አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Thursday, 20 April 2017

ሰመራ ሚያዝያ 12/2009 በአፋር ክልል የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም ጥረቶች ቢደረጉም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ግርዛት በድብቅ እየተፈጸመ መሆኑን ክልሉ ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ዘሀራ መሀመድ እንደተናገሩት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የአርብቶአደር ሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማሳደግ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች አበረታች ውጤት ተገኝቷል።

የሴት ልጅ ግርዛትን ጨምሮ ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆም ሰፊ የማህበረሰብ ንቅናቄ ከማድረግ ጀምሮ ግርዛትን የሚከለከል የህግ ማዕቀፍ እስከማውጣት ሥራዎች ተከናውነዋል።

ሕብረተሰቡ በሕጉ ላይ ግንዛቤ አንዲኖረው ችግሩ ጎልቶ በሚታይባቸው 11 የክልሉ ወረዳዎች ቢሮው እስከ ቀበሌና ጎጥ ድረስ ወርዶ በየደረጃው የማስተማርና የማህበረሰብ ውይይት አድርጓል። 

ይሁንና እነዚህ ወረዳዎችን ጨምሮ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ዛሬም ግርዛት በድብቅ እየተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።

በድብቅ የሚፈጸመውን ግርዛት ለመከላከል ቢሮው የሚሰራው ተከታታይ የግንዛብ ማስጨበጫ ሥራዎች ቢኖሩም የድርጊቱን ፈጻሚዎች  አሳልፎ ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሕብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ወይዘሮ ዘሀራ አስታውቀዋል።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፋጡማ መሃመድ በበኩላቸው፣ ቢሮው ግርዛትን ጨምሮ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች ለሕብረተሰቡ የንቃተ ህግ ትምህርትና ለአቃቢ ህጎች የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል።

ቢሮው ከሚሰጠው የንቃተህግ ስልጠና በተጨማሪ በዚህ ዓመት በደዌ እና አሚበራ ወረዳዎች የሴት ልጅ ግርዛት ሲፈጽሙ የተገኙ ሁለት ሰዎች በቀላል እስርና በገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ማድረጉን አመልክተዋል።

እንደ ወይዘሮ ፋጡማ ገለጻ፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ከመከላከል አንጻር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚደረገው ጥረት ውስንነቶች አሉበት።

ይህንን ችግር ለመፍታት 13 ከሚሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር ቢሮው በቅንጅት ለመስራት ባለፈው መጋቢት ወር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሞ ወደስራ መገባቱን ተናግረዋል።

በሰመራ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍልተማሪ ፋጡማ እድሪስ በበኩሏ ባለፉት ዓመታት ግርዛትን አስመልክቶ በተከናወኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በህብረተሰቡ የአመለካከት ለውጥ እየተፈጠረ መሆኑን ገልጻለች።

ይሁንና አሁንም ድረስ አንዳንድ ሰዎች ልጆቻቸውን ከማስገረዝ ያልታቀቡ መኖራቸውንና ይህም ሴቶችን በተለይም በወሊድ ወቅት ለከፋ ስቃይ እየዳረገ በመሆኑ ድርጊቱን የሚፈጽሙ ሰዎችን አጋልጣ ለመስጠት መዘጋጀቷን ተናግራለች።

የክልሉ እስልምና ጉዳይ ፕሬዚዳንት ሼህ መሃመድ ደርሳ በበኩላቸው፣ በክልሉ በአስከፊ ሁኔታ ይፈጸም የነበረዉን የሴትልጅ ግርዛት ለማስቆም የሃይማኖት አባቶች ግርዛት ሃይማኖታዊ መሰረት እንደሌለዉ በማስተማር ጉልህ ሚና ሲጫወቱ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።

በእዚህም የተወሰነ ለውጥ ቢመጣም አሁንም በየደረጃዉ ከሃይማኖት መሪዎች እስከ ፖለቲካ አመራሩ ድረስ ግርዛትን በተመለከተ የግንዛቤ ልዩነት መኖር የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ አድርጓል ብለዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ማይጨው ሚያዝያ 12/2009 የአላማጣና የኮረም ሆስፒታሎች የተሟላ አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው መቸገራቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተጠቃሚዎች ገለጹ።

ያለባቸውን የመድኃኒትና የባለሙያ እጥረት በመፍታት ችግሩን ለማቃለል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ እንደሚገኙ የየሆስፒታሎቹ ኃላፊዎቸ ተናግረዋል።

የአላማጣ ከተማ ነዋሪው አቶ ንጉስ ሃይለስላሴ እንደተናገሩት ወደ አላማጣ ሆስፒታል ለህክምና አገልግሎት ሄደው አገልግሎት የሚሰጣቸው ባለሙያ በማጣታቸው ለበርካታ ቀናት እየጠበቁ ይገኛሉ።

በሆስፒታሉ ተኝተው ያለ ምንም የህክምና እርዳታ በመቆየታቸውም ላልተፈለገ ወጪ መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

የጨርጨር ከተማ ነዋሪው አቶ ደሳለኝ አሰፋ በበኩላቸው ለህክምና ወደ ሆስፒታሉ ገብተው እንዲተኙ ከተደረገ በኋላ በሐኪም እጥረት ምክንያት የቀዶ ህክምና ባለማግኘታቸው መጉላላት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የኮረም ከተማ ነዋሪው ሼክ ከማል መሃመድ እንደገጹት የኮረም ሆስፒታል ሰራተኞችና የህክምና ባለሙያዎች ህሙማንን የማስተናገድና የመንከባከብ ጥረታቸው የሚመሰገን ቢሆንም በቂ ህክምናና መድኃኒት ማግኘት አስቸጋሪ ነው።

"አሁን ወደ ሆስፒታሉ የመጣሁት በሚጥል በሽታ ለታመመ ህፃን ልጄ መድሃኒት ለመግዛት ነበር፤ነገር ግን መድሃኒቱ የለም ተብለናል፤ ሆስፒታሉ መድሃኒቱን በጊዜው አያመጣም፤ አሁን ህፃኑ እየሰቃየ ነው"ብለዋል።

የዚሁ ሆስፒታል ሌላው ተጠቃሚ ወይዘሮ መርየም ብርሃኑ በበኩላቸው እንደገለጹት የሆስፒታሉ አግልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ ቢሆንም  የሚታዘዝላቸውን መድሃኒት ስለማያገኙ በውድ ዋጋ ከውጪ ለመግዛት እየተገደዱ ነው።

የአላማጣ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ጠዓመ አረዶም እንደገለጹት ሆስፒታሉ ያሉበትን ችግሮች ለማቃለል ቀደም ሲል በሽልማት ያገኘውን 1ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ጨምሮ ከክልሉ ጤና ቢሮ የሚሰጠውን ድጎማ በመጠቀም የመድሃኒት ግዢ ያከናውናል።

የክልሉ ጤና ቢሮም ችግሩን ለመፍታት ለሆስፒታሉ ተጨማሪ አምስት ዶክተሮችን የመደበ በመሆኑ በዚህ ረገድ ያለው እጥረት መቃለሉን ተናግረዋል።

የኮረም ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ቴድሮስ ግርማይ  እንደገለጹት ሆስፒታሉ ያሉበትን የስፔሻሊስቶች እጥረት ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በተደረገ ግንኙነት በመጪው ሐምሌ ወር  ችግሩ ይቃለላል።

ከዚህ ባለፈም በሆስፒታሉ የሚያጋጥመውን የመድሃኒት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከጤና ቢሮው የሚገኘውን ድጋፍ ጨምሮ የተለያዩ አማራጮችን ተግባራዊ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

አዳማ ሚያዝያ 12/2009 በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥረው በሚሰሩ ሴቶች ላይ የፆታ ትንኮሳና ሌላም በደል እንደሚደርስ  በክልሉ ህፃናትና ሴቶች ጉዳይ ቢሮ የተካሄደ ጥናት አመለከተ።

ቢሮው በኢንዱስትሪ ተቋማት ውስጥ የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚቻልበት ላይ ያዘጋጀው  ኮንፍረንስ በአዳማ ገልመ አባገዳ ተካሂዷል።

ጥናታዊ ጽሁፉን ያቀረቡት በቢሮው የህፃናትና አጠቃላይ የሴቶች ተቋማት ክትትል የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ኡስማን ኢብራሂም  እንዳመለከቱት ጥናቱ የተካሄደው በፊንፊኔ ዙሪያ፣ቡራያ፣ሰበታ፣ሞጆ፣ቢሾፍቱ፣ባቱና አዳማ በተመረጡ  10 ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ነው።

ባለፈው አንድ ወር ውሰጥ  የተካሄደው   ጥናት  በኢንዱስትሪዎቹ ተቀጥረው የሚሰሩ ሴትና ወንድ ሰራተኞች እንዲሁም የአካባቢውን ማህበረሰብ ማዕከል በማድረግ ነው፡፡

በጥናቱ መሰረት በኢንዱስትሪዎቹ  ተቀጥረው በሚሰሩ ሴቶች ላይ ከሚደርስባቸው በደሎች መካከል  የፆታ ትንኮሳ መብዛት፣  በአንድ አይነት ስራ ላይ ተመሳሳይ  ክፍያ አለመኖር፣ የወሊድና የህመም  ፈቃድ አለመስጠት ይገኝበታል፡፡

በማሽን ስራ ላይ ሲጎዱ አስፈላጊውን ኢንሹራንስ ላለመክፈል ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ እስከ መግባትና ጨርሶ የማይከፈልበት ሁኔታም እንዳለ በጥናቱ ተመልክቷል።

ለደህንነት የሚገባቸው ቁሳቁሶችን የኢንዱስትሪ ባለቤቶች አሟልተው ባለመገኘታቸው ሰራተኞች በቀላሉ በፋብሪካ ውሰጥ በሚጠቀሙባቸው ኬሚካሎች ለጉዳት ይጋለጣሉ፡፡

ነፍሰጡሮች ከስራ የሚገለሉበት፣ የፆታ ትንኮሳ ፣ በቅጥር፣ በእድገት፣ በደመወዝ ጭማሪና በዝውውር ረገድም በደሎች እንዳሉ ነው ጥናቱ የዳሰሰው።

ኤች.አይቪ ቫይረስ በደማቸው ያለባቸው  ሴቶች ልዩ እንክብካቤ እንደማይደረግና በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ልቅ የሆነ  የግብረ ሥጋ ግንኙነት መስፋፋቱም በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡

በኢንዱስትሪዎቹ የህፃናት ማቆያ ስፍራ አለመኖሩና ሌሎችም በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው በደልና ችግር እንዲፈታ ሴቶችን ወደ አመራርነት ማምጣት ወሳኝ መሆኑን በጥናቱ ከተመለከቱት መፍትሄዎች ይጠቀሳል።

የሴቶች ማህበራት በፋብሪካዎች የሚቋቋሙበትና የሚጠናከሩበት አቅጣጫ መቀመጥ እንዳለበት ጥናቱ ጠቁሞ በዚህ ላይ የጋራ መግባባት ላይ ሊደረስ እንደሚገባም ተጠቁሟል።

የሚቋቋሙት ማህበራትም ለኢንዱስትሪ ምርታማነት ማደግና ሰላም መስፈን ሊታገሉ እንደሚገባ እንዲሁ።

የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አዚዛ አብዲ በበኩላቸው በሀገሪቱ ለተፈጠረው የኢንዱስትሪዎች እድገት መንግስትና ባለሀብቱ ትልቅ ደርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ሆኖም በኢንዱስትሪዎቹ ውስጥ በተለይ  በሴቶች ላይ የተለያዩ ፆታዊ ትንኮሳና  የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ እንዳለ በጥናቱ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

ችግሩን  በጋራ  ማስወገድ በሚቻልባቸው ስልቶች ላይ በመምከር መንግስት፣ ባለሀብቱና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በቀጣይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ  ኮንፍረሰንሱ መዘጋጀቱን  ገልጸዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ከተሳተፉት መካከል  ወይዘሪት ፈትያ መሐመድ በሰጠችው አስተያየት በኢንዱስትሪ ውስጥ ተቀጥራ እንደምትሰራ ተናግራ  የፆታ ትንኮሳ እንደሚደርስባቸውና  ከፍያቸውም ካለባቸው የስራ ጫና አንጻር ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ተናግራለች፡፡

መንግስት የሚደርስባቸውን በደል ተገንዝቦ  እልባት እንዲሰጣቸውም ጠይቃለች።

ርካሽ የሰው ጉልበት አለ በሚል ከውጭ የሚመጡ ባለሀብቶች ለዜጎች ያላቸው ክብር እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ በሰራተኛው ላይ ከፍተኛ በደል እንደሚፈጸም  ያመለከቱት ደግሞ አቶ ንጉሴ አበራ የተባሉት የመድረኩ ተሳታፊ ናቸው።

የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ጅሎ በክልሉ እየተስፋፋ በመጣው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የተፈጠረው የሥራ እድል ቀጣይነት እንዲኖረው  መንግስት  እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይ በአሠሪና ሠራተኞች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ጥቅማቸውን ሊያስጠብቁ የሚያስችላቸውን አሠራር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ለአንድ ቀን በተካሄደው ኮንፍረንስ  ከመንግስት፣ ከአሰሪዎች፣ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተወካዮችና ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 12/2009 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ አስመልክቶ ይፋ ያደረገውን የምርመራ ውጤትና ምክረ ሀሳብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

ምክር ቤቱ ያጸደቀው ሪፖርት በሁከቱና ብጥብጡ ወቅት የተሳተፉ ግለሰቦችና ተቋማት በህግ መጠየቅ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥቶቷል ።

በሁከቱና በብጥብጡ ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን የፌዴራልና የክልሎቹ መንግስታት በቅንጅት የማቋቋም ሥራ እንዲሰሩም ምክር ቤቱ በውሳኔው አካቷል።

የምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ ዙሪያ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማክሰኞ ባቀረበው ሪፖርት ላይ የውሳኔ ሀሳብ እንዲያቀርብ መመራቱ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ ባቀረበው ሪፖርት መሰረት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎችና በጌዲኦ ዞን በተካሄዱት ሁከትና ብጥብጦች የ669 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፤ ወደ 20 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል።

የተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ ዋነኛ መንስኤ ስር የሰደደውን የመልካም አስተዳደር ችግር በወቅቱ አለመፍታትና ለወጣቱ በቂ የሥራ እድል አለመፍጠር መሆኑም ተመልክቷል።

ሁከትና ብጥብጡን ያባባሱት መንግስትን በኃይል የመቀየር ዓላማ ያላቸው ሽብርተኛ የተባሉ ድርጅቶችና በህጋዊነት የተመዘገቡ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

ኮሚሽኑ የችግሩን መንስኤና ያስከተለውን ጉዳት የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ፣ ሚዛናዊ መረጃ ላይ ተመስርቶ ያጣራውን ሪፖርትና ምክረ ሀሳብ ትክክለኛነት ቋሚ ኮሚቴው በሙሉ ድምጽ ተቀብሎታል።

በዚህም መሰረት ምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴው "በሁከቱና በብጥብጡ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦችና ተቋማት በህግ እንዲጠየቁ" ሲል ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል።

በሁከቱና በብጥብጡ ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን የፌደራልና የክልሎቹ መንግስታት በቅንጅት ወደ ቀድሞ ኑሯቸው እንዲመለሱ አስፈላጊውን የማቋቋም ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉም በውሳኔው ተካቷል።

በባህር ዳር ከተማ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ለክልሉ መንግስት ጥያቄ አቅርበው በዕለቱ በቦታው ባለመገኘት ከተማዋን ለቀው የሄዱ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባል ላደረጉት ኃላፊነት ለጎደለው ተግባርና ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ እንዲሆኑም ምክር ቤቱ ወስኗል።

በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላትና ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ የወሰዱ የፀጥታ ኃይሎች ተገቢውን ማጣሪያ ተደርጎ ለህግ እንዲቀርቡ በኮሚሽኑ የቀረበውን ምክረ ሀሳብም ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ደግፎታል።፡

ምርመራቸው ተጀምሮ ያልተጨረሱ ሥራዎች በኮሚሽኑ ክትትልና ቁጥጥር ሂደት እየተጣሩ ፍጻሜ እንዲያገኙም ምክር ቤቱ ወስኗል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ ሁከትና ብጥብጥ በተከሰተባቸው ቦታዎች  በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኖርና አለመኖሩን መርምሮ ሪፖርት ማቅረብ ችሏል።

ይህ የኮሚሽኑ ተግባር በአገሪቷ እየተገነባ ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓትና በህገ መንግስቱ የተቀመጡ መርሆች በጥልቀት እንዲተገበሩ ያስችላል።

በተጓዳኝም በህግ አውጪው፣ በህግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው መካከል የክትትልና የቁጥጥር ስርዓቱ ጠንካራ እንዲሆን  እንደሚያደርግ አመልክተው፤ ይህም ተመሳሳይ ችግሮች ሲያጋጥሙ መንግስትና ህዝብ በመተባበር በራስ ዓቅም ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑን ነው የገለጹት።

በዚህም ምክር ቤቱ በኮሚሽኑ በቀረበው ሪፖርት መሠረት የመከታተል፣ የመደገፍ፣ እርምት የማስወሰድና በእርምት የማይመለሱት ላይ እርምጃ የመውሰድ ተግባሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስቧል።

ቀደም ሲል በኦሮሚያ 15 ዞኖችና 91 ወረዳዎች፣ በአማራ 5 ዞኖችና 55 ወረዳዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን አራት ወረዳዎች ሁከትና ብጥብጥ  መከሰቱ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ ምርምራውን ያካሄደው በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችን፣ አባገዳዎችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የኃይማኖት አባቶችንና የመከላከያ ሠራዊት አባላትን በማናገር መሆኑም ተገልጿል።

Published in ፖለቲካ

አዳማ ሚያዝያ 12/2009 በአገሪቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአንድ ሺህ በሚበልጡ ድርጅቶች የሥራ ላይ አደጋ መድረሱን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

በአደጋው 42 ሰዎች ሲሞቱ 1 ሺህ 742 ሰዎች ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

" ጥልቅ የተሀድሶ ንቅናቄ ለማህበራዊ ለውጥ!" በሚል መሪ ቃል የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሴክተርን ያለፉት ዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም የሚገመግም የሁለት ቀናት መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል ።

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዕቅድ ዝግጅት፣ የፕሮጀክት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ በቀለ በመድረኩ ላይ ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደገለጹት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሦስት ሺህ 365 ድርጅቶች ላይ ክትትል ተደርጎ በ1 ሺህ 14 ተቋማት የሥራ ላይ  አደጋ መድረሱ ተረጋግጧል።

በአደጋው 12 ሴቶችን ጨምሮ 42 ሰዎች ሲሞቱ በ1 ሺህ 742 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የሥራ ላይ አደጋ ጉዳት እየተስፋፋ መምጣቱን ጠቁመው፣ ክትትሉን በማጠናከር አደጋውን መከላከል የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በሪፖርቱ እንደተገለጸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሥራ ፈላጊዎች ተመዝግበው አስፈላጊው ድጋፍ ከተደረገላቸው በኋላ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ። 

በተጠቀሰው ጊዜ በርካታ ስኬቶች ቢገኙም በገጠርና በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም 1 ሚሊዮን 457 ሺህ 652 ዜጎች ተገቢውን የቀጥታ ድጋፍ እንዲያገኙ የተያዘውን ዕቅድ ተግባራዊ አለመደረጉ በሪፖርቱ በድክመት ተነስቷል ።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ መድረኩን ሲከፍቱ እንደተናገሩት የጋራ ጉባኤው ባለፉት ዘጠኝ ወራት የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ከመገምገም ባለፈ ክፍተቶቹን በማረም በቀጣይ ሦስት ወራት ዓመታዊ ዕቅዱን ለማሳካትና ለሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ፅኑ መሰረት የመጣል አላማ  ነው።

የዕቅዱን ዓበይት ተግባራት ጨምሮ በለውጥ ሠራዊት ግንባታ፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነትን በመከላከል በኩል ውጤታማ ተግበራት መከናወናቸውን ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በጥልቅ ተሃድሶ አቅጣጫ በመንቀሳቀስ የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ አረጋውያንን ለመንከባከብና፣ የአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ለመደገፍ የሚረዱ ምቹ መደላድሎች ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ተወካዮች፣ የክልል ቢሮ ኃላፊዎች ፣ የህዝብ ክንፍ አባላት፣ ባለድርሻ አካላትና ሚኒስትር ዴኤታዎች በጉባኤው ተሳትፈዋል።

ጉባኤው በሁለት ቀናት ቆይታው የሚኒቴር መስሪያ ቤቱን፣ የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀሲን እንዲሁም የግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ማህበራዊ

አርባምንጭ ሚያዝያ 12/2009 በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሔደ ያለው የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ የከተማዋን ገጽታ እየለወጠው መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች ገለጹ።

በከተማው የነጭ ሣር ክፍለ ከተማ ውሃ ምንጭ ቀበሌ ነዋሪው  አቶ ሂዲታ ኮይራ እንደተናገሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለአረንጓዴ ልማት የተሰጠው ትኩረት የከተማዋን ገጽታ እየቀየረው ነው።

በውበትና ፅዳት ሥራ ለረዥም ጊዜ መስራታቸውን የገለጹት አቶ ሂዲታ ቀደም ሲል ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ አሠራሮች ባለመዘርጋታቸው በከተማዋ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ሳይታይ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

"አሁን በባለቤትነት የሚንቀሳቀሱ በርካታ ማህበራት በአረንጓዴ ልማት ተደራጅተው በመስራታቸው እየመጣ ያለው ለውጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት"ብለዋል።

በከተማዋ በመንገድ አካፋዮች የሚደረገው የአረንጓዴ ልማትና የችግኝ ማፍያ ቦታዎች መስፋፋት ጥሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በሸቻ ክፍለ ከተማ የጫሞ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ካሳሁን ካንኮ ናቸዉ ፡፡

"ከደረቅ ቆሻሻ ጋር ተያይዞ በመንደራቸው በየ15 ቀኑ የልማት ዘመቻ መኖሩን ጠቁመው የከተማዋ ነዋሪ ተመሳሳይ ተግባራትን በመፈጸም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል፡፡

በእያንዳንዱ አባወራ ደጃፍ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ዕቃዎች ተዘጋጅተው የመጠቀም ልምዱ እንዲጎለብት እየተደረገ መሆኑን ተናግረው ለአረንጓዴ ልማት የተሰጠው ትኩረት እንዲጠናከር የሚጠበቅባቸውን እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በአረንጓዴ ልማት ተደራጅተው ወደ ሥራ ከገቡ 8 ማህበራት ውስጥ የጭሊሎ አረንጓዴ ልማት ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ይበልጣል ኤሊያስ በበኩሉ እንደገለጸው በዘርፉ መሰማራታቸው የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ከተማዋን አረንጓዴና ውብ ለማድረግ እያስቻላቸው ነው።

በተያዘው ዓመትም 7ሺ 600 ካሬ ሜትር የመንገድ አካፋዮችን ማልማታቸውን ገልጾ ቆሻሻን ወደ ብስባሽ ቀይረዉ ኮምፖስት በማምረት ጥቅም ላይ ለማዋል ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውንም ጠቅሷል።

በአርባምንጭ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅና የአከባቢ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አምሳሉ መውዜሩ በተያዘው በጀት ዓመት በመንገድ አካፋዮች 3 ነጥብ7 ኪሎ ሜትር ሣርና ችግኝ በማህበራት እንዲለማ መደረጉን ገልጸዋል ፡፡

"የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱን ለማዘመን ከከተማው በ7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራ ግንባታ እየተጠናቀቀ ነው"ብለዋል።

ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻ በመሆኗ ፓርኮችን ፣የትምህርት እና የሃይማኖት ተቋማትን በማልማት የአረንጓዴ ልማቱ ለአከባቢው ህብረተሰብ የሚሰጠውን ጠቀሜታ ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 12/2009 ፎረሙ ከተሞች ተሞክሯቸውን እንዲለዋወጡ ከማድረግ ባሻገር የሚያከናውኗቸውን የልማት ተግባራት በተነቃቃ መንገድ እንዲተገብሩ ዕድል ፈጥሯል ተባለ።

7ኛው የከተሞች ፎረም ከሚያዚያ 21-28 ቀን 2009 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ይካሄዳል።   

ፎረሙን አስመልክቶ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ያዘጋጀው የፓናል ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በውይይቱ የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም አጀማመር፣ የተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች የተዳሰሱ ሲሆን ቀደም ሲል ፎረሙን ያዘጋጁ ከተሞች ልምዳቸውን አካፍለዋል።    

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ደምሴ ሽቶ ፎረሙ ከተሞች ልማትን ለማረጋገጥ በሚከተሉት አሰራር ተሞክሮ እንዲለዋወጡ በማድረግ የላቀ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት የተካሄዱት ፎረሞች በከተሞቹ ዘንድ የልማት መነቃቃት መፍጠራቸውን በመግለፅ። 

ከተሞች በተለይ በኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን እምቅ አቅም የሚያሳዩበት ዕድል መፈጠሩን ገልጸው በጽዳት አጠባበቅ በኩልም የተሻለ ተሞክሮ ያላቸው ከተሞች ልምዳቸውን ማካፈላቸውን አንስተዋል።

በጎንደሩ ፎረም ላይ ለመሳተፍ 226 ከተሞች መመዝገባቸው ፎረሙ ጠቃሚ ስለመሆኑ ግንዛቤ እየተፈጠረ መምጣቱን ያመለክታል ብለዋል።

"በከተሞች የልማት ፖሊሲ ዙሪያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት የሚደረግበት በመሆኑ የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦችን ለማሰባሰብ ይረዳል" ነው ያሉት።           

"ፎረሙ የምርምርና በዘርፉ ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው ተቋማትና ግለሰቦች የሚሳተፉበት በመሆኑም ጠቀሜታው የጎላ ነው" ያሉት ደግሞ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ሰለሞን ካሳሁን ናቸው። 

በቆሻሻ አወጋገድ፣ በትራንስፖርትና በተለያዩ የመሰረተ ልማት ዘርፎች ከተሞች ያሉባቸውን ክፍተቶች እንዲሞሉ በማስቻል ረገድ ፎረሙ የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰዋል።  

የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢሳ በበኩላቸው ሁለተኛው የከተሞች ቀን በሃዋሳ መካሄዱን አስታውሰዋል።

ፎረሙ "የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ያስቀመጣቸውን የከተማ ልማት ስትራቴጂዎች ማቀጣጠል የተቻለበትን ሁኔታ ፈጥሮ አልፏል" ሲሉ ገልጸውታል።

የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ የህዝብ ተሳትፎ አማካሪ አቶ መሃመድ አብዱራህማን በበኩላቸው በዚያ በተካሄደው ፎረም ዓለም አቀፍ ተቋማት የከተሞችን ልማት ማሳለጥ ስለሚቻልበት ሁኔታ ያላቸውን ልምድ ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል። 

"በፎረሙ ላይ ባዛርና ኤግዚቢሽኖች የሚዘጋጁ በመሆኑ ቀላል የማይባል የገበያ ትስስር ይፈጠራል" ያሉት ደግሞ የፌዴራል የከተሞች ስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ መንግስቱ ናቸው። 

የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል ስለተደረገው ቅድመ ዝግጅት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን 7ኛውን የከተሞች ፎረም ለማስተናገድ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

"ከተማዋ ያሏትን የቱሪዝም ሃብቶች ለማስተዋወቅ ተዘጋጅታለች" ያሉት ከንቲባው ቡድን ተቋቁሞ ቀደም ሲል ፎረሙን ካዘጋጁ ከተሞች ልምድ የመቅሰም ስራ መከናወኑን ገልጸዋል። 

እንግዶችን ለማስተናገድ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መደራጀታቸውን፣ በከተማዋ ሆቴሎችን ጨምሮ ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሰራተኞች ስልጠና መሰጠቱንም አብራርተዋል።

6ኛው የከተሞች ፎረም በድሬዳዋ ከተማ የተካሄደ ሲሆን 166 ከተሞች ተሳትፈውበታል። 

የመጀመሪያው የከተሞች ፎረም "የከተሞች ቀን" በሚል ስያሜ በ2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 12/2009 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 13 የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ለዝርዝር እይታ መራ።

የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አማኑኤል አብርሃም ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ አገሮች ጋር የተፈራረመቻቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት አስመልክቶ ስለተዘጋጁት ረቂቅ አዋጆች ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ረቂቅ አዋጆቹ አገሪቷ ከተለያዩ አገሮች ጋር በግብርና ልማት፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በመንገድ፣ በመሰረተ ልማት፣ በባህል፣ በአየር ትራንስፖርት የምታደርገውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለሙ የትብብር ስምምነቶች ናቸው።

የትብብር ስምምነቶቹ በኢትዮጵያና በኩዌት፣ በሱዳን፣ በጅቡቲ፣ በኬንያ፣ በአልጄሪያ፣ በጋቦን፣ በጋና በኮሞሮስ፣ በኮሪያ ሪፐብሊክና በአየርላንድ  መንግስታት መካከል የተደረሱ ናቸው።

ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጆቹን አስፈላጊው ግብዓት ተካቶባቸው እንዲዳብሩ ለሚመለከታቸው ኮሚቴዎች መርቷል።

ረቂቅ አዋጆቹ የተመራላቸው የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የባህል፣ ቱሪዝምና መገናኛ ብዙኃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ናቸው። 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 12/2009 በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል ከወሰን ማካለል ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን አለመግባባት በመፍታት አጎራባች አካባቢዎችን ለማልማት እንደሚሰሩ የክልሎቹ ርዕሰ መስተዳድሮች ተናገሩ።

በሁለቱ ክልሎች መካከል ከወሰን ማካለል ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት የሚያስችል አስተዳደራዊ የወሰን ማካለል ሥምምነት ትናንት ተደርሷል።

በሥምምነቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃመድን ጨምሮ የክልሎቹ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ሥምምነቱ ቀደም ሲል በወሰን ማካለል ጋር በተያያዘ የተጠናቀቁ ሥራዎች ላይ ተጨማሪ ተግባራትን ለማከናወንና አለመግባባቶችን በዘላቂነት ማስቀረትን ዓላማ ያደረገ ነው።

በሁለቱ ክልሎች መንግሥታት የፌዴራል አካላትና በሕዝቡ የጋራ ጥረት ሥምምነት ላይ ደርሰው ወደ ተግባር የገቡትን አካባቢዎች የወሰን ማካለል ሥራም ይጨምራል።

ስምምነቱ በሰባት ዞኖች 33 ወረዳዎች ሥር በሚገኙ 147 ቀበሌዎችና መንደሮች መካከል አስተዳደራዊ ወሰን ማካለልንም ያጠቃልላል።

ይህን ሥምምነት ተከትሎ ርዕሰ መስተዳድሮቹ ግጭት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ዘላቂ ልማት በማረጋገጥ አለመግባባቶችን ከመሰረታቸው ለመፍታት እንደሚሰሩ ነው ያረጋገጡት።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃመድ እንደተናገሩት ሁለቱ ክልሎች በሃይማኖት፣ በቋንቋና ባህል የተጣመሩ በመሆናቸው የሚያጋጭ ምክንያት የላቸውም።

የሁለቱ ክልሎች ግጭት በዋነኝነት በተፈጥሮ ጫና የተነሳ በአካባቢው ልማት ባለመኖሩና ከድህነት ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው አቶ አብዲ የተናገሩት።

ለዚህም ደግሞ በአካባቢው በተለይም የውሃና የመንገድ መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት የአካባቢውን የልማት ጥያቄ በዘላቂነት በመፍታት ግጭቶችን ለማስቀረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ይህም ለአካባቢዎቹ ብቻ ከሁለቱ የክልል መንግሥታት በጀት በመፍቀድ እንደሚከናወን አቶ አብዲ አረጋግጠዋል።

የተደረሰው ሥምምነት ለሕዝቡ ችግር ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥና በተለይም ለአመራሩ ትልቅ ትምህርት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው በክልሎቹ መካከል ያለው የመሬት ችግር አይደለም፣ ሁለቱም ክልሎች ከበቂ በላይ የመሬት አቅርቦት አላቸው ይላሉ።

ይሁንና ሁለቱ ክልሎች የሚጋሯቸውን አካባቢዎች በማልማትና መልካም አስተዳደር ለማስፈን እንደሚንቀሳቀሱና አለመግባባቶችን ለመፍታት  በጋራ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

አካባቢው ለዘመናት ልማት ተነፍጎ ቆይቷል፤ ይህንን ለመቀልበስ የልማት ሥራዎችን በሥፋት በመሥራት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ኑሮ መቀየር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ ያደረጉ ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ እንደሚሰራ የፌዴራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር አካባቢ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።

Published in ፖለቲካ

ጊምቢ ሚያዝያ 12/2009 ከአዲስ አበባ ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሲጓዝ የነበረ አውቶብስ ጊምቢ ወረዳ ሲደርስ በመገልበጡ በ23 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ መድረሱን የምዕራብ ወለጋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ። 

በመምሪያው የትራፊክ ፖሊስ ዲቪዥን ሃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር አብዱራዛቅ ምትኩ እንደገለፁት አደጋው የደረሰው የፋሲካን በዓል ከቤተሰቦቻቸው ጋር አክብረው ወደ ስራቸው የሚመለሱ የህዳሴ ግድብ ሰራተኞችን የጫነ ቢሾፍቱ አውቶብስ በመገልበጡ ነው።

ትላንት ከአዲስ አበባ የተነሳው አውቶብስ ዛሬ ከጧቱ አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ ጊምቢ ወረዳ መልካ ጋፊ ቀበሌ ሲደርስ ባጋጠመው የመገልበጥ አደጋ በ13 ሰራተኞች ላይ ከባድ በ10 ሰራተኞች ላይ ደግሞ ቀላል የመቁሰል አደጋ የደረሰ ሲሆን የሞተ ሰው እንደሌለ ገልጸዋል።

የአደጋው መንስኤ ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር መሆኑን የገለፁት ምክትል ኢንስፔክተሩ 150 ሺህ ብር የሚገመት የንብረት ውድመት መድረሱንም ገልጸዋል።

"የአውቶብሱ አሽከርካሪ መቶ አለቃ ዛኪር ያሲን በቁጥጥር ስር ውለው በምርመራ ላይ ሲሆኑ ጉዳት የደረሰባቸው ሰራተኞችም በህክምና ላይ ይገኛሉ" ብለዋል ።

ወደ ህዳሴ ግድብ ከሚደረገው ጉዞ ጋር ተያይዞ በዞኑ የመኪና አደጋ መጠን እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ምክትል ኢንስፔክተሩ የመንገዶችን ጠመዝማዛነት በማየት በተለይ ለቦታው አዲስ የሆኑ አሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን ጠብቀውና ረጋ ብለው እንዲጓዙ መክረዋል፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 5

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን