አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 21 April 2017

ሃዋሳ ሚያዚያ 13/2009 የደቡብ ህዝቦች ክልል ሴቶች ማህበር የሴቶችን ሁለንተናዊ አቅም በማጎልበት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ሊሰራ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

የክልሉ ሴቶች ማህበር በሃዋሳ መለስ አካዳሚ ለሴት አመራሮች ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል፡፡

የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት  ሃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ እንዳሉት ሴቶች  ከተናጠል ይልቅ በጋራ ተደራጅተው  በመንቀሳቀስ  በልማቱ የተሻለ  ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡

ሴቶች በሚያደርጉት የለውጥ ጉዞ ውስጥ ተግዳሮት እየሆነ የሚገኘውን እንደ ጠባብነት፣ አክራሪነት እና ኪራይ ሰብሳቢነት መታገል እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ልማት፣ ሰላምና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ለስርዓቱ የህልውና ጉዳይ እንደሆኑ ተናግረው በተለይ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ማህበሩ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አስቴር ይርዳ በበኩላቸው "ስልጠናው በሴቶች የለውጥና የልማት ፓኬጅ፣ በሴቶች ማህበራት አመራር መመሪያዎችና ፓሊሲዎች ዙሪያ ትኩረት ያደርጋል "ብለዋል፡፡

ማህበሩ ሴቶችን በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆኑ አቅማቸውን በማጎልበት በህዳሴ ጉዞ ውስጥ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ እንደሚያግዝም ገልጸዋል፡፡

ለ15 ቀናት በሚቆየው ስልጠና አዲስ አበባ የሚገኙ የክልሉ ተወላጆችን ጨምሮ ከክልሉ ሁሉም ዞኖችና  ልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ  1ሺህ 200  ሴት አመራር አባላት እየተሳተፉ ነው፡፡ 

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 13/2009 በአዲስ አበባ ከተማ መገናኛ አካባቢ የተገነባውና በአንድ ጊዜ 90 ተሽከርካሪዎች የማስተናገድ አቅም ያለው ‘ስማርት የተሽከርካሪ ማቆሚያ’ የሙከራ ሥራ ጀመረ።

በተጨማሪም 50 ተሽከርካሪዎችን የመያዝ አቅም ያለው ‘የመሬት ላይ ተሽከርካሪ ማቆሚያ’ም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

የከተማዋ የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንደገለጸው፤ አዲሱ ዘመናዊ የተሸከርካሪ ማቆሚያ 15 ደረጃዎች አሉት።

መንግሥት በመደበው ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባው የተሽከርካሪ ማቆሚያ በጥቂት ቀናት ውስጥ የሙከራ ሥራውን አጠናቆ ወደ ሙሉ አገልግሎት እንደሚገባ ነው የተመለከተው።

በጽህፈት ቤቱ የመሠረተ ልማት ክፍል ተወካይ አቶ ትንሳኤ ወልደገብርኤል እንደገለጹት፤ የተሽከርካሪዎቹ ማቆሚያዎች በአካባቢው የሚታየውን የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ ያቃልላሉ ተብሎ ይታመናል።

የተሽከርካሪ ማቆሚያው በ170 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ ነው።

ፕሮጀክቱ የሙከራ ሥራውን አጠናቆ ወደ ሙሉ አገልግሎት ሲገባ መንግሥት በተመነው ተመጣጣኝ ክፍያ አገልግሎት ይሰጣል።

ከ20 ለማያንሱ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል እንደሚፈጥርም አቶ ትንሳኤ አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ቅድሚያ በተሰጣቸው በአንዋር መስጊድ፣ በቸርችል ጎዳና እና በወሎ ሰፈር አካባቢዎች የመሬትና ስማርት የተሽከርካሪ ማቆሚያ ግንባታ በመካሄድ ላይ ይገኛል። 

በቀጣይም በመዲናዋ በተመረጡ 60 ቦታዎች የተሽከርካሪ ማቆሚያ ግንባታ ይከናወናል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 13/2009 ለመልካም አስተዳደር መስፈንና ለዜጎች መብት መከበር የዴሞክራሲ ተቋማት የተጣለባቸውን ኃላፊነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አሳሰበ።

ጽህፈት ቤቱ ለኢዜአ በላከው ሳምንታዊ መግለጫ እንዳመለከተው መንግሥት ራሱን በራሱ ማረም እንዲችል ነጻ ሆነው የተመሰረቱት የዴሞክራሲ ተቋማት  የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛሉ።

ለመልካም አስተዳደር መስፈንና ለዜጎች መብት መከበር የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሆነም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከት አስመልክቶ ያደረገውን የምርምራ ውጤትና ምክረ ሀሳብ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን በማሳያነት ጠቅሷል።

ምክር ቤቱም የምርመራ ውጤቱንና ምክረ ሀሳቡን በመርመር ሪፖርቱን መቀበሉና ውሳኔዎች ማሳለፉ የዴሞክራሲያዊ ተቋማቱ ለህግ የበላይነት መረጋገጥና ለዜጎች መብት መከበር እያከናወኑ ያለውን ስራ የሚያሳይ ነው ብሏል።

ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የጀመሩት ውይይትም ለዴሞክራሲ ዕድገት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ነው መግለጫው የጠቀሰው።

የዴሞክራሲ ተቋማቱ የጀመሯቸው ስራዎች የተሀድሶ እንቅስቃሴውን በማገዝ መንግስት ለህግ የበላይነት መከበርና ለዜጎቹ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ መጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳኩ እንደሆነም ፅህፈት ቤቱ አስታውቋል።

ተቋማቱ የጀመሩትን መሰል እንቅስቃሴ የሚያበረታታ መሆኑንና በቀጣይም ይህን ተግባራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አሳስቧል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 13/2009 የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ለኢትዮጵያ የኮሪያ ዘማች ቤተሰቦች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።

ኢትዮጵያዊያን ኮሪያ የዘመቱበት 66ኛ ዓመት መታሰቢያ በኢትዮጵያ የኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክ ተከብሯል፡፡

በበዓሉ የተገኙ የክብር እንግዶችም ለኮሪያ ዘማቾች በተሰራው መታሰቢያ ሀውልት ላይ የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።

በዚህ ወቅት በኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር የሰው ኃይልና ደህንንነት ምክትል ሚኒስትር ሁዋንግ ው ዎንግ “ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ወደ ኮሪያ ያዘመተች ብቸኛ የአፍሪካ አገር በመሆኗ በደም የተሳሰረች አጋራችን ነች” ብለዋል።

ኢትዮጵያና ሌሎች አገራት በከፈሉት መስዋትነት ኮሪያ አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ መድረስ ችላለች ያሉት ሁዋንግ ይህን በማሰብም የኮሪያ መንግስት ለዘማች ቤተሰቦች የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችል ትልቅ ህንፃ ለማስገንባት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።

በቀጣይም አገራቸው ለኢትዮጵያ የኮሪያ ዘማች ቤተሰቦች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው የተናገሩት።

በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር ሙን ሁዋን ኪም "አገሬ በጦርነት ቀጠና በነበረችበት ወቅት ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥላ ስር ከሌሎች አገራት ጎን በመሰለፍ ሰላምና ነፃነትን ለማስከበር በመዋጋቷ ጥልቅ የክብር ስሜት ይሰማኛል" ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ተወካይ አቶ አሰግድ ጌታቸው በበኩላቸው በህዝቦች ደም የተገነባው የሁለቱ አገራት ግንኙነት እየተጠናከረ ሄዷል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ለተያያዘችው የህዳሴ ጉዞ ደቡብ ኮሪያ የበኩሏን ገንቢ ሚና እያበረከተች እንዳለች ተናግረው ለኮሪያ ዘማች ቤተሰቦች ለሚደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

"የቃኘው ሻለቃ የጦር አባላት ያስመዘገቡት አኩሪ የጀግንነት ገድል በአዲሱ ትውልድ ሲዘከር ይኖራል" ብለዋል አቶ አሰግድ።

የኮሪያ ዘማቾች ማህበር ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መለሰ ተሰማ በዓሉ አገሪቱ ለዓለም ሰላም ተልዕኮ ፈር ቀዳጅ በሆነው የጦር ሜዳ ተካፋይ በመሆን በዓለም ሰላም እንዲሰፍን ያላትን ፅኑ እምነት ያሳየችበት ነው ብለዋል።

ወጣቶች የጀግኖች አባቶቻቸውን ገድል እንዲገነዘቡ በዓሉን ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በኮሪያ ጦርነት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ኢትዮጵያም በመንግስታቱ ድርጅት ጥላ ስር በመሰለፍ 6 ሺህ 37 ወታደሮችን አሰልፋ 122 ህይወታቸውን ሲያጡ 536 ወታደሮች ደግሞ ቆስለዋል።

ከዘመቱት ወታደሮች መካከል አንድም የተማረከ ኢትዮጵያዊ ወታደር አለመኖሩ በወቅቱ የዓለማችን መገናኛ ብዙሃን አነጋገሪ አጀንዳ እንደነበር ይታወሳል።

 

Published in ማህበራዊ

ሚያዝያ 13/2009 በደቡብ ሱዳን 14 ግዛቶች በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ቢያንስ 172 ሰዎች መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት አስታወቀ፡፡ 

በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ይፋ ባደረገው መረጃ የበሽታው መከሰት ከታወቀበት እኤአ ሰኔ 18/2016 ጀምሮ እስከአሁን 6 ሺህ 222 ያህል የኮሌራ ህመምተኞች እንዳሉ አመልክቷል፡፡ 

“ደረቅ የአየር ፀባይን ተከትሎ አዳዲስ ታማሚዎች ከአዳዲስ ቦታዎች ሪፖርት መደረጋቸው ቀጥሏል “ያለው የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ጁባ ላይ አዲስ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡  

የተባበሩት መንግስታትን ጠቅሶ ሲጂቲን እንደዘገበው ቀጣዩን የዝናብ ወቅት ተከትሎም ወረርሽኙ እየሰፋ የሚሄድ ይሆናል፤ የማያቋርጠው ግጭት፣ መፈናቀልና በቂ ያልሆነ የውሃና የንፅህና አቅርቦት ሁኔታውን የሚያባብስ ይሆናል፡፡

የኮሌራ በሽታ የምግብ መውረጃንና አንጀትን የሚያጠቃ ሲሆን በአብዛኛው በተበከለ ውሃና ምግብ ይከሰታል፤የከፋ ተቅማጥ በማስከተልም የሰውነት ድርቀቱ ለሞት ይዳርጋል፤በሰአታት ውስጥም የኩላሊት ተግባር እንዲቆም ያደርጋል ፡፡

የተባበሩት መንግስታት አዳዲስና ኮሌራ ይከሰትባቸዋል በተባሉ ደክ፣አዮድ፣ጆንግሊ በተሰኙ ግዛቶች የጆንግሊ የጤና ባለሙያችንና Water, Sanitation and Hygiene (WASH) ቡድኖችን በማስተባበር ምላሽ እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል፡፡ 

ወረርሽኙ ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ካገኘች እኤአ 2011 ጀምሮ የተከሰተ አስከፊ ወረርሽኝ መሆኑም ታውቋል፡፡

የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት በላብራቶሪ እቃዎች እጥረት ሳቢያ አንዳንድ ቦታዎች ላይ  የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ በምርመራ አልተረጋገጠም፤ በመሆኑም ሰብአዊ ድርጅቶች ሁኔታውን ለመድረስ እየሰሩ መሆኑን ዘገባው ገልጿል፡፡

Published in ማህበራዊ

ባህርዳር ሚያዚያ 13/2009 የአፍሪካ ዩንቨርሲቲዎች የየአገራቸውን እድገት ለማስቀጠልና ውጤታማ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምን ለማስፈን መስራት እንዳለባቸው የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት አሊሴጉን ኦባሳንጆ ገለጹ።

 የስድስት የአፍሪካ ሀገራት ዩንቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንቶች “የተፈጥሮ ሃብት አስተዳደር በአፍሪካ” በሚል ርዕስ በጣና ከፍተኛው የሰላምና ደህንነት ቅድመ ፎረም ነጻ የውይይት መድረክ በባህርዳር ዩንቨርሲቲ አዘጋጅነት ዛሬ ማምሻውን ተካሂዷል። 

 በውይይት መድረኩ ላይ በእንግድነት የተገኙት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እንደገለጹት የአፍሪካ ዩንቨርሲቲዎች ለአገራቸው እድገትና ለህዝባቸው ጥቅም በትኩረት መስራት አለባቸው።

 በተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም፣ አያያዝ፣ ልማትና ጥበቃ የህዝባቸውንና የሀገራቸውን ጥቅም መሰረት አድርገው የመማር ማስተርም ሆነ የምርምር ስራ መስራት እንዳለባቸው መክረዋል።

 “የዩንቨርሲቲዎች የአካዳሚክ ነጻነት በሚል ሰበብ ከመንግስት፣ ህዝብና ሀገር ፍላጎት የተገለለ ስራ ጥቅም የሌለው መሆኑን በመገንዘብ ትክክለኛውን መርህ መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው “ብለዋል።

 የአፍሪካ ዩንቨርሲቲዎች የጋራ የተፈጥሮ ሃብትን በፍትሃዊነት በማልማትና በመጠቀም ላይ በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አድማሱ ጸጋዬ ናቸው።

 “የአካባቢያችንን ሃብትና ጸጋ በመለየትና በመመርመር የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሳይንሳዊ መንገድ ለመፍታት መዘጋጀት ይኖርብናል” ብለዋል።

 “የሃሮማያ ዩንቨርሲቲ እያለ የሃሮማያ ሃይቅ ሲጠፋ፣ የሃዋሳ ዩንቨርሲቲ እያለ የሃይቁ ውሃ ሲቀንስ፣ የባህርዳር ዩንቨርስቲ እያለ የጣና ሃይቅ በመጤ አረም ሲወረርና ሌሎች ችግሮች በተፈጥሮ ሃብቶቻችን ላይ ሲደቀኑ ቸል ማለት የለብንም” ብለዋል።

 ለዚህም በዩንቨርሲቲዎች የሚካሄዱ የመማር ማስተማር፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች የመንግስትን፣ የህዝብን እና  በሀገርን ፍላጎት በማሟላት  ላይ ተመስርተው በመከናወን ከመደርደሪያ  ያለፈ ጥቅም ሊሰጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።

 የአፍሪካ ዩንቨርሲቲዎች የመጭው ትውልድ ጥቅምና ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ከወዲሁ ሊሰሩ ይገባል ያሉት ደግሞ በደቡብ ሱዳን የጁባ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጆህን አፑሩ ናቸው።

 “ይህም የውሃ፣ የደን፣ የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ፣ የዱር እንስሳትና ሌሎች ተፈጥሮ ሃብቶችን በአግባቡ በመጠበቅ፣ በማልማትና በመንከባከብ የሚኖረንን ሚና ለማሳደግ ያስችለናል” ሲሉ ገልጸዋል።

 የምንሰራው ስራ ሁሉ በግልና በመንግስት ተቋማትና በህብረሰተሰቡን ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ሆኖ በሚዘልቅ መልኩ መቃኘት አለበት ያሉት ደግሞ በደቡብ አፍሪካ የዌስተርን ኬፕ ዩንቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ቫይቬኔ ላዋክ/Vivienne Lawack / ናቸው።

 “ዋናው ችግር የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ስራዎች ዩንቨርሲቲዎች ከመንግስት ተቋማት ጋር ተቀራርበው ከመስራት ይልቅ በውጭ ረዲኤት ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ የተመሰረቱ መሆናቸው ነው”ብለዋል። 

 የባህርዳር ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ባይሌ ዳምጤ በበኩላቸው ዩንቨርሲቲያቸው የላቀ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም የሚያጎለብቱ የትምህርት ክፍሎችን በመክፈት የተማረና የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት ላይ ይገኛል።

 የፖሊሲ አውጪዎችና ፈጻሚዎችን በሳይንሳዊ የተፈጥሮ ሃብት አያያዝና አስተዳደር ለመደገፍ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩንም ገልጸዋል።

 በጣና ሃይቅ ላይ የተጋረጠውን መጤ አረም መጀመሪያ ከማግኘት ጀምሮ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የመከላከልና የማስወገድ መርሃ ግብር ነድፎ ከአካባቢ መስተዳድሮች ጋር የሰራው ስራ ውጤት እያሰገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

 እስከ አሁንም ከግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በላይ በማሳተፍ የመከላከል ስራ ከመሰራቱም በላይ መጤ አረሙን በዘላቂነት ለማስወገድ የሚያስችል ዘመናዊ ማሽን በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን በማሳያነት አቅርበዋል።

 ዛሬ ማምሻውን በተካሔደው የውይይት መድረክ ላይ ከኢትዮጵያ፣ ናይጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የመጡ የዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች  ተሳትፈዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ጂግጂጋ ሚያዝያ 13/2009 የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች በጋራ ለተስማሙት  የወሰን ማካለል ስራ ተግባራዊነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት እነዚህ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ስምምነቱን እንደሚደግፉት ተናግረዋል፡፡

ገራድ ኮልሚዬ ገራድ መሀመድ የተባሉት የሀገር ሽማግሌ እንደገለጹት ስምምነቱ በሁለቱ ክልሎች አጎራባች ወረዳዎች፣ ቀበሌዎችና መንደሮች የነበረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትያስችላል፡፡

በተጨማሪም  ስምምነቱ የሁለቱ አጎራባች አካባቢዎች ወንድማማች  ህዝቦችን በጋራ የመኖርና የማልማት የቆየ ባህላቸውን በጋራ እንዲጠበቅ የሚስችል በመሆኑ እንደሚደግፉትም አመልክተዋል፡፡ 

እንደ ሀገር ሽማግሌ ከሁለቱም መንግስታት ጋራ በመተባበር ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን  ገልጸዋል፡፡

"በሁለቱ መንግስታት የተደረሰው ስምምነት በወሰን አካባቢዎች የነበረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መሰረት ይሆናል "ያሉት ደግሞ ሼክ አብዲራህማን አሊ ናቸው፡፡

ከአስተዳደር ወሰን ጋር ተያይዞ በአካባቢዎቹ የተከሰተውን ግጭት ለመፍታትና ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት ለእምነቱ ተከታዮች ስለ ሰላም ጠቀሜታ ለማስተማር እንደሚሰሩም ጠቅሰዋል፡፡

ሱልጣን አብዲ አደን በበኩላቸው አጎረባች የሆኑ የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች የጋራ ባህል፣ ቋንቋና እምነት የሚጋሩ በመሆናቸው ስምምነቱን ለመተግበር የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ክልሎች ባደረጉት ስምምነት መሰረት በሰባት ዞኖች 33 ወረዳዎች ሥር በሚገኙ 147 ቀበሌዎችና መንደሮች መካከል አስተዳደራዊ ወሰን እንደሚካለል ቀደም ብሎ ተገልጿል፡፡

Published in ፖለቲካ

ባህርዳር ሚያዝያ 13/2009 በአማራ ክልል ከእጣንና ሙጫ ሀብት የሚፈለገው ጥቅም እየተገኘ አለመሆኑን ባለድረሻ አካላት አስታወቁ ።

በበጀት ዓመቱ 35 ሺህ ኩንታል የእጣን ምርት ለመሰብሰብ ቢታቀድም በዘጠኝ ወር የተሰበሰበው 5 ሺህ 300 ኩንታል ብቻ ነው ።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና አጠቃቀም የሥራ ሂደት መሪ አቶ ጌታቸው እንግዳየሁ ለኢዜአ እንደገለፁት፣ በአያያዝና አጠቃቀም ጉድለት በደን ላይ እየደረሰ ያለውን  ውድመት ለመታደግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ እየተሰራ ነው።

ይሁን እንጂ የእጣንና ሙጫ ዛፎችን ጨምሮ በተፈጥሮ ጥብቅ ደኖች ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት የሚፈለገውን ያህል አለመቀነሱን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ በኢንቨስትመንት ስም የሚደረግ የደን ምንጣሮ፣ ልማዳዊ የሆነ የሰደድ እሳት ቃጠሎ፣ ከሰል ለማክሰል የሚደረግ የዛፍ ቆረጣና የእጣን ዛፍ በሽታ ለችግሩ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።

ቢሮውን ጨምሮ በማህበራት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በሚመለከታቸው አካላት መካከል ተናቦና ተቀናጅቶ የመስራት ልምድ አለመኖርም ለችግሩ ሌላው ክፍተት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ በባለድርሻ አካለት መካከል ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠርና ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ በማውጣት ሀብቱን ከጥፋት ለመታደግ የሚቻልበት ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

በክልሉ ሕብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የግብይት ትስስር ባለሙያ አቶ አማረ አደመ በበኩላቸው በተፈጥሮ የሚገኘውን የእጣንና ሙጫ ሀብት በመጠበቅ ዘርፉን የገቢ ምንጭ ለማድረግ እየተሰራ ነው ።

በአሁኑ ወቅትም በ13 መሰረታዊ ሕብረት ሥራ ማህበራትና በአንድ ዩኒየን አማካኝነት ለሀብቱ ጥበቃ በማድረግ ምርቱ ለገበያ እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

"ይሁን እንጂ በክልሉ በየአመቱ 70 ሺህ ኩንታል የእጣን ምርት ማግኘት የሚያስችል አቅም ቢኖርም በተጨባጭ እየተመረተ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ከ10 በመቶ አይበልጥም " ብለዋል ።

በተያዘው በጀት አመት በማህበራቱና በዩኒየኑ አማካኝነት 35 ሺህ ኩንታል የእጣን ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ በዘጠኝ ወራት  5 ሺህ 300 ኩንታል ብቻ ለመሰብሰብ መቻሉን  ለአብነት ጠቅሰዋል ።

እንደ አቶ አማረ ገለፃ የተሰበሰበውን የእጣን ምርት ለአገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ከሽያጩ  ከ29 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ።

በሰሜን ጎንደር ዞን መተማ የሚገኘው ቴዎድሮስ የተፈጥሮ ሃብት ዩኔን ስራ አስኪያጅ አቶ ሐብታሙ አያሌው በበኩላቸው፣ የዩኒየኑ አባላት የእጣን ሀብቱን በህገ ወጥ መንገድ እንዳይመረት ጥረት ቢያደርጉም በደን ሃብቱ ላይ የሚደርሰውን ውድመት ለማስቆም እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

በተለይም በኢንቨስትመንት ስም በደን ሀብት ላይ የሚደርስ ምንጣሮና የእጣን ዛፉን የሚቆርጡ አካላትን ይዘው ወደ ህግ ማቅረብ ቢችሉም ተገቢውን ቅጣት እየተሰጣቸው አለመሆኑ ችግሩን እንዳባባሰው ጠቁመዋል ።

በተለይም በቀበሌ ደረጃ የሚገኙ የአመራር አካላት ስለ እጣን ዛፉ ያላቸው የግንዛቤ ማነስና ወጥ መመሪያ አለመኖር በሚያካሄዱት የመከላከልና እንክብካቤ ስራ ውጤታማ እንዳይሆን እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ የግብይት ዋና የሥራ ሂደት መሪ አቶ ዘላለም አዲስ በበኩላቸው በየዓመቱ የእጣን ምርት ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ይገኝ እንደነበር አስታውሰዋል።

ለዚህም በ2007 ዓ. ም በባህር ዳር ቅርንጫፍ ብቻ ለውጭ ገበያ ከቀረበ 320 ኩንታል የእጣን ምርት 94 ሺህ 400 ዶላር  ገቢ መገኘቱን ለአብነት የጠቀሱት አቶ ዘላለም፣ ካለፈው በጀት አመት ወዲህ ምርቱ ለውጭ ገበያ እየቀረ አለመሆኑን አስታውቀዋል ።

በክልሉ በሰሜን ጎንደር፣ አዊ፣ ዋግህምራ፣ደቡብ ወሎ፣ ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ዞኖችና በሌሎች ዞኖች ቀደም ሲል በወጣ መረጃ መሰረት 630 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን የእጣን ዛፍ መኖሩ ተገልጿል ።

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ ሚያዝያ 13/2009 የከተማ ሴፍትኔት የቀጥታ ድጋፍ ፕሮግራምን ወደ ትግበራ ለማሸጋገር በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መሆኑን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ ።

ሰርተው መኖር የማይችሉ አረጋዊያንንና አካል ጉዳተኞችን ለቀጣይ አሥር ዓመታት ተጠቃሚ ለሚያደርገው ፕሮግራም የመጀመሪያው ምዕራፍ ማስፈፀሚያ 450 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በጀት መመደቡም ተመልክቷል።

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዕቅድ ዝግጅት፣ የፕሮጀክት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ በቀለ እንደገለጹት፣ የሴፍትኔት ፕሮግራሙ ልማታዊ ሴፍትኔትና ማህበራዊ ሴፍትኔት ተብሎ በገጠርና በከተማ የሚካሄድ ነው።

የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት በከተሞች ሥራ ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አማካኝነት የሚመራ ሲሆን ማህበራዊ ሴፍትኔቱን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በበላይነት ይመራዋል።

የከተማ ማህበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ሰርተው መኖር የማይችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ፕሮግራሙን በሙከራ ደረጃ በ11 ከተሞች ለመጀመር ሰዎችን የመለየት ሥራ መከናወኑን አቶ ደጀኔ ገልጸዋል።

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ደህንነት ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ፈለቀ ጀንበር፣ የማህበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ የመጀመሪያው ስለሆነ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፉ ረዘም ያለ ጊዜ መውሰዱን ገልጸዋል።

በዘጠኝ የክልል ዋና ከተሞችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች በተያዘው ሚያዚያ ወር ወደ ትግበራ ለመግባት የተሟላ ዝግጅት መደረጉንና በዚህም 604 ሺህ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞችን የቀጥታ ድጋፉ ተጠቃሚዎች ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።

አቶ ፈለቀ እንዳሉት፣ ፕሮግራሙ በየአምስት ዓመቱ  በሁለት ምዕራፎች ተከፋፍሎ ለቀጣይ 10 ዓመታት የሚካሄድ ሲሆን ከኢትዮጵያ መንግስትና ከዓለም ባንክ በብድር የተገኘ 450 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በጀት ተይዞለታል።

በጀቱ እንደጊዜው ተጨባጭ ሁኔታ ሊጨምርና ሊቀንስ እንደሚችልም ተናግረዋል።

በ11 ከተሞች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ የሚሆነው የከተሞች ማህበራዊ ሴፍትኔት የቀጥታ ድጋፍ ፕሮግራም በሁለተኛው ምዕራፍ 972 ከተሞችን ተደራሽ እንደሚያደርግ ተመልክቷል ።

በገጠር 4ኛ ዙር ላይ የደረሰው ልማታዊና ማህበራዊ ሴፍትኔት ተጠናክሮ መቀጠሉንና ተጠቃሚ ከሆኑ ሰባት ሚሊዮን አርሶአደሮች መካከል ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ አረጋዊያንና አካልጉዳተኞች እንደሚገኙበት አቶ ፈለቀ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሪት ቃልኪዳን ሽመልስ  በበኩላቸው መንግስት  የአካል ጉዳተኞችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገ ቢሆንም "አካል ጉዳተኞች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ስላሉብን የሁሉንም ወገን ድጋፍ እንፈልጋለን" ብለዋል ።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበር የቦርድ አባልና የኦሮሚያ አካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አቡነ ለሚ ፣ መንግስት ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁንና የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ብቻ በቅርበት የሚመለከት ራሱን የቻለ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ቢቋቋም የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ ሚያዚያ13/2009 የዳኝነት ስርዓቱን ከማዘመን አኳያ የፍትህ አካላትና ባለሙያዎች የስልጠና ማዕከላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ገለጹ።

የፌዴራልና የክልሎች ፍትህ አካላት ባለሙያዎች ስልጠና ማዕከላት የጋራ የምክክር መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀመረ።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉጌታ አጎ እንዳሉት የፍትህ ሴክተሩን የሚቀላቀሉ አዲስ ዳኞችና አቃቤያነ ህጎች ወደ ስራ ከመግባታቸው አስቀድሞ የተግባር ስልጠና ማግኘታቸው ተገቢ ነው።

የፍትህ አካላት ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቁ በቀጥታ ወደ ስራ እንዲገቡ ይደረግ እንደነበርም አስታውሰው "ይህ አሰራር የፍትህ ስርዓቱ በዘመናዊ መርሆዎች ያልተመራ ሆኖ እንዲቆይ አድርጎት ነበር" ብለዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ፕሮግራሞች ተነድፈው የህግ ምርምርና ጥናት ስራዎችን ለማከናወን በፌዴራልና በክልሎች የስልጠና ማዕከላት በማቋቋም ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ ገልጸዋል።

በፍትህ ስርዓቱ ከፍተኛ ሙያዊ ብቃትና ስነ-ምግባር የተላበሰ ህዝባዊ አመኔታ ያለው ለህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ተቆርቋሪ አመራር ከማፍራት አንጻር ማሰልጠኛ ማዕከላቱ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የፌዴራል የፍትህ አካላት ማሰልጠኛ ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር አቶ መሀመድ አህመድ በበኩላቸው የፍትህ ስርዓቱ በመንግስትና በህዝብ የሚፈለግበትን አግልግሎት በመስጠት ውጤታማ ለመሆን የስልጠና ማዕከላት ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

ዳኞችና አቃቤያነ ህጎች ምን አይነት ስልጠና እንደሚያስፈልጋቸው በመለየት በጥናት ላይ የተመረኮዙ ስልጠናዎችን በመስጠት በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ማቀላጠፍ እንደተቻለ ጠቁመዋል።

የደቡብ ክልል ፍትህ አካላት ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ማተያ ማሬ እንዳሉት ማዕከሉ በ2002 ዓ.ም ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ ለጀማሪና በስራ ላይ ለሚገኙ ከ12 ሺህ በላይ የፍትህ አካላት ስልጠና ተሰጥቷል።

"ማዕከሉ ከመደበኛ ፍርድ ቤት የፍትህ አካላትና አቃቤያነ ህጎች በተጨማሪ አማራጭ ፍርድ ቤቶችና ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ውስጥ የሚሰጠውን የዳኝነት አገልግሎት ዘመናዊ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ለዳኞች ስልጠና በመስጠት ለውጦች ማምጣት ችሏል" ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ የፍትህ አካላት ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዲያሬክተር አቶ አለማየሁ መሰለ በበኩላቸው እንደገለጹት በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ኢንስቲትዩቱ ክፍተቶችን በጥናት በመለየት እየሰራ ይገኛል።

ኢንስቲትዩቱ ለፍትህ አካላት ከሚሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና በተጨማሪ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማጥናት አቅጣጫ ከማስቀመጥ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል፡፡

"በጥናቶችም በኦሮሚያ ክልል በፍትህ ስርዓቱ ዙሪያ የሚስተዋሉ የዲሲፕሊን ችግሮች ሙስና፣ በጥቅም መስራት፣ በዘመድ ፣በጎሳ ፣ገንዘብ በመቀበል ባለጉዳይ በማመናጨቅና በመሳሰሉት መልኩ ፍትህ የማጓደልና ውሳኔ የማጓተት ሁኔታዎች ተለይተዋል" ብለዋል፡፡

እነዚህን የጥናት ውጤቶች መሰረት በማድረግ የተዘጋጀው ሰነድም በክልሉ ለተካሄደው የፍትህ አካላት በጥልቀት የመታደስ የግምገማ መድረክ ማገልገሉን አቶ አለማየሁ ተናግረዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የጋራ ጉባኤ ላይ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 5

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን