አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Tuesday, 04 April 2017

ድሬዳዋ መጋቢት 26/2009 በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን አርብቶ አደሩን ወደ ከፊል አርሶ አደርነት ለመለወጥ እየተካሄዱ ያሉት የልማት ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ሀገር አቀፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ገለጹ

የጋራ ምክር ቤት አባላቱ  የኢዴፓ፣ የኢህአዴግ፣ የአንድነት፣ የመኢብን፣ የአትፓ፣ የቅንጅት፣ የኢዴአን፣ የኢፍዴሀግ እና የኢሰዴፓ አመራሮች  በዞኑ ስድስት ወረዳዎች እየተሰሩ ያሉ የተለያዩ የልማት ተግባራትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

ከተመለከቷቸው መካከል የትምህርት፣ የመንገድ፣ የመንደር ማሰባሰብ ፣የመስኖ ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃና  ሌሎችንም የመሠረተ-ልማት አውታሮች ይገኙበታል፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ትዕግስቱ አወሉ  በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት በድርቅ ሣቢያ በዞኑ  የተከሰተን ችግር ለመፍታት አርብቶ አደሩን በአንድ አካባቢ በማሰባሰብ ህይወታቸውን ለመቀየር የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው፡፡ 

የእንስሳት መኖና የምግብ ሰብል  እንዲያመርቱ እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ የሚደረገውን ጥረትም አድንቀዋል፡፡ 

አርብቶ አደሩ በተለይ የእርሻ ስራ እንዲለምድ ፣ በመንደር የማሰባሰቡን ተግባርና መንደሮችን  ከዋና የአስፋልት መንገዶች ጋር የሚያገናኙ መስመሮችን  በመዘርጋት ህይወቱን ትርጉም ባለው መንገድ ለመቀየር የሚከናወነው ስራ መጠናከር እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ መስፍን ሽፈራው በበኩላቸው በዞኑ የአርብቶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ እየተሰሩ የሚገኙ ልማቶች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ልማቱ ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር መሠረት የሚጥልና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 

"እዚህ በረሃ ይህን የመሰለ አረንጓዴ ልማት መመልከት እጅግ ያስደስታል፣አርብቶ አደሩን ወደ አርሶ አደርነት ለመለወጥ የሚደረገው ጉዞ ይበረታታል" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሠላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሪ  አቶ ወንደሰን አካሉ ናቸው፡፡

ሥራውን በግብርና ባለሙያዎች የማገዙና በመንደር የማሰባሰቡን ጉዞ በማጠናከር ገበያ ተኮር ምርቶች እንዲመረቱ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የሲቲ ዞን ዋና  አስተዳደሪ አቶ አብዲ ወሊ ለጋራ ምክር ቤቱ አባላት እንደገለፁት በፌደራልና በክልሉ መንግስት የተቀናጀ ጥረት ከ3ሺህ ሄክታር በላይ የሚያለሙ 50 ጥልቅ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡

ለእንስሳትና ለሰው የሚያገለግሉ የውሃ ገንዳዎችና የውሃ ማጓጓዣ ቱቦዎች ተዘርግተው አርብቶ አደሩ እየተጠቀመባቸው ይገኛል፡፡

ለግብርና በተዘጋጀ 2ሺህ ሄክታር መሬት  ላይ  በመንደር የተሰባሰቡ 2000 የሚሆኑ አባወራ አርብቶ አደሮች በግብርና ሥራ እንዲሰማሩ ተደርጓል፡፡

አቶ አብዲ እንዳመለከቱት ምርጥ ዘርና ትራክተሮችን ተከፋፍሎ አርብቶ አደሩ  በዓመት ሶስት ጊዜ በቆሎና ማሽላ  እያመረተ ይገኛል፡፡

አርብቶ አደሩ  ለእንስሳት  በቂና ዘላቂ የመኖ ምርት እያመረተ በድርቅ ሣቢያ የሚደርስ የመኖ ችግርን  በመከላከል  ራሱን  ከመቻል አልፎ  ድርቅ ለሚያጠቃቸው ሌሎች የክልሉ ዞኖች ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡

በመንደር ለተሰባሰቡት አባወራዎች የጤና፣ የንፁህ መጠጥ ውሃና የትምህርት መሠረተ-ልማቶች እንደተሟላላቸው ያመለከቱት አቶ አብዲ  በቀጣይ  ገበያ ተኮር በሆኑ የጥጥ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ እንዲሰማሩ የሙያ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ወሊ ሐጂ መሐመድ  በክልሉ በድርቅ ሣቢያ በአርብቶ አደሩ ላይ የሚደርሱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመረውን የመንደር ማሰባሰብ ስራ በማጠናከር  ህይወቱን  ለመለወጥ  እየተደረገ ያለው ጥረት  ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዓመት ሶስቴ በማምረት ቤተሰብን ከመመገብ ተሻግረው ምርታቸው ለገበያ የሚያቀርቡ ከፊል አርብቶ አደሮች እየተፈጠሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በሲቲ ዞን አዲጋላ ወረዳ የሚኖሩት ከፊል አርብቶ አደር አህመድ ሐሰን እንዳሉት በተሰጣቸው አንድ  ሄክታር መሬት ላይ ለሁለተኛ ጊዜ በቆሎ በማምረት ራሳቸውን ችለዋል፡፡

አምና በመኖ እጥረት እንስሳት ቢጎዱባቸውም  ዘንድሮ ባመረቱት መኖ  ችግር እንዳልደረሰባቸውም ገልጻዋል፡፡

" እኔ አሁን የተወለድኩ ሰው ነኝ፤መንግስት ላድረገልኝ ድጋፍ አመሰግናለሁ፤በቀጣይ ራሴን ችዬ የገቢ ማግኛ የገበያ ምርቶችን አመርታለሁ"  ብለዋል፡፡

የመኢሶ ወረዳ አርብቶ አርብቶአደሮች ተወካይ አቶ  መሐመድ አብዱላሂ በበኩላቸው " በአካባቢው እንስሳት በድርቅ እንዳይጎዱ የመኖ ምርት በመስኖ እያመረትን ነው፡፡ በመኖ ራሳችንን ችለን ዶሎ፤አፍዴር፣ደገሃቡር ለሚገኙ አርብቶ አደሮች እየላክን ነው" ብለዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ግራር ጃርሶ መጋቢት 26/2009 አሁን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በኑሯቸው ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻላቸውን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ግራር ጃርሶ ወረዳ የሚኖሩ ሴት አርሶ አደሮች ገለጹ።

የኢህአዴግ (የኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ህወሃትና ደኢህዴን) ሴቶች ሊግ አመራር አባላት በግራር ጃርሶ ወረዳ የሚገኙ ግንባር ቀደም የሆኑና ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን ሴት አርሶ አደሮች ጎብኝተዋል።

ግንባር ቀደም ሴት አርሶ አደሮቹ ለቡድኑ እንደገለጹት፤ በአገሪቷ ተግባራዊ እየሆነ ባለው የገጠር ልማት ፖሊሲ ተጠቀሚ ለመሆን ችለዋል።

የሚሰጣቸውን የግብርና ፓኬጅ ትምህርቶች በሚገባ በመከታተልና ተግባራዊ በማድረግ በኑሯቸው ላይ ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል።

ወይዘሮ ዓይናለም ጥላሁን እንደሚሉት፤ የግብርና ባለሙያዎች በሚሰጧቸው ምክር አማካኝነት ስራቸውን በማሻሻላቸው ቀድሞ ከሚያገኙት የበለጠ ማምረት ችለዋል። ከዕለት ጉርስ ባለፈም ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን አሳድገዋል።

አርሶ አደሯ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ያላቸው ሲሆን፤ በባንክም 80 ሺ ብር ቆጥበዋል።

በዚሁ ወረዳ የሚገኙት ሌላዋ አርሶ አደር ወይዘሮ አስካለ ከበደ፤ እስከ አምስት መቶ ሺ ብር የሚገመት ቋሚና ተንቀሳቃሽ ሃብትና 80 ሺ ብር በባንክ እንዳላቸው ይናገራሉ።

በዚህም ልጆቻቸውን በአግባቡ ማስተማር እንደቻሉና የራሳቸው ህይወት እንደተቀየረ ይመሰክራሉ።

በተመሳሳይ ቡድኑ በወረዳው እስከ 500 ሺ ብር ሃብት ያላቸው አርሶ አደሮችን ስራ ተመልክቷል።

ሴት አርሶ አደሮቹ እንደሚናገሩት፤ ተግተው በመስራታቸው ጥሩ የመኖሪያ ቤት ገንብተዋል። ልጆቻቸውን እያስተማሩ ናቸው። ሌሎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ከማሟላት አልፈው ገንዘብ እየቆጠቡ ናቸው።

በስፍራው ተገኝተው ጉብኝት ያደረጉ የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ አመራር አባላት በበኩላቸው ሴት አርሶ አደሮቹ ያካበቱት ሃብትና የፈጠሩት ኢኮኖሚያዊ አቅም በራስ መተማመናቸውና የመደራደር አቅማቸውን እንዳጎለበተው መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

ሴቶች በአካባቢያቸው ያለውን ሃብትና ጉልበታቸውን ተጠቅመው መለወጥ እንደሚችሉ የሚያሳይ ጥሩ ተሞክሮ መሆኑንም ነው የገለጹት።

እንደ አመራር አባላቱ ገለጻ፤ ሴት አርሶ አደሮቹ በራስ መተማመናቸው ከፍ ያለ ነው። ይህ ደግሞ የፈጠሩት ኢኮኖሚያዊ አቅም ጠንካራ በመሆኑ የተገኘ ነው።

የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ ሊቀ መንበር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንደገለጹት፤ እውነተኛ የሴቶች ነጻነት ማረጋገጫው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እውን መሆን ነው።

የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተደራጀ መልኩ እንዲንቀሳቀሱና የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያዳብሩም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በገጠር ትራንስፎረሜሽን የሴቶች መለወጥ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው መደረጉን አመልክተው፤ “ለውጥ እየመጣ መሆኑን የዛሬ ባለ ጥሩ ተሞክሮ ሴቶች ህይወት ላይ ይንጸባረቃል” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት “አደረጃጀቶችን በመጠቀም የፖለቲካ አቅም በማጎልበትና ሌሎች ሴቶች እንዲጠነክሩ በማድረግ የመሪነት ሚና እየተጫወትኩ ነው” ብለዋል።

የሊጉ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መጋቢት 28 ቀን 2009 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም ግምገማ የሚያደርግ ሲሆን፤ የዚህ ጉብኝት ዓላማም በተጨባጭ የተገኘውን ለውጥ መገምገም መሆኑ ታውቋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2009 'የኢትዮ-ሱዳን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ወዳጅነት ለሌሎች አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው' ሲሉ የአገራቱ መሪዎች ገለጹ።

አገራቱ ነጻ የንግድ ቀጠና ለመመስረት በዝግጅት ላይ ናቸው።

የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ይገኛሉ።

ፕሬዚዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የአገራቱን ሁለንተናዊ ግንኙነትና ትብብር በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ከውይይቱ በኋላም ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

የአገራቱ መሪዎች በዚሁ ጊዜ የኢትዮ- ሱዳን የረጅም ዓመታት ታሪካዊ ወዳጅነት ለሌሎች አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም አገራቱ በኢኮኖሚ ያላቸውን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ከኢትዮጵያ ሱዳን ድረስ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩን አስታውሰዋል።

ከኢትዮጵያ ሱዳን ወደብ ድረስ የባቡር መሰረተ ልማት ለመዘርጋት አስፈላጊው ጥናት መካሄዱንና በሚቀጥሉት ወራት ወደ ትግበራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሱዳንን ወደብ መጠቀም መጀመሯንና በተያዘው ዓመትም ወደቡን በመጠቀም ማዳበሪያ ማስገባቷን ነው የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም።

አገራቱ በኤሌክትሪክ ሃይል መተሳሰራቸውም ለኢኮኖሚያዊ ትስስራቸው ማሳያ ነው ብለዋል።

የአገራቱን የረጅም ዓመታት ወዳጅነት በኢኮኖሚው ዘርፍ የበለጠ እየተጠናከረ መምጣቱንና ለሌሎች አገራት ምሳሌ እንደሚሆን ነው አቶ ሃይለማርያም የተናገሩት።

''በሱዳን የሚከሰተው ማንኛውም የጸጥታ ችግር የኛም ችግር ነው።በኢትዮጵያ የሚከሰት ማንኛውም የጸጥታ ችግር የሱዳን ችግር ነው ስለዚህ በደህንነትና በጸጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንሰራለን''ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም

የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ የሁለቱ አገራት ብቻ አለመሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ሶማሊያን ከአልሸባብ ለመከላከልና መልሶ ለማቋቋም ከኢጋድ አባል አገራት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ነው የገለፁት።

በቅርቡ ወደ ካርቱም በመሄድ ተመሳሳይ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በበኩላቸው አገራቱ ቀደም ሲል በጋራ ለመስራት የተፈራረሟቸውን ስምምነቶች ተግባራዊ እያደረጉ ነው ብለዋል።

ሁለቱ አገራት በኢኮኖሚ በማህበራዊና በፖለቲካ ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩም ነው የገለፁት።

ኢትዮጵያ ከሱዳን ቤንዚል ማስገባቷና ሱዳንም ከኢትዮጵያ 300 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ሃይል መጠቀሟ የኢኮኖሚ ትስስሩ ማሳያ ነው ብለዋል።

በደህንነትና ጸጥታ ጉዳዮች የገቧቸው ስምምነቶችም ተግባራዊ መደረጋቸውን ፕሬዚዳንት አልበሽር አመልክተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአካባቢያዊና ማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ ጥናት ከተጠናቀቀ በኋላ ሶስቱ አገራት የጋራ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2009  የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል አገሮች ለስደተኞች የሚሰጡት የፀረ- ቲቢና ኤች. አይ. ቪ /ኤድስ አገልግሎት የተሻለና ጥራት ያለው እንዲሆን በቅንጅት እንዲንቀሳቀሱ ተጠየቀ።   

ኢጋድ ከአባል አገራቱ የፀረ- ቲቢና ኤች. አይ. ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት ያካሄደው ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል። 

የኢጋድ የጤናና ማህበራዊ ልማት መርሃ ግብር ስራ አስኪያጅ ፋቲሃ አልዋን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢጋድ አባል አገሮች በቀጣናው ስደተኞች ከአንዱ ወደ ሌላው አገር የሚፈልሱበት መሆኑን ተገንዝበው በጤናው መስክ ለሚሰጡት አገልግሎት መቀናጀት ይኖርባቸዋል። 

''ይህም አገራቱ የተሻለና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ከማድረግ ባለፈ ያለውን ጥቂት ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላል'' ነው ያሉት።

የስደተኞች ጉዳይ የአህጉሩ ትልቅ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን የጠቀሱት ስራ አስኪያጇ፤ አባል አገሮቹ ለሕዘባቸው ከሚያቀርቡት የጤና አገልግሎት ጋር በፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲያስተሳስሩትም ጠይቀዋል።     

የተሻለና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት ኢጋድና አባል አገራቱ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያገኙትን የገንዘብ ድጋፍ በአግባቡ እንደሚጠቀሙና የሚያጋጥማቸውን ችግሮች በጋራ ለመፍታተ እንደተስማሙ አብራርተዋል። 

በኢጋድ የጤና ፕሮግራም አማካሪ ዶክተር ፀጋዬ ለገሰ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የአገራቱ በቅንጅት መስራት በስደተኞች መጠለያ ውስጥ የቲቢ ተጠቂዎችን በፍጥነት ለይቶ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙና በሽታውን የተላመደ የቲቢ በሽታ እንዳይኖር ለማድረግ ያስችላል። 

የኤች.አይ.ቪ /ኤድስ የምርመራ አገልግሎትና የመድሃኒት አቅርቦት እንዲኖር እንዲሁም አስፈላጊውን "የስደተኞችን መረጃ ለመለዋወጥና ግብዓት ለማቅረብም ይረዳል" ሲሉ አክለዋል።

በዚህም በስደተኞች መጠለያ ወስጥ ለሚከሰተው የቲቢ በሽታ የህክምና አገልግሎት ለማመቻቸት፣ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በሚመክረው መሰረት የጤና አገልግሎት ለማቅረብና አገልግሎትን ለማስፋፋት ነው።  

በኢጋድ የስነ-ተዋልዶ፣የእናቶችና ህፃናት ጤና አስተባበሪ ዶክተር ፋጡማ አደን "በጉባዔው ለእናቶችና ህፃናት በተለይም በቲቪ በሽታ ለተጠቁና በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ለተያዙ ሰዎች እንዴት የተሻለና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንደምንሰጥ ተወያይተናል" ብለዋል። 

በዚህም አባል አገራቱ በበሽታዎቹ ላይ የሚሰጡት የምርመራ፣ የመረጃ ማሰባሰብ፣ የማስተዳደርና ወጥ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

''የአባል አገሮቹ ቁርጠኝነት መኖር ደግሞ የስነ-ተዋልዶ አገልግሎት አሰጣጡ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ያደርጋል'' ነው ያሉት።   

ኢጋድ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ የኀብረተሰብ ክፍሎች የሚሰጠው የጤና አገልግሎት የተሻለና ጥራት ያለው እንዲሆን ዝግጁ መሆኑንም አስተባባሪዋ አረጋግጠዋል።       

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ መጋቢት 26/2009 በምስራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ዝቋላ ወረዳ ጥብቅ ደን ውስጥ ለደረሰው ቃጠሎ ተጠያቂ የሆነው ግለሰብ በስምንት ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት።

ግለሰቡ በጥብቅ ደን ውስጥ  በድብቅ ገብቶ ከሰል ለማክሰል የለኮሰው እሳት 631 ሔክታር የተፈጥሮ ደን እንዲወድም ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኝነት ሃላፊ ምክትል ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ እንደገለጹት አሻ ቲማ የተባለው ግለሰብ ቅጣቱ የተወሰነበት መጋቢት 1/2009 ዓ.ም.በወረዳው አዴሌ ሜጫ ቀበሌ ገበሬ በማህበር ጥብቅ ደን ላይ ውድመት በማድረሱ ነው።

በዚህም በሦስት ቀናት ቃጠሎ 21 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የተፈጥሮ ደን ሲወድም እሳቱን ለማጥፋት ከሰባት ሺህ በላይ የአካባቢው ነዋሪ ፣ የፖሊስና የአየር ሃይል አባላት መሳተፋቸውንም አመልክተዋል።

የሊበን ዝቋላ ወረዳ ፍርድ ቤት መጋቢት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ድርጊቱን በፈፀመው ግለሰብ ላይ ቅጣቱ የተላለፈበት መሆኑን   ምክትል ኮማንደሩ አስታውቀዋል፡፡

''ህዝቡ  በበጋ የተፋሰስ ልማት በነቂስ ወጥቶ በሚረባረብበት ወቅት በደን ልማት ላይ እንዲህ ዓይነት ጉዳት መድረሱ አሳዛኝ ነው'' ያሉት ምክትል ኮማንደር አስቻለው ህብረተሰቡ ደኑን ከማንኛውም ጥቃት እንዲጠብቅ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

Published in ማህበራዊ
Tuesday, 04 April 2017 22:32

በቀን አስር!!

ሚስባህ አወል /ኢዜአ/

ሰሞኑን በመገናኛ ቡዙሃን እየተዘከረ ወይም እየተከበረ ያለ አንድ አንኩዋር ጉዳይ አለ፡፡ የትራፊክ አደጋን በጋራ ለመከላከል ያስችል ዘንድ ታስቦ የተሰናዳ ነው፡፡

ከጥር 22 ቀን 2009 ጀምሮ እስከ ግንቦት 7/2009 ድረስ  “ከትራፊክ አደጋ የፀዳ የትራንስፖርት አገልግሎት ለሀገራዊ ህዳሴ” በሚል መሪ ቃል ነው እየተዘከረ ያለው፡፡

እኛም ይህን አሳሳቢ ጉዳይ መሰረት አድርገን በፍትህና ህግ ዘገባችን ልንዳስሰው ሞከርን! እነሆ!!

የትራፊክ አደጋ በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት አሳሳቢ መሆኑን የአለም ባንክና የዓለም ጤና ድርጅት በጋራ ባወጡት መግለጫ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡

ተቋማቱ በ2015 ባወጡት ሪፖርት መሰረት በአካባቢው ሀገራት በየቀኑ ከአምስት እስከ አስራ አምስት ዓመት የሚሆኑ ህፃናት ህይወታቸውን በጎዳና ላይ በዚሁ አደጋ እንደሚያጡና ከዚህ ቀደም በአካባቢዎቹ ገዳይ ከሚባሉት ወባና ሌሎች በሽታዎች በላይ ገዳይ እየሆነ መምጣቱን ይጠቁማሉ፡፡

ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያም ስንመጣ ለዓብነት ብንጠቅስ ባለፈው 2008 ዓ.ም ብቻ በትራፊክ አደጋ ከሶስት ሺሀ ስምንት መቶ በላይ ዜጎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የወጣው ሪፖርት ያሳያል፡፡

ሪፖርቶቹን እዚህ ጋር ገታ አደርገን ወደ ፍትህ ስርዓቱ ጎራ ስንል ከሚገኙ በርካታ ፋይሎች አንድ ሁለቱን እንይ፡፡

ፋይሎቹን ያገኘነው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ሲሆን ከሳሽ የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ነው፡፡

ተከሳሽ ወርቁ አሰፋ ይባላል፡፡ የተከሰሰበት ወንጀል ደግሞ ሾፌር በመሆኑ የሌላ ሰው የህይወት ደህንነት የመጠበቅ የሙያ ግዴታ እያለበት በቸልተኝነት ነሀሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 2፡00 /ሁለት ሰዓት/  ሲሆን የሚያሽከረከረውን የአንበሳ አውቶቡስ ደህንነት ሳያረጋግጥና የቴከኒክ ችግር ያለበት መኪና በመንዳት በነዋሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የክሱ መዝገብ ያስረዳል፡፡

በዚህም ሳቢያ በእለቱ ከሽሮ ሜዳ ወደ ኪዳነምህረት በሚወስደው መንገድ ኪዳነምህረት ጠበል ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ግራ መስመራቸውን ይዘው ይጉዋዙ የነበሩ ዳንዔል ገበየሁ፤ ዘሪሁን ጉዱ፤ አስራት ማሞ ፤ ሮማን ማሞ ፤ ድርብነሽ ተክሌ ፤ ምስራቅ ምስጋናው እና አስራተ ማሪያም የተባሉ  ሰባት ግለሰቦችን በመግጨት ህይወታቸው እንዲያልፍ በማድረጉ በፈፀመው በቸልተኝነት ሰውን የመግደል ወንጀል ክስ ሊቀርብበት ችሏል፡፡

ይህም በ1996 ዓመተ ምህረት የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 572 በመተላለፍ የተመሰረተው ክስ የተከሳሽን የቤተሰብ ሁኔታና ሌሎች የቅጣት ማቅለያ ደንቦችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ ስምንት ዓመት ከአራት ወር ፅኑ እስራት እና ሁለት ሺህ ብር ቅጣት በመጣል ፋይሉን ዘግቷል፡፡

ተመሳሳይ ባይሆንም አንድ አነስ ያለ የቅጣት ውሳኔ የተጣለበትን ፋይል እንመልከት፡፡ ከሳሽ  አሁንም የፌደራል ዓቃቤ ህግ ሲሆን ተከሳሽ ደግሞ አዳነ ጌታቸው ይባላል፡፡

የክስ መዝገቡ እንደሚያትተው ከሆነ ተከሳሽ የሰውን ህይወት እና ደህንነት የመጠበቅ የሙያ ግዴታ እያለበት ይህን ባለማድረጉ በታህሳስ 3 /2007 ዓ.ም በግምት ከጠዋቱ  አንድ ሰዓት ሲሆን ቄራ አካባቢ ልዩ ቦታው ቄራ መስጊድ አካባቢ በመንገዱ ላይ ከቀኝ ወደ ግራ ትጓዝ የነበረችውን ስሟ ያልታወቀውን ሟች የመንገዱንና የትራፊኩን እንቅስቃሴ መሰረት አድርጎ በማሽከርከር ቅድሚያ ሰጥቶና ጥንቃቄ አድርጎ  ሊያልፍ ሲገባው ይህን ሳያደርግ በመኪናው የፊት የግራ ክፍል ሟችን በመግጨት ባደረሰባት ጉዳት ህይወቷ እንዲያልፍ ማድረጉን ያትታል፡፡

በዚህም ሳቢያ በተከሰሰበት በቸልተኝነት የሰው መግደል ወንጀል ክስ የቅጣት ውሳኔ አግኝቷል፡፡

የቅጣት ውሳኔው እንደሚያስረዳው ከሆነ ተከሳሹ ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የወንጀል ድርጊት የሌለው በመሆኑ የቤተሰብ አስተዳዳሪነቱን እና ተከሳሹ ሟችን ከወደቀችበት አንስቶ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመውሰድ  ህክምና እንድታገኝ ሙከራ ማድረጉ በመረጋገጡ የወንጀሉን ድርጊት ያቀለለት መሆኑን ያብራራል፡፡

በመሆኑም ተከሳሹ  በስድስት ወር ቀላል እስራትና በአንድ ሺህ ብር እንዲቀጣ ውሳኔ በመስጠት ፋይሉን ዘግቷል፡፡

እዚህ ጋር የቅጣት ውሳኔው በእጅጉ እንዲቀል ካደረገው ነጥብ አንዱ ከደረሰው አደጋ በሁዋላ ህይወትን ለማዳን የተደረገው ጥረት ይመስለኛል፡፡

በተለይ በምሽት በመኪና አደጋ የሚቀጠፉ ሰዎች በአብዛኛው ህይወታቸው የሚያልፈው አደጋ አድርሰው ጥለው በሚሸሹ አሽከርካሪዎች ሳቢያ መሆኑ ሲነገር ይሰማል፡፡ በተለይ ጠጥተው በሚያሽከረክሩ ግለሰቦች አማካይነት መሆኑ ነው በስፋት የሚነገረው፡፡

በቅርቡ የገጠመኝን አንድ የአደጋ ወሬ ላውጋችሁ ጉዋደኛዬ በዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነው፡፡ ዝዋይ የምትኖር አንድ አብሮ አደግ እህት አለችው፡፡ ያደጉት ደብረብርሃን አጎታቸው ጋር መሆኑን አጫውቶኛል፡፡

ታድያ እኚህ አሳዳጊ አጎቱ ይታመሙና ደብረብርሃን ሄዶ ጠይቆ ሲመለስ ዝዋይ ለምትኖረው መሰሉ ይነግራትና ወደ ዲላ ይወርዳል፡፡

ነዋሪነቷን በዝዋይ ለበርካታ አመታት ያደረገችወና በንግድ ስራ የምትተዳደረው መሰል ታድያ የእረፍት ቀኗን ለመጠቀም እሁድን ጠብቃ በአባዱላ ተሳፍራ ወደ ደብረብርሃን ጉዞ ትጀምራለች፡፡

ዳሩ ምን ያደርጋል አዲስ አበባም ሳትደርስ ገና በንጋቱ 12 ሰዓት ላይ 12 ሰዎችን ጭኖ ይበር የነበረው አባዱላ የህዝብ ማመላለሻ ‹‹ቀይ ሽብር›› የሚል ቅጥያ ከተሰጠው ሲኖ ትራክ ጋር ይገጣጠማል፡፡ ይህ ጣዕረ ሞት የተጫጫነው ሲኖ በፍጥነት ከሚሽከረከረው አባዱላ ጋር ይላተማል፡፡ በዚሁ ዘገናኝ አደጋም በተሸከርካሪው  ውስጥ የነበሩ 12ቱም ሰዎች በዛ የእረፍት ቀን መጀመሪያ በደንብ እንኩዋን መንጋቱን ሳያዩ ላይመለሱ እስከወዲያኛው ተሰናበቱ፡፡

ነዋሪነቷ ዝዋይ እድገቷ ደግሞ ደብረብርሃን የሆነችው አመለ ሸጋዋ መሰሉ በሁለቱ ከተሞች የሚያውቋትን ነዋሪዎች እምባ ካስረጨች ሶስት ወር እንኩዋን እንዳልሞላት ነበር ያጫወተኝ ጓደኛዬ ፡፡  

በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመጣው የትራፊክ አደጋ በቀን ከሚሞቱት 10 ሰዎች በተጨማሪ 31 ሰዎች ለአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ የትራንስፖርት ባለስልጣን ከሚያወጣው ሪፖርት መረዳት ይቻላል፡፡

ታድያ በቀን 10ን እና 31ን በዓመት ሲያሰሉት አያስፈራም ለዚህም ሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ መሆን የሚችልበት የንቅናቄ መድረኮች በየጊዜው ሊፈጠሩ ይገባል መልእክታችን ነው፡፡

 

                                                                                                                                                                                                                                         ቸር እንሰንብት!!

 

አርባምንጭ መጋቢት 26/2009 በጋሞ ጎፋ ዞን ሁለት ወረዳዎች አዲስ የበቆሎ ትል መከሰቱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ አሰታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አሸብር ደምሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የትሉ ወረርሽ የተከሰተው በዞኑ "ቦንኬ" እና "ዑባ ደብረፀሐይ" በተባሉ ሁለት ወረዳዎች ነው።

በበቆሎ ላይ ጉዳት ያደርሳል የተባለውና "የአሜርካ ትል" የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ ትል የበቆሎ ውስጠኛውን ሙሽራ በመቁረጥና በመብላት ሰብሉን ከጥቅም ውጭ ያደርጋል፡፡

ትሉ የሚራባው በቢራቢሮ መሳይ ነፍሳት መሆኑ ከፍተኛ የስርጭት ፍጥነት እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ትሉ ከኬኒያ በመሻገር በደቡብ ኦሞ ዞን ከአራት ቀን በፊት ቢስተዋልም በፈጣን ሁኔታ በጋሞ ጎፋ ዞን በሁለት ወረዳዎች 261 ሄክታር የበቆሎ ማሳ መውረሩን ገልጸዋል።

ትሉ ከአበባና ቅጠሉ ይልቅ በበቆሎው የውስጥኛው ክፍል ላይ የሚቀመጥ መሆኑ ለመድኃኒት ርጭት ምቹ አለመሆኑንና ለመቆጣጠርም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል አስረድተዋል።

"በዝናብ መዘገየት ምክንያት በዞኑ አብዛኛው የበልግ ማሳ በዘር አለመሸፈኑ ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩን የገለጹት አቶ አሸብር፣ ወረርሸኑ በተከሰተባቸው አካባቢዎች "ማላታይን" የተባለ ኬሚካል የመርጨት ሥራ መጀመሩን አመልክተዋል።

እንደ አቶ አሸብር ገለጻ፣ የትሉን ወረራ ለመቆጣጠር የሚያስችል አስቀድሞ የተዘጋጀ አንድ ሺህ ሊትር ማላታይንና በበቂ ሁኔታ የሰለጠነ ባለሙያ አለ፡፡

ርጭቱ በጠብታ መልክ የሚካሄድና ለአንድ በቆሎ ሰብል ሁለት ጠብታ ማላታይን የሚደረግ በመሆኑ ሰፋፊ ማሳዎችን በአጭር ጊዜ ለማዳረስ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

በዞኑ ከሚመረተው 31 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ዓመታዊ ምርት 50 ከመቶ የሚሆነው ምርት የሚገኘው ከበልግ እርሻ ሲሆን ከዚህ ውስጥም በቆሎ ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2009 የኬንያው ኮከብ ኪፕቾጌ ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች በመግባት "አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዘግባለሁ" አለ።

በአሁኑ ወቅት ክብረ ወሰኑን ለመስበር በዝግጅት ላይ መሆኑን ኬኒያዊው አትሌት ኪፕቾጌ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጿል።

ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች ማጠናቀቅ ከተቻለ ቀጣይ የሩጫ ምትሀታዊ ብቃት ይሆናል።

ማራቶንን በሳይንሳዊ ልምምድ፣ በአመጋገብ፣ ስነ ልቦናና ስፖርት ትጥቅ  በመታገዝ ከሁለት ሰዓት በታች እንዲሮጡ በናይኪ ከተመረጡ ሶስት ምርጥ አትሌቶች መካከል የኬንያው ኪፕቾጌ የመጀመሪያው ነው።

የምስራቅ አፍሪካ ኩራቶች የሆኑት የቦስተን ማራቶን አሸናፊ ኢትዮጵያዊው ሌሊሳ ዴሲሳ እና የረጅም ርቀት ሯጩ ኤርትራዊው ዘረሰናይ  ታደሰ ከኬኒያው አትሌት ቀጥሎ ማራቶንን በ1:59:59 ሰዓት ያጠናቅቃሉ ተብለው ተገምተዋል።

ይህ  በኬንያዊው ዴኒስ ኪሜቶ በ2014 ተይዞ የነበረውን 2:02:57 ሰዓት ክብረወሰን በሶስት ደቂቃ የሚያሻሽል ነው።

"ይህ እብደት አይደለም፤ ማንም ሰው ከሁለት ሰዓት በፊት አልሮጠም፤ እናም የመጀመሪያው ሰው መሆን እፈልጋለሁ" ሲል ኪፕቾጌ ተናግሯል።

የአምስት ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮኑ አትሌት ባለፈው ዓመት የለንደን ማራቶንን 2: 03: 05 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ በመሆን ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

ኪፕቾጌ ወደ ማራቶን ሩጫ በመምጣት ከ2013 ወዲህ ከተሳተፈባቸው ስምንት ውድድሮች ውስጥ ሰባቱን አሸንፏል።

ታዋቂው "ራነርስ ወርልድ" የተሰኘው መፅሄት በትንታኔ ላይ ተመስርቶ በሰጠው ትንበያ ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች ማጠናቀቅ የሚቻለው እ.ኤ.አ በ2075 ነው፤ የናይኪ ሀሳብ ግን "ተጨባጭ ያልሆነ ነው" በማለት ገልጿል።

ውድድሩ የፊታችን ግንቦት በጣልያን ሞንዛ ይካሄዳል።

ነፋሻማው አየር ከፈጣኑ ሩጫ ጋር ተዳምሮ አትሌቶቹ ባላቸው አቋም ላይ ችግር እንደሚሆንባቸው ቢነገርም የኮፕቾጌ አሰልጣኝ ግን አትሌቱ እንደሚሳካለት እርግጠኛ አቋም አላቸው።

ናይኪ ሯጮቹን ለመርዳት የተለየ ጫማና ክብደታቸውን ሊያስተካክሉ የሚችሉ ትጥቆችን ቢያዘጋጅም ኪፕቾጌ ግን ከእነዚህ ነገሮች ይልቅ ችሎታና በራስ መተማመን ልዩነት ለማምጣት እንደሚረዳ ይገልፃል።

"ልዩነቱ የአስተሳሰብ ብቻ ነው፤ አንተ እንደማይሆን ታስባለህ እኔ ግን እንደሚሆን አውቃለሁ" በማለትም ተናግሯል።

"ከተሳካልኝ ውጤቱ ለእኔና ለሩጫው ዓለም ብቻ ሳይሆን ለሰው ዘርም ነው፤ ከተባለው ሰዓት በታች ከሮጥኩኝ የሰው ልጆች ገደብ አላቸው የሚለውን አስተሳሰብ መቀየር እችላለሁ" ብሏል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2009 የትራንስፖርት ማህበራት በትራፊክ ደህንነት ዙሪያ ለአሽከርካሪዎች ሥልጠናዎች በመስጠት አደጋን ለመቀነስ መሥራት አለባቸው ተባለ።

የትራንስፖርት ባለሥልጣን ከትራንስፖርት ማኅበራት ጋር በብሔራዊ ደረጃ በሚካሄደው የትራፊክ አደጋ ቅነሳ ንቅናቄ ላይ ተወያይቷል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታው አቶ አብዲሳ ያደታ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ማኅበራት በትራፊክ ደህንነት ዙሪያ አሽከርካሪዎች ያላቸውን ግንዛቤ ሊያጎለብቱ ይገባል።

ለዚህም ማኅበራቱ ለአሽከርካሪዎች በትራፊክ ደህንነትና አደጋ መከላከል ዙሪያ የሚያጠነጥን ተከታታይ ሥልጠናዎችን ሊያመቻቹ ይገባል ብለዋል።

ከዚህም ጎን ለጎን ማኅበራቱ የተሽከርካሪዎች ወቅታዊ ፍተሻ በማካሄድ ደህንነታቸውን ሊያረጋግጡ ይገባልም ነው ያሉት።

በተጓዳኝ አሽከርካሪዎች ሙያዊ ብቃትና ሥነ-ምግባረ የተላበሱ መሆናቸውን ሊከታተሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

እነዚህና ሌሎች የቅደመ-መከላከል ሥራዎችን በመሥራት ማኅበራት አደጋን መቀነስ እንደሚችሉ ነው ሚኒስትር ዴኤታው እምነታቸውን የገለጹት።

የውይይቱ ታዳሚዎች የትራፊክ አደጋ ዋና ተዋናይ አሽከርካሪዎች በመሆናቸው በሙያዊ ብቃትና ሥነ-ምግባር ላይ ሊተኮር ይገባል ብለዋል።

የትራንስፖርት ማህበራቱም  የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

የትራንስፖርት ባለሥልጣን ‹‹ከትራፊክ አደጋ የፀዳ የትራንስፖርት አገልግሎት ለአገራዊ ህዳሴ›› በሚል መሪ ቃል ከጥር እስከ ግንቦት 2009 ዓም ድረስ የሚቆይ የትራፊክ አደጋ ቅነሳ ንቅናቄ እያደረገ ይገኛል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2009 የኢትዮጵያና የሱዳን መከላከያ ሠራዊቶች የጋራ ድንበር ደህንነት በመጠበቅ ተባብረው እየሰሩ መሆናቸውን የ12ኛ ክፍለ ጦር አስታወቀ።

የመከላከያ ሠራዊት ከሌሎች የአገር ውስጥ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር በቤንሻንጉል ጉምዝ ጉባ ወረዳ የሚገነባውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ድንበር ለ24 ሰዓት እየጠበቀ ይገኛል።

በክፍለ ጦሩ የስድስተኛ ሬጅመንት አዛዥ ኮሎኔል አረጋዊ ኪዳነ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ሠራዊቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ ለ24 ሰዓት ጥበቃ ያካሂዳል።

በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይም ሆነ በቀጠናው እንከን እንዳይፈጠር ሁል ጊዜ ያለእረፍት እየሰራ ነው።

ሠራዊቱ ይሄን ተልእኮ በብቃት እየተወጣ በመሆኑ "የግድቡና የአካባቢው ደህንነት አስተማማኝ ነው" ብለዋል።

አካባቢውን ሰርጎ ከሚገቡ የፀረ ሰላም ኃይሎች ለመጠበቅ በሚደረገው ሥራ ከሱዳን መከላከያ ሰራዊት ጋር በመተባበር "በጋራ የድንበሩን ደህንነት እየጠበቅን ነው" ብለዋል።

በታላቁ የህዳሴ ግድብም ሆነ በሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ መጥፎ የሚያስብ ጠላትን  በሩቅ ሳለ የመከላከል አቅምና ድንበር ለመጣስ ከቀረበም በአስተማማኝ የሚደመስስ ኃይል መኖሩን ነው ያመለከቱት።

ይሄን ለማሳካት በድንበር አካባቢ በጋራ ድንበር ደህንነት ከሱዳን መከላከያ ሠራዊት ጋር የሚያደርገው ትብብር ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

ጸረ ሰላም  ኃይሎችን በመከላከል ረገድ ሁለቱን አገሮች በሚያዋስናቸው ድንበር አካባቢ  ከሱዳን መከላከያ ሰራዊት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ኮሎኔል አረጋዊ ገልፀዋል።

በተለይ በቅርቡ ድንበር ጥሰው በገቡ ጸረ ሰላም ኃይሎች ላይ ኢትዮጵያ እርምጃ ስትወስድ ወደ ሱዳን ሊያመልጡ የነበሩትን በመያዝ "የአገሪቷ ሠራዊት አሳልፎ መስጠቱ የትብብሩን ውጤታማነት ያሳያል" ነው ያሉት።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ  ፖሊስ፣ ፀረ ሽምቅ ኃይልና ሚሊሻም የአካባቢውን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ኡስማን አህመድ ገልፀዋል።

ምክትል ከሚሽነሩ እንደገለጹት፤ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከፌደራል ፖሊስና ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ስራዎችን ሰርተዋል።

ቅንጅቱ በግንባታ ላይ የሚገኘውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ በሰላም ለማከናወን ማስቻሉን ገልፀው፤ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ተቀናጅቶ መስራቱ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በቅርቡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጥቃት ለመሰንዘር ወደ ቤንሻንጉል ጉምዝ የገቡ የፀረ ሰላም ኃይሎች መደምሰሳቸውና መማረካቸው ይታወቃል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን