አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 05 April 2017
Wednesday, 05 April 2017 23:55

ገዳ ለዴሞክራሲ

Published in ቪዲዮ

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2009 የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ዘመኑ ከደረሰበት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኢንዱስትሪ ጋር እኩል እንዲራመዱ የጀመራቸውን የድጋፍና አቅም ግንባታ ሥራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።     

የምክር ቤቱ የባህል፣ ቱሪዝምና መገናኛ ብዙኃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጽህፈት ቤቱን የሥራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ የመስክ ምልከታ አድርጓል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲያ የሱፍ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኢንዱስትሪ በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ ይገኛል።

ጽህፈት ቤቱ ዘመኑ ከደረሰበት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኢንዱስትሪ ጋር እኩል የሚራመድ ተቋምና ሚዲያ ለመፍጠር የአሰራር፣ የሰው ኃይል ማብቃትና የአደራጃጀት ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል።

መረጃ ከመንግስት ወደ ህዝቡና ከህዝቡ ወደ መንግስት በጥራትና በፍጥነት እንዲደርስ የህዝብ ግንኙነት ሥራን የማጠናከር፣ በተለያዩ ድረ-ገጾች የህዝብ አስተያየቶችን የመሰብሰብና የመተንትን እንዲሁም የሚዲያ ፖሊሲዎችንና ደንቦችን የማዘጋጀት ተግባርም እያከናወነ ነው። 

በህዝብ፣ በመንግስትና በግል መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛ የመረጃ ፍሰት እንዲኖርም እየሰራ መሆኑንና የጀመረው ሥራና የሚሰጠውን የድጋፍና አቅም ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሰብሳቢዋ አሳስበዋል።  

በአገር ውስጥ የሚገኙ የውጭ አገር የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ጋዜጠኞች በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመርኩዘው እንዲዘግቡና የአገሪቱን ገጽታ እንዲገነቡ ድጋፍና ክትትል መደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል። 

ጽህፈት ቤቱ የአገሪቱ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራ በጥናትና ምርምር የተደገፈ እንዲሆን የሚዲያ ጥናትና ምርምር ተቋም እንዲቋቋም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንዲሰራም አሳስበዋል።

የተቋማት ኃላፊዎች ለህዝብ ግንኙነት ሥራና ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተው አስፈላጊውን የሰው ኃይልና ቁሳቁስ እንዲያሟሉ ምክክርና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንዲሰሩም አመልክተዋል።  

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጠው አስተያየትና ግብረ መልስ ለቀጣይ የጽህፈት ቤቱ የሥራ እንቅስቃሴ በግብዓትነት የሚወሰድ ነው።   

ተቋማት መንግስትና ህዝብ የሚፈልገውን መረጃ በወቅቱ፣ በጥራትና በፍጥነት እንዲለቁ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አቅም የማጠናከርና አቅጣጫ የመስጠት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ በኤፍ ኤም ሬዲዬዎችና በህትመት የተቋማትን የሥራ እንቅስቃሴ የሚመለከቱ መረጃዎች በዜና፣ በዜና ትንታኔና በዘጋቢ ፊልሞች ለኀብረተሰቡ በየጊዜው እየቀረቡ ነው ብለዋል።  

ጽህፈት ቤቱ ከፌደራል እስከ ክልል ቀበሌ ድረስ ባሉት መዋቅሮች ደረጃውን የጠበቀና ለጥቃት ያልተጋለጠ መረጃ ወቅቱን ጠብቆ ለማድረስ እየሰራ ቢሆንም በሚያጋጥሙት የተለያዩ ተግዳሮቶች በስፋት መስራት አልተቻለም ሲሉም አክለዋል።  

በየተቋማቱ የተሟላ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ፣ ቁሳቁስና ቢሮ ያለመኖር እንዲሁም በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጁት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ፖሊሲዎችና ደንቦች በወቅቱ ጸድቀው ወደ ተግባር ያለመግባት ካጋጠሙ ችግሮች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።  

የሰራተኛ ፍልሰት፣ የመስክና የከተማ ተሽከርካሪዎች እጥረት፣ የዘመናዊ መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖርም እንዲሁ ሌሎች ችግሮች መሆናቸውን አንስተው ጽህፈት ቤቱ በቀጣይ ያሉትን ክፍተቶች በመፍታት የበለጠ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል።

በተለይም የገጽታ ግንባታ ሥራን በስፋት ለማዳረስ ትክክለኛ መረጃ ለውጭ ጋዜጠኞች ለመስጠትና  በውጭ የሚገኙ ኤምባሴዎችን ለመጠቀም የተለያዩ ሥራዎች እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ነገሪ ገለጻ የዴሞክራሲ ባህል መገንባት፣ የኢኮኖሚ እድገቱና የዜጎች ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፣ ሕዝቡ ቅሬታ የሚያነሳባቸውን ዘርፎች በዳሰሳ ጥናት ለይቶ አስፈላጊውን መለስ ማሰጠት በቀጣይ ከሚሰሩ ተግባራት መካከል ናቸው።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2009  በቆሼ በደረሰው አደጋ የተጎዱና በህጋዊ ቤቶች ተከራይ የነበሩ 56 ሰዎች የ10/90 የጋራ መኖሪያ ቤት ቁልፍ ተረከቡ።

ከንቲባ ድሪባ ኩማን ጨምሮ የከተማዋ ከፍተኛ የአመራር አባላት የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ከጎበኙ በኋላ ዕጣ በማውጣት ተጎጂዎቹ ቁልፍ እንዲረከቡ ተደርጓል።

የህጋዊ ቤቶች ተከራይ የነበሩ 60 ሰዎች የአደጋው ሰለባ የነበሩ ሲሆን፣ ከመካከላቸው አራቱ ቀደም ሲል የኮንዶሚኒየም ቤት የደረሳቸው በመሆናቸው ለዚሁ ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።

ለ56ቱ ተጎጂዎች የተላለፉትና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቂሊንጦ ሳይት የሚገኙት ቤቶች እያንዳንዳቸው 82 ሺህ ብር ዋጋ ያላቸው ናቸው።

ቤቶቹ የውሃ፣ መብራት እና መንገድ መሰረተ ልማቶች የተሟላላቸው መሆናቸውን ከንቲባ ድሪባ ኩማ ገልጸዋል።

ተጎጂዎቹ ከተሰጣቸው ቤት በተጨማሪ ለሦስት ወር መሰረታዊ ፍጆታ የሚሆናቸው ለእያንዳንዳቸው የ13 ሺህ 500 ብር ካሳ ተሰጥቷቸዋል።

ከንቲባ ድሪባ ተጎጆቹ በዘላቂነት እስከሚቋቋሙ መንግስት በሚቻለው ሁሉ ድጋፉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

መኖሪያ ቤት የተሰጣቸው ተጎጂዎችም መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

ወይዘሮ እታለም ተሾመ "መንግስት ያደረገው ነገር ከጠበቅነው በላይ ነው፤ ሰለተደረገልኝ ነገር ደስታዬ ወደር አልባ ነው ነው" ብለዋል።

ወይዘሮ ጥሩሰው አንተነህ በበኩላቸው መንግስት አደጋው ከደረሰ ጀምሮ እያደረገ ያለውን ድጋፍ ገልጸው ቤት ስለተሰጣቸው ደስታቸው ከልክ ያለፈ መሆኑን ተናግረዋል።

መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም ምሽት በቆሼ አካባቢ በደረሰው አደጋ የበርካታ ዜጎች ሕይወት ማለፉ ይታወቃል።

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ መጋቢት 27/2009 የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ጋህአዴን) ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት አምርሮ በመታገል የህዝቡ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እንደሚሰራ አስታወቀ።

የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሜቴ የተለያዩ  ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ለአምስት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ዛሬ አጠናቋል ።

የጋህአዴን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡኩኝ ኡቡያ ለኢዜአ  እንደገለጹት የድርጅቱ ዋነኛ አደጋ የሆነውን ሙስናና ኪራይ ሰብሰቢነት በመታገል የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት በትኩረት እየሰራ ነው።

ባለፉት ዓመታት በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች የተከናወኑት የልማት ስራዎች ህዝቡ በተፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ ሳይሆን  መቆየቱን በተካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ መድረክ መለየቱን ተናግረዋል።

"ለዚህም ዋንኛ ምክንያት በየደረጃው የሚገኙ የድርጅቱ አመራሮች ስልጣንን ለህዝብ ሳይሆን ለራሳቸው መጠቀሚያ አድርገው መቆየታቸው ነው" ብለዋል።

ድርጅቱ በተለይም በሙስና ፣ በኪራይ ሰብሳቢነትና በብልሹ አሰራሮች ውስጥ የተዘፈቁ አመራሮችን ቀጣይነት ባለው ጥልቅ የተሃድሶ መድረክ በማጥራት የተጠናከረ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ጋህአዴን ላለፉት አምስት  ቀናት ባካሂደው የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ውስጥ የተዘፈቁ ሶስት ከፍተኛ የድርጅቱ አመራሮች ከድርጅቱ ማሰናበቱንም አስታውቀዋል፡፡ 

ድርጅቱ በተለይም በግብርና ፣ በትምህርት ፣በሌሎችም የልማት  ዘርፎችና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት ሰጥተው ለመስራት አቅጣጫ ማስቀመጡን ጠቁመዋል፡፡

የጋህአዴን ጽህፈት ቤት ኃላፊው እንዳመለከቱት በከፍተኛ አመራር የተጀመረውን ቀጣይነት ያለው ጥልቅ የተሃድሶ ግምገማ እሰከ ቀበሌ በማውረድ ተመሳሳይ እርምጃ የመውሰዱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ 

 

 

 

Published in ፖለቲካ

ጎባ መጋቢት 27/2009 በትልቅ ተሃድሶ የተለዩ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰሩ በባሌ ዞን የሚገኙ የኦህዴድ  አባላትና ደጋፊዎች አስታወቁ።

አባላቱ የኦህዴድን 27ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በዞን ደረጃ በባሌ ሮቤ ከተማ በፓናል ውይይት አክብረዋል።

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል የጊኒር ወረዳ ነዋሪው የድርጅቱ አባል አቶ ደበላ ኤብሳ እንዳሉት  "ድርጅቱ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባሮችን ለማስወገድ ለህዝቡ ቃል ገብቷል።''

በዚሁ መሰረት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት  የተገባው ቃል በተግባር እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ሌላው ከዲንሾ ወረዳ የተወከሉት የድርጅቱ አባል አቶ ሀሰን አህመዶ  በሰጡት አስተያየት ኦህዴድ በተሃድሶ ወቅት በህብረተሰቡ የተነሱ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ መፍታት መጀመሩ የሚያበረታታ ነው።

''በአሉን ስናከብር የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር በመነሳሳትና ችግሩን በዘላቂነት በመፍታት ህዝቡን ልንክሰው ይገባል'' ብለዋል።

በተለይ የዞኑ ህዝብ ችግር ሆነው የቀጠሉ የመብራት አገልግሎት መቆራረጥና የስልክ ጥራት መጓደል ትኩረት የሚሹና ቀጣይ የቤት ስራዎች መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የሮቤ ከተማ ነዋሪና  የድርጅቱ አባል አቶ መሀመድ አሀመድ ናቸው፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደም ቃሲም በበኩላቸው እንደገለጹት ድርጅቱ ካስመዘገባቸው ድሎች ጎን ለጎን ህብረተሰቡ በጥልቅ ተሃደሶ ያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር፣የኪራይ ሰብሳቢነትና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።

ከዞኑ 18 ወረዳዎች የተወጣጡ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ትላንት በተከበረው በዓል ላይ የተሳተፉ ሲሆን በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ጽንሰ ሐሳብና በዞኑ የልማት ችግሮች ዙሪያ መክረዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2009 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ከሎተሪ ሽያጭ 125 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታወቀ፡፡

ጽሕፈት ቤቱ ገቢውን ለመሰብሰብ ዛሬ ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ሎተሪው ከሚያዚያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ወራት ገበያ ላይ የሚውል መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡

የጽህፈት ቤቱ የፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ የአካባቢ ጥበቃና ስነ-ጥበብ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ተካ እንዳሉት ሎተሪው በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ቅርንጫፎች፣ በግድቡ ምክር ቤት ጽህፈት ቤቶች፣ በመንግስት ተቋማት፣ በሲቪክ ማህበራትና በልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ይሰራጫል።

በመሆኑም የመንግስት ተቋማትና የሲቪክ ማህበራት የታቀደውን ገቢ ለማሰባሰብ ሰራተኞቻቸውንና አባሎቻቸውን በማስተባበር እንዲሰሩ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

ተቋማቱ ከሚሸጡት የባለ 25 ብር ቲኬት 15 በመቶ የሚታሰብላቸው ስለሆነ ገቢውን ከማሰባሰብ በተጨማሪ ራሳቸውን የሚያጠናክሩበት ዕድል የሚከፍትላቸው በመሆኑ ተሳትፏቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ነው ያሉት አቶ ሰለሞን፡፡

ሎተሪው ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን በአንደኛ ዕጣ ባለ ሶስት መኝታ መኖሪያ ቤት፣ በሁለተኛ ዕጣ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ፒክ አፕ መኪና፣ በሶስተኛ ዕጣ ባለሁለት መኝታ የመኖሪያ ቤት እና ሌሎችንም ሽልማቶች ይዟል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2009 በኦሮሚያ፣ ጋምቤላና ደቡብ ክልሎች የሚገኙ ሶስት መንገዶችን ደረጃ ማሳደግና መገንባት የሚያስችሉ ስምምነቶችን ተፈረሙ።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ መንገዶቹን ደረጃ ማሳደግና መገንባት የሚያስችሉ ስምምነቶች ተፈራርሟል።

ባለሥልጣኑ ስምምነቱን የተፈራረመው አፍሮ ጽዮንና ራማ ኮንስትራክሽን እንዲሁም ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ኩባንያ ከተሰኙ አገር በቀል የሥራ ተቋራጮች ጋር ነው።

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ወጪ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ነው።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ግርማይ፣ የኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ኃይለዓለም ወርቁ እንዲሁም የራማና አፍሮ ፅዮን ኮንስትራክሽን ሥራ አስኪያጆች አቶ ፍሬው ተድላና አቶ ሲሳይ ደስታ ስምምነቶቹን ተፈራርመዋል።

የሚገነቡት መንገዶች ጠቅላላ ርዝመት 210 ኪሎ ሜትር ሲሆን በገጠር እስከ 12 ሜትር በከተማ ደግሞ 21 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት ይኖራቸዋል።

በኦሮሚያ፣ ጋምቤና ደቡብ ክልሎች የሚገነቡት መንገዶቹ በጠጠር ደረጃ የነበሩና በአስፋልት ኮንክሪት የሚቀየሩ መሆናቸው ተገልጿል።

ፕሮጀክቶቹ ቀደም ሲል ምንም የመንገድ መሰረተ ልማት ያልነበረባቸውና በጠጠር ደረጃ የነበሩ ሲሆኑ ባላቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ በአስፋልት ደረጃ መገንባት አስፈላጊ ሆኗል።

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ከ1 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩም ተገልጿል።

ግንባታቸው ሲጠናቀቅ የስኳር ምርት ለማጓጓዝ፣ የግብርና ምርቶችን ወደ ገበያ ለማቅረብና የቱሪስት ፍሰቱን በማቀላጠፍ የውጭ ምንዛሪ የማስገኘት ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን አቶ አርአያ ግርማይ ተናግረዋል።

በአካባቢዎቹ የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ ህብረተሰቡ ወደሚፈልገው ስፍራ ለመንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ ነው ያሉት።

የመንገዶቹ ግንባታ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ የየአካባቢዎቹ አስተዳደር አካላትና ነዋሪዎች እንዲተባበሩም አሳስበዋል።

የፕሮጀክቶቹን የማማከርና የቁጥጥር ስራ የሚከውኑ አማካሪ ድርጅቶችን ለመምረጥ በጨረታ ሂደት ላይ የሚገኝ ሲሆን አገር በቀል ድርጅቶች ብቻ እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።

ፕሮጀክቶቹ በሶስት ዓመት እንደሚጠናቀቁም በስምምነት ፊርማው ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የዛሬውን ጨምሮ በተያዘው በጀት ዓመት የ24 ነጥብ 38 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክቶችን ተፈራርሟል።

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር  መጋቢት 27/2009 በሀገር አቀፍ ደረጃ በጎንደር ከተማ የሚካሄደውን ሰባተኛው የከተሞች ፎረም ለማስተናገድ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን  የአማራ ክልል ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሽቤ ክንዴ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት የፎረሙ ዓላማ  ከተሞች የእርስ በርስ ቅርርብና ትውውቅ ለማጎልበት፣  በመካከላቸው ጤናማ ውድድር እንዲፈጠር፣  መልካም ተሞክሮዎች ለማስፋፋት ፣ ተቀራራቢ  ልማትና ዕድገት እንዲረጋገጥ ለማድረግ ነው። 

የልማት ስራቸውን የሚያሳዩበት፤ የኢንቨስትመንት፤ የገበያ፤ የቱሪዝምና ሌሎች መስህቦቻቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ እንዲሆን ለማድረግ ጭምር እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

በፎረሙም የመሬት ልማትና ማኔጅመንት፣  የከተሞች መሰረተ ልማት አቅርቦት፣ የከተማ ምግብ ዋስትናና የስራ ዕድል ፈጠራ በሚሉና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ  የፓናል ውይይቶች ይካሂዳሉ።

የክልሉ መንግስት በቅድመ ዝግጅት ለሚከናወኑ ማህበራዊና መሰረተ ልማት ስራዎች የሚውል 25 ሚሊዮን ብር ለጎንደር ከተማ አስተዳደር የበጀት ድጋፍ አድርጓል።

ኮንሰርትና አውደርዕይ  የሚካሄድበትን ቦታ የማልማትና የማስዋብ፣ የመንገድ ግንባታና የዋና ዋና መንገድ መብራት የማሻሻል ስራ ተከናውኗል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ እንዳመለከቱት የክልል መንግስትም ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ፎረሙን በስኬት ለማጠናቀቅ የተዋቀሩ ስምንት ንዑሳን ኮሚቴዎችን የመገምገምና የመደገፍ ስራ እያከናወነ ይገኛል። 

በተለይም በአማራ ክልል የሚገኙ 65 ከተሞች በፎረሙ ላይ ተገኝተው ገጽታቸውን የሚገነቡበትና ጸጋቸውን ለማስተዋወቅ ቀድመው መመዝገባቸውንም ጠቁመዋል።

ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች  የሚመጡ ከ200 በላይ ከተሞች፣  ከ10 የማያንሱ አጋር ድርጅቶችና ዓለም አቀፍ እንግዶችም በፎረሙ ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

ከመላ ሀገሪቱ የሚመጡ ተሳታፊ እንግዶች ወደክልሉ ጎንደር ከተማ ሲመጡ በየመንገዱ የአካባቢውን ወግና ባህል መሰረት ያደረገ አቀባበል እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ፎረሙ " የከተሞች ዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደር ለህዳሴያችን" በሚል መሪ ሀሳብ በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ከሚያዚያ 21 እስከ 28/2009ዓ.ም ይከበራል።

Published in ኢኮኖሚ

አምቦ መጋቢት 27/2009 የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በሳይንስ ትምህርት ዘርፍ እንዲሳቡና ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ በመስጠት እያበረታታ መሆኑን የአምቦ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በአምቦ አካባቢ ለሚገኙ  ሰባት ሁለተኛ  ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ባዘጋጀው የማህበረሰብ አገልግሎት የማጠናከሪያ ትምህርት  መርሃ ግብር ላይ  እንደተገለጸው  ተማሪዎች ተነቃቅተው የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ትምህርት ክፍሎችን እንዲቀላቀሉ  ድጋፍ እያደረገ ነው።

የሁለተኛና የመሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር ሂደት እየተላመዱ እንዲቆዩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን  በዩኒቨርሰቲው  የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የተማሪዎች ጉዳይ ሃላፊ ዶክተር በቀለ ጋሼ  ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ተግባር ተኮር የመማማሪያ መድረክ በማዘጋጀት ተማሪዎች በሳይንስ ትምህርት ዘርፍ እንዲሳቡና ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ በመስጠት እያበረታታ ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የፊዚክስ መምህር አቶ ይብራህ ጎይቶም በበኩላቸው የማጠናከሪያ ትምህርቱ የሚሰጠው አምቦ አካባቢ በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ላስመዘገቡና የሳይንስ ዝንባሌ ላላቸው ተማሪዎች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም "ከዩኒቨርሲቲው የሚያገኙትን እውቀት በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ለሌሎች ተማሪዎች ማካፈል የሚችሉ በመሆናቸው አላማውን ለማሳካት ዋነኛ ግብአት አድርገን ልንጠቀምባቸው እንችላለን" ብለዋል።

በማጠናከሪያ ትምህርቱ ላይ የተሳተፉት ከአምቦና ጉደር መሰናዶ ትምህርት ቤቶች፣ አዋሮ፣ ፊውቸር ጀነሬሽን ሆፕ፣ ሊበን መጫ፣ በከልቻ-በሪና ሜጢ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 130 ተማሪዎች ናቸው።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌታቸው ፈታሄ ተማሪዎቹ በጽንሰ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር ማየታቸው ወደፊት የሀገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

"ወደፊት ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምትከተለው ኢትዮጵያ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን  መፍጠር የሚችል ብቁ  የተማረ የሰው ሀይል በብዛትና በጥራት መፍጠር ይቻላል " ብለዋል።

የፊውቸር ጀነሬሽን ትምህርት ቤት ተማሪ  ናቶሊ ሲራክ  እንዳለው  የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሚሰጠው የማህበረሰብ አገልግሎት የማጠናከሪያ ትምህርት ፕሮግራም ላይ ሲሳተፍ ለሶስተኛ ጊዜ ነው፡፡

" በየትምህርት ቤታችን በንድፈ ሃሳብ የተማርነውን  በቤተ ሙከራ በማየታችን መነቃቃትን ፈጥሮልናል " ብሏል። 

በየትምህርት ቤታቸው የተግባር ትምህርት የሚከታተሉባቸው በቂ ቤተ መከራዎች እንደሌሉ የተናገረው ደግሞ የአምቦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ኦሊያድ ለማ ነው፡፡

" የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሚሰጠውን የማህበረሰብ አገልግሎት ተጠቃሚዎች በመሆናችን በተግባር ትምህርቶች እንድንነቃቃ ረድቶናል "ብሏል፡፡

   

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2009 የአዕምሯዊ ንብረት መረጃዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መያዝ የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ የሙከራ ትግበራ ተጀምሯል።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት የጀመረው የሙከራ ትግበራ የአዕምሯዊ ንብረት አውቶሜሽን ሥርዓት (አይፓስ) የሚል መጠሪያ ያለው መሆኑን ገልጿል።

የፅህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ ወይዘሪት ዙልፋ አብዱ ለኢዜአ እንደገለጹት የአውቶሜሽን ስርዓቱ በኢንፎርሜሽን ኮሙዮኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመታገዝ የፓተንት፣ የንግድ ምልክትና የኮፒራይት መረጃዎችን ይመዘግባል።

የተመዘገበውን የአዕምሯዊ ንብረት መረጃ በቋት ውስጥ የሚያከማች በመሆኑ በወረቀት የነበረውን ኃላቀር የመዝገብ አሰራር ያስቀራል።

ስርዓቱ በጽህፈት ቤቱ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ ያሳድር ለነበረው የሰነድ መጥፋት ችግር ዓይነተኛ መፍትሔም ይሆናል።

የአዕምሯዊ ንብረት መረጃዎችን ማስመዝገብ የሚፈልጉ ተቋማትና ግለሰቦች አገልግሎቱን በፍጥነት ማግኘት እንደሚያስችላቸውም  ወይዘሪት ዙልፋ አስረድተዋል።

ቴክኖሎጂው በዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት ድርጅት ድጋፍ የተዘረጋ ሲሆን ሁለቱ ተቋማት እ.አ.አ ከ2015-2017 የመረጃዎች አያያዝ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ የቀረጹት ፕሮጀክት ነው።

በፕሮጀክቱ አማካኝነት ከዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት ድርጅት የመጡ ባለሙያዎች ለኢትዮጵያውያን ስልጠና ሰጥተዋል።

በፅህፈት ቤቱ የሚገኙ 10 ሺህ የአዕምሯዊ ንብረት ሰነዶችን ወደ ዲጂታል ስርዓት የማስገባት ስራም አከናውነዋል።

የሙከራ ትግበራ የጀመረው የአውቶሜሽን ቴክኖሎጂ ስርዓት (አይፓስ) በስራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታትና ተሞክሮዎችን በመውሰድ በቀጣዩ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ መታቀዱን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት ድርጅት አባል በመሆኗ ከድርጅቱ የተለያዩ ድጋፎችን እንደምታገኝ ገልጸዋል።

አዕምሯዊ ንብረት ማለት የሰው ልጅ አዕምሮ ውጤት የሆኑ የፈጠራ ሥራዎች ሕጋዊ መብት ሲሆን በፓተንት፣ በንግድ ምልክትና በኮፒራይት ዘርፎች የሚገኙ የፈጠራ ስራዎችን ያካትታል።

Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን