አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Thursday, 06 April 2017

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2009 የኳታሩ አሚር ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ የሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ሰኞ አዲስ አበባ ይገባሉ።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የኳታር ኤምባሲ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በኳታሩ አሚር የሚመራው የአገሪቷ ከፍተኛ ባለስልጣን ልዑክ ሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም አዲስ አበባ እንደሚገባ ይጠበቃል።

አሚር ታሚም ቢን ሃማድ አል-ታኒ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወደ መንበረ ሥልጣን ከመጡበት እ.ኤ.አ ከ2013 አንስቶ የመጀመሪያው የአፍሪካ ጉብኝታቸው ነው።

አሚሩ በሁለት ቀናት የኢትዮጵያ ቆይታቸው ከፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተለይ በቀጣናዊና ሁለቱን አገሮች ተጠቃሚ በሚያደርጉ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው ይወያያሉ።

የሁለቱን አገሮች የጋራ ጥቅም ሊያስከብሩ የሚችሉ ስምምነቶችና የመግባቢያ ሰነዶች እንደሚፈራረሙም የኤምባሲው መግለጫ አትቷል። 

ባለፈው ዓመት የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ቢን አብዱልራህማን አል-ታኒ በኢትዮጵያ በነበራቸው የሥራ ጉብኝት 11 ስምምነቶችንና የመግባቢያ ሰነዶችን መፈራረማቸው ይታወሳል። 

 

Published in ፖለቲካ

ነቀምቴ መጋቢት 28/2009 በቄለም ወለጋ ዞን  ባለፉት ሰባት ወራት በመደበኛ መርሀ ግብር 22 ሺህ 734 ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች መሰማራታቸውን የዞኑ የስራ እድል ፈጠራና የከተሞች የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።

የፌዴራል መንግስት በመደበው  ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ  ደግሞ ከ28 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ስራ ለማስገባት እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ደጀኔ ጢቂ ለኢዜአ እንደገለፁት ወጣቶቹን በ3 ሺህ 100 ማህበራት በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል ።

ለወጣቶቹ የ40 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የብድር አገልግሎት በማመቻቸት ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል፤ በተጨማሪም ለስራ የሚሆን 482 ሄክታር መሬት፣ 19 የማምረቻና የመሸጫ ቤቶች ተሰጥቷቸዋል።

እንደ አቶ ደጀኔ ገለፃ ወጣቶቹ ከተሰማሩባቸው የስራ መስኮች መካከል ንግድ፣ግብርናና  ግንባታ ይገኙበታል።

በበጀት ዓመቱ በመደበኛ መርሀ ግብር 42 ሺህ 692 ሥራ አጥ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት  የሚደረገው ጥረት እንደቀጠለ ነው።

በሌላ በኩል የፌዴራል መንግስት በመደበው  40 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ  ከ28 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ስራ ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም  ሀላፊው ተናግረዋል ።

የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተለዩ ወጣቶች ውስጥ 5 ሺህ 868 በማደራጀት እንደየ ምርጫቸው በሚሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።

እሰካሁን በ8 ማህበራት የተደራጁ 60 ወጣቶች 796 ሺህ ብር ብድር ተሰጥቷቸው በንግድ ስራ ተሰማርተዋል፤ የተለዩት ቀሪዎቹ  ወጣቶችም በተመሳሳይ ወደ ስራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

አቶ ደጀኔ እንዳመለከቱት በተዘዋዋሪ የብድር ገንዘቡ ተጠቃሚ ለሚሆኑ ወጣቶች ለስራ የሚሆን 96 ሄክታር  መሬት በከተማና በገጠር ተዘጋጅቷል፡፡

የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል በዞኑ በዳሌ ሰዲ ወረዳ የጫሞ ቀበሌ ነዋሪ  ወጣት በዳሳ ብርሃኑ በሰጠው አስተያየት ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመደራጀት በቆጠቡትና ከመንግስት በብድር ባገኙት 85 ሺህ 500 ብር የእህል ወፍጮ በመትከል ወደ ስራ ለመግባት  በሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2009 አምራቾችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች የጥራት ምስክር ወረቀትና ደረጃ ሳያገኙ ምርታቸውን ወደ ገበያ እንዳያስገቡ የሚከለክል መመሪያ ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው በምርትና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና የደረጃ ምልክት አጠቃቀም ዙሪያ  ከአምራቾች፣ ከአገልግሎት ሰጭዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር  በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለው መኮንን በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ከ2004 ዓ.ም አንስቶ በሥራ ላይ የነበረው መመሪያ  አምራቾችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ለተወሰኑ ወራት የጥራት የምስክር ወረቀትና ደረጃ ባይኖራቸውም  ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ እንዲያስገቡ የሚፈቅድ ነበር።

ይህ ደግሞ የምርት ጥራት ምስክር ወረቀት ያላቸውና የሌላቸው እኩል ገበያ ላይ እንዲቀርቡ በማድረጉ ምርቶችን ለመቆጣጠርና በሰው ላይ የጤና ችግሮችን እንዲፈጥሩ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡

እንደ አቶ እንዳለው ገለፃ "አዲሱ መመሪያ  አምራቾችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ማምረት ከመጀመራቸው በፊትና በምርት ሂደት ላይ ደረጃቸውን በማሳወቅ የኢትዮጵያ ደረጃ ምልክትን በምርታቸው ላይ እንዲያሳትሙ የሚያስገድድ ነው።"

መመሪያው ከሁለት ወር በኋላ ተግባራዊ እንደሚደረግ አቶ እንዳለው በተለይ ለኢዜአ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ደረጃ ምልክት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በአምራቾችም ሆነ በተጠቃሚዎች የግንዛቤ ክፍተት ደረጃዎች በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ እንዳይውል ማድረጉ በውይይቱ ተነስቷል።

በመሆኑም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የምልክቱን ጠቀሜታ በመረዳት እንዲገለገልበት ያሳሰቡት አቶ እንዳለው ምልክት የሌለውና ህጋዊ ያልሆነ ምልክት የሰፈረባቸው ምርቶች ሲያጋጥሟቸው ለኤጀንሲው እንዲያሳውቁም ጥሪ አቅርበዋል።

Published in ኢኮኖሚ

መጋቢት 28/2009 ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ደቡብ ምእራብ ጋምቤላ የገቡ ስደተኞች 366 ሺህ መድረሱን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽንን ጠቅሶ  አናዶሉ የዜና ወኪል ዘገበ፡፡

በመጋቢት ወር ብቻ ከ16 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ  ክሱት ገብረእግዚአብሄር ለአናዶሉ ተናግረዋል፡፡

ይህም በየካቲት  ወር ከተመዘገበው ሶስት እጥፍ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በሃገሪቱ ባለው አለመረጋጋትም ከ2 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል ብሏል ዘገባው፡፡

ግማሽ ያህሉ የደቡብ ሱዳን ህዝብም አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ይሻል፡፡

ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው 830 ሺህ ስደተኞች 44 ከመቶ ያህሉ ደቡብ ሱዳናውያን ናቸው፡፡

እኤአ ከመስከረም 2016 ጀምሮ ከገቡ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች 65 ከመቶ ያህሉ ልጆች ሲሆኑ ከ17 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከወላጆቻቸው የተለዩ እና ብቸኞች መሆናቸውንም አቶ ክሱት ተናግረዋል 

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ስደተኞቹን ለመርዳት ያስፈልገኛል ካለው 157 .7 ሚሊየን ዶላር መገኘት የተቻለው 6 ከመቶ ያህሉን ብቻ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ 

 “ፈንዱን ለማግኘት ካለው ችግር አኳያ አስቸኳይ አገልግሎቶች ላይ ብቻ ትኩረት አድርገናል” ያሉት አቶ ክሱት ለማስፈፀም ረዥም ጊዜ የሚወስዱትን እንደ ትምህርትና ስልጠና ያሉትን ወደ ጎን ትተናል ብለዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አርባምንጭ መጋቢት 28/2009 በጋሞ ጎፋ ዞን ሰሞኑን የተከሰተውን የፀረ-በቆሎ ትል ለመከላከል ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ የመከላከል ስራ በዘመቻ መጀመሩን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በዞኑ ሁለት ወረዳዎች በ261 ሄክታር የበቆሎ ማሳ ላይ የተከሰተው የፀረ-በቆሎ ትል በ48 ሰዓት ውስጥ አራት ተጨማሪ ወረዳዎች ላይ መከሰቱን የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ ጋሻው ሞላ ለኢዜአ ገልጸዋል።

"የአሜርካ ትል" የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ ትል በምሽት በሚያደርገው በረራ በፍጥነት በመሰራጨት በእነዚሁ ወረዳዎች ከ467 ሄክታር ላይ የበቀለውን የበቆሎ ማሳ ወሯል።

በዚህም ከ1 ሺህ 100 በላይ አርሶ አደሮች ማሳ የወረርሽኙ ሰለባ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ተባዩን ለመከላከል በተደረገው ጥረት 130 ሄክታር ማሳ ላይ “ማላታይን” የተባለ ኬሚካል ርጭት ቢካሄድም የትሉ የስርጭት ፍጥነት ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ የመከላከል ስራ በዘመቻ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በዘመቻው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ጨምሮ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚያሳተፉ ይገናሉ፡፡

ተባዩን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

ተባዩ ከተከሰተባቸው ወረዳዎች መካከል የካምባ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሰፋጽዮን ዘነበ በበኩላቸው የተከሰተው ወረርሸኝ ከባድ በመሆኑ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከለ ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ትሉ ጧትና ማታ ካልሆነ የማይንቀሳቀስና በቀን በሚካሄድ ኬሚካል ርጭት የማይሞት መሆኑ ወረርሽኑን ለመቆጣጠር የተጀመረውን ስራ አስቸጋሪ እንዳደረገውም ገልጸዋል።

የሣር ግጦሸን ጨምሮ 83 የሰብል ዓይነቶችን ያጠቃል የተባለው ይሄው ፀረ-በቆሎ ትል ባህሪይውና አደገኛነቱ ከፍተኛ በመሆኑ በኬሚካል ርጭት ብቻ መከላከል እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

በወረዳው ከ81 ሄክታር በላይ የበቆሎ ማሳ በትሉ መያዙን ገልጸው፤ ወራርሸኑን ለማሰቆም ሁሉን የህብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈ የመከላከል ሰራ እየተሠራ መሆኑንም ገልፀዋል።

ወረርሽኙ በዝናብ መዘገየት ምክንያት በዘር ያልተሸፈኑ ማሳዎች አከባቢ እንዳይዛመት ጉድጓድ የመቆፈር፣ እንስሳት የማሰማራትና ሌሎች ባህላዊ የመከላከል ሰራዎች መጀመራቸውንም ገልጸዋል።

በጋሞ ጎፋ ዞን ለበልግ እርሻ ከተዘጋጀው 57 ሺህ 463 ሄክታር በቆሎ ማሳ 14 ሺህ የሚሆነው በደጋፊ መስኖ በመልማት ላይ ሲሆን ከ467 ሄክታር በላዩ በጸረ- በቆሎ ትሉ ተወሯል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2009 ኢትዮጵያ በዓለም እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ 20 ደረጃዎችን አሽቆለቆለች።

ባለፈው ወር ከነበረችበት 104ኛ ደረጃ 20 ደረጃዎችን በማሽቆልቆል ነው ከዓለም በ124ኛ ከአፍሪካ ደግሞ በ36ኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠችው።

የፊፋ የደረጃ ሠንጠረዥ የሚወጣው አገራት በሚያደርጓቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮችና በፊፋ ዕውቅና ባላቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች ነው።

በነዚህ ውድድሮች የተሻለ ውጤት የሚያስመዘገቡ ብሄራዊ ቡድኖች ደረጃቸውን የተሻለ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን /ዋልያዎቹ/ በ2009 ዓ.ም ምንም ዓይነት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን አለማድረጉ ለደረጃው መውረድ ምክንያት አንደሆነ ይጠቀሳል።

አዲሱ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከጋና ጋር ላለባቸው  ውድድር እንዲረዳቸው ሶስት የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ አቅደዋል።

በወዳጅነት ጨዋታዎችና በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የተሻለ ውጤት ካስመዘገቡ በቀጣይ የዋልያዎቹ ደረጃ የሚሻሻል ይሆናል።

በ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሽንፈት ያላስተናገደችው ብራዚል  በፊፋ ደረጃ ሰንጠረዥ ከሰባት ዓመታት በኋላ አንደኛ መሆን ችላለች።

በደረጃ ሠንጠረዥ ለረጅም ጊዜ አንደኛነቷን አስጠብቃ የቆየችው አርጀንቲና ሁለተኛ ስትሆን ጀርመን፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ፈረንሳይ፣ ቤልጂዬም፣ ፖርቹጋል፣ ስዊዘርላንድና ስፔን እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሦስተኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

በ2017ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚ የነበረችው ግብጽ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ 19ኛ ስትሆን ሴኔጋል ከአፍሪካ ሁለተኛ ከዓለም 30ኛ ደረጃ ስትይዝ፤ የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ካሜሮን ከአፍሪካ ሶስተኛ ከዓለም  ደግሞ 33ኛ ሆናለች።

ቡርኪና ፋሶና ናይጀሪያ ከአፍሪካ አራተኛና አምስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያን የምትገጥመው ጋና ከአፍሪካ ስምንተኛ ከዓለም 45ኛ ሆናለች።

አንጕላ፣ ባሃማስ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ጂብላርተርና ቶንጋ በዜሮ ነጥብ  ከፊፋ  አባል አገራት የመጨረሻውን ደረጃ ይዘዋል።

 

 

Published in ስፖርት

መጋቢት 28/2009 የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ “ፋርማጆ” በሀገሪቱ ስር የሰደደውን የሀይማኖት አክራሪነት ለመዋጋት  አዲስ ስልት ይፋ አድርገዋል፡፡

ለዚህም በ60 ቀናት ውስጥ እጃቸውን ለሚሰጡ የአልሻባብ ታጣቂዎች ምህረት  እንደሚደረግ  አስታውቀዋል፡፡

በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ እጃቸውን ለሚሰጡ ታጣቂዎች የትምህርት፣ የስልጠናና የስራ ቅጥር እድሎች እንደሚመቻቹላቸውም ፕሬዝዳንቱ ቃል ገብተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ምህረቱን ያደረጉት በመዲናዋ ሞቃዲሹ በሚገኝ የመንግሥት ህንጻ አቅራቢያ በተፈጸመ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ሰባት ሰዎች በሞቱ ከአንድ ቀን በኃላ ነው፡፡

አልሻባብ የሶማሊያን መንግስት ለማንኮታኮትና የማያፈናፍን የእስልምና ህግ በሀገሪቱ ለመተግበር ካለው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ  በምስራቅ አፍሪካ የሚፈጽመውን የሽብር ጥቃት አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በታጣቂ ቡድኑ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ ያመቻቸው ዘንድም የፖሊስ ኃይሉንና የደህንነት አገልግሎቱን በከፍተኛ የደህንነት ሃላፊዎች ተክተዋል፡፡

 ፕሬዝዳንቱ ሙሉ ወታደራዊ ልብስ በመልበስ ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት  አቋማቸውን ታጣቂ ሃይሉ እንዲገነዘብ ለማድረግ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል፡፡

ተንታኞች የፕሬዝዳንቱ አዲስ የደህንነት እርምጃ በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮ ሰላም አስከባሪና የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር የተቀናጁትን  ድል ያጠናክረዋል ብለዋል፡፡

አልሻባብ በሀገሪቱ ባካሄደው ለአስር ዓመታት ያህል የዘለቀ ጦርነት በሺህዎች የሚቆጠሩትን ገድሏል በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ አፈናቅሏል፡፡

 

ምንጭ፡- ሲጂቲኤን

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2009 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዜጎች ቅሬታ የሚያቀርቡበትና መረጃ የሚያገኙበት አዲስ ድረገጽ ፖርታል ይፋ አደረገ።

ኮሚሽኑ በዛሬው ዕለት አዲስ የዌብ ፖርታል፣ የሰብዓዊ መብት ክትትል እና ምርመራ ማንዋል ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እያካሄደ ነው።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር በወቅቱ እንደገለጹት ዌብ ፖርታሉ ኮሚሽኑ ለዜጎች ያለውን ተደራሽነት ለማስፋት የተዘጋጀ ነው።

ኮሚሽኑ የዜጎችን ቅሬታና አቤቱታ በነጻ የስልክ መስመር ሲቀበል መቆየቱን ገልጸው አሁን ይፋ የተደረገው ዌብ ፖርታል ማንኛውም ዜጋ ያለውን ቅሬታና ጥቆማ ኢንተርኔትን በመጠቀም ቀጥታ (ኦንላየን) ለኮሚሽኑ ማቅረብ ያስችላል።

በምክክሩ የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አባዱላ ገመዳ እንዳሉት ኮሚሽኑ አገሪቱ የራሷን የሰብዓዊ መብት ችግሮች በራሷ ተቋም በመመርመር መፍታት እንደምትችል የሚያሳዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ዌብ ፖርታሉም የኮሚሽኑን ተደራሽነት በማጠናከር ዜጎች በቀላሉ ቅሬታዎችን በማድረስና መፍትሔ ለማግኘት ያግዛልም ብለዋል።

ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገው ዌብፖርታል በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሲሆን ድረ-ገጹ www.ehrc.org.et ነው።

በተጨማሪም ዌብ ፖርታሉ ህገ-መንግስቱን ጨምሮ ዓለም ዓቀፍ ህጎች፣ የኮሚሽኑ እቅዶች፣ ፕሮግራሞች፣ የምርመራ ሰነዶችና ጥናቶች ይጫኑበታል ተብሏል።

በዓለም ጤና ድርጅት የፕሮግራም ማስፈፀም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ፍቅር መገርሳ እንዳሉት ዌብፖርታሉ የዘገየ ቢሆንም በአግባቡ አገልግሎት ከሰጠ ዜጎች የሚደርስባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፍትሔ ለማግኘት ያግዛል።

እንዲሁም ግልጽነትን በማስፈን ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

አዲስ አበባ መጋቢት 28/2009 ሊሰማሩበት የፈለጉበት የስራ ዘርፍና የሙያ ስልጠና ጊዜው ተመጣጣኝ አለመሆኑን በአዲስ አበባ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው በስልጠና ላይ የሚገኙ ወጣቶች ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ቢሮ በበኩሉ አሁን እየተሰጠ ካለው ስልጠና በተጨማሪ  ወደ ስራ ከተሰማሩ በኋላም  ተከታታይ ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል ብሏል።

መንግስት ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው የራሳቸውን ስራ እንዲጀምሩ ለማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ወጣቶችን እያሰለጠን ይገኛል።

በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች በስልጠና ላይ ያሉ ወጣቶችን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ተዘዋውሮ  አነጋግሯል።

ወጣቶቹ የስልጠናው ይዘት ጥሩ ቢሆንም ሊሰማሩ ያሰቡበት የስራ ዘርፍ የሚጠይቀው ዕውቀትና ለስልጠናው የተሰጠው ጊዜ ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ከሰልጣኞቹ መካከል ወጣት አበራሽ እንዳይላሉ በጄነራል ዊንጌት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ውስጥ  የልብስ ስፌት ስልጠና እየወሰደች ብትሆንም በስልጠናው ማጠር ምክንያት ተመልሳ ወደ ተቀጣሪነት አንዳትገባ ስጋት እንዳላት ገልጿለች።

ሌላው ሰልጣኝ  በድሩ አሊ በብረታ ብረት ሰልጥኖ መንግስት በፈጠረለት ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ራሱን ለመለወጥና አገሩን ለመጥቀም ቢፈልግም  እየወሰደ ባለው ስልጠና በቂ እውቀትና ክህሎት ለማግኘት የስልጠና ቀን እንደሚያጥር ተናግሯል።

የስልጠና ጊዜው ራሹን ችሎ ለመስራት ቀርቶ ተቀጥሮ ለመስራትም እንደማያስችለው የተናገረው ደግሞ ሰልጣኝ አማረ ሽፈራው  ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ቢሮ የስራ ዕድል  ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ማደራጀት ዋና የስራ ሂደት  መሪ አቶ ግርማ ወርቁ  በበኩላቸው "ስልጠናው ከሰባት ቀን ጀምሮ እስከ ሶስት ወር የሚሰጥ ነው" ብለዋል።

ይህም ከመደበኛው ስልጠና  አንጻር ሲታይ ጊዜው አጭር ቢሆንም የሚሰጠው ስልጠና ግን በቂ ነው ያሉት አቶ ግርማ  በመሰጠት ላይ ያለው ስልጠናው ወደ ስራ ለመግባት የሚያስችላቸው እንደሆነም ተናግረዋል።

ለወጣቶቹ ከሙያ ስልጠና ባሻገር ችግርን የመቋቋም አቅማቸውን ሊያሳድጉ የሚችሉ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንደሚሰጡም ገልጸዋል።

በቀጣይም ወጣቶቹ ሙያቸውን እንዲያዳብሩ የስራ ላይ  ስልጠና እንደሚሰጡ ገልፀዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ከ3 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ተለይተው በተለያዩ ዙሮች ስልጠና በመሰጠት ላይ ሲሆኑ  በአዲስ አበባ ደግሞ ከ19 ሺህ በላይ ወጣቶች በጀነራል ዊንጌት፣እንጦጦ፣ተግባረ ዕድና ሌሎች የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በመሰልጠን ላይ ናቸው።

Published in ማህበራዊ

ማይጨው መጋቢት 28/2009 የበልግ ዝናብን በመጠቀም ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎች በማልማት ላይ መሆናቸውን የትግራይ ደቡባዊ ዞን አንዳንድ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ በበኩሉ በዞኑ በአምስት በልግ አብቃይ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮች  ከ14 ሺህ ሄክታር  በላይ መሬት እያለሙ  መሆናቸውን  ገልጿል።

አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት "ካለፈው የካቲት ወር አጋማሽ  ጀምሮ መጣል የጀመረው የወቅቱ ዝናብ  መቆራረጥ ቢታይበትም የተገኘውን እርጥበት ተጠቅመን በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎችን እየዘራን ነው" ብለዋል ።

የራያ አዘቦ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር የማነ አብርሃ እንደገለፁት የወቅቱን ዝናብ በመጠቀም አንድ ጥማድ ማሳቸውን  በሦስት ወር በሚደርስ የጤፍ ዝርያ እየሸፈኑ ነው ።

እንደ አርሶ አደሩ ገለፃ ከሚዘሩት ጤፍ የተሻለ ምርት ያዘጋጁትን ከ200 ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማሳቸው ተጠቅመዋል ።

"በማሳዬ  ውስጥ የሰራሁት  የአፈርና ውሀ  ጥበቃ ስራ በምርት ወቅቱ የዝናብ ውሀና እርጥበት ለማቆየት እረድቶኛል " ብለዋል ።

ሌላው የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር  በሃይሉ ባይራይ  በበኩላቸው ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ የጣለውን ዝናብ በመጠቀም በሁለት ጥማድ ማሳቸው ላይ የዘሩት ጤፍ ለቡቃያ መድረሱን  ጠቅሰዋል ።

የበልጉ ዝናብ  ግዜውን  ጠብቆ ቢጀምርም በመቆራረጡ ምክንያት ማሳቸው ሊከሰት የሚችለውን አረም ለመከላከል ደጋግመው የመገልበጥ ስራ እንደሚሰሩም አመላክተዋል ።

በማሳቸው የሰሩት እርከን እርጥበት በማቆየት ለምርት መጨመር ይረዳኛል የሚል እምነት እንዳላቸው አርሶ አደር በሀይሉ አስረድተዋል ።

በራያ አላማጣ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አብርሃ ታደሰ በበኩላቸው "ከየካቲት ወር በፊት  አንድ ጥማድ ማሳየን አርሼ በማዘጋጀቴ የበልጉ ዝናብ መጣል እንደ ጀመረ ጤፍ ዘርቻለሁ " ብለዋል፡፡

የጤፍ ዝርያው በአጭር ጊዜ የሚደርስ መሆኑን የገለፁት አርሶ አደሩ የዝናቡ ስርጭት በዚሁ ከቀጠለ እስከ 25 ኩንታል ምርት ሊያገኙ እንደሚችሉ አመላክተዋል።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የእንስሳት ሃብት ልማት ቡድን መሪ አቶ ሃይለ ከሳ እንደገለጹት በዞኑ በልግ አምራች በሆኑ አምስት ወረዳዎች ከ25 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም ማሳቸውን በዘር እየሸፈኑ ነው ።

የዝናቡ ስርጭት የተቆራረጠ ቢሆንም አርሶ አደሩ ውሀ በመያዝና እርጥበት በመጠቀም ማሳውን በዘር እንዲሸፍን ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

ተሳታፊ አርሶ አደሮች ያዘጋጁትን ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በምርት ወቅቱ ጥቅም ላይ አውለዋል ።

በዞኑ በምርት ወቅቱ በጤፍ፣ በስንዴ፣ በገብስ፣ በሽምብራ፣በደቆቆና በአተር ሰብሎች ከሚለማው  ከ14 ሺህ ሄክታር  በላይ  መሬት ከግማሽ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ሃይለ አስታውቀዋል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን