አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 09 April 2017

ደብረብርሃን ሚያዝያ 1/2009 ለኢንዱስትሪ መንደር ማሳለጫና ለአማራጭ መንገዶች አገልግሎት መስጫ የሚሆኑ ሁለት ድልድዮች ግንባታ በ31 ሚሊዮን ብር ሊያከናውን መሆኑን የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ስፋቸው ደስታ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የድልድዮቹን ግንባታ ለማስጀመር ከአሸናፊ ተቋራጮች ጋር ውል  ተደርጓል።

በበሬሳ ወንዝ ላይ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት የሰጠውን አንድ ድልድይ ወደ ሁለት የማሳደግ ሥራ የሚሰራ ሲሆን ይህም በከተማዋ በማደግ ላይ ያለውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ይበልጥ ለማቀላጠፍ ያስችላል ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ በፌደራል መንግስት ለሚገነባው የኢንዱስትሪ መንደር መሰረተ ልማትን ቀድሞ ለማሟላት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የግንባታ ሥራው በቅርቡ የሚጀመረው ይህ ድልድይ 50 ሜትር ርዝመትና 20 ሜትር ስፋት ያለው መሆኑን ተመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት ለግንባታው አማካሪ መሀንዲሶች መቀጠራቸውን የገለጹት አቶ ስፋቸው፣ ድልድዩ ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር በሁለቱም አቅጣጫ በአንድ ጊዜ አራት አራት ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኪስ ኮንስትራክሽን ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ኃይለልዑል ጌትየ እንዳሉት፣ ግንባታውን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ውል ተገብቶ በአሁኑ ወቅት የሳይት ርክክብ ተፈጽሟል።

ሁለተኛው ድልድይ የሚገነባው በከተማው ቀበሌ 05 እና ቀበሌ 04ን ከፍሎ በሚገኘው ወንዝ ላይ ሲሆን ይህም በአካባቢው የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ የቀበሌ 07 ዋና አስተዳዳሪ መቶ አለቃ ጭንቅል ጉችማ እንደገለጹት፣ የድልድዩ ግንባታ ሕብረተሰቡ ለዘመናት ሲያነሳው የነበረውን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ያስችላል።

በተለይ ቀበሌያቸው የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች በመምጣቷ ባለሀብቱም ሆነ ነዋሪው በአማራጭ መንገዶች ለመጠቀም እንደሚያስችለው ተናግረዋል።

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ በጋሻው ኃይሌ በበኩላቸው፣ የከተማዋን ዕድገት የሚመጥኑ ዘመናዊ ድልድዮች መሰራታቸው የሕብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድገው አመልክተዋል።

የድልድዮቹ ግንባታ ሲጀምር በአካባቢው ለሚገኙ በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ መቀሌ ለሚዘልቀው መንገድ በደብረ ብርሃን ከተማ የነበረው ድልድይ አንድ ብቻ በመሆኑ ብዙ ጊዜ የትራፊክ መጨናነቀ ይከሰት እንደነበረና የድልድዮቹ መገንባት ችግሩን ይፈተዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ ሚያዚያ 1/2009 በማዕድን ዘርፍ የሚታየውን ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለመግታት መገናኛ ብዙሃንና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን የማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከሚዲያ ተቋማት ጋር በግንዛቤ ፈጠራ ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያችስለውን ምክክር በቢሾፍቱ ከተማ አካሒዷል።

በመድረኩ ላይ በሚኒስቴሩ የማዕድን ኢንዱስትሪ ግልጸኝነት ኢንሼቲቭ ብሔራዊ ኮሚቴ አባል አቶ አብረሃም ታደሰ እንደገለፁት በማዕድን ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ዙሪያ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የዩኒቨርሲቲዎችና የሚዲያ ተቋማት ድርሻ የላቀ ነው።

ሀብቱ ለህዝብና ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ህጎችን ከመፈተሽ ጀምሮ በአሰራሮችና መመሪያዎች ዙሪያ ህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው አንደሚገባ አመልክተዋል።

በባህላዊ መንገድ  ማዕድን የሚያለሙ ፣በኩባንያዎች፣በመንግስትና በህብረተሰቡ መካከል በሚኖረው አጠቃቀምና አስተዳደር ዙሪያም የጋራ መግባባት እንዲኖር መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የጂማ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬዲዮ አስተባባሪ ወይዘሮ ፍትህ ዓለሙ እንደገለፁት የሬዲዮ ጣቢያው ህብረተሰቡ በአካባቢው ልማትና ዕድገት ላይ ግልፀኝነት እንዲኖረው ይሰራል ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በማዕድን ግልጸኝነት ኢንሼቲቭ ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑ በዘርፉ የሚታየውን ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት በጋራ ለመታገል እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

አስተባባሪዋ አያይዘውም አሰራሩ "በዘርፉ በአስተዳድርና የህግ ጉዳዮች ዙሪያ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችለን ነው" ብለዋል።

ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ዘለቀ ተሾመ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በማዕድናት አጠቃቀምና አስተዳደር ግንዛቤ ማስጨበጡ ዙሪያ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በጋራ ይሰራል።

በተጨማሪም ህብረተሰቡ ህገ-ወጥነትን እንዲከላከል እንዲሁም በየአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀምና እንዲያስተዳድር በኦሮምኛና በአማርኛ ቋንቋዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለማከናወን መዘጋጀቱንም አስረድተዋል።

ትላንት በተካሔደው የአንድ ቀን የምክክር መድረክ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ተሳታፊዎችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተካፋይ ሆነዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ጅማ ሚያዚያ 1/2009 በጅማ ከተማ የክለቦች እግር ኳስ ሻምፒዮና ውድድር ተጀመረ፡፡

በጅማ ከተማ እግር ኳስ ፌደሬሽን አዘጋጅነት ዛሬ የተጀመረው የክለቦች ሻምፒዮና ወድድር ተተኪ እግር ኳስ ተጫዋቾችን ለማፍራት የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል አወቀ ውድድሩ እስከ ሚያዚያ 15 ቀን 2009 ዓ.ም እንደሚቆይና ስድስት ክለቦች እንደሚሳተፉበት ጠቁመዋል።

ዛሬ በተካሄደው የመክፈቻ ጨዋታ የአምናው የኮካኮላ ሻምፒዮና ጅማ አባጅፍር ከጅማ አባቡና ተስፋ ጋር ተጫውቶ 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡

የጅማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከተቋቋመ አምስት ወር ቢሆነውም በእግር ኳስ የሚታየውን የተተኪ ስፖርተኞች ችግር ለመፍታት የሚያስችል ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ በውድድሩ መክፈቻ ላይ ተገልጿል፡፡

ባለፈው የካቲት ወር ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች የሚገኙት በስልጠናና በውድድር እንደሆነ በመታመኑ ለአርባ ሁለት የክለብ አስልጣኞች የእግር ኳስ ሳይንስ የደረሰበትን ዕውቀት ለማስጨበጥ በጅማ አባቡና ክለብ ስልጠና መሰጠቱ የሚታወስ ነው፡፡

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ሚያዝያ 1/2009 የሌፍተናንት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።

በኢትዮጵያ አርበኞች ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያላቸው ሌፍተናንት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ባደረባቸው ህመም በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ሲረዱ ቆይተው በ96 ዓመታቸው መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር ያረፉት።

ዛሬ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞችና ዘመድ ወዳጆቻቸው በተገኙበት ሥርዓተ ቀብራቸው በክብር ተፈጽሟል።

ሌፍተናንት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ በፋሺስት ኢጣሊያ የግፍ ወረራ ወቅት በ15 ዓመት ዕድሜያቸው ከታላቅ ወንድማቸውና ከአጎታቸው ጋር በመሆን በአርበኝነት ለመታገል መዝመታቸውን ታሪካቸው ያስረዳል።

በወቅቱም በዱር በገደል እየተዘዋወሩ የኢጣሊያን ወራሪ ኃይል በጀግንነት ተዋግተዋል።

በአርበኝነት ዘመናቸው ያደረጓቸውን ጦርነቶች በድል እንደተወጡም ይነገራል።

ከኢጣሊያ ጋር የነበረው ጦርነት በድል ከተጠናቀቀ በኋላም አገራቸውን በሻለቅነት፣ በብርጌድ መሪነትና በብሔራዊ ጦር አዛዥነት በማገልገል የሌፍተናንት ጄኔራልነት ማዕረግ አግኝተዋል።

ሌፍተናንት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ በህይወት ዘመናቸው በርካታ የክብር ሽልማቶችንም ተቀብለዋል።

የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ፣ የዳግማዊ ምኒልክ፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ኒሻኖች እንዲሁም የቀድሞው የቀዳዋዊ አጼ ኃይለስላሴ የጦርና የአርበኝነት ሜዳሊያዎች ጥቂቶቹ ናቸው።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ሌፍተናንት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ከአርበኞች ጋር በመሆን ጠላትን ድል ያደረጉና ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ እውቀት የነበራቸው ጀግና ነበሩ ብለዋል።

ይህ ትውልድም ከጥንት አርበኞች ፍቅርና አንድነትን ይዞ መራመድ እንዳለበት አሳስበዋል።

ሌፍተናንት ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ በጠላት ላይ ከፍተኛ ጀብዱ ከመቀዳጀት ባሻገር፤ በርካታ የኢጣሊያ የጦር አዝማቾችን ማርከው ለፋሺስቶች የኢትዮጵያዊያንን ርህራሄ ማሳየታቸውንም ታሪካቸው ይዘክራል።

በቀድሞው ጅባትና ሜጫ አውራጃ በደንቢ ዮብዲ ወረዳ ዮብዶ በሚባል ቦታ ከአቶ ኬሎ ገሮና ከወይዘሮ ጠላንዱ ኢናቱ ጥር 21 ቀን 1913 ዓ.ም. የተወለዱት ጀግናው አርበኛ ሌፍተናንት ጄኔራል ጃጋማ የአንድ ወንድና የአምስት ሴቶች ልጆች አባት ነበሩ።

10 የልጅ ልጆችና ስድስት የልጅ ልጅ ልጆችም አፍርተዋል።

በ2001 ዓ.ም “የበጋው መብረቅ” በሚል ርዕስ በሕይወት ታሪካቸው ላይ ያተኮረ መጽሀፍ ታትሞ አንባቢያን ዘንድ ደርሷል።

 

Published in ማህበራዊ

ዲላ ሚያዚያ 1/2009 በጌዴኦ ዞን በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከ32 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት መምሪያ ገለጸ፡፡

ካለፈው የካቲት ወር አጋማሽ ጀምሮ በዞኑ ሲካሄድ የቆየው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በቡሌ ወረዳ ኮቾሬ ቀበሌ በተደረገ የመስክ ጉብኝት ተጠናቋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የጌዴኦ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሃብት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዝናቡ ወልዴ እንደገለጹት፣ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራው በዞኑ 33 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

ለሰላሳ ቀናት በተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራም 32 ሺህ 926 ሄክታር መሬት በመሸፈን የዕቅዱን 98 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡

በልማት ሥራው ከ800 ሺህ በላይ አርሶአደሮች መሳተፋቸውንና በእዚህም 26 ሚሊዮን ብር የሚገመት የሰው ጉልበት ጥቅም ላይ መዋሉን አመልክተዋል፡፡

አቶ ዝናቡ እንዳሉት፣ በተፋሰስ ልማቱ የቡና ልማት ሥራው ትኩረት ስለተሰጠው በሦስት ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ የቡና ጉንደላ ሥራ ተከናውኗል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በቀጣይ በሚኖረው የሥነ-ሕይወታዊ ሥራ 23 ሚሊዮን የቡና ችግኞችን ለመትከል መታቀዱንና በአሁኑ ወቅትም የ22 ሚሊዮን ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

የቡና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርም 800 ሺህ ሜትር ኪዩብ የሚጠጋ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን ነው የጠቆሙት።

የለሙ የወል መሬቶችን በገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች የማስተላለፍ ሥራ መጀመሩን የጠቆሙት አቶ ዝናቡ፣ በቡሌ ወረዳ ብቻ 4 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት በንብ ማነብና በእንስሳት መኖ ምርት ለተሰማሩ ወጣቶች መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡

የቡሌ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ታደለች አየለ በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም በጎርፍ ተሸርሽሮ ለምነቱን ያጣው መሬታቸው በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች እያገገመ መምጣቱንና  ምርታቸውም እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመስመር የመዝራት ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በሚዘሩት ገብስም ቀድሞ ከአንድ ዘለላ ያገኙት የነበረውን ከ35 ያልበለጠ ፍሬ ወደ 73 እንዳሳደገላቸው ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በተከናወነበት መሬት ላይ የከብቶች መኖ በማምረት ስምንት የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን በጎችን ማርባት እንደጀመሩም ተናግረዋል።

የአካባቢው ስነ-ምህዳር ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ በንብ ማነብ ሥራ ላይ መሰማራቱን የገለጸው ደግሞ ወጣት ሙሉጌታ መለሰ የተባለ የቀበሌው ነዋሪ ነው፡፡

አምና ለሙከራ በጀመረው አንድ የንብ ቀፎ ሥራ 28 ኪሎ ግራም ማር በማግኘቱ ዘንድሮ የቀፎዎቹን ቁጥር ወደ 10 ማሳደጉን ተናግሯል።

ከጉብኝቱ በኋላ በልማት ሥራው የላቀ አፈጻጸም ለነበራቸው አርሶአደሮች የምስክር ወረቀት እና የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡

 

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 1/2009 የለቡ መብራት ኃይል አደባባይ ፈርሶ በትራፊክ መብራት መተካቱ የትራፊክ እንቅስቃሴውን እንደሚያሳልጠው ተገለጸ።

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በመዲናዋ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ለማስወገድ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው።

በአደባባዮች አካባቢ የሚከሰተውን የተሽከርካሪዎች ግጭት፣ መጨናነቅና አደጋ ለመቀነስ አደባባዮችን አፍርሶ በትራፊክ መብራት የመተካት ስራ ከእርምጃዎቹ መካከል ይጠቀሳል።

የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጥዑማይ ወልደገብርኤል ለትራፊክ እንቅስቃሴ አስቸጋሪና አደጋ ፈጣሪ የሆኑ አደባባዮችን በማፍረስ በመብራት መተካት አማራጭ መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል።

ለትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት የነበሩት የ18 ማዞሪያ፣ ቦሌ ሚካኤልና ጀሞ አደባባዮችን በማፍረስ የተወሰደው እርምጃ ለትራፊክ ፍሰቱ መሳለጥ ትልቅ ለውጥ አስገኝቷል።

ከትናንት ምሽት ጀምሮ እየፈረሰ ያለው የለቡ መብራት ኃይል አደባባይም የትራፊክ ፍሰቱን በማሻሻል እየተከሰተ ያለውን አደጋ ይቀንሳል ብለዋል አቶ ጥዑማይ።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሞተር ቁጥጥር ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር ተስፋዬ በዳዳ በበኩላቸው እንዳሉት የለቡ አደባባይ ለዓመታት በትራፊክ እንቅስቃሴው ላይ ችግር ሲፈጥር ቆይቷል።

በመሆኑም አደባባዩ ፈርሶ በመብራት መተካቱ የተሻለ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡት የከባድ መኪና አሽከርካሪም አደባባዩ ፈርሶ በመብራት መተካቱ የነበረውን ችግር በማቃለል የትራፊክ እንቅስቃሴውን ፈጣን ያደርገዋል ነው ያሉት።

የለቡ መብራት ኃይል አደባባይን የማፍረሱ ስራ በነገው ዕለት እንደሚጠናቀቅና ለተሽከርካሪዎች ክፍት እንደሚሆን አቶ ጥዑማይ አስታውቀዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ጎንደር ሚያዝያ 1/2009 በሰሜን ጎንደር ዞን በዘንድሮ የክረምት የሰብል ልማት አዳዲስ የግብርና አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎችን በስፋት በመጠቀም ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰብል ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በዞኑ በክረምት የሰብል ልማት ሥራ ለሚሳተፉ ከ113ሺህ በላይ  ግንባር ቀደምና ሞዴል አርሶአደሮች አዳዲስ የግብርና አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የሚያስችላቸውን ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

በዞኑ አምና በተካሄደው የክረምት የሰብል ልማት ሥራ በሄክታር የተገኘውን 20 ኩንታል የሰብል ምርት ዘንድሮ ወደ 26 ኩንታል ለማድረስ ግብ መጣሉን የመምሪያው ኃላፊ አቶ ግዛት ጀመረ ተናግረዋል፡፡

በሰብል ልማቱ ጥቁር አፈር የእርሻ መሬትን የማንጣፈፍ ቴክኖሎጂ፣ ምርት መስጠት ያቆሙ አሲዳማ መሬቶችን በኖራ አፈር የማከምና ዋና ዋና ሰብሎችን ሙሉ በሙሉ በመስመር የመዝራት ቴክኖሎጂዎችና አዳዲስ አሰራሮች ትኩረት ይሰጣቸዋል።

አርሶአደሩ መሬቱን ደጋግሞ እንዲያርስ፣ የአረምና የተባይ መከላከል ሥራ እንዲሰራ፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያን እንዲጠቀም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አመለክተዋል።

በተጨማሪም  አርሶአደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በስፋት አዘጋጅቶ ጥቅም ላይ እንዲያውል በማድረግ የዞኑን የሰብል ምርት ከፍ ለማድረግ ታቅዷል፡፡

አቶ ግዛት እንዳሉት፣ በድህረ ምርት የሰብል አሰባሰብ ላይ የሚደርሰውን የምርት ብክነት መቀነስ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ በማዋል በዞኑ የምርት ጭማሪ ለማስመዘግብ ርብርብ ይደረጋል፡፡

የምርት ዘመኑን የሰብል ምርት ዕቅድ ማሳካት እንዲቻልም በዞን፣ በወረዳና በመንደር ደረጃ ለአርሶአደሮች የተሰጠው ስልጠና የተጠናቀቀ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ስልጠናው በጎጥ ደረጃ በመሰጠት ላይ ነው፡፡

የአርሶአደሮችን የግበርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እውቀትና ክህሎት ከማጎልበት አንጻርም በገበሬ ማሰልጠኛ ማዕከላት አማካኝነት ለአርሶአደሮች ተግባር ተኮር ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ባለፈው ዓመት በመኽር የተመረተውን 17 ሚሊዮን ኩንታል በመጭው ክረምት ወደ 25 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ የተጠናከረ ርብርብ እንደሚደረግ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

"በክረምት የሰብል ልማት ሥራው 941ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ በተለያዩ ሰብሎች ይሸፈናል" ያሉት ኃላፊው እንደ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ ፣በቆሎ፣ ሰሊጥና ማሽላ የመሳሰሉት ሰብሎች ሙሉ በሙሉ በመስመር እንደሚዘሩ ጠቁመዋል።

የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር ቢያይልኝ መልካሙ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ በግብርና ባለሙያዎች የተሰጣቸው በተግባር የተደገፈ ስልጠና ከተለምዷዊው የግብርና ሥራ ተላቀው ዘመናዊ የግብርና አሰራር እንዲጠቀሙ ያነሳሳቸው መኑን አመልክተዋል።

"ቀደም ሲል ለአንድ ሄክታር የእርሻ መሬት የምጠቀመው ማዳበሪያ በግምት ነበር" ያሉት ደግሞ የምስራቅ በለሳ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር ማሬ ሰጠኝ ናቸው፡፡

"አሁን ለአንድ ሄክታር መሬት ምን ያህል ኩንታል ማዳበሪያ መጠቀም እንዳለብኝ ትምህርት አግኝቻለሁ፤ ምን አይነት ማዳበሪያ መቼና እንዴት እጠቀማለሁ በሚለው ላይም እውቀት ጨብጫለሁ" ብለዋል፡፡

መሬት ምርት መስጠት ሲያቆም ለከብት ግጦሽ መዋያ ነበር የምደርገው፣ አሁን ግን በኖራ አፈር በማከም ማልማት እንደሚቻል ትምህርት አግኝቻለሁ በማለት የተናገሩት ደግሞ የደባርቅ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር ምህረት ገላዬ ናቸው፡፡

"አምና የኖራ አፈር ቴክኖሎጂን ተጠቅሜ ለበርካታ ዓመታት ከምርት ስራ ውጪ የነበረውን የእርሻ መሬቴን ምርት እንዲሰጥ ማድረግ ችያለሁ፤ ወደፊትም የቀሰምኩትን እውቀት ለሌሎች ለማካፈል ዝግጁ ነኝ" ብለዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ ሚያዝያ 1/2009 የትግራይ ሰማዕታት ኃውልትን የቱሪስት መስህብ ለማድረግ በ700 ሚሊዮን ብር ወጪ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ለማከናወን መታቀዱ ተጠቆመ።

የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድሜነህ ግርማይ ትናንት ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የልማት ሥራዎቹ በሓውልቱ ውስጥ ያሉ ታሪካዊ ቅርሶች በአግባቡ ተጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው።

ለልማት ሥራ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አባላትና ደጋፊዎች መገኘቱን ገልጸው፣ በገንዘቡ ስፍራውን የቱሪስት መስህብ ለማድረግና በውስጡ ያሉ ቅርሶችን ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የቅድመ ዝግጀትና ዕቅዱን የማስገምገም ሥራ መከናወኑን የገለጹት አቶ ወንድሜነህ፣ በቀጣይ አምስት ዓመታት በሰማዕታት ኃውልቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ዘመናዊ ሕንጻዎች ቅርጻቸውና ይዘታቸው ሳይቀየር ጥገና እንደሚደረግላቸው አመልክተዋል።

የጥገና ሥራው በከፍተኛ የኃውልትና ቅርስ ጥገና ባለሙያዎች አማካኝነት የሚካሄድ ሲሆን፣  በሐውልቱ የተወሰኑ አካባቢዎች፣ በመሰብሰቢያ አደራሾችና ቅርሶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚከናወን አመልክተዋል።

በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በሐውልቱ ግቢ ውስጥ መሰራት የነበረባቸውና ሳይሰሩ የቀሩ ተጨማሪ የግንባታ ሥራዎች እንደሚካናወኑ አቶ ወንድሜነህ ተናግረዋል።

"አዲስ ከሚከናወኑ የግንባታ ሥራዎች መካከል የህጻናት መዝናኛ፣ መዋኛና የልዩ ልዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራዎች ይገኙበታል" ብለዋል።

ሥፍራውን በአገር በቀል እጽዋት ከማስዋብ ባለፈ የተለያዩ የዱር እንስሳትን እንዲይዝ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ሥራው እንደሚከናወን  የተናገሩት አቶ ወንድሜነህ፣ ዘመናዊ ቤተ መጻህፍት እንደሚኖረውም አመልክተዋል።

የህወሓትና የትግራይ ህዝብ የትጥቅ ትግል ታሪክ የሚጠበቅበት ማዕከል እንዲሆን ከማድረግ በተጨማሪ የክልሉ የጥናትና ምርምር ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል የሚሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ለዚህም በክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ነው የጠቆሙት።

የአሁኑ ትውልድ ነባሩ ትውልድ ለሰላምና ለዴሞክራሲ ሲባል ያሳለፈውን መከራና የከፈለውን መስዋዕትነት ወደ ማዕከሉ በመምጣትና  በድረገጽ የሚያገኝበትን መንገድ ለመፍጠር መታቀዱን አስረድተዋል።

ሥፍራው ከለማ በኋላ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ኤግዚቢሽንና ፓናሎችን የሚያዘጋጁበት ሥፍራ እንደሚሆንም አቶ ወንድሜነህ  ገልጸዋል።

ሰማዕታት ኃውልትን ሲጎበኙ የኢዜአ ሪፖርተር ካነጋገራቸው የአገር ውስጥ ጎብኚዎች መካከል ከአዲስ አበባ የመጡ አቶ ተክሊት ገብረመድህን "ማዕከሉ በቀደምት ትውልድ በቀላሉ ለማመን የሚያስቸግር ድንቅ ታሪክ መሰራቱን የሚያሳዩ ቅርሶች ያሉበትና ሁሉም ሊጎበኘው የሚገባ ልዩ ሥፍራ ነው" ብለዋል።

የተሰራውን ታሪክ ለመጠበቅና አካባቢውን የቱሪስት መስህብ ስፍራ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አረጋግጧል።

ከሁለት ልጆቻቸው ጋር የሰማዕታት ኃውልቱንና በውስጡ ያሉትን ቅርሶች ሲጎበኙ የነበሩት ዶክተር ዮሐንስ ኃይላይ በበኩላቸው፣ የትግራይ ህዝብ የሰራውን ድንቅ ታሪክ ለመጠበቅ ሁሉም ድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የትግራይ ሰማዕታት ኃውልት በ108 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ በየዓመቱ በአማካይ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚጎበኝ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ሚያዚያ 1/2009 በኢትዮጵያ የኳታር አምባሳደር አብዱላዚዝ ቢን ሱልታን አል ሩማሂ የኳታሩ አሚር ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ የኢትዮጲያ ጉብኝት  በሁሉም ዘርፍ የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት እንደሚያጠናክር መግለፃቸውን ኤምሬትስ የዜና ወኪል ዘገበ፡፡  

አምባሳደሩ ለኳታር የዜና ወኪል የተናገሩትን ጠቅሶ ዘገባው እንዳመለከተው  አሚሩ ከፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ይወያያሉ ፤  የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ትብብርን በኢኮኖሚ፣ፖለቲካ፣ ኢንቨስትመንት፣ ማህበራዊና የባህል ጉዳዮች ለማጠናከር  እንዲሁም  የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑት በአህጉርና  በአለምአቀፋዊ ጉዳዮች ላይም ይመክራሉ፡፡   

አምባሳደሩ እንደተናገሩት አሚሩ  ወደ  አፍሪካ ከሚያደርጉት ጉብኝት  ኢትዮጵያ የመጀመሪያ መዳረሻቸው ነች ይህም በዶሃ እና በአዲስ አበባ መሃከል ያለውን  የመሪዎችና የሁለትዮሽ  ግንኙነት ያጠናክራል፡፡

 

 

Published in ፖለቲካ

ቤይጂንግ ሚያዚያ 1/2009 የቻይናዋ ጂያንሱ ግዛት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ።

የግዛቷ አስተዳደር በበኩሉ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ረገድ ለአፍሪካ አገራት አርዓያ ነች ብሏል።

በደቡብ ምሥራቅ ቻይና የምትገኘው ጂያንሱ ግዛት 80 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ያላትና የዳበረ ኢኮኖሚ ካላቸው የአገሪቱ ግዛቶች ተጠቃሽ ናት።

በተለይ በኢንዱስትሪ አቅሟ በመስኩ የቻይና ምሰሶ እንደሆነች የሚነገርላት ስትሆን በዓለም ተወዳዳሪ የሆኑ ማሽነሪዎች፣ ኬሚካሎች፣ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችና አውቶሞቢሎችን በማምረት ትታወቃለች።

እናም እነዚህ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት መስክ በስፋት ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ነው የገለጹት።

ግዙፉ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች አምራች ሹጆ ኩባንያም ኢትዮጵያ ውስጥ በዘርፉ ለመሰማራት እንደሚሻ ነው ያስታወቀው።

የሹጆ ኮንስትራክሽን ማሽነሪ ኩባንያ ረዳት ፕሬዚዳንት ዶክተር ሃንሰን ሊዩ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኩባንያው አፍሪካ ውስጥ በስፋት መሰማራት ይፈልጋል።

ለዚህ ደግሞ "ኢትዮጵያ እየገነባቻቸው ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለኢንቨስትመንት መዳረሻነት ተመራጭ እንድትሆን ያስችላታል" ብለዋል።

የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን በማምረት በዓለም በ5ኛ ደረጃ የተቀመጠው ሹጆ ኩባንያ በአሁኑ ጊዜ ከመከላከያ ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ (ሜቴክ) እና ከመስፍን ኢንጂነሪንግ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንና በቀጣይ ራሱን ችሎ በማምረቻ ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ረዳት ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ ሰፊ ገበያ ያላት አገር በመሆኗ ለኢንቨስትመንት ሳቢ አገር ናት” ያሉት ደግሞ የቻይና ጂያንሱ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና የቴክኒክ ትብብር ግሩፕ ምክትል ፕሬዚዳንት ጉ ያውሼንግ ናቸው።

ያውሼንግ እንዳሉት በአልባሳትና ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ፣ በኮንስትራክሽንና ኢንጂነሪንግ የተሰማራው ይህ ግሩፕ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ በኢንቨስትመንት መስክ የመሰማራት ዕቅድ አለው።

ግሩፑ ከአፍሪካ አገራት ጋር ላለፉት 30 ዓመታት በትብብር ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው "ይህን ልምድ ወደ ኢንቨስትመንት ለማሸጋገር ይሰራል" ብለዋል።

የጂያንሱ ግዛት የውጭ ጉዳዮችና የኢንፎርሜሽን ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ጋኦ ያን በበኩላቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን የምታደርገው ጥረት ለአፍሪካ አገራት አርዓያ መሆን የሚችል ነው።

የግዛቷ ኩባንያዎች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2007 ጀምሮ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በስፋት መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

በምስራቅ የኢንዱስትሪ ዞን ብቻ ከ260 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የጂያንሱ ኩባንያዎች በኢንቨስትመንት መስክ መሰማራታቸውን በማሳያነት አንስተዋል።

እናም "የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባት ግዛቷ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ እንዲጎለብት የሚያደርግ ነው" ብለዋል።

በዚህ ረገድ የግዛቷ አስተዳደር የጂያንሱ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በስፋት እንዲሰማሩ እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። 

የኢትዮ-ጂያንሱ የኢንቨስትመንት ፎረም እንደ ጎርጎሮሳዊያን የጊዜ ቀመር በ2015 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት በግዛቷ መዲና ናንጂንግ መካሄዱ ይታወሳል።

በፎረሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የጂያንሱ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እያደረጉ ያሉትን የነቃ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ አድንቀዋል።

የጂያንሱ ኩባንያዎች አፍሪካ ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች 9 ነጥብ 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አፍስሰዋል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን