አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Saturday, 08 April 2017

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2009 የተማሪዎችን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ተጋላጭነት ለመቀነስ የተሰራው ስራ አጥጋቢ አለመሆኑን የአዲስ አበባ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር በመተባበር የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

በትምህርት ቤቶች አካባቢ ለቫይረሱ አጋላጭ የሆኑ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለማስወገድ የንግድና ኢንዱስትሪ፣ የትምህርት ቢሮዎችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት በቅንጅት ባለመስራታቸው ውጤታማ መሆን ያልተቻለበት አንዱ ምክንያት ነው ይላሉ።

ውይይቱ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት ያለበት አጠቃላይ ሁኔታ፣ የተማሪዎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የባለድርሻ አካላትና የመገናኛ ብዙሃን ድርሻ ላይ ያተኮረ ነው።

በጽህፈት ቤቱ የማህበረሰብ ንቅናቄና ሜንስትሪሚንግ ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ቦጋለ ለኢዜአ እንደተናገሩት በትምህርት ቤቶች አካባቢ የአደንዛዥ ዕጾች መጠቀሚያና የጭፈራ ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች ለቫይረሱ አጋላጭ የሆኑ የንግድ እንቅስቃሴዎች በስፋት ይስተዋላሉ።

በአሁኑ ወቅት ወጣቱ በሽታውን መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶች ላይ ዕውቀት ቢኖሩትም አጋላጭ የሆኑ እንቅስቃሴዎች ካልተወገዱ በስተቀር ስርጭቱን መግታት አዳጋች ይሆናል  ብለዋል።

በመሆኑም ቁጥራቸው አነስተኛ የማይባል ተማሪዎች የቫይረሱ ተጋላጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ማህበረሰቡም በሽታውን የመከላከል ስራን በባለቤትነትና በተቆርቋሪነት በማየት በተለይም አጋላጭ የሆኑ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ከመሳተፍ መታቀብ ይኖርበታል ነው ያሉት።

የኤች. አይ. ቪ/ ኤድስ በሽታን የመከላከል ስራን የልማት ስራ አካል በማድረግ በኩል በየደረጃው ያሉ አመራሮች በኩልም ውሱንነት በመኖሩ የአገር ውስጥ ኃብትን አንቀሳቅሶ ስራ ላይ በማዋልም እንዲሁ ክፍተቶች አሉ ብለዋል።

በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁ የኤች. አይ. ቪ/ ኤድስ  በሽታ የመከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶች ላይ በቂ ሽፋን አለመስጠትም ለችግሩ ሌላው ምክንያት መሆኑን ነው የሚናገሩት።

በአዲስ አበባ ከ86 ሺህ በላይ የኤች. አይ. ቪ/ ኤድስ በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖች ሲኖሩ ከ2 ሺህ 900 በላይ የሚሆኑት በተያዘው ዓመት  አዲስ የተያዙ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ ከዚህ ውሰጥም አብዛኛውም ወጣቶች ናቸው።

Published in ማህበራዊ

ሶዶ መጋቢት 30/2009 በ22ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ ወላይታ ድቻና ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ እኩል ተለያዩ።

የጨዋታው የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሲቀረው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ምንተስኖት አዳነ ከመሃል ሜዳ ያሻገረለትን ኳስ የዲቻ ተከላካዮችን አለመናበብና የግብ ጠባቂውን መውጣት ተጠቅሞ አዳነ ግርማ ወደ ጎል ለውጦታል።

ወላይታ ዲቻም አቻ ያደረገችውን ጎል በ51ኛው ደቂቃ በ20 ቁጥሩ አብድልሰመድ አሊ አስቆጥሯል።

በሁለተኛዉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የወላይታ ዲቻ ቡድን ስህተቶችን አርሞ በመግባት የጨዋታ ብልጫ የወሰደ ቢሆንም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር አልቻለም

በተለይ በ58ኛው ደቂቃ ላይ ሰባት ቁጥር ለባሹ አናጋው ባደገ ሞክሮት ለጥቂት የጎሉ አግዳሚ  የመለሰው ኳስ ክለቡን የሚያስቆጭ ነበር

በርካታ ተመልካች በወላይታ ሶዶ ሁለገብ ስታዲየም ተገኝቶ አዝናኝ የነበረውን ጨዋታ ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ ተከታትሏል።

Published in ስፖርት

ሀዋሳ መጋቢት 30/2009 የሳውዲ አረቢያ መንግስት ያለ ፈቃድ የሚኖሩ የውጪ ሀገር ዜጎች ለማስወጣት ያወጣውን አዋጅ ተከትሎ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ ኢትዮጵያውያንን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን የኦሮሚያና ደቡብ ክልል የዳያስፖራ ጽህፈት ቤቶች ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከክልል የዳያስፖራ ማህበራት ጋር ሰሞኑን በሀዋሳ ውይይት አካሂዷል።

የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አብዱላዚዝ ኢብራሂም እንደገለፁት በሳውዲ አረቢያ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አብዛኞቹ የክልሉ ተወላጆች ናቸው፡፡

"ማህበሩ በሳውዲ አረቢያ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተሰጠው የጊዜ ገደብ ያለምንም እንግልት ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹ በኩል እየሰራ ይገኛል" ብለዋል ፡፡

በሳውዲ የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በህገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ ወገኖችን እንግልት ሳይደርስባቸው በሰላም ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ በኩል የድርሻቸውን እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዜጎቹ ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ በመደራጀት በተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ ለማስቻል ከክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

የደቡብ ክልል ዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘላለም አስራት በበኩላቸው ከደቡብ ልማት ማህበር ጋር በመተባበር ያለ ፍቃድ በሳውዲ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

ቀደም ሲል በተለያዩ ምክንያቶች ከውጭ የተመለሱ የክልሉ ተወላጆች በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው ራሳቸውን መለወጥ እንደቻሉ አስታውቀዋል፡፡

"በቀጣይ ወደ ክልሉ የሚመጡ ተመላሾችን በተለያዩ ማህበር ተደራጅተው ራሳቸውን የሚችሉበትን መንገድ ለማመቻቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው " ብለዋል ።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ደመቀ አጥናፉ እንዳሉት በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሳውዲ አረቢያ ሄደው በዚያው የሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ጠቅሰዋል ።

እንደ አቶ ደመቀ ገለፃ ከወገኖቹ ውስጥ ጥልቁን ቁጥር የያዙት የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የደቡብና የትግራይ ተወላጆች ናቸው ።

ኢትዮጵያውያኑን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በፌደራል ደረጃ ኮማንድፖስት መቋቋሙን ጠቁመዋል ።

በኮማንድ ፖስቱ የየክልሉ ርዕሰ መስተዳድሮች የተካተቱበት መሆኑን የገለፁት አቶ ደመቀ  ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከሳውዲ አረቢያ መንግስት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል ።

የሳውዲ መንግስት በፍቃድም ሆነ ያለ ፍቃድ የሚኖሩ የማንኛውም አገር ዜጎች በ90 ቀን ውስጥ ከሀገሩ መውጣት እንደሚችሉና በጊዜ ገደቡ ሳይወጡ በሚገኙ ህጋዊ ያልሆኑ የውጭ ዜጎች ላይ የቅጣት እርምጃ እንደሚወስድ በተያዘው ወር ህግ አውጥቶ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2009 የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር ለቀጣይ ሁለት ዓመት ማኅበሩን የሚመሩ አዲስ የቦርድ አባላት ምርጫ በክርክርና ውዝግብ ታጅቦ ተካሄደ።

የተወሰኑ የማህበሩ አባላትና የቀድሞው የማህበሩ የቦርድ አባላት ምርጫው "ፍትሀዊ አይደለም" የሚል ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ ላይ በተነሱ የተለያዩ ቅሬታዎች ምክንያት ሳይጸድቅ ቀርቷል።

ማህበሩ ነሐሴ 2008 ዓ.ም ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ አዲስ የቦርድ አባላትን ለመምረጥ ውሳኔ ያሰለፈ ሲሆን ይህንንም ጉዳይ የሚከታተል የአስመራጭ ኮሚቴ እንዲቋቋም አድርጓል።

ለቦርድ አባልነት ለመወዳደር በራሳቸው ፍላጎት፣ በአባላት ጥቆማና የዳያስፖራውን ፕሮፋይል በማየት 100 ዕጩዎች ቀርበው የነበረ ሲሆን፣ አስመራጭ ኮሚቴው ባደረገው ማጣራት 12 ዕጩዎች ለመጨረሻው ዙር አልፈዋል፡፡

የቦርድ አባላት በመሆን የመጨረሻውን ዙር ካለፉት እጩዎች መካከል አምስቱ ሴቶች ናቸው።

ምርጫው ከመደረጉ በፊት የአስመራጭ ኮሚቴዎቹ ከቀረቡት እጩዎች መካከል ሁለቱ በምርጫው መወዳደር እንደማይፈልጉ ማሳወቃቸውን ገልጸው ከአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ሁለት ሰዎች በቀሩት ምትክ እጩ ሆነው ይወዳደሩ የሚል ሀሳብ በአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ ቀረበ።

ነገር ግን አንዳንድ የማህበሩ አባላት የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት የቦርድ አባል ሆነው ከተመረጡ "የፍላጎት ግጭት" ይፈጠራል እንደ አካሄድም ልክ አይደለም ስለዚህም እጩ መሆን የለባቸውም የሚል ሀሳብ አቀረቡ።

ጠቅላላ ጉባኤው በዚህ ጉዳይ ላይ ክርክር ካደረገ በኋላ የቀረቡት እጩዎች ካላቸው ልምድ አንጻር የቦርድ አባላት ቢሆኑ ማህበሩን ይበልጥ ያገለግላሉ በማለት በምርጫው እንዲሳተፉ ከስምምነት ላይ ተደረሰ።

ከቀረቡት እጩዎች መካከል ዶክተር ብርሃኑ ግዛው በስራ ጫና ምክንያት ራሳቸውን ከውድድሩ በማግለላቸው ምርጫው በ11 እጩዎች መካከል ተካሂዷል።

ከዚህም በኋላ ምርጫው ተካሂዶ ሰባት የቦርድ አባላት ተመርጠዋል።

በዚህም መሰረት እድሪስ አህመድ በ129፣ ወይዘሮ አብነት መኩሪያ በ127፣ መምህር ያሲን ራጅ በ125፣ አቶ ማሂር እስማኤል በ121፣ ዶክተር ዮሐንስ ገብረስላሴ በ107፣ ወይዘሪት ሳሪቱ ሱሌማን በ102 እና አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ በ100 ድምጽ የቦርድ አባላት ሆነው ተመርጠዋል።

ወይዘሮ ቅድስት አምሀ በ91 እና ወይዘሮ ኤፍራታ ለማ በ88 ድምጽ ተጠባባቂ ሆነዋል።

ከምርጫው በኋላ አንዳንድ የማህበሩ አባላት እንዲሁም የቀድሞው የማህበሩ ቦርድ አባላት "የምርጫው መካሄድ መረጃ የደረሰን ከሶስት ቀን በፊት በፅሁፍ መልዕክት ነው" በመገናኛ ብዙሃን ማሳወቅ እየተቻለ ለምን በፅሁፍ መልዕክት ስለ ምርጫው መረጃ ተላከ? የፅሁፍ መልዕክቱ የተላከው "ለተወሰኑ አባላት ነው የተላከው" ይህም "የማህበሩ ስድስት ሺህ አባላትና አጠቃላይ የዳያስፖራውን ማህበረሰብ አይወክልም" የሚል ቅሬታ አቅርበዋል።

ጠቅላላ ጉባኤው የማህበሩ አባላት እንዲሁም የቀድሞው የማህበሩ ቦርድ አባላት "የምርጫው መካሄድ መረጃ የደረሰን ከሶስት ቀን በፊት በፅሁፍ መልዕክት ነው" ምርጫውን አስመልክቶ በመገናኛ ብዙሃን በአገር ውስጥና በውጭ ላሉ የዳያስፖራ አባላት ቢተላለፍ የሚለውን ሀሳብ አግባብነት ያለው ቢሆንም ምርጫው "የማህበሩ ስድስት ሺህ አባላትና አጠቃላይ የዳያስፖራውን ማህበረሰብ አይወክልም" የሚለውን ሀሳብ ግን ውድቅ አድርጓል።

ለዚህም ጉባኤው በምክንያትነት ያነሳው ማህበሩ የሚያገለግለው የተመዘገቡ አባላትን ነው እንጂ አጠቃላይ የዳያስፖራው አባላትን የሚወክል ባለመሆኑ ምርጫው "ፍትሀዊ" ነው በሚል ተቀብሎታል።

በቦርድ አባላቱ ምርጫ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ማህበሩ የሚተዳደርበትን ደንብ ለማጽደቅ ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቦ ውድቅ ተደርጓል።

በተለይም የቀድሞው የማህበሩ ቦርድ አባላት እንዲጸድቅ የቀረበው መተዳደሪያ ደንቡ "እኛ የማናውቀው ነው" የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ማህበሩ ሲቋቋም የነበረው መተዳደሪያ ደንብ ረቂቅ ላይ ማሻሻያ አድርጉ ባለው መሰረት በድጋሚ ለኤጀንሲው አቅርቦ ምላሹን እየተጠባባቀ ባለበት ሰአት ይህ መተዳደሪያ ደንብ ረቂቅ ከየት መጣ? የሚል ሀሳብ አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የቀረበው ደንብ በማህበሩ ዋና ዳይሬክተርና የቦርድ አባላት መካከል የኃላፊነት መደራረብ የሚፈጥር በመሆኑ ውድቅ ሊሆን ይግባል የሚል ሀሳብም ተነስቷል።

በነዚህ ሀሳቦች አዲስ የተመረጡት የቦርድ አባላት መተዳደሪያ ደንቡ ማን እንዳረቀቀው እንዲያጣሩና አዲሱና የቀድሞው የቦርድ አባላት አዲስ የመተዳደሪያ ደንብ በማርቀቅ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለጠቅላላ ጉባኤው እንዲቀርብ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

የተመረጡትም የቦርድ አባላት ቃለ-መሐላ የፈጸሙ ሲሆን የቦርድ አባላት በዳያስፖራውና በመንግሥት መካከል እንደ ድልድይ ሆነው ለማገልገል በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

ጠቅላላ ጉባኤ የቦርዱ ሊቀ-መንበርና ምክትል ሊቀመንበር ምርጫ አዲስ በተመረጡት የቦርድ አባላት እንዲከናወን ፈቃድ ሰጥቷል።

ስድስት ሺሕ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር በ2005 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፣ ዳያስፖራው በአገሩ ልማት ተሳታፊ እንዲሆን መረጃ ለመስጠት፣ የልምድ ልውውጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግበትን ሁኔታ ለማመቻቸትና በዳያስፖራውና በመንግሥት መካከል ድልድይ ሆኖ ለማገልገል መቋቋሙ ተጠቅሷል፡፡ 

Published in ማህበራዊ

ጅማ መጋቢት 30/2009 በቡና ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች እንዲፈቱ የዘርፉ ተዋንያን ጠየቁ፡፡

የቡናና ሻይ ባለስልጣን ”ለዓለም ቀድመን ያስተዋወቅነውን የቡናችንን ሕዳሴ እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ቃል ትናንት በጅማ ከተማ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር ውይይት አካሂዷል።

ከተሳታፊዎች መካከል ከኢሉአባቦራ ዞን የመጡትና ቡና ለጅማና አዲስ አበባ ማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ የተሰማሩት አቶ አብዱራህማን ያሲን እንደገለፁት የቡና ግብይት ደላላ የበዛበትና ጊዜ ቆጣቢ ባለመሆኑ የዘርፉን ተዋንያን ተጠቃሚ እያደረገ አይደለም።

''ቡና ከሚመረትበት ወረዳ አንስቶ  እስከ ምርት ገበያ ድረስ ላልተገባ የኮሚሽን ከፍያ፣ ለመጋዘንና ለጭነት ወጪ ዳርጎናል'' ብለዋል።

የቡና ግብይቱ በአገናኝ ደላላ መካሄዱ ለህገወጥ ግብይት እድል የሚሰጥ በመሆኑ  ገበያው እንዳይረጋጋና የዘርፉ ተዋንያንም ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ ከጋምቤላ ክልል የመጡት ቡና አምራች አለቃ ግርማ ነጋ በበኩላቸው የቡና ጆንያ እጥረት በስራቸው ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አንድ ጆንያ እስከ አንድ መቶ ብር ገዝተን ለመጠቀም እየተገደድን ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው ''ወጪው በግብይት ወቅት ታስቦ ሊመለስልን ይገባል'' ብለዋል፡፡

የጅማ ዞን ተሳታፊ ባለሀብት አቶ ናስር አብዱ በበኩላቸው የቡና ደረጃ አሰጣጥ አድሎ የሚታይበት በመሆኑ  የሚስተካከልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የቡና ልማት ፕሮሞሽን ምክትል ኃላፊ አቶ ጣባ  ጁንፌንሳ  ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ በቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ዘርፍ ያሉትን ተግዳሮቶች የሚፈታ አዲስ አደረጃጀትና አሰራር ተፈጥሮ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ።

ባለስልጣኑ ጥናት በማድረግ በዘርፉ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የሚያቀርብ፣ እሴት የሚጨምሩ ኢንዱስትሪዎችን የሚደግፍ የገበያ ልማትና ድጋፍ እንዲሁም የመረጃና የቁጥጥር አደረጃጀት መፍጠሩን ገልጸዋል።

''በአዲሱ አሰራር ማንኛውም አቅራቢ ሆነ አምራች አገናኝ ደላላን ሳይጠቀም የመሸጥ መብት አለው'' ብለዋል።

የጆንያ ዋጋን በተመለከተም "ከአሁን በኋላ ተመለሽ ይሆናል " ብለዋል፡፡

ምክትል ኃላፊው እንዳሉት የቡና ዋጋ ከአምስት በመቶ በላይ ከፍና ዝቅ እንዳይል ይደረጋል።

እንዲሁም 300 ሄክታር ለሚያለማ ብቻ ይሰጥ የነበረው የብድር አገልግሎት በአዲሱ አሰራር 30 ሄክታር የሚያለማም የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆን አብራርተዋል።

ይህም አገሪቱ በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በዓለም ያላትን የአምራችና ላኪነት ደረጃ ከአምስተኛ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል።

በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ሞዴል ቡና አምራቾች፣ ባለሃብቶች፣ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ ላኪዎችና አቅራቢዎች፣ ባለሙያዎችና አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ መጋቢት 30/2009 በትግራይ ክልል ነጻ የህግ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር ሊዘረጋ መሆኑን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።

የተቀናጀ ነጻ የህግ ድጋፍ ለመስጠት እንዲያስችል በቢሮው በተዘጋጀ ረቂቅ ህግ ዙሪያ በውቅሮ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሒዷል።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ ልኡል ካህሳይ በውይይት መድረኩ ላይ እንደገለፁት ረቂቅ ህጉን ማዘጋጀት ያስፈለገው ቀደም ሲል በተበታተነ መልኩ ሲከናወን የነበረውን አገልግሎት ለማደራጀት ነው።

ረቂቅ ህጉ በሚመለከታቸው አካላት በውይይት ዳብሮ ሲጸድቅም በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን በአግባቡ በመፍታትና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በቢሮው የፍትሐብሄር ጉዳዮች አቃቤ ህግ አቶ አዲሱ ገብረስላሴ እንደገለፁት የረቂቅ ህጉ መነሻ ዜጎች ለፍትህ ተደራሽና በህግ ፊት እኩል መሆናቸውን በተግባር ለማረጋገጥ ነው።

ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት የማማከር፣ውሎችና ክሶችን የማዘጋጀት፣የይግባኝ መብት ፣ ክርክር ፣ የአፈፃፀም ጉዳዮችንና ሌሎችንም ያከተተ እንዲሆን በረቂቅ ህጉ መቅረቡንም ገልጸዋል።

"አገልግሎቱን ማቅረብ የሚገባቸው አካላትም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የክልሉ ፍትህ ቢሮ፣የግል ጠበቆች፣ተከላካይ ጠበቆች፣ህዝባዊ ማህበራትን ያካትታል''ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ተባባሪ  ፕሮፌሰር መብራህቶም ፍትዊ እንደገለፁት ፍትህን ሊያዛቡ የሚችሉ ጉዳዮችን በአግባቡ ለመፍታት ነጻ የህግ ድጋፍ ለሚገባቸው ወገኖች ሁሉ መስጠት ተገቢ ነው።

''ኢትዮጵያ ውስጥ የተጠለሉ የጎረቤት ሀገር ስደተኞችም በማእቀፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ሀገራችን የፈረመችባቸውን የዓለም አቀፍ ህጎች ተፈፀሚነት ያረጋግጣል'' ብለዋል።

አገልግሎቱ በአብዛኛው የንብረት ባለቤትነት፣የልጅ ማሳደጊያ ቀለብ ፣የመስራት፣የመማርና ድህንነቱ በተጠበቀ ቦታ የመኖር መብትን ስለሚያካትት ከሰብአዊ መብት ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

''ህፃናት ፣ ሴቶች ፣ አካል ጉዳተኞች በተለይም መስማት የተሳናቸው ወገኖች  ጠበቃ ለመቅጠር የማይችሉ የእድሜ ባለፀጎች ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ይገባቸዋል'' ብለዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አማኑኤል አሰፋ ''ረቂቅ ህጉ በፍትህና በዳኝነት ዘርፍ በሚሰሩ ተቋማትና ግለሰቦች፤በክልሉ ምክር ቤት ታይቶ አዋጅ ሆኖ ቢወጣ ተመራጭ ይሆናል '' ብለዋል።

ከአዋጅ ባነሰ ደረጃ  ከወጣ ሁሉንም የፍትህና የዳኝነት  አገልግሎት ሰጪ  ሴክተሮች ላያካትት እንደሚችል ጠቁመው ድጋፉ ለጠበቆች መክፈል ለማይችሉ ሁሉ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ከክልሉ ፍትህ ቢሮና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተወጣጡ ምሁራንና የህግ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል። 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2009 ኢትዮጵያ ሳተላይት ለማምጠቅ የሚያስችላትን ዝግጅት አጠናቅቃ ፈቃድ እየጠበቀች መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የበላይ ጠባቂ አቶ ተፈራ ዋልዋ ተናገሩ። 

በኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ ዘርፉን በበላይነት የሚመራ የኢትዮጵያ ኤሮስፔስ ኢኒስቲትዩት መቋቋሙንም ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው የሶሳይቲው 11ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።      

አቶ ተፈራ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አገሪቱ ሳተላይት ወደ ህዋ ለማምጠቅ በቂ ደረጃ ላይ ደርሳለች።         

ሳተላይቱን ወደ ማምጠቅ ሥራው ለመግባት ከአሜሪካ፣ ከሩሲያ ፣ ከጀርመን፣ ከቻይናና ጃፓንን ከመሳሰሉ በመስኩ የላቀ ሚና ካላቸው አገራት ፈቃድ እየተጠባበቀች ነው ብለዋል።       

''ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሳተላይት የማምጠቅ አቅሙ አላት'' ያሉት የበላይ ጠባቂው ለተግባራዊነቱ በዘርፉ አቅም ካላቸው አገራት ጋር ተባብሮ ለመስራት ስምምነት መፈረሙን ጠቅሰዋል።         

እስራኤል፣ ቻይናና ኮሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ከተፈራረሙ አገራት መካከል ናቸው።    

በመስኩ የሰው ኃይል ለማብቃትም ከአሜሪካው የጠፈር ምርመር /ናሳ/ ጋር ስምምነት በመደረጉ ተማሪዎች ስልጠና እየወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።        

በእንጦጦ የህዋ ሳይንስ ምርምር ጣቢያ በመቋቋሙም ሰልጣኞች እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረግ በዘርፉ ባለሙያዎችን የማፍራት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅትም በምርምር ጣቢያው ከ40 በላይ ባለሙያዎች ስልጠና እየወሰዱ መሆኑን አስረድተዋል።                   

በጅማ፣ በባህዳርና ሌሎች ዩኒቨርስቲዎችም የህዋ ሳይንስ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።  

''የህዋ ሳይንስ የእብድ ሥራ ሳይሆን የልማት መሳሪያ ነው'' ያሉት አቶ ተፈራ በመስኩ የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት የአመለካከት ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።          

አገሪቱ የራሷን ሳተላይት ማምጠቋ ለደህንነት፣ አሸባሪን ለመዋጋት ሠላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል። 

ለግብርና ልማት፣ የግድቦች ግንባታና የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ወሳኝ ሚና እንዳለው የተናገሩት አቶ ተፈራ በዚህ በኩል አገሪቱ የምታወጣውን በርካታ ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስቀር አስረድተዋል።           

መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ ትልቅ ትኩረት መስጠቱን የገለጹት የበላይ ጠባቂው ዘርፉን በበላይነት የሚያስተዳድር ኤሮ ስፔስ ኢኒስቲትዩት መቋቋሙንም ጠቁመዋል።   

ኢኒስቲትዩቱ በዘርፉ የሚወጡ አዋጆችን ተፈጻሚነት ከመከታተል ጀምሮ ስልጠናዎችና የሳተላይት ግንባታ ጉዳዮችን በበላይነት የሚያስተባብር ነው።  

በዚሁ መሰረት ኢኒስቲትዩቱ በተያዘው ዓመት መቋቋሙንና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ምክር ቤት እንዲኖረው መደረጉ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ማሳያ እንደሆነ ነው ያብራሩት።         

ኢኒስቲትዩቱ አስፈላጊው የሰው ኃይል ተመድቦለት በተደራጀ መልኩ ወደ ሥራ መግባቱንም አቶ ተፈራ ተናግረዋል።    

የሶሳይቲው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብነት እዝራ በበኩላቸው ከምድር ውጪ ያለው የህዋ ዓለም ምን እንደሚመስል የሚያሳይ /ፕላኒተሪየሞች/ ''የስፔስ ቲያትር'' ለመገንባት የአዋጭነት ጥናት መጀመሩን ገልጸዋል።   

የባህዳር ዩኒቨርስቲ የአዋጭነት ጥናቱን እያካሄደ መሆኑን ጠቁመው አዲስ አበባን ጨምሮ በአምስት ክልሎች ግንባታውን ለማከናወን እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

የፕላኒተሪየሞቹ መገንባት ኅብረተሰቡ ስለ ህዋ ያለውን ግንዛቤ በማስፋት አገሪቱ ከመስኩ የሚኖራትን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድገው አብራርተዋል።   

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ በ1996 ዓ.ም ነው የተቋቋመው። 

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2009 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም ለቱሪስቱ የሚደረገው ጥንቃቄና የፀጥታ ሁኔታ የተሻለ መሆኑን የሚያረጋግጥና በእነርሱም ዘንድ መተማመን የሚፈጥር ነው ሲሉ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ያዕቆብ መላኩ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት የአዋጁ ለቀጣይ አራት ወራት መራዘም በአገሪቱ ለቱሪስቶቹ የነበረው ጥንቃቄና ፀጥታ አሁን በአንጻራዊ መልኩ መኖሩን የሚያረጋግጥ ነው።

በቱሪስቶቹ ዘንድም መተማመንን የሚፈጥር ነው ብለዋል አቶ ያዕቆብ።

በሌላ በኩል የአዋጁ መራዘም ቱሪስቶች የሚገዙትን የሕይወት መድህን ከፍ እንዲል በማድረግ ፍሰቱን የመቀነስ አዝማሚያ ሊኖር ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ይሁንና ካለፉት ስድስት ወራት ጋር ሲነጻጸር ቀጣይ ሶስት ወራት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች ፍሰት የሚቀንስበት ወቅት በመሆኑ በኢንዱስትሪው ላይ ያን ያህል ጉዳት ላያደርስ ይችላል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘሙ ለቱሪስቶች ደህንነት ስጋት አይሆንም ያሉት ደግሞ የሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ዜናዊ መስፍን ናቸው።

አገራችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ብትሆንም ሰላምና ጸጥታው ስጋት ላይ የሚጥል አለመሆኑን ለመግለጽ በግልም በማህበርም እንቅስቃሴ እያደረግን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል ከድር ደግሞ በሚቀጥሉት አራት ወራትም ቢሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ድርጅቱ የቱሪስት ፍሰቱ እንዳይቀንስ ነባራዊ ሁኔታውን በኦንላይን የማሳወቅ ስራውን ይቀጥላል ነው ያሉት።

"የቱሪስት ፍሰቱ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በዚህ ዓመት ያሳየው መቀነስ መጠነኛ የሚባል ነው፤ ከዚህ አንጻር ጉዳቱም ከፍተኛ አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪስት አገልግሎቶች ብቃት ማረጋገጥ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርበው በበኩላቸው አዋጁ ቢራዘምም ቱሪስቶች የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ እየተረዱ ነው ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ኢትዮጵያን ጎብኝተው የተመለሱ ቱሪስቶችም በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ስለመኖሩ ምስክርነታቸውን እየተሰጡ መሆኑን በመግለጽ።

በ2008 በጀት ዓመት ኢትዮጵያን የጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር 916 ሺህ ሲሆን በዚህ ዓመት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቱሪስቶች አገሪቱን እንደሚጎበኙ ነው ሚኒስቴሩ በዕቅዱ ላይ ያሰፈረው።

Published in ማህበራዊ

 አዲስ አበባ መጋቢት 30/2009 "አዲሱ የግብርና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም" የኢትዮጵያን ግብርና በማዘመን ምርትና ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስትሩ ገለጹ።

ሚኒስቴሩ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን መጨረሻ 500 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅዷል።

"የኢትዮጵያ ግብርና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም" የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የነበረ ቢሆንም አሁን በተጨባጭ ተግባራዊ ለማድረግ ዝርዝር አላማ፣ ግቦችና የአፈፃፀም መመሪያዎች ተቀምጠውለታል።

የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ በሚያዘምኑ ዋና ዋና ስትራቴጂዎችና የአፈፃፀም ስልቶች ዙሪያ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና እና አርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢያሱ አብርሃ እንዳሉት፤ ስትራቴጂው በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎሜሽን እቅድ በስምንት በመቶ እያደገ ያለውን ግብርና በእቅድ ዘመኑ በእጥፍ ማሳደግ ያስችላል።

የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ስራዎችን ማጎልበት እንዲሁም የዘርፉን ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት የማስፈፀም አቅም መገንባት የእቅድ ዘመኑን ለማሳካት የተያዙ የስትራቴጂው ቁልፍ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ምርትና ምርምታማነት ለማሳደግና የእቅድ ዘመኑን ግብ ለማሳካት ለግብርናው በተቀመጡ ስትራቴጂዎች ላይ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ስትራቴጂውን ተግባራዊ በማድረግ በግብርናው ዘርፍ እመርታ ለማምጣትና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ እንዲሁም አርሶአደሮችና አርብቶአደሮች በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ዶክተር ኢያሱ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ኤክስቴንሽን አሶሴሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጭምዶ ሀንጫላ አገሪቱ የምትከተለውን የግብርና ፖሊሲ ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ አጋጣሚ ነው ይላሉ።

"በተፈጥሮ ኃብት አጠቃቀም፣ በአፈር አያያዝ፣ በአየር ንብረት ጥበቃ እንዲሁም በሴቶችና ወጣቶች ላይ ያለብንን የአፈፃፀም ችግሮች በዚህ የኤክስቴንሽን ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ አለብን" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

የምግብ ሰብሎችን ምርታማነት ማሳደግ፣ ገበያ መር የአመራረት ስርዓት፣ የልማት ቀጠናዎችን መሰረት ያደረገ የግብርና ልማት መከተል ግብርናውን ማዘመን የሚያስችሉ የስትራቴጂው ግቦች ናቸው።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ካሴ በሪሁን ግብርናውን በማዘመን የአርሶአደሮችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ያስችላል ብለዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር መጋቢት 30/2009 በአማራ ክልል በመጭው መኸር ጥቅም ላይ የሚውል ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለማሰራጨት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው የግብዓት ግብይት፣ አቅርቦትና ስርጭት ክትትል ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ጌታቸው አሊጋዝ  ለኢዜአ እንደገለጹት የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት በአሁኑ ወቅት  ምርጥ የሰብል ዘር የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡

እስካሁንም ከ132 ሺህ ኩንታል የሚበልጥ የበቆሎ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ጤፍና ሌሎች ምርጥ የሰብል ዘር የማሰባሰብ ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

ከተሰበሰበው ምርጥ ዘር ውስጥም ከ80 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው ከአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የተገኘ ሲሆን ቀሪው በዩኒዮኖችና በግል ከሚያባዙ አርሶ አደሮች የተሰበሰበ  ነው።

ምርጥ ዘሩን በህብረት ስራ ማህበራት በኩል ወቅቱን ጠብቆ በማቅረብ ለማሰራጨት የሚያስችል ቀልጣፋ አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

እስካሁን ያልተሰበሰበውን ከ69 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር በቀሪው ጊዜ አሰባስቦ ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተለይም በየዓመቱ ውል ይዘው ዘር የሚያባዙ አርሶ አደሮች የራሳቸውን ዘር በበቂ ሁኔታ ከመሸፈን ባሻገር ትርፉን ለማህበራትና ዩንየኖች በማቅረብ ተጠቃሚነታቸው እያደገ እንዲመጣ አስችሏል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ ዳጊ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አድጎ ዘውዱ ምርጥ ዘር መጠቀም ከጀመሩ አምስት ዓመት እንደሆናቸው ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የአካባቢ ዘርን ተጠቅመው ከሚያለሙት የበቆሎ ማሳ በሄክታር ያገኙት የነበረው ከ30 ኩንታል ያልበለጠ ምርት አሁን ላይ ምርጥ ዘርና የተሟላ ግብዓት ተጠቅመው በማልማት ምርታቸው ከእጥፍ በላይ ማደጉን ገልጸዋል።

ምርጥ ዘር ተጠቅመው በማልማት የበቆሎ ምርታቸውን በሄክታር ከ25 ወደ 70 ኩንታል፤ የስንዴን ደግሞ ከ28 ወደ 40 ኩንታል ማሳደጋቸውን የገለጹት ደግሞ በወንበርማ ወረዳ የማር ወለድ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ባዩ ተጃረ ናቸው።

የተሻለ ምርት በማግኘት ተጠቃሚ እየሆኑ በመምጣታቸውም በመጭው የመኽር ወቅትም ሁሉንም የእርሻ ማሳቸውን ምርጥ ዘርና በቂ ግብዓት ተጠቅመው ለማልማት መዘጋቸታቸውን አርሶ አደሮቹ አስረድተዋል።

ባለፈው የምርት ዘመን በክልሉ ከ200 ሺህ ኩንታል የሚበልጥ ምርጥ ዘር ለተጠቃሚ አርሶ አደሮች ቀርቦ ጥቅም ላይ መዋሉን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያስታውቃል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን