አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 03 April 2017

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2009 የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ለሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ።

ፕሬዚዳንቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተደረገላቸው ግብዣ ነው ለጉብኝት  አዲስ አበባ የሚገቡት።

ሁለቱ አገሮች የረጅም ዓመታት ታሪካዊና ባህላዊ ግንኙነት አላቸው።

የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ እንደገለጹት፤ ሁለቱ አገሮች ከህዝብ ለህዝብ ወዳጅነታቸው ባለፈ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን እያሳደጉ መጥተዋል።

አገሮቹ የንግድ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር በመንገድ መሰረተ ልማት የጀመሩትን ትስስር በባቡር መስክም ለመድገም መታቀዱን ዶክተር ነገሪ ተናግረዋል።

ኢትዮ - ሱዳን ያላቸው ግንኙነት ለሌሎች አገሮች ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ በምታካሂደው የልማት እንቅስቃሴ የሱዳን ድጋፍ እንዳልተለያት ነው የገለጹት።

አገሮቹ የዓባይ ወንዝን በፍትሃዊነት መጠቀም ላይ የጋራ መግባባት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

በፕሬዚዳንቱ የሶስት ቀናት ጉብኝት የሁለቱን አገሮች ሁለንተናዊ ግንኙነት የሚያጠናክሩ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ይፈረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2009 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ከሙያዊ አስተዋጾኦ ባሻገር የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ሠራተኞች ገለጹ።

የኤጀንሲው አመራሮችና ሠራተኞች የህዳሴው ግድብ መሰረት የተጣለበትን 6ኛ ዓመት አክብረዋል።

ግድቡ የፈጠረው የ'ይቻላል' መንፈስ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶች መነቃቃት እንዲፈጠር ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰይፈ ደርቤ ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገው ድጋፍ አሻራውን የሚያሳርፍበት መሆኑን ይበልጥ ተገንዝቦ ድጋፉን እንዲቀጥል ተቋሙ መረጃ የመስጠት ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ግድቡን በራስ አቅም ለመገንባት መቻሉ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ለተጀመሩና ለሚጀመሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ይበልጥ የመነሳሳት ስሜት እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

ሕዝቡና መንግስት ግድቡን ለመገንባት የወሰዱት ቁርጠኛ አቋም የፕሮጀክቱን አስቸጋሪ ስራ በማለፍ ግንባታውን 57 በመቶ ማድረስ ማስቻሉን አብራርተዋል።

ግድቡ በፍጥነት እንዲከናወንና በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተቋሙ ከሚሰራቸው ዜና፣ ዜና ትንታኔ፣ ፕሮግራሞችና ዶክመንተሪዎች ባሻገር ሠራተኛው የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ይቀጥላል ብለዋል።

የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የኤጀንሲው የቴሌቪዥንና ፕሮዳክሽን ዋና አዘጋጅ ወይዘሮ ወርቅነሽ ፈይሳ የግድቡ መጀመር አገሪቷ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካ መስክ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ማስገኘቱን ገልጸዋል።

ግድቡ ካሳደረው የ'ይቻላል' መንፈስ ባሻገር ብሔራዊ መግባባት፣ የስራ ዕድል፣ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም ለአገር ውስጥ ቱሪዝምና ንግድ መነቃቃት መፍጠሩን ተናግረዋል።

በሠላምና በዲፕሎማሲ መስክ እየተደረጉ ያሉ ውይይቶችንም ግድቡ ካመጣቸው ጠቀሜታዎች መካከል ናቸው ሲሉ ጠቅሰዋል።

ግድቡ ሲጠናቀቅ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉና የኤሌክትሪክ ስርጭት ሽፋን አሁን ካለበት 51 በመቶ ወደ 90 በመቶ እንዲያድግ ያደርጋል ነው ያሉት።

ለዓሣ እርባታ፣ ለቱሪዝም መዳረሻ፣ ለውጭ ምንዛሪ ግኝትና ከጎረቤት አገሮች ጋር ለሚፈጠር ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚኖረውን ጠቀሜታም አብራርተዋል።

ግድቡን ምክንያት አድርገው የሚካሄዱ ኹነቶችና ማኅበራዊ መስተጋብሮችን ከማጎልበትና የቁጠባ ባህልን ከማሳደግ ባሻገር የአገሪቷን በጎ ገጽታ እየገነባ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ኤጀንሲው የግድቡ ግንባታ እስካሁን ያስገኘውን ጥቅም አስመልክቶ ለህዝቡ በየጊዜው መረጃ እያዳረሰ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ለፕሮጀክቱ ስኬት ምሳሌ የሚሆኑ ግለሰቦችን፣ ተቋማትና የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘገባዎቹ ማቅረብ እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል።

የግድቡን የግንባታ ሂደት ሕዝቡ እንዲያውቅ ማድረግ ድርጅቱ የተጣለበት ሙያዊ ኃላፊነት መሆኑንና ይህም በቀጣይ ለሚገነቡ አዳዲስ ፕሮጀክቶች መነቃቃት እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የኤጀንሲው ሠራተኞችም ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።

ጋዜጠኛ ሰለሞን ዲባባ አባት አርበኞች አገሪቷንና ህዝቦቿን ነጻ ለማውጣት ውድ ህይወታቸውን እንደከፈሉ ሁሉ ይህ ትውልድም "ድህነትን ድል ለማድረግ እውቀትና ሃብቱን እያዋጣ ነው" ብሏል።

ትውልዱ እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ ደማቅ ታሪክ ሆኖ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ ጋዜጠኛው ህዝቡን የማሳወቅና የማነሳሳት ሥራውን አጠናክሮ መስራት አለበት በማለት አስተያየት ሰጥቷል።

አቶ ሰለሞን እምሩ በበኩላቸው የህዝቡ አስተዋፅኦ ቀጣይ እንዲሆን ጋዜጠኛው በዓል ሲከበር ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ ድጋፉን የሚያጠናክሩ የተለያዩ መረጃዎችን ማቅረብ ይጠበቅበታል ብለዋል።

የኤጀንሲው የፕሮግራምና ፕሮዳክሽን ዳይሬክተር አቶ ነጋሲ አምባዬም ትውልዱ የተጠየቀው እንደ አባቶቻችን የህይወት መስዋዕትነት ሳይሆን ካለው እውቀትና ሀብት አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ነው ብለዋል።

ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ከሚያደርጉት ሙያዊ እስተዋፅኦ ባሻገር አቅማቸው የሚችለውን ድጋፍ የማድረግ ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

የህዳሴው ግድብ መሰረት የተጣለበት 6ኛ ዓመት "ታላቁ የህዳሴ ግድባችን አገራዊ ህብር ዜማ የህዳሴያችን ማማ" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2009 ለከተሞች ህዝብ የሚመጥንና ነዋሪዎች የጤና ፍላጎት በበቂ ደረጃ መልስ የሚሰጥ የመሰረታዊ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ቀርጾ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ''ከተሞቻችን ለጤና ተስማሚና ለኑሮ ምቹ እናድርግ'' በሚል መሪ ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ አገር አቀፍ የከተማ ጤና ጉባኤ  ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።

በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ካለው የኢኮኖሚ እድገትና ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የአኗኗር ዘይቤ እየተቀየረ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በከተሞች የህዘብ ቁጥሩ ማደግ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ማቅረብ የግድ እንደሚል ነው ጥናቶች የሚያረጋግጡት።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር ከበደ ወርቁ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የከተሞች መሰረታዊ ጤና አገልግሎት አሰጣጥን በመቅረጽና ተግባራዊ በማድረግ የተለያዩ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የከተማ አስተዳደሮች፣ ጤና ቢሮዎች፣ የምርምር ማዕከላት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ሌሎች አካላት አገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ነው ሚኒስትር ዴዔታው ያመለከቱት።

“ለከተማው ህዝብ የሚመጥን እና እያደገ ለመጣው የነዋሪዎች የጤና ፍላጎት በበቂ ደረጃ መልስ መስጠት የሚችል የመሰረታዊ ጤና አገልግሎት” ተቀርጾ ተግባራዊ  መሆን እንዳለበት ነው የገለጹት።

መንግስት ተግባራዊ ያደረገው የከተማ የሕብረተሰብ ጤና መርሃ ግብር ገና በጅምር ደረጃ የሚገኝና ብዙ ተግዳሮቶች ያሉበት መሆኑን ጠቁመው፤ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና አሃድ መልሶ ክለሳ በማድረግ በአዲስ አበባ ሶስት ክፍለ ከተሞች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ተሞክሮ በተለያዩ ከተሞች የማስፋት ስራው እየተተገበረ እንደሚገኝም ነው ያመለከቱት።

የቤተሰብ ጤና ቡድን በማደራጀት በበቂ በማህበረሰቡ ውስጥ የሥራ ስምሪት የሚሰጥበትና የተገልጋዮች ቅብብሎሽ የሚፈጥር በመሆኑ በጤና ጣቢያዎች አስፈላጊው የሰው ኃይል ሊሟላ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ዶክተር ታቦር ገብረመድሕን በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰቡን የጤና ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ አዳዲስና  የተለያዩ የጤና ስትራቴጂዎች ማዘጋጀት አለበት።

የከተማ ጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር የመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ በአካባቢና በከተማ ጤና ጉዳይ መረጃን መሰረት ያደረገ ፖሊሲን መተግበር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በተለይም ከፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ የንጽህና አቅርቦት እንደሌሎች ዘርፎች ሁሉ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንዲሰጡት ጥሪ አቅርበዋል።

''ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል አንዱ የከተማውን ነዋሪ ጤንነት መጠበቅ ነው'' ያሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የመልካም አስተዳደር ፍትህና ማህበራዊ ዘርፍ ፖሊሲ ዕቅድ አፈጻጸምና ክትትል ውጤታማነት ሚኒስትር አቶ ሙክታር ከድር ናቸው።

የከተሞች እድገትና የነዋሪውን ሕዝብ "ማህበራዊ የግል የኑሮ ደረጃና የአኗኗር ዘይቤ መቀየር የጤና ችግሮች ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል" ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

መንግስት የሕብረተሰቡን የጤና ችግር ለመፍታት የተለያዩ የጤና ስተራቴጂዎችና ፕሮግራሞችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክተዋል።

በከተሞች የሚኖረው ህዝብ ከአምስት አመት በፊት ከነበረው 15 ነጥብ 2 ሚሊዮን ከሃያ አመት በኋላ ከአምስት እጥፍ በላይ በማደግ 42 ነጥብ 3 ሚሊዮን እንደሚሆን ከማእከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ጉባኤውን  የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤድ) በቅንጅት እንዳዘጋጁት ታውቋል።      

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2009 የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ብሄራዊ ፌዴሬሽኖችና ክልሎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አሳሰበ።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በዘጠኝ ወር ዕቅድና ተልዕኮዎቹ አፈጻጸም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ነው።

የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን ጨምሮ በአገሪቱ የሚገኙ ማዕከላት የሚፈለገውን አገልግሎት እየሰጡ አይደለም።

ማዕከላቱን ለታለመላቸው ዓላማ በማዋል ረገድም ክፍተቶች ይስተዋላሉ።       

የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ራሱን አለማስተዋወቁና የሌሎች አካላትን ድጋፍ አለማግኘቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጥ እንዳደረገው ለአብነት አንስተዋል።   

የስፖርት ማዕከላትና ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ከመገንባት ባሻገር አጠቃቀማቸው ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ማዕከላት ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ብሄራዊ ፌዴሬሽኖችና ክልሎች ትልቁን ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

"መንግሥት የስፖርት ልማቱን ለማሳለጥ የማዘውተሪያ ስፍራና የዘርፉን ባለሙያዎች እጥረት ለማስወገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው" ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው በበኩላቸው ከባላድርሻ አካላት ጋር እየተደረገ ያለው ውይይት የአካዳሚውን ተልዕኮ ለማሳካት የሚያግዙ ምክረ ሀሳቦች እንደሚገኙበት ታምኖበታል ነው ያሉት።  

በዘጠኝ የስፖርት ዓይነቶች 484 ስፖርተኞችን እያሰለጠነ የሚገኘው አካዳሚው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር ችግር ፈቺ የስፖርት ጥናትና ምርምር ማካሄዱን ጠቁመዋል። 

በሜዳ እድሳት ምክንያት የማዘውተሪያ ችግር፣ የትራንስፖርት፣ የበጀትና ክለቦች የአካዳሚ ሰልጣኞችን ያለመመልከት ችግሮች መኖራቸውንም አንስተዋል።

እንዲያም ሆኖ ከ480 በላይ ሰልጣኞች ለብሄራዊ ቡድንና ለክለቦች መሸጋገራቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ አካዳሚው የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ከክለቦችና ከብሄራዊ ፌዴሬሽኖች ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል። 

በውይይቱ የአካዳሚው የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም ተገምግሟል።

የባለሙያዎችን አቅም በመገንባት፣ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማድረግ፣ በህጻናት የስልጠና ሰነድ ዝግጅት እንዲሁም ለብሄራዊ ቡድን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ረገድ ችግሮች መኖራቸው በግምገማው ተለይተዋል። 

ውይይቱ ነገ በብሄራዊ ቡድን ድጋፍና ክትትል፣ በችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮች እንዲሁም በስፖርት ህክምናና ማገገሚያ ማዕከል ማቋቋም ዙሪያ ይቀጥላል።  

Published in ስፖርት

ነቀምቴ መጋቢት 25/2009 ኦህዴድ በጥልቅ ተሃድሶው ለሕብረተሰቡ የገባውን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ በጽናት እንደሚረባረቡ የምስራቅ ወለጋ ዞን የኦህዴድ አባላትና ደጋፊዎች ገለፁ ፡፡

አባላቱ ይህን የተናገሩት ዛሬ የኦህዴድ 27ኛ ዓመት ምሥረታ በዓልን በዞን ደረጃ በምስራቅ ወለጋ ዞን በጉቶ ጊዳ ወረዳ በዑኬ ከተማ በተከበረበት ወቅት ነው፡፡

አባላቱና ደጋፊዎቹ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ በክልሉ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነትን በማስወገድ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጥልቅ ተሀድሶ የተገባውን ቃል በተግባር ለማረጋገጥ የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ይሰራሉ።

ከአባላቱ መካከል የጉቶ ጊዳ ወረዳ ነዋሪ አቶ ዮሴፍ ተርፋሳ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት፣ በዓሉ ኦህዴድ/ኢህአዴግ በውስጡ የተፈጠረውን ችግር ቆም ብሎ አይቶ ጥልቅ የተሀድሶ ግምገማ ባካሄደበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል።

ኦህዴድ በተሃድሶው ወቅት ለህብረተሰቡ የገባውን ቃል ደረጃ በደረጃ መፍትሔ እየሰጠ በመሆኑ የህዝብ ተጠቃሚነት እስኪረጋገጥ ድረስ  መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

የነቀምቴ ከተማ ቀበሌ 03 ነዋሪ አቶ ቱላም ጉዲና በበኩላቸው፣ አመራሩ ብቻ ሳይሆን አባላትና ደጋፊዎችም ቅን፣ ታዛዥና ትክክለኛ የህዝብ አገልጋይ መሆን እንዳለባቸው ገልፀው፣ ለተግባራዊነቱ አርአያ ሆኜ እንቀሳቀሳለሁ ብለዋል ።

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የምስራቅ ወለጋ ዞን ኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባድር አምዳ በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት፣ ለህብረተሰቡ የተገባውን ቃል ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ የድርጅቱ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች በታላቅ የሕዝብ ወገንተኝነትና ቁርጠኝነት  መስራትና መታገል እንዳለባቸው አስረድተዋል ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ሞገስ ኤደኤ በበኩላቸው፣ የዞኑ ሕዝብ በመተባበርና በአንድነት በመነሳሳት በድህነትና በኋላቀርነት ላይ መዝመት እንዳለበት ገልጸዋል።

በአገሪቱ ብሎም በክልሉ ቀጣይነት ያለውን ዕድገት በማስመዝገብ ሁሉም ዜጋ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ዕድል ለመፍጠር በአንድነት መነሳት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ጂግጂጋ መቱ ጎባ ሀረር ፍቼ መጋቢት 25/2009 የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) የተመሰረተበት 27ኛ ዓመት በዓል በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በኢሉአባቡር ፣ በመዳወላቦ ዩኒቨርሲቲ፣ በድሬደዋ ፣ በሐረርና በሰሜን ሸዋ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከበረ፡፡

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ትናንት የተከበረው የድርጅቱ በዓል የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪና  የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ  ተማሪ የሆኑ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች በተሳተፉበት  የፓናል ውይይት ነው፡፡

በውይይቱም ኦህዴድ ባለፉት ዓመታት ለኦሮሞ ህዝብ ያስገኘውን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ስኬቶች እና ያጋጠማቸውን ፈተናዎች የተመለከተ ጽሁፍ ቀርቦ በተሳታፊዎች ተመክሮበታል፡፡

የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኦህዴድ ሰብሳቢና በተቋሙ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ሊቀመንበር አቶ ገብረወልድ ጋዲሳ እንደገለጹት ድርጅቱ ኦሮሚያ ክልልን መምራት ከጀመረ ወዲህ አመርቂ የልማትና የዴሞክራሲ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡

በተለይ በዓሉ ድርጅቱ ባለፉት ዓመታት የተጓዘበት አቅጣጫ መልሶ በመገምገም የተሻለ ስራ ለማከናወን ተሀድሶ የጀመረበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ የተለየ ያደርገዋል።

በጅግጅጋ ከተማ የኦህዴድ ኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች አስተባባሪ አቶ ክፈተው አየለ በበኩላቸው ድርጅቱ ባለፉት ዓመታት የታየው የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን እየታገለ ለውጤት መብቃቱን ተናግረዋል፡፡

በጅግጅጋ ከተማ ከሰባት መቶ በላይ የኦህዴድ አባላት እንደሚገኙ የተናገሩት አስተባባሪው " በከተማዋ እየተከናወኑ ባሉ  የልማት ስራዎች ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ "ብለዋል።

ድርጅቱ ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ በተሃድሶ የጀመሯቸውን የማስተካከያ እርምጃዎች ለማጠናከር የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉም አባላቱና ደጋፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ 

በተመሳሳይ በኢሉአባቦር ዞን የቢሎ ኖጳ ወረዳ የኦህዴድ አባላትና ደጋፊዎች በዓሉን ባከበሩበት ወቅት እንደገለጹት ድርጅቱ ባስገኘው ድል አርሶ አደሩ  የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ከማግኘት አልፎ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም ምርታማነቱን  ማሳደግ ችሏል፡፡

ከአባላቱ መካከል በወረዳው የአገታ ቀበሌ አርሶአደር ደበላ ጅፋር እንዳሉት ባለፈው ስርዓት አርሶአደሩ ትኩረት ተነፍጎት ሰፊ መሬት ይዘው በድህነት ይኖር ነበር፡፡

በኦህዴድ/ኢህአዴግ የትግል ውጤት ትኩረት አግኝተው በግብርና ባለሙያ ድጋፍ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ተጠቅመው በመስመር እየዘሩ በማልማት ከራሳቸው አልፎ ለገበያ የሚበቃ ምርት እያገኙ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሴቶች የመሬት ባለቤትነታቸው እንዲረጋገጥና ከወንዶች እኩል የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የቻሉት በድርጅቱ የትግል ውጤት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ሴት አርሶአደር አቦነሽ ቶለሳ ናቸው፡፡

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ደጀኔ ከበደ በበኩላቸው ኪራይ ሰብሳቢነት፣ጠባብነት እና የአክራሪነት ዝንባሌዎችን ከመሰረቱ በመናድ  የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማጎልበት ከህብረተሰቡ ጋር ስራቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመደወላቦ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት የድርጅቱን በዓል  ትናንት በባሌሮቤ ከተማ  በፓናል ውይይት አክብረዋል።

ከበዓሉ ተሳታፊዎች  መካከል የሶስተኛ ዓመት የህግ ተማሪ  ኡመር ቴና ድርጅቱ የብዙሃኑን ተጠቃሚነት  እንዳይረጋገጥ ማነቆ የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ለህዝብ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚጠበቅበት ጠቅሶ ለዚህም የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

"ድርጅቱ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ባደረገው ትግል የኦሮሞ ህዝብ ቋንቋው ፣ ባህሉና ማንነቱ ሊከበር ችሏል" ያለችው ደግሞ  የማህበራዊ ሳይንስ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ወጣት ኤልሳቤት ጥለሁን ናት፡፡

በዩኒቨርሲቲው  የኢህአዴግ ድርጅቶች  ሰብሳቢ አቶ ዘላለም ጥላሁን የድርጅቱ አባላትና  ደጋፊዎች ኪራይ ሰብሳቢነትንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመግታት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የባሌ ዞን የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ኢብራሂም በበኩላቸው  ኦህዴድ የኦሮሞ ህዝብ በአፍ መፍቻ ቋንቋው  እንዲማርና  ራስን  በራስ ለማስተዳደር እንዲበቃ ታሪክ መስራቱን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ድርጅቱ ከህዝቡ ጋር በመሆን  በተሀድሶ መድረኮች  የተነሱ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም  አቶ አህመድ አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በድሬዳዋ አስተዳደር ከ2 ሺህ በላይ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች በዓሉን  በፓናል ውይይት አክብረዋል።

በበዓሉ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል ወጣት አብዲ አብደላ እንደገለጸው መራራ ትግል በማድረግ በተገኘው ድል  ህዝቡ ለዘመናት ሲጠይቅ የነበረው የኦሮሞ የማንነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ አስችሏል።

የኦህዴድ/ ኢህአዴግ ታጋይዎች በከፈሉት መስዋትነት የተገኘውን ድል ወጣቱ በመንከባከብ ለዘላቂ ሰላም፣ልማትና እድገት ርብርብ እንደሚያደረጉና ለስኬታማነቱም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

" ድርጅቱ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በሚያካሂደው የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የህዝቡ ተጠቃሚነት እየጎለበተ በመምጣት ላይ ይገኛል "ያሉት ደግሞ  የትምህርት ባለሙያው አቶ ሰቦ አህመድ ናቸው።

የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ባካሄዱት የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ህዝቡ ሲያነሳቸው የነበሩ የሰላም የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመፈተሽ አፋጣኝ ምላሽ በተሰጠበት ማግስት በዓሉ መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው አመልክተዋል።

በአስተዳደሩ የቀበሌ ዜሮ ሁለት  ነዋሪ ወይዘሮ ዘይነባ ኢብሮ የድርጅቱ ታጋዮች  በከፈሉት   መስዋዕትነት በተገኘው ድል ሴቶች በሀሉም ዘርፍ  እኩል የመሳተፍና የመጠቀም መብት መጎናጸፋቸውን ተናግረዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው ኦህዴድ/ ኢህአዴግ ከምስረታው ማግስት ጀምሮ ባካሄደው ትግል  በርካታ ድል በማስመዝገብ የኦሮሞ ህዝብና ሌሎችም ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

እንደ አስተዳደሩ ተጨባጭ ሁኔታ ኦህዴድ/ ኢህአዴግ ከእህትና አጋር ድርጅቶች  ጋር  ነዋሪውን በልማት ፣በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና በሌሎች ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።

በተመሳሳይም የኦህዴድ  የምስረታ በዓል በሐረሪ ክልል ትናንት በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል፡፡

እንዲሁም በኦሮሚያ  ሰሜን ሸዋ ዞን  ኩዩና ውጫሌ  ወረዳዎች ያሉ አርሶ አደሮች ፣የመንግስት ሰራተኞችና የከተማ ነዋሪዎች በዓሉን በጽዳት፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራና  በፓናል ውይይት  አክብረዋል ።

የኩዩ  ወረዳ ሴቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ስንቅነሽ ዱገባሳ  በድህነት ላይ የተጀመረውን ዘመቻ ከግብ ለማድረስ ሕዝቡ  የሚያደርገውን ድጋፍ  አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

በወጫሌ ወረዳ በተከበረው በዓል ላይ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰለሞን መኮንን እንደገለጹት  የኦህዴድ 27ኛ ዓመት በዓል ልዩ የሚያደርገው  ድርጅቱ ከጥልቅ ተሃድሶ ማግስት ለቀጣይ ተልዕኮ  ራሱን እያዘጋጀ ባለበትና ድህነትን ለማጥፋት እንደ ሃገር  ርብርብ የሚደረግበት ወቅት በመሆኑ ነው።

 

Published in ፖለቲካ

ነገሌ መጋቢት 25/2009 ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ ለማሰባሰብ በአራት የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል ለሶስት ሳምንታት የሚቆይ  የእግር ኳስ ውድድር በነገሌ ቦረና ከተማ ትናንት ተጀመረ ።

የከተማው  ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ሌሊሳ አራርሳ እንደገለፁት የውድድሩ ዓላማ ለግድቡ ግንባታ ከመግቢያ ትኬት ሽያጭ  ገቢ  ለማሰባሰብና ተተኪ ስፖርተኞች ለማፍራት ነው ።

በውድድር ላይ በከተማው የሚገኙ የሳህል ክሊኒክ ፣ የነፊሳ ዱቄት ፋብሪካ ፣ የገናሌ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ቁጥር ሶስትና የካዚም ዱቄት ፋብሪካ እግር ኳስ ቡድኖች ተሳታፊ ናቸው ፡፡

የነገሌ ከተማ ዜሮ ሁለት ቀበሌ ነዋሪ  ወጣት አብዲኑር አህመድ በሚቀጥለው ዓመት በቡድን ታቅፎ እግር ኳስ መጫወት እንደሚፈልግና አቅሙ በፈቀደ መጠን  ለህዳሴ ግድብ ቦንድ ለመግዛት ማቀዱን  ገልጿል፡፡

በከተማው የዜሮ ሶስት  ቀበሌ ነዋሪና የቀን ሰራተኛ ወጣት አክሊሉ አየለ በበኩሉ ገንዘብ ኖሮት ቦንድ መግዛት ባይችልም ለህዳሴ ግድብ በሚደረግ እንዲህ አይነት ጥረት በመሳተፍ የድርሻውን ለማበርከት ፍላጎቱ መሆኑን ተናግሯል ።

 

እየተዝናኑ ለሀገር ልማት የበኩላቸውን ድጋፍ ለማበርከት የከተማው ነዋሪዎች ውድድሩን ስታዲዮም ተገኝተው እንዲከታተሉት የውድድሩ አዘጋጆች ጥሪ አቅርበዋል ።

Published in ስፖርት

የኢፌዲሪ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን መጋቢት 25/2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች እለታዊ የገበያ ዋጋ መረጃ አድርሶናል፡፡

No automatic alt text available.

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 25/2009 የሕፃናት ፍልሰትን ለመግታትና የጉዲፈቻ ሕጻናትን ደህንነት ለመጠበቅ የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር የጀመራቸውን ተግባራት እንዲያጠናክር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ባካሄደው የሚኒስቴሩ የጉዲፈቻ ሕጻናት መብትና ደህንነት አጠባበቅ የክዋኔ ኦዲትና የ2007 ዓ.ም የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ተወያይቷል።

በጉዲፈቻ ህጻናት መብትና ደህንነት አጠባበቅ ረገድ ሚኒስቴሩ አዋጆችና መመሪያዎችን ተከትሎ ከመተግበር አንጻር የአሰራር ግድፈቶች እንደነበሩበት የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት አመልክቷል።

ለአብነትም በ2003 ዓ.ም የተዘጋጀው የብሔራዊ ረቂቅ የሕጻናት ፖሊሲ እስከ 2008 ዓ.ም መጨረሻ እንደሚጸድቅ ቢጠበቅም አለመፅደቁ ተገልጿል።

በሕጻናት ማሳደጊያ ተቋማትና በጉዲፈቻ አስፈጻሚ ድርጅቶች መካከል በግልጽ የሚታወቅ የስራ ግንኙነት መመሪያ ተዘጋጅቶ ባለመሰራጨቱና ባለመተግበሩ ህጻናቱ ለችግር ከመጋለጣቸው በተጨማሪ ለተቋማቱ ጥቅም ማስገኛ ሰለባ እንደሚሆኑም ተጠቁሟል።

የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትሯ ወይዘሮ ደሚቱ ሀምቢሳን ጨምሮ የሚኒስቴሩ የስራ ኃላፊዎች ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሯ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ከቤት ወደ ጎዳና የሚያደርጉት ፍልሰት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅም በአገሪቷ ከፍተኛ የሕጻናት ፍልሰት የሚታይባቸው ከተሞች በጥናት ተለይተው ለህጻናቱ ገንዘብ መስጠት ሳይሆን በሙያ ሰልጥነው ስራ እንዲፈጥሩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የስነ-ልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉና ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ለማድረግም በክልሎች የሕጻናት ማቆያ ተቋማት እንዲመሰረቱ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በመጪው ሰኔ 9 የዓለም ህጻናት ቀን ሲከበር አራት ሺህ የጎዳና ላይ ሕጻናትን ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ መታቀዱን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ቤተሰብ የሌላቸውን ሕጻናት በማሳደጊያ ተቋማት በማስገባትና በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ በመስጠት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በማሳደጊያ ተቋማት የሚገቡና በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ የሚሰጡ ህጻናትን ደህንነት ለመጠበቅ ወጥ መመሪያ ተዘጋጅቶ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መሰራጨቱንም አክለዋል።

ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ ሚኒስቴሩ የራሱ የስራ ሂደት ከፍቶ እየሰራ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

በአገር ውስጥ ያልተቻሉትን እንደ መጨረሻ አማራጭ ለውጭ አገር ጉዲፈቻ መስጠት እንደሆነም ገልጸዋል ሚኒስትሯ።

ቋሚ ኮሚቴው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሕጻናትን ፍልሰት ለመግታት የጀመራቸው እንቅስቃሴዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጿል።

ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከአባ ገዳዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመተባበር የህጻናት ፍልሰትን ለመግታትና የጉዲፈቻ ህጻናትን ደህንነት ለመጠበቅ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስቧል።

የሕጻናት ጉዳይ የኅብረተሰቡ አጀንዳ እንዲሆን መስራት እንዳለበትም ነው ቋሚ ኮሚቴው ያስገነዘበው።

ለውጭ አገር ጉዲፈቻ የተሰጡ ህፃናትን ደህንነት ለመጠበቅ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በየአገራቱ በሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንሲላዎች  የሚደረገው ክትተልና ቁጥጥር እንዲጠናከርም አመልክቷል።

የውጭ አገር ጉዲፈቻን ለመቀነስና በአገር ውስጥ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንዲካተቱ የማስተዋወቅ ስራ እንዲሰራም መክሯል።

በሂሳብ ኦዲት ረገድ ሊታረሙ የሚገባቸው የራሱ ውስንነቶች ቢኖሩበትም ሚኒስቴሩ ከሌሎች የመንግስት ተቋማት አንጻር የተሻለ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ገምግሟል።

የ2007 ዓ.ም የድርጊት መርሃ ግብር አለማዘጋጀቱ የተገለጸ ሲሆን በአስቸኳይ አዘጋጅቶ ለዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት እንዲያቀርብ ቋሚ ኮሚቴው ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅና የመንግስት ሒሳብ አያያዝ መመሪያን በመተላለፍ የተከናወኑ የሒሳብ ኦዲት ግኝቶችን ሚኒስቴሩ ከሂስነት ባለፈ አስቸኳይ የማጣራትና የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባዋልም ተብሏል።

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ  መጋቢት 25/2009 በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) አባላትና ደጋፊዎች ድርጅቱ የተመሰረተበትን 27ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በጋምቤላ ከተማ በፓናል ውይይት አከበሩ።

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ቶሎሳ ዋቅጋሪ በፓናል ውይይቱ ላይ እንደገለጹት፣ ኦህዴድ የደረግ ሥርዓትን ለመጣል ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ያሳየውን ተጋድሎና ድል በፀረ ድህነት ትግሉ በመድገም የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው።

ድርጅቱ ባለፉት ዓመታት በሁሉም የልማት መስኮች ውጤታማ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት የማይናቅ ሚና ማበርከቱንም ገልጸዋል።

ኦህዴድ በየደረጃው ባካሄደው ጥልቅ የተሃድሶ ግምገማም ችግሮቹን ከመለየት ባለፈ  የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

"ድርጅቱ በክልሉ ብሎም በአገሪቱ የተጀመረውን የልማት፣ የፀረ- ድህነትና የሕዳሴ ጉዞ ቀጣይነት ለማረጋገጥ መላ አባላቱንና ሕዝቡን አስተባብሮ እየሰራ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህአዴን) ጽህፈት ቤት ኃላፊና የመንግስት ተጠሪ አቶ ኡኩኝ ኡቡያ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ ኦህዴድ የአምባገነኑን ሥርዓት ለመጣል ከታገሉት ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው።

አምባገነኑን የደርግ ሥራዓት ለመጣል በተደረገው የትጥቅ ትግል ብቻ ሳይሆን በፀረ-ድህነት ዘመቻም ኦህዴድ ባለፉት ዓመታት የአንፀባራቂ የልማት ድሎች ባለቤት ጭምር መሆኑንም ገልጸዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ ከተገኙት የድርጀቱ አባላትና ደጋፊዎች መካከል አቶ ደረጀ መንገሻ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት፣ በጥልቅ ተሃድሶ የተለዩ ችግሮችን በመፍታት በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የተጀመረውን የልማትና የሕዳሴ ጎዞ ለማሳካት ድርጅቱ በትጋት ሊሰራ ይገባል።

ኦህዴድ ከጋህአዴን ጋር ሕብረት በመፍጠር ከልማትና ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራ የገለጹት ደግሞ ሌላው የፓናል ውይይቱ ተሳታፊ አቶ በድሉ ጉግሳ ናቸው።

 በፓናል ውይይቱ ላይ የብአዴን፣ የህወሓትና የደህዴን እህት ድርጅቶች ተወካዮች የእንኳን አደረሳቹህ መልክት አስተላልፈዋል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን