አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 07 April 2017

መቀሌ መጋቢት 29/2009 የትግራይ ክልል ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤውን የፊታችን ማክሰኞ መጋቢት 4/2009 ዓ.ም. እንደሚያካሒድ ስታወቀ።

በምክር ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና የኮንፈረንስ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ታረቀ እንደገለጹት ጉባኤው የክልሉን ተጨማሪ በጀትና የአዳዲስ ዳኞችን ሹመት ያጸድቃል ።

ከዚህ በተጨማሪም ጉባኤው ሌሎች አዋጆችንም ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ፖለቲካ

ነቀምቴ መጋቢት 29/2009 በተሃድሶ የተለዩ ችግሮችን በማቃለል በሁሉም መስክ የተመዘገቡ ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የወለጋ ዩኒቨርሲቲና የነቀምቴ መምህራን ኮሌጅ የኦህዴድ አባላትና ደጋፊዎች አስታወቁ።

የተቋማቱ መምህራንና ተማሪዎች 27ኛውን የኦህዴድ የምስረታ በዓል "እየተማርን እንታደሳለን እየታደስን እናስተምራለን" በሚል መሪ ቃል ትናንት በነቀምቴ ከተማ አዳራሽ አክብረዋል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት  የጋዜጠኝነት ተማሪ  ማርታ አብዲሳ እንደገለጸችው ድርጅቱ በተሃድሶ መድረክ የለያቸውን ችግሮች ጊዜ ሳይሰጥ ለመፍታት በሚያደረገው ጥረት የድርሻዋን ለመወጣት ተዘጋጅታለች።

በተለይ ግለኝነት፣ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር እጦት የሰላምና የልማት ደንቃራ ስለሆነ በአፋጣኝ ለማስወገድ መስራት እንደሚገባም ተናግራለች።

በዩኒቨርሲቲው የአንደኛ ዓመት የጂኦሎጂ ተማሪ ዘውድነሽ ተገኑ በበኩሏ እንደገለጸችው ድርጅቱ ለኦሮሞ ህዝብ ነፃነትና መብት ታግሎ ያታገለ በመሆኑ የምስረታ በዓሉ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው።

የነቀምቴ መምህራን ኮሌጅ ተማሪ ጋሮማ ቀነዓ ኦህዴድ ከዚህ ቀደም የኦሮሞ ሕዝብ ምኞትና ፍላጎት የነበረውን የራሱን ቋንቋ፣ታሪክ፣ባህልና ወግ የማሳደግ መብቱን ያረጋገጠ ድርጅት ነው።

የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተልዕኮውን   ለማሳካት በጥልቅ ተሃድሶ  የተለዩ ችግሮችን በመፍታት  የተመዘገቡ  ስኬቶች  ቀጣይነት  እንዲኖራቸው ለማድረግ የበኩሉን እንደሚወጣም ተናግሯል።

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ እሱባለው ዳባ እንደገለጹት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተማሪዎች የአገልጋይነት መንፈስን ለማረጋገጥና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን ለመታገል ከፍተኛ ሚና አላቸው ።

በመሆኑም የድርጅቱን ተልዕኮና ራዕይ ከግብ ለማድረስ በሚሰሩበት ተቋም የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የላብ አደሮች፣ የትምህርት ተቋማት አደረጃጀትና ፖለቲካ  ዘርፍ ሃላፊ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ እንዳስታወቁት የዘንድሮውን በዓል ልዩ የሚያደርገው በተሃድሶ ለተለዩ ችግሮች ፈጣን መልስ እየተሰጠ ባለበት ወቅት የሚከበር መሆኑ ነው።

ሕዝቡ ከድርጅቱ ፈጣን ምላሽ ስለሚጠብቅም የጸረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ ተጋግሎ በውጭና በአገር ውስጥ ያሉ  ፀረ-ሰላም ሃይሎች የሀሰት አጀንዳ የተደፈቀበት ወቅት መሆኑንም አስረድተዋል።

ህብረተሰቡ ለድርጅቱ የሚያቀርባቸውን ጥያቄዎች መመለስ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን በመረዳት አባላቱና ደጋፍዎቹ ከድርጀቱ ጎን በመቆም የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

በበዓሉ ላይ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ተወካዮች በመገኘት ለኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት አጋርነታቸውን አሳይተዋል።

Published in ፖለቲካ

ነቀምቴ መጋቢት 29/2009 በምስራቅ ወለጋ ዞን በሕብረተሰቡ ተሳትፎ ከ143 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ሥራ መካሄዱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ብሩክ ጫላ እንደገለጹት የዘንድሮው የበጋ ወራት የልማት ሥራው የተካሄደው በተመረጡ 297 ተፋሰሶች ላይ ነው።

ተፋሰሶቹ በሚገኙባቸው 17 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 286 የገጠር ቀበሌዎች 14 ሺህ ሄክታር በሚሸፈን መሬት ላይ የተለያዩ የስነአካላዊ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

በዞኑ ከጥር አጋማሽ ጀምሮ ለ30 ቀናት ከተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች መካከል 76 ሺህ ኪሎ ሜትር የእርከን ሥራ፣ የውሃ መፋሰሻ ቦዮች ቁፋሮ፣ እርጥበት ማቆያ ስትራክቸሮች ይግኙበታል።

ከዚህ በተጨማሪ ከ33 ሺህ 453 ሄክታር የሚበልጥ መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ተከልሎ እንዲያገግም በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘውዴ መኮንን በበኩላቸው፣ በዞኑ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በየዓመቱ በአማካይ በ300 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራ ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል።

በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው በመሳተፍ ላይ ከሚገኙት 376 አርሶአደሮች መካከል 115 ሺህ 620 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ በአካባቢ ጥበቃ ሥራው ከጥቅም ውጭ የሆኑ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙና እንዲለመልሙ እየተደረገ ነው።

ባለፉት ዓመታት ጠንካራ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በመከናወኑ የዞኑ የደን ሽፋን ከዘጠኝ በመቶ ወደ 13 በመቶ ማሳደግ ተችሏል።

በየጊዜው የሚከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች እንዳይበላሹም ሕብረተሰቡ በኃላፊነት ስሜት ተረክቦ ተገቢውን ጥበቃና ከለላ እያደረገ መሆኑን አቶ ዘውዴ አስረድተዋል።

የተፋሰስ ልማት ሥራ በተካሄደባቸው አካባቢዎች በቂ ውሃና የግጦሽ ሣር ማግኘት በመቻሉ በበጋ ወራት ሲያጋጥም የነበረውን የውሃና መኖ እጥረት ለማቃለል እንደተቻለም አስረድተዋል።

ለመስኖ ልማት ሥራው ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ነው የገለጹት።

በቦነያቦሼ ወረዳ የጀዊስ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ጌታሁን ከበደ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የተፋሰስ ልማት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ችግኞች በብዛት በመተከላቸው የተራቆቱ መሬቶች ልምላሜ እየተላበሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች የአፈር መከላትን ከመከላከል ባለፈ የደረቁ ምንጮች መልሰው እንዲፈልቁ በማድረጋቸው ለእንሰሶቻቸው በቂ ውሃና ሳር በቀላሉ በማግኘት እየቻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህም በቀጣይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራቸውን አጠናክረው ለማስቀጠል አንዳነሳሳቸው ነው የገለጹት።

በጊዳ አያና ወረዳ የአንዶዴዲቾ ቀበሌ አርሶአደር ፈይሣ ዱሬሣ በበኩላቸው የተፋሰስ ልማቱ ካስገኘው ውጤት መካከል ጠፍተው የነበሩና ለምርምር ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው እንደ ግራዋ፣ ዶቅማና ሌሎች አገር በቀል ዛፎች መልሰው እንዲበቅሉ ማድረጉን ተናግረዋል።

በዚህም እርሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው አርሶአደሮች ከመደበኛው የእርሻ ሥራቸው በተጓዳኝ  በንብ ማነብ ሥራ ላይ በመሰማራት ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በምስራቅ ወለጋ ዞን ባለፉት አምስት ዓመታት 721 ሺህ 706 ሄክታር መሬት ላይ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ መከናወኑ ተገልጿል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 29/2009 የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገነባቸውን ሶስት የአውሮፕላን ጥገናና ቀለም መቀቢያ ሼዶች ሊያስመርቅ ነው።

ሼዶቹ አየር መንገዱን በ21ኛው ከፍለ ዘመን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በንቃት መሳተፍ ያስችላሉ ተብሏል።

ትልቁን ቦይንግ 1-B747-8OO አውሮፕላን ማስተናገድ የሚችለውን ጨምሮ ቢሮዎችና የተለያዩ ሱቆች የተሟሉላቸው ሼዶቹ ከሚያዚያ 3-6 ቀን 2009 ዓ.ም በሚካሄደው ዓለም ዓቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ሲምፖዚየም ለምረቃ ይበቃሉ።

ሼዶቹ አውሮፕላን ቀለም መቀባትና ሙሉ ጥገና ማከናወን በሚያስችል መልኩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጁ መሆናቸው ተነግሯል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ለ2025 የአየር መንገዱ ራዕይ ስኬት የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ዋናው ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

አየር መንገዱ የጀመረውን ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠል በ115 ሚሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ግንባታ እያከናወነ መሆኑን አስታውሰዋል።

የተገነቡት ሼዶችም አየር መንገዱ ራሱን እንዲችል በማድረግ በ21ኛው ከፍለ ዘመን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በንቃት መሳተፍ ያስችሉታል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት ለአስካይ፣ ለማላዊ፣ ለሩዋንዳ ኤይር፣ ለኮንጎ ኤይር ዌይስ፣ ለሴይባ ኢንተርኮንቲኔንታል ካም ኤይር-ኮ እና ለጃምቦ ጀት አየር መንገዶች ሙሉ የጥገና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አየር መንገዱ እያስገነባው የሚገኘው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ግንባታ 40 በመቶ መድረሱንም አቶ ተወልደ አክለዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ፍቼ   መጋቢት 29/2009 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የተሻሻሉ የወተት ላም  ዝርያዎችን የተጠቀሙ አርሶ አደሮች ገቢያቸውን በማሳደግ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለፁ፡፡

 በየቀኑ  ከ27ዐ ሺህ ሊትር በላይ ወተት ተመርቶ ለገበያ እንደሚቀርብ የዞኑ እንስሳትና አሣ ሀብት ልማት ጽፅፈት ቤት ገልጿል ፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የውጫሌና ግራር ጃርሶ ወረዳ አርሶ አደሮች  እንደገለፁት የተሻሻሉ የወተት ላሞችን ማርባት ከጀመሩ ወዲህ ከወተት፣ ወተት ተዋጽኦ ሽያጭ በሚያገኙት ገቢ ኑሮአቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡

የውጫሌ ወረዳ አርሶ አደር ኑሬ አብሩ እንደገለፁት ከዚህ ቀደም የአካባቢ ዝርያዎችን በመጠቀም የሚያገኙት የወተት ምርት ከራሳቸው  ፍጆታ የማያልፍ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከተለያዩ የምርምር ማዕከላት የተገኙ ምርጥ የላም ዝርያዎች በመጠቀማቸው ከልፋታቸው ጋር የተመጣጠነ ወተት በማግኘት ተጠቃሚ ሆነዋል ።

ከአንድ ላም በየቀኑ የሚያገኙትን እስከ 35 ሊትር የሚደርስ ወተት ለእድገት ወተት አቅርቦት ማህበር በማስረከብ በወር ከ6 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኙ ገልፀዋል፡፡

የተሻሻሉ የወተት ላሞችን መጠቀም ከጀመሩ አራት ዓመት እንደሆናቸው የሚናገሩት የዚህ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ፅጌ አበበ በበኩላቸው የግብርና ባለሙያዎች ምክር መቀበል በመቻላቸው የተሻለ ውጤትና ገቢ እንዳስገኘላቸው ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም መላ ቤተሰባቸውን በማስተባበር በየቀኑ ከ 6 ላሞች  ከአንድ መቶ ሊትር በላይ ወተት በማምረት በዓመት ከወተት ሽያጭ ብቻ እስከ 15ዐ ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኙ ገልፀዋል፡፡

በዚህም ልጆቻቸውና እራሳቸውን በተረጋጋ የኑሮ ሁኔታ  ከመምራትና ከማስተማር ባሻገር ወደ ከፊል ባለሃብትነት እያመሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የተሻሻሉ የወተት ላሞችን ማርባት ከጀመርኩ ወዲህ ህይወቴ ተለውጧል ያሉት ደግሞ የግራር ጃርሶ ወረዳ የቶርባን አሼ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ድሪባ ወሰኑ ናቸው፡፡

ቀደም ሲል ከአንድ የአካባቢ ዝርያ በቀን የሚያገኙትን ከአራት ሊትር የማይበልጥ የወተት ምርት  የተሻሻሉ ዝርያዎች በማርባት ወደ  25 ሊትር አሳድገዋል፡፡

ይህም ከራሳቸው ተርፎ ለገበያ በማቅረብ  በዓመት እስከ 7ዐ ሺህ ብር ገቢ በማግኘት የተሻለ ኑሮ ለመምራት እንዳስቻላቸው ገልፀዋል፡፡

ለሰባት ዓመታት ካከናወኑት የወተት ሽያጭ ገቢም አይሱዙ የጭነት መኪና ገዝተው አገልግሎት በመስጠት ተጠቃሚ በመሆን  ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በቀን  ከ27ዐ ሺህ ሊትር በላይ ወተት ተመርቶ ለገበያ እንደሚቀርብ የዞኑ እንስሳትና አሣ ሀብት ልማት ጽፅፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ግዛቸው ነጋሹ ገልፀዋል፡፡

ወተቱ ለገበያ የሚቀርበው በማህበር በተደራጁ ወተትና የወተት ተዋፅኦ  አምራቾችና አርሶ አደሮች አማካኝነት ነው፡፡

ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ ከ72 ሚሊዮን ሊትር በላይ ወተት በማምረትና በልዩ ልዩ መልክ በማቀነባበር ካመረቱት ምርት ሽያጭ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ጽህፈት ቤቱ ለአካባቢው ወተት አምራቾችና አርሶ አደሮች የወተት ምርት ለማሳደግ በተመጣጣኝ ዋጋ የተሻሻሉ ጊደሮች፣ መድሃኒትና መኖን በማስተዋወቅና በማከፋፈል ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ዓመት ብቻ 56 ሺህ የሚጠጉ ከብቶችን በሰው ሰራሽ ዘዴ የማዳቀል ሥራ መስራቱን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአምራቾቹ የሚነሳው የወተት ዋጋ ማነስና የገበያ ችግር ለማስወገድ የሚያስችል የተሻለ አማራጭና አደረጃጀት ለመመስረት ጥናት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የቢፍቱ ሰላሌ የወተት አምራቾች ሕብረት ሥራ ዩኒየን ተወካይ አቶ ተስፋዬ ጉቱ እንደገለፁት አምራቾቹ በመደራጀታቸው ከዚህ ቀደም በገበያ እጦት ምክንያት ይባክን የነበረው ምርታቸው የተሻለ ዋጋ እያገኘ ነው፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ሰመራ መጋቢት 29/2009 እያደገ የመጣውን የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና እደገት ፓኬጅ ዙሪያ ከወረዳና ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር የአንድ ቀን ውይይት ትናንት በሰመራ ከተማ አካሂዷል።

በውይይት መድረኩ ላይ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ ርስቱ ይርዳው እንደተናገሩት መንግስት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማረጋገጥ ያወጣቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በአግባቡ ተግባራዊ በተደረገባቸው አካባቢዎች ስኬታማ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

ይሁንና ከጊዜው ጋር እየተለወጠና እያደገ የመጣውን የወጣቶች ፍላጎት ለመመለስ ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ አዲስ የለውጥና የዕድገት ፓኬጅ በመቅረጽ ወደሥራ መግባት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ በአዲሱ የወጣቶች የለውጥና እድገት ስትራቴጂ በዋናነት ለወጣቶች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ መረጋገጥ ምቹ ሁኔታዎችንና መድረኮችን በየደረጃው መፍጠር ትኩረት ተሰጥቶታል።

በተጨማሪም ወጣቶችን ለማብቃት በየደረጃው የወጣቶችን አደረጃጀቶች በማጠናክርና ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን የበለጠ አጎለበተው እንዲቀጥሉ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

"ለዚህም ከቀበሌ ጀምሮ በየደረጃው ከወጣቱ ጋር ግንኙነት የሚደረግበት ቋሚ መድረክ አመራሩ ሊፈጥር ይገባል" ብለዋል። 

ይህም በየጊዜው እያደገ የሚመጣውን የወጣቶች ኢኮኖሚዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች በየደረጃው እንዲፈቱ በማድረግ ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር በበኩላቸው እንዳሉት፣ ባለፉት 15 ዓመታት አርብቶአደር ወጣቶች በክልሉ ለተመዘገቡ ሁለንተናዊ ልማትና ዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ከመሪው ፓርቲ አብዴፓ እና ከክልሉ መንግስት ጎን በመሆን ጉልህ ሚና ሲያበረክቱ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣም ይህን አስተዋጿቸውን አጎልብተው እንዲቀጥሉና ከዕድገቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በክልሉ በኩል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ወጣቶችን በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ ለማድረግ ሥራአጥ ወጣቶች እንዲለዩ መደረጉንና መንግስት ለክልሉ የመደበውን 206 ሚሊዮን ተዘዋዋሪ ፈንድ ለወረዳዎች በመደልደል ወደተግባር እየተገባ መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት ተሳታፊዎች ከስራዕድል ፈጠራና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ያሏቸውን ጥያቄዎች አንስተዋል።

ወለድ ከአፋር ባህልና እምነት ጋር የሚጋጭ መሆኑ ወጣቶቹ የፈንዱ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እንቅፋት ሊሆን ስለሚችል ምን የተሳበ ነገር አለ? አርብቶአደሩ ሕብረተሰብ በተለያየ ጊዜ በድርቅ የተጠቃ በመሆኑ ወጣቶች ወደሥራ ለመሰማራት የሚያስፈልጋቸውን 10 በመቶ ቅድሚያ ለመቆጠብ አይቸገሩም ወይ? ወጣቶች ወደሥራ ከገቡ በኋላ ምን አይነት የቴክኒክ ድጋፍ ይደረግላቸዋል? ወደሥራ ለመሰማራት ቀድሞ የንግድ ዕቅድ ማውጣት የግድ ነው ወይ? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን በመድረኩ ላይ አቅርበዋል።

ለተነሱ ጥያቄዎች ሚኒስትሩ ምላሽ ሲሰጡ እንዳብራሩት ለአፋርና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች የገንዘብ ብድር ከወለድ ነጻ በሆነ አግባባ የሚሰጥበት ሁኔታ ተመቻችቷል።

አሥር በመቶ ቀድመው መቆጠብ የማይችሉ ወጣቶች ብዙ ገንዘብ በማይጠይቁ የሥራ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ ክፍተቱን መሙላት እንደሚቻልና ወጣቶችም በዋናነት አንችልም የሚለውን አመለካከት ማስወገድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የንግድ ዕቅድ ማዘጋጀትና የክትትልና ድጋፍ ስራን በተመለከተ ከሰመራ ዩኒቨርሲቲና ከተማሩ የአርብቶአደር ልጆች ጋር በቅንጅት መስራት ከተቻለ ሥራውን ወጤታማ በሆነ መንገድ ማከናወን እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በሰመራ ከተማ ለአንድ ቀን በተካሄደው ውይይቱ ላይ ከ32ቱ የክልሉ ወረዳዎችና ከአምስት የዞን መስተዳደሮች እንዲሁም ከሴክተር መስሪያቤቶች የሥራ ኃላፊዎች መሳተፋቸው ተገልጿል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 29/2009 ሩዋንዳ ሁለንተናዊ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ለማምጣት የምታደርገው ጥረት ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ምሳሌ እንደሚሆን የአፍሪካ ኅብረት አስታወቀ።

ኢትዮጵያ በበኩሏ ከአፍሪካ አገሮች ጋር በመሆን በአህጉሪቷ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዳይፈጸም ለማድረግና ወንጀለኞችንም ለሕግ በማቅረብ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደምተሰራ ገልጻለች። 

በሩዋንዳ የተፈጸመውን የዘር ጭፍጨፋ 23ኛ ዓመት የመታሰቢያ ቀን በአፍሪካ ኅብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተከብሯል።

በሩዋንዳ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1994 በተፈጸመ የዘር ጭፍጨፋ በመቶ ቀናት ውስጥ ከ800 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎቿ ህይወታቸው አልፏል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሞሳ ፋኪ ማሃማት በምክትላቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት፤" በአሁኑ ወቅት በሩዋንዳ የሚታየው ለውጥ የመምራትና የማስተዳደር ስኬት ማሳያ ነው" ብለዋል።

በአገሪቷ ሕዝቦቿ በጋራ እንዲኖሩ፣ ማኅበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን ሁለንተናዊ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት እንዲመጣ እየተደረገ ያለው ሥራ የሚያበረታታ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ይህም ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን በመግለጽ።

በአገሪቷ ለተመዘገቡት ለውጦች የፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ድርሻው የጎላ መሆኑን ተናግረው፤ ለዚህም “ኅብረቱ ምስጋና ያቀርባል” ነው ያሉት።

ለእድገቱ የወጣቱ ሙሉ አቅም ወደ ልማት እንዲቀየር በማድረግ በአገሪቷ የተፈጠረው መልካም አስተዳደር ሥርዓትም ሌላኛው የስኬቱ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የሩዋንዳ አምበሳደር ሆፕ ቱምኩንዴ ጋሳቱራ በበኩላቸው፤ ብዝኃነትን በአዎንታዊ መልኩ መቀበል ልማት ለማምጣት የሚያስችሉ መሰረታዊ ሁኔታዎች ናቸው።

ከዚህ ጎን ለጎን አገሮች በተለይም ግጭት የሚቀሰቅሱ ግለሰቦችን ተጠያቂ የሚያደርግ “ሥርዓት ለመዘርጋት መሥራት ይኖርባቸዋል” ብለዋል።

በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የጥላቻ አልያም ደግሞ ግጭትን የሚያባብሱ ጽሁፎችና ምስሎችን እንዲሁ በትክከለኛ መንገድ መመከት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

ኢትዮጵያ የዘር ጭፍጨፋ እንዲቆም ከማድረግ በዘለለ በአሁኑ ወቅትም ከአገሪቷ መንግሥት ጎን በመሆን እያደረገች ያለው ድጋፍ ምስጋና ሊቸረው እንደሚገባ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በተወካያቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰብዓዊ መብት  ለማረጋገጥ በትኩረት ትሰራለች።

ይህንም ለማድረግ በቅድሚያ በሰዎች ላይ የሚፈጸሙትን ኢ-ሰብዓዊ ደርጊቶች ለማስቆም በመረባረብ ያላትን አጋርነት በማሳየት እንደምታረጋግጥ ነው ያመለከቱት።

ይህም ብቻ ሳይሆን ወንጀል የሚፈጽሙ ግለሰቦችንም ተጠያቂ በማደረግ ለሕግ እንዲቀርቡ ትሰራለች ነው ያሉት።

በመታሰቢያ በዓሉ ላይ በርካታ የዲፕሊማቲክ ማኅበረሰብ አባላት የተገኙ ሲሆን፤ በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የህሊና ጸሎት ተደርጓል።

Published in ፖለቲካ

ሃዋሳ መጋቢት 29/2009 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ትስስር በመፍጠር ለአገራዊ አንድነት መጠናከር አስተዋፆ ማድረጉን የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የሃገር ሽማግሌዎች ገለፁ ፡፡

"የአገር ሸማሌዎች በበኩላቸው ወጣቱ በግድቡ ግንባታ የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም የጀግንነት ታሪካችንን በድህነት ላይ መድገም ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል፡፡

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር  ሚልኪያስ ባሳ ለኢዜአ እንደገለጹት የህዳሴ ግድብ በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል የነበረውን ትስስርና መደጋገፍ ያጠናከረ ፕሮጀክት ነው፡፡

ግድቡ በራስ ጉልበትና አቅም የሚሠራ ብሄራዊ ፕሮጀክት መሆኑም አገራዊ አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከር አስተዋፆ ማድረጉን ተናግዋል ።

ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳውም  የላቀ መሆኑን  ገልፀዋል ።

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ በዚህ ዓመት የ13 ሚሊዮን ብር ቦንድ ለመግዛት በገቡት ቃል መሰረት ተፈፃሚ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል ።

ብሄር ብሄረሰሰቦችና ህዝቦች የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሰገንዝበዋል ።

"ምሁራን ጥናትና ምርምር በማድረግ ለግድቡ ግንበታ ዘላቂት የሚጠበቅባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል"ብለዋል ።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃኑ ኩማ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ አሻራውን ያሳረፈበት በመሆኑ ለብሄራዊ አንድነት መጠናከር ትልቅ አስተዋፆ ያበረከተ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"የግድቡ ግንባታ የአገር በቀል ሃብት መጠቀምን መነሻ ያደረጉ ትላልቅ መሰረተ ልማቶች ለማካሄድ መነሳሳት የፈጠረ ነው " ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል ከመፍጠርና የቁጠባ ባህልን ከማጎልበት ባለፈ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሀይል በማመንጨት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

እንደ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገለፃ ግድቡ የተፈጥሮ ሃብት እንዲጠበቅ በማድረግ፣ ለቱሪዝም ዘርፍ ባለው ጠቀሜታ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ ነው ።

"ግድቡ የኤሌክትሪክ ሃይል ለውጭ አገራት በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት በተጨማሪ አገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዳስትሪ ዘርፍ  ለመሸጋገር የሚደረገውን ስትራቴጂ ለማሳለጥ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው " ብለዋል።

"የሀገር ሸማግሌዎች በበኩላቸው  ወጣቱ ግድቡ የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም ቀደምት የምንታወቅበትን የጀግንነት ታሪክ በድህነት ላይ መድገም  ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል ። 

የወላይታ ዞን የሀገር ሽማግሌ አቶ ተክሌ ታኪሶ በሰጡት አስተያየት የህዳሴ ግድብ  ኢትዮጵያ ቀደምት ወደምትታወቅበት ገናና ታሪክ በድህነት ላይ ለመድገም እያደረገች ያለው ጉዞ የሚያመላክት ነው ።

"አገሪቱ ለአዲስ ትውልድ መፃኢ ዕድል ጥሩ መደላደል እየፈጠረች ትገኛለች፤ ወጣቱም ከአላስፈላጊ ምግባር ታቅቦ አጋጣሚውን በመጠቀም ታሪኳን መድገም አለበት" ብለዋል አቶ ተክሌ  ፡፡

ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ አቶ ሃይለማርያም ሃልቻየ በበኩላቸው ለግድቡ ግንባታ የ150 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

"የግድቡ ግንባታ አሁን ያለበት ደረጃ ይደርሳል የሚል እምነት አልነበረኝም፤ 56 በመቶ መድረሱን ሳውቅ በመንግስት ከፍተኛ እምነት እንዲሁም መነሳሳት ፈጥሮብኛል" ብለዋል ።

"የህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ አገራትም ተምሳሌት በመሆን ብዙ ነገር ያስተምራል" ያሉት አቶ ሃይለማሪያም ወጣቱ ተጠቃሚነቱን በማስተዋል የሚጠበቅበትን ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል ።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 29/2009 ኢትዮጵያ የአፍሪካን ጥቅሞች በሚያስጠብቁ ጉዳዮች እያከናወነቻቸው ያሉ የዲፕሎማሲ ስራዎችን አጠናክራ እንደምትቀጥል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ገለጸ።

ፅህፈት ቤቱ ለኢዜአ በላከው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫው እንዳለው ኢትዮጵያ ለአካባቢያዊና አህጉራዊ ትስስርና የጋራ ጥቅም መረጋገጥ እያካሄደች ያለውን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ አጠናክራ ትቀጥላለች።

በአፍሪካ አገራት መካከል ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ በመካከላቸውም ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት እንዲፈጠር፣ አህጉሪቱ በዓለም መድረክ ተሰሚነት እንዲኖራት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን ጠቁሟል።

በዚህ ረገድ እያደረገችው ያለው ጥረት በአህጉሪቱ ማኅበረሰብ ዘንድ አድናቆትን ያተረፈ ተግባር እንደሆነም መግለጫው ጠቅሷል።

አገሪቷ ለጎረቤት አገራት፣ ለአካባቢያዊ፣ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ሰላምና ልማት መጠናከርም እየሰራች መሆኑና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ትኩረት ባደረገው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እየተሰሩ ያሉት ስራዎች ተቀባይነት እያደገ መምጣቱን መግለጫው አትቷል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ

አገራችን ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅማችንን በማስጠበቅና አገራዊ ህልውናችንን በማረጋገጥ ላይ ያነጣጠረ የውጭ ጉዳይ እና የአገራዊ ደህንነት ፖሊሲ አውጥታ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። ይኸው ፖሊሲያችን በዋነኝነት የሚያጠነጥነው ህዝቦቻችን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እውን በማድረግና ለዚሁ የተመቻቸ ሁኔታን በመፍጠር ላይ መሆኑም ይታወቃል።

ከዚህ አንጻር ከምስራቁም ይሁን ከምዕራቡ ዓለም ጋር ግንኙነታችንን በማጠናከር ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና ለልማት የሚሆን ፋይናንስ ወዘተ በማፈላለግ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የኢኮኖሚ ዲኘሎማሲ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንገኛለን። ፈጣን ልማትን ለማረጋገጥ  ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አኳያም በሀገራችን፣ በአካባቢያችንና በአህጉራችን ብሎም በዓለማችን ዙሪያ ሰላም፣ ፀጥታና መረጋጋት እንዲሰፍን የተቻለንን ሁሉ በመሥራትም ላይ ነን።

አገራችን ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለአጎራባች አገራት፤ ለአካባቢያዊ፣ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ሰላምና ልማት መጠናከርም አበክራ እየሰራች ትገኛለች። ይህም ዓለም አቀፍ አድናቆትና ክብር እንዳተረፈላት አይዘነጋም።

በተለይም በአፍሪካ አገራት መካከል ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ በመካከላቸውም ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር እና የጋራ ተጠቃሚነት እንዲፈጠር ከምታደርገው ጥረት ባሻገር የአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲያገኙና አህጉሪቱ በዓለም መድረክ ተሰሚነት እንዲኖራት እያደረገችው ያለው ጥረት በአህጉሪቱ ማህበረሰብ ዘንድ አድናቆትን ያተረፈ ተግባር ሆኗል።

በዚህ በኩል በተለይም ከአጎራባች አገራት ጋር፡ የህዝቦችን ጥቅም ባስቀደመ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርተን በሰራነው ተግባር አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ እና የአገራዊ ደህንነት ፖሊሲያችን በግልጽ እንዳስቀመጠው፡ በጎረቤት ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት፡ ይልቁንም ለሰላማቸውና ለልማታቸው የሚጠበቅባትን ዋጋ በመክፈል ጭምር ዕምነት የሚጥሉባት ጎረቤት ለመሆን ችላለች፡፡ የኃይል ልማት፣ የመንገድና የባቡር መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት ሀገራቱንና ህዝቦቻቸውን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረትም ከጊዜ ወደጊዜ እያደገና በተገቢው መልኩ ዕውቅና እያገኘ መጥቷል።

በዚህም ከሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኬኒያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ጋር ያለን ግንኙነት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ ከነዚህ አገራትም አልፎ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች  በተለይም ከሩዋንዳና ዩጋንዳ፣ ከታንዛንያና ቡሩንዲ ጋር ያለን ግንኙነት  ጠንካራ ወደሚባል ደረጃ አድጓል፡፡ ከአባይ ወንዝ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋርም ታሪካዊ የሚባል አዲስ ግንኙነት መፍጠር እየተቻለ ነው።

ከነዚህ አገራት ጋር ያለንን በጎ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ሲባልም በመሪዎች ደረጃ ኦፊሴላዊ ጉብኝቶችን የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ለአብነትም ሰሞኑን የጅቡቲና የሱዳን ሀገራት ፕሬዚዳንቶች በአገራችን ያካሄዱት ጉብኝት፣ እንዲሁም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በታንዛኒያ ያካሄዱዋቸው ጉብኝቶችን መጥቀስ ይቻላል።

በአጠቃላይ አገራችን ከራሷ ጥቅም ባለፈ ለአጎራባች አገራት ሰላም ዕድገትና ብልጽግና መረጋገጥ ብሎም ለአካባቢያዊና አህጉራዊ ትስስርና የጋራ ጥቅም መረጋገጥ እያካሄደች ያለውን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ አጠናክራ የምትቀጥለው ይሆናል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 29/2009 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ70 ሚሊዮን ብር ወጪ በስድስት ክልሎች የሕዝብ ጤና ጣቢያዎች ሊገነባ ነው።

ባንኩ ለሚያስገነባቸው ጤና ጣቢያዎች የስራ ማስኬጃ ውል ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የባንኩ ተጠባባቂ የቢዝነስ ልማት መኮንን አቶ ለገሰ ጢቆና የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አሚን አማን ተፈራርመዋል።

አማራ ፣ትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ሶማሌ፣ አፋርና ሀረሪ ጤና ጣቢያዎቹ የሚገነቡባቸው ክልሎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማኅበራዊ ተቋማት ክፍተቶችን በመሙላት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ አቶ ለገሰ ተናግረዋል።

ኃላፊነቱን ከሚወጣባቸው ዘርፎች መካከል የጤና ተቋማትን መደገፍ ትኩረት ሰጥቶ የሚያከናውነው መሆኑንና ስምምነቱም የዚሁ አካል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በሁሉም ክልሎች የሚያካሂደው የጤና ተቋማት ግንባታም ለኅብረተሰቡ ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግን ዓላማ ያደረገ መሆኑን አክለዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አሚን አማን ባንኩ በጋምቤላ፣በደቡብ ብሄር ብሄረሰብና ህዝቦች እንዲሁም ኦሮሚያ ክልሎች ያስጀመራቸው ሶስት ጤና ጣቢያዎች ግንባታቸው 60 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

መንግስት በቀጣይ ለጤናው ዘርፍ የሚያስፈልጉ ወጪዎች በአገር ውስጥ ምንጮች እንዲሸፈኑ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለተጀመሩም ሆነ ወደፊት ለሚገነቡ የጤና ተቋማት ከውጭ የሚመጣ ብድርና እርዳታን በመቀነስ በአገር ውስጥ ትልልቅ ድርጅቶች የሚሸፈንበትን አቅጣጫ በሂደት ተግባራዊ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ባንኩ የሚገነባቸው የጤና ጣቢያዎች ሲጠናቀቁ ለ200 ሺህ ሰዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችሉ ተገልጿል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን