማድረግ የመከላከሉ ሥራ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም በባህላዊ መንገድ የተባዩ ቁጥር ባልተስፋፋባቸው ማሳዎች ተባዩን ከበቆሎ አንገት ለቅሞ በመግደል ጭምር ለመከላከል እንዲችሉ ለአርሶ አደሮች ምክር በመስጠት የወደፊት አቅጣጫ  መቀመጡን አቶ ዘብዲዎስ አስገንዝበዋል፡፡

 

የመከላከል ውጤት

እስከ አሁን ሶስት  ፀረ-ተባይ ዓይነቶች (ማላታዮን፣ ዲያዚኖንና ክሎሮፓይርፎስ) ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን በሁሉም ርጭቱ በተካሄደባቸው ወረዳዎች ተገቢ የሆነ የፀረ-ተባይ መጠን በተገቢ የውሃ መጠን ተበጥብጦ በትክክለኛ ሰዓት ጧትና ማታ በተገቢው የርምጃ መጠን የተረጨባቸው አካባቢዎች ሁሉ ጥሩ ውጤት መመዝገቡን ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች መግለጻቸው ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪ የመስክ ሱፐርቪዢንና ክትትል ድጋፍ ቡድን መጀመሪያ በተከሰተባቸውና ቀድሞ መከላከል በተደረገባቸው ማሳዎች የበቆሎ ሰብል እንደገና አቆጥቁጦና አዘርዝሮ ራስ አውጥቶና በደንብ ሸጉጦ ለመመልከት ችሏል፡፡

የመከላከል ሥራው በደንብ ተይዞ በአርሶ አደሩ፣ በባለሙያውና በአመራሩ የተሻለ ትኩረት ተሰጥቶት በቀጣይ ወራት የሚመራ ከሆነ በምርት ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጉዳት መጠን  መቀነስ ይቻላል ነው የተባለው፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 23/2009 የአርጆ ደዴሳ ስኳር ፋብሪካ የመስኖ ልማት ግድብ ግንባታ በወቅቱ ተጠናቆ ወደ ስራ ባለመግባቱ ስኳር ማምረት ማቆሙን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ  አስታወቁ።

ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ካባ መርጋ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ ፋብሪካው በያዝነው ዓመት ውስጥ በሸንኮራ አገዳ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ለተከታታይ አራት ወራት የስኳር ምርት ሙሉ በሙሉ ማምረት አቁሟል። ከ2007ዓ.ም ጀምሮ ፋብሪካው ስኳር የማምረት ተግባሩን በከፊል ጀምሮ እንደነበር ጠቁመው፤ ሆኖም ዘንድሮ በአገዳ አቅርቦት እጥረት ሳቢያ ለሁለት ወራት ብቻ አምርቶ ሥራ ማቆሙን ተናግረዋል።

በነዚህ ወራት ያመረተው ስኳር 118 ሺ 123  ኩንታል እንደነበር ገልጸዋል።

የመስኖ ልማት ግድብ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት እሰከሚሰጥ ድረስ በዝናብ የሸንኮራ አገዳ ለማምረት ቢሞከርም ከመስኖው ጋር ሲነጻጸር ሩብ ያክል መሆኑን ተናግረዋል። ሸንኮራ አገዳ በመስኖ ሲመረት በሄክታር እስከ ሁለት መቶ ቶን ማግኘት እንደሚቻል አቶ ካባ ጠቁመው፤ "በአሁኑ ወቅት እየተገኘ ያለው በሄክታር እስከ ስድሳ ቶን አገዳ ብቻ ነው" ብለዋል።

 የግድቡ ግንባታ በመዘግየቱ ፋብሪካው የመስኖ ፓምፖችን በመጠቀም ውሃ ከወንዝ በመጥለፍ የተወሰኑ የአገዳ ማሳዎችን ለማጠጣትና ምርታማነቱን ለማሳደግ ሙከራ ማድረጉን አመልክተዋል።

 ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል በቂ ባለመሆኑ ምርታማነቱን ለማስቀጠል ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱ አስረድተዋል።

 ለፋብሪካው አገልግሎት የሚውል ለኤሌትሪክ ኃይል አገልግሎት የማከፋፈያ ንዑስ ጣቢያ እንዲያቋቁም ጥያቄ ማቅረቡን ጠቁመው፤ እስከ አሁን ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን ገልፀዋል።

 በተጓዳኝ የግድቡ ግንባታ ስራም መፋጠን እንዳለበትም አሳስበዋል።

 በኦሮሚያ የውሃ ሥራዎች ዲዛይንና ቁጥጥር ድርጅት የአርጆ ደዴሳ ግድብና ተጓዳኝ ሥራዎች ኃላፊ ኢንጂነር መርጊ ሚሊኬ እንደተናገሩት፤ ግንባታው በበላይነት የሚሠራው የኦሮሚያ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ነው።

 የግድቡ ስራ በ2003 ዓ.ም ተጀምሮ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙን አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት በ48 ነጥብ 3 በመቶ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 ሥራው ከመጀመሩ በፊት እንደ አሸዋ፣ ድንጋይ፣ ቀይ አፈር እና መሰል ግብዓቶች አቅርቦት በኩል በቂ ዝግጅት አለመደረጉና የዲዛይን ለውጥ ማስፈለጉ፣ የኮንትራክተሮች ዘግይቶ ወደ ሥራ መግባት እንዲሁም የመንገድ መሠረተ ልማት ያለመኖር ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

 "ግብዓቶቹ በቅርብ ይገኛሉ ተብሎ ታስቦ ነበር" ያሉት ኃላፊው ወደ ተግባር ሲገባ ግን እስከ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ለመጓዝ እንደተገደዱ ተናግረዋል።

 ከዚህ በተጨማሪም የግድቡ ውሃ በሚጠራቀምበት ቦታ ላይ ያሉ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ካሳ ተከፍሎዋቸው በወቅቱ አለመነሳታቸው በአካባቢው ያለውን  የግንባታ ግብዓቶች ለመጠቀም አለመቻሉን ሌላው ችግር መሆኑንን ገልፀዋል።

 ከዚህ በኋላ መሰረታዊ ስራ እና የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ በመጠናቀቁ እንዲሁም የስራ ተቋራጮች ቁርጠኝነት በመኖሩ ቀሪውን የግድብ ግንባታ "በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ተጨማሪ ጊዜ ይጠይቃል" ሲሉ ኢንጂነር መርጊ ተናግረዋል።

 ግድቡ 50 ሜትር ከፍታ እና 502 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ በዓመት ሁለት ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ በማጠራቀም እስከ ሰማኒያ ሺ ሄክታር ማልማት ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

 ከዚህ ውስጥ ሃምሳ ሺ ሄክታር ለፋብሪካው አገዳ ልማት እና ቀሪው ሠላሳ ሺ ሄክታር በአዋሳኝ በሚገኙ የኢሊ አባቦራና የጅማ ዞን አርሶ አደሮች የመስኖ አገልግሎት እንደሚሠጥ ታውቋል።

 የመስኖ ልማት ግድቡን የሚያስገነባው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ሲሆን፤ የመስኖ ልማት ግድቡ በሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በጀት የሚገነባ መሆኑ ታውቋል።

Published in ኢኮኖሚ

ሰመራ ሚያዚያ 23/2009 ለተቋሙ የሚቀርቡ  አቤቱታዎች ቁጥር መጨመር ህብረተሰቡ መብትና ጥቅሙን የማስጠበቅ ባህሉ እየጎለበተ ስለመምጣቱ አመላካች መሆኑን የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ።

ተቋሙ 8ኛ ቅንርጫፍ ጽህፈት ቤቱን ሰሞኑን በሰመራ ከተማ ከፍቷል።

የተቋሙ የምርምራ ዳይሬክተር አቶ ደነቀ ሻንቆ በዚሁ ጊዜ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት ተቋሙ በ1997 ዓ.ም የቀረበለት 66 አቤቱታ ቁጥር በ2009 ዓ.ም ዘጠኝ ወራት ብቻ ወደ 1ሺህ 200 አድጓል ።

“ወደ ተቋሙ እየመጡ ካሉ አቤቱታዎች መካከል የመሬትና ተያያዥ የሆኑ የይዞታ ጉዳዮች፣ ከአስተዳደራዊ በደልና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያየዙ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው “ ብለዋል ።

 ከእነዚሁ አቤቱታዎች ውስጥ 300 ዎቹን መርምሮ እልባት ለማሰጠት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል ።

ህብረተሰቡ የሚያቀርባቸው አቤቱታዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ መብትና ጥቅሙን የማስጠበቅ ባህሉ እየጎለበተ ስለመምጣቱ አመላካች መሆኑን ጠቁመዋል ።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ተቋሙ የሚሰጠውን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግና ለሚቀርቡለት አቤቱታዎች ፈጣን ምላሽ ለማሰጠት በሰጠው ትኩረት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱን እያስፋፋ ነው ።

በሰመራ የከፈተው ስምንተኛ ቅርጫፉም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

ተቋሙ ከመልካም አስተዳርና ከሌሎች ጉዳዮች  ጋር ተያይዞ ከህብረተሰቡ ለሚቀርቡለት አቤቱታዎች አፋጣኝ ምላሽ ለማሰጠት በሚያደርገው ጥረት የመንግስት አስፈፃሚ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በጋራ እንዲሰሩ ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል ።

የአፋር ክልል ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡስማን መሃመድ በበኩላቸው ህብረተሳቡ በጥልቅ ተሀድሶ መድረኮች ላነሳቸው የመልካም አስተዳር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 ከዚህ ባለፈ ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው የመብት ጥያቄዎች መፍትሄ ለመስጠት  ከተቋሙ ጋር በጋራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

 

Published in ፖለቲካ

መቐለ ሚያዝያ 23/2009 በሚቀጥለው ዓመት የመላው አፍሪካና ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫልን በጥምረት ለማስተናገድ የሚያስችለውን ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ዩኒቨርስቲው በፌስቲቫሉ ዝግጅት ለሚሳተፉ 1 ሺህ በጎ ፈቃደኛ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣የመቀሌ ከተማ ወጣቶችና የስፖርት ኮሚቴ አባላት የሁለት ቀን ስልጠና ሰጥቷል።

የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ዲንና የመላው ኢትዮጰያ ዩኒቨርስቲዎች ስፖርት ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር  ከሰተ ለገሰ ለኢዜአ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው በመጭው ዓመት ለሚያስተናግደው አህጉራዊና ሀገራዊ የዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል እየተዘጋጀ ነው።

በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢና በስሩ በሚገኙ አራት ካምፓሶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ኳስ ስታዲሞች ግንባታ በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

የእጅ ኳስ ፣የቅርጫት ኳስና የዋና ስፖርት ውድድሮችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የስፖርት ዓይነቶችን የማስተናገድ ዓቅም ያላቸው አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የውስጥና የውጭ ሜዳዎችና የዘመናዊ ህንጻዎች ግንባታም በአብዛኛው መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው  ምክትል ፕሬዝዳንቶች የሚመራና የተለያዩ ተቋማትን በአባልነት ያቀፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ ለዝግጅቱ ድምቀት የሚያገለግሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲው በዓለም አቀፍ ደረጃ የዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል ዝግጅት ላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሳተፍ መልካም ተሞክሮ ካለው አንድ የኮሪያ የበጎ ፈቃደኛ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በጋራ ለመስራት መስማማቱንም ተናግረዋል።

የመላው ኢትዮጰያ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫልን ለመጀመሪያ ጊዜ አስተናግዶ በስኬት ማጠናቀቁን የተናገሩት ደግሞ የመላው ኢትዮጰያ ዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አባይ በላይነህ ናቸው።

"የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ከራሱ አልፎ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ነው"ያሉት አቶ አባይ፣ ለመላው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል እያደረገ ያለው ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በመጪው ዓመት ከሚያዘጋጀው የመላው ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል ባለፈ የመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ፌስቲቫልን የሚያዘጋጀው በተደረገው የምረጡኝ ውድድር በማሸነፉ ነው።

Published in ስፖርት
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን